ምስጋና ለመብት ተሟጋቾችThanks to Ethiopian Advocates

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

ምስጋና ለመብት ተሟጋቾችThanks to Ethiopian Advocates

Postby እሰፋ ማሩ » Sat Sep 30, 2017 7:57 pm

September 30, 2017 – ቆንጅት ስጦታው
ለእስካሁን ድካማቹ ምስጋና ይገባችኋል !!
“ውጤቱ እንደሚጠበቀው ባይሆን እንኳንህ፤የእስካሁን የአብሮነት ጉዞ እና ጽናት ለነገ ሥራ ብርታት እና ተምሳሌት ስለሚሆን ይሄም ሌላኛው ድል ነው !”
አዎ ! እንዲህም መልካም የሆነውን ነገር ሳይታክቱ ለሃገራቸው እና ለወገኖቻቸው የሚሰሩ ምስጎን ሰዎች አሉ ፡፡ በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በውጪ ሃገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉት በጎ አሰተዋአዖኦ ቀላል የሚባል አይደለም ። በእስከ-ዛሬው ተሳትፎአቸው እጅግ አኩሪ ተግባራትን ፈጽመዋል። ለዚህም ምስጉን ሥራቸው በአግባብ ሊመሰገኑ ይገባል !! በመልካም ሥራቸው ሊመሰገኑ እና አክብሮት ሊሰጣቸው የሚገባቸው ጥሩ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ ። ካሉበት ምቹ ቦታ ሆነው በነፃ ኢንተርኔት የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀዳሽ እና አንጋሽ ፤እኔ እና እኔ ብቻ ነኝ በማለት እራሳቸውን የጀግና ጀግና አድርገው ፤ በሃገር ውስጥ የአገዛዙ ሥርዓት አፍንጫ ሥር ሆነው የተቻላቸውን አሰተዋአዖኦ ለማድረግ የሚጥሩ ግለሰቦች እና ተቋማትን ፤ በማብጠልጠል እና በመዝለፍ በነውራቸው ከመዘባበት ውጪ አንዳም ነገር ያልሰሩ በውጪ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው ጭምር የአደባባይ ምስጢር መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።

አሁን ግን ለሃገር እና ለወገን ግድ የሚሰጠን ኢትዮጵያዊያን ሁሉ፤ በአንድነት ልናመሰግናቸው እና በሰሩት መልካም ሥራ ልናከብራቸው የሚገባን ምርጥ ወገኖቻችን አሉን !! እርግጥ ነው የሰሩት መልካም ሥራ የዜግነት ግዴታቸው ቢሆንም፤ ግዴታቸውን በአግባቡ በመፈጸማቸው ፣ከምንም በላይ ለአመታት በጽናት ቆመው የያዙት ዓላማ እንዲሳካ ያደረጉት ጥረት እጅግ በጣም ከባድ እና ፈተኛ እንደነበረ በቀላሉ መገመት የሚቻል ነው፡፡ ለዚህም አኩሪ ተግባራቸው እጅ ነስተን፤ ልፋታቸው ተሳክቶ እንኳን ደሰ አለን/አላችሁ ለመባባል ከጫፍ ተደርሷል ። ምን አልባት ፣ እንደው-በምን አልባት ውጤቱ እንደሚጠበቀው ባይሆን እንኳን ፤ የእስካሁን የአብሮነት ጉዞ እና ጽናት ለነገው ብርታት እና ተምሳሌት ስለሚሆን ይሄም ሌላኛው ድል እንደሆነ አድርጎ መቀበል የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ ነገር እንዳልሆነ ታሳቢ ቢደረግ መልክም ነው ፡፡ በሂደቱ በየትኛውም መንገድ የሚመጣው ውጤት የተሻለውን በጣም ጥሩ ነገር አበላልጦ መምረጥ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ድል ነው።

በ1997 ዓ.ም የተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ እና እሱን ተከትሎ ፣ በሥልጣን ላይ የሚገኘው “መንግሥት” በዜጎች ላይ የወሰደውን የሃይል እርምጃ እና በዚህም ምክንያት የደረሰው የዜጎች ሕይወት መጥፋት እና አካል ጉዳት ፣ እንዲሁም የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎችን የመንግሥት ባለሥልጣናትን ተጠያቂ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ መዘጋጀቱ የሚታወቅ ነው። ይህ ረቂቅ ሕግ ሲዘጋጅ በውጪ ሃገር የሚገኙ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን የነበራቸው አሰተዋአዖኦ እጅግ በጣም ከፍ ያለ ነው ! እንዲሁም በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለውን የሰብዓዊ እና የዴሞክራሲ መብቶች ጥሰት ያሳሰባቸው የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መመሪያ ሁለቱ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባላት እያደረጉት ያለው እገዛ የሚደነቅ እና የሚበረታታ ነው።

