ጥላ ዓልባ__________(ልብ ወለድ)

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ዋናው » Sun Jun 11, 2006 8:20 pm

.
.
.
ወደቤቱ ሲገቡ መብራቱን በዳበሳ ቦ ሲያደርገው ብርሁ ቀለም ያለው የአንተነህ የቀለም ቅብ በእንኳን ደህና መጣችሁ ስሜት ይቀበላል:: በእስኴር ቅርፅ ባለው ሸራ ላይ መጠኑ ትንሽ ገዘፍ ያለ ዘመናዊ ተብሎ የሚመደብ አይነት ሰዕል ነው: እንደአንተነህ ሁሉ ለማንኛውም ሠው አይገባም ግን አለመግባቱና የቀለማቱና የቅርፆቹ ስብጣሬ አንዳች ስሜትን በውስጥ ያጭራል::

መጀመሪያ ቦርሳዋን ጣል አድርጋ ከዛም ራሷም የመወደቅ ያህል ሶፋው ላይ ዘፍ አለች እንቅልፍ, ድካም, ስካር, ግራመጋባትና እንግዳነት ውስጧ ተንጫጩ በደከሙ አንዳች ዓይነት ስሜት በሚረጩ ዐይኖቿ ዓየችው::

''ሚጠጣ ነገር ትፈልጊያለሽ ሠባዊት?''

''የጠጣውትንም እንዴት እንደማወጣው ጨንቆኛል ዘኪ...''
አለችው ወደሶፋው መደገፊያ ለጠጥ እያለች

''እንደሱ አይነት ነገር ቤቴ የለም::''
አላት ፈገግታዋን በራሱ ፈገግታ እየመለሰላት

''እቺ ማነች?''
አለችው ከቫኔሳ ጋር ተቃቅፈው የተነሱትን ምስል ከግድግዳው ጥግ እያስተዋለች

''ቫኔሳ ግርሀም ትባላለች አንዲት እንግሊዛዊ ነች ሠቢ...''

ስሟን አቆላምጦና አሳጥሮ ሲጠራት የመጀመሪያው ነበር የሆነ ደስ የሚል ስሜት ተሰማት...ግን ደግሞ ስለቫኔሳዋ መስማት ፈልጋለች

''ምንህ ነች?''

''እኔንጃ....ሠቢ''

''እንዴት እኔንጃ....ሚስትህ ነች?''

''አላገባውም::''

''እሺ ምንህ ነች?''
ከንፈሮቿን እየመጠጠች ታርሳቸውና የታችኛውን ወደታች ገፋ ስታደርግና ለፈገግታ ወደዓይኖቿ ከፍ የሚሉት ጉንጩቿ ሠባዊትነቷን የሚናገሩ የተለዩ የውበቷ ነፀብራቆች ናቸው::

''ያንን ያህል ለማውቅ ለምን ፈለግሽ?''

''እኔንጃ በቃ ማለቴ...........ከደበረህ ተወው::''
አጠገቧ ተቀምጦ ሲጋራውን አወጣና
''ለመጨረጫ ጊዜ ላጭስ?''
አላት

''አጭስ ምን ያ ሁሉ ሲጋራ ሲቦንብኝ አልነበረም ምን አዲስ ነገር መጣ...''
አላጨሰውም ወደፓኬቱ መለሰውና

''መተኛት ፈልገሻል መሰለኝ አይኖችሽ አነሱብኝ...''
አላት ስታዛጋ አይቷት:: ወደ መኝታ ቤቱ ገበና ከትንሽ መደራገም በዋላ ተመልሶ መጣ

''ያው አዘጋጂቼያለሁ አይዞሽ መኝታቤቴ ስለማላጨስ ጥሩ አየር አለው::''

ጭጋጉ የለንደን ግራጫ የቀን ብርሀን የዘካሪያስን መኝታ ክፍል መስኮት አልፎ ሹክክ ብሎ ገብቶ ሠባዊት ፊት ላይ አረፈ: በእጇ ውደ ጎኗ ስትዳብስ ትንሽ ከበድ አላት ግራ ተጋባች የመኝታው ጠረን እንግዳ ቢሆንባታም የጠላችው አይነት ስሜት ውስጧ አልነበረም: በደንብ ዳስሳ ስታይ በድብ ቅርፅ የተነረተ አሸንጉሊት ነበር ግራ ተጋባች ወደመኝታ ክፍሏ አስገብቷት ግንባሯን ስሟት ከሄደ በዋላ አልተመለሰም ነበር ለምን? እንደወንድነቱ በዚህ ላይ መጠጥ ውስጡን አሙቆት እንዴት ክንዶቹንኳን ሊያቅፏት አልተዘረጉም.......? እነኚህን ጥያቄዎች ማታ ጠብቃቸው የነበሩ ስለነበርንጂ ከርሱ አሁን ካሰበችው አንዱን'ንኳን እርምጃ ቢሞክር የምትመልስለትን አዘጋጅታ ነበር:: አንዳንዴ እራሳችንን ላንድ ነገር ስናዘጋጅ ያ ያዘጋጀንለት ነገር በሌላ አቅጣጫ ሆኖ ስናገኘው መገረምም መናደድም...ዓይነት ስሜት ውስጣችንን ይሰማናል
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው________________________________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Wed Jun 14, 2006 6:04 pm

(-20-)
.
.
.
የሞባይል ስልኩ ሲያንጫርር ከተኛበት ሶፋ ላይ እምር ብሎ ተነሳ ዕንቅልፍና የማታው ሲጋራ የደራረበውን ድምፁ እየሞረደ አነሳው: ቫኔሳ ነበረች

''ሀይ......''
አላት ያኮረፈ ሰላምታዋን በስልኩ ውስጥ እያስተዋለ

''ጥለህኝ ወጣ አይደል ማታ?''

''አጋጣሚ ሆኖ ነው ቫኒ ላመሽ አላሰብኩም ነበር 11 ሰሃት ላይ ልደውልልሽ አስቤ ነበር በዋላ ላትመጪ ቲቺያለሽ ብዬ ተውኩት..''

''ክከነማን ጋር ነበርክ ዘካር.....?''

''ባለፈው የነገርኩሽ ከኢቲዮጲያ መልዕክት ይዛልኝ የመጣችውን የእሕቴ ጓደኛ ለንደንን ላሳያት ብዬ ከሷና ከአንተነህ ጋር ነው የወጣነው....''

''ታውቃለህ አይደል እንደምቀና ዘካር...?''
ምልልሷን በቀልድ ቀይሮ ካላሳሳቃት እየባሰባት እንደምትመጣ ያውቃል

''ስለምትወጂኝ ነዋ....እኔም'ኮ በድኔ'ንጂ.....ነፍሴ አንቺጋር ነበረች.....''

''እየቀለድኩኝ አይደለም......እሺ አሁን በሦስት ሰሃታት ውስጥ መገናኘት አለበን ብቸኝነት ተሰምቶኝቃል ካጠገቤ እንድትኖር እፈልጋለሁ''

''ቫኒ.........''
አምቧረቀችበት ያ ፊቷ ፍም ሲመስል ታየው ስልኩን ዘጋውና ሲጋራውን ሲሎክስ ሠባዊት ከመኝታ ክፍሏ ቀስ ብላ መጣች ::
ድንግጥ ብሎ ተነሳና

''እንዴት አደርሽ...ሠቢ?''

''ሰላም አደርክ አንተ ሰካራም....''
የጠዋት ፈገግታዋን የማየቱ የመጀምሪያ እድሉ ነበር በመስኮት ቡዝዝ ብላ ከተንሿከከችው የለንደን ጀንበር የርሷ ፈገግታ ይሞቃል::

''ሠላም ተኛሽ?''

''መጠጡም ነው መሰለኝ እል____ም ያለ እንቅልፍ ነው የወሰደኝ''
አለችው እያዛጋች ያይኖቿን ጠርዞች በሌባ ጣቷ እያበሰች ዘካሪያስ ከላዩ የደረበውን አነሳሳና ተንጠራርቶ

''ቁርስ ልስራ አንቺ ሻወር እስክትወስጂ ይደርሳል ቆይ ፎጣ ላውጣልሽ?''
አላት::
ስሃቷን ተመልክታ
''ሚስትህ ቶሎ ድረስ ብላ ስታዋክብህ ነበር ለሷም ታስፈልጋታለህ .....ደግሞ እኔ አስተጓጉዬህ የሰው ትዳር ልትበጠብጥ የመጣች እንዳልባል ...''
አለች ባማረ ፈገግታዋ እያየችው

''የሠው ሚስጥር መስማት ይቻላል?''
አላት
''የሠው ሚስጥር መስማት ባልወድም ጆሮዬን ያለትህዛዝ መድፈን አልነበረብኝም....ነው ወይስ እንግሊዘኛውን መስማት መቻል አልነበረብኝም...?''

ዘካሪያስ አንድ የማያውቀው ስሜት ውስጡ ተሰማው መስማቷን አለመደገፉ ይሁን...ብቻ አላወቀውም

''ማታ ስጠይቅህ ሚስቴ አይደለችም ለምን አልከኝ?''
አለችው እጆቿን አጣምራ እግሮቿን ደራርባ በጎን እያየችው

''አልተጋባንማ...''

''ግን እሷ ነች አይደል?''
አለችው ወደፎቶው እያመለከትችውና ዳግም እያየቻት:ዘካሪያስ በአወንታ ራሱን ነቀነቀ

''ቆንጆ ነች...ትወዳታለህ?''

''እኔንጃ...?''

