ግፈኛ በሚደግፉ የሃይማኖት መሪዎች ሃገር አልወለድም

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

ግፈኛ በሚደግፉ የሃይማኖት መሪዎች ሃገር አልወለድም

Postby እሰፋ ማሩ » Mon Feb 05, 2018 2:06 pm

ጠገናው ጎሹ-ሳተናው ፌብርዋሪ 4/2018
እኔ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ፣ያደግሁትና ፊደል የቆጠርኩት ከሃይማኖቱ መሪዎች ፣ ቄሶች ፣ ሰባኪ ወንጌላዊያን እና ሌሎች አገልጋዮች ጋር በተያያዘ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ አስተያየት ወይም ትችት መሰንዘር እንደ ነውርና ከዚያም አልፎ እንደኅጢአተኝነት በሚቆጠርበት ማህበረሰብ ውስጥ በመሆኑ በዚህ ጽሁፌ ምቾት አለመሰማት ብቻ ሳይሆን ውጉዝ ከመአርዮስ ብለው ለማውገዝ የሚቃጣቸው ወገኖቼ ቢኖሩ የማይጠበቅ ወይም ያልተለመደ ነው የሚል የድንቁርና አስተሳሰብ ጨርሶ የለኝም ።
የሚከተለውን ግን ከወዲሁ ግልፅ ላድርግ ። የፅሁፌ መነሻና መድረሻ ለሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ ተቋሞቻችን በበላይ ኀላፊነት (በአመራርነት) ቦታ ላይ የሚቀመጡ ወገኖች የአስተሳሰብ ፣ የአመራር፣ የሥልጣንና የተግባር ደካማነት ከሚመሩት ተቋም አልፎ አገርና ህዝብ ወደ ተሻለ ወይም ወደ ላቀ ሁለንተናዊ ነፃነት ፣ እኩልነትና ብልፅግና በሚያደርጉት ጥረት(ትግል) ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅእኖ ምን ያህል እንደሚጎዳ ከእኛው ከራሳችን የበለጠ ማስረጃ የለምና ቆም ብለንና ትንፋሽ ዋጥ አድርገን በማስተዋል ወደ እምንፈልገው ግብ የሚያደርሰን አቅጣጫ፣ ተልእኮና ሥራ ላይ እንረባረብ ለማለት እንጅ በሃይማኖታቻችን (ክርስትንና እና እስልምናን በዋናነት ለማለት ነው) መሠረታዊ የእምነት እሴቶች ፣ መርሆዎች ፣ የተፃፉም ሆነ ያልተፃፉ ሥርአቶች እና እንዲሁም ትውፊቶች ላይ ጥያቄ ለማንሳት አይደለም ።በቅርበት ስለማውቀው የክርስትና ሃይማኖት መናገር ስለአለብኝ ነው እንጅ በእስልምናም ሆነ በሌሎች የክርስትና ሃይማኖት ተከታይ ተቋማትም ይኸ መሪዎችንና ሌሎች አገልጋዮችን አስመልክቶ አስተያየትና ትቸት የመሰንዘሩ ጉዳይ ብዙም የተሻለ አይመስለኝም ።

እንኳን እጅግ በቀላሉ ስሜትን ዘልቀው የሚገቡ ሃይማኖታዊ (መንፈሳዊ) ጉዳዮች ይቅርና በአንፃራዊ መልኩ ስሜታችን በምክንያታዊነት (በተጠየቅ/ቂ ልጠይቅህ/ሽ) እየተቆጣጠርን የምንወያይባቸውና የምንከራከርባቸው ዓለማዊ ( ፖለቲካዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ ፣ ባህላዊ) አስተሳሰቦቻችንና አመለካቶቻችንን አቅርበንና በአግባቡ ተወያይተን ለሩብ ምዕተ ዓመት የመከራና የውርደት ማቅ ያከናነቡንን ዘረኛ ገዥ ቡድኖችን በማስወገድ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ የሰብአዊ መብትና ክብር ፣ ሰላም ፣ ፍቅር እና የጋራ ብልፅግና በሰፈነባት አገር ለመኖር እስከአሁን አልቻልንም ። አሁን የምናየውና የህይወት መስዋዕትነት እየተከፈለበት ያለው የብሩህ ተስፉ ህዝባዊ እምቢተኝነት እንዳለ ሆኖ ።

በተለይ እንደኛ ባለ መሠረታዊ የዜግነትና የሰብአዊ መብት ጥያቄ ጨርሶ ተከብሮ በማያውቅበት አገር የአመለካከትና የአስተሳብ ልዕልና ለማምጣት ሁለገብ አርበኝነትን (all round patriotisim) የሚጠይቅ የመሆኑ ጉዳይ የሚያስማማን ይመስለኛል ። ሁለገብ ስል ዓለማዊ (secular) እና ሃይማኖታዊ (spiritual ) ተልኳችን አገርና ወገን በዘረኛና ጨቃኝ የገዥ ቡድኖች ተገደው ከገቡበት የመከራና የውርደት ህይወት የማውጣት አርበኝነት ማለቴ ነው።

“አይ ሃይማኖታዊ ተልኮ፣ ኅላፊነትና ተግባር ቤተ እምነት ወይም ቤተ መቅደስ ውስጥ ሆኖ እግዚኦ መሃረነ! ከማለትና በሰላ አንደበት ወንጌል ከመስበክ ማለፍ የለበትም” የሚል በተለይ ፊደል የቆጠረ የሃይማኖቱ ተከታይና ጥሩ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚል ካለ ስለክርስቶስና ክርስትና ማነብነቡን እና የሰንበትና የበዓላት ቀን መቁጠሪያ ላይ ምልክት እያደረገ ወደ ቤተ እምነት መመላለሱን እንጅ ከዚያ አልፎ የሚሄድና አገርንና ወገንን እስከመስዋትነት በሚያደርስ ተጋድሎ የመታደግ ተልኮ እንዳለው ጨርሶ አስቦ እማያውቅ መሆን አለበት ። ይህ ሂሳዊ አስተያየቴ ምናልባትም ለአንዳንድ ወገኖቼ ለመቀበል ቀርቶ ለመስማት ወይም ለማንበብም ሊያስቸግራቸው እንደሚችሉ እረዳለሁ ። ደግሜና ደጋግሜ ልበለውና የሚበጀን ከራሳችን ጋር በአርበኝነት ታግለንና ወደ ትክክለኛው መንገድ ገብተን ለዓለማዊውም ሆነ ለመንፈሳዊ ህይወታችን የተቃና የሚያደርገውን የአብሮነት ጉዞን መያያዙ ነው የሚጠቅመን እንጅ እግዚአብሔር የማይጠላውን ሁሉ ኀጢአትና ነውር እያደረግን የትም አንደርስም ።

እናም በአሁኑ ጊዜ የሃይማኖት ተቋማት የበላይ መሪዎችና በየደረጃውና በየሙያቸው ኅላፊነት ላይ ያሉ አባላት እንደተቋምም ይሁን እንደየግላቸው ህሊና ተልኳቸውን በአግባቡ ለመወጣት ያለመቻላቸውን ጉዳይ እንደ ማያሳስብና እንደተለመደ ባህሪና አሰራር ተቀብለን በዚያው መንገድ የመንጎዳችን ችግር የሚጎዳው ዓለማዊውንም ሃይማኖታዊንም (መንፈሳዊንም) ህይወታችን ነው። የሁለቱም ስኬት ወይም ውድቀት የሚለካው በዚሁ በምድር ላይ እያለን በምንሠራው የሥራ መጠንና ጥራት ነውና ። ክርስቶስ ያስተማረለት፣ በቁም ስቃይ የተቀበለለት ፣ በመስቀል ላይ የዋለለትና ሞትን አሸንፎ የተነሳለት ምስጢር የሚገለፀው ለነፃነት ፣ ለፍትህ ፣ ለሰብአዊ መብትና ክብር ፣ ለደግነት ፣ ለፍቅር ፣ ለሰላም ፣ ተካፍሎና ተሳስቦ ለመኖር በሚደረግ እራስን አሳልፎ የመስጠት መስዋዕትነት ካልሆነ ሌላ በምን ይሆናል ? “እመኑ ትድናላችሁ” ማለትስ እሱ ሆኖና አድርጎ ያሳየንን እንደሱ እንኳ ባይሆን በሰውነታችን (በፍጡርነታችን) መጠን ሆነንና አድርገን እንድንገኝ እንጅ ዘወትር “አምናለሁ ! አምናለሁ ! አምናለሁ !” የሚል ቃለ መሃላ እያነበነብን መዳንን ወይም ጽድቅን እንድንናፍቅ አለመሆኑን ለመረዳት የቲዎሎጅ መፃህፍትን ማገላበጥ የግድ የሚል አይመስለኝም ።

