ፀሎታችን የት ገባ

Issues and Articles of General Interests including topics related to religion

ፀሎታችን የት ገባ

Postby ቀዳማይ » Thu Mar 20, 2014 4:54 pm

ሰላም ዋርካዊያን ሰላምና ፍቅር በያላችሁበት :: ዛሬ አስደናቂ ምስክርነት የዲያቢሎስ አምላኪ ከነበረ ሰው ይዠላችሁ መጥቻለው :: ድሮ ድሮ አባቶቻችን ፀሎታችን ከዳመና በታች እንዳይቀር ምግባራችንን እናሳምር ሲሉ ያስተምሩ ነበር :: ለመሆን ምን ማለታቸው ነው? ይሄ ትውልድ ያላወቀው ምስጢር ተገልፆላቸው ይሆን ? ታሪኩ የተፃፈው በእንግሊዝኛ ቢሆንም ተርጉሜ ላገሬ ልጆች ለማካፈል እዚህ ተገኘቻለው :: ፀሀፊውን ሆኘ ነው የምተርክላችሁ :: ሶፋችሁ ላይ ተመቻችታችሁ ወይም አልጋችሁ ላይ ደገፍ ብላችሁ ተከታተሉት:: ለነብስም ለስጋም ጥንካሬን የሚሰጥ ድንቅ ምስክርነት ::

ፀሎታችን የት ገባ በ ጃን ምሊንዲ
ተጻፈ ኖፌምበር 2000


ዛሬ ከሰይጣን አምላኪ ከነበረና በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ካገኘ ሰው ያገኘውትን ላካፍላችሁ :: መጀመርያ ይሄ ሰው ምስክርነት ሲሰጥ ለማመን እጅግ ከመቸገሬ የተነሳ እውነትነቱን ሁሉ ተጠራጠርኩኝ :: አስር ቀናት በጦምና በፀሎት ጌታን አጥብቄ ጠይቄም ነበር :: ጌታ ግን ለፈለጉት ራሱን የማይሰውር ሚስጢራትን የሚያሳውቅ የተደበቀን የሚገልጥ ቸር አምላክ ነውና ስንፀልይ በመንፈሳዊው አለም ምን እንደሚደረግ ገልፆልኛል ::

ባለ ታሪኩ የተወለደው እራሳቸውን ለዲያቢሎስ ካስገዙ እናትና አባት ነው :: ወላጆቹም ገና ከመወለዱ አስቀድሞ የሉሲፈር አገልጋይ እንዲሆን ቃል ኪዳን ገብተው ስለነበር ከመወለዱ የእርሱ ባርያና ተገዢ ለመሆን ተገዷል :: አራት አመቱ ላይ ሰይጣናዊ ሀይልን በመጠቀም ብዙ ነገሮችን ማድረግ ጀመረ :: እናትና አባቱም የሚያደርገውን በመመልከት ይፈሩትና ያከብሩት ነበር :: ስድስት አመት ሲሞላው አባቱ ለጠንቋዮች በመስጠት ልጁን እንዲያሳድጉለት ለመናቸው :: ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ከልጅነቱ ጀምሮ ጥንቆላንና ሌላም ሰይጣናዊ ምትሐቶችን እየተማረ እንዲያድግ በማሰብ ነው :: በአስር አመቱም አስደናቂ ሰይጣናዊ ምትሐቶችን እየፈፀመ በጠንቋዮቹም ሳይቀር እየተፈራ መምጣት ጀመረ ::