''እድለኛ ነች አንተን ማግኘቷ::''
አለች ተነስታ ገላዋን ለመታጠብ ወደ ባኞው እያየች ::

ሠባዊት ዘካሪያስን ስለመከጀሏ እርግጠኛ የሚያደርጋት ስሜት ተሰማት ፈገግታው አቋሙ እርግታውና አንደበቱ አይኖቿን ስትጨፍን ሁሉ ይታያት ጀምሯል

__________________________________________________

ይቀጥላል

ዋናው__________________________________________::[/list]
Last edited by ዋናው on Tue Apr 10, 2007 6:35 pm, edited 3 times in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sat Jun 24, 2006 4:30 pm

(-21-)
.
.
.
ሠው ሲያንቀላፋ ምድር ለአንቀላፊዎች ፍራሽ ትሆናለች ነግቶ ሲራወጡ ምድር ታራውጣለች ደቂቆች ተንዳቅቀው አሁን ሲተዘቱ ትዝታት ታሪክ ሲሆኑ ደግሞ ነገ ይረገዛል ከዛም ይወለዳል ....''ግሪን ዴይስ'' የተሠኙ የሮክ ስልት አቀንቃኞች አሜርካን ኢዲየት በተሠኘ የሙዚቃ አልበማቸው ላይ ....''ሠው እንዴት ለተወለደበት አንድ ዓላማ መሆን ያቅተዋል?ማንም ሲወለድ አንድ አይለኛ ነገር ውስጡ አለ ያንን ሳያገኙ መሞት መዋረድ ነው.....''የሚል ሕሳቤ ያለው ሌሪክስ/ የዘፈን ግጥም አለ ይህ ዓይነቱ ስሜት አንተነህ ውስጥ ትልቅ ስፍራ አላቸው አንተነህ ዛሬን ሲኖር የሚያስበው የሚታየው ነገ ሲመጣ ላይታየው ስለሚችል እነዚህን ነገሮች በጥበቡ ያሰፍራቸዋል ለሱ አንድ መዝገብ ናቸው የመደነቅና የእጁ አሻራን ውበት ሚስጥር ሌላ የመውለዱ ማንነቱ ነው::

ዘርካሪያስ ማልዶ ቤቱ መጥቶዋል ፊቱ ክፍት ብሎታል ፂሙን ሳይላጭ ቀናቶች መነባበራቸው ላለባብሱ ግድ አለመስጠት ውስጡ የመሸገው ስሜት ምንነትን ይናገራል

''....እሺ ጋሽ ዘኩ እና ምን ሆነህ ነው የሠባዊትን ስልክ የማታነሳው?''
አለው አንተነህ

''የነሙሴን ምላስ ብዋስ በንግግር ስሜቴን መደበቅ እችል ነበር ያቺ ነጭ ሤይጣን ተነስቶባታል በሁል ነገር ትቀናለች እኔ ከሠባዊት ጋር የሻይ ቡና መባባሉ ድራማ ከቀጠለ ወደሌላ ስሜት መግባቴ እንደማይቀር ስሜቴ ነግሮኛል....''

''ያ...ስሜትህ ግን ማንን አለህ ዘኪ?''

''እኔንጃ ፒካሶ ቫኔሳ የምትሠጠኝ ፍቅር ልክ እንደዚህ አግር ቤኔፊት አለ አይደል...በቃ ባይበቃህም ያኖርሀል ስልህ ጥሩ ሤት ናት በጣም ዋይዝ ናት በተለይ ከማንም ሴት ለሷ ነገ ይታያታል በዚ ላይ ደግሞ እኔ የሚገባኝን ነገሮች ከኔ ቀድማ እሷ ታውቀዋለች ብቻ በደንብ ገብቼያታለሁ .....ችግሩ የሷ ነገና የኔ ነገ መለያየቱ ነው''
አንተነህ ያጎፈረ ፀጉሩን እየቆጣጠረ ፈገግ አለና

''ያንተ ነገና የሷ ነገ አይዋህድም?''

''ፒካሶ ደግሞ አንቺ ፓሌት ላይ እንደምትቀላቅዪው ቀለም መሰለሽንዴ?....?''

''እሺ ሠባዊትስ ውስጥህ ምን ትላለች?''
ዘካሪያ ወደሶፋው ለጠጥ ብሎ አንገቱን እያሻሸ

''...እሷን ማን እንደላከብኝ አላውቅም የሆነ የሚገርም ድባብ አላት ድምጿ ፈገግታዋ እርጋታዋ......ያሳሳል በዚህ ላይ ፊቷን ሳስተውለው አንዳች ነገር ታወቀኝ''

''እንደኔ እንደኔ ውስጥህን በደንብ አዳምጠው....''
አለው አንተነህ ስኬች የሚያደርግባቸውን ወረቀቶች በክሊፕ ቆንጥጦ አከናወነና ቦርሳው ውስጥ ከተታቸው የከሰልና የክራዮን መንደፊያዎቹን ከላጲስ ጋር ሰብስቦ ሌላኛ የቦርሳው ኪሱስጥ ከተተና.....
''በል ወንድሜ ክላስ አለኝ ''
ብሎ እኩል አብረው ተነሱ

''ቅዳሜ ቃለመጠይቅ ልታደርግህ ትፈልጋለች ሠባዊት''
አለው ዘኪ

''ስንት ሠሀት ላይ?''

''አንተ በተመቸህ ሰሃት ብላለች::

''ዝግጁ ነኝ::''

_________________________________________

የቫኔሳን የመኪና በር ከፍቶ ሲገባ ከድምፁም ከሰላምታውም የከናፍርት ትስስራቸው ቀደመና ከጎኗ ቁጭ አለ::

''የት እንሂድ ዘካር?''

''ቢራ አምሮኛል ከዛም ብራንዲ....''
አላት

''ዛሬ እንዴት በጊዜ መጠጣት አሰኘህ?''

''እኔንጃ መጠጣት ሳይሆን መስከር አማረኝ ቫኒ''

''በሰላም ነው?''

''እኔንጃ እሱን ብዋላ ሞቅ ሲለኝ ስሜቴን እጠይቀዋለሁ...''
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
[/list]
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Mon Jul 03, 2006 4:21 pm

.
.
.
ቫኔሳ ለብርድ ብላ አንገቷ ላይ የጠመጠመችውን ያንገት ሻርፕ እያስተካከለች በቀኝ እጇ የያዘችውን የመኪናዋን መሪ እየዘወረች በጎን ዓይኗ ዘካሪያስን ታይዋለች::ዘካሪያስ የለኮሰውን ሲጋራ እየማገ ጪሱን ያቦናል
'' የኔ ፍቅር ሲጋራው አልበዛም?''

''በዝቷል::''

''ምን ሆነካል ዛሬ?''

''ምንም::''
ወደሷ አይመለከትም ፊትለፊቱን እያየ ከጪሱ መሀል የውስጡን እየተነፈሰ

''አንዳንዴ ከመሬት ተነስቶ ከፍቶሽ አያውቅም?''
አላት:

''ያለምንም ምክኒያት...እኔንጃ ከፍቶኝ አያውቅም:''

''እኔንን ግን ይከፋኛል ያስጠላኛል, ይጨንቀኛል...''

''ዘካር...ሰሞኑን አንድ የሆነ ስሜት ውስጥህ አለ እኔ እጮኛህ ነኝ ምናልባትም የነገ ሚስትህ... ልታማክረኝ ይገባል እኔ ትንሽ ነገር ሲደርስብኝ ሮጬ መጥቼ ላንተ አዋይሃለው እንዲህ ዓይነቱን ስሜት ስትደብቀኝ ልታርቀኝ የወሰንክ ሁሉ ይመስለኛል''

''እሺ ዛሬ እንድሰክር ፍቀጂልኝ....?''

''ያንተ ስሜት የጠየቀህን እኔ የመከልከል መብቱ የለኝም ከልክዬህም አላውቅም...''

''አመሰግናለሁ ቫኒ...''
''እምጱዋ!!!'' ሳማት ድምፅ ፈጥሮ::

ሆሎዌይ የተሰኘ ስፍራ ሄደው ፑል እየተጫወቱ የስቴላ ፓይንት መጠጣት ጀመሩ:: ቫኔሳ ሁለት ፓይንት ስትጠጣ የጎን ጉንጮቿ የፈማሉ አይኖቿ ቡዝዝ ብለው ፈገግታና ጨዋታዋ ይደምቃል የማንነት ህግ...የንግሊዝ አባዜ ከውስጧ ይሸሻል የነፃ ትውልድ መንፈስን ስሜቷ ይመኛል ነፃ አስተዳደግና የዛሬ ነፃ ይሰለጠነ ኑሮዋ በወላጆቿ የትላንት ህግጋት የዘር ትሥሥር በደም ወደሷ ሾልኮ የማንነቷ ስሜት ከንዲህ ዓይነቱ የስካር ግልቢያ ነፃነት መሻት ጋር ሲጋጭ በ''ሆድ ያባውን ብቅል ያወጠዋል'' ቅኔ ሲታይ ቫኔሳ ዘካርያስን የመወዳጀቷ ምክኒያት ምክኒያታዊ ያደርገዋል::

''ከሁለት አንዳችን መንዳት ስላለብን አንዳችን መስከር የለብንም::''
አላት ዘካሪያስ

''እኔም መስከር አምሮኛል::''

''እሺ ጠጪ ካብ/ታክሲ ይዘን እንሄዳለን''
ብሎ ሞልቃቃ ከናፍርቷን ሳማቸው:: ከዛም የመኪና ቁልፏን ቀማት::

ዘካሪያስ መጀመሪያ ቫኔሳን ተዋውቋት እራት ይዟት ሲወጣ በስሜት ቅልጥ ማለቷን ሲያይ እንደሌሎች እንግሊዛዊ እንስቶች ሁሉ የወሲብ ስሜት ያጦዛት ብቻ መስሎት ነበር:: የመገናኘታቸው ድግግሞሽ ወደመነፋፈቅ ሲጀመር ዘካሪያስ ፍቅር ሁሉ ጀማምሮት ነበር አንዳንዴ ፍቅር የሚያይለው አንዱ አሳዳጅ አንዱ ተሳዳጅ ሲሆን ነውና የሁለቱ እኩል መነፋፈቅ እኩል እሺታና መስማማት የፍቅር ህመምን ሳያስነሳ መዋሀድ ብቻ ሆነ::

''እንግዳህ ሄደች?''

