የዋናው አቁማዳ==>ሸራ ስላልወጠርኩ

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ዋናው » Mon Jun 27, 2011 11:57 am

ይድረስ ለናቴ


እትዬዋ ይሄንን ደብዳቤ ስጥፍልሽ ያዩኝ እዚህ ከሃገሬው የተመሳሰሉ ሃበሾች በሳቅ ሆዳቸው ንፍር ነው ያለው:: በዚህ ዘመን ብህር ከወረቀት አገናኝቶ ደብዳቤ ሚጥፍ ሰው ማየት ብርቅ ነው አሉ:: ሚገርመው ገጠር የኮምፕተር ደብዳቤ መነበብ እንደማይቻል ሊገባቸው አለመቻሉ ነው::

እስቲ ተያቸው ስለነሱ ኋላ እመለስበታለሁ... አንቺ እንዴት ነሽ? ይሄው እንግሊዝ ኣገር ከገባው የፊታችን ባለግዚያር ለት ሁለት ወር ሊሞላኝ ነው እንዲያው የናንተ ናፍቆት ደርሶ ትክዝ እያደረገኝ መቆዘሜን ያዩ ሃገሬዎቹ ድፕሪሽን ይዞክ ነው እያሉ እንደወንጀለኛ በጥያቄ ያደክሙኛል... እትይዬ አንቺ እንዴት ነሽ? መቼም ይሄ በልግ ሲመጣ ያ አስምሽ ተነስቶ ያሰቃይሻል እያልኩ ሁሌ ነው ማስብ... እስቲ ባይሆን ወቅቱ እስኪቀየር ትልቋ እማማጋ ሂደሽ ክረሚ... የኔ ነገር ዳሩ ከብቶችን ለማን አደራ ብለሽ...? ጊደሬ እንዴት ነች? አደገች? የጋሽ አምሳሉ ኮርማ እንዳይደፍርብኝ አደራ እትይዬ...
እስቲ ስለኔ ላጫውትሽ ... አየ ፈረንጅ ሃገር... ምን ጉድ ነው እትየዋ....? ገና ቀትር'ኮ ነው ሚጨልም... ፈጣሪ ምን ሲል ጀምበር እንደሰሰተባቸው? በዚህ ላይ ውርጩ ክምር ልባሽ ተሸክሜ ውዬ ክምር ብርድ ልብስ ሰሸከም ተኝቼ ይነጋል ጠአይቱን እዚህ ከመጣው ሁለት ቀን ነው ያየዋት እሱንም አየዋት አይባልም እንደ እጅ ባትሪ ብልጭ ብላ ጥፍት ነው ያለችው እረ እስቲ ለብርዱ ሠው ከተገኘ ጥሩ ካቲካላ ስደጂልኝ
እዚህ ካየር መሳፈሪያው ወርጄ ጆሮዎቼ በነጎድ እንደነጎሉ ጓዜን ይዤ ስቅበዘበዝ የጋሽ አዘነ ወንድም ልጅ ደርሶ ተቀበለኝ ብረሓኑ ነው ስሙ ባለንጀሮቹ ግን ቡርኖ እያሉ ነው 'ሚጠሩት እንዴት ያለ ደግ ሠው:: 15 ዓመት ሙሉ ታክሲ ሲሾፍር ነው የኖረ ግን ክፉ ሚስት አለቸው መቼም እሱ አሟልቶ አይሰጥ... እና እልሻለሁ በማግስቱ እጅ ስጥ ብሎ ቢያማክረኝ... እኔ ያንቺ ልጅ ዘራፍ አልኩልሻ ዘርማንዘሬ አዳፍኖ ላሶጣው ነጫጭባ ደጁ ድረስ መጥቼ እንዴት እጅ ልስጥ ብዬ ዘራፍ አልኩልሽ.... ኋላ ለካስ ነገሩ ሌላ ነው... እዚህ ሃገራቸው እንድቀር መላው ሂዶ ለነሱ የውሸት ማልቀስ ነው... እትይዬ... እስቲ ባክሽ የነፍስ አባትሽ አባ ወ/ዮሓንስ ጋር ሂደሽ ይቅር ይለኝ ዘንድ አስለምኝሊኝ... መቼም የዋሸዉት ውሸት እትይ... መቼም አስተርጓሚ ተብዬው ሳያውቅብኝ የቀረ አይመስለኝም...
መልሱ ለትንሳሔ አካባቢ ነው ሚደርሰው ብለዉኝ እየጠበቅኩኝ ነው:: እስከዛው ጎተራ ምታክል ክፍል ሰጥተዉኝ እዛ እኖራለሁ ግን ጸአዳ ነው ምግባቸዉን ግን ልለምደው አልቻልኩም እሳት ያልመታው ነጭ እንቁላል ንፍሮ ከመሰለ ነገር ጋር እየሰጡኝ ወስፋቴ ዝግት ብሎልሻል 'ንዲያው ለአጭ ለአጭ'ኮ ነው 'ሚለው ይልቅ ብረሓኑ እየመጣ አንዳንድ ጊዜ ያገሬ ምግብ ያለበት ሆቴል ወስዶ ይጋብዘኛል... እንጀራቸው ንጣቱ እንደበረዶ ነው ማባያዉን ግን ብዙም አልለመድኩት ብቻ ከምኖርበት ቤት ምግብ ይሻላል:: እትዬዋ ሳልረሳው ልንገርሽማ እዚህ ሃገር ከመጣው ዶሮዎቹን ፈጀዋቸው አልኩሽ: መቼም የዶሮ ግፍ ካለ እኔኑ ፈንግል ይዞኝ ፍንግል እንዳልል ፈራው አንዳንዴ ለኪስ ብለው ከሚሰጡኝ ሳንቲም ሁቴል ሄጄ በወረቀት ቁና ሙሉ ዶሮ ገዝቼ እበላለው... የብዛቱ ነገር ተዪኝ... በዚህ ላይ ብቻዉን ነው 'ሚበላው ሽንኩርት የለ በርበሬ የለ አንዳንዴ እንደገንፎ አፍ ውስጥ ከሚላወስ ድንች ጋር ይሰጡኛል