የረከሰን ተግባር በመፈፀምና እጁ በደምና በሃጢያት ተነክሮ ሀያኛ አመቱን አከበረ :: ከስጋውም በመለየት በመንፈስ የፈለገው ቦታ መሄድም ይችላል :: ሰይጣንም ይህንን ሰው ቤተክርስቲያንን ለማፍረስና ፓስተሮችን ለማጥቃት በሰፊው ይጠቀምበታል :: አንድ ቀን እንዲህ ሆነ ከዲያቢሎስ በተሰጠው ትዕዛዝ መሰረት አንድ ቤ /ክርስቲያንን ለማጥፋት ጉዞ ጀመረ :: ልብ በሉ ይሄ ሰው በመንፈስ እንጂ ስጋው ከቤቱ ነው ያለው :: ከጭፍሮቹም ጋር በመሆን ጥቃቱን በመጀመር ቤ /ክርስቲያኑ ውስጥ ከባድ ረብሻና ሁከት አስነሳ :: ይሁን እንጂ ፓስተሩ ተከታዮቹን ዲያቢሎስን ለመቋቋም እንዲፆሙና እንዲፀልዩ አዘዛቸው :: በዚህም የፆምና የፀሎት ግዜ ብዙሃን ንሰሀ በመግባት እራሳቸውን ለጌታ አሳልፈው ሰጡ :: ተሰብስበውም ፀሎታቸውን በመቀጠል ጌታን አጥብቀውም ለመኑት :: ይሁን እንጂ ይህ ሰው ከጭፍሮቹ ጋር እየተመላለሰ ጥቃቱን አላቋረጠም :: ጭርሱንም ሊደመስሳቸው በማሰብ ብዙ ጭፍሮችን አስከትሎ ወደዚህ ስፍራ አመራ :: በመንፈስም የቤ /ክርስቲያኑ አናት ላይ ቆሞ ጥቃቱን ጀመረ :: ድንገት ግን ሳያስበው አካባቢው በብርሃን ተጥለቀለቀና ከሰማይ መላእክተ ሰራዊት ሲወርዱ ተመለከተ :: ጭፍሮቹም መላእክቶቹን መቋቋም አልቻሉምና ተሸንፈው ሲሸሹ እሱን ግን ምንም ሳያደርጉት እጅና እግሩን ይዘው አስረው በቤ /ክርስቲያኑ በር ላይ አኖሩት :: ህዝበ ክርስቲያኑ አሁንም ይፀልያል ፓስተሩም ፀሎቱን በመምራት ተጠምዷል :: ድንገትም እንዲህ የሚል ቃል በጆሮው ሰማ (ቀንበሩ ተሰብሯል የዲያቢሎስም ጭፍሮች ተሸንፈዋል ከደጅ ያለውን ሰው ወደ ውስጥ አስገብተህ ጌታን እንዲቀበል እርዳው ) ፓስተሩም አይኑን ሲገልጥ አንድ ወጣት በር ላይ ወድቆ ተመለከተ :: ይሄ ወጣት ስጋውን ትቶ በመንፈስ ቢመጣም በሩ ላይ ግን የነበረው ከነስጋው ነበር እንዴት ስጋው ከመንፈሱ እንደተቀላቀለ እስካሁን የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ወጣቱ ይናገራል :: ድንቅ የእግዚአብሄር ተአምር እንጂ ሌላ አይደለምና :: ፓስተሩም በመገረም እየተመለከተው 'ማን ነህ ?' ሲል ጠየቀው :: በውስጡ ያሉት አጋንንትም በታላቅ ድምጽ እየጮሁ መውጣት በመጀመራቸው ፓስተሩና ተከታዮቹ ለዚህ ሰው ፀሎት አደረጉለት ::

ጌታን ተቀብሎም ከነፃ በኌላ ያለፈበትን የሕይወት ጎዳናና የሰይጣንን ተንኮል በማጋለጥ ስራ ተጠመደ : ይሄ ወጣት ዛሬ የወንጌል አርበኛ በመሆን ወንጌል እየሰበከ ስለ ጌታ እየመሰከረ እጅግ ብዙ ሰዎችን ወደ ጌታ እንዲመጡ አድርጓል :: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተመሰገን ይሁን :: እንግዲህ ይህንን ታሪክ ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ ለማመን ተቸግሬ ብዙ ቆየው :: አንድ ቀን ግን እሱ ይገኝበታል የተባለ የምሽት ጉባዔ ላይ ተገኘቼ ምስክርነቱን ለመስማት በቅቻለው :: በዛች ምሽትም ስለ ብዙ ነገር ተናገረ ስላደረገው ነገር በማልቀስ ስለተደረገለትም ምሕረትም እያመሰገነ ይሄ ወጣት ከፊታችን ቆሞ የሚደንቅ ምስክርነትን አካፈለን ::

