በወያኔ የተቀፈቀፈው በድን ብአዴን

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

በወያኔ የተቀፈቀፈው በድን ብአዴን

Postby እሰፋ ማሩ » Sun Mar 04, 2018 9:03 pm

ህውኃት- ዛሬም በጉልበት፤ኦህዴድ በአስቸጋሪ-መንገድ፣ብአዴን (በድን ፣ይገረም አለሙ)
March 4, 2018
ከብአዴን አባላት የተዛመዳችሁ፣
ለቅሶ ተቀመጡ ማቅ ተከናንባችሁ
አካላቸው ገዝፎ ህያው ቢመስሉንም
ባይሞቱም ሞተዋል ህሊናቸው የለም፡፡

ጊዜ ደጉ ብዙ እያሳየን ነው፡፡በህውኃት ማሽን ተፈልፍው ፓርላማ በሚባል መጋዘን ተከማችተው ከነበሩት መካከል የለም እኛ ሰዎች እንጂ የፋብሪካ ምርት እቃዎች አይደለንም ያሉ ሰዎች ለማየት በቅተናል፡፡ታሪክ ለሁሉም በእኩል ወቅታዊ ፈተና ያቀረበላቸው ሲሆን ፈተናውን አልፈው የነገን ባናውቅም ለዛሬ ለክብር የበቁ በጣም ጥቂት ሰዎች ተገኝተዋል፡፡ይህ ደግሞ በራሱ መጪውን ግዜ አመላካች ይመስለኛል፡፡እኛንም የፓርላማ አባላቱን በጅምላ የሙታን መንደር፣ የእሺዎች ስብስብ፣ እጅ እንጂ ህሊና የሌላቸው ወዘተ እንዳንል የሚያደርግ ነው፡፡በጉልበቱ የሚታበየውን በጉልበት መመከት፤ መንገድ የቀየረውንና ከመንጋው ለመለየት የሚጣጣረውን መርዳት፣ በድኑን ደግሞ ወደ ቀብር መሸኘት ከእንግዲህ የህዝቡ ቀሪ ስራ ይመስለኛል፡፡እዚህም ያደረሰው እሱ ነውና፡፡ወደ ኋላ የለም ነው ያለው ዘፋኙ፡፡

በቅዱስ መጽሀፍ “በትልቅም ቤት የእንጨትና የሸክላ ዕቃ ደግሞ አለ እንጂ የወርቅና የብር ዕቃ ብቻ አይደለም፡፡እኩሌቶቹም ለክብር እኩሌቶቹም ለውርደት ይሆናሉ፡፡እንግዲህ ማንም ራሱን ከእነዚህ ቢያነጻ ለክብርም የሚሆን የተቀደሰም ለጌታውም የሚጠቅም ለበጎ ስራ የተዘጋጀ ዕቃ ይሆናል፡፡” (ጢሞቲዎስ 2፣2፣20) ተብሎ እንደተጻፈው ሰው የሚለውን የወል መጠሪያ ይዘው፣ ነገር ግን ሰውን ሰው ያሰኘው ህሊናቸው እንደ ኮምፒውተር ሶፍት ወሬ በወያኔ ተቀይሮ ለአመታት በርቀት መቆጣጠሪያ እየተመሩ ከኖሩት መካከል ዛሬ ህዝባዊ ግለቱ አንጥሮአቸው እንጨትና ሽክላው፣ ወርቅና ብሩ መለየት ጀምሯል፡፡ ነገም ሌላ ቀን ነው እናያለን ገና፡፡ህውኃት-ዛሬም በጉልበት፡፡
ሰሞነኛዎቹ ክንውኖች ከምንም ነገር በፊት የደደቢት አመለካከት ካልተሸነፈ በስተቀር በኢትዮጵያ ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል ለተስፈኞች በቂ ትምህርት የሚሰጡ ይመስለኛል፡፡ ደደቢቶች ሲነሱም ጉልበታቸውን ተማምነው፣ ሀያ ሰባት አመት ሲገዙንም ጠመንጃቸውን አስቀድመው ነውና የሰለጠነ ፖለቲካዊ አሰራር አይገባቸውም፡፡እንደውም ጸረ ሥልጣን አድርገው ነው የሚያዩት፡፡በርግጥ በእነርሱም አይፈረድባቸው፤ ያንን ግዙፍና እስከ አፍንጫው የታጠቀ የነበረ የኢትዮጵያ ሰራዊት ለማሸነፍ ያበቃቸው፤በየግዜው የተነሱ የተማሪም ሆነ የፖለቲከኛ ተቃውሞዎችን ጸጥ በማሰኘት ምንይልክ ቤተ መንግሥት ያከረማቸው ጠመንጃቸው ነው፤ ከዚህ ሌላ እውቀቱም ልምዱም ተሞክሮውም የላቸውም፡፡

