<<ቃል ለምድር ለሰማይ!>><<ሤሪ ሤሩማ! >><<ቃል አቴ አለሆ!>>

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

<<ቃል ለምድር ለሰማይ!>><<ሤሪ ሤሩማ! >><<ቃል አቴ አለሆ!>>

Postby ወለላዬ » Mon Oct 17, 2005 11:09 am

<<ቃል ለምድር ለሰማይ!>><<ሤሪ ሤሩማ!>>
------------<<ቃል አቴ አለሆ!>>---------

የአርባ ልጆች አርባ እስካወጣ ድረስ
ሳልነግርህ ዘገየሁ አደራዬን መለስ
አለብኝ መሀላ በአለም ላይ እስካለሁ
ቃል ለምድር ለሰማይ እበቀልሀለሁ!
በጥይት ተመቶ ከመንገድ ላይ ወድቆ
አንገቱን ቀና አድርጎ በደም ተጨማልቆ
አስምሎኛል ልጄ ተይዞ በሲቃ
<<ሤሪ ሤሩማ!>>አልኩኝ አከተመ በቃ!
ተራራ ወጥቼ ሜዳ ገደል ጭሬ
ምሽግህ ገብቼ ብትሮጥ አባርሬ
አለቅህም በቃ እንግዲህ አንት አውሬ
ደሙ ፈሶ እንዳይቀር ልጄ በጣር ጮሆ
አደራህ ብሎኛል <<ቃል አቴ አለሆ!>>

ላገዛዝህ እድሜ ለንግስናህ ጭዳ
ልጄን አስገድለህ ስለጣልከው ሜዳ
የጅህን አታጣም ትቀምሳለህ ፍዳ
እንዳይመስልህ ከቶ መንግስትህ የረጋ
ገና ብዙ ውርደት አለብህ አደጋ
ምክር ቤት ፍርድ ቤት ምርጫና መቀጫ
እያለ ደጋፊህ ቢጯጯህ ቢንጫጫ
ያሻው ቢንሸራተት ከስፍሩ እንደተልባ
ፈርቶ ቢኮለኮል እሸንጎ ቢገባ
አንተም መሪ ሆነህ ወጥተህ ብትኮፈስ
ባጋዚ ሰራዊት አገርን ብታምስ
ቃሌን አለውጥም እንድታውቀው መለስ

በዘር ተደራጅቶ መግደልና ማሰር
መቼ ጠቀማቸው ለነ አዶልፍ ሂትለር
ያ የሰይጣን ቁራጭ ኢዲያሚን ዳዳ
መቼ ሰነበተ በክብሩ ውጋንዳ
በግፍ የተነሱት እነ ሳሙኤል ዱ
አላየህ ይሆን ወይ? እንደያ ሲዋረዱ
ይሄው ነው ውጤቱ መጨረሻው ያንተም
ከስራት ከቅጣት ፍጹም አታመልጥም
አዲስ ምክር ቤትህ አስር ነገር ቢአረቅ
ያንተን ሹመት ክብር በጭብጨባ ቢአጸድቅ
አይችልም እውቀው ወንጀልህን ሊፍቅ

የአርባ ልጆች አርባ እስካውጣ ድረስ
ሳልነግርህ ዘገየሁ አደራዬን መለስ
አለኝ መሀላ በአለም ላይ እስካለሁ
ቃል ለምድር ለሰማይ እበቀልሀለሁ!
በጥይት ተመቶ ልጄ መንገድ ወድቆ
አንገቱን ቃና አርጎ በደም ተጨማልቆ
ደሙ ፈሶ እንዳይቀር የጣር ጩኸት ጮሆ
አደራህ ብሎኛል <<ቃል አቴ አለሆ!>>
አስምሎኛል ልጄ ተይዞ በሲቃ
<<ሤሪ ሤሩማ!>> አልኩኝ አከተመ በቃ!

ያልጠገበ ልጄን ገና እንኳን እሮጦ
አምሮበት ለባብሶ ሳይታይ አጊጦ
ያልፍልኛል ብሎ ሲደክም ሲለፋ
ባንተ ነብሰ ገዳይ በጥይት ሲደፋ
አገር አስተውሏል ወድቆ ሲንደፋደፍ
ተጠያቂ አንተ ነህ ለተፈጸመው ግፍ
ስለዚህ ልንገርህ በቋንቋህ እነሆ
አለቅህም በቃ<< ቃል አቴ አለሆ!>>
ቢመቻች ቢነጠፍ የስልጣንህ አልጋ
ብደረድራቸው ሹሞች ብታንጋጋ
ተቃዋሚን ወገን ብታስር ብትፈታ
ህግ ጅኒ ብትል ከንቱ ብታምታታ
ቃለን አላጥፋትም ታሪክ ይፋረደኝ
የልጄም አጥንቱ እሾህ ሆኖ ይውጋኝ
የሱን ደም መላሹ እኔው እራሴው ነኝ
በራሴ ፍርድ ቤት በራሴ ዳንነት
ፈርጄብሀለሁ ይግባኝ የሌለው ሞት
የልጄን ደም እንዲህ እንደላሰው ውሻ
ተውርደህ ስትሞት አንተም መጨረሻ
ውድቀት ስቃይህን ማየት ነው የምሻ
የሰው ንቀት ይዞህ ታብየህ በጉራ
ይቅርታ አልተይቅም ነገሩ እስኪጣራ
ብለህ ማለትህን ሰማሁኝ ሲወራ
እንደው ለነገሩ ይቅርታስ ብትጠይቅ
ይመስልህ ይሆን ወይ ነጻ ምትለቀቅ
እኔስ መቼ ኖሮኝ ይቅርታ ባንተ ላይ
ብየአለሁኝ እኮ ቃል ለምድር ለሰማይ
ሙጣጭም ይቅርታ የለኝም ጨርሶ
የልጄ ደም መንገድ ተንጣሎ እንዲህ ፈሶ
ተራራ ወጥቼ ሜዳ ገደል ጭሬ
ምሽግህ ገብቼ ብትሮጥ አባርሬ
አለቅህም በቃ! እንግዲህ አንት አውሬ
እንድበቀልለት ልጄ በጣር ጮሆ
አደራህ ብሎኛል <<ቃል አቴ አለሆ!>>
እውቀው እንግዲህ የወያኔ አለቃ
ቃሌን አላጥፋትም አከተመ በቃ!!
እፋረድሀለሁ እስካለሁ ባለም ላይ
<<ሤሪ ሤሩማ!>> ነው ቃል ልምድር ለሰማይ!!
ወለላዬ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 403
Joined: Wed Jan 26, 2005 11:20 am
Location: united states

Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: Google [Bot] and 5 guests