ሰላም መርፌው
ጥያቄዎችህ ሞራላዊ እረፍት ለማግኘት የከመፈለግ መነጩ ከሆነ አጋርህ ነኝ:: በጥቅሉ እኔም እንዳንተው አዕምሮዬ አስተውሎት ሕሊናዬ መዝኖት ሊቀበላቸው የማይችላቸው በርካታ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዛት አይቻለሁኝ:: ፍጹም ሞራላዊ ነው ከሚባል ፈጣሪ በደካማው የዘመኑ ሰው ጭንቅላት እንኳን ሲታሰብ የሚዘገንን ትምህርት ሊመነጭ ይችላል ብሎ እንዴት ማሰብ እንደሚቻል በጣም ግራ ይገባኛል:: እንዳልከው አንድ ሰው አካሉ ስለጎደለ አይጠጋኝ የሚል ፈጣሪ....አንድ ፍጥሩ ያለእርሱ ፍቃድና ምርጫ ከጋብቻ ውጪ ስለተወለደ ብቻ አይጠጋኝ የሚል ፈጣሪ....ነጻ ፍቃድ ሰጥቻለሁኝ እያለ ግን እኔን የማያምኑት ይገደሉ የሚል ፈጣሪ (ለዛውም ነፍስ የማያውቁ እና ምርጫ የሌላቸውን ሕጻናትን ጨመሮ)...አይሁድን ብቻ ለይቶ የተቀረውን የሰው ዘር እንደ እቃ ለባርነት እንዲሸጥና እንዲለወጥ የሚፈቅድ ፈጣሪ....አንዱ በሰራው ሀይጢያት ዘር ማንዘር ትውልዱ የእዳ ወራሽ እንዲሆን የሚፈቅድ ፈጣሪ....ሴቶች ምንም ቢያውቁና ቢልቁ.. በአደባባይ ትንፍሽ እንዳይሉ የሚከለክል ፈጣሪ...ወዘተ..ባጭሩ በብልዩም ሆነ በአዲስ ተዘርዝሮ የማያልቅ ማንም በነጻ አዕምሮ ከመዘነው ሞራላዊና ፍትሀዊ ነው ብሎ ሊቀበለው የማይችለው ትምህርቶችን አያለሁኝ::
የሚገርምህ ግን ታዲያ እነዚህን ጥያቄ ስታነሳ ስብዕናህን መንካት, መዝለፍና መስደብ እንጂ ነጥብ በነጥብ የሚመልስልህ በምናባዊዋ ዋርካ አይደለም ከእምነት መሪዎችም ማግኘት ከባድ ነው (የግል ተመክሮዬ እስካሁን ያሳየኝ ይሄንን ነው::)!! የማይሰድቡህ ካገኘህ ትንሽ መንገድ ይሄዱ እና ከዛ ወይ ከጥያቄህ ውጪ አዕምሯቸው ውስጥ ያለውን እንደመፈክር ይደግሙልሀል ወይ አንተ የጠየከውን ሳይመልሱ ሌላ ትክክል ነገር ፈልገው ያመጡልሀል!! ስለጳውሎስ ስትጠይቅ ወንጌልን አንብብ ይሉሀል:: አንዴ የመጻህፍ ቅዱስ ጸሀፊዎች በፈጣሪ መንፈስ ተመርተው የእርሱን ፍቃዳ ነው ያስተማሩት ይሉህና.... የማያፈናፍን ኢሞራላዊ ትምህርት ሲያጋጥማቸው... አይ ይሄ የፈጣሪ ፍቃድ ሳይሆን እነ ሙሴ ለዘመኑ ህዝብ የጻፉት ትዕዛዝ ነው ይሉሀል!! አንዴ የፈጣሪ ፍቃድ ዘላለማዊ እና ሁሌም የማይቀየር ነው ይሉሁና... ከዛ ደግሞ አይ ይሄ ትምህርት በብልዩ ቀርቷል ይሉሀል:: አንዴ ኮንትኬስቱን አልተረዳህም ይሉሁና ምንም በማያወላዳ መልኩ ስታስቀምጥላቸው ደግሞ 'ይሄ የፈጣሪ ፍቃድ ነው..በቃ ሴት ትለጎም..ባሪያም ይገዛ...ቆራጣውም ከጉባዬ ይራቅ" ይሉሀል!..እንደዚህም ቢሆን የምመክርህ አዕምሮህ ሁሌ ሀሳብህን ሊያስቀይር ለሚችል መልስ ክፍት ይሁን ብዬ ነው:: በነጻነት የማሰብ ጸጋ እንዳይለይህ እመኛለሁኝ!