ከሰይጣን ጭፍሮች ጋር በመሆን እርኩስ መንፈስን በአየር ላይ ይረጫሉ :: ሁሉም የስራ ድልድል ስላላቸው ይሄንን ጠብቀው በክርስቲያኖች ላይ ጦርነት ያውጃሉ :: በምድር ያሉ የሰይጣን ተከታዮች የሰይጣን ጭፍሮች ለስራ ሲወጡ አብረው በመቀላቀል ወደ ምድር ዳርቻ በመውረድ መንፈሳቸውን ያድሱና ጉልበታቸውን ያበረታሉ :: ይህም የሚወሰነው ከምድራዊው የሰይጣን አገልጋይ ጋር እንዳላቸው ቃልኪዳን ነው :: አንዳንዶቹ በምድር ሌሎቹ ደግሞ በውሃ ውስጥ ቃልኪዳናቸውን በማድረግ መንፈሳቸውን ያድሳሉ :: የሚበዛው ግን በውሃ ውስጥ ነው :: መንፈሳቸውንም የሚያጠነክሩትና የሚያድሱት የተለያዩ አይነት መስዋዕት በመሰዋት ነው:: ከመስዋዕቶቹም መካከል የሰው ደም ማፍሰስ , ጽንስን ማስወረድ መልካቸው ጥቁር የሆኑ እንሰሶችን ማረድና አፀያፊ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኝነት ማድረግን ይካትታሉ :: ወንድና ወንድ ሴትና ሴትም ሲገናኙ በማየት መንፈሳቸውን ያረካሉ :: (በነገራችን ላይ የሰው ልጆች የግብረ ስጋ ግንኘነት ሲያደርጉ መመልከት በጠንቋዮችና በእርኩስ መንፈስ አምላኪዎች ዘንድ የተለመደና ጥንታዊ የሰይጣን አሰራር ዘዴ ነው :: ከጥንትም ጀምሮ የሰይጣን ተከታዮች ይሄንን ሲመለከቱ ነበር መንፈሱ እላያቸው ላይ የሚወርደው ) ይህንንም የሚያደርጉት ቅድም እንዳልኩት ሰውየውና ጭፍሮቹ በመረጡት ቦታ ቢሆንም አብዛኞቹ ግን ሃይቆችንና ወንዞችን ይመርጡ ነበር::

እንግዲህ ወደ ገነት ከመድረሳችን በፊት ሰማይ ክፍሎች ክፍሎች ሲኖሩት የሰይጣን ጭፍሮችም በመካከለኛው ሰማይ ተቀምጠው ይጠባበቃሉ :: የክርስቲያኖችም ፀሎቶች በሶስት መልኩ በፊታቸው ይደርሳል :: አንዳንድ ሰዎች ፀሎቶቻቸን እንደ ጭስ የመሰሉ ሲሆኑ ወደ ላይ ከመቅረባቸው በፊት ከደመና በታች ተበታትነው ይጠፋሉ :: እንደነዚህ አይነት ሰዎች በሕይወታቸው ከሃጢያት ጋር የሚኖሩና ሃጢያታቸውንም ተናዘው ንሰሃ እንደመግባት በላይ በላዩ የሚጨምሩበት ናቸው :Sad(መጠጥ መጠጣት , ቂም , ጥላቻ , ሀሜት, ዝሙት ........የመሳሰሉት) ፀሎታቸው በጣም ደካማና ኮስማና ከመሆኑ የተነሳ እንደ ጠዋት ጤዛ ብትን ብትን እያለ ከደመናው ጋር ይሰወራል :: ሁለተኛውም እንደ ጭስ ቢሆንም ደመናውን ጥሶ ጠጣርና ድንጋያማ የሆነውን ሰማይ አልፎ መሄድ ስለማይችል እዚያው ተበታትኖ ይቀራል :: ይሄ አይነቱ ፀሎት የሚፀልዩት ሰዎች ደግሞ እራሳቸውን ከሃጢያትና ከመጥፎ ቢጠብቁም እምነት ግን የጎደላቸው ሰዎች ናቸው :: የሚፀልዩት ነገር እንደሚሆንላቸው የማያምኑ እምነት ቢሶች ወይም ተጠራጣሪ በመሆናቸው መጠየቅን እንጂ መቀበልን አይችሉምና ፀሎታቸው ደርሶ ደርሶ ምሽግ መስበር እንዳቃተው ወታደር ከደጃፍ እየደረሰ ይመለሳል :: (እግዚአብሄርን ስራ እንዲሰጣቸው ጠይቀውት እነሱ ግን ሲጨነቁ ያድራሉ , በጌታ ይሆናል ይፈፀማል ብሎ ልብን ሙሉ አለማድርግ ጉዳቱ ብዙ ነው :: በጌታ ልባችን ሙሉ ይሁን ምንም ነገር አይሳነውም የኛ ጌታ ) ሶስተኛው ደግሞ እንደ ጭስ ቢሆንም በእሳት የታጀበ ነው :: እጅግ ሃይለኛ ከመሆኑ የተነሳ ደመናውን አቋርጦ ሰማዩን በጥሶ የመጨረሻውን እንደ ድንጋይ የጠጠረውን ሰማይ አቅልጦ በጌታ ዙፋን ፊት ይደርሳል ::

