የወያኔን ስራ አስፈጻሚ መታገል ወያኔን መታገል ነው::

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

የወያኔን ስራ አስፈጻሚ መታገል ወያኔን መታገል ነው::

Postby ጥልቁ1 » Thu Feb 09, 2006 1:14 am

ቀጥሎ የምታነቡት ተከታታይ የመልስ ምት ; ልደቱን ለመደገፍ ለተጻፈው (http://www.aigaforum.com/lidetu.pdf) የተዘጋጀ ሲሆን ለልደቱ እና ዋልጌ ደጋፊዎቹም ይጠቅም ይሆናልና እነሆ!

ክፍል1
በተቃዋሚ ስም የሚንቀሳቀሱ ፣ የወያኔ ስራ አስፈጻሚዎችን መታገል ፣ ወያኔን መታገል ነው።

በጽሁፍ አለም ፣ ለሚቀርቡ ትንታኔዎች የሚሰጣቸው አርእስት ፣ የአጠቃላይ የጽሁፉን አላማ እና ንጥረ ሃሳብ የሚያዳብሩ ይመስለኝ ነበር። ‘ነበር’ እንድል ያደረገኝ ፣ አቶ ልደቱ አያሌውን አስመልክቶ ፣ “አንዴ አይበቃም እንዴ?” በሚል አርእስት አቶ ንጉሴ የጻፉትን ለመተቸት ሲሉ ፣ አቶ አስግድ ንጉሴ ፣ “ትግሉ በኢህአዴግ ላይ መሆኑ ቀርቶ ፣ በአንድ ልደቱ ላይ ማተኮሩ ምን ይባላል?” በሚል “አርእስት” ስር የጻፉትን መመልከቴ ነው።

እንደጽሁፉ አርእስት ከሆነ ፣ እሳቸውም ብእራቸውን “በኢህአዴግ” ላይ በቀሰሩ ነበር። ነገር ግን በተቃራኒው ፣ “ኢህአዴግን” እያገለገለ ያለውን ስጋዊ ቅሪት ፣ ፖለቲካዊ ነፍስ ለማላበስ የተበዩት መሆኑን ሳይ ፣ “በሰው ቁስል …” የሚለውን አስታውሶኛል።

ጸሃፊው ትችታዊ ሃሳባቸውን ሲጀምሩ ፣ እራሳቸውን “በቅንጅቱ ውስጥ ሆኖ እያንዳንዱን ሂደት የታዘበ” ግለሰብ አድርገው በማስተዋዎቃቸው ፣ እኔን ከሩቅ ያለሁትን አይነት ኢትዮጵያዊ ፣ የተለየ ምስጢር የሚያካፍሉን እንዲመስለን አድርጓል። ውስጠ-አዋቂ መሆናቸውንም የሚያሳዩን ፣ የቅንጅቱ የውህደት ችግር ፣ ዘርፈ-ብዙ እንጅ “የማህተም ምታ አልመታም ብቻ አይነት አይደለም” ማለታቸው ሲሆን ፣ ከነዛ ብዙ ዘርፎች ውስጥ ዋነኛው የሚሉት እና ያቀረቡት ብቸኛ ዘርፍ ግን “በአመራሩ መካከል የታየው የሁለት ትውልዶች ቅራኔ ነው” ብለውናል። ይሄንን ግን ፣ እሳቸው የውስጥ አዋቂዎች ምስጢር አድርገው ከማቅረባቸው በፊት ፣ ከአቶ ልደቱ አንደበት ከሰማነው ውሎ አድሮ ሰንብቷል። »»»“ፖለቲካ ውስጥ የገባሁት የጡረታ ጊዜየን ላሳልፍ አይደለም” አቶ ልደቱ

