ደምወዝ ለማግኘት እንጂ ለማወቅ ገና አልመሸም፡፡

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

ደምወዝ ለማግኘት እንጂ ለማወቅ ገና አልመሸም፡፡

Postby ክቡራን » Sat Jan 21, 2017 2:07 pm


ለዲጎኔ aka እሰፋ ማሩ ምሳሌ ቢሆን በሚል የቀረበ፡፡
Image
ቄስ አስፋው ይትባረክ ድቁና ከተቀበሉ ከ40 ዓመታት በኋላ የቅስና ክህነትን ለመቀበል የበቁ፤ በጡረታ ዘመናቸው የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በመማር ትምህርት ዕድሜ እንደማይገድበው ያስመሰከሩ ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ ቦታዎች በሙያቸው ያገለገሉ፤ ሰው ናቸው:: የእኒህን ሰው የሕይወት ልምድ ዛሬ እነሆ
መልካም ንባብ!
ስለትውልድና ዕድገት በመጨዋዎት ቆይታችንን እንጀምር?
የተወለድኩት በቀድሞው በጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ጎንደር አውራጃ በአሁኑ ደንቢያ ወረዳ ልዩ ስሙ ጉራምባ ሚካኤል በሚባል ቦታ ሐምሌ 21 ቀን 1945 ዓ.ም ነው::
ዕድሜዬ ለትምህርት እስኪደርስም በዚያው አድጌያለሁ:: በኋላ ግን አባቴ በጎንደር ከፍተኛ የቤተክርስቲያን መምህር ስለነበር ወደዚያው ሄጄ ትምህርት ቀጥያለሁ::
ከፊደል እስከ ውዳሴ ማርያም ድረስ ከአባቴ ተማርኩ፤ በመቀጠል ከመጋቤ አዕላፍ ሄኖክ ወልደሚካኤል በጎንደር ባታ ጾመ ድጓ፣ መስተጋብዕ፣ አርባዕት፣ አርያም፣ … ቀጸልኩ::
የአባቴ ፍላጎት እኔ እርሱን እንድተካ ነበር፤ እኔ ግን ለአስኳላ ትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ወደዚያው አዘነበልኩ::
የሳይንስ ትምህርት ቤት ቆይታዎት እንዴት ነበር?
በራሴ ፍላጎት የተነሳ ጥቅምት 16 ቀን 1956 ዓ.ም በጎንደር ከተማ በሚገኘው ጻድቁ ዮሐንስ ትምህርት ቤት አንደኛ ሀ ክፍል ገባሁ::
ወዲያው ደግሞ በ'ተርም' አልፌ ወደ ሁለተኛ ክፍል ገባሁ:: በዚያን ጊዜ በዓመት ሁለት ክፍል እያለፉ መማር ይቻል ነበር፤ ያ ሂደት ተርም ይባላል:: ከሁለተኛ ክፍል ደግሞ በቀጥታ ወደ አራተኛ ክፍል “በደብል ፕሮሞሽን” (በአንዴ ሁለት ክፍሎችን በማለፍ) ገባሁ::
ከአራተኛ ክፍል ደግሞ ወደ ስድስተኛ ክፍል አሁንም በቀጥታ አለፍኩ::
ያን ጊዜ ደግሞ ከስድስተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ስለነበረ እሱንም ተፈትኜ በጥሩ ውጤት አጠናቀቅሁ:: በዚህ መልኩ በደረጃ ትምህርቴን እያለፍኩ በመጨረሻ በሕዝብ ጤና ጥበቃ ማሰልጠኛ (በአሁኑ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ) በስነ-ንጽሕና የጤና ባለሙያ (ሳኒተሪያን ኸልዝ ኦፊሰር) ሰኔ 12 ቀን 1965 ዓ.ም ተመረቅሁ::
በመጀመሪያ ሥራ የተመደቡት ሁመራ ነበር?