የመሳፈሪያዉን ነገር አታንሺው እንደቤታቸው ባለፎቅ አውቶብስ አላቸው እሱ ላይ መስታወቂያ ነገር ሹፌሩ መዘውር ላይ እያስነካን ነው ምንሳፈር አያምኗቸዉም መሰለኝ ሳንቲሙን ሌላ ቦታ ነው ምንከፍል ታዲያ ተንደርድሬ ፎቅ ላይ እወጣና ከተማይቱን ቁልቁል እየቃኘው ስዞር ይመሻል ሹፌሮቹ ከውካዋ ቢጤ ናቸው ተሳፋሪ መቀመጫ ሳይዝ ስለሚያበሩ ስንት ቀን የፈርንጅ አሮጊት ላይ ወደቅኩ መሰለሽ? ደግሞ አሉ እዚህ ሃገር ሰው መንካት ነውር ነው አንድ ቀንማ አንዷ እንደቄብ ዶሮ ስታስካካብኝ ግንፍል ብሎኝ አደብ ግዢ ብዬ በቋንቋዬ ዘራፍ አልኩባታ... መቼም ያንን ውሸት ያስፈታልኝ ተርጓሚ አግኝቼው ቢተረጉምልኝ አጥንት ሚነካ ስድብ እንደሰደበችኝ ቀልቤ ነግሮኛል
የባቡሩን ብዛት አታንሺው እትይዋ... ሃገሩን ቀፎ አስቀሩትኮ እንደፍልፈል ከስሩ ፈልፍለው ፈልፍለው ደግሞ ሲበሩ እንደጥይት ነው::