ሚስጥሩ እዚ ላይ ነው :: ፀሎት ስንጀምር በመጀመሪያ እንደ መጀመሪያው አቅም የሌለው ይሆንና ከዚያም እንደ ሁለተኛው ይሆናል በደንብ እየተመሰጥን በስሜት ሆነን በሙሉ ልባችን መፀለይ ስንጀምር እንደ ሶስተኛው ይሆንና በእሳት ታጅቦ አድማሱን አቋርጦ እንደፈነዳ እሳተ ጎመራ እያጓራ የሰይጣን ሃይላትን እያስፈራራ ከጌታ ዙፋን ይደርሳል :: ያኔ አጠገባችን የሚቆም ምንም አይነት ሀይል አይኖርም :: የሰይጣን ጭፍሮችም ግን ፀሎታችን ሃይል እያገኘ መምጣቱን ሲመለከቱ ወደ እሳት ከመቀየሩ በፊት ከታች ከምድር ላሉት ጭፍሮች በመንገር ሊያሰናክሉን ይሞክራሉ :: ብዙ ግዜ ልብ ብላችሁ ከሆነ ተመስጠን ስንፀልይ ስልካችን መጮህ ይጀምራል :: አንዳንድ ግዜ ታዲያ ቆይ ግድ የለም አዋርቼ ወደ ፀሎቴ እመለሳለው እንላለን :: ይህንን ነው ሰይጣን የሚፈልገው አቋርጠን ስንመለስ እንደመጀመሪያው ተመስጠን ሳንፀልይ ፀሎታችንም ጉልበት አጥቶ እኛም ደክመን እናቆመዋለን :: ሌላ ግዜ ደግሞ ሽንት ቤት መሄድ እንፈልጋለን ወይም የተንበረከክንበት ቦታ አልመች ብሎን መቁነጥነጥ እንጀምራለን :: አንዳንዴም ከዚ በፊት የሌለ ውጋት መሰል ህመምም ይሰማናል :: ረሃብ ቢጤ የሚሞረሙረን ግዜም አለ :: ብዙ ክርስቲያኖች ፀሎት ስንጀምር በቀስታ እንጀምርና ሃጢያታችንን ተናዘን ይቅርታን ስንጠይቅ ፀሎታችን ወደ እሳትነት ለመቀየር ይቃረባል :: በዚ ግዜ ልብ ብላችሁ ካያችሁ ፍፁም እንመሰጣለን ፀሎቱ ይጥመናል መነሳት ይደብረናል :: ይሄኔ ነው ፀሎታችን ወደ እሳትነት ተቀይሮ አጠገባችን ሊያደናግሩን የቆሙትን አጋንንት ገርፎ ወደ መንበሩ የሚሄደው :: አባታችን ይሄኔ ደስ ይለዋል በፊቱ ሞገስን እናገኛለን ፀሎታችንም መልስ ያገኛል :: ሁላችንም ለዚህ አይነቱ ፀሎት ያብቃን ወገኖች
::............ይቀጥላል ገና አላበቃም እመለሳለው ::
ቀዳማይ
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 60
Joined: Thu May 09, 2013 6:02 am

