የእብዱ ማስታወሻ=> (ልቦለድ)
እዚህ ከተማ ውስጥ ሀያ ሦስት ዓመት ሲኖር ያተረፈው ቢኖር ዕብድ የሚለዉን ስም ብቻ ነው ይጠጣል ያነባል ይተኛል... የራሱ ማሕበረሰብ አግልሎታል የተዋሰው ምድር ሕዝብ ደግሞ ንቆ ትቶታል::
የማትበረክተዋ የለንደን በጋ ሙቀቷን የብርቅ ያህል ለቃዉ ሰዉ ሁሉ ራቁቱን ነው::
''እስቲ ፓይንት ግዛልኝ...''
አለኝ ብብቱ ስር አጥፎ ያቀፈዉን መፅሔት ጠረጴዛው ላይ ወርወር አድርጎ: በዓይን እንተዋወቅ እንጂ ተነጋግረን አናውቅም ሁሌም ፈገግ ሲልልኝ የሲጋራ ሚጠይቀኝ እየመሰለኝ ኪሴ ስገባ ፈጥኖ ይሸሸኛል
''ቁጭበል''
አልኩት ጠረጴዛው መሀል የተተከለዉን የፀሐይ ዣንጥላ አጮልቄ ፊቱን እያየው : ተቀመጠ::
''አናግረህኝ አታውቅም...''
አልኩት ፈገግ ብዬ
''አንተም እንደሌሎቹ ሃበሾች ከንፈርህን ምትመጥብኝ ስለሚመስለኝ ይሆናላ...''
አለኝ:: ሲጋራ ካጠላቸው ከናፍርቱ መሀል ፈገግ ሲል ብልጭ ያሉት ጥርሶቹ እንደጠበቅኳቸው ያህል አልነበሩም ይልቅስ ፊቱን ደስታ ሊሞሉት የተቃቀፉ ይመስላሉ
''ሌሎች ሃበሾች ከንፈሮቻቸዉን ይመጡብሀል...?''
አልኩት ከመጠጥ ቤቱ ውስጥ ያመጣዉለትን የስቴላ ፓይንት አቀብዬው
''መምጠጥ ብቻ.... አንዳንዴ ሳልሞት የሬሣ ሁሉ ሚያዋጡልኝ ይመስለኛል ...
አለኝ ባንድ ትንፋሽ ሩብን ያህል አጋምሶለት
''አንተ ያገርህን ሠው አትቀርብም እንዴት ይህንን ልትገምት ቻልክ እንዲያዉም ዛሬ ባማርኛ ስታዋራኝ ገርሞኛል...''
''ያገሬ ሠዎች ባስፈለጉኝ ጊዜ አልደረሱልኝም ፍቅር በፈልግኩበት ጊዜ ሠላምታ እንኳን ነፈጉኝ... ግን አሁንም ቢሆን ከነጩ ፈገግታ እና ይውሸት ፍቅር ያገሬ ኩርፊያና መጠየፍ ይሻለኛል... ለምን ይሄንን እደምልህ ግን ታውቃለህ...?''
መልስ ከኔ እንደፈለገ ሁሉ ወሬዉን ገታ አደረገ: አንገቴን ወደጎን ነቀነቅኩለት
''ምክኒያቱም ባለማውቅ ነዋ... እኛ'ኮ አናውቅም ምስኪ'ኖች ነን ---- ናችሁ ሲሉን አዎ ---- ነን እንላለን ግን ምርጫ ስለሌለንም ይሆናል እኔ ምን ሆኜ እንዲህ እንደሆንክ አንድም ሠው ጠይቆኝ እንደማያውቅ ታውቃለህ....?''
አሁንም ወሬዉን ገታ ሲያደርግ አንገቴን ነቀነቅኩለት
''ማንም... ግን ካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ መማሬ ለጉራ ሲጠቅማቸው ያወሩታል... አይደል... አዎ አውቃለሁ ያወሩታል ምን ሆነህ ነው ያለኝ ግን የለም
''መጠየቅ ከፈቀድክልኝ ምን ሆነህ ነው ግን?''
አልኩት እንደመፍራት እያልኩኝ ባንድ እጁ መፅሔቱን ሲያገላብጥ ሳየው የእጆቹ ጣት ጥፍሮች አድገው ውስጣቸው ቆሻቻ ቅመዋል
''ስለጠየቅከኝ ደስ ብሎኛል ... በነገራችን ላይ ይቅርታ ለዚህ ጠላ ሳላመሰግንህ ነው የተጎነጨዉት....''
