ጥላ ዓልባ__________(ልብ ወለድ)

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ዋናው » Wed Jul 19, 2006 6:12 pm

.
.
.
(-25-)

ዘካሪያስ ከቤቱ ሲወጣ 4 ሠሃት አልፎዋል የከሠሃቱ ቀዝቃዛ አየር ንፋስ ቀላቅሎ ውሽንፍር ይረጭ ነበር ዣንጥላ እየተላፋ ቆብ እየነጠቀ ታዳሚውን ያበሳጫል:: ዘካሪያስ የውሽንፍሩ ርጥበት የሚያጠፋውን ሲጋራ ደጋግሞ እየሎከሠና እየማገ በእግሩ ወደ ሠፈሩ ባቡር ጣቢያ አመራ:: ሠባዊትን ቀጥሯታል ዛሬ አብረው ቡና ሊጠጡ::
ባለፈው ከእህቱ የተላከለትን የቤተሰብ ደብዳቤ ዛሬ ደጋግሞ ሲያነበው ነበር የመጀመሪያ ቀን ያላስተዋለውን ነገር ዛሬ ያስተዋለው '''.......ሠባዊትን ተንከባከባት መቼም ብልጥ አይደለህምን'ጂ እንደምንም ብትቀርባት ትጠቅምሀለች ...''' ነበር ደብዳቤው የሚለው

''....ዘካሪያስ?''

ከዋላው የሴት ድምጽ ጥሪ ከትውስታው ሲያነቃው ዞረ

''...እርግጠኛ ነኝ እንድላረሳህኝ?''
አለችው የአፍረት ፈገግታ እያሳየችው

''ጤና ይስጥልኝ የእኔ እመቤት አልረሳውሽም::''
አላት ጨብጦ ለፈገግታዋ አጸፋውን እየመለሰ: ከዚህ በፊት እዚሁ ባቡር ጣቢያ የተዋወቃት ሴት ነበረች

''...እንዴት ስሜን አልረሳሽውም?''

''አልረሳውትም ሁሌም ትዝ ትለኝ ነበር እዚህ የባቡር ጣቢያ ስመጣ...''

''እንዴት ነሽ ሠላም ነሽ በተረፈ?''

''ምንም አልል አንተስ እንዴት ነህ ባለፈው ከዛ ቀጭኑ ፀጉሩ ትልቅ ጓደኛህ ጋር አይቼህ ሠላም እንዳልልህ ባስ ውስጥ ነበርኩኝ...''
አንተነህን መሆኑ ገብቶት

''ይሆናል ...ይቅርታ የእኔ እመቤት ስምሽን ግን አላስታወስኩትም...''
አላት እየፈራ ተቅለስልሶ

''ሥሜንማ አልነገርኩህም አንተም አልጠየቅከኝም ''
አለችው በሚያባብል ፈገግታዋ... ባለፈው ካያት ዛሬ ተለይታበታለች አጭር ፀጉሯን የተለየ ቀለም ተቀብተዋለች::

''ለምን?''
አላት እያስተዋላት:

''እኔንጃ አላስፈለገህ ይሆናላ ....''

''አሁን ልትነግሪኝ ቲቺያለሽ?''
አላት የባቡሯን የተለመደ መዘጊየት አስተውሎ ሰሀቱን እያየ ወዲያው ከጣቢያ እንደሁሌም የሴቷ ማስተባበያ ይቅርታ አስተጋባ 5 ደቂቃ እንደሚዘገይ ተናገረች::

''ኤልሳቤት!''
አለችው በሚያተኩሩ ዓይኖቿ እያስተዋለችው

''ታውቂያለሽ ባለፈውም ከወረድኩ በዋላ ምስልሽ ውስጤ ቀርቶ ነበር በዚህ ላይ ባቡር ውስጥ ስናወራ የጠየቅሽኝ ጥያቄ ነበር ያንን ስሜት ተለይቼሽ ከወረድኩም በዋላ ሳስበው ነበር...እንዴት ነሽ አሁን ውስጥሽ ሰላም ነው::''