''አለች::''

''አትመለስምንዴ?''

''ትንሽ ትቆያለችንጂ መመለሷ አይቀርም''

''ለምን አላስተዋወቅከኝም ...ስለኔ አልነገርካትም አይደል?''
ፀጉሮቿ ስር የሻጠችው እጇ መዳፍ ጀርባ የተዘረጉት ድምስሮች አረንጓዴ ሆነው ፈጠዋሉ

''ነግሬያታለሁ አስተዋውቅሻለሁ::''

''ዘካር....የኔ ፍቅር ብዙ ጊዜ ከሤት ጋር የመቀራረቡ ልምዱ እንደሌለ ነግረህኛል ከዚች እንግዳ ጋር ግን በጣም መቀራረብህ አልዋሽህም እንድቀና አድርጎኛል አንድ ነገር ሲፈጠር እንደሚታወቀኝ ታውቃለህ አይደል የምጠላው ነገር ደግሞ ድብብቆሽ ነው ልብህ እንኳን ቢከጅላት ንገረኝ::''

''ቫኒ........ ''
ለኮሰች ሲጋራ የሱን የልምምጥ ጥሪ በሴትነት ገጿ ጥላው

''...ውስጤ የመረበሹ ጉዳይ ይሄ መስሎሽ ከሆነት ተሳስተሻል::''

''እና ምንድነው ዛሬም አባትና እናትሽ አይወዱኝም ልትለኝ ነው?''
ሳታውቀው ድምጿ እየጨመረ መጣ

''እሱ ሌላ ርህስ ነው ሌላ ቀን እናወረዋለን....''
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው___________________________________::[/list]
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sun Jul 09, 2006 6:41 pm

(-22-)
.
.
.
ፈጣሪ ለራሱም ዕረፍት ሲል ቅዳሜን ፈጠረ ይላል አንተነህ አማኞችን ለማስጮው ሲፈልግ ...ፈጣሪ ጎበዝ ሆኖ ሰባቱንም ቀን ቢለፋ ኖሮ ዓለም አሁን ካለችበት ገፅታ የተለየ የሁለት ቀን የፍጡር ለውጥ አምጥታ እኛም ያለረፍት እንዳክር ነበር....

አንተነህ 10:30 ሲል ካልጋው ላይ ለዛሬ ቀን እንደሁሌም ተወልዶ ቅዳሜን መዘከሩን ጀመረ ጠዋት ላይ ሬጌ ሙዚቃ መክፈት ያስደስተዋል ቅዳሜ በመሆኑ ድምፁን ከፍ አድርጎ በሙዚቃው እይተወዛወዘ ነው:: ''ስቲል ፐልስ''የተሰኙ የሬጌ አቀንቃኞች ''ኢሞሽናል ፕሪዝነር'' በሚለው ዜማቸው
ከሻወር በዋላ ወፍራም ቡና አፈላና ቁርሱን ሳንዱዊች ሰርቶ አቀራረበ በመስኮት በኩል ሲያይ ለንደን አኩርፋለች ቅጠል ያራቆተ ውርጯ በቅዝቅዜ እየገረፋት ለንቦጯን ጥላለች:: ያንተነህ ስልክ ሲያንጫርር አነሳው ሠባዊት ነበረች ዛሬ ለቃለ መጠይቅ ቀጠሮ አላት:: የሚመቻት ባቡር ጣቢያ ቀጠራት:: ውዲያው ወደ ዘካሪያስ ድወለ::

''ዘኪ እንዴት ነህ?''

''አለው አንተ እንዴት ነህ?''

''ምን እሆናለሁ ብለህ ሰዕል እንዴት ነው ዝግጅት ምናምን...?''

''አሪፍ ነው ለኢግዚቢሽኑ ነው?''

''አዎ ደርሷል አይደል?''

''አዎ ሣምንት ነው የሚቀረኝ...ስማ ዛሬ ብቅ አትልም'ንዴ ሠባዊትህ ትመጣለችኮ?''

''እመጣለሁ ግን ትንሽ አምሽቼ ነው የምመጣው ማለቴ ወደ 4...5...አካባቢ''

''ምነው?''

''አንድ የሚጠቅመኝ ነጭ ቀጥሮኛል ባክህ የ አይ.ቲ.ቪ ኦዲዮ ኤዲተር ነው ማታ ቤተ-ብልግና ተገናኝተን ...የቫኒ ዘመድ ነገር ነው...እና ዛሬ ጠቃሚ ነገር ሊያዋራኝ 2:30 ላይ ቡና ልንጠጣ ተቃጥረናል::''

''ኣ....ሀይ እንደዛ ከሆነስ መልካም ቀኖችን እንደማከብር ታውቃለህ እቺህ ቀን ምናልባት ህይወትህን ትለውጥ ይሆናል መልካም ውሎ ታዲያ እንዳትቀር እንግዳህን ብዙም አልተላምርድኳት ባይሆን አብረን ሻይ ቡና እንላለን''

ተስማምተው ስልኩን ዘጉት ዘካሪያስ ማታ በጭቅጭቅ...በፍቅር...በስሜት...እይተፈራረቁ ከ ቫኔሳ ጋር አመሹና ታክሲ ይዘው ወደ ሱ ቤት ነበር ያመሩት ቫኒ ስክር ብላ ነበር በቅናት ብ.ግ.ን ያደረጋት ውስጧን ለዘካር ያሳየችበት መንግዶች ብዙ ነበሩ ጥፊ...የሲጋራዎች መብዛትና ቲማቲም ፊቷ እስኪፈም ማለብለቧ...ማሳረጊያው ያልጋ ላይ ግልቢያ ነበር የዘካሪያስ ወገብ እስኪርድ::
በጠዋት ተነስታ የዘውትር ተግባሯ የመጀመሪያ የቀኑን ሲጋራ ለኩሳ የዘካሪያስን ሸሚዝ ለብሳ ወደሳሎን ሄዳ ቲቪውን ከፍቶ ዜና ማየት....እንግሊዞች እንዴት ማደራቸው ብቻ አይደለም ለነርሱ ...ዓለም እንዴት አደረች?....'ንጂ
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sun Jul 09, 2006 7:04 pm

.
.
.
የድምፅ መቅረጫውን ለመስራቱ ደጋግማ ሞከረች

''እዚሁ ለንደን ነው የገዛዋት ዘመናዊ ነች አይደል?''
አለችው ላንተነህ በፀሐይ ፈገግታዋ

''በእኔ ድምጽ መመረቁ ዕድለኛ ነኝ::''

''ጥያቄዬ ቅድም እንዳሳወቅኩህ ባወጣውት ቅደም ተከተል ነው:: እና የማትፈልገውን ርዕስ ካነሳውብህ ምልክት ትሰጠኛለህ....''
አለችው ሲጋራውን አጭሶ ጨርሶ ሲያጠፋ ዓይኖቿ ወደአሽትሬው እየተከተሉት::በምልክት መስማማቱን ገለፀላት

''መጀመሪያ ለቃለ መጠየቁ ፍቃደኛነትህ በዝግጅት ክፍሎቹ እና በጋዜጣው አንባቢያን ስም አመሰግንሀለው::....ራስህን በማስተዋወቅ ቃለ ምልልሱን እንጀምራለን''

''ስሜ አንተነህ ሢሳይ ይባላል ባዲስ አበባ ስ/ጥበብ ት/ቤት የ አራት ዓመት ትምሕርቴን ተከታትዬ በቀለም ቅብ የመጀመሪያ ዲፕሎማዬን ወስጄያለሁ አሁን እዚህ ደግሞ እንግዲህ ይሄ የማያልቅ ትምህርት ይሄው ትምህርቴን ከቀጠልኩኝ እዚሁ ብቻ ሰባተኛ ዓመቴን ይዢያለሁ::''

''እሺ ሰዕል ላንተ ምንድነው?''

''በጣም በከባድና በ አሪፍ ጥያቄ ነው የጀመርሽኝ ሠባዊት ...ስዕል ለእኔ ልሳኔ ነው ...ዕይታዬ ነው...አስተውሎቴ ነው... እንዴት ነው አሁን አንቺ ታይኛለሽ አይደል....? አይተሽኝ ለአህምርሽ የምትልኪው መሴጅ አለ:: ያ በፈረንጅ አፍ ሲጠራ ይቀላል ልበል....ኦብስኩራ ይሉታል በግልባጭ ዕይታ... ያ ኢሜጅ ነው ለኔ ቦታ የሚሰጠው ታዲያ ማየት ስልሽ ወደውስጥም አጮልቄ ኣያለሁ ውስጣችን የብዙ ዕይታዎች ጥ ር ቅ ም አለ ያንን ዘርግፈው ያወጡ ጥቂት ኣያላን የጥበብ ሠዎች ናቸው እኛ ደግሞ እንዳቅማችን ጨልፍን ምሥልና ብርሀን እናስታርቅበታለን...የሚያይልሽ ሠው ያደንቅሻል ግማሹ አልገባኝም ብሎ ያልፍሻል በርግጥ ኣይገባም ውስጣችን ለሌላው ሠው ኦፔክ ነው የተገደብ ዕይታ ....ግን ቀለማትና ገፆች ሲተራመሱ...ኮ አንቺም ምስል መፍጠር ትቺያሌሽ....በዕኔ ካንቫስ ''

ሠባዊት ሲናገር የእጆቹን መወናጨፍ እያስተዋለች በማይገባ ሀሳቡ እየተማረከች ቱክረቷ ወደሱ የመሳቡ ሁኔታዋ ጎልቶዋል::

''ሰዕል ላንድ ትውልድ የባሕል ወይም የስልጣኔ መሳሪያ ነው ብለህ ታምናለህ....አንተነ[/list]?''