ይህ ሁኔታችን የሚነግረን ነገር ቢኖር በዚህ የህይወታችን ዘርፍ (በመንፈሳዊው) እየገጠመን ያለው ፈተና ቀላል አለመሆኑን ነው። ይህ መንፈሳዊ የህይወታችን ዘርፍ ደግሞ ከሌሎች የባለ ብዙ ዘርፍ የእኛነታችን እሴቶች ጋር በአወንታዊም ሆነ በአሉታዊ ተፅእኖው በእጅጉ የተቆራኘ በመሆኑ “የሃይማኖት መሪዎችና የሌሎችም ቀጥተኛ አገልጋዮች ጉዳይ ነው” በሚል በጭራሽ ልንሸሸው የሚገባን ጉዳይ አይደለም ።እግዚአብሔርም ይህን የሁላችንም የሆነውን ጉዳያችን ኅላፊነት ወስደን ተገቢውን የማስተካከያ (የእርምት) እርምጃ መውሰድ ሲሳነን ወይም ሳንፈልግ ስንቀር ወደ ሌሎች የመግፋቱንና ከደሙ ንፁህ ነኝ የማለቱን አባዜ ከቶ የሚቀበለው ነገር አይመስለኝም ።

አዎ ! ክርስቶስ በቁሙ ስቃይና መከራ ከተቀበለም በኋላ በመስቀል ላይ ተቸንክሮ የመጨረሻዋን የሞት ፅዋ የተቀበለው ለምድርም ሆነ ለሰማዩ ህይወታችን ይበጃል ያለው የዕውነት ፣ የሰብአዊ መብትና ክብር ፣ የፍትህ ፣ የሰላም እና የፍቅር ኅያልነት እውን ይሆን ዘንድ እንጅ ኩነቱን እያስታወስን እና ስቅለትህንና ትንሳኤህን እናምናለን እያልን ድርጊት አልባ የዘወትር ጸሎትና እግዚኦታ መሪዎችና ተመሪዎች እንድንሆን አልነበረም ። አይደለምም ።

ሌት ተቀን ታላቁን መፅሃፍ እየሰበኩ በተግባር ግን አንድም ለይቶላቸው ከጨካኝ የገዥ ቡድኖች ጋር ቆመው የአገርንና የወገንን መከራና ውርደት የሚያራዝሙ (የአዲስ አበባውን “ቅዱስ የጳጳሳት ጉባኤ/ሲኖድ” እና በውጭ ያሉና ያንኑ “የቅዱስ አባታቸውን” መመሪያና ተልኮ እሚያስፈፅሙ) ፣ ወይም የአርበኝነት አንደበታቸው በአድርባይነት የተዘጋ (በሁለቱም ሲኖዶሶች ውስጥ ወይም ሥር የሚገኙ)፣ ወይም በመካከላቸው (በውስጣቸው) እየተናቆሩ ከምስኪንና የዋህ ምዕመናን የሰበሰቧትን ሳንቲምና ከነሱ የተሟላ (የአንዳንዶችም ከመሟላት በላይ ሳይሆን አይቀርም ) ሥጋዊ አኗኗር የተረፈችውን የፍርድ ቤት እሰጥ አገባ ማስፈፀፈሚያ የሚያውሉ የሃይማኖት አባቶችና በየደረጃው የተሰየሙ ኀላፊዎች (ይህ ችግር በስደት ላይ ባለው ሲኖዶስ ሥር ባሉ ይብሳል) ጉዳይ አሳስቦን እንዴትና ለምን ብለን ካልጠየቅን ክርስቶሳዊያነታችን የስም እንጅ የዕወነት አይሆንም። ለምንና እንዴት ብለን የምንጠይቀው የግለሰቦችን የግል ባህሪና ህይወት አይደለም ። ሊሆንም አይገባም ። የሚያሳስበንና እንድንጠይቅ የሚያስገድደን ሃይማኖታዊ ፣ ሞራልዊና ስነምግባራዊ ሰብእናችን በፖለቲካ ቀጥታ ከመሳተፍ ወይም ጣልቃ ከመግባት ባሻገር ባሉ አገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮቻችን ዙሪያ በንቃትና በብቃት የመሳተፋችን ጉዳይ ጎልቶ ያለመታየቱ ብቻ ሳይሆን ይባስ ብሎ የግፈኛ ገዥ ቡድኖች ሰለባ የመሆናችን ነገር ነው ።

አዎ! መስሎና አስመስሎ የመኖር ክፉ ልማድ እስረኝነታችን እና የሞራልና የተግባር አርበኝነት ድህነታችን ከምር አምነንና ከራሳችን ጋር ታግለን አውቀንም ሆነ በስህተት እየነጎድን ካለንበት ጨርሶ የመውደቅ ጉዞ ተመልሰን ለምድሩም ሆነ ለሰማዩ ህይወታችን ወደ እሚበጀን ፍኖተ ጉዞ የመግባቱ ጉዳይ ከቶ ለነገ የምንለው ጉዳይ አይደለምና ዛሬም አልፎ ትናንት እና ከትናንት በፊት ሳይሆን አሁንኑ እንፍጠን ። “የመዳን ቀን ዛሬ ነው” ማለት ከዚህ የተለየ ስውር ወይም ረቂቅ ምሥጢር ያለው አይመስለኝም ። ይህ ኅይለ ቃል የተነገረው “ስለሰማያዊ ቤታችን ስለሆነ ከመድራዊ እኛነታችን ጋር ግኑኝነት የለውም” ብለው ሊያርሙኝ የሚፈልጉ ወገኖቼ ሊኖሩ እንደሚችሉ እገምታለሁ ። መልሴ ግን የሰማያዊው ድነት ( ጽድቅ ) ዋስትናው እዚችው ምድር ላይ በህይወት እያለን በተለይ ለአገርና ለወገን በነፃነት ፣ በፍትህ ፣ በክብር ፣ በሰላም ፣ በፍቅርና በጋራ ብልፅግና መኖር የምንከፍለው ዋጋ በመሆኑ ይህን አድርገን ሳንገኝ ስለሰማያዊው ቤታችን ማሰብ ከምኞት የሚያልፍ ነገር አይደለም :: ወይም ደንቁሮ ማደንቆር ነው ። ለመቀበል ቢቸግረንም ዕውነቱ ዩኸው ነው ።

አሁን አሁን አገርና ወገን እንዲሁም ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን የሚገኙበት እጅግ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን አደገኛ ሁኔታን ተገንዝበን የአርበኝነት (አርበኝነት ባለብዙ ዘርፍ የእውነተኛ ሰብእና መገለጫ መሆኑን ልብ ይሏል) እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኝነቱና ደፋርነቱ ከሌለን የተሟላ አካላዊና አእምሯዊ ብቃት ሰጥቶ “ሥሩበትና እረዳችኋለሁ” ብሎ በፈጠረን እግዚአብሔር ስም የራስን ምድራዊ ኑሮ እና የሥልጣንና ማህበራዊ ዝናን በማፍቀር ልክፍት ተለክፈናልና ተስፋ ሳንቆርጥ ወይም የባሰ እልህ አመጣሽ ስህተት ውስጥ ሳንወድቅ የመመለሱ ጉዳይ ለነገ ወይም ለቀጣዩ ትውልድ የምንተወው ሊሆን አይገባም ። የነገው ትውልድ የራሱን እጣ ፈንታ የሚመራበትና የሚወስንበት የራሱ ኅላፊነትና የቤት ሥራ ይኖረዋልና ።