አይታው የሰለቸ ፈገግታ አሳየችውና
''....ዘካሪያስ ስቃይና መከራ ሲበዛም ይለመድና ያንን ስቃይ ኢንጆይ ማድረግ ትጀምራለህ ...ሠላም ነኝ እጄ እግሬ ሁለመናዬ ይሰራል እንደገና መወለድ ብፈልግም እነዚሁኑ ይዤ ነው የምወለደው ስለዚህ ተስፋ ባጣ'ንኳን በዚህ ጤንነቴ እፅናናለሁ::''
አለችው::

''ኤልሳቤት ስለዚህ አገር መጥፎነት ነግሬሽ የሰለቸሽን ማስጠንቀቂያና ምክር አልሰጥሽም ከሁኔታሽ ብዙ ነገር የገባሽ ይመስለኛል ...ዛሬን ጤነኛ ነሽ ያ ከምንም መልካም ነገር ነው ቀኖችን አመስግኚ::''
አላት ዘካሪያስ የባቡሩ መምጫ መድረሱን ሲያውቅ ሲጋራውን ቶሎ ቶሎ ምጎ አጠፋና ረግጦ በእግሩ ደፈጠጠው::

ስልክ ተለዋውጠው በሌላ ቀን ሻይ ቡና ለማለት ፍቃደኛነቱ ከሷ ጥያቄው ከዘካሪያስ ሆነና ለቅድመ ቀጠሮው ስልክ በመደዋወል እንደሚገናኙ አውርተው እንደባለፈው ሁሉ ዘካሪያስ ቀድሟት ወረደ::

.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው_____________________________________::
Last edited by ዋናው on Sat May 22, 2010 8:38 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Thu Jul 20, 2006 6:03 pm

.
.
.
''ዛሬ እንዴት ነው ቁንጅናሽ ጎላብኝ ልበል?''
አለ ዘካሪያስ ያማሰለውን እስፕሪኤሶ/እንደወረደ/ ጥቁር ቡና ተጎንጭቶ:: ሠባዊት ጀርባዋን የስታርባክ ቡናቤቱ የወምበር መደገፊያ ላይ አደላድላ ፀጉሯን ወደጀርባዋ ንስንስ አድርጋ በኩራት ይሁን በፍርሀት በማይታወቅ ስሜት ዘካሪያስን ታይዋለች::

''ሌላ ቀን ደብዛዛ ነበርኩ?''
አለችው ወደ ያዘችው ማንኪያ ዓይኖቿን እየሰበረች::

''አልወጣኝም ዛሬ የተለየ ውበት አየውብሽ ለማለት ነው ሠቢ የሴት ልጅ ውበት ደስ የሚለው ነገር እንደየስሜቷን እና እንደ ቀኗ ይለዋወጣል ስለዚህ አይሰለችም ሁሌም አዲስ ነው::''

''አመሰግናለሁ ዘኪ ....የውንድስ ውበት?''

''ወንድ ምን ውበት አለው? ምናልባት አቋሙ......ትሉ ይሆናልን'ጂ ወንድ መልክ አይፈጅም ትሉ የለ ራሳችሁ....?''
ሠባዊት ፈገግ ብላ

''ለነገሩ ወንድ አቋሙና ወንዳወንድነቱ በቂ ነው::
አለችው::

''እሺ ሠቢ ባለፈው የጀመርሽልንን ልትጨርሽልኝ ነበር ዛሬ ቀጠሯችን አይደል?''

''ቆያ አንተነህ ይምጣኣ...?''

''ይደርሳል አሁን ምን እሱኮ ቀጠሮ ላይ ዜሮ ነው ወይ ቀድሞ ይገኛል ወይ ያረፍዳል::''

''ሠቢ እዚህ የመጣሽበትን ምክኚያትኮ ግልፅ አድርገሽ አልነገርሽኝም ?''