''በነ ቬንቺ እና አንጀሎ ዘመን ከስልጣኔም አልፎ የመኗኗሪያ ትልቅ መሳሪያ ነበር ዛሬ ለባይሎጂ ምንጭ መፈጠር ሰዕል ነው:: የሠው አናቶሚ ለማጥናት ነበር እነ ሬምብራንት ሬሳ መቅደድ የጀመሩት....ዛሬ ግን እንዳልሽው አሁን ባለንበት የሰለጠነ ዘመን ውስጥ የስዕል መሳሪያነትና አቢዮተኛነትን የሚሻሙ ብዙ ነገሮች አሉ::ስለዚ ስዕል ዛሬ ኤስቴቲካል መልዕክቱ (የጥበባዊ ውበት መስሕቡ) ያመዝናል በርግጥ አሁን ያለንበት ሲቪላይዝድ ዘመንም ስዕል ለስነ-አሕምሮ /ሣይኮሎጂ/ መነሻ ሀሳብ እንደሚረዳቸው ይታወቃል::''

''ከውጪዎቹ ሠዐሊያን እነማንን ታደንቃለህ....?''

''በተለያየ ያሳሳል መንገድ እንደ ዐይለኝነታቸው ብዙ የማደንቃቸው ሠዓሊያን አሉ ለምሳሌ እንደነ ማርክ ሻጋል...ማቲስ...ቫንጎግ...ሞዲግሊኒ.....በራሳቸው ስልት ሀሳባቸውን ለመግለፅ የሚጠቀሙባቸው ያሳሳል ቴክኒክ (ዘዬ) በጣም ይገርሙኛል:: በተረፈ ለእኔ ዳግም መፈጠር ቢችል አስሬ ቢወለድ የምፈልገውና በሕይወቴ በጣም በጣም የማደንቀው ሠዐሊ ፒካሦ ነው:: ዘርፈ ብዙ ዕውቀት ያለው ያለማችን ድንቅ ሠው ፒካሦ ነበር::''

ሢጋራውን እየለኮሠ የቀኝ እግሩን መዳፍ ጎን ግራ ጉልበቱ ላይ አኑሮ ቅንድቦቹን በቅርፅ ከዕይታው አስተውሎት ጋር እየቀያየረ ጥያቄዎችን እያብራራ መለሰላት::

''... አንተነህ እስቲ ከምታደንቃቸው ያገራችን ሠዐሊያን ትንሽ ብትገልፅልን...''
አለችው ሠባዊት የድምፅ መቅረጫዋን ወደርሱ እያስጠጋች
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Mon Jul 10, 2006 4:42 pm

.
.
.
''ከአገራችን ሠዐሊያን ዕውቀት ያስጨበጡኝን መምህሮቼ ውስጤ አሉ መቼም ይኖራሉም...በተለይ መዝገቡ ተሠማ ኮቴው ሁሉ እውቀት ነው:: ውስጡ ያለው የቀለም ክምችቱን ሳስብ ምናልባትም ዓይኑ የተለየ ነው ብዬ ሀስብ ነበር ያኔ የሱ ተማሪ ሳለው....በተረፈ እስክንድርና ገብሬ አፈር ይቅለላቸውና ላገራችን የስዕል አቢዮት መለወጥ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው ዘመናዊ ስዕልን /ሞደርን አትርት/ ያስተዋወቁን እነርሱ ናቸው:: እንግዴ ዕውቀትና ማድነቅና ችሎታን ማድነቅ ይለያያል ሠባዊት ::በሰዕል እውቀቱ በቀለ መኮንን አሁን እዚህ ኤውሮፕ ውስጥ እያደገ ያለው የጥበብ ፈጣሪያን የሚከተሉትን መንገድ ነው የሚከተል የነበረው አሁንም እንደዛ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ:: ዛሬ ስዕል ማለት ማሰብ ነው መሣል ደግሞ ወይም መፍጠር ....እንዴት እንዳሰብሽ ማሳየት ነው:: እናም በቄን በጣም አደንቀዋለሁ ሌሎችም ብዙ አሉ እነ ታደሰ መስፍን በሀይሉ...ልዑል...በርካቶች አሁን አሁን ደግሞ በዌብሳይት እያየናቸው ያሉ ምርጥ ወጣት ሰዐሊያን እየተበራከቱ ነው አበሻ ስቱዲዮ በሚል የሚታወቁ ወጣት ሠዐሊያንን ጥቂት ስራዎች አይቼ በጣም ነው የተደሰትኩት.......''

''አንተነህ ስራዎችህን ምን ያህል ጊዜ የት የት ለህዝብ አሳይተሀል...?''

''አገሬ'ንኳን ብዙም አላሳየሁ ወዲያው ነው የወጣውትና ሂልተን አሊያንስ አስይቼ ነበር...በውጪው አለም ጣሊያን ፈረንሳይ ስፔን እንዲሁም እዚህ ብሪታኒያ በርካታ ጊዜ የተለያዩ ስፍራዎች አሳይቼያለሁ::''

የአንተነህ እና የሠባዊት ቃለ ምልልስ ወደ ሁለት ሠሀት ፈጀ በሀሳቡ ልዩነት ተገርማ በዕውቀቱ ተደንቃ እርሱን በመጠየቋ ኩራት ሁሉ ተሰምቷት ነበር::ያቀረበላትን የቡርቱካን ጂዩስ ተጎንጭታ ሰሃቷን ስታይ

''ሠባዊት የለንደንን ደመና አይተሽ የመሸ እየመሰለሽ መደናበሩን አሁንም አለመድሽውም አይደል?''
አላት::

''ለነገሩ አልመሸም ግን ይጨልማል ሲያስጠላ አየራችሁ...''

''ስትለምጂው ይሻላል..... እንዴት ነው ሠባዊት እዚች ሰፈሬ አንዲት ሬስቶራንት አለች እዛ ብንሄድ ከቤቴ የተሻለ ምግብ ትበያለሽ...''

''አልራበኝም አንተነህ የበላውት የረፈደ ቁርስ ገና አልተፈጨም::''

''ተይ...እንግዴ እኔ መለምን አልችልበትም ንፉግነት እንዳያስመስልብኝ...''

''ግዴለም እኔም ከራበኝ አልግደረደርም ቅቅቅ''
የአንተነህ ምርጫ ሙዚቃ ሁለቱንም ወደ ሀሳብ ከተተ ኤኒያ የተሰኘች ለየት ያለ ያሞዛዘቅ ስልት ያላት አቀንቃኝ ና የፒያኖ ተጫዋች ነች ፔንት ዘ ስካይ የተሰኘ አልበሟ ነው:: ወደክላሲካል ስልት ይወስደዋል:

''እስቲ ስላንቺ አጫውቺኝ ሠባዊት እኔ ደግሞ እስቲ ያለ ቴፕ ኢንተርቪው ላድርግሽ....''
ትንሽዬ አፍረት የተላበሰ ፈገግታ አሳይታው አዛጋችና

''...ስለኔ ምን?''
አለችው::

''ላይፍ እንዴት ነው ማለቴ ደስተኛ ነሽ....?''

''ዋው......ከዚህ በፊት ማንም ጠይቆኝ የማያውቅ ጥያቄ ነው... እኔንጃ...በትክክል ምን እንደሚሰማኝ አላውቅም ግን ብቻ ህይወቴ ጎደሎ ነው ሁሌም ነገን አስባለሁ አሳዛኝ ሕይወት ያለኝን ያህል አልተጎዳውም::''

''ላይፍ እንዴት ...ምን አጓደለችብሽ?''

''በጣም ትልቅ አንተነህ ለእናትና አባቴ አንድ ብቸኛ ልጅ እኔ ነበርኩኝ የወንድምና የእሕት ፍቅር ተርቤ ባድግም ሁለቱ የቤተሰብ አባሎች ግን አንቀባረው ስላሳደጉኝ የልጅነት ሕይወቴ ያማረ ነበር እኔ 15 ዓመት ልጅ ሳለው እናትና አባቴ በመኪና አደጋ ሞቱ:: ከዛ እቺህ ዓለም ብቸኝነት እድሌ መሆኑን ነግራኝ ተሳልቃ አሳደገችኝ ቀሪውን እድሜዬን የኖርኩት ከአባቴ እህት ጋር ካክስቴ ዘንድ ነበር:: ሌላው በጣም ረጅም ታሪክ ነው...አንተነህ ለዕንቆቅልሽ የተፈጠርኩኝ ሠው ነኝ........''

አንተነህ ጉልህ ዓይኖቿ መደፍረስ ሲጀምሩ እንባ ማሰባቸውን አወቀ የታሪኳ አጀማመር ግን አጓጉቶታል::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
[/list]
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Tue Jul 11, 2006 11:51 am

(-23-)
.
.
.
ሠባዊት የእናቷ የእናትነት ፍቅር የአባቷ እንስፍስፍነት ባስታወሰችው ቁጥር ፊቷ በእንባ ይሞላል::አባቷ ቀይ የፊቱን ገፅ የዋህነቱን አላብሶ ዘውትር ምሽት ከርሷ ጋር የሚጫወቱት ጨዋታ የሚላፉት ልፊያ ከአህምሮዋ አይጠፋም:: ገና ሳታድግ ነበር የጎረቤቶቿን አይታ ትንሽ እሕት ወይም ወንድም እንደምትፈልግ የነገረችው 'ቆይ ትንሽ ቆይ ትንሽ...' እያሏት ነፍስ አወቀችና መውለድ አለመቻል ምንነቱን ስታውቅ አንድ ለቤተሰቦቿ እንደሆነች አመነችበት::
አባትና እናቷን የነጠቃት ጨካኙ ሞት እንደ አጎት የምታየውን ያባቷን ጓደኛ በዐመቱ ደግሞ ወሰደባት:: የሙት ልጅ ያለኑዛዜ የተረከቡት ያባቷ ጓደኛ አቶ ግሩም ይባሉ ነበር ከሠባዊት አባት ከአቶ ፍቃዱ ጋር የጋራ ሰፊ የንግድ ካንፓኒ ነበራቸው እኚህ ሰው ሲሞቱ ሠባዊት የቤተሰቧ ንብረት ይዛ በቤተሰባዊ ሸንጎ የአባቷ እህት አክስት ጋር እንድትሆን ተደረገ::

አክስቷ የሠባዊትን እናት በጣም ስለምትጠላት ሠባዊት በኣካሏ ከፍ እያለች ስትመጣ እናቷን መምሰል ስትጀምር አክስቷ ትጠምዳት ጀመር ልጆቿም የቤተሰባዊ ወንድማማችነት ፍቅራቸው የሳሳ ነበር:: ሠባዊት የጋዜጠኝነት ትምህርቷን ጨርሳ ጥቁር ቆቧን ስትደፋ በቤተሰብ አልታጀበችም:: 21 ዓመት ሲሞላት ራሷን ችላ ተከራይቶ የነበረው ያደገችበት የእናትና ያባቷ ቤት ውስጥ ለመኖር መውሰኗን ተናገረች:: እንዳሠበችው በቀላሉ እሺታውን ከአክስቷ አላገኘችም ነበር አንድ ቀን አምሽታ ስትገባ

''የኛ ጎረምሳ ቤ/ሠቦችሽ ያስረከቡኝ በስርዐት እንዳኖርሽ እንጂ እንደፈለግሽ እንድትፈነጭ አይደለም.....''