ይህን መሪር እውነት ለመቀበል የአርበኝነት ወኔውን (patriotic courage) ባጣን ቁጥር አገርንና ወገንን ከመከራና ከውርደት ከመታደግ ጋር በእጅጉ የተሳሰረውንና ከፈጣሪ የተቀበልነውን እውነተኛውን ተልኮና ሥልጣን በከንቱ እንዳባከነው ልብ እንበል ።

እስኪ የሚከተለውን እጅግ ፈታኝ ሂሳዊ እይታ (critical way of thinking) ቅንነትንና ደፋርነትን በተላበሰ አእምሮና ልቦና አብረን እናንበበውና በዕውነት ስለዕውነት ዛሬ እራሳችን የትና በምንስ ሁኔታ ላይ እንደምናገኘው እንጠይቅ።

የአቤ ጎበኛው አልወለድም እንዲህ ይሞግተናል፥

“ስለኋለኛው ህይወትም በእርግጥ ነፍሴ በእግዚአብሔር ፊት የምትቀርብ ከሆነች በተስፋ እንጅ በፍርሃት አልሄድም ። እግዚአብሔር እውነትንና ቅንነትን የሚወድ አምላክ እንጅ የግል ክብሩንና ጥቅሙን ለመጠበቅ የሚቆርጥና የሚፈልጥ ዲክቴተር እንዳልሆነ ይሰማኛል ። …. ። ሃይማኖት ያለኝ ሰው መሆኔን ከገለፅሁ አይቀር የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ መሆኔን ልግለፀው ። ኢየሱስ የሰው ልጅም ቢሆን የእግዚአብሔር ልጅ በሁለቱም በኩል ቸር መሪ ነው። የሰው ልጅ በመሆኑ ለሰዎች ፍቅርን ፣ርህራሄን ፣ ቸርነትንና ርዳታን በሥራ በማስተማር ገልጿል። የአምላክ ልጅ በመሆኑም ከፍተኛውና መልካሙ ትምህርቱ በጥቂት ሰዎች አስተማሪነት ለዓለም ህዝብ ሁሉ እንዲዳረስ አድርጓል። የእኔም ክርስቲያንነት በአንድ ወላዋይ ቄስ እጅ በውሃ ተጠምቄ ክርስቶስ የሚጠላውን ሃሰትና ማጭበርበር እየሰራሁ ክርስቲያን ነኝ በማለት ሳይሆን እንደርሱ ቅን ትምህርትንሳስተምር በግፈኞች እጅ ደሜ ፈሶ በደሜ ተጠምቄ የክርስቲያንነትን ፀጋ በመቀበልና የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል ነው።” አቤ ጎበኛ ፡ አልወለድም , ሐምሌ 1966 ዓ፡ም ::
በተለይ የሙግቱ (የንግግሩ) የመጨራሻው አረፍተ ነገር የተሸከመውን መልክት እያነበብኩ ሳለሁ ዛሬም የአቤ ጎበኛው አልወለድም ከኖረበት ብዙ ዓመታት በኋላ በአገሬ እየሆነ ካለው ሁለንተናዊ ቀውስ ጋር አስተያየሁት ። ስሜቴን በእጅጉ በሚፈታተን ሁኔታ በቃላት መግለፅ የሚያስቸግር የተደበላለቀ ስሜት ወደ ውስጤ ዘልቆ ተሰማኝ ።
የአገሬ ወጣቶችና ሌሎችም ንፁሃን ዜጎች በሚያጅቧቸው ታቦታት ፊት መግለፅ የሚያስቸግር ጭካኔ ባላቸው የዘረኛ አምባገነን ገዥ ቡድን ወታደሮች ጥይት ተመተው ሲወድቁና ደማቸው ጎዳናውን ሲያቀልመው እራሳቸውን ቀና ፣ የሰላም አመልካች እጣቶቻቸውን ከፍ አድርገው የተናገሩት የአርበኝነት ኅይለ ቃል ሆኖ ተሰማኝ ። በሌላ በኩል ግን ገዳዮችን “የአምላክ ትዕዛዝ ነውና እንኳን ንፁሃንን ወንጀለኛ ተብሎ የተጠረጠረን ሰው ቢሆን ያለ ተገቢው የፍርድ ሂደት አትግደሉ” ለማለት ወኔው በከዳው የሃይማኖት ተቋም መሪ ወይም ባለሌላ ማዕረግ አገልጋይ(ቄስ) እጅ ተጠምቆ እንዴት ሰው የጥምቀተ ብርሃኑ በረከት ደረሰኝ ይበል ? መስቀሉንስ ተሳልሞ እንዴት መስቀል ኅይል ሆነኝ ይበል ? ጠበልስ ጠጥቶ ወይም ተረጭቶ እንዴት ፀጋና በረከት ተትረፈረፈልኝ ይበል ? የሚሉና ተያያዥ አስጨናቂ ጥያቄዎች አእምሮየን አጥለቀለቁት። ጥያቄዎቹ ከባድና የእያንዳንዳችን ህሊና የሚፈትኑ ናቸው ። እንደ ክፉ ልማድ ሆኖብን ልፍስፍስ ምክንያት እየፈጠርን ካልሸሸናቸው በስተቀር በብርቱ እየተፈታተኑን ያሉ ፈተናዎቻችን ናቸው ።

ለጥያቄዬ እጅግ አበረታች ምላሽ ሆኖ ወደ አገኘሁት ጉዳይ ልመለስና “በወላዋይ ቄስ ከምጠመቅ ደሜ ፈስሶና በደሜ ተጠምቄ … . “ የሚለውን የዚያን ዘመን አልወለድም የአርበኝነት ተጋድሎ ዛሬም ብርቅየ የአገሬ ወጣቶች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎችና በተለይ ደግሞ በአማራና በኦሮሚያ ለነፃነትና እኩልነት በሚፈሰው ደማቸው መጠመቃቸው ለአገርና ለትውልድ የሚዳረስ የመከራና የውርደት ማርከሻ ሆኖ ተሰማኝ። ይህን የወጣት አርበኞቻችን ተጋድሎ ሁላችንም በንፁህ ልቦና እና በአርበኝነት መንፈስ ተቀብለን የመጨረሻውን የመዳን ቀን እውን ማድረግ አለብን ። ሆኖና አድርጎ በመገኘት መዳንን በዕውን የምንሻ ከሆነ ። ይህ የብሩህ ተስፋ ተጋድሏችን ለዚያች የመዳን ቀን ዕውን መሆን የሚኖረው ወሳኝነት እና ከድል በኋላም ለምንመሠርተው እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማህበረሰብ የሚለግሰው አስተዋፅኦ ግዙፍና ኅያል ነውና በሙሉ የአርበኝነት ስሜት እንጠቀምበት ። ደጋግመው እጃችን ውስጥ የገቡ መልካም አጋጣሚዎችን (opportunities) መልሰን መላልሰን ለባለጌ ፣ጨቃኝና ዘረኛ ገዥዎቻችን እያስረከብን ለሩብ ምዕተ ዓመት የተሽከምነው የመከራና የውርደት ቀንበር መሰበሪያው አሁን ካልሆነ ከዚህ በእጅጉ የከፋ የመከራና የውርደት ቀነበርን ለመሸከም መዘጋጀት አለብን።በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ክርስቶሳዊ ተልኳቸውን መሆንና ማድረግን በተላበሰ አኳኋን ማለትም የሰብአዊ መብትና ክብርን ፣ የነፃነትን ፣ የፍትህን ፣ የአገርና የወገን ኩራትና ክብርን ፣ የሰላምን ፣የፍቅርንና የጋራ ብልፅግናን እውን ለማድረግ በሚያስችል ሰብዕና እና መርህ ማከናወን የተሳናቸውን የሃይማኖት “መሪዎች” በይሉኝታ ወይም የማዕረግ ስማቸውን በማየት ወይም በመስማት ብቻ የፈጣሪን ሥልጣን የተጋፋን እየመሰለን ለዘመናት በድንቁርና የኖረውን እኛነታችን ጨርሶ ማስወገድ ባንችልም ከድንቁርናው የምንወጣበትን ሂደት ማፋጠን አለብን።
አገርና ወገን የጨካኝ ገዥዎች የመከራና የውርደት ዶፍ (ሸክም) ማራገፊያ ሲሆኑ የማይገደውን ወይም ከግፈኞች ጋር የሚሞዳሞደውን የሃይማኖት ‘መሪ ወይም አባት’ “ኅጢአቱ የራሱ ነውና እኔ ምን አገባኝ” በሚል ይባርኩኝና ይቀድሱኝ ከማለት የበለጠ ኅጢአት ያለ አይመስለኝም ። ይህ አስተያዬቴ አንዳንድ ምናልባትም ብዙ የዋህ አማኝ ወገኖቼን አስቆጥቶ “ይኸ ደግሞ የማን ተሃድሶና መናፍቅ (reformist and heretic) ነው?” ቢያሰኛቸው በመግቢያዬ እንዳልኩት ጨርሶ የማልጠብቀው ነገር አይደለም ። ለዚህም ነው የሃይማኖታዊ ወይም መንፈሳዊ እሴቶቻችን ጉዳይ እንደ አማኝነታችን ብቻ ሳይሆን እንደ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያዊነታችን ያሳስበናልና ደፍረን መነጋገሩን አንፍራው የምለው ።