እትዬ አሁን ቋንቋ መማር ጀምሪያለው ሃገሬ እስከ5 የተማርኩት ጠቅሞኛል ብቻ ያስተማሪዋ አፍ አልያዝ አለኝ እንጂ መጻፉንስ ደሕና ነኝ ሁለት መንፈቅ ከተማርኩ የነብርሓኑ ዓይነት አፍ እንደማወራ ተስፋ አለኝ:: ቋንቋ ተማሪ ቤት ስሄድ መንገድ ላይ ያገሬን ልጆች ሳይ እጅ ነስቼ ሰላምታ ስሰጣቸው ልክ እንደጸበኛ ገላምጠዉኝ ያልፋሉ ካንድም ሁለቴ ብረሓኑን ምነው ሰው ሃገር ፍቅር ነሳን ብዬ ጠየቅኩት... "እዚህ ሃገር 'ማታውቀዉን ሠው ሠላም ማለት ነውር ነው" አይለኝም እረ እውቅና ይንሳቸው እትዬዋ ምጽዋት አልጠየቅኩ አሳድሩኝ አላልኩ የግዜር ሰላምታ ማንን ገደለ?
አንድ ቀን ደግሞ የማሪያም ንግስ ቀን ብረሓኑ ቤተስኪያን ይዞኝ ሄዶ ሕጣናቱ ሁሉ ሂሳብ መደመሪያ ማሽን መሳይ ነገር ይዘው ነፋስ እንደሚወዘውዘው ዛፍ ግራ ቀኝ ዘመም ሲሉ ይውላሉ በዚህ ላይ ስጋዎ ደሙን ሲቀበሉም ያቺ ማሽን ከጃቸውና ካይናቸው አትነቀልም... ክብረ-በዓሉ አልቆ ምዕመናኑ ሲበተን የኮረዶቹን አለባበስ አይቼ ማሪያምን ይቅር በዪኝ ብዬ ከደጇ ተመለስኩ... እትይዬ መሰልጠን እንዲህ ነው'ንዴ?

መቼም ብዙ አወራሁብሽ ምን ላድርግ እዚህ ከመጣው ከልብ ያዋራዉት ሰው የለም ሁሉም ወተት እንደጣደ ጥድፍ ጥድፍ እንዳለ ነው... የብርሓኑ ባለንጀሮች ቤት አንድ ሁለት ቀን ሄጄ ነበር ሙሉ ቤተ-ሰብ ተኳርፈው ቴሌቭዢን ላይ ያፈጣሉ ዓይኖቻቸው ከቴሌቭዢን ሲነቀሉ ልጆቹ ቅድም የነገርኩሽ ነገር ላይ ... አዋቂዎቹ ደግሞ ስልኮቻቸው ላይ አንገታቸዉን ይደፋሉ:: እትይ ከምር ሰው ከሰው ማያወራበት ምድር'ኮ ነው የመጣዉት::
ሳልረሳው ላውራልሽማ... እዚህ ሃገር ሚሽቲቱ ሶፋ ላይ ጥፍሯን እያሾለች ባልየው ማጀት ገብቶ ዓይኖቹ በሽንኩርት ያነባሉ... ተደብቄ "አበስኩህ ገበርኩህ" ብዬ አማተብኩኝ::
በይ እስቲ ልተዉሽ እትይዋ... ለሚቀጥለው እኔም ካገሬው ሃበሻ ጋር ለመመሳሰል በዛዉም ቋንቋዉን ለማወቅ በጉራማይሌ እጥፍልሻለው እስከዛው ሰላም ሁኚ ከዘመድ እስከ ጎረቤት ሳሚልኝ:: ብዙ ምታዋራ ካርድ ብረሓኑ ሲጠቁመኝ አዲሳባ እነአንዳርጌ ጋር ደውዬ ድምጼን አሰማለሁ::

ሰላም ሁኚ ውይ ዬኔ ነገር ብረሃኑ ሰው ሲሰናበት "ችርስ" ነው ሚባል ብሎኝ ነበር


ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2804
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby እአምሮ » Tue Jun 28, 2011 11:59 am

ዋናው:

እጅግ ድንቅ ደብዳቤ ነው:: ባላገሩ ወገናችን ጥሩ ታዝቦናል::

በርታልንና ደግሞ በመጽሀፈ መልክ አቅርብልን::

አድናቂህ
እአምሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 256
Joined: Mon Apr 12, 2004 12:35 pm

Postby ዋናው » Fri Jul 08, 2011 12:03 pm

አመሰግናለሁ አእምሮ
አርብ ኦገስት 5 የባለፈው ፕሮግራም አለን ከተመቸህ ብቅ በል::
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2804
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Re: የዋናው አቁማዳ==>ሸራ ስላልወጥርኩ (ክፍል 1)

Postby ዋናው » Sun Nov 20, 2016 2:16 pm

ሸራ ስላልወጥርኩ (ክፍል 1)
ንሁስ ርዕስ (ሌሊት ጀምበር አለ)