አዎ! እንደተመረቅሁ የተመደብኩት ሁመራ ነበር፤ በመቀጠል ወደ ደቡብ ጎንደር እስቴ ጤና ጣቢያ ተዛወርኩ::
በወቅቱ ግራዝማች አድማሱ በላይ የተባሉ ሰው ደርግን የሚቃወሙ ሰው ነበሩ፤ በእርሳቸውና በደርግ መካከል በነበረ ግጭት ከሥራ ተፈናቅዬ ጎንደር ተቀመጥኩ:: በዚህ መካከል ፈንጣጣን ለማጥፋት በተደረገው ዘመቻ የደብረ ታቦርና ጋይንት የቅኝት ባለሙያ (ሰርቪላንስ ኦፊሰር) ሆኜ መሥራት ጀመርኩ::
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ፈንጣጣ ከምድረ-ገፅ እስከጠፋበት 1972 ዓ.ም ድረስ በዚሁ የፈንጣጣ ማጥፋት ፕሮግራም ቆየሁ::
ከ1972 ዓ.ም በኋላ ደግሞ “የፀረ-ስድስቱ” ክትባት በሕጻናት ላይ ሲጀመር መሥራች ሁኜ ቀጠልኩ:: በኋላም የጭልጋና የደንቢያ ወረዳ የተላላፊ በሽታዎች መከላከያ አስተባባሪ ሆኜ አገለገልኩ::
ቀጥሎ የዞኑ የክትባት መድኃኒቶች ጥበቃ የዞን ኃላፊም ነበርኩ፤ የጎንደር አውራጃ ጤና ጥበቃ በአውራጃ ደረጃ ሲቋቋምም ገብቼ ሠራሁ:: በመቀጠል በ1983 ዓ.ም የዞኑ የሃይጅንና ጤና አጠባበቅ ትምህርት አስተባባሪ ሆንኩ፤ ቀጥሎ “ኤክስፐርት” የሚባል ስም መጣ፣ ኤክስፐርት ሆንኩ::
በዚያው ውስጥ የድንገተኛ ወረርሽኝ ሕመሞች ባለሙያ ሆንኩ፤ በ2003 ዓ.ም በዚሁ ሙያ እያለሁ በአንድ ተቋም (በጤና ጥበቃ ሥር) ለ40 ዓመታት አገልግዬ ጡረታ ወጥቻለሁ::
ከሁመራ የወጡት በአንድ ውሻ ሞት የተነሳ ነው አሉ?
አዎ! በወቅቱ በሁመራ አካባቢ የውሻ እርባታ በዛ፤ ውሾቹ ደግሞ በተከዜ ወንዝ አካባቢ ወደ አውሬነት ተለውጠው በግና ፍዬል እያባረሩ መብላት ጀመሩ:: በዚያን ጊዜ ልክስክስና ባለቤት አልባ ውሾችን ማስወገድ የኛ የሥራ ኃላፊነት ነበርና እነዚህን በረኸኛ ውሾች እንዲያስወግዱ ለባለሙያዎች ትዕዛዝ ሰጠሁ::
አንድ ቀን አንድ ሰው ሽጉጥ ታጥቆ ወደቢሮዬ መጣ፤ ሁኔታው ሁሉ በጣም እንደተቆጣ ያስታውቃል:: የተቆጣበት ሁኔታ አልገባኝምና እንዲቀመጥ ጋበዝኩት፤ “ምን ተቀመጥ ትለኛለህ! ምን አደረገ ብለህ ነው ውሻዬን የገደልከው?” ብሎ አምባረቀብኝ:: ‘እኔ ካንተ ደጃፍ መጥቼ ውሻህን አልገደልኩም፤ መረጃ የሰጠህ ሰው አሳስቶሀል::
እኔ ሙያዬ ስለሆነ ባለቤት አልባ የዱር ውሾች እንዲገደሉ ፕሮግራም ቀይሻለሁ፤ ከዚያ ያለፈ በየቤቱ ያሉ ውሾችን አልገደልኩም፤ አላስገደልኩም:: የግድያውን ምክንያት ታውቀዋለህ፤ ተከዜ ውስጥ አሸዋ ውስጥ ተደብቀው ፍዬልና ሰው የሚያድኑ ውሾችን ነው የገደልነው:: የአንተ ውሻ ወደዚያ ሄዶ ሞቶ ከሆነ የኛ ጥፋት አይደለም’ ብዬ መለስኩለት:: የተወሰነ በረድ አለ::
በዚህ ስጋት ገብቶኝ ለመልቀቅ መዘጋጀቴን ለአንድ ወዳጄ ነገርኳቸው፤ ኤም ዋን መሳሪያ የታጠቀ ወንድማቸውን መድበው ለተወሰነ ጊዜ አስጠበቁኝ፤ እኔ ግን የሰውየው የብስጭት ሁኔታ ትዝ ሲለኝ አካባቢውን መልቀቅ እንዳለብኝ ወሰንኩ::
በሄሊኮፕተር ታጅበው የተዳሩ ብቸኛው ሰው እንደሆኑ ሰማሁ፤ እውነት ነው?