አቶ አሰግድ ብቻ ሳይሆኑ ፣ በቅርቡም አቶ ልደቱ ፣ በኢህአፓ ጊዜ ታጋይ የነበሩ ታላቅ ወንድማቸውን የተለየ ትውልድ አድርገው ስለአቀረቧቸው ፣ እስኪ ትውልድ የሚለውን ቃል ትኩረት ሰጥተን እንመልከተው። እያንዳንዳችን ፣ “ትውልድ” ለሚለው አይነት ቃል የየራሳችን ትርጓሜ ልንሰጠው እንችላለን። በእኔ እምነት ግን ፣ የአንድ አገር ትውልድ የአስተዋጽኦ ድርሻ ፣ እንደየ የአስተዋጽኦው መገለጫ ቦታ ይለያይ ይሆናል እላለሁ። እንጅ ፣ አንድ ትውልድ አገርን ከማገልገል ሙሉ በሙሉ የሚገለልበት ወቅት ሊኖር ይገባል ብየ አላምንም። እንበል ለምሳሌ ፣ በየትኛውም የስፖርት መድረክ ፣ በወጣነቱ ለአገሩ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ ስፖርተኛ ፣ ሁሌ የውድድር መድረኩ ውስጥ እኔ ብቻ አገሬን ካልወከልሁ ቢል እና ወደ የውድድር አደባባይ ቢወጣ ፣ ከእኛ ይልቅ ፣ ቀርጾ የሚያሳየን የቪዲዮ ካሜራ ይህንን ሰው ጥርስ አውጥቶ ይስቅበታል ለማለት ይቻላልና ለሚተካው ትውልድ ቦታውን መልቀቅ ይገባዋል። ያካበተውን ልምድ ለማካፈል ግን ፣ እድሜ ይወስነዋል አልልም።

ወደ ፖለቲካው ወይም ሌላ ማህበራዊ አኗኗሮች ስንመጣ ደግሞ ፣ ለአመራር ብቃት አስተዋጽኦ ከሚያደርጉት አንዱ ፣ በእድሜ የሚያካብቱት ልምድና እውቀት ነው ብየ አምናለሁ። ጸሃፊው ካሉትም በመንደርደር ፣ የእድሜ ልዩነቶች በመግባባት ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ይኖራል በሚለው “እጅግ በጥቂቱ!” አምናለሁ። ይህን በጥቂቱ የማምነውን ሙጥጥ አድርጎ ከውስጤ የሚያወጣው ግን ፣ በአለም አቀፍ መድረክ እና በተለያዩ የስራ ገበታዎቻቸው ፣ ከፖለቲካ እና ማህበራዊ ኑሮ ተለያይተው የማያውቁ ምሁራንን ፣ እግዚያብሄር በአደላቸው የእድሜ ጸጋ ለማሳነስ መሞከር ፣ የወጣት ሳይሆን የብልግና ባህርይ መስለኛል። በእድሜ ክፍያ ፣ የአንድን አገር ትውልዶች በመለያየት ፣ እንዴው በጭፍን ፣ ወጣቱን መምራት ያለበት ወጣቱ ነው የሚል የድምዳሜ እንድምታ ላይ መድረስ ፣ ከሃቅ ጋር መጋጨት ይመስለኛል። ምክንያቱም ፣ በአገራችን ያለው ወጣት ፣ በየእለቱ በአጋዚ ጥይት የሚታረደው ፣ የአቶ ልደቱ የፓርላማ ውስጥ መቀመጫ “ወርቅ ይነጠፍበት i” ብሎ ሳይሆን ፣ የህዝቡን ጥያቄ ተቀብለው ፣ ለህዝብ ትግል እራሳቸውን አሳልፈው የሰጡት “መሪዎች ይፈቱ” በማለት ነው። ወጣት ፖለቲከኛ በእድሜ ለበሰሉት የሚመኘው ከተሳትፎ ማግለልን ከሆነማ ፣ የፖለቲካው መድረክ የልምምድ መድረክ (Improvisational Theater Space) ሆነ ማለት ነው?!።

ክፍል2 ይቀጥላል
ጥልቁ1
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 767
Joined: Tue Jan 27, 2004 4:32 am
Location: bhutan