ሠፈሬ ነው ያልሁት
ኣዲሳባ ትላልቅ የኮንክሪት ጥርሶች ኣብቅላ ስቃ ተቀበለችኝ ጎርምሳ ነው መሰለኝ ጠረንዋ ተቀየሯል ከተማይቱ በግራጫ ቀለም ቡዝዝ ብላለች
ሰፈሬ እንደደረስኩኝ ልጅነቴን ሚያስታውሰኝ የዓይን ትዝታ ለመሻት ያህል ቆም አልኩኝ ግን ምንም አላገኘሁም እናም ያጣሁትን ት ዝታ ‘ማሰፍርበት ሸራ ስላልወጥርኩ ብሩሽ ስላላራስኩ ቃላት ፈላልጌ ስንኝ ቋጠርኩለት
በቀዳዳ ካልሲ ኳስ የሰራንበት
በበረኪና ዋንጫ የርግብ ያዜምንበት
ሌባ ፖሊስ ብለን የተሯሯጥንበት
በርግጫ ተዛለን የቆሳሰልንበት
የለም ያ… አሁን
ታርሷል ያኛው ዳገት።
-ሜዳው በኮብልስቶን
ዛፉ በቆርቆሮ
-ጣሪያው በዲሽ መንጋ
ለጉድ ተቀይሮ
-በአባሮሽ ሽሽት
የሮጥንበት ጓሮ
-ለባቡሩ ሃዲድ
ቁልቁል ተቆፍሮ
የለም ያ ትዝታ
ሕልም ሆኖ’ም አይፈታ
-እንኳን እኔ መጤው
ካገሩ ለራቀ
-እነሱም ረስተዉት
“ነበር እንዴ?” ብለው
ቅንድብ አጠጋግተው
ተገርመው ጠየቁ
ባጣውት ት ዝታ የሹፈት እየሳቁ
ድሮ
-እንግዳ ሲያንኳኳ
ማነው ሚባልበት
-ቆጣሪ ሲመጣ
ውሻ ምናስጮህበት
ያ ሰ…ፊ ጊቢ
-አሁን ደረጃ ሆኗል
ችፍግ ፎቅ በቅሎበት
-ጊቢ አልባ ነዋሪ
ተጎረባብቶበት

-ሳልሸኘው ላጣሁት
ለጥንቱ ት ዝታ
-ሙሾ ማውረድ አምሮኝ
እዘገምኩ በማታ
-ወንድሞቼን ይዤ
ገባሁኝ መሸታ

-ጠርሙስ ውስኪ ከበው
ወፍራም ሳቅ ሚስቁ
-የጮማ ውላጅ ቦርጭን
በሸሚዝ ያነቁ
-ቆነጃጅት ሴቶች
መሃላቸው የሸጎጡ
-ጥቂቶች ነበሩ
በሌላው ያፈጠጡ

ከውጪ

ድቅድቅ ያለ ሌሊት ነው፣ ግን ፍንትው ያለ የሌሊት ብረሐን ጎዳናው ላይ ፈሷል ጨረቃይቱ ያዲሳባን ጉድ ብቻ ለማየት የጓጓች ይመስላል።
በብርቱካናም ረጃጅም መብራቶች ሕልም ከመሰለው የመኪና መንገድ ላይ ፫ የምሽት ንግስቶች ተርታዉን ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመዋል። ግማሽ እርቃናቸውንና ግማሽ ገበናቸዉን ለጨረቃ እያስሞቁ የጭን ወደአፍ እንጀራቸዉን ይጠባበቃሉ። የመኪናው መንገድ መሃል ላይ አንዲት ጥቁር ውሻ ፫ ቡችላዎቿ በመኪና ተገጭተውባት አምርራ ታለቅሳለች ገጪው ግድ አልነበረዉም የመኪና ጎማው ያጠቀሰዉን ትኩስ ደም እያሰመረ ቁልቁል ከንፏል። ይሄኔም ባደረገው ነገር በድል ኣድራጊነት በስካር የታጀበ ሳቅ እየሳቀ ነው።
ከምሽት ንግስቶች አንዷ ልጆቿን ባጣችው እናት ውሻ ሃዘን እርሷም ልቧ አዝኗል፤ ትኩር ብዬ ሳያት የራሷን ሃዘን በመስታወት ምታይ ሁሉ መሰለኝ።.
.
.
እናም ለዚህ ቅኔ ምሽት ቀለም የማጎርሰው ሸራ ወጥሬ ስላልነበረ አጭር ስንኝ እንዲህ ቋጠርኩለት