Postby ቀዳማይ » Thu Mar 20, 2014 7:26 pm

............ ፀሎታችንን ከጨረስን በኌላ በፀሎት የከፈትነው ሰማይ ክፍቱን ይቆያል:: ከምንፀልይበትም ቦታም ተነስተን ወደ ሌላ ቦታ በምንሄድበት ግዜ እርኩሳን መናፍስት, የሴጣን ጭፍሮች, አጋንንቶች ሁሉ ከኛ ይሸሻሉ ከፊታችን መቆም ይሳናቸዋል:: ለዚህ ነው አንዳንድ ግዜ በፆምና በፀሎት የሚተጉ ቅዱስ ሰዎች ገና ሲመጡ አጋንንት ከሰው ውስጥ እየዘለሉ የሚወጡት:: እነዚህ ሰዎች ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚያደርጉትም ማሕበራዊ ሕይወት በሌሎች ሰዎች ላይ ያለው የሰይጣን ሃይል ተሰብሮ ይወድቃል:: ድግምትም ሆነ ጥንቆላ ከነዛ ሰዎች ይወገዳል:: ፀሎት የሚፀለይበት ቤትና ቦታ ላይ ድንገት ስንገኝ ውስጣችን ሰላም ሞልቶ ሲፈስ ይሰማናል:: ሰይጣን እንደነዚህ አይነት ሰዎችን አጥብቆ ይጠላል:: ከሌላውም ሰው በበለጠ መልኩ በመከታትል ሊያጠፋቸው ይሞክራል::


ይሄንን ሰው የሚናገረውን ነገር በጥሞና እናዳምጣለን አዳራሹ በፀጥታ ከመሞላቱ የተነሳ ዝንብ እንኳን ስትበር ይሰማ ነበር:: በመሀል በመሀል ለጥቂት ሰከድ ቆም እያለ ይመለከተንና ንግግሩን ይቀጥላል:: ወደ ጌታ ከመምጣቱ በፊት ምን ያደርግ እንደነበርና ያየውን በሰፊው መተረኩን ቀጥሏል:: እንዲህም አለን በፀሎታቸው ሰማይን የከፈቱ ሰዎችን ሰይጣን በተለያየ መልኩ ያጠቃቸዋል:: በመጀመሪያ ጥቃቱን ከመሰንዘሩ በፊት ግን ያጠናቸዋል ይገመግማቸዋል:: እነዚህንም ሰዎች ምልክት አድርገው አተኩረውን ማጥናት የቀን ተቀን ስራቸው ነው:: ልብ አድርጉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን በሰይጣን ተፈትኗል:: ፀሎታቸው እየበረታ የሰይጣን ሃይላት መቋቋም ሲያቅታቸው አስቀድመው ባጠኑት መሰረት የሰውየውን ደካማ ጎን ያውቃሉና ከታች ባሉ ጭፍሮቻቸው አማካኝነት መልክት በመለዋወጥ በዚ አሰናክሉት ይሄንን ሰው ላኩበት እያሉ ያጣድፉታል:: ይሁን እንጂ ሰማይ በላዩ የተከፈተ ስለሆነ ሊነኩት አይደለም ሊቀርቡት አይቻላቸውም:: ቢሆንም ግን ደካማ ጎኑን እየነኩ ይፈትኑታል የተከፈተውን ሰማይ ሊዘጉበት አጥብቀው ይጥራሉ:: ለምሳሌ ደካማ ጎኑ ንዴት ከሆነ የሚያናድድና የሚያበሳጭ ሰው ይልኩበታል:: ሰይጣንን ገስፆ ካጠገቡ ካላጠፋው በንዴት ጦፎ ክፉ ክፉ ነገር ሲናገር ወይም ማሰብ ሲጀምር የተከፈተው ሰማይ ይዘጋል ያኔ የዲያቢሎስ ጭፍሮችም በደስታ ይቦርቃሉ:: ይሄም ሰው ከንዴቱ ተመልሶ ወደ ቀድሞ ይዞታውና የቀድሞ ሰላሙን ቢፈልገው አያገኘውም ወይም እንደ ድሮው አይነት ሰላም አልሰማው ይላል:: ምክንያቱም እሱ እዚ ሲጮህና ሲጣላ ወይም በዝሙት ሲጠመድ ወይም በሃሜት ሲጠመድ እነሱ ከላይ የተከፈተውን ለመዝጋት በስራ ይጠመዳሉ:: ድንጋያማና ጠጣሩን ሰማይ መዝጋት ከቻሉ ከጌታ ጋር ያለው ግንኘነት ተቋረጠ ማለት ነው::