Postby ጥልቁ1 » Thu Feb 09, 2006 1:17 am

ክፍል 2

ከዚሁ ፈቀቅ ሳንል ፣ ጸሃፊው የቅንጅቱን አመራር ሲጨመድዱት፣ ለአለፉት 30 አመታት ሲፋጩ የነበሩት ፖለቲከኞች ፣ “ውስጡን ለመፈንዳት የሚብላላ ፣ አብረው የነበሩ ሃይሎች የተቀየጡበት እና ከደርግ/ኢሰፓዎች ጋር ያበሩ” ብለውታል። እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በድጋሜ ፣ ጸሃፊው ወያኔን ለማገልገል የተጠቀሙት መጣጥፍ መሆኑን የሚያመላክት። ከሃሳባቸው በመነሳትም ፣ ወይም ወያኔ ስለቅንጅቱ የሚናገርው ሁሉ ሃቅ ነው ፤ አለበለዚያም ጸሃፊው ቅንጅቱን “ደርግ/ኢሰፓዎች” ማለታቸው ከወያኔ ጋር አብረው የተሰልፉ እንዲያስመስላቸው ይጋብዛል። እዚህም ላይ አንድ በትልቁ የማልስማማበት ሃቅ ቢኖር ፣ “ደርግ/ኢሰፓ” የሚባለው የፖለቲካ መዋቅር ፣ በግለሰቦች ላይ የተጫነ የአንድ ወቅት ብናኝ የፖለቲካ መዋቅር እንጅ ፣ ሰዎች የተጠመቁበት ሃይማኖታዊ ጸንሰ-ሃሳብ አይመስለኝም።

በሰለጠነው አለም ፣ አንድ ግለሰብ ከአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወደሌላ ፓርቲ ለመቀየር ወይንም ፣ ከምንም የፖለቲካ ፓርቲ እራሱ በማግለል የግል እምነቴን ላራምድ ቢል ፣ የፖለቲካ ንስሃ (Political Confession) አይጠበቅበትም። በእኛም አገር ፣ በየትኛውም የፖለቲካ መድረክ የተሳተፈ ግለሰብ ፣ ወደሌላው መድረክ ቢዞር ፣ የሚያስወቅስ ሊሆን አይገባም። ያ ማለት ግን ፣ ያለምንም ተጨባጭ ምክንያት ፣ በቅንጅት ስም ምርጫ አሸንፎ ሲያበቁ ፣ አንድ ወይም ሁለት ግለሰቦች በአመለካከት ብቃታቸው ፣ በስሜታዊነታቸው ፣ በስልጣን አነሰኝ ባይነታቸው ፣ በክህደትም ሆነ በማናቸውም ምክንያት ፣ በግለስብ ደረጃ ከአመራር ሲወገዱ ፣ በመጽሃፍ ቅዱስ ውስጥ ፣ ከአባቱ ኮብልሎ እንደተመለሰው ልጅ ወይም ደግሞ የአዲስ ፍቅረኛ እጅ ሲያጥር ወደቀድሞ ፍቅረኛ እንደሚዞር አባይ አፍቃሪ ፣ “… በጨው አጥቦ” “ባይፈጀኝ በእጀ ቢፈጀኝ በማንኪያ” ማለት አይደለም። ምንም ይሁን ምን ፣ የፖለቲካ ሰዎች ፣ ዞሮ መግቢያቸው የሚወክሉት ህዝብ ነው። በጠራራ ጸሃይ “የህዝብን ጥያቄ አስተናግዳለሁ” ሲል የኖረ መላስ ፣ በአንባገነት ህዝብን መካድ ተገቢ አይደለም። ይህ አይነቱ ድርጊት ፣ የፖለቲካ ምህዋርን መቀየር ሳይሆን ፣ ታሪካዊ ተጋድሎን በስጋዊ አድልኦ መለውጥ ነው እላለሁ። እስኪ አቶ ልደቱ ወደ ፈረሰው ኢዴአፓ-መድህን ቤት ከመዞራቸው በፊት ፣ መራጩ ህዝብ ምን ይል ይሆን ብለው ጠይቀው ነበር?! በተጨማሪም ፣ ህዝቡ በአሁኒቱ ሰአት ቁም ስቅሉን እያየ ያለው ቅንጅቱን ብቻ ብሎ መሆኑን ያውቃሉን?!