ሠባዊት እጇ ላይ ያጠለቀችውን የእጅ ጌጥ ባንድ እጇ እየነካካች ትልልቅ ዓይኖቿ ውበትን.......ህይወትን......እያውነትን....እየተመሰሉ ወደውኃላ ነጎዱ ባህርና ውቂያኖስ ተሻግራ በሀሳብ ወደአዱ ገነት ሸፈተች::
.
.
.
የቤቷ በር በኃይል ይንኳኳል

''ጓ ጓ ጓ!!!!!''
ተጨናብሳ ኮመዲናዋ ላይ ያለውን መብራት በዳበሳ ፈልጋ አበራችው:: 11:30 ከጠዋቱ

ከገዛህኝ ጋር በፀብ ከተለያየች በዋላ ጊቢው ውስጥ ያለውን ዋናውን የቤተሰቧን ቤት አከራይታ እሷ ሰርቪስ ቤት ውስጥ ነበር የምትኖረው እሷ የምትጠቀምበት የውጪ ትንሹ በር ከርሷ ቤት አጠገብ ነው ያለው ዋናው የጊቢው በር በትልቁ ቤት ትይዩ ይገኛል::

ፒጃማዎን አስተካክላ ለመክፈት እየተጣደፈች የቤቷን በር ከፍታ ወደውጪው አመራች
''ማነው....?''

''እኔ ነኝ ''
ድምጿን ስትሰማ ደነገጠች የመርዶ ሰኃት በመሆኑ ግራ ተጋብታ '...ምንስ የሚረዳ ሰው አለኝና ' አለች ለራሷ::

''መጣው!''
በሩን ከፈተች የጊቢው ውሻ ከዛ በኩል ይጮዋል ንፋሱ የጊቢውን ዛፍ በማለዳ ያስዘምራል አዋፍ ከዛፉ የንፋስ ኪልኪላ ጋር እየትጋፉ የጠዋት ጫጫታቸውን ያሰማሉ::

አክስቷ ነበረች: በደቀደቀ ሌሊት ከቤቷ ገፍትራ ካስወጣቻት በዋላ አላየቻትም :: ራሷን ጭምር የተከናነበችው ነጭ ጋቢ በሌሊቱ ቦዝዞ እየታየ ከውስጡ ግራ የመጋባት ገፅታን የያዘው ያክስቷ ፊት ያስፈራል::

''ምነው አክስቴ???''
ደነገጠች ሠባዊት በሩን ከፍታ እንድትገባ መንገድ ስትሰጣት አክስቷ ግን ዝምብላ ቆመች

''ምነው በሰላም ነው አክስቴ?''

''መጀመሪያ ደጅሽን ሳልረግጥ ይቅርታሽን ስጪኝ የኔ ልጅ?''

''የምን ይቅርታ ......ኸረ ግቢ ደግሞስ ምን መጣ በዚህ ሌሊት ንገሪኝ አታስጨንቂኝ...''

''በሰላም ነው ሠባዊት አንቺ ብቻ ይቅርታሽን ስለምንሽ እሺ በዪኝ አጥፍቼያለሁ በደሌ ረፍት ነስቶኛል''

''ይቅር ብዬሻለሁ አክስቴ ድሮም እኔ ቂም አልያዝኩብሽም ግቢ......''

ወደቤት ገብተው አክስቷ ካልጋዋ ግርጌ ፈንጠር ብሎ ወዳለው የስፖንጅ ወምበር ላይ ተቀምጣለች ሠባዊት አሁንም አልተረጋጋችም

''...ምን አመጣሽ አክስቴ እስቲ ንገሪኝ ጨንቀኝ'ኮ''

''መጀመሪያ የመጣውት ዛሬ የ16 ቀኑ የፍልሰታ ፆም ስለሚጀመር ወደ ሱባኤ መሄዴ ነው ከነአጢያቴ ብሄድ የምማፀነው አምላክም አይታረቀኝም ለዛ ነው:: ሁለተኛ እስከዛሬ ሚስጥር የሆነ ጉዳይ ነበር ያንን ነገር ላንቺ ከኔ በቀር ማንም ሊነግርሽ ስለማይችል በዛው እሱንም ልነግርሽ ነው አመጣጤ...''
ሠባዊት ዓይኖቿ ፈጠጡ የሌሊት እንቅልፏ ተሰለብ

''የምን ሚስጥር አክስቴ?''
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው___________________________________::
[/list]
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Fri Jul 21, 2006 8:32 pm

.
.
.
''ልጄ አሁን አንቺ ትልቅ ልጅ ሆነሻል የሙት አደራነቴን ቀርጥፌ መብላቴ ሳያንሰኝ ያንቺ ወንድምሽን የማግኘቱን መብትሽንም ነፍጌሻለሁ .....''