ለደቂቃ ስጋዊ ስሜታችን አሸንፎን ስንዘናጋ ሮጠው በሩን ይጠረቅሙታል:: ምናልባት አንዳንዶቻችሁ አይ ይሄማ እንዴት ይሆናል ሰው ስለሆንን መዘናጋታችን አይቀርም ልትሉ ትችላላችሁ:: መፅሐፍ ቅድስ ላይ እንዲህ ይላል 'የመዳንንም ራስ ቁር የመንፈስንም ሰይፍ ያዙ እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ነው።' ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6:17 አስታውሱ ጌታ ኢየሱስ እንዴት አድርገን መፀለይ እንዳለብንም አስተምሮናል:: እንዲህም ብላቸው ፀልዩ ብሎናል '........አቤቱ ወደ ፈተና አታግባን ከክፉ ሁሉ አድነን እንጂ....' ምንም እንኳን በፀሎታችን የሰማይ በሮችን ብናስከፍትም ሰው መሆናችንንና ደካማ መሆናችንን እንዳንረሳ:: በፀሎታችን ማሳረጊያም እንዲህ ብለን ጌታን አንለምነው::


ጌታ ሆይ ከፀሎቴ ስነሳ ከሚጠብቀኝ የዳቢሎስ ፈተና ሰውረኝ:: ወደ ሰይጣንም ወጥመድ እንዳልወድቅ ጠብቀኝ:: ጠላት ወጥመዱን ዘርግቶ እየጠበቀ መሆኑን ባውቅም ምን ሆኖና በምን ተመስሎ እንደሚመጣ ግን አላውቅም:: ጌታ ሆይ ደካማነቴን አውቃለው ከክፉ ነገር ሁሉ ትጠብቀኝ ዘንድ ባንተ እታመናለው:: እግሮቼ ወደ መጥፎ መንገድ እንዳይሄዱ አንተ በመንገዴ ሁሉ ቅደም:: በሕይወቴ ጣልቃ ግባ ከቶ ብቻዬን አትተወኝ:: አሜን:: ታላቁ ጌታ እግዚአብሄር ፀሎታችንን ይሰማል ከክፉም ይጠብቀናል:: ክፉ ነገር ሲያጋጥመን ክፋቱን ስንረዳና የሰይጣን ተንኮልን ሲገለጥልን ጌታን እናመስግነው 'ጌታ ሆይ አመሰግንሃለው' እንበል:: እንዲህም ተብሎ ተፅፏልና 'በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና' 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5:18 አንዳንድ ግዜ አሳዛኝና አስጨናቂ ውኔታውስጥ ልንወድቅ እንችላለን ይሁን እንጂ ጌታ ይሄንን ያደረገው ለምን እንደሆነ አናውቅም ከከፋ መከራና ከዲያቢሎስ ጥቃት እየጠበቀን መሆኑን ግን ስናውቀው እናመሰግነዋለን:: ጉልበታችንም እየበረታ ሲመጣ በእግዚአብሄር ፍፁም መታመንን እንማራለን:: በሁሉም ነገር እናመሰግነዋለን:: የሰማይ ደጆችን በፀሎታችን ስናስከፍት ሁሌም ፀሎታችን በፍጥነት ይመለስሉናል:: ይሁን እንጂ አንዳንድ ግዜ ፀሎታችን ወደ እኛ ላይደርስ ይችላል ለምን ይሆን? ባለ ታሪካችን እንዲህ ብሎ ያስረዳናል
..........ይቀጥላል::
ቀዳማይ
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 60
Joined: Thu May 09, 2013 6:02 am

Postby ቀዳማይ » Fri Mar 21, 2014 8:27 pm

......መስካሪያችን ምስክርነቱን ቀጥሏል:: እኛም እንሰማለን እናንተም ከኔ ጋር ናችሁ ጌታም ከኛ ጋር ነው:: የሚቃወመን ሰይጣን በክፉ አይኑ እየተመለከተ ከስር ከስራችንና በላያችን የሚያንዣብበው የሰይጣን መንፈስ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተሰበረ ይሁን:: አሜን::