ለሃይማኖት መሪዎቻችና በተለያየ የሥልጣን ተዋረድ ላይ ለሚገኙ አገልጋዮች የድረሱልኝ ጥሪ መጮህ ከጀመረች ብዙ ዓመታት የሆናትን ኢትዮጵያን ታሪካዊትና አገረ እግዚአብሔር እያሉ ከመስበክ አልፈው ይህ ትውልድ የራሱ ታሪክ እንዲሰራና አገሪቱም በዕውን አገረ እግዚአብሔር ትሆን ዘንድ ሆኖና አድርጎ በአርአያነት ለመቆም እንደተሳናቸው እራሳቸውን ለመመርመር የሚያስገድዳቸው አሁን ካለንበት የበለጠ አጋጣሚ ያለ አይመስለኝም ።

እስኪ እንደገና ወደ አልወለድም እንመለስ ፥

ይሙት በቃ ሊያስፈርዱበትና ሊፈርዱበት የተዘጋጁትን ራስ ወዳድና ጨካኝ ባለስልጣናትን፣ የፍትህ ሳይሆን የኢፍትሃዊነት ዳኞችን ፣ እና ጥቅመኛና አሽቃባጭ የሃይማኖት መሪዎችን በእንዲህ አይነት ጥልቅ በሆነ አስተሳሰብ የሚሞግተው ከዚያ ዘመን ደፋርና ድንቅ ደራሲያን አንዱ የነበረው አቤ ጎበኛ የኢፍትሃዊነትን ፣ የነፃነት እጦትን ፣ ልክ የሌለው የሃብትና የአኗኗር ልዩነትን ፣ የሃይማኖታዊ እምነትና የሞራል መሸርሸርን፣ ወዘተ አስከፊነት ለመግለፅ (ለማሳየት) በማህፀን ውስጥ እንዲናገር ያደረገው አልወለድምን ነው ።
በእኩይ የአገዛዝ ሥርዓታቸው የግል ጥቅማቸውን በሚያሳድዱ ገዥዎችና ባለስልጣናት ምክንያት የጎዳና ላይ ህይወትን (ህይወት ከተባለ) እንድትገፋ የተገደደችውን ምስኪን እናቱን አንችን ቁራሽ ማደሪያ መሬት ነስተው ለዚህ ህይወትሽ የዳረጉሽ ክፉዎች በሚፈነጩበት ዓለም መወለድ አልሻምና አምጨ እወልዳለሁ ብለሽ አትድከሚ ብሎ ገና በማህጸን እናቱን የሞገተው የአቤ ጎበኛው አልወለድም ነው ። ከዛሬ አርባ አምስት ዓመት በፊት ። አዎ ! ግፈኛ ገዥዎችን ፣ ፍርደ ገምድል ዳኞችን ፣ የበግ ቆዳ ካባ ለባሽ ተኩላ የሃይማኖት መሪዎችን/ቄሶችን (ሁሉንም አለመሆኑን ልብ ይሏል) እኩይ ባህሪና ተግባር ነው ለመስዋዕትነት በተዘጋጀ የአርበኝነትና የጀግንነት ኅይለ ቃል የሚሞግተው ። ገና ከዚያች ምስኪን እናት ማህፀን ውስጥ እያለ ስግብግቦችና ጨካኞች ወደ ሚገዟት ምድር አልወጣም ብሎ የተሟገተውና በገንዛ አገራቸው አገር አልባ እንዲሆኑ የተደረጉትን ምስኪን ዜጎች እንደሰው ሰው ሆኖ የመኖር ጥያቂያቸውን በመሪነት አንግቦ አደባባይ በመውጣት መሪር ጩኸታቸውን የጮኸው የአቤ ጎበኛው አልወለድም ነው ። ወደ ዚች አለም የመጣውና አድጎ ለራሱ ብቻ ሳይሆን በግፈኞች ከተገፉና በነፃነት ሠርተን እንኑር እያሉ ይጮሁ ከነበሩ ወገኖቹ ጎን በመቆሙ ገና በማህፀን እያለ እንደፈራው ይሙት በቃ የተፈረደበት የአቤ ጎበኛው አልወለድም ነው ዛሬም ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ የትና በምን ሁኔታ ላይ እንደምንገኝ ተጠየቁ የሚለን ።

አቤ ጎበኛ እንደገና በአልወድምና በምስኪ እናቱ መካከል በተደረገ ጥያቄ አዘል የሃሳብ ምልልስ ውስጥ ዛሬም ከአራት አሥርተ ዓመታት በላይ ቆይታ በኋላ ተጠየቁ ይለናል ። ደራሲው እናትና የማህፀን ልጇን እንዲህ እንዲነጋገሩ ያደርጋቸዋል ፥
ምስኪን እናት ፡ “… ለምን አትወለድም ?”
አልወለድም( የማህፀኑ)፡ “ተወልጄ በችግር መሰቃየት አልፈልግም ።”
እናት ፡ “እኔ በተቻለኝ መጠን አሳድግሃለሁ ::”
አልወለድም ፡ “ሊያኖረኝ የሚችል ሃብት አለሽ ?”
እናት ፡ “እንደዚሁ ለምኘም ቢሆን አሳድግሃለሁ ።”

አልወለድም ፡ “ሞት ይሻላል ፣ እኔ ማን መሰልሁሽ አንች? ልመናን ተማምኘ የምወለድልሽ ? በገንዛ ሃገርሽ ላይ የምትችይውን ሠርተሽ በመኖር ፈንታ እንዴት ልመናን ተስፋ አድርገሽ ትኖሪያለሽ ? ያንች በዚህ ሁኔታ መጎሳቆል አንሶ ደግሞ ማደጊያ የሌለው ልጅ ለምን ትወልጃለሽ ? ቀማኞችና ነፍሰ ገዳዮች እንዲሁም የነፃነት ጠላቶች በሰለጠኑበት ዓለም ደግሞ ምን እድል አለኝ ? የድሆች ልጆች የሚጠብቃቸው የወላጆቻቸው መከራና ችግር ብቻ ነው ። ” ይልና “መከራና ችግርን ከድሆች ትክሻ ላይ ለማውረድ እንደኔ ከሆድ ውስጥ ጀምሮ ለመብትና ለንፃነት መሟገት ያስፈልጋል። ” በማለት እስከመፍትሄው ሲነግራት፣

ምስኪን እናት ፡ “እረ ስለፈጠረህ ብለህ ተወለድ ” ብላ ስትማፀነው ፣

” ፈጣሪም የፈጠረኝ ለባርነትና ለችግር ከሆነ እሱንም አሻፈረኝ ብየዋለሁ ። ግን እሱ እስከዚህ ቂል አይደለም ። እሱ የነፃነት ዓለም ፈጠረ ። ግፈኞች ነፃውን ዓለም የባርነት ዓለም አደረጉት ። ቂሎችና ደካሞችም የባርነት ማስፈራሪያ አደረጉት ።” በማለት እርሷ እየኖረችበት ያለውን የስግብግቦችና የጨቋኞች ዓለም አስከፊነት በማህፀኗ ውስጥ ሆኖ ያስረዳታል ።

ዛሬስ ቅድስት ወይም አገረ እግዚአብሔር እያልን በምንጠራት አገር ስንት አልወለድሞች አሉ? ለአገርና ለወገን ልዕልና እና ብልፅግና በፃፉና በተናገሩ ፣ በጮሁ ፣ በታገሉና ህዝብን ባስተባበሩ የተገደሉ ፥ የቁም ስቃይ የሚፈፀምባቸው ፣ የካድሬ ወይም የሆድ አደር አቃቤ ሀጎችና ዳኞች ኢፍትሃዊና አስከፊ ፍርድ ሰለባ የሆኑ አልወለድሞች ስንት ናቸው ? ጧሪና ቀባሪ ወጣት ልጆቻቸው በየመንገዱና በየአደባባዩ እና ይኸውና አሁን ደግሞ ለሃየማኖታዊ ክብረ በዓል በወጡበት በገዥ ቡድኖች ነፍሰ ገዳይ ኅይሎች ተገድለውባቸው ቀሪ እድሚያቸውን የደም እንባ እያነቡ እንዲኖሩ የተፈረደባቸው የአልወለድሞች እናቶች ስንት ናቸው ?