በደቡብ ምእራብ የሀገራችን ክፍል የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን “ከመጠረቢያ ብረት የተሰራ ጦር ወደ አቡጀዲ ቢወረውሩት ወደ ጉቶ ይሄዳል” እንደሚሉት ወያኔ ወደ ሰላም፣ ወደ ፍቅር፣ ወደ መነጋገር ወዘተ ሊጎትቱት ሲሞከር እሱ ፈጥኖ የሚያስበው በጡንቻው፤ የሚሄደውም ወደ ጠመንጃው ነው፡፡ ከፖለቲካዊ ጉዳዮች አልፎ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ውስጥ በአባ ጳውሎስ ላይ ተቃውሞ ያሰሙ ጳጳሳት ለሊት ቤታቸው እየተንኳኳ የተፈጸመባቸው ተራ የዱርዬ ስራ ይዘነጋ ይሆን ! እንቦቀቅላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ረበሹ ሲባል ፈጥኖ የሚላከው ጠመንጃ ያነገተ ወታደር እንጂ ሀሳብ የያዘ ምሁር አይደለም፡፡ የወያኔ እንነጋገር ጭንቅ ግዜን ለማሳለፊያነት እንጂ በተግባር የሚታወቀው ልክ እናስገባችኋለን ዛቻ፤ ደመሰስናቸው፣ በቁጥጥር ስር አዋልናቸው ፉከራ ነው፡፡ዛሬም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ የተባለውን ለማጸደቅ የሄዱበትን የጉልበት መንገድ አያየነው ነው፡፡ ነገም በጠቅላይ ምኒስትር ምርጫው ላይ ይሄው የጉልበት አካሄድ እንደማይደገም ተስፋ ማድረግ አይቻልም፡፡

ብአዴን -በድን፤
በርግጥ ጥሩንባ ተነፍቶ ወዳጅ ዘመድ እንባ ተረጭቶ ግብአተ መሬታቸው አልተፈጸመም እንጂ ብአዴኖች የሞቱት በመለስ ቀጭን ትዕዛዝ በአንድ ጀንበር ከኢህዴንነት ወደ ብአዴንነት የተቀየሩ ዕለት ነው፡፡ይህን የሙታን ስብስብ አሰባስቦ የሚቀብር ጠፍቶ አቶ መለስ በግሉ ሲጫወትባቸው ኖረ፡፡ ዛሬ ደግሞ የእሱ ሌጋሴ አስቀጣዮች እርስ በእርስ ያጫውቱዋቸዋል ይጫወቱባቸዋልም፡፡ በእውነቱ የብአዴን አባል የሆነ ዘመድ ወዳጅ ያላችሁ ሰዎች በእጅጉ ልታዝኑና ልታፍሩ ይገባል፡፡የህዝብ ደም የሚከረፋው፣ የወገን ዋይታ የሚሰመው እንዴት አንድ ሰው ከመካከላቸው ይጠፋል? በ1993 ዓ.ም መለስ ከጉያው የተነሱበትን ተቀናቃኞቹን ደፍጥጦና ዳግም ላይነሱ ረጋግጦ ለማለፍ የበቃው እነዚህነን ሙታኖች ተጠቅሞ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ዛሬም ህውኃት ከገባበት ውጥረት ለመውጣትና በለመደው ጉልበት ጨፍልቆ ለመግዛት እንዲበቃ እነዚሁኑ ሙታኖች እየተጠቀመ ነው፡፡እንደ ኦህዴዶቹ ( ከፊሎቹ)ብአዴኖችም ውስጥ እኔ የማሰቢያ አዕምሮ ሰጥቶ እግዜር በአምሳሉ የፈጠረኝ ሰው እንጂ የፋብሪካ ዕቃ አይደለሁም የሚሉ አስርም ሀያም ሰዎች ቢገኙ ኖሮ ህውኃት በስመ ፓርላማ ውሳኔ የግድያ ፈቃድ ባላገኘ ነበር፡፡ነገ ደግሞ ሌላ አሻንጉሊት ጠቅላይ ምኒስትር ለማስመረጥ እነዚሁ ሙታኖች እጃቸውን ያወጣሉ፡፡ ማፈሪያዎች፣ ስጋቸው የደለበ አዕምሮአቸው የደደበ ከንቱዎች፡፡( ይቅርታ ይህን የወንዝ ውኃ ምን ያጮኸዋል ከውስጡ ያለው ድንጋይ እንዲሉ ሆኖብኝ ነው፡፡) ባይገባቸው እንጂ የማሰቢያቸው ክፈል ባለመስራቱ እንኳንስ በእነርሱ በሙታኖቹ ቀርቶ ወያኔ በማንም ቢደገፍ ጀንበር አዘቅዝቃበታለች፡፡

የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን መጽደቅና የአጸዳደቁን እንዴትነት ዜና ስሰማ በተለይም ፓርላማ ውስጥ ያሉት ወያኔዎች ወደ ኋላ በመዞር ስራቸው ምን ያህል መስራቱን ሲቃኙና ብአዴኖች በጅምላ እጅ ማውጣታቸውን ስመለከት የኤርትራ ጉዳይ በሚለው የባህሩ ዘውዴ መጽሀፍ ውጥ አክሊሉ ኃብተወለድ ተናገሩት ተብሎ የተገለጸ ቃል ትውስ አለኝ፡፡

የኤርትራ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታ ድርጅት እየታየ ባለበት ወቅት የፖላንድ መንግስት የመልእክተኞች መሪን “አንተን የመሰለ የአንድ ታላቅ ታሪክ ያለው ሀገር እንደራሴ የጣሊያን አምባሳደር ምን ያህል ዝቅተኛ ግምት ቢኖረውና ምንስ ያህል ንቀት ቢያድርበት ነው ይህን የመሰለ የሀሰት ፓሮፓጋንዳ እንድታነብ ጽፎ የላከልህ፤ እኔ በጣም የማዝነው ጣሊያን የተባበሩት መንግሥታት አባሎችን ለማታለል በመሞሩ ሳይሆን አንተን የመሰለ ታሪክን የማይመረምሩ የተጻፈላቸውን ብቻ አንብበው የሚሰለፉ ደጋፊዎችን ለማግኘት መቻሉ ነው” ነበር ያሉት እኛ እውቅ ኢትዮጵያዊ፡፡

ወደ አሁኑ ጉዳይ ስናዞረው፤ አዎ በህውኃት አይታዘንም የሚሰሩት ለዓላማ ፣የሚጓዙት ከደደቢት ሲነሱ ወደ አስቀመጡት ግባቸው ነውና፡፡የሚታዘነውም የሚታፈረውም (ከዚህም በላይ የሚባል ካለ) በበድኖቹ ብአዴኖች ነው፡፡ “ሰማይ ሲደማምን ይወረዛል ገደል፣ ወተት ይሸፍታል እንኳን ሰው ሲበደል፡፡” ከሚል ማበረሰብ የወጡ ወይንም እሱን እንወክላለን የሚሉ ሙታኖች የሀያ ሰባት አመት አሽከርነት ትንሽም አልሰማቸው ብሎ ይልቁንም ተስማምቶአቸው እንደ ፋብሪካ ምርት አንድ አይነት ሆነው በወያኔ አገልጋይነት መቀጠላቸው በርቀት መቆጣጠሪያ የሚታዘዙ ዕቃዎች መሆናቸው ነው፡፡