አለና ብርጭቆዉን አንስቶ በሁለተኛው ትንፋሹ ወገቡ ላይ አደርሰው::
''...እ.....''
በሃሣብ ጭልጥ ብሎ ሄደ ድፍርስ ዓይኖቹ ተተክለው ቀሩ:: ዝምታው ሲያስፈራኝ ግራና ቀኜን ገልመጥ አድርጌ ድምፄን ሞረድኩ
''አዎ''
የማህልና አውራ ጣቱን አጣብቆ ከመዳፉ ጋር ጧ! አድርጎ አጮኸና ቀጠለ
''አዎ... በጣም ረጅም ታሪክ ነው ባንድ ጀምበር ሚያልቅ አይደለም ግን ልነግርህ እፈልጋለው ለምን እንዲህ እንደምልህ ታውቃለህ.... እ... ታውቃለህ....?''
ራሴን ወደጎን ነቀነቅኩለት
''የሆነ የተለየ ገፅታ ስለማነብብህ ነው ብዙ ጊዜ ልታዋራኝ ፈልገህ ፈርተህ እንደምትተዉም አውቃለሁ ወይ ብልጥ ነህ ወይም ሞኝ አይደለህም ..... ልክ ነኝ?''
''እኔንጃ ''
አልኩት ከት ብሎ ሳቀና ፓይንቱን ጨለጠው:: ሌላ አመጣዉለት
''ትላንትና ኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሄጄ ነበር... ራሳቸው እየተጨቃጨቁ ሳይስማሙ ኢትዮጵያን ሚያስማማ ማኒፌስቶ አዘጋጅተናል ይላሉ... የዚህ ሃገር መንግስት ጀርባቸዉን እየጠበጠበ አይዟችሁ ይላቸዋል በሞራል መፈክር እየፃፉ... አልኩህ.... ይልቅ ለምን እንደሄድኩኝ ልንገርህ.... ፕሊስ.... እ?''
''ንገረኝ''
''ይቅርታ ግን ስምህን አላውቀዉም....''
ነገርኩት የርሱንም ነገረኝ
''አዎ... አንዲት ብጣቂ ማስታወሻ ነበረችኝ እና ወራዊ መፅሔታችሁ ላይ አሳትሙልኝ ስላቸው.... ፅሑፉንም አላዩትም ፊታቸዉን አጠቆሩብኝ ኡ ኡ መብቴ ነው ብዬ መክሰስ እችል ነበር ግን እነሱም እንጀራቸው ነው በስንፍናም ይሁን በምንም የሚያገኙትን ብር እዚህ ብቻቸዉን እንደማይበሉት አውቃለዋ... እዛች ምስኪን ሃገር ነው ሚልኩት.... እኛ'ኮ ሆዳሞች አይደለንም አይደል...? ''
ወሬዉን ገታ አድርጎ አዎንታዬን ሲጠብቅ ራሴን ከፍና ዝቅ አደረግኩለት::
''...ነጭ'ኮ ሆዳም ነው.... የፈለገ ነገር ቢሆን ካንተ አንድ ነገር ሳይፈልግ አይሰጥህም አንዳንዴ ሳስበው የዚች ዓለም አአቀማመጥ ራሱ ምክኒያታዊ ነው....''
እንዴት?''
''ይልቅ ፅሑፌን ተርጉመህ አንተ ታሳትምልኛለህ... አማርኛ ሚያዋራኝ ስለሌለ ሃሣቤን ሰብስቤ ለመፃፍ አስቸግሮኝ ነው በቡዳዎቹ ቋንቋ የፃፍኩት''
አለኝና መፅሔቱን ገልጦ ባደፈ ወረቀት የተፃፈ ፅሑፍ ሠጠኝ:: ዓይኖቼ ገና ማንበብ እንደጅመሩ... ድንገት ይቅርታ ጠይቆኝ ተቀበለኝና
''ቀሽም ሆንኩብህ አይደል... አማርኛ አልችልም ማለቴ.... ለቋንቋው ክብር ስላለኝ አልተማምንኩም እንጂ ሞክሬዋለሁ እንዲያዉም እሱን ልስጥህና ...''
ብሎኝ ሌላ ያደፈ ያማርኛ ፅሑፍ ሠጠኝ:
''ይሄ መግቢያው ነው''
በፈገታ ተቀብዬው ዓይኖቼን ወደ ፅሑፉ ስወረውር ድንገት እሙር ብሎ ተነሣና
''ቡዳዎቹ እየመጡብኝ ነው ልሂድ ሠባራ ፍላጎታቸዉን መጠገን አለብኝ እነሡ ቀጣፊ ለመሆን እኔ ተቀጣፊ መሆን አለብኝ እሺ....