ትክክል ነው! ያገባሁት በ1969 ዓ.ም የፈንጣጣ ማጥፊያ ፕሮግራም ውስጥ እየሠራሁ ሳለ ነው:: ያኔ ሠርጌ በሄሊኮፕተር ታጅቧል:: ባለቤቴ የጎርጎራ ሰው ነች፤ እኔ ሳላውቅ ጓደኞቼ ከጎርጎራ እስከ ጎንደር (እስከ ቤቴ) በሄሊኮፕተር እንድመጣ አስበው ተዘጋጅተው ነበር::
ሐሳባቸውን ሲነግሩኝ “ሠርጌን ለማጀብ የመጡ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣናት፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ ምሁራንና የሃይማኖት አባቶች በመሬት እየሄዱ እኔ በሄሊኮፕተር አልሄድም!” ብዬ ፈቃደኛ ሳልሆን ቀረሁ::
በዚህ የተነሳ ፓይለቱ በዳሱ በላይ እየበረረ ከረሜላና ቄጠማ ይበትን ነበር፤ በወቅቱ የሠርጉ ታዳሚና እኔ አስቀድሞ ዕውቅና ስላልነበረን ተደናግጠናል::
ያን ጊዜ ደግሞ ደርግ ብዙም ያልተረጋጋ ስለነበረና ጎንደር የኃይለሥላሴ ደጋፊ ተደርጎ ስለሚቆጠር “ለማስፈራራት” ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ይፈፀም ነበር:: በዚህ የተነሳ መጀመሪያ መረበሽ ተፈጥሮ በዕቃና በምግብ ላይ ሁሉ የመረጋገጥና የመደፋፋት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፤ በኋላ ግን ስናውቀው ሠርጉን ለማጀብ ሆነና ተረጋጋን::
በዚያን ጊዜ አባቴና ጎረቤቶቼ እንዲሁም ታዳሚው በሙሉ ትልቅ ኩራት ተሰማቸው፤ እኔም ደስታዬ ወደር አልነበረውም:: የተዳርኩትም በዲቁና ማዕረግ ስለነበረ ለአባቴም ለእኔም ደስታው እጥፍ ድርብ ሆኖልናል:: ያንን የደስታ ቀን መቼም በሕይወቴ አልረሳውም::
የትዳር ሕይወትዎ ምን ይመስላል?
በትዳሬ በጣም ደስተኛ ነኝ! ለዚያም ነው ከ40 ዓመታት በላይ አብረን የኖርነውና ልጆችን ለቁም ነገር ያበቃነው:: አንዷ ልጃችን ባለሁለተኛ ዲግሪ ነች፤ ሁለቱ ልጆቻችን ደግሞ የመጀመሪያ ዲግሪ አላቸው:: ሌላኛ በዲፕሎማ ተመርቋል፤ አንዷ ልጃችን ደግሞ ውጭ ሀገር ትኖራለች::
ትዳራችን የተመሠረተው ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ ነው፤ እኔ እንዳልኩ ዲያቆን ሆኜ ሁመራ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ሥራዬ ጎን ለጎን አገለግል ነበር፤ እርሷ ደግሞ እዚያው ዘወትር ታስቀድስ ነበር:: ከዚያ ተያይተን በቤተ ክርስቲያን ቃል ተጋባንና ለቤተሰብ ሽማግሌ ልከን ተጋባን::
ከዚያን ጊዜ አንስቶ ቤተሰብ የምትመራ እርሷ ነች:: እኔ የማገኘውን ደመወዝ ለእርሷ ከመስጠት በቀር በቤት ውስጥ የማደርገው አስተዋፅዖ ዝቅተኛ ነው:: ባለቤቴ መምህር ነበረች፤ አሁን ሁለታችንም ጡረታ ወጥተን በደስታ ከልጅ ልጃችን ጋር እየተጫወትን እየኖርን ነው::
ይህንን ያህል ጊዜ ስንኖር የጎላ ልዩነት ኖሮን አያውቅም፤ ትንሽ የሚያጋጨን የእኔ አለባበስ ጉዳይ ነው:: እኔ ብዙ ጊዜ ራሴን የመጠበቅ ልምድ የለኝም፤ እርሷ ደግሞ በደንብ አምሬ እንድታይና እንድደምቅ ስለምትፈልግ “ይህን ልበስ! ይህን አትልበስ” ትለኛለች::
ዛሬም አንተን ለማግኜት እንደምወጣ ስነግራት “ፀጉርህ አድጓልና ተስተካክለህ ሂድ” ብላ ብር ሰጥታኝ ተስተካክዬ ነው የመጣሁት፤ ከዚህ ያለፈ ልዩነት የለንም::
በኢሕአፓነት ተጠርጥረው ለእስር ተዳርገው ነበር፤ የኢሕአፓ አባል ነበሩ?