ዛሬ እኛን የገጠመን ከባዱ ፈተና በአንድ በኩል እርሱ (ፈጣሪ) በነፃነትና በፍቅር እንድንኖርባት ያደለንን ታላቋን ምድር ኢትዮጵያን ዘረኛና ግፈኛ ገዥዎቻችን የመከራና የውርደት ምድር የማድረጋቸው ጉዳይ ሲሆን ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ደካማ ወይም አድርባይ ወይም ደግሞ በግልፅ እንደምናየው ለይቶላቸው ነፍሰ ገዳዩን አገዛዝ የሚባርኩ ተገዳዩን ግን “አርፈህ ተቀመጥ ሰላምን አታውክ” በማለት ፈጣሪን የባርነት ማስፈራሪያ ያደረጉትን “ቅዱስ አባታችን/ቅዱሳን አባቶቻችን” እያልን እራሳችን ብቻ ሳይሆን ፈጣሪንም እያታለልን የመቀጠላችን ነገር ነው ።

ይህን አስተያዬቴን ከዚህ በተሻለ “የትህትና” አገላለፅ ባስቀምጠው ደስ ባለኝ ነበር ። መሪሩን እውነት ስለማይገልፅልኝ አላደረግሁትም ። አላደርገውምም ። ለምን ? ለሚለኝ ግን መልሴ አጭርና ቀላል ነው ። ጎዳን እንጅ አልጠቀመንም ። ጨርሶ የሚጠቅመንም አይደለምና ይልቁን ይህን የአስተሳሰብ ድውይነት (አዙሪት) ሰብረን እንውጣ ነው የምለው።

የሃይማኖታዊና ሞራላዊ ሰብእና በጎደለው አባት ወይም አባቶች መሪነትና አሳራጊነት የምናደርሰው ኪዳን ፣ የምፀልየው ፀሎት፣ እግዚኦ የምንለው የምህላ ጩኸት ፣ የፀሎታችን ሁሉ ማሳረጊያችን አባታችና እመቤታችን ሆይ እንደገደል ማሚቶ እንሰማው እንደሆነ እንጅ የትም አይደርስም ። በፈጣሪ ሥራና ውሳኔ ጣልቃ መግባት አይሆንም እንዴ ? የሚሉ ብዙ ወገኖች የመኖራቸውን ጉዳይ በሚገባ እረዳለሁ ። ምክንያቱንም እንደዚሁ ። ምክንያቱ ከዚሁ ከምንነጋገርበት የአመራር ደካማነት (ድውይነት) ችግር ጋር የተቆራኘ ነው። በመሆኑ በሂደት በመንመሠርተው ዴሞክራሲያዊና ፣ የእምነትና ሌሎች የሰብአዊ መብቶች ሳይሸራረፉ በሚከበሩበት ህዝባዊ ሥርአት ተገቢውን መፍትሄ የሚያገኝ እንጅ እንዲህ በቀላሉ እመን/ኝ ወይም አሳምነኝ/ አሳምኝኝ እሰጥ አገባ የምንፈታው ጉዳይ አይደለም ።

እራሳችን እናታለው ካላልን በስተቀር ከብዙ ዓመታት በኋላም በማይዋዥቅ የጋራ ጥረትና ፀንቶ በሚዘልቅ መርህ ላይ ተመሥርተን የጋራ እጣ ፈንታችን ወደ እሚወስነው የትግል ጎራ ለመቀላቀል ዕውነተኛ የአርበኝነት ቁርጠኝነት መላበሻው የሚያጥረን ጥቂቶች አይደለንም ።

የሃይማኖት መሪዎችና ወንጌል ሰባኪዎችም (በራሳቸው ተነሳሽነት ከሚሞክሩት እጅግ ጥቂቶች በስተቀር ) ተልኳቸውን እንኳን በአርበኝነት ስሜት ይቅርና እንደማነኛውም በደልን አይቶ ዝም እንደማይል ቅን የአገሬ ሰው በደል ወይም ግፍ የእግዚአብሔር አይደለም ፣ እኛም የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነንና የኢትዮጵያ ህዝብ ሁለንተናዊ ስቃይና ውርደት ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ ያብቃ ብሎ የሚያስብ አእምሮና የሚናገር አንደበት ሲቸግራቸው ማየትና መታዘብ በዕውነት ያማል ።

የዚህ የድርጊት ድውይነት ምክንያቱ ብዙ ጥናትና ትንታኔ የሚጠይቅ አይደለም ። በተለምዶ እንደምንለውም አለመታደል ሆኖብንም አይደለም ። ይልቁንም እኛው ራሳችን ስለምንፈልገው ነገር ሌት ተቀን እየደሰኮርን (እየሰበክን) ፣ እየዘመርንና እየዘፈን ፣ እያቅራራንና እየፎከርን ፣ ቅኔ እየተቀኝን ፣እግዚኦ! እያልን ፣ የነፍስ ይማርና የምህላ ፕሮግራም እያወጅን ፣ ወዘተ በተግባሩ ሜዳ ላይ ግን መልሰን መላልሰን በመውደቃችን እንጅ ። ይህ ደግሞ “እንግዴህ ይህ ዓለም ፍፁም የእኔ/የእኛ አይደለም” በሚሉ የሃይማኖት መሪዎችና በየደረጃው የሚገኙ ኀላፊዎችና አገልጋዮች ብሶ ሲገኝ ከአሳሳቢነት አልፎ ልብ ይሰብራል ።

ይህን መሪር ዕውነት በፀጋ ተቀብሎ ወደ እሚበጀው የሃሳብና የተግባር መስመር መግባቱ የአርበኝነት አንዱ መገለጫ ነውና ተጨማሪ ጊዜ ፣ የሰውና የማቴሪያል ሃብት ሳይባክን ብቻ ሳይሆን ተጨማሪ የማይተካ የንፁሃን ዜጎች ህይወት ሳይቀጠፍ በአብሮነትና በፅናት ቆመን የመከራና የውርደት ጊዜያችን እናሳጥር ። የአገር ፣ የወገን እና ያለነዚህ ህልውና እና ደህንነት ትርጉም የሚያጡት ሃይማኖታዊ ተቋሞቻችን አደጋ ላይ መውደቅ ከምር የሚሳስበን ከሆነ የድንቁርና ወይም ሃፍረተ ቢስ የብልጠት ምክንያት መደርደሩን ከተቻለ ትተን ካልሆነም ቀንሰን ወደ እሚበጀን ተግባራዊ ሜዳ አብረን በመውረድ የስኬትና የድል ባለቤቶች እንሁን።