ጸሃፊው በገጽ 2 ያቀረቡት ሃሳብ ሲጨመቅ የሚወጣው ፣ በቅንጅቱ ውስጥ አቶ ልደቱ ከመጀመሪያው ጀምሮ ሲያንጸባርቁት የነበረው አመለካከት ፣ ከሰውየው ብቃት እና ግለሰቡ ከወከሉት ፓርቲ ጥንካሬ አንጻር ትክክል በመሆኑ ፣ እሳቸው ያሉት ባለመሆኑ “ዛሬ ሁሉም የእጁን ያገኘበት ውጤት ተመዝግቧል” የሚል እንድምታ ይንጸባረቅበታል። ይህ አገላለጻቸው “በፍጥነት ስትንሸራተት ፣ የሰውነትህ ክብደት ይቀልና ትወድቃለህ” የሚለው የፊዚክስ መላምትን አሰታውሶኛል። የአቶ አሰግድ ገለጻ ፣ የሚከራከሩላቸውን ግለሰብ ለመታደግ ሲሉ ፣ ቅንጅትን ፋይዳ ያለው ስራ ያልሰራ አስመስለው አቅርበውታል። ሃቁ የሚያሳየው ግን ፣ የቅንጅቱ አመራሮች ፣ ብቃት ያለው ስራ የሰሩ መሆኑን ነው። ከህዝብ የወጡ መሪዎች እንደመሆናቸውም ፣ አንድም ጊዜ የህዝብን ፍላጎት ሳያጓድሉ ፣ ከህዝብ ፍቅር ጋር ዛሬ እስር ቤት ቢሆኑም ፣ የትላንት የትግል ጓዶቻቸው ስለካዷቸው ፣ “የእጃቸውን አገኙ” ሳይሆን ሊያስብል የሚገባው “እጃቸው አመድ አፋሽ ሆነ” ነው የሚያሰኝ። በዚህ አለም ላይ በክብር እራስን አሳልፎ ከመስጠት የተሻለ መሰዋትነት ያለ ግን አይመስለኝም። በእኔ እመነት ፣ የቅንጅቱ አመራሮች ብቃት ከተፈተነባቸው አንደኛው ፣ በአቶ ልደቱ እና በአቶ ሙሸ ላይ የስነ-ስራት እርማጃ መውሰድን ያካትታል። በስህተት ውስጥ ሆኖ ለሚያይ ሃቅን ለማገናዘብ ይከብደው ይሆናል እንጅ ፣ የሁለቱ ከአመራሩ መታገድ ፣ ቅንጅቱ የአመራር ብቃቱን ያስመሰከረበት ለመሆኑ ፣ ሁለቱም በርከት ያሉ ቃለ-መጠይቆችን አድርገው ፣ አንድም ህዝብን የሚያሳምን ምክንያት አለማቅረባቸው ፣ ለምለው ምስክሬ ነው። ከህዝብ እኛ እንበልጣለን ከሆነ ፣ እራሳቸውን ሲመሩ ይኖራሉ ማለት ነው። እዚህ ላይ አንድ ግለሰብ በVOA ራዲዮ ላይ የሰጡትን አስተያየት ልድገም። “ኢዴአፓ-መድህን ነን የምትሉ ግለሰቦች ፣ እስኪ የአዲስ አበባን ህዝብ ለስብሰባ ወይንም ሰላማዊ ሰልፍ ጠርታችሁ ደጋፊያችሁን አሳዩን?!” ብለዋል።
ጥልቁ1
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 767
Joined: Tue Jan 27, 2004 4:32 am
Location: bhutan