በ1971 ዓ.ም ከወንድሜ ጋር በኢሕአፓነት ተጠርጥረን ታስረናል፤ እኔ ዕድለኛ ሆኜ ተርፌያሁ:: ወንድሜ ግን በእስር ቤት ውስጥ በደረሰብት ከፍተኛ ስቃይ መቋቋም ሳይችል ቀርቶ ከፊቴ ላይ ሞቷል:: ይፈፀምብን የነበረው ግፍ እጅግ ዘግናኝ ነው፤ ላላየው ሰው ቢነግሩት አይገባው ይሆናል:: የእስር ጊዜው አጭር ነው፤ ከመጋቢት እስከ ሰኔ ነበር የታሰርኩት:: ስቃዩ ግን የዓመታት ያህል ከባድ ነበር::
የታሰርነው በማስረጃ አይደለም፤ ወንድሜ በኢሕአፓነት ተጠረጠረ፤ እኔ ደግሞ “ከወንድሙ ጋር ነገር ይኖረዋል” ተብዬ ነው:: ይሁን እንጅ የምናውቀው ነገር አልነበረም፤ ግን የማናውቀውን “ሚስጥር አውጡ” እየተባልን ተሰቃዬን፤ ወንድሜ ስቃዩን አልቻለምና ሞተ፤ እኔ ተረፍኩ:: ለጥርጣሬው መነሻ እኔ በተደጋጋሚ የደርግ የፖለቲካ አባል እንድሆን ተጠይቄ አለመቀበሌ ነው፤ ከዚህ የተለዬ ምክንያት የለም ነበር::
እስራቱ የውጭ የትምህርት ዕድል እንደነጠቆትም የነገሩኝ ሰዎች አሉ፤ እስኪ ይንገሩን?
ትክክል ነው! በፈንጣጣ ማጥፊያ ፕሮግም ውስጥ አንዳቤት ወረዳ ወፍጫሜ ጊዮርጊስ እየሠራሁ ነበር ዕድሉን ያገኘሁት:: በወቅቱ በፈንጣጣ የታመሙ ሰዎች እዚያ አካባቢ እንዳሉ ጥቆማ ይደርሳል፤ ጥቆማ ለሚሰጥ በወቅቱ ለአንድ በሺተኛ ጥቆማ 30 ብር ሽልማት ይሰጥ ነበር:: ባለሙያዎች በሄሊኮፕተር ሲሄዱ ግን ታማሚዎቹን አያገኟቸውም:: ይኼኔ አለቃዬ የነበረው ፈረንጅ ጉዳዩን ነገረኝ:: በሄሊኮፕተር ሳይሆን በእግር መሄድ እንዳለብን ነገርኩት::
አለቃዬ በሀሳቡ ተስማማና ሄድን፤ ለአካባቢው ትልልቅ ሰዎችም ከጤና ጥበቃ እንደተላክን አስተዋዎቅንና የፈንጣጣውን ጉዳይ ትተን ስለጤና ትምህርት መስጠት ጀመርን:: የዓይን ሕመም መድኃኒቶች በብዛት ይዘን ስለነበረ ጠብታ በነፃ ለታማሚዎች መስጠት ጀመርን፤ ፈውስም አገኙ፤ ጎን ለጎን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ጀመርኩ::
በዚህ ጊዜ የአካባቢው ሕብረተሰብ እምነት ጣለብኝና በደንብ ይቀርበኝ ጀመር:: ቀስ በቀስ ስለፈንጣጣ ታማሚዎች ስጠይቃቸው ጥቆማ በትክክል ይሰጡኝ ጀመር፤ በዚህ አግባብ ስድስት ሰዎችን አገኘሁ::
እነዚህን ሰዎች ከዚያ ቀደም በሄሊኮፕተር አሰሳ ሲመጣ ጎታ ውስጥ ይደብቋቸው እንደነበረ ጭምር ነገሩኝ:: በዚህ ሥራዬ በሽልማት መልኩ የውጭ ሀገር የትምህርት ዕድል ተሰጠኝ፤ ግን ወዲያውኑ ታሰርኩና ሳይሳካ ቀረ::
ለጡረታ በተቃረቡበት ዘመን የመጀመሪያ ዲግሪ ተምረዋል፤ አልመሸም?