ምዕመናንም ሰንበትንና በዓላትን እየጠበቅን በየቤተ እምነቱ በመታደም ቅዳሴውን ቁመን ስለአስቀደስን ፣ ዝማሬውን በጭብጨባና በዕልልታ ስለአደመቅን ፣ እግዚኦ ያንተ ያለህ!ብለን ስለተማፀን ፣የሚታደለው ፀበል ስለደረሰን ብቻ የውሸት እርካታ እየተሰማን ከዚህ ባሻገር ያለውን ለሱ ትቸዋለሁ (ትተነዋል ) እያልን እራሳችን የመሸንገሉ ልማድ ሊያሳስበን ይገባል ። “በሰጠኋችሁ ልዩ አካላዊና አእምሯዊ ብቃት ተጠቅማችሁ ህዝቤንና የሚኖርበትን ምድር ጠብቁ ። በጥረታችሁም አልለያችሁም ” ያለንን መልካም ትዕዛዝ በቅጡ ሳንተገብር “አገራችን ጠብቃት !” እያልን መጮሃችን ብቻውን የት አደረሰን ? የትስ ያደርሰናል ? በህይወት የመኖራችንና ዓለማዊም ሆነ መንፈሳዊ ኅላፊነታችንና ተግባራችን ለአገርና ለወገን የሚጨበጥ ትርጉም ካልሰጠ በየት በኩል አልፈን ነው የሰማይ ቤት ወራሽ የምንሆነው ? ብለን የራሳችን ህሊና እንጠይቀው ።

አዎ! ዛሬም ጥምቅትን በየዓመቱ እንደተለምዶ “አከበርነው” እንጅ በዕውን ተጠምቀን እኛም አልዳንም ፣ ወገንና አገርንም ከመከራና ከውርደት አልታደግነውም ። አጥማቂውስ ምን አይነት መንፈሳዊ ሰብእና አለው ? ብለን ወይ አልጠየቅንም ብንጠይቅም ቄሱ የሚያገለግለው ባዶውን ህንፃ ይመስል “እኔ በእርሱ ኅጢአት ምን አገባኝ” እያልን በእጁ መጠመቃችን ለፅድቅ መስሎን ተቀብለነዋል ። እንዴትና ለምን ? ብለን በመጠየቅ መልሱን ፍለጋ የስቃይና የመከራ ዓመታትን እንዲገፋ ወደ ተገደደው የዋህና አማኝ ህዝብ በእውነት አልዘለቅንም ።

የሐዋርያት ሥራና ገድል እያልን የምንሰብከው ሃይማኖታዊ ታሪክ የሚነግረን ይህ በየቤተ እምነቱና በየቤተ መቅደሱ መሽጎ ሐዋሪያ ወይም የወንጌል አርበኛ ነኝ ማለትን አይደለም ። ሐዋርያነት የሚያስተምረን ወደ ህዝብ የሃይማኖት አደባባዮች ፥የህዝብ የሃዘንና የመከራ ጩኸት ወደ ሚሰማባቸው መንደሮች ፥ህዝብ በመከራውና በውርደቱ ላይ የሚፈነጩ ጨካኝ ገዥዎችን ለማስወገድ ወደ እሚመካከርባቸው አደባባዮች ፣ ምን እናድርግ ተብሎ ወደ ሚመከርባቸው የአዛውንቶችና እና የምሁራን ጉባኤዎች ፣ ወልዳና አሳድጋ በልጇ አስከሬን ላይ ተቀመጭ ወደ ተባለችና በታቦት ፊት ታዳጊ ወጣት ልጇ በጥይት ተመቶ ወደ ወደቀባት እናት በመሄድ አለኝታነትን በድርጊት መግለፅን ነው ። ግፈኛ ገዥዎች በድሆችና እራሳቸውን ለመከላከል እንኳ አቅም በሌላቸው ንፁሃን ላይ የሚጭኑት የመከራና የውርደት ቀንበር ይሰበር ዘንድ እስከ መስዋዕትነት የሚሄድ ሰብእናን ነው ሐዋርያነት የሚያስተምረን። አጥማቂና ተጠማቂ በየጥምቀተ ባህሩ ወይም አውዱ የሚሰማውን የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የሰብአዊ መብትና ክብር ፍለጋና ጩኸት ከመስማት አልፎ በተሰበረ ልብ ማዳመጥንና በድርጊት የሚገለፅ ሰብእናን ነው የሐሪያነት ውሎና ታሪክ የሚነግረን ። አገረ እግዚአብሔር የምንላት ኢትዮጵያ እና የአኩሪ ታሪክና ባህል ባለቤት ነው የምንለው ህዝብ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ እጅግ በአስከፊ ሁኔታ የመከራና የውርደት ሰለባ ሆነው የዓለም መዘባበቻም ከንፈር መምጠጫም ሲሆኑ የእኛ ሐዋርያነት የት ነበር ? አሁንስ የት አለ? እውነት የሆነውን መልስ ልባችን እያወቀው ከተልኳችን ጋር የሚመጣጠን አርበኝነት በእጅጉ ስለሚጎድለን ይህን ራስን የመፈተሽ ጥያቄም ለመመለስ እንደምንቸገር ይገባኛል ። ከእውነቱ ጋር ደፍሮ ከመጋፈጥና እራስን ነፃ ከማውጣት ሌላ የነፃነት መንገድ ግን የለም ። ከምር ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትህ የሰፈነበት አገር እንዲኖረን የምንፈልግ ከሆነ ።

ጥምቀተ ክርስቶስ ማለት የዕውነትነቱ ምሥጢር የተገለፀበት ማለት አይደል እንዴ ? ታዲያ ያ ሚሥጥር በዕውን ወይም በድርጊት የተገለፀው ለበጎ ነገር ፣ ለሰው ልጆች መንፈሳዊም ምድራዊም ነፃነት ፣ ለሰብአዊ መብትና ክብር ፣ ለፍትህ ኅያልነት ፣ ለሰላምና ለፍቅር መስፈን እና የምድርን በረከት በጋራና በመተሳሰብ ለመሳተፍ ይቻል ዘንድ በተከፈለ የቁም ስቃይና የመስቀል ላይ ሞት አይደል እንዴ ? ታዲያ የአሁን አሁን ነገረ ሥራችን ከዚህ እጅግ ግዙፍ ፣ ጥልቅና ግልፅ የጥምቀት ምንነት ጋር እንዴት እናነፃፅረው ? እንዴትስ እናጣጥመው? እንዴትስ በዕውን አጥምቀን አዳን እና ተጠምቀንም ዳን እንበል ?

እውነተኛ ጥምቀትን እየናፈቁ በየሄዱበት ሥርዓተ ጥምቀትና በየሚያጅቡት ታቦት ፊት የነፃነት ያለህ እያሉ የጮሁ የነገ የአገር ተስፋ ወጣቶች ከተሸከምነው ታቦት ሥር ወይም ፊት በጥይት አረር ሲወድቁና የፈሰሰ ደማቸውን ተራምደን ስንሄድ ምን ተሰማን ? ምንስ አልን ? ምንስ አደረግን ? “ባንናገረውም በልባችን ውስጥ አዝነናል ፣ ጭካኔውንም አውገዘናል” ካላሉን በስተቀር የሃይማኖት መሪዎች ነን የሚሉትና በየደረጃው የሚያገለግሉ አባላት ሲሰጡት የምንሰማው ምላሽ በተግባር ሲለካ ዝም ጭጭ ከመሆኑም አልፎ አሁንም “ዝም ብላችሁ በየቤታችሁና በየቤተ እምነቱ አልቅሱና እግዚኦ ! በሉ” የሚለውን ደምሳሳና አደንቋሪ ስብከታቸውን ከምር ልብ ካልነው ልብ ይሰብራል ።