''ምን...................?''
አለች ሠባዊት ደንግጣ ብርክ ይዟት

''.....አክስቴ ወንድም አለኝ እኔ?''

''አዎ ልጄ.... አባትሽ ደረጀ ያንቺን እናት ከመውለዱ በፊት ገነት ከምትባል አንዲት ሤት ወንድ ልጅ ነበረው ያ ያባትሽ ልጅ ወንድምሽ ያሬድ ይባላል ከዘመድና ከቤተሰብ ተገልሎ ሀረር ነበር ያደገው ...''

''እና አሁን በህይወት አለ አክስቴ...?''
አለች የደስታ ይሁን የድንጋጤ የማይታወቅ እንባዋን እያበሰች

''አዎ አለ ::እናቱ ሌላ እንግሊዛዊ አገባችና ወደ እንግሊዝ አገር በሄደች ባመቱ እሱም እሷን ተከትሎ ካገሩ ወጣ:: ካባትሽ ጋር የነበረው ቅርርብ እምብዛም ነበር:: ካገሩ ከወጣ በዋላ ግን አባቱን በጣም ፈልጎ ዘውትር ይደውል ነበር .....አባትሽም ያንቺን ከልጅነትሽ ጀምሮ አብሮ የኖረውን የወንድምና የእህት ፍቅር እያሰበ እናትሽን አሳምኖ ይህ ወንድምሽን 'ያሬድን' ድንገት አንድ ቀን አምጥቶ ወንድምሽ መሆኑን ሊነግርሽ ያስብ ነበር ...ግን ያ ሀሳቡን እውን ሳያደርግ አፈር ለበሰንጂ...''
አክስቷ ስታለቅስ እምባዎቿ መንታ ሆነው ቁልቁል ሲወርዱ ላሳለፈችው ጊዜ የበደለኝነት ፀፀቷ ፊቷ ላይ ይታይ ነበር::

''...አባትና እናትሽ ከሞቱም በዋላ ግን ዘውትር እኔ ዘንድ አጠያይቆ እየደወለ አንቺን እንዳገናኘው ይጠይቀኝ ነበር እኔ ግን እንደማላገኝሽና ያለሽበትን እንደማላውቅ ስነግረው ተስፋ ቆርጦ ተወው::''

''ለምን አክስቴ...ማን ነበረኝ በዚች ምድር እናትና አባቴ ሞቱ አንቺም ፊትሽን አዞርሽብኝ ምናለበት ወንድም'ንኳን እንዲኖረኝ ብትፈቅጅልኝ...?''
አክስቷ ተምበርክካ ሠባዊት ጉልበት ላይ አነባች ራሷን ረገመች የሠባዊት ንፅሑ እንባ ውስጧን ጭምር ለበለባት::

''...እሺ አሁን የት ብሄድ አገኘዋለሁ?''
አለች ሠባዊት በተከፋ ፊቷ
አክስቷ ለሱባኤ ብላ ከሰነቀችው ጓዟ ውስጥ የወንድሟ ያሬድን ደብዳቤዎች ሰጠቻት የተነበቡና ያልተነበቡ

''...ልጄ ፀፀቱ ለብልቦኝ ሰሞኑን ያላፈላለኩበት ቦታ አልነበረም የበፊቱን ስልክና አድራሻ ቀይሯል ቢቸግረኝ እናቱ ዘንድ ደወልኩኝ ግን እናቱ አልነበረችም ያ ነጭ እንግሊዛዊ ባሏ ያገባት አዲስ ሚስቱ ከተፋቱና ከተለያዩ ሁለት ዓመት እንደሆናቸው...አድራሻዋንም እንደማታውቅ ነገረችን::''