''አክስቴ አምሽቼ እንደምመጣ ተናግሬ ነው የሄድኩት ጠዋት ተስማምተሽ ነበር አሁን ምን ተገኘ?''
አለቻት ለነገር ግምባሯ ወደተሸበሸው አክስቷ እይተመለከተች

''ባስፈለገኝ ሰሃት ልቆጣች መብቴ ነው ደግሞ ትመልሺልኛለሽ?''

''አንዳችን ስንጠይቅ አንዳችን ካልመለስን እንዴት መግባባት እንችላለን አክስቴ...?''

''አንቺ ምን ታደርጊ ቤ/ሠቦችሽ ናቸው አጨማልቀው አሳድገውሽ እኔ ላይ የወረወሩሽ...''

አለች አክስቷ የምታስተካክለውን ልብስ በንዴት ወደቁምሳጥኑ እየወታተፈች

''...እነርሱማ ድንገት በአደጋ ሕይወታቸው ባታልፍ ወጉ ደርሷቸው ታመው ቢሆኑ የሞቱት ዓይናቸው እያየ አንቺጋር እንድኖር አይፈቅዱም ነበር እኔም ለዚ ነበር አጎቴ ግሩም ጋ መኖርን የፈለኩት ግን ምን ያደርግጋል 'ገፊ!' ነኝና እሱም ሞተ::''

''ለምን ታዲያ ምንቅር ብለሽ አትዬጂም.....?''

''ወስኚያለሁ እኔ አንቺ እንዳልሽው ተጨማልቄ ስላላደግኩኝ ራሴን ማስተዳደር አያቅተኝም የእናትና አባቴ ቤት ሄጄ እኖራለሁ::''
አለች ሠባዊት እምባዋ ብርሁ ዓይኖቿን አደፍርስሦ

''ከመቼ ወዲህ ነው እንዲህ አፍ ያበቀልሽው ባክሽ ድሮስ የአፈኛ ትምህርት መምረጥሽ.......''

''ስፈጠርም ከነአፌ ነው የተፈጠርኩት በአግባቡና በቦታ እጠቀምበታለሁንጂ...''

በዚህ ፀብ በሸተተው ምሽት ነበር ባክስቷ ተገፍትራ በሙሉ ጨረቃ የተባረረችው:: ለአንድ ዓመት የቆየችበት እንዳጎት የምታያቸው ሟቹ ግሩም ቤት ሄዳ አንኳኳች ልጃቸው ገዛህኝ ከፈተላት:: በመጠጥ ስካር ፊቱ ቡዝዝ ብሎ ነበር ከ5 ዓመታት በፊትም ቤታቸው ልትኖር ስትመጣ ገና ሠውነቷ መፈርጠም ሲጀማምር የገዛህኝ ዕድሜ አፍላው ላይ ነበር ልቡና ስሜቱ ገፍትረውት ምራቁን ቢውጥም ያኔ ዕድሜውና የቤተሰብ ህግ ፍራቻው ቆንጥጠውት ነበር::

የሱ የዛኔው ማታ ሞቅታና የሠባዊት ትኩስ የጨረቃ እንባ ለየቅል የራሳቸውን ስሜት ያረገዙ የህይወት ሚስጥሮች ነበሩ ፈገግታው አላምርሽ አላት
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው___________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Wed Jul 12, 2006 8:36 pm

.
.
.
ገዛህኝ በመጠጥ ስካር የተቋጠረ ደምስሩና የቀላሉት ዓይኖቹ ፈጠው ጓዟን ይዛ በትኩስ እንባ ድንገት የመጣችውን እንግዳ በመገረም ሲያያት ስካሩ እየሸሸው ሲመጣ ታወቀው:: ሠባዊት እንዳሰበችው ሳይሆን አዝኖላት እያባበላት ነበር የተቀበላት::

የሕይወት ስንክሳሯን በትውስታ እያውጠነጠነች ለአንተነህ ስትነግረው ያ የቆነጀ መልኳ በሀዘን ድባብ ተውጦ ነበር:: አንተነህ ግን ያ, ለርሱ ውበት ነው 'በቆንጆ ሤት ሀዘን ያምራል' ይላል በፊቱንም ወሬ ሲጣፍጠው ሲጋራውን ያከታትላል::

''በዚህ ዕድሜሽ ብዙ አይተሻል ሠባዊት ለዚህ ተዋናይ ሊያደርግሽ ነው ፈጣሪም ይሄንን ውበት የቸረሽ ልበል.....እስቲ ቀጢይልኝ''

''...እዛ ቤት ውስጥ እየኖርኩኝ የቤተሰቦቼን ሀብት የይገባኛል ጥያቄዬን መከራከር ጀመርኩኝ ገዛህኝ በጣም ረዳኝ ለጠበቆች ከፍሎ እሱ ነበር ላይ ታች ይልልኝ የነበረው እናቱ አጎቴ ግሩም ሕይወቱ ሳያልፍ በፊት ጀምሮ ያልጋ ቁራኛ ናቸው::''

በመሀል አፍልቶ ያቀረበላትን ቡና እየተጎነጨች ዓይኖቿ ወደአኮረፈው የለንደን አየር በመስኮቱ ተተክለው በሃሳብ ሄደች ወደ አዲሳባ የርሷና የገዛህኝ የፍቅር ወዳጅነት...

አዲስ አበባ በሀምሌ ዝናብ ንጭንጭ ግራ ግብት ብሏታል ያንን ሠሞን እረፍት አልባው ካፊያ የመዲናይቱን ታዳሚ ሁሉ ንጭንጭ አድርጎ ነበር የሰፈሩ ጪቃ የመኪናዎች የጎማ ፍንጣቂ... የታክሲው ቶሎ አለመገኘት ብቻ የጠዋት የሠራተኛው እሮሮ ነበሩ:: ሠባዊት የክረምቱ የትምህርቷ መዘጋት ቤት የመዋሏ ጉዳይ ሆኖ ነበር:: ገዛህኝ የቀረበለትን ቁርስ በላልቶ እንደተለመደው የመኪናውን ቁልፍ ሄዶ አላነሳም ወደ ሠባዊት ክፍል ብቅ አለ::

''ተነስተሻል...'ንዴ እንዴት አደርሽ ሠቢ?''

''እንዴት አደርክ ገዝሽ ለጠዋት እንቅልፍ እምብዛም ነኝ ታውቅ የለ... ምነው አረፈድክ ዛሬ ሱቅ ቀድሞ የሚከፍትልህ አለንዴ?''
አለችው ወደግድግዳው ሰሃት እያየች አልጋዋ ጫፍ ቁጭ ብላ የያዘችውን የአንገት አብል ተክዛ እየተመለከተችው ነበር: የእናቷ ስጦታ ነው::

''እደርሳለሁ... ማታ እራት አብረን ብንበላ ምን ይመስልሻል?''

''ምነው ምን ተገኘ..?''
አለችው ትንሽዬ ፈገግታ ከትንፋሽ ጋር እያሳየችው

''ምንም ካንቺ ጋር እራት መብላት ፈልጌ ነው...ምነው የምትሄጂበት አለ?''

''የለም::''

አስተያየቱ አልፎ አልፎ '...ይሔ ልጅ ይከጅለኝ ይሆን...?' ብላ ራሷን እንደምትጠይቀው ቀን ሆነባት እሱን ብላ ዘውትር የምትደውል ትርሲት የምትባል ሴት መኖሯን ታውቃለች::

ሞዛዛው የሐምሌ ቀን ረፍዶ ውሎ መምሸት ጀመረ የሠፈሩ ሕፃናት
'አንበጣ ና ሾርባ ጠጣ
ስኳር የለኝም እንዳትቆጣ'..... እያሉ የዛፍ ለምለም ቀምበጥ ይዘው ከቁመታቸው እንጣጥ እያሉ አንበጣ ተብዬ የክረምት ቢራቢሮዎችን ለመንካት ይታገላሉ ዶሮዎች በጭፍግጉ ቀን አይቅርብኝ ብላ የማታ የማታ ብቅ ያለችውን የምታባብል የክረም ፀሐይ አጓጓቷቸው ወደማደሪያ ቆጣቸው ከማቅናት እነርሱም እየዘለሉ ቢራቢሮዎችን ቀብ ያደርጋሉ...አዋፋትም በሠማይ እንደጥይት ተተኩሰው አንበጣዎቹን ይለቅማሉ .....ከነዚህ ሁሉ የተረፉት ቢራቢሮዎች የቀን ትንሽዬ እድሜያቸውን ከተፈለፈሉበት አፈር ወጥተው በነፃነት በረው ዳግም ወደ አፈር መግባትን በመሻት ውር ውር እያሉ ለቀኑ መገባደድ ድምቀትን ለግሰዋሉ:: አይመሽ የለ መሸ አዲሳባ በቡርትካናማው የጎዳና ማብራት ስቃለች ገዛህኝ ሠባዊትን ከጎኑ አስቀምጦ መኪናውን ወደ 22 ማዞሪያ ሲከንፍ የርሱም ልብ እየሳቀች ነበር::

''ዛሬ ግን ከምር እንዴት እራት ልትጋብዘኝ ሀሰብክ ገዝሽ...?''
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
[/list]
Last edited by ዋናው on Tue Oct 03, 2006 6:30 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Thu Jul 13, 2006 7:33 pm

.
.
.
''እኔንጃ መደሰት ሲያምረኝስ...?''