ጆሮ ያለው ይስማ እንሆ እቀጥላለው:: መስካሪያችን በስተመጨረሻ የተናገረው ነገር እጅግ የሚገርም ነገር ነበር:: እንዲህም አለ:: የሰው ልጆች በተለይ ክርስቲያኖች የሚያገለግሉን መላእክት አሉን:: ስንፀልይ ፈጣሪ በዙፋኑ ይሰማንና መልሱን በመላእክት እጅ ይልክልናል:: የጹሑፌም ምስጢርና አላማ ወዲህ ነው:: መላእክትና ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ግንኘነት አላቸው:: ልብ በሉ መፅሐፍ ቅዱስ ላይ እንዲህ ተብሎ ተፅፏል:: 'እንግዲህ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፥ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ፥ በሰላም ወንጌልም በመዘጋጀት እግሮቻችሁ ተጫምተው ቁሙ፤' ::ወደ ኤፌሶን ሰዎች 6: 14-15 ወገኖች ይሄን የፅድቅ ጥሩር ነው ለፀሎታችን መልስ ትልቅ ሚና የሚጫወተው:: መልእክቱን የሚያመጣው መላእክት የሚለብሰው በኛ እምነት መሰረት ነው:: ወደ እኔ የሚመጣው መላእክትና ወደ እናንተ የሚመጣው መላእክት እኩል አይለብሱም:: የሚፀልየው ክርስቲያን ከላይ ለጠቀስነው መንፈሳዊ ትጥቅ ግድ የማይሰጠውና የማይከተለው ከሆነ መላእክቱ ካለ ምንም ትጥቅ ነው ወደ እሱ የሚመጣው:: ግማሹን ተከትሎ ግማሹን የማይከተል ደግሞ መላእክቱ ያልተሟላ ትጥቅ ለብሶ ነው የሚመጣው:: ለምሳሌ አለ መስካሪያችን,.. በጭንቅላቱ ለሚያስበው ነገር የማይጭነቅና ለመቆጣጠር ምንም አይነት እርምጃ የማይወስድ ሰው መላእክቱ ወደ እርሱ ሲመጣ የራስ ቁር አይኖረውም:: መላእኩ ወደ እሱ በሚመጣ ግዜ ከታች ያሉት የሰይጣን ጭፍሮች በደንብ ያስተውሉታል:: መላእክቱ በደንብ የተሸፈነ ከሆነ ሃይለኛ ስለሚሆንባቸው አይቀርቡትም ምንም ትጥቅ የሌለው ወይም አንድ ሁለት ነገር የጎደለው ከሆነ ወዲያውኑ ማጥቃት ይጀምራሉ:: ለምሳሌ የራስ ቁር እንደሌለው ከተመለከቱ ወዲያውኑ እራሱ አካባቢ ጥቃት ይጀምራሉ:: ጫማ ከሌለው እግሩን እግሩን በእሳት ያቃጥሉታል:: ተሳክቶላቸው መላእኩን ማሸነፍ ከቻሉ ሮጠው የያዘውን ነገር ይቀሙታል:: አላማቸውም ይሄ ነበርና:: ለምን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ከመስጠቴ በፊት ይቺን የመፅሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላስታውሳችሁ:: 'በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው....." የያዕቆብ መልእክት 1:17 እንዴ! እንግዲህ በጎ ነገር ሁሉ ከላይ ከመጣ ሰይጣን ለወዳጆቹ ከየት እያመጣ ነው የሚሰጣቸው:: ወገኖቼ ሰይጣን የሚሰጣቸው ነገር ሁሉ ከደካማ ክርስቲያኖች እየነጠቀ ነው:: እስከመጨረሻው ፀንተው ከማይፀልዩ ክርስቲያኖች:: ከላይ እንዳልኩት ከመላእኩ የፀሎታችንን መልስ በመቀማት ለራሳቸው ሰዎች ይሰጡታል:: 1ኛ ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 5:17-18 እንዲህ ተብሎ ተፅፏል 'ሳታቋርጡ ፀልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና።' ኢየሱስ ክርስቶስ በተቀመጣችሁበት ቦታ ያገናችኌል ወይስ ተስፋ ቆርጣችሁ ፀሎታችሁን ሰይጣን እንዲሰርቀው ታደርጋላችሁ?:: እነኘሁ የሰይጣን ጭፍሮች መላእኩን በመቀማት አይመለሱን ደጋግመው በማጥቃት ከተሳካላቸው እንደ እስረኛ አድርገው ያቆዩታል:: ይሄ ሲሆን ክርስቲያኖች በየቦታው ያለ ርህራሄ ይጨፈጨፋሉ ጠላት ይሰለጥንብናል:: ለማመን እጅግ ከመቸገሬ የተነሳ እንዲህ ብዬ ጠየኩት 'እንዴት መላእክት በሰይጣን ሃይላት ሊሸነፉ ብሎም ሊታሰሩ ይችላሉ' ብዙ አስረው አያቆዩትም በአካባቢ የሚኖሩ ክርስቲያኖች መፀለይ ሲጀምሩ መላእክት ከሰማይ ይወርዱና የታሰረውን መላእክ ያስለቅቁታል:: ልብ አድርጉ ይሄ ሰው ያየውን እያካፈለን ነው:: በአካባቢው ግን የሚፀልዩት ክርስቲያኖች ፀሎታቸው የሰማይን በሮች መክፈት ካልቻለ በእስር ያቆዩታል:: ሰይጣንም ያኔ የብርሃን መላእክት መስሎ ወደ ሰውየው ይሄዳል:: በዚህም የተነሳ ሰዎች, የተሳሳተ ራእይ ያያሉ, የተሳሳተ ትንቢት ይናገራሉ, የተሳሳተ ፓስተር ይነሳል, ህዝቡንም ወዳልተፈለገ መጥፎ አቅጣጫ ይመራዋል::