ስለኢትዮጵያ የሰበዓዊ እና የዴሞክራሲ መብት አያያዝ የሚመለከተው SEN.RES168 እና H.RES128 ረቂቅ ሕግ በሁለቱም ምክርቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ድጋፍ ማግኘቱ የሚታወስ ነው፡፡ ረቂቅ ሕጉ የመነሻ ሃሳቡ በ1997 ዓ.ም የተፈጸመው አስከፊ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት ቢሆንም፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በስልጣና ላይ የሚገኘው “መንግሥት” በተከታታይ በዜጎች ላይ የሚፈጽመው መንግሥታዊ በደል የረቂቅ ሕጉ አስፈላጊነት ከጊዜ ወደ-ጊዜ እየጎለበተ ለመምጣቱ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀስ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ለረዥም አመታት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግበት የነበረው ረቂቅ ሕግ በሁለቱም ምክርቤት የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ አልፏል፡፡ የረቂቅ ሕጉ ከመነሻው ጀምሮ በሥልጣና ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ “መንግሥት” ከፍተኛ የሎቢ ድርጅቶችን በመቅጠር ረቂቅ ሕጉ ውድቅ እንዲሆን ከፍተኛ ጥረት ማድረጉ በተለያየ መንገድ መገለጹ የሚታወቅ ነው፡፡

ይሁን እንጂ ሃገር ወዳድ በሆኑ ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ከፍተኛ ጥረት “የመንግሥት” ፍላጎት ሣይሳካ ቀርቶ ፤ በአሜሪካ መንግስት ሁለቱ ምክርቤቶች የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በሙሉ ድምጽ ረቂቅ ሕጉ ድጋፍ ሊያገኝ ችሏል፡፡ለዚህም ነው የወደፊቱ ድል እንደጠጠበቀ ሆኖ ይሄም በራሱ ሌላ ድል ነው የሚያስብለው፡፡ የሕጉ ረቂቅ በሁለቱ ምክር ቤቶች የውጪ ጉዳይ ኮሚቴ ድጋፍ አግኝቶ ለመጨረሻ ውሳኔ ለቀጣዩ ድምፅ ወደ ሙሉው ምክርቤት ተልኳል። የአሜሪካ ምክርቤት የኢትዮጵያን ጉዳይ የሚመለከተውን H.Res 128 ሕግ በምክርቤቱ ቀርቦ ድምፅ ለማሰጠት October 2, 2017 በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር መስከረም 22 ቀን 2010 ዓ.ም ቀን ተቆርጧል፡፡ይህ ሕግ በንኡስ ክፍሎች ሁለት ጊዜ ቀርቦ በሙሉ ድምፅ የውሳኔ ሃሳቡ ማለፉ ተከትሎ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበባሰ የመጣው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንዲሁም በሃገር ውስጥ የሚታየው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ረቂቅ ሕጉ የመጽደቅ እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ ከወዲሁ ተገምቷል፡፡

ይህ ረቂቅ ሕግ H.Res 128 (Human Rights and Encouraging Inclusive Governance in Ethiopia) በመባል የሚታወቀዉና በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት እንዲከበር የሚጠይቀው ሕግ ሲጸድቅ ጠቀሜታው ከፍ ያለ ሲሆን፤ በተለይ የመንግሥት ባለስላጣናት በዜጎች ላይ ለፈጸሙት በደል ተጠያቂ የሚያድርግ ሕግ ሲሆን፤የውሳኔ ሃሳቡ ካለፈ ለመጀመሪያ ጊዜ አሜሪካ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን የሰበአዊ መብት ጥሰት በማውገዝ ተጨባጭ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚያስችላት ይገመታል፤ይህ ረቂቅ ሕግ በላይኛው ምክር ቤት በሴኔት ከፀደቀ በኋላ ወደ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለፊርማ ይቀርባል።የመንግሥት ባለሥልጣናት ቀጥተኛ ተጠያቂ የሚያደርገው ይህ ረቂቅ ሕግ ጸድቆ በሥራ ላይ ከዋለ ከአሜሪካ ባሻገር በአውሮፓ እና በሌሎች ሃገሮች መስል የሕግ ማዕቅፎቹ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያደርገው እገዛ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ በጉዳዮ ዙሪያ የሚወጡ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጥረው ዲፕሎማሲ ተጽእኖ እጅግ በጣም ከፍተኛ እንደሆነ ጭምር እየተነገረ ነው፡፡ በዚህ ደረጃ አለም አቀፍ አንድምታ ያለውን ከባድ ሥራ ለሰሩ እና እዚህ ደረጃ እንዲደርስ ላደረጉ፤ ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን እና ተቋማት በድጋሚ አክብሮት እና ምስጋና ይገባቸዋል።በቀጣይ ደግሞ ፈጣሪ ቸር ወሬ ያሰማን ! ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር !!
እሰፋ ማሩ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1504
Joined: Mon Sep 12, 2016 8:47 pm

Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: Bing [Bot] and 5 guests