''ከእኔ ጋር እራት መብላቱ ነው የሚያስደስትህ?''

''በጣምን'ጂ አንቺን ከመሰለ ውብ ጋር እራት መብላቱ መታደል አይደል'ንዴ....ሠቢ?''
እጆቿን አጣምራ ወደውኃላ ዥው ዥው እያሉ የሚያልፉትን የጎዳና የመብራት ቅስቶች ዓይኗን አቅረዝርዛ እያየች...

''ዛሬ የተለየ ስሜት ሳይብህ ገርሞኝ ነው ገዝሽ?''
አለችው::
ወደ አንድ ሬስቶራንት ሲደርሱ መኪናውን አቁሞ ወርዶ በሩን ሲከፍትላትም በመገረም ነበር የምታየው እንደ የሜዳ አህያ ቆዳ የተዥጎረጎረ ቀለም ያለው የምግብ ቤቱ አንዳች ለየት ያለና ደስ የሚል ገፅታ አለው::

''...ሠቢ ሳልቾክል ጊዜ በመጠበቄ ትህግስቴን ሳታደንቂው የምትቀሪ አይመስለኝም?''
አላት ምግቡን አዘው የምግብ ዝርዝር ሜኖውን አጥፎ ከላዩ ላይ ባኖረው የመኪናው ቁልፍ በጣቱ እየተጫወተ

''ሁሉም ነገር አልገባኝም ገዝሽ ልትነግረኝ ያሰብከው ነገር አለ?''
አለችው በድንግዝግዙ መብራት ጉልህ ዓይኖቿን በግርምት ወደገዛሕኝ እያንከባለለች

''ሥሜቴን ከፊቴ አይተሽ ሳታነቢ የቀረሽ አይመስለኝም በጣም ጥልቅ እና ብርሁ አሕምሮ እንዳለሽ አውቃለሁ::''

ይሄኔ ሠባዊት አንገቷን ደፋች ደነገጠች ቀና ብላን'ኳን ዓይኖቹን ለማየት ተሳቀቀች

''...እንደማንኛውም ወንድ ውበትሽን ብቻ ብዬ አይደለም ያሰብኩሽ ሠቢ ከመቀራረብና ከመላመድ የተረገዘ ፍቅር ነው ውስጤ ያለው::''
.
.
.
በዚህ ምሽት ነበር የሠባዊትና የገዛህኝ የፍቅር ግንኙነት የተፀነሠው ስልክ ስለምትደውልለት ሕንስት ስትጠይቀው የንፅሁ ጓደኝነት ቅርርብ በስተቀር ሌላ ነገር በመሀከላቸው እንደሌለ ነገራት:: ውለታ ይሉንታን ይወልዳል ይሉንታ ደግሞ የራስ ነፃነትን ይነፍጋል...... የመጀመሪያዎቹ ሰሞናት ውስጧ ምንም ፍቅር ሳይኖር የአብሮ መውጣቱ ጉዳይ ቀጠለ... በዚህ መልኩ ያላቸውን ቅርርብ ከጀመሩ 6ወር በኋላ ነበር አንሶላ እንኳን የተጋፈፉት:: በኋላ ግን በፍቅሩ ወደቀች::
ገዛህኝ የረጅም ጊዜ ህልሙን እውን አደረገ ቤቱስጥ እግራቸውን በሽታ የሸበባቸው እናቱ የዚህ ድራማ ተሳታፊ ነበሩ ከዛም ቤቱስጥ የሁለቱን የፍቅር ቅርርብ እያዳመቁ ለልጃቸው መልካም ምኞታቸውን በህሊናቸው ያስቡ ነበር::
በእርግጥ ገዛህኝ ያቺ ትርሲት የምትባል ሴት የርሱ ወዳጅ ነበረች ከርሷ የፈለገውን ፍቅር ቀድሞ ስላገኘው ከሠባዊት የሚጓጋውን ሀብቷን ፍለጋ ነበር ትላንት ሆኖ ለዛሬና ለከነገወዲያ እያሠበ....

የሠባዊትና የአንተነህ የመስማትን የማዳመጥን ትልቅ ቀልብ ዘካሪያስ መጥቶ በበሩ ደውል አደፈረሰው:: አንተነህ በመገረም ተነሳና ቁልቁል ወደሶፋው ሠባዊትን እያየ
''ትቀጢይልኛለሽ መጣው ለዘኪ በር ልክፈት''
አላት::

ዘካሪያስ መላጣውን እያበሰ ካንተነህ ጋር እየተላፋ ገባ

''ሠላም ሠቢ....አንቺ ያንን ያህል ትናፍቂኛለሽ ብዬ አልገመትኩም ነበር ሙች::''

''ጉረኛ ብናፍቅህማ ነው እየደወልክ ዕረፍት የነሳህኝ...''
እያለችው ጉንጩን በጉንጯ ሳመች::

''...ምን አንቺስ ሚስድ ኮል እንኳን ይደረጋል'ኮ ካላስታወሱን ደግሞ የማን ፈጣጣ ነው የምንባል እየመሰለን እንፈራለን ....''

የሰላምታ ፈገግታዎች ለዛን በተላበሱ ምልልስ ሦስቱም መሀል ቆየ:: አንተነህ ሠሃቱን ተመልክቶ

''ዘኪ ታውቃለህ ሠቢ ያለ ፕሌን አዲሳባ ወስዳኝ ነበር እንዴት ጣፋጭና ልብን የሚያንሰፈሰፍ ታሪክ እየነገርችኝ ነበር መሰለህ አንተ መጣህና የእርጎ ዝንብ ጥልቅ አልክ'ንጂ''

''ተውንጂ ...ታዲያ እኛም እንስማዋ....''

''ኖ ኖ እስካውንም እየረገመችኝ ነው ይሔኔ..... ምሳ አልበላችም በቡና ነው ሆዷን የማጮወው እስካሁን..... ተነስ እህል ቢጤ እንቀማምስ...''

''...ጭ! ፒካሶ ካሞን ሰዉ ሁሉ እንዳንተ ወስፋታም እየመሰለህ ነው አይደል በሰው ሆድ የምታላግጠው...ምንነካህ?''

''ሠላም ነኝ ዘኪ ብዙም አልራበኝም''
አለች ሠባዊት ሆዷን በለግላጋ አለንጋ ጣቶቿ እያበሰች የቦርጭ ስሜቱም የላትም እሷም ያንን ስለምታውቅ የምታደርጋቸው አጭር ባተሌት ያላቸው ሱሬዎችና ሆዷን የሚያሳይ አለባበስ ነው::

''ጠይቄያት ነበር ልስራ ብያለሁ ልጋብዝም ብዬ ነበር ማግደረደር እንደማልችል እያስታወስኳት.....አይደል ሠባዊት?''

''አዎ!''
አለች እተቀመጠችበት ፈገግ ብላ ለምስክርነቷ:: ተነስተው ወጡ::ብርዱ ጋብ ቢልም ሠማዩ ዝናቡን ሊያነባው እንዳሰበ ሁሉ ከሩቅ መብረቅ እየተብለጨለጨ ይንጓጓል::
.
.
.
(ጥላ አልባ ይቀጥላል እንዴት ነው ወደዱት? እስቲ አስተያየትዎ ይጠቅመኛልና ከርሦም እሻለሁ...)

ከብዙ ብዙ ማክበር ጋር
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው__________________________________::
[/list]
Last edited by ዋናው on Tue Jul 18, 2006 8:13 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sun Jul 16, 2006 3:55 pm

(-24-)
.
.
.
ዕለቱ ሰኞ ነው ብርዱ ጋብ ቢልም ያጠላው ሰማይ ዕይታው ይበርዳል:: ሁለቱን የእረፍት ቀናት አታክኮ ሦስተኛው የእረፍት ቀን በአገሩ ነገስታት የተሾመው የባንክሆሊዴይን ሁሉም ያገሬው ሰው ይደሰትበታል ምራቂን ማን የሚጠላ አለና... እቺህ ቀን የአንጎቨር ቀነ ነች ከአርብ እስከ እሁድ የተንቆረቆሩ ያአልክሆል ጎርፎች ተጠረቃቅመው ራስ ምታትን ድካምን ያሚያጉሩበት ስሜት...በጠዋቱ አንጎልን ድው! ድው! ሲያደርግ ባናቱ ያገሬው ለንደናዊ ቢራ ይቸልስበታል::

ዘካሪያስና ሙሴ ስለሺ ቤት ቀድመው ተገኝተዋሉ ሙሴ ከፍተኛ የጫት ሱስ አለበት በሳምንት ቢያንስ ሦስት ቀናት ይቅማል:: ምሳቸውን በልተው ለጫቱ ሲሰናዱ አንተነህ ደረሰ

''ፒካሶ ደግሞ እንደ ሲልቨር ሊንክ ትሬን ሁሌም እንደዘገየህ....?''
አለው ስለሺ ቀና ብሎ ቦርሳውን ከትከሻው የሚያወርደውን አንተነህ ገልመጥ አድርጎ

''ሄሎ ፌሎስ.......''
አለና አንተነህ በየተራ ተሳለማቸው::

''ምን ያድርግ እሱ እንደዘማች ጓዙ ብዙ ነው...''
አለው ሙሴ ወደአንተነህ ቦርሳ እያየ:: ዘካሪስ በሳቅ አያዋዛ ለአንተነህ የተሰነዘሩትን ተረቦች ያዳምቃል::

''በይ ኪችን ግቢና የተረፈ ጥብስ አለ እሷን ቀማምሺና መጥተሽ ተመሳሰይ ፒካሶ....''
አለው ስለሺ::

''ባለቤትህስ...?''
አለው ወደኪችኑ ገብቶ በዓይኑ እየቃኘ

''ስላሤዎች ይነግሳሉ ብላ በጠዋት ነው የሄደችው::''

''የሷ ስላሤውች ደግሞ እንደፈለጉ ነውን'ዴ ያሚነግሱት...''
ሁሉም ሳቃቸው በረከተ

''እሱን ስትመጣ ጠይቃት የኔ ድርሻ እንሂድ ስትል እምቢ ልሂድ ስትል መፍቀድ ነው ፒካሶ...''