አክስቷ በእንባ በፀፀት በአፍረትስሜት እየተፈራረቀች ይሄንን የማለዳ ዜና ስትነግራት አዲስ ጀምበር ተወለደች ጠዋቱን አሳቀችው ትላንት ከጭለማው ጋር አብሮ አርጅቶ ተተዘተ:: ሠባዊት አሰበች ዛሬን ከስሯ ለይቅርታ የተደፋች አክስቷን ቁልቁል እያየች .........አስታወሰች ትላንትን ያ ጣፋጭ የቤተሰባዊ ጊዜ........አሰበች ነገን ልክ በዛሬው ማለዳ ቋ! ቋ! እያሉ ለጊዜ መገስገስ እንደሚራወጡት ሴኮንዶች እሷም ለነገ ተስገበገበች: በእጇ የአባቷ አብራክ ክፋይ የሆነውን የገዛ ወንድሟን የእሕትነት ፍቅር የራበውን ደብዳቤ ይዛለች::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው_____________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sat Jul 22, 2006 7:20 pm

.
.
.
ሠባዊት በእንባ ታጅባ የማሳዘን ውበታዊ ግዝፈቷ እየጎላ ታሪኳን ስታጫውታቸው አንተነህ ቦርሳውን ከፍቶ ወረቀት ዘርግቶ ምስሏን በከሰል/ቻርኮል/ እየነደፈ ነበር:: ሠባዊት በትውስታዋ ብትመሰጥም የአንተነህን የሚያተኩሩ ዓይኖች በመገረም እያየቻቸው ነበሩ:: ሠባዊት የእንባ ጅረት ያደፈረሰው ዓይኖቿ ላስተዋላቸው ያንሰፈስፋሉ:: በመሀል በለስላሳ የፊት ማበሻ ወረቀት ያይኖቿን ጥጎች ያፈተለኩ እንባዎች ትጠራርጋለች ደግሞ ትቆይና የታችኛዋን ወለላ ከንፈሯ በላይኛዋ ከንፈሯና ጥርሷ በስሱ ነከስ ታደርግና ያይኖቿ የታችኛ ቆቦች እየተርገበገቡ ዘካሪያስን ያያሉ::
ይሄ እይታዋ ይሄ አስተውሎቷና የፊቷ እንቅስቃሴ የዘካሪያስን ልብ ተፈታተኑት
ማንነት...........የራስነት.......ማንሰፍሰፍ......ድንቅ ውበት.....ማሳዘን.......እነኚህ ነገሮች ውስጡ እየተንጫጩ ነፍስያው ሠባዊትን አለችው:: መወደድ ባይችልን'ጂ መውደድ በመቻሉ እርግጠኛ ነበር::

''እዚህ ከመምጣትሽ በፊት በቅርብ የምታግገኚያቸው የራስሽ ሌሎች ዘመዶች አልነበሩሽም?''
አላት ዘካሪያስ በረጅሙ ተንፍሶ የሎከሰውን ሲጋራ አጣጥሞ በስሜትና በደስታ እየሳበው አጫጫሱ አጫሾችን ሁሉ የሚገፋፋ ነበር::