Postby ጥልቁ1 » Thu Feb 09, 2006 1:18 am

ክፍል 3

ሌላው ፣ እዚሁ ገጽ ሁለት ላይ የተሰነዘረው “በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን ስለአገራቸው አያገባቸውም” የሚለውን የዘለፋ እንድምታ ፣ እንኳንስ በጽሁፍ ፣ በቪዲዮም ያየንላችሁ ስለሆነ ብዙም አይገርምም። አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ፣ በአገር ውስጥ ሆኖ መታገል አማራጭ የሌለው የትግል ስልት ቢሆንም ፣ በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያዊ የሚሰንዝራቸውን ፖለቲካዊ አመላካከቶች ፣ የበአድ አድርጎ መመልከት ፣ “የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም” አይነት ካልሆነ በቀር ፣ የሚጎዳው ያው ተናጋሪውን ነው። በጣም የሚገርመው ነገር ፣ በአሳያችሁን የራሳችሁ ቪዲዮ ውስጥ ፣ “ሃምበርገር ሲበሉ ኖረው ወደ አገራቸው የተመለሱ” ስትሏቸው የነበሩት ፣ በእስር የሚገኙት የዛሬዎች የቅንጅት መራሮች ፣ ስጋቸው ምንም ሳይጎድልበት ፣ ወደአገራቸው ተመልሰው ሲታገሉ በመሆኑ ፣ ውጭ አገር ለሚኖር ኢትዮጵያዊ ያላችሁ አላስፈላጊ ጥላቻ ፣ ግራ ያጋባል። ነው ወይስ ከእድሜ ቀጥሎ ሌላው የመለያያው መስፈርታችሁ ፣ ውጭ አገር በኖረ እና ባልኖረም መካከል ነው።?! በዚህ አጋጣሚም ፣ ሊታወቅ ከሚገባው አንዱ ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ከሩቅ ሆኖ ለሚያይ ሌላ ኢትዮጵያዊ ከሚሰማው ቁጭት አንዱ ፣ “እንዴት እኔ በውጭ አገር ያለኝን ነጻነት የአገሬ ዜጋ በገዛ አገሩ ያጣል?!” ሊል እንደሚችል አትዘንጉ። ይህ በእንግዲህ እንዳለ ፣ በውጭ አገር እየኖሩ ፣ በቅን መንፈስ ለትውልድ አገራቸው ፣ በጎ የሚመኙላት እንደአሉ ለማንጸባረቅ እንጅ ፣ ማህበራዊ የኑሮ አስተዳደርን ፣ በፖለቲካ ለማስተናገድ ፣ ትልቁ የመሪዎች ምንጭ እናት ኢትዮጵያ መሆኗን ላሰምርበት እዎዳለሁ።

ወረድ ብለው ፣ ለውህደቱ አለመሳካት ፣ የቅንጅቱን ማእከላዊ ኮሚቴዎች የሚወቅሱት ፣ የቅርንጫፍ ጽ/በቶች ሳይዋሃዱ ፣ ወደ አጠቃላይ ውህደት እናመራለን በማለታቸው ነው ብለዋል። እንግዲህ የሁለቱ ትውልዶች ልዩነት ፣ አንደኛው ችኩል ትውልድ ፣ ሁሉም ጽ/ቤቶች አሁኑኑ ይዋሃዱ ሲል ፣ ሌላው በረጋ መንፈስ ከታች የሚኖረው ውህደት ጊዜ የሚፈልግ በመሆኑ ፣ አሁን የወያኔ ምርጫ ቦርድ በህጋዊ አንድነታችን ላይ የፈጠረብንን ችግር እንቅረፍ ማለት ይመስለኛል። ይህ አይነት የቴክኒካል ስራ ፣ ለውህደቱ የሚያበረክተው ችግር ቀላል ባይባልም ፣ መሰረታዊ ነው ለማለት ግን ይቸግራል። ምክንያቱም ፣ አራት የራሳቸው የነበረውን ታላቅ የተናጠል ጉዞ ጥለው ፣ የከሰሙ ፓርቲዎች ፣ ምንም አይነት የንብረት ርክክብ ላይ ችግር ቢፈጠር ፣ በውይይት የማይፈታበት ምክንያት ይኖራል ለማለት ይከብዳል።