እዚህ ላይ እያነሳሁና እየጠየቅሁ ያለሁት አንዳንድ የአባ ማቲያስ ካቢኔ አባላት ( የቅዱሳን ጉባኤ ብሎ መጥራት በቤተ ክርስቲያኗና በራሱ በፈጣሪ መቀለድ ስለሚሆን) የሁኔታዎችን ከባድነትና የህዝብን ወቀሳና ውግዘት በሥልጣን ላይ ከመቆየታቸው እጣ ፈንታ አኳያ እያሰሉ በግለሰብ ደረጃ ገዥዎችን የሚገስፅ የሚመስል ንግግር ወይም መግለጫ ቢጤ ስለመስጠታቸው አይደለም ። ምክንያቱ ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ ከዚህ የማስመሰል ዲስኩር ቢጤ አልፈው ለመሄድና ቤተ ክርስቲያኗ እንደተቋም ከገዳዮች መዳፍ ነፃ እንድትወጣ ያሳዩት አንዳችም ትርጉም ያለው ነገር የለምና ነው ። ይህ ደግሞ በሃይማኖት አባትነት ካባ ሥር ተመቻችቶ የተቀመጠ አድር ባይነት ካልሆነ በስተቀር ሐዋርያዊ አርበኝነት ከቶ ሊሆን አይችልም ። የሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ጉዳይ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል የምለውም ለዚህ ነው ።
ይህ ዓይነት እጅግ ቅጡን ያጣ የሃይማኖት መሪነትና ሰባኪነት ጨርሶ የተሳሳተ ነውና ወደ ትክክለኛው መንገድ እንመለስ ብለን በድፍረትና በቅንነት መናገር ያለብን ለራሱ ለሃየማኖታችንና ለየቤተ አምልኮቻችን ትርጉም ያለው ህልውናም ብለን መሆን አለበት ። ለተተኪው ትውልድ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ ሰብአዊ መብት/ክብር ፣ ፍቅር፡ሰላምና የጋራ ብልፅግና የሌለባት አገር ላለማውረስ እስከ መስዋዕትነት የሚወስድ ትግል ማድረግ እንዳለብን ሁሉ መንፈሳዊ ተልኳቸውን በዕውነትና በአግባቡ የማያከናውኑ (የማይወጡ ) የሃይማኖት ተቋማትንም ማስተላለፍ የለብንም ። ለዚህ ነው ህዝብ ጨርሶ ሰብአዊነት በጎደላቸው ገዥዎች የመከራና የውርደት ቀንበር ሲጫንበት “ፖለቲከኞች ይጨነቁበት፣ እኔ/እኛ ጉዳዬና/ጉዳያችንና ተልኮዬ/ተልኳችን ሃይማኖታዊ ነውና” ስንል አዋቂነት ሳይሆን የለየለት ድንቁርና ፣ ኩራት ሳይሆን ሃፍረት ፣ ቅዱስነት ሳይሆን እርኩስነት ፣ አርበኝነት ሳይሆን ወስላታነት ፣ አስተማሪነት ሳይሆን አደንቋሪነት የሚሆነው ።የአገሬ ህዝብ ሁሉም በሚያሰኝ ደረጃ ከክርስትና እና ከእስልምና ሃይማኖት ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። ይህም በአንድ ወይም በሌላ መንገድ እንደ አንድ ባለታሪክ አገርና ህዝብ ነፃነትን ፣ ፍትህን ፣ ሰብአዊ መብትን/ ክብርን ፣ እኩልነትን ፣ አብሮነትን ፣ ፍቅርን ፣ ሰላምን እና የጋራ ብልፅግን በሚያረጋግጥ ሥርዓተ ማህበረሰብ ሥር ለመኖር በሚያደርገው ግብ ግብ (ትግል ) ላይ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅኖ የማሳደሩ ነገር በዚያው ልክ ከፍተኛ ነው ። በመሆኑም የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና በየደረጃቸውና በየችሎታቸው የሚያገለግሉ አባላት ሃይማኖታዊነትን (መንፈሳዊነትን) ከህዝብ ወይም ከምእመናን ሁለንተናዊ የህይወት እጣ ፈንታ ጋር እንዴት ነው የሚያዩት? የሚረዱትስ ? የሚተገብሩትስ? ብሎ መጠየቅ ብቻ ሳይሆን በአግባቡና በአክብሮት ሃሳብን ፣ ትችትን እና ይበጃል ወይም ገንቢ ነው ተብሎ የሚታመንበትን አስተያየት በነፃነትና ያልምንም አላስፈላጊ ይሉኝታ መግለፅ ወይም ማድረስ ሊበረታታ የሚገባው ጤናማ ነገር ስለመሆኑ የምንጠያየቅበት ጉዳይ አይመስለኝም ።

ለሰማዩም ሆነ ስለምድሩ ህይወታችን በዕውነት ስለዕውነት መነጋገር ይበጃልና በዚሁ መሠረት እንነጋገር ካልን አያሌ ዓመታትን እያስቆጠረ ላለው የአገርና የወገን መከራና ውርደት ተጠያቂነቱን ለፖለቲከኞች፣ ለሰብአዊ መብትና ለአገር ክብር ተከራካሪዎች ፣ መነሻቸውና መድረሻው የአገርና የህዝብ ኩራትና ዕድገት ለሆነ የብዕር ሰዎች ፣ የብዙሃን መገናኛ ባለሙያዎች፣ ወዘተ ብቻ ማስታቀፍ ጨርሶ ሚዛናዊነትና ፍትሃዊነት የለውም ። ቀደም ብየ ለመግለፅ እንደሞከርኩት በተለይ እንደኛ ላለ ስቃይና መከራውን ሁሉ “እግዚአብሔር ያመጣውን እሱው እስኪመልሰው ፥ እርሱ ሰጠ እርሱ ነሳ ፥ እርሱ ፈጠረ እርሱ ገደለ ፥ እርሱ ሾመ እርሱ ሻረ ፥ እርሱ ባሪያ አደረገ እርሱ ጌታ አደረገ ፥ እርሱ ገዥ አደረገ እርሱ ተገዥ አደረገ” በሚል ከራስ ኅላፊነት የመሸሽና የሚያስከትለውን አሉታዊ ውጤትም ከነምክንያቱ ከራስ ወደ ፈጣሪ ወይም ወደ ሌሎች ወገኖች መገፋትን ወደ መንግሥተ ሰማያት መግቢያ እዮባዊ ትዕግሥት አድርጎ የመውሰዱን ጉዳይም ቆም ብለን በቅጡ ልናየው ይገባል ።

በእንዲህ አይነት ደምሳሳና ከኅላፊነት የመሸሽ ሰበብ ድርደራ መቸም ቢሆን የትም አንደርስም ። ክርስቶስ “እኔ እንዳደርግሁት ሁሉ ክፉውን ነገር ሁሉ እስከመስዋዕትነት ሄዳችሁ ተቃወሙ” ብሎ በድርጊት ያሳየንን ገድል ለእኛ ደካማነት ወይም መስሎና አስመስሎ መኖር እንዲመቸን አርገን እየተረጎምንና እየሰበክን በሥጋም ይሁን በነፍስ የትም አንደርስም ። ለዚህ ደግሞ የሃይማኖት ተቋማት መሪዎችና አገልጋዮች የሚኖራቸው አወንታዊውም ሆነ አሉታዊ አስተዋፅኦ እጅግ የጎላ ነውና የሚበጀውን ሁሉ ያደርጋሉ ብለን ተስፋ እናድርግ ።

የጥምቀት ክብረ በዓላችን ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ባህላዊና ማህበራዊ መስተጋብሮች የሚታደሙበትም በመሆኑና ልዩ መስህብነትን ስለሚፈጥር በተለይ የቱሪስቱን ቀልብ የመሳቡን ነገር ከእኛ በበለጠ የውጭ ሰዎች በመፅሐፍ ሆነ በሌላ መልክ በቂና የተሟላ ወይም እኛ እንደምንፈልገው ባይሆንም መስክረውለታል ። በዚህ መነሻነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNSECO) በዓለም የቅርስ ሃብትነት እንዲመዘገበው ጥረት መጀመሩን ሰምተናል ። አንብበናልም ። በመሠረተ ሃሳቡና በጥረቱ የሚከፋው ቅን ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም ።