''አልነበረኝም ማንም.....አክስቴ ለበደሏ ማካካሻ እንዲሆናት እዚህ እስክመጣ ብዙ ነገር ተባበረችኝ ግን አብሪያት ልኖር እንደማልችል ነገርኳት እንደነገርኳችሁ እዚህ የተቀበሉኝ የጎረቤቶቼ ቤተሰቦች ነበሩ እነርሱም እኔም ከመምጣት በፊት ወንድሜ ያሬድ ደረጀን ለማፈላለግ ብዙ ጥረዋሉ እዚህም እንደመጣው አብሬያቸው ከለንደን ወጥተን ሁሉ አፈላልገነዋል:: በተረፈ አገር ቤት እኔ የጋዜጠኛነቱን ስራ ብሰራም ከእናትና ከአባቴ የወረስኩት ገንዘብ እኔን ቀርቶ የልጅ ልጄን ሁሉ የሚያኖር ነው:: ግን ሀብት ብቻውን ምንም ዋጋ የለውም ሀብትን የሚያክል ነገር ቀርቶ እህል'ንኳን ብቻህን ቆርሰህ መብላቱ ያስጠላል ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሰው ያስፈልግሀል....ለዛም ነው እኔ በቤተሰቦቼ ሀብት ውስጥ ተሳታፊ ያልሆንኩት ድርጅቱን ኮንትራት ሰጠው, ቤቱን አከራየው ቀሪው ብር ባንክ ነው:: ፈጣሪ መቼም ጨርሶ አይረሳህም አሁን ደግሞ ከረፈደ ወንድም እንዳለኝ አወቅኩኝ.....''

ሠባዊት ስታወራ የመሰማት ሞገስ አላት ድምጿ ያዜማል::

''ሠባዊት እርግጠኛ ነኝ ወንድምሽን ታገኚዋለሽ እኛም የበኩላችንን እንተባበራለን::''
አላት ዘካሪያስ: አንተነህ በስሜት የሷን ምስል ነድፎ ራሱን እንደ ደቂቃ ቆጣሪ እያዟዟረ አንዴ ምስሉን አንዴ እሷን እያየ ከዛም ዓይኖቹን ገርበብ ያደርግና እንደገና ወደውኃላ ለጠጥ ብሎ ራቅ ብሎ ያየዋል::

''እስቲ አላለቀም.....?''
አለችው ፈገግ ብላ በአኩኃኑ ለማየት ቸኩላ አሳያት....

ዘካሪያስም ሠባዊትም እኩል የመገረም ቅላፄ ሲያወጡ በቡና ቤቱ ያለው ሁሉ ትኩረቱ ወደነሱ ሆነ:: በጣም አስመስሎ አስቀምጧታል የአንተነህ ችሎታ ሠባዊትን ብቻ ሳይሆን የስታርባክ ታዳሚያኑ ሁሉ አስደመሞ ነበር:: ይሄን ጊዜ ዘካሪያስ በኩራት ከጥቂት ቀናት በዋላ የሚከፍትውን የአንተነህን ኢግዚብሽን ማስታውቂያ ለተደማሚያኑ ማደል ጀመረ::
.
.
.
ዋናው___________________________________::
Last edited by ዋናው on Wed Mar 12, 2008 11:43 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sat Jul 22, 2006 7:21 pm

.
.
.
ይቀጥላል
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sun Jul 23, 2006 10:17 pm

(-26-)
___የፍቅር ምሽት___
.
.
.
ዕለተ ረቡዕ እንደ ታናናሽ ወንድሞቿ ሰኞና ማክሰኞ አብቅታ ልትሸኝ ነው:አኩራፊው የብሪታኒያ ደመና ለንቦጩን በለንደን ላይ እንደጣለ መሸ ይበርዳል ይወረጫል... ዘካሪያስ ስሜቱ ስቋል ውስጡን ግን አላወቀውም ወይም ሊያዳምጠው የፈለገ አይመስልም ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ቫኔሳ ደውላ ፍቅር በተራበ አንደበቷ አናግረዋለች እሱ ግን አሁን ከሠባዊት ጋር ነው:: አንተነህ ዛሬ አዳሩን እየሰራ የሚያነጋው የቀለም ቅብ እንዳለ ነግሯቸው ሄዷል ድንገት ተነስቶ:: ውስጡ አንድ ሀሳብ ሲወለድ ምጥ እንደያዛት ሤት ተቅብጥብጦ ወደ ስቱዲዮው መሮጥ ልምዱ ነው::