''አንተ ግን ለምንድነው ቤ/ቲያን የማትሄደው ስሌ የክርስቲያን ልጅ አይደለህ....ዘኪ'ንኳን ያቺ ነጭ ሚስቱ ካቶሊክ ቸርች ይዛው እየሄደች ነው አንተነህ ደግሞ ጭራ የሌለው ሤይጣን ነው ቢሄደም ወይ እንደ ሎጥ ሚስት የጨው አምድ ሆኖ ይቅራል ወይም እንደሻማ ይቀልጣል.....ያንተ ግን ይገርማል...''
አለ ሙሴ የሸሚዙን እጅጌ በቅጡ እያጠፈ: ይሄን ጊዜ ዘካሪያስ

''አይ ሙሴ ቺክ ፍለጋ ሄደሽ የአባን መስቀል ብትሳለሚ በረከቱን ያገኘሽ መሰለሽ አይደል...?''
አለው ተንበርክኮ መቀመጫ ትራሱን እያስተካከለ...

''ምን ያድርግ ብለህ ነው የሚሄደውም የሚሳለመውም የሚሳለውም እነሱን ለማግኘት ነው የለንደን ሴቶች ደግሞ ይሄንን የመሰለ ሽቅርቅር እያዩ ......''
አለ ስለሺ::

ጫቱን ጀምረው ወጉን ቀጠሉ:ዘካሪያስ ለጫት እምብዛም ነው በሁለትና በሦስት ወር የዚህን ዓይነቱን አጋጣሚውን ካገኘ ነው የሚቅመውም አንተንህና ስለሺም እንደዛው ናቸው ጊዜውም ስለሌላቸው ትዝም አይላቸው::ትንሽ ቆይቶ ሌላኛው የጫት ታዳሚያቸው ዮሐንስ መጣ ድፍርስ ትልልቅ ዓይኖች አሉት በአካሉ ቀጠን ያለ ቢሆንም መደንደን የጀመረ ሠውነቱ ልብሱን ወጣጥረውታል::

''ጆኒ ዘ-ገዳም ወንድማችን የጠፋ የገዳም ሠው.....''
ስለሺ ተነስቶ ተሳልሞ ተቀበለው: የራሱን ድርሻ ጫቱን እና ለስላሳውን በፌስታል አንጠልጥሎዋል በየተራ ሰላምታ ተለዋውጦ አውልቆ የያዘውን ጃኬቱን ይዞ ዓይኑን ሲያንከራትት ስለሺ ተቀበለው

''ምሳ በልቼያለሁ ብትለኝ ይሻልሀል?''

''ሁሉንም አድርሼያለሁ አሁን አሽትሬ ብቻ ነው የምፈልገው ለጊዜው ከዛ ቦታ ዲስፐርስ አድርገኝና ልመሳሰል...ቅቅቅ''

''ተጠፋፋን አይደል ጆኒ ቤትም መጥቼ አላውቅ...አንተም እኔጋ አትመጣ ....''
አለው አንተነህ

''ምን ጆኒ'ኮ የገዳም ሠው ነች ቤቷ ተቀምጣ አታያትም ብርቱካን መስላ እንደምትወጣ.....''
አለው ሙሴ ጫቱን እየቀጠፈ አሽሞንሙኖ እየጎረሳት

''ይሻላል እንዳንተ በብርድ ያለስራ አስሯ አንደር ኤጅ ሤት ቤት እንደ ሶሻል ወርከር ከመዞር...''
አለው ዘኪ በማብሸቅ ዜማ

''ወንድሜ እናንተ አሹፉ እኔ የሚሞቀኝን ስፍራ እራሴ አውቃለሁ...''

''ለኔ ቤቴ እንደምትሞቀኝ ለሙሴ ደግሞ ሄስና አንስሎው ይሆናል የሚሞቀው ...''
አለው ዮሐንስ ጫማውን እያወለቀ ወደጫቱ መድረክ ዓይኖቹ እየቀላወጡ: ሀንስሎው እና ሄስ ወደ ለንደን ገብተው እድሜያቸውን አሳንሰው አሳይለም /የስደተኛ ጥገኝነት/ ለሚጠይቁ አበሻ ሤቶች የሚመደቡበት የሰፈር ስም ነው::
ጆኒ ዘ-ገዳም የሚል ስያሜ የተሰጠው ዮሀንስ ቤቱን በጣም ስለሚወድ ነው ለቀናት ብቻ ሳይሆን ለሳምንታት ከቤቱ ሳይወጣ ይቆያል:: ግን ምክኒያት አለው ቤቱ የስራ ቦታውም...የመዝናኛ ስፍራውም...ራሱን የሚያዳምጥበት የራሱም ገዳም ነው::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው__________________________________::[/list]
Last edited by ዋናው on Tue Jul 18, 2006 8:20 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sun Jul 16, 2006 4:29 pm

.
.
.
ዮሐንስ በፀባዩ ከሰዎች ለየት ያለና ሌሎች ያላዩትን ያመለካከት መንገድ በራሱ እይታ እያየ መቃረንን ተቃርኖ ትክክል ነው ብሎ መከራከር የሚወድ ነው: ዘካርያስ ስለዮሀንስ ግለ-ባሕሪህ ሲያወራ ...''ጆኒ የአየር ራንድ 'ዘ ቨርቺ ኦፍ ሰልፊሽነስ' የተሰኘ የግል ፍልስፍና ውስጡ ያለ ከመጉዳት የተቆጠበ ራስወዳድነት ያለው ሠው ነው::'' ይለዋል
ስለሺ ደግሞ...'' ጆኒ ሲከራከር ብረት ያዝጋል...ሆኖም ግን አንዳንዴ የሚያነሳቸው ርህሶችና የሚከራከርባቸው መንገዶች ያላየናቸውን እንድናይ ስለሚያደርግና ጨዋታን ስለሚያሰፋ ደስ ይለኛል በተረፈ ዲሞክራትነቱን እወድለታለሁ...''
ይላል

አንተነህ ደግሞ ''ጆኒ የማወቅ አድማሱን ለማስፋት ከሚጥሩ ሰዎ አንዱ ነው ግን ሊያውቅ በዳሰሳቸው ግኝት ዕውቀቶች ጭብጥ ሁሉ የራሱ ጥርጣሬ አለው... ሁሌም አንድ ነገር ስታሳየው የዛን ነገር ጀርባ ማየት ይፈልጋል ልክ እንደ ኢንፕረሺንስት ሰዓሊያን ከምናብ ዘልቆ ውስጠ ደመነፍስን ለመርመር ያለ የማወቅ ርሀብ ......''
ይላል::

ዮሐንስ ጫቱን እየቀነጠበ በደፈረሱ ዓይኖቹ ወደ አንተነህ እያየ

''የአውኑ አርብ ኤግዚብሽንህ ይከፈታል አልከኝ አንቱሽ...?''
አለው::ራሱን እየነቀነቀ
''ከሞላ ጎደል ሁሉ ነገር አልቋል የዴይሊ ሚረርና የአካባቢው ጆርናል ጋዜጦች ለቃለ መጠይቅ እንደሚመጡ የጋለሪው ስ.አስኪያጅ ነግሮኛል::

''እንዴት ነው ጥሩ ስራዎች እንደምናይ ተስፋ አለን:''

''ብለናል እንግዲህ ምስል መፍጠር ዓይቶ መናገር ነው ምስሉን ማየትና ማሰብ ነበር የሚከብደው ...የሚገርምህ ኤግዚቢሽኔን ይመጥናሉ ካልኳቸው ስራዎች አንድ የሚጎለኝ ነበር ...ያንን ኮምፖዚሽን ባልጠበኩት መንገድ ካልጠበኩት ስፍራ አገኘውት...አንዲት ከአገር ቤት የመጣች እንግዳ አለች እሷ ውስጧን ዘልቄ እንድመረምር የሚያደርገኝ ዕውነተኛ የሚገርም ታሪኳን ስትነግረኝ እኔ ውስጤ ስዕል መሳል ጀመረ...''
.
.
.
ይቀጥላል
ዋናው__________________________________::
Last edited by ዋናው on Sat May 22, 2010 8:12 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Mon Jul 17, 2006 12:17 pm

.
.
.
''እንዴት ነው ፒካሶ ስዕል ዲያሪ ይሆናል'ንዴ...? የቀን ገጠመኝህን ወደ አርት መቀየርህ አልገባኝም...?''
አለው ስለሺ ያገጩን የተንጨባረረ ፂም በቀኝ እጁ ሌባ ጣትና አውራ ጣቱ እየፈተለ በሌላኛ እጁ የያዘውን የጫት ቀምበጥ በክንዱ ስር ሸጉጦ

''ቀኖች ማለት የህይወትህ ንሁስ መስመሮች ናቸው የነዚህ የቀኖች ምክኛታዊ ገጠመኞች ስብስብና ስብጥር... ውስጥህ ለምትወልደው ኮምፖዝሽን ወይም ምስል ትልቅ መንስሄ ይሆናሉ... በዚህ አጋጣሚ ለእኔ በየቀኑ የምሰራቸው ስኬቾቼ ዲያሪዎቼ ናቸው የዛሬ ሦስትና አራት ዓመት የነደፍኳቸውን ስኬቾች ዛሬ ባያቸው እነዛ ቀናት ግጥም አድርጌ አስታውሳቸዋለሁ....::''
አለ አንተነህ ለስላሳውን ተጎንጭቶ በዓይኑ የያዘውን ሲጋራ የሚሎክስበት ዕሳት እየፈለገ

''የንሁስ መስመሮች ያልከውን አገላለፅ ወድጄልሀለው...አንቱሽ ግን ታዲያ የነዛ መስመሮች ስብስብ ምስል ውስጥህ ለመፍጠር ትንሽ መብዛት ወይም ብዙ መወሳሰብ ያለባቸው አይመስልህም...''
አለ ዮሀንስ ሲያወራ የእጆቹ እንቅስቃሴዎች ይጎላሉ:

''እዚጋ አንድ ነገር እንጫወትና.....'' ቀጠለ ዘካሪያስ የልምዱን በቀኝ እጁ ያንገቱን ጀርባ እያበሰ ....''....ውስጥህ ለምታስበው አንድ ምሥል ምስሉን ስትሮንግ ለማድረግ የግድ ብዙ መስማት ማየት ወይም ማድረግ የለብህም እንዴት ነው አንዳንዴ ባንዲት ትንሽዬ ቅፅበትን'ኳን የሚገርም ነገር ዓይተን ወይም ኦብዘርቭ አድረገን እናውቅ የለንዴ...''