ደግሞ አደራህን እዚህ ሃገር ሞኝ ሆነህ ኑር.... ጠላ ስለጋበዝከኝ አመሰግንሀለው ፈቃደኛ ከሆንክ ሌላ ጊዜ እብደቴን እስብክሀለሁ::
ሳይጨብጠኝ መፅሔቱን ብብቱ ስር ከትቶ ፈጥኖ እየተራመደ ሄደ ስሙን ጠርቼ ላስቆየው ብሞክር አልዞረልኝም::
የማላውቀው ስሜት ተሠማኝ :: ከዛም ማንበቤን ቀጠልኩኝ
ዘመን ዘመንን ሸኝቶ እኛን እቼቼ ብሎን እየገሠገሠ ነው አቻምና የገረሙን ነገሮች ዛሬ ተራ ነገር ሆነዋል የትላንት ነውሮች ዛሬ የጨዋ ደምብ እየሆኑ ነው ጊዜ ከስሯ 'ሚራወጡትን ሁሉ በምትዓቷ አሳምና ዛሬኛን ሆነው እንዲከተሏት ታደርጋለች ምርጫ የለንም እንደ ላም እምቡቡቡቡ... ባንልም እንደሠው ሆ.... እያልን እንከተላታለን አታምልጣቹ ተብሎ ስለተነገረን እንንቀዠቀዣለን ወይም ደግሞ ሲያደርጉ አይተናልና እንዋከባለን... ዛሬን ሳትሠራባት ካለፈችብህ ከዕድሜህ ተሠርቀሀል ተብሎ በተረት ስላስፈራሩን እርጋታችንን ማዶ ለግተን ቆም ብሎ ማሰባችንን ተነጥቀን እንበራለን... መብረር... መሮጥ... መንጦልጦል....
ወሬዉን አጣፍጠው በመስኮት ሲሰብኩን ጋዜጣ ላይ ፅፈው ሲሰጡን እንቀበላለን ሁሉም ነገር የገባን እየመሠለን የነርሱን ዲስኩር በቃምን እኛ እንክኮፈሳለን... ''እንዲህ ሆነ '' እያልን የገደል ማሚቱ ሆነን እናስተጋባለን የነርሱን ትንሽነት አሳምረው ሲያሳዩን የኛን ትልቅነት እንረሳለን... ኋላ ቀራችሁ ሲሉን ሆድ ብሶን እንንደረደራለን አልደረሳችሁም ሲሉን ተስፋ እንቆርጣለን...
በዛ በኩል
ምድር በራሷ ምን እንዳንቀዠቀዣት እንጃ ያለቅጥ እየሮጠች ታረጃለች እንዳሮጌ ዣንጥላ ተቦዳደሰች በበጋ እያነባች በክረምት ትደርቃለች... ላንዱ ሃሩር ሆና ላንዱ ትጎርፋለች...
በጎን
መንግስታት እያስታረቁ ያጣላሉ... እያጣሉ ያስታርቃሉ ጥይት ዘርተው እያጨዱ ሠላምን ይሰብካሉ... አማላጅ ሆነው ገብተው እነሱ ዳግም አማላጅ ይሻሉ... ለቆመ ጎርፍ ግድብ ይገነባሉ... ባሕል ሳይኖራቸው ሠው ምድር ላይ ባሕል ይተክላሉ.... ጨዋነትን ገፈው ነውርነትን ያለብሳሉ... ዝምታው ማንነቱ የሆነዉን በግድ መብትህ ተነካ ብለው ያስዋሻሉ... እሱን እየመጡ ለኛ ይሰብኩና እኩልነት ይላሉ....