ቪክቶሪያ የተሰኘ የለንደን ሰፈር ናቸው ትኩስ ጥንዶቹ ዛሬ ምሽት:: በርካታ መቶውች ዘመናትን ያስቆጠረው የቪክቶሪያ ባቡር ጣቢያ ሁሌም ግርግር ነው የማይታይ ዓይነት የሠው ዘር የለም ሁሉም ሻንጣውን እየጎተተ ይዋከባል ተቀባይና ሸኚዎች በአበባና በስንብት መሳለም ሰፈሩን ያደምቁታል:: ከዋናው የባቡር ጣቢያ ወጥተው ያገሩ ቀያየ ባለፎቅ አውቶብሶችና ጥቋቁር ታክሲዎች የሚርመሰመሱበትን መንገድ አቋርጠው ትይዩ ሲሄዱ የከተማው የታወቀ የሙዚቃ ትዕይንት የሚታይበት 'አፖሎ' ቲያትር ቤት አለ:: ከስሩ ተነጥፈው በወፍራም የሌሊት ልብስ የተጀቦኑ የጎዳና ነዋሪዎች ቢራዎቻቸውን ይጎነጫሉ ከፊሉ እያጨሰ መፀሀፉን ያነባል::

አስተናጋጁ ያመጣውን የወይንጠጅ ለዘኪና ለሠባዊት አስጎብኝቶ ካበቃ በዋላ ያሸረጠለትን ነጭ ጨርቅ በቄንጥ እያስተካከላት በቀረበላቸው ብርጩቆውች ቀዳላቸው: ቀይ ወይን.... ደብዛዛ የቤቱ ብረሀን.... መሀላቸው ፍቅርን የሚያሳይ የሻማ ብርሀን.... ለምሽቱ ማማር የራሳቸውን አስተዋጽዖ አድርገዋሉ:: በመስኮት የለንደን ያረጁ የድንጋይ ፎቆች ውስጥ ብቅ ያሉት መብራቶችና የጎዳናው ብርቱካናማ መብራት ይብረቀረቃል::
ብርጭቆዋቸውን አንስተው ሲያጋጩ ለ...... ብለው ስያሜ መስጠቱን ሁለቱም አሳፍሯቸዋል ብቻ ''ችርስ'' ብለው አንዳች አይል ካለው የፍቅር መሽኮርምም ጋር ፅዋቸውን አነሱ::

''ሠቢ ከመጣሽ ስንት ጊዜ ሆነሽ?''
አላት ዘካሪያስ የእግራ እጁን በቀኝ እጁ እያሻሸ ሠባዊት በውበቷ ላይ ሌላ የቆነጀ አንዳች ሃይል ያለው ሌላ ውበት ደርባ የማስፈራት ሞገስ አላት

''ሁለት ወር አለፈኝ አቤት ጊዜው እንዴት ይሄዳል?''

''መቼ ነው የምትመለሺው?''

''ነግሬህ የለ አስር ቀናት ቢቀሩኝ ነው:''

''በጣም ፈራው::''
አላት ወደወይኑ ብርጭቆ ዓይኖቹን ሰብሮ

''ለምን?''

''ውስጤ የነበረሽን ስፍራ በየዕለቱ እያሰፋሽው አሁንማ በቃ መላ ኣዋሳቶቼ አንቺን አንቺን ይሉኝ ጀምረዋል....''
የመደንገጥ ፈገግታ ከጥቂት ትንፋሽ ጋር አውጥታ ወደወምበሯ መደገፊያ ለጠጥ ብላ ተመለከተችው በነኚያ የፊት እንቅስቃሴዎቿ....

''ለምን?''

''እኔንጃ እኔም አላውቀውም እንደወደድኩሽ እርግጠኛ ከሆንኩ ግን ቆየው''

''ልብህ ሁለት ሰው እንዴት ያስተናግዳል ዘኪ?''
ይሄን ጊዜ አሳላፊው ያመጣውን የሰላጣ ምግቦች በጥንቃቄ በየፊታቸው አኑሮ የገቢያ ፈገግታውን አሳይቶ ሄደ

''ሠቢ ምንም ዓይነት ማስተባበያ ልልሽ ያዘጋጀውት ነገር የለም አዎ ቫኔሳ እጮኛዬ ናት ግን.................