እኔ የምማረው ለማዎቅ እንጅ ደመወዝ ለማሳደግ አይደለም፤ ስለዚህ ደመወዝ ለማግኜት እንጅ ለማዎቅ አልመሸም::
የመጀመሪያ ዲግሪያን በ2003 ዓ.ም በማኅበረሰብ ጥናት (ሶሾሎጂ) አጠናቀቅሁ:: በዚያ ዕድሜዬ ስማር የተመለከተ አንድ የውጭ ዜጋ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የመከታተል ፍላጎት እንዳለኝ ጠየቀኝ፤ እኔም ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ መማር እንደምፈልግና ለጊዜው በቂ ገንዘብ እንደሌለኝ ነገርኩት:: ከዚያ “የሁለተኛ ዲግሪህን የመማር ፍላጎትማ ካለህ ወጭውን እኔ እሸፍናለሁ!” ብሎ ቃል ገባልኝ::
ወዲያው አስተማሪዎቼ “ና የመግቢያ ፈተና ተፈተን! ክፍያውን ለመሸፈን ቃል ገብቶልሀል” አሉኝና ሄጄ ተፈተንኩ፤ አለፍኩ:: ከዚያ ያ የውጭ ዜጋ ለሁለት ወሰነ ትምህርት ከፍሎልኝ “አቅም አጠረኝ” አለ:: የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ያለፈ የአገልግሎት ዘመኔንና የትምህርት ፍላጎቴን ተመልክቶ ቀሪውን ከክፍያ ነፃ እንድማር ፈቀደልኝ፤ አሁን ትምህርቱን ጨርሼ የመመረቂያ ጽሑፍ እየሠራሁ ነው::
በቅርቡ እንደምመረቅ ተስፋ አደርጋለሁ:: ጥናት እየሠራሁ ያለሁት “ማኅበረሰቡ በጤና ትምህርቶች ላይ ያለውን ዕውቀት፣ ግንዛቤና ተግባር” በተመለከተ ነው::
እንዳልኩህ የምማረው ለደመወዝ ማሳደግ ሳይሆን ለማወቅ ነው፤ ለደመወዝ ማሳደግ ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በጡረታ መውጫዬ ጫፍም ቢሆን በጤና ዘርፍ አደርገው ነበር፤ ግን አይደለም::
የተማርኩት የትምህርት መስክ ካገለገልኩበት ሙያ ጋር ተያያዥ ስላልሆነ የደመወዝ ጭማሪ እንደማያመጣ እያወኩ ነው የተማርኩት፤ የሁለተኛ ዲግሪየን ደግሞ እየተማርኩ ያለሁት ከጡረታ በኋላ ለዕውቀት ነው::
ለእርስዎ መማር ማለት ምንድን ነው?
መማር ለእኔ ማወቅ፣ ያንንም መተግበር ነው:: መማርህን የያዝከው ወረቀት ሳይሆን ያለህ ዕውቀት መመስከር አለበት:: ድሮ ሰዎች የሚማሩት በሆነ ዘርፍ ሊቅ ለመሆን ነበር፤ የተማሩትም ሲጠየቁ በኩራት ከቻሉ ይመልሳሉ፤ ካልቻሉ ደግሞ “በዚህ ጉዳይ ላይ ከእኔ እገሌ ይሻላል!” ብለው ይጠቁማሉ::
በዚህ ጊዜ ሌሎች ስለሌሎች ዕውቀት ምስክርነት እየሰጡ ነው፤ አሁን ግን ወረቀት ያለው ብዙ ነው፤ ለዕውቀት ማጣቀሻነት የምትጠራው ግን በጣም ትንሽ ነው:: ለእኔ መማር ማለት እንደድሮዎቹ በወረቀት ሳይሆን በሰው የተመሰከረለት የዕውቀት ምንጭ መሆን ነው:: ‘እገሌ በዚህ ሊቅ ነው’ ለመባል መማር ይገባል::
በነገራችን ላይ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ስር ለ40 ዓመታት አገልግዬ ጡረታ የወጣሁት እኮ ሌላ መስሪያ ቤት ስላላገኘሁ አይደለም:: በየቀኑ በዕውቀት ላይ ዕውቀት እየጨመርኩ በሙያዬ የተሻለ ሠራተኛ መሆን ስለምፈልግም ጭምር ነው:: በተማርኩበት ዘርፍ ለረዥም ዓመት ሳገለግል በዚያው ልክ ሰፊ ዕውቀት አካብቸበታለሁ፤ ስለሆነም በሙያዬ ዙሪያ ለሚነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የመስጠት አቅም ገንብቻለሁ:: ሰው በተማረው ልክ መሥራት አለበት፤ እኔ ዲፕሎማዬን ከዲፕሎማ በላይ ሠርቸበታለሁ::
ከጡረታ በኋላ ምን እየሠሩ ነው?