ሌላው ፣ እንደ ፋሽን ሆኖ በጸሃፊው ቢጤ ሰዎች የሚሰነዘረው ቅንጅቱን የማጥቂያ መሳሪያ ፣ “እኛ ትክክል ነን ፣ ካላመናችሁን የቀረጽነውን ቪዲዮ ታዩታላችሁ” የሚለው አካሄድ ነው። እጅግ ክብደት ተሰጥቶት ፣ ለተለያዩ ቃለ-መጠየቆች ማዳበሪያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው የማስተያያ (Reference) ፣ 3ኛው የፓርቲያቸው አጠቃላይ ስብሰባ ቪድዮ ነበር። ውስጡ ሲታይ ግን ፣ ቅንጅቱን ከማጣጣል ፣ እና በውህደቱ ላይ ችግር የፈጠሩትን ግለሰቦች ከማገልገል ይልቅ ፣ እነዚሁ ግለሰቦች የሚጫዎቱትን እጅግ አስቂኝ የፖለቲካ ትርኢት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነበር። ይህንን ቪድዮ ለመተቸት ራሱን የቻለ መጣጥፍ ይፈልጋልና ልተዎው። ነገር ግን ፣ ሌላ “ልታዩት ይገባል” ፣ የተባለው ቪዲዮ ደግሞ ፣ ቅንጅቱ ምን ሲያደርግ ያሳየን ይሆን ብለው ከሚጠብቁት ኢትዮጵያዊያን ግን አንደኛው አይደለሁም። በተያያዘም ፣ ጸሃፊው ፣ “አቶ ልደቱ ተገፍተው ወጡ” ብለው ከመናገራቸው በፊት ፣ አንድ የቅንጅቱ አመራር ፣ የሰጡትን መግለጫ ለመጥቀስ ያህል ፣ ከአቶ ልደቱ ጋር ሌሎች የቅንጅቱ ካውንስል ፣ ለ3 ሰአታት ያህል ውይይት አድርገው እንደነበረና ፣ ነገር ግን አቶ ልደቱ እጅግ ስነ-ምግባር በጎደለው ሁኔታ ፣ የሽማግሌዎችን ልመና ሁሉ ረግጠው ከስብሰባው እንደወጡ ገልጸዋል። ለእኔ እንዴውም የሚቀለኝ ፣ እራሳቸው አቶ ልደቱ ፣ አፋቸውን ሞልተው ፣ “ምንም እንኳ ዲሞክራሲ ማለት በብዙሃን ድምጽ መገዛት ቢሆንም ፣ ለማላምንበት ግን አልገዛም” የሚሉትን መጥቀሱ ነው። ይህ እንግዲህ “እንስሣት ሁሉ እኩል መብት ዓላቸው ፣ አሳማዎች ግነ የበለጠ እኩል ናቸው” የሚለውን አይነት መሆኑ ነው። ስለዚህም ፣ አቶ ልደቱን ገፍቶ ያስወጣቸው ፣ “ከእኔ በላይ ለአሳር” የሚለው አባዚያቸው ነው።

ለማጠቃለልም ፣ በእኔ ግምት ራሴን ጨምሮ ሰዎች ስለአቶ ልደቱ የሚጽፉበት ምክንያት ፣ ግለሰቡን ለማጥቃት ሳይሆን ፣ ግለሰቡ እና መሰሎቻቸው ለወያኔ የሚሰጡትን ጠቀሜታ ለማጋለጥ እና ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙት ታሪካዊ ክህደት ፣ ምን ያህል ኢትዮጵያዊያንን እንደሚያቃጥል በማሰብ ነው። በተጨማሪም፣ እሳቸው የቅንጅቱ መሪዎችን በመወንጀል እና በላያቸው ላይ ለምስክርነት የሚሆን መጽሃፍ ሲጽፉባቸው ፣ ልቡ የሚቃጠለው ህዛባችን የሚተነፍስበት መስክ ስለሌለው ፣ የህዝብንም ስሜት ከመጋራት አንጻር ነው። ዛሬ አይንን በአፈጠጠ መልኩ ፣ “እኔ በቅንጅቱ ምልክት ልወዳደር እንጅ ፣ የቀድሞው ፓርቲየን ግን አልቀየርሁም” ብሎ በአደባባይ ከሚክዱ ግለሰቦች በላይ ማንን መሟገት ይገባል ይላሉ?!። እርሰዎስ ቢሆኑ ፣ ጽሁፎትን ያስነበቡን በወያኔ ድህረ-ገጽ መሆኑን እረሱት?! ጸሃፊው እንዳሉትም ፣ ወያኔማ እስከአፍንጫው የታጠቀ ሃይል ብቻ ሳይሆን ፣ ከዚህ በኋላ በስጋዊ ፍላጎት ከደከሙ ግለሰቦች ጋር እንጅ ፣ የህዝብ ተአማኒነት ከአላቸው ፖለቲከኞች ጋር በህዝባዊ አጀንዳዎች ዙሪያ አልድራደርም ብሏል። ስለዚህ ፣ የህዝቡን ሞራል በማርከስ የወያኔን የፖለቲካ ስራ እየሰሩለት ያሉትን አገልጋዮችን መታገል ፣ እራሱን የቻለ ወያኔን መታግል ነው እላለሁ።