የሙታኖች ስብስቡ ብአዴን ለወያኔ የግድያ ፈቃድ ሰጥቷል፡፡ብአዴን ሲባል ደግሞ አባላቱ በሙሉ ናቸው፡፡ ይሄ ህገ ወጥ ጸረ ህዝብ ውሳኔ አይመለከተኝም ብለው በይፋ እስካልተናገሩ ድረስ ደግሞ ውሳኔው የሁሉም የብአዴን አባላት ነውና ሞት ላወጁብን ሰዎች ዝምድናም ይቅርታም ሊኖረን አይችልም፡፡“ጠላትማ ምን ግዜም ጠላት ነው አስቀድሞ መግደል አሾክሹዋኪው ነው” እንደሚባለው ከወያኔም በላይ ቀዳሚው ትኩረት ሙታኖችን ሰብስቦ መቅበሩ ላይ ቢሆን ይመረጣል፡፡

ኦህዴድ-በፈታኝ መንገድ፡፡
ከቅርብ ግዜ ወዲህ እያወቅናቸው የመጣነው አዳዲሶቹ የኦህዴድ ሰዎች ከወያኔ ስብስብ የተለዩ ናቸው፡፡ ነገር ግን ከተለመደው መንገድ መውጣትና አዳዲስ አስተሳሰብ ይዞ መምጣት ብዙ ተግዳሮት እንደሚገጥመው የታወቀ በመሆኑ በፈታኝ መንገድ ላይ ይገኛሉ፡፡ ስለ አቶ ለማና ዶ/ር አብይ ከሚነገር ከሚጻፈው ተነስቶ እንደነዚህ አይነት ሰዎች እንደምን ይህን ያህል አመት በወያኔ ሰፈር መቆየት ቻሉ፡፡ በተለይ ደግሞ የማሰቢያ ክፍላቸው አዲስ አለም ከተማ ላይ በወያኔ ተቀይሮ ደደቢት ሰራሽ ማሰቢያ በተገጠመላቸው የእስካሁኖቹ ኦህዴዶች መመራትን እንዴት ችለው ኖሩ የሚል ጥያቄ ያጭራል፡፡ተስማምቶአቸው ወይንስ ይህን ግዜ እየጠበቁ፣ወይንስ ይህ ግዜ እንዲመጣ ውስጥ ለውጥ እየሰሩና እየተዘጋጁ፡ ነበር፤ እነርሱ ናቸው የሚያውቁት፡፡

ምንም ሆነ ምን ግን ከደደቢቶች ጋር በቅርብ ያውም በስለላው መስሪያ ቤት ዙሪያ ሰርተዋልና ሴራቸውንም ስራቸውንም በደንብ ስለሚያውቁ ወደ አደባባይ መውጣታቸው በፊት ይህን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን በቂ ዝግጅት አድርገው ሰፊ ድርጅታዊ ስራም ሰርተው ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም ፓርላማ የታየው እጅ አወጣጥ ግን ገና ብዙ የውስጥ ሥራ እንደሚቀራቸው ያሳየ ነው፡፡ በዙሪያቸው ብዙ አባይ ጸሀዬዎች እንደሚኖሩ መገመት ላለመበለጥ ይረዳል፡፡ በህውኃት ክፍፍል ወቅት አባይ ጸሀይ የሰራውን የምንረሳ አይመስለኝም፡፡ እነ ስዬና ገብሩ ከእኛ ጋር ነው ሲሉ ነው በድንገት ፊት ኋላ ዞሮ መለስ እግር ስር የተገኘው፡፡ የእነ ለማ ኦህዴድ እንደዚህ አይነት ሰዎችን በማጥራት ጥግ ማስያዝ ይዋል ይደር ሊለው የማይገባ ስራ መሆን አለበት፤አለበለዛ ወያኔ በእነዚህ ሰዎች እንዴት መጫወት እንደሚችል ያውቅበታልና መንገዳቸውን ይሰናከላል ሀሳባቸው ያመክናል፡፡