ጥያቄ ማንሳት ግን ይቻላል ። ተገቢ ነው ። እናም ለመሆኑ ጥምቀትን የዓለም ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ የምንለው በሃይማኖታዊነቱ ነው ወይስ አሁን አሁን እንደምንታዘበው ከሃይማኖታዊ እሴትነቱ በላይ ባህላዊና ትውፊታዊ የሆኑ ትርኢቶች ጎልተው እንዲታዩ በማድረግ የቱሪስት ገቢን ከፍ ለማድረግ ነው ? ብሳሳት ደሰተኛ እንደምሆን እየገለፅሁ ምናልባት ሊሆን ከቻለም በሁለተኛው ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ዩኔስኮ የአንድን ሃይማኖት አንድ ክብረ በዓል በዓለም ቅርስነት መዝግቦ ጥበቃና እንክብካቤ እንዴት እንደሚያደረግ አላውቅም። መመዘኛው ቀላል የሚሆን አይመስለኝም ። ከላይ እንዳልኩት ሃይማኖታዊ ይዘቱን የሚያደበዝዙ ግን ለቱሪስቱም ሆነ ለእኛም የእይታ እርካታን (amusement, not happiness) በመስጠት የገቢ ምንጭን ከማስፋት አኳያ ያስኬድ እንደሆን ማሰብ ይቻል ይመስለኛል ። ለዚህም ይመስለኛል ከዓመት ዓመት በዋዜማው (ከከተራ) ጀምሮ ልዩ ልዩ ድንቅ የአርት(የእጅ ጥበብ) ሥራዎች በተሽከርካሪ እየተጎተቱ ሲታጀቡ ፣ ቀሳውስትና ዘማሪ ወጣቶች የሚተውኗቸው ልዩ የአሰላለፍና የእርግዶ ትርኢቶች እና ሌሎችም ዓይነ ገብ ( ልበ ገብ አላልኩም) እንቅስቃሴዎችን ማየት የጀመርነው ።

ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት ሳይሆን ይህን ያህል ለበዓሉ ዓለማቀፋዊ እውቅና እና ጥበቃ ማስገኘት “ተጋድሎ“ እያደረግን ነው የሚሉን የሃይማኖት መሪ ተብየዎቻችን ይህን ዘመቻ ሲያበስሩን ምነው የራሳቸውን ውድቀትና የመከረኛውን ህዝብ አኳኋን ዞሮ የሚያይ ህሊና ጨርሶ ከዳቸው ብሎ መጠየቅ ግድ ይላል ለማለት ነው ። ሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ እጅግ በርካታ ንፁሃን ዜጎች በአሸባሪ ገዥ ቡድኖች የሰቆቃ መፈተኛ ሲሆኑ ፣ ቤተሰባቸው ተበትኖ በየማጎሪያ ቤቱ ማለቂያና መጠን የሌለው የግፍ በትር ሰለባዎች ሲሆኑ ፣ ነፃነት ብለው በጮሁ በግፍ ሲገደሉና ይኸው አሁን ደግሞ ታዳጊ ወጣቶች እና ህፃኑም ሳይቀር ጥምቀትን ለማክበር በወጡበት በጥይት ሲያሩ ቢያንስ ትንሺ የሰብአዊነት ስሜት ተሰምቷቸው ገዳዮችን አትግደሉ ፣ የተገዳዮችን ዘመድ አዝማድ እና መላው የኢትዮጵያን ህዝብ ደግሞ ያፅናችሁ ለማለት ያልደፈሩ ጥምቀትን ወደ ቱሪስት መስህብነት ለውጦ ገንዘብ ስለማግኘት ዘመቻቸው ለዚህ መከረኛ ህዝብ “የተጋድሏችን ቅዱስነት” እመን ሲሉት በዕነቱ ህዝብን ብቻ ሳይሆን ራሱን እግዚአብሔርንም በብርቱ ማሳዘን ነው ።

ይህ ነው እንግዴህ ጊዜም ገና ያልፈታው እኛም ለመፍታት ያቃተን እጅግ ከባዱ ፈተናችን ። የእየራሳችን የልብና የውስጥ ነፍሳችን በድፍረት ተጋፍጠን የወደቅንበትን አገራዊና ወገናዊ አዙሪት ሰብሮ ለመዉጣት ያለመቻል ፈተና ። የክርስቶስን ትምህርትና መስዋዕትነት አብዝተን እየተረክን እኛ ግን የምንችለውን ሆነንና አድርገን ያለመገኘት ፈተና ።

የማይጨበጥ ተስፋ አላሚዎች የመሆን አባዜን ሰብሮ በመውጣት ታላቋንና ብቸኛ የእኛነታችን የክብርና ኩራት ምድር የሆነችውን ኢትዮጵያን ለሁላችንም ዓለማዊውም ሆነ መንፈሳዊ ህይወታችን የምትመች እናድርጋት ። ለልጆቻችንም ይሁን የልጅ ልጆቻችን እንደዚህ ቁልቁል የወረደውን ሁለንተናዊ ማንነታችን አውርሰን እነሱም ከሱ ጋር ሲወድቁና ሲነሱ ጥሏቸው የሚገሰግሰው ዓለም መዛበቻና ከንፈር መምጠጫ ቆስቋሎች እንዲሆኑ አንፍረድባቸው።

የምንፈራው ቀርቶ የሚበጀን ዕውን መሆን ካለበት በአንድ እጅግ አቢይ ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባት ላይ መደረስን ግድ ይለናል ። ዕውነተኛ ዴሞክራሲያዊና ህዝባዊ መብት ጨርሶ በሌለበት እንደኛ ባለ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ የእነምነትም (የሃይማኖትም) ሆነ የማነኛውም ሌላ ነፃነት ወይም መብት መከበር ጨርሶ የሚታሰብ አይደለም ። ይኸ ደግሞ በጭፍን ገዥዎችን ለማጥላላት ወይም ለመወንጀል የሚነገር ሳይሆን ለሩብ ምዕተ ዓመት ሙሉ የእያንዳዱን ዜጋ ህይወት ምስቅልቅሉን እያወጣ የመጣና እየተሻለ ሳይሆን በእጅጉ እየከፋ በመሃሄድ ላይ ያለ መሪር ሃቅ መሆኑ ለገዳዮችና አስገዳዮች ካልሆነ በስተቀር ለማነኛውም የጤናማ አእምሮ ባለቤት ኢትዮጵያዊ ግልፅና ግልፅ ነው ።

ታዲያ በተለይ የሃይማኖት መሪዎች እና ወንጌል ሰባኪዎች (አስተማሪዎች) ነን የሚሉ ወገኖች ለህዝብ የሚበጅ ሥርዓት እንዲመሠረት የሚደረገው ህዝባዊ ተጋድሎ ሰሚ እንዲያገኝና አስፈላጊውና ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ገዥዎችን ከመገሰፅና ከመምከር ይልቅ የእብደቱ ፖለቲካ አካል ሆነውት ሲያርፉ እንዴት አያሳስበን ? እንዴት ልባችን አይሰበር? እንዴትስ“ቅዱሳን አባቶች” እያልን የቅዱስነትን ምሥጢር እናራክስ ? እንዴትስ መንፈስ ቅዱስ በእነሱ ላይ አድሮ የቅድስና ሥራውን ይሠራል ወይም እየሠራ ብለን እንቀበልና እንመን ? እርሱን (እግዚአብሔርን) የኢትዮጵያውያን መከራ ወይም ስቃይ የማይገደው ጨካኝ ማድረግ አይሆንም እንዴ ?

ታዲያ ይህ ካላሳሰበን ፣ እረፍት ካልነሳን እና ከዚሁ ሁሉ ውድቀት መገላገያው መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ብቻ በመሆኑ ቁልፍ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ ተስማምተን ለተግባራዊነቱም በሁለገብ የአርበኝነት ሰብእና አብረን ካልቆምን የመከራውንና የውርደቱን ቀንበር አንዱ ተሸንፎ ሲወድቅ ሌሎቻችን በየተራ እየተቀባበልን እንቀጥላለን ።

ለፈተናችን በወቅቱ ትክክለኛውን መልስ ባለመመለሳችን እየተከማቼና በይዘትም እየከበደና እየተወሳሰበ በመሄዱ በዚህም ርዕሰ ጉዳዬ ላይ ብዙ ባልኩ ደስ ባለኝ ። ግን ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ ።

ከዚህ ለመዳን የምናደርገውን ማናቸውንም የትግል ጉዟችን እግዚአብሔር ይባርክልን !

ይህን ለመወጣት እንድንችል ቅንነትና አርበኝነት የተላበሰ አመራር እየሰጡ ላሉት የበለጠ ብርታትን ይለግስልን !

በደካሞች የውድቀት መንገድ ላይ ያሉት ደግሞ እራሳቸውን መርምረው ወደ ትክክለኛው ህዝባዊ መንገድ እንዲመለሱ ይርዳቸው !
እሰፋ ማሩ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1550
Joined: Mon Sep 12, 2016 8:47 pm

Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 2 guests