በዚህ አጋጣሚ ፣ ጸሃፊው አንድ የዘነጉት ነገር ቢኖር ፣ “እኔን የሚመጥን ትውልድ እስኪፈጠር እራሴን ከፖለቲካው ባርቅ ይሻላል” ያሉት እራሳቸው አቶ ልደት መሆናቸውን ነው። ዛሬ ፓርላማ ገብቶ ፣ “አይሰጥ አዛኛ ቅቤ አንጓች” አይነት ንግግር ማድረግን ጨምሮ ፣ ማናቸውም የአቶ ልደቱ እንቅስቃሴ ፣ ከማንም በላይ በታሪክ የሚጎዳቸው እራሳቸውን ብቻ ነው። የአገሬ ሰው ሲተርት ፣ “ሰው ይውደድህ ድንጋይ ይጫንህ” ይላል።

በአለማችን ውስጥ የነበሩት እና የአሉት አንባገነን መሪዎች ፣ ለመሪነት የሚደርሱት ፣ በአላቸው ርትኡ አንደበት ነው። ዛሬ አቶ ልደቱም ፓርላማ ላይ የሚያደርጉዋቸው ንግግሮች የከፉ ባይሆኑም ፣ የግለሰቡ በብዙሃን ድምጽ አለመገዛት ጎልቶ የወጣበትን ወቅት ማንም ስለማይዘነጋ ፣ እራሳቸው በአሳተሙት መጽሃፍ ውስጥ ፣ ስለወያኔዎች የተናገሩትን በመጥቀስ እሰናበታለሁ። “የህውኀት /ኢህአዴግ ታጋዮች የት ላይ ሲደርሱ የባህሪ ለውጥ እንዲያደርጉ በጥብቅ መታዘዛቸውን ባለውቅም አዲስ አበባ ሲገቡ ከስድስት ዓመት በፊት ካየኋቸው በጣም የተለዩ ሆነው አገኘኋቸው::” አዎን! ሁሉም ሰው የሚፈልገውን እስኪያገኝ አፉ ቅቤ ነው። እንደ አቶ ልደቱን አይነት አንባገነን ግን ፣ የስልጣን ፈረስ ጋልበው ፣ ብዙም ሳይርቁ መያዛችን ፣ ይህ ትውልድ ሁሉን ነገር በጥንቃቄ እንዲያይ አስተምሯል።

በነገራችን ላይ ፣ በጸሃፊው መስፈርት መሰረት ፣ እኔም የዚህኛው ትውልድ አባል ነኝ። የእኔ ትውልድ ; ከሀዲው መለስን የሚከተል ቢሆን ኖሮ ግን ትውልዴን በጠላሁት ነበር:: ነገር ግን ; ኢትዮጵያ ያለው ሳር ቅጠሉ ; ወያኔ እና አገልጋዮቹ ይጠላልና ትውልዱን እኮራበታለሁ::


8)
ዘብሄረ ኢትዮጵያ
ጥልቁ1
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 767
Joined: Tue Jan 27, 2004 4:32 am
Location: bhutan

Postby ዛግሪ » Thu Feb 09, 2006 12:54 pm

ለማጠቃለልም ፣ በእኔ ግምት ራሴን ጨምሮ ሰዎች ስለአቶ ልደቱ የሚጽፉበት ምክንያት ፣ ግለሰቡን ለማጥቃት ሳይሆን ፣ ግለሰቡ እና መሰሎቻቸው ለወያኔ የሚሰጡትን ጠቀሜታ ለማጋለጥ እና ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የፈጸሙት ታሪካዊ ክህደት ፣ ምን ያህል ኢትዮጵያዊያንን እንደሚያቃጥል በማሰብ ነው።
.....
ዛግሪ
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 966
Joined: Sat Dec 17, 2005 11:31 pm


Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 2 guests