ራሳቸው እየጮዑ ራሳቸው እያጮዑተደፈር ን እርርሪ ብለው ለብቀላ ይዘምታሉ... የራሳቸዉን ዜጋ ልከው ራሳቸው ያሳደጓቸዉን ጠያይም እነሱ ጠላት አድርገው ጠለፏቸው... አፈኗቸው.... ብለው በወሬ ዓለምን ይነዛሉ... ከካሜራው ጀርባ ያሉት ጠላፊና ተጠላፊዎች ካሜራው ኦፍ ሲሆን መለኪያቸዉን አንስተው ሴሌብሬት ያደርጋሉ... (ፊታቸው ካልታየ ባለ ጊዜ ሆነው ይኖራሉ ፊታቸው ከታየ ተገደሉ ተብለው ድምፃቸውም ሕይወታቸዉም ይጠፋል)ይሄን ጊዜ ሽብርተኛው አልጠፋም በርቱ ካላችሁበትም እንዳትለቁ የሚል መመሪያ ራሳቸው አውጥተው የነቀሉትን ዱንካን መልሰው ይተክላሉ... የመቶዎች ዓመታት ዕድሜ ያለዉን ሙከራቸዉን ስልት ቀይረው ለመቶዎች ዓመታት ዳግም ደባ ይጠነስሳሉ...
በዚህ በኩል
እነርሱ እዛ ሆነው ማንነታቸውን እዚህ ይልካሉ በቴክኖሎጂ አንደበታቸው የማይሽር በሽታ ይዘራሉ ብልጭልጭ ጉዕዝን አሳምረው እየፈነጩበት ሕይወት ማለት እንዲህ ነው እያሉ ምስኪኑን ሕይወቱን እንዲንቀው ያታልላሉ ውስጣቸው የሠላም ደሃ ሆነው በውሸት ፈገግታ ሠላም እንዳላቸው ያስመስላሉ ከንቱነትን ባሕል አድርጎ ለሚፈጥር ዘመንኛ ወጣት ዋንጫ ይሸልማሉ ብር ሰጥተው ላይ አድርሰዉት ሠዉን ሁሉ መንገድ አስቶ መጨረሱን ካረጋገጡ በኋላ መልሰው ገንዘቡን ሳይሆን ሕይወቱን ይነጥቁታል ተገዳደሉ ብለው ዜናቸዉን ይሰብካሉ... ከዛ ደግሞ ሌላ ይመለምላሉ... <= ይህንን ሁሉ ቅንብራቸዉን ለምስኪኑ ሕዝብ በሚዲያ ያሳያሉ::
ምስራቃዊያን የባሕል የማንነት ሌብነታቸዉን አውቀው መስኮትና ጆሮዋቸዉን ድፍፍፍፍን በማድረጋቸው በንዴት ይጮዋሉ ምንም ያላለዉን ሕዝብ መብታቸው ተነካ የዓለምን አኪያሄድ እንዳያውቁ ተነፈጉ ብለው ዳግም ይጮኻሉ ስልጣኔን ከነርሱ እየተቀበሉ ሕዝቡ እንዳይሰለጥን በሩን ዘጉበት ብለው ይደሰኩራሉ ... ግንብና ተራራን ሚያደንቅ ቱሪስት መስለው ገጠር ገብተው ሊለያዩ ተንኮል ይሸርባሉ ...
እኛ ግን ይሄን ሁሉ በየዋህነት ነው ምናየው አጎዛ አንጥፈን ጠባብ አፍና ሠፋፊ ጆሮ እናዘጋጅላቸዋለን ወተት ከሚዘንብበት ቅቤ ከሚቆፈርበት ሃገራችሁ ውሰዱን ብለን እንማፀናለን... ይወስዱናል ወተት ባይዘንብም ቅቤ ባይቆፈርም ደም ተፍተን ሳንቲም እናገኛለን እሱን ስንቆጥር ያዩ ሁሉ የቃልኪዳን ምድርን በተስፋ ምድር ሊቀይሩ ከራሳቸው ጋር ግብግብ ይፈጥራሉ.... እናት አልባ አባት አልባ ጨቅላ አራስ ልጆቻችንን ጠቅልለን እንሰጣለን የላክናቸው ልጆች መሰልጠናቸዉን መሰይጠናቸዉን አናውቅም ... በርግጥ ብዙ ሰጥተው ብዙ ብዙ ያወራሉ የገዛ ሕዝባቸዉን መልካም ስራ መስራታቸዉን ሰብከው ጭብጨባ ያጠራቅማሉ ....
ስርዝ ድልዝ የበዛበትን ፅሑፍ በጉጉት እያነበብኩኝ ወደሚቀጥለው ገፅ ስሸጋገር በእንግሊዘኛ ፅሑፍ አንድሬው ኮሊን የተባለ ፀሐፊ ስለፒራሚድ ስለፃፈው የወሰደዉን ማስታወሻ አየው::
አንድ ነገር ለማወቅ ውስጤ ግብግብ አለ ምን ሆኖ ይሆን?
ተፈፀመ