የአቶ አባ ዱላ ገመዳም ጉዳይ የዚሁ አካል መሆን አለበት፤ እለቃለሁ ካለ በኋላ ወያኔ በርሱ ሊጠቀም ያሰበውን ጉዳይ እንደ ኃይለማሪያም ስላልጨረሰ ለምኖ ይሁን አስገድዶ አስቀምጦት ይቀላምዳል፡፡የእነ ለማ አካሄድ ለምጣዱ ሲባል አይጧ ትለፍ አይነት ተገቢ ስልት የተከተለ ቢመስልም እንደ አባዱላ ያሉ ባልተጋባ ቦታ ተቀምጠው ወገንን የሚያስጠቁ ሰዎችን በቸልታ ማለፍ ግን በራስ ዱላ መደብደብን ያስከትላል፡፡ ስለሆነም አባ ዱላን በጥያቄው መሰረት በአስቸኳይ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡

በፈታኝ መንገድ ላይ የሚገኘው የእነ ለማ ኦህዴድ በአንድ በኩል ከውስጡ አባይ ጸሀዬዎችን ማጥራት፣ በሌላ በኩል የወያኔን ሴራ መጋፈጥ ከዚህ በላይ ደግሞ በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ስም የተደገሰላቸውን ጥቃት መመከት ተጋርጦባቸዋል፡፡ምንም ተባለ ምን ግን አዲሶቹ የኦህዴድ መሪዎች በሚያስተዳድሩት ክልል ብቻ ሳይሆን በመላው ኢትዮጵያና በውጪም የብዙዎችን አክብሮት አግኝተዋል፡፡ ደደቢቶች ደግሞ አይደለም ከእነርሱ ውጪ ያለ ከመካከላቸው እንኳን የህዝብ ፍቅርና አክብሮት ያገኘ ሰውን በዝምታ እንደማይመለከቱ ይታወቃልና ይህን የህዝብ አክብሮትና ተቀባይነት ጠብቆ ማቆየትም ሆነ የወያኔን ሴራ ተራምዶ ማለፍ ከባድ ፈተና ነው ፡፡ ስለሆነም ማድነቅ በግጥምና ዜማ ማወደስ እንዲህ እንዲያ አድርጉ ማለት ብቻውን በቂ አይደለምና በሚቻለው ሁሉ መደገፍ ያስፈልጋል፡፡ የምንፈልገውን የሥርዓት ለውጥ ለማግኘት እኛ በምንለው መንገድ ብቻ አሁኑኑ ከማለት ወቅት የፈጠራቸው አጋጣሚዎች ወደዛ እንዲያመሩ መስራት አርቆ አሳቢነት ነው፡፡

የወያኔ ጉለበተኝነትም ሆነ የበድኑ ብአዴን በወያኔ ደጋፊነት መሰለፍ ያመረረውን ህዝብ ሊገታው አይችልም፡፡የሚያሳዝነው የህዝቡ አምቢተኝነት ወያኔን ይህን ያህል አንበርክኮትና ፈረካክሶት እያለ ተቀዋሚ ተብዬዎች ዛሬም ከነበሩበት አንድ ርምጃ ወደ ፊት መምጣት አለመቻላቸው ነው፡፡ ስብሰባ፣ የውግዘት መግለጫ፣ ዋይታ ይብቃ ፡፡ ዛሬም እንደትናቱ ወያኔ አፈሩን አራግፎ ከመነሳቱ በፊት ነገ ሳይሆን ዛሬ ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር ተግባር ተግባር፡፡የሚችል መሰለፍ የማይችል ከማደናቀፍ ማረፍ፤ሁሉም ነገር በጉልበቱ የሚመካውን ወያኔ ለማንበርከክ፣ በድኑን ብአዴን ለመቅበር፣ ኦህዴድን ደግፎ ለሀገራዊ የሥርአት ለውጥ አዋላጅ ማድረግ ይሁን፡፡
እሰፋ ማሩ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1550
Joined: Mon Sep 12, 2016 8:47 pm

Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: Google [Bot] and 4 guests