በአሁኑ ወቅት ልምድ ያለው ሰው ብዙም አይፈለግም፤ ድሮ ልምድ ያለው ሰው ገና ጡረታ ሊወጣ ሲል ነበር የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የሚፈልጉት፤ አሁን ያ ሁኔታ የለም:: እኔም ወጥቼና ወርጄ ለመሥራት አልችልም:: ግን ዝም ብዬ አልተቀመጥኩም፤ ማኅበራዊ አገልግሎት እሰጣለሁ:: በምኖርበት ቀበሌ የአረጋውያን የስልጠናና የፕሮጀክት ቀረጻ አስተባባሪ ነኝ፤ የአካባቢ ጽዳት እንዲጠበቅም ሕዝቡን አስተባብራለሁ::
ሰዎች በአካባቢው ሲጋጩም የግልግል ዳኝነት ሥራ አሠራለሁ፤ በዚህም እቀጥላለሁ:: በማኅበረሰብ ዙሪያ የማጠናውም ለዚያ ነው::
ከዲቁና ወደ ቅስና ማዕረግ የተሸጋገሩት ከ40 ዓመታት በኋላ ነው፤ ለምን?
ልክ ነው፤ በጣም ቆይቻለሁ:: ክህነትን ለመቀበል ሙሉ በሙሉ አገልጋይ መሆን ይጠይቃል፤ እኔ በመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ላይ ስለነበርኩ ሙሉ ጊዜዬን ለቤተ ክርስቲያን መስጠት ይቸግረኛል:: ለሥራ ወደ መስክ እወጣለሁ፤ በክብረ በዓላት ወቅት ለመንግሥታዊ ተልዕኮ እሄዳለሁ:: በዚህ ምክንያት ለ40 ዓመታት ክህነት ሳልቀበል ቆይቻለሁ::
አሁን ጡረታ ስወጣ ግን ሙሉ ጊዜዬን ለፈጣሪ መስጠት ስለምችል ክህነቱን ተቀብያለሁ፤ በነገራችን ላይ ይህንን ጥያቄ ክህነት የሰጡኝ ጳጳስም ጠይቀውኛል:: ክህነቱን ከተቀበልኩ አሁን ታኅሣስ ዓመት አለፈኝ:: ቀሪ ዘመኔን ለማገልገልም በደብረ መንክራት ቅዱስ ቂርቆስ ማገልገል ጀምሬያለሁ::
የረዥም ጊዜ የሥራና የሕይወት ልምድዎትን ስላካፈሉን አመሰግናለሁ!
እኔም አመሰግናለሁ!
በኩር ጋዜጣ (አብርሃም በዕውቀት) ጥር 08 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም
ለህብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!!
የአማራ ብዙሃን መገናኛ ድርጅት
አማራ ቴሌቪዥን ፣በአማራ ራዲዮ እና በኤፍኤም ባህር ዳር 96.9 ዜናዎች እና ዝግጅቶች ዙሪያ ለሚኖርዎት ጥቆማና አስተያየት ለአማራ ቴሌቪዥን(ATV)፣ ለአማራ ራዲዮ(AR)፣ ለኤፍኤም ባህር ዳር 96.9 (FM) እና ለበኩር (AB) በማስቀደም በ8200 ማድረስ ይችላሉ፡፡
ክቡራን
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 7963
Joined: Tue Mar 04, 2008 4:24 pm

Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: Bing [Bot] and 6 guests