አንተነህ ለምላሹ እየተቁነጠነጠ ያደግ ጭብርር ፀጉሩን እየፈተለ
''...ወደጆኒ ጥያቄ ልመለስና ባንቺ ዓይን ያለፍቃድ ላይብሽ ነው አሁን ...ጆኒ...ይሄውልሽ አንድ አሪፍ ነገር ለመስራት ብዙ ነገሮች ማሰብና በብዙ የዛ ነገሮች መሰናዶዎች መዘጋጀት አለበት ባይ ነሽ ባልሳሳት.....''
ጆኒ/ዮሐንስ አንገቱን በአወንታ ነቀነቀ በጉሩፑ ውስጥ ወሬ ሲጣፍጥ አንዱ አንዱን ሲጠራ አንቺ ማለቱ የተለመደ ነው::...ቀጠለ አንተነህ

''...ውስጥሽ የሆኑ ፎርሙላዎች አሉሽ እነዛ ነገር ሁሌም ላንድ ነገር ሬዲ ናቸው ያንቺን ኮማንድ ብቻ ነው የሚጠብቁት ገብቶሻል አይደል እና ቅድም ላልኩሽ መሰናዶ እነዚህን አስቀምጪአይቸውና ዘኪ ያለሽን ቅፅበታዊ ልብን የሚደምም አጋጣሚ ጨምሪበት....''
ስለሺ ፈገግ ብሎ በአንተንህ መልስ መርካቱን አሳወቀ::

ይሄ ሁሉ ሲሆን ሙሴ ስልኩ ላይ ተጥዶዋል ጫቱን እየቃመ ከእንስቶች ጋር እትትህ እያለ ነው በራሱ ዓለም እየዋኘ ነው:: የጫቱ ፕሮግራም እንደዚህ በጨዋታዎች እየደመቀ ሰኞ እየተዘከረች ነው:: ጥቁር ተብሎ የወጣላት ስያሜ በቀን ውሎ ግምገማ ሲታይ እንደ የሰዉ የራሷ ቀለም ይኖራታል::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
Last edited by ዋናው on Sat May 22, 2010 8:19 pm, edited 2 times in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Mon Jul 17, 2006 1:20 pm

.
.
.
''በተወሰነ ሰሞን ከተለያዩ ቆነጃጅት ጋር ስትተኛ የሚሰማህን ስሜት ልትነግረኝ ትችላለህ ሙሴ እስቲ ደግሞ አንተን የሚያሳትፍ ርህስ እንፍጠር...''
አለው ዘካሪያስ ወደጎን ርዕሱ ወደአልጣመው ሙሴ እያየ ሙሴ ፈገግ ብሎ አየውና
''ዘኪ ግን ለምን አተውኝም በቃ እኔ ያለነሱ እቅፍ እቺ ዓለም የምትደፋብኝ ነው የሚመስለኝ::''
አለው ሙሴ የሸሚዙን ኮሌታ እያስተካከለና ትከሻውን ዘርግቶ ወደላይ እየሰበቀ

''እንስት የሚጠላ ማን አለ ብለህ ነው ሙሴ...ዝምበላቸው ባክህ ደግ አደረክ::''
አለው ስለሺ

''እኔ ምን አገባኝ መጥፊያው እንዳይሆኑ ብዬ ነው ይሄንን የመሰለ ሸበላ...''
አለው ዘካሪያስ ሲጋራውን እየሳበ

''ሙሴ'ንኳን ብልጥ ናት ፕሮቴክሽኑን አትረሳም እንዴት ነው አንቱሽ ለላንድስኬፕ ሲወጣ ያለብሩሽ ይወጣል...?እንደዛ ነው::''
አለው ዮሐንስ እየሳቀ:አንተነህ ሳቁን ጨርሶ...
''እስቲ ፅደቂብን እኛኮ ካንቫስ ስር ተደፍተን የሴት ድምፅም ናፈቀን ...''
አለው::
''አገሩ ሁሉ የአበሻ ሴት ነው አንድ ማታ ያበሻ ጭፈራ ቃኘት አድርግና አራት አምስቱን አፍሰህ ትገባለህ...እረ እንዲያውም ማንነትህን ቢያውቁማ እነሱ ቀድመው ያፍሱሀል...''
አለው ሙሴ

''እኔኮ የዚህ አገር ያበሻ ሴት በፍፁም መግባባት አልችልም ማለቴ ደስ ይሉኝላ ያሳዝኑኛል ...ግን አለ አይደል ውበታቸው ስሜቴን ከማናገሩ በፊት ማንነታቸውን እንዳውቅ ይገፋፋኛል ስቀርባቸው በማንኛውም የማውቅ አቅጣጫ የሉም በቃ ኢንፎርሜሽን ዜሮ!!! ግን የዋህነታቸውና አዛኝነታቸው ለቤተሰብ በመራወጥ መድከማቸውን ሳስብ ደግሞ በጣም ነው የሚያሳዝኑኝ::
አለ አንተነህ

ዘካሪያስ ወሬውን አዳምጦ ካጣጣመ በዋላ
''...እዚጋ አንድ ነገር እንጫወት...''ብሎ ጀመረ..''...ሁሉም የአበሻ ሴት አንተ እንዳልካቸው አይደሉም በጣም ጂኒየስ እንስቶች በስንት የለንደን ትምህርት ተቋማት እንዳሉ አትዘንጋ ያብዛኞቹ መማር ያለመፈለጋቸው ጉዳይ ድሀ ቤተሰባቸውን ለመርዳት ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ነው ፒካሶ...''አለ::

''እኔኮ በዛ በኩል ድሀ ቤተሰቧን እየረዳች በፍቅር ለተቆራኛት የወንድ ጓደኛዋ ግን የሚገርም የፈለጣ ስ/ስርዐት ታኪያሄድበታለች: ሾፒንግ ብላው ልቡን ታደርቀውና ኦክስፎርድ ሰርከስ ወስዳው ቶፕ ሾፕ,ሪቨር አይስላንድ, ጋፕ, ሊቫይስ...እያለች ልቡ ፍቅር ያሸፈተውን ኪሱን ሙጥጥ!!! የወደደ ሞኝ ነው የሳምንት ላቡ ሲጠራረግ አይታወቀውም ፌስታሎቿን ታቅፎላት ቤቷ አድርሷት ከንፈሯን ስሞ ወደቤቱ ሲያዘግም መንገድ ላይ ይደወልለትና ....እስቲ በናትህ ካርድ ገዝተህ ቁጥሩን ቴክስት አድርግልኝ ይባላልላ::''
አለ ሙሴ ::የዚህ ዓይነቱ አጋጣሚ ያልዳሰሰው ወንድ አልነበረምና ሁሉም ሳቃቸውን ለቀቁት:

''እኔን'ኳን ከዚህ ዓይነቱ ደባ ነፃ ነኝ ስለማውቅባቸው ሾፒንግ ሲሉ የለውም.....ገና ደውላ ካርድ እንደፈለገች በድምጿ ስለማውቅ ቤት ገባውኮ....:: እላታለሁ እንደነቃውባት ስለምታውቅ ምንም አትልም::
ብሎ ሲያወራ ሙሴ

''ለምትወዳት ሴት ብታደርግ ምንም አይደለም...''
አለው ዮሐንስ

''አይ ጆኒ ለንደን የምትወዳት መች ጠፋች የምታምናት'ንጂ''
አለው ሙሴ መልሶ በሹፈት ዛቻ ፊቱን እየነቀነቀ::
የለንደን የፆታዎች ግጭት በርግጥም የበዛ ነው:: መተማመን የለም: ሴቷ ወንዱ ላይ ትፈርዳለች ወንዱ ሤቷ ላይ ይፈርዳል:: አንዱ አንዷን አይምንም: ገና ወደአገረ ብሪታኒያ እግሩ ለረገጠ አበሻ የሚሰበከው ይሄንን አለመተማመን ነው::
''እዚህ አገር ሰዉ አይታመንም አውሬ ነው:: ደግሞ ባስ ላይ ባቡር ላይ ስታይ ሰላም እንዳትል ...ይስቁብሀል...'' እየተባለ እየተለመደ ይሄ መጥፎ የማስፈራሪያ መወቃቀሻ ማስጠንቀቂያ ተወራርሶ ዛሬ ዛሬ ያበሻ ዜጎች ሲተያዩ መገለማመጡ አሳፋሪ ሆኗል::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Wed Jul 19, 2006 6:11 pm

:[/list]
Last edited by ዋናው on Fri Jul 21, 2006 6:46 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

PreviousNext

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 1 guest