የማታውን ጉባዔ ጨርሰን ስንወጣ ጭንቅላቴ በጥያቄ ተሞልቶ እጅግ ተጨንቄ ነበር ቤቴ የደረስኩት:: አስር ቀናትም በመፆምና በመፀለይ ጌታን በመጠየቄ ጌታ የነገሩን እውነትነት መግለጥ ብቻ ሳይሆን ነገሮችን በተለያየ አቅጣጫ እንዳይ አድርጎኛል:: ወገኖች በፅድቅ እንመላለስ እራሳችንን ከሃጢያት እናድን የሰይጣን መሳሪያና መጠቀሚያ እንዳንሆን እንጠንቀቅ:: የፅድቅን ጥሩር ልበሱ ጌታ ለኛ እንዲዋጋ እንፍቀድለት:: ጌታ ስሙ እንኳን አጋንንትን ያስፈራራል አይቀርቡንም የኝ ጌታ የሃይለኞች ሁሉ ሃይለኝ ነው:: ልባችንን ከከፈትንለት መንፈስ ቅዱስ ይመራናል:: አንዳንዴ ተነስና ፀልይ ስንባል እናመነታለን እንቅልፋችን ይበልጥብናል:: ነገ ፁም ሲለን ሰበብ አንፈልጋለን:: የመንፈስ ቅዱስን ምክር ችላ ማለት በሕይወታችን ትልቅ ችግር ያመጣብናል:: ምክንያቱም መንፈስ ቅዱስ እኛ የማናየውን አይቷልና እያዘጋጀን ስለሆነ ከመፀለይና ከመፆም አንቦዝን:: በተለይ በተለይ በቅድስና ለመፆም እንሞክር:: የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ፀቃ ከሁላችን ጋር ይሁን::አሜን::


ዋርካ እኔም ጨርሻለው:: ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ ሰላምና ፍቅር ይብዛላችሁ በሰይጣን የታሰራችሁ በጥላቻ የታወራችሁ, በቂም ለምትሰቃዩ ወደ ጌታ ፊታችሁን አዙሩ የማያልቅ ሰላም በልባቹ ይፈሳል:: ስለተከታተላችሁኝ አመሰግናለው:: ጌታ አብዝቶ ይባርካችሁ:: አሜን::
ቀዳማይ
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 60
Joined: Thu May 09, 2013 6:02 am


Return to Warka General

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 6 guests

cron