ሌሊት ጀምበር አለ::
ኳክብት ቆጥሬ
-ጠንቁየም ባላውቀው
ሌሊት ጀምበር አለ
-ተረኛው 'ሚሞቀው
አዎ ቀን ግፊያውም በርክቷል
አጫጭር እግሮችም 'ሚቆሙበት ጠፍቷል
ረጃጅም እጆች
-አጫጭሩን ጋርደዋል::
ረጃጅም ጩእቶች
-በግሳት ተውጠዋል::
እናም
ጠዋት ከሰዓት ተብሎ
-በእርከን የማይለካ
ሌሊት ጀምበር አለ
-ለሟቂው 'ሚበቃ
አዎ ሌሊት እንጀራ አለ
በቀን ትርፍራፊ ተፈጭቶ 'ሚቦካ
ስጋ ስጋን በስጋ አባብሎ
ለስጋው ሲል ያድራል
ሙዳ ተንተርሶ ያንን ዓለም ጥሎ
ቀን የተዘጉ በሮች
-ሌቱን ያለእፍረት ተከፍተው
ፀሓይቱን ተሽኮርምመው
ጨረቃ ላይ ፈጠው
ሙቀቱን ደርበው
ብርዱን ተገላልጠው
አዎ ይታያሉ
የራሳቸዉን ጀምበር ፈጥረው::
ለጠጪው ጠማቂ
ላናቂው ታናቂ
ለናቂው ተናቂ
ላለቃው እላቂ
እንዳለ ሁሉ
ልግደል ብሎ ለወጣም
-ለሞታቸው ንግስና ያልደገሱ ብዙ ሟቾች አሉ
በራሳቸው ጀምበር
-ጥቁር ጥላ የጣሉ::
ቀን የሰቡ ቦርጮች
ሌቱን ሳያንኮራፉ
የጎፈየ ሕልውናን
ባልኮል ሲያንሳፍፉ
ጨለማን በሐር አድርገው
በስሜት ሲቀዝፉ
ጀልባ ሆኖ ያሳፈራቸው
ጊዜን መሻገሪያ
የእሕቶቻቸው ሕልውና መሆኑ ተስኗቸው
ሲያቃስቱ ያድራሉ
ግሳት አልቆባቸው።
.
.
.
ያቺ ጥቁር ውሻ
-ወደ ሰማይ ጮወች
ልቧ ባዘን ደምቶ
-ወደምድርም ጮወች
ግራ ቀኙን አይታ
-አልቃሽም ፈለገች
እሷው ወላጅ
እሷው ቀባሪ
እሷው ሃዛኝ ሆና... ብቻዋን ሮጠች::

(ከደርሶ መልስ ማስታወሻ)
2014

ዋናው
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2804
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Re: የዋናው አቁማዳ==>ሸራ ስላልወጠርኩ

Postby password » Tue Nov 22, 2016 2:15 am

". . . ለጠጪው ጠማቂ
ላናቂው ታናቂ
ለናቂው ተናቂ
ላለቃው እላቂ
እንዳለ ሁሉ
ልግደል ብሎ ለወጣም
-ለሞታቸው ንግስና ያልደገሱ ብዙ ሟቾች አሉ
በራሳቸው ጀምበር
-ጥቁር ጥላ የጣሉ::. . . "


ዋናው፥ ሰላም ነህ? ወዳጄ
ይህን ግጥምህን ስንቴ ደጋግሜ እንዳነበኩት ኣላውቅም ። ወደ ፊትም ኣነበዋለሁ። ግጥም እንደ ልቦለድ ኣንዴ ተነቦ የሚተው ሳይሆን እንደ ሙዚቃ ደጋግመው ሲያነቡት የባስ እየጣመ፥ ሚስጥሩም እየተገለጠ የሚሄድ ነው።
ከኣቁማዳህ ኣውጥተህ ስላስኮመከምከን ምስጋናው ይድረስህ። ብዕርህ ሆነ ብርህ ኣይንጠፍ!!!

ፓስ
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Re: የዋናው አቁማዳ==>ሸራ ስላልወጠርኩ

Postby ዋናው » Wed May 22, 2019 11:02 pm

ፓስወርዴ እንዳልጠፋብኝ ለማወቅ ያህል ተዘግቶ የከረመ ቤቴ ውስጥ ሳላማትብ ገባው
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2804
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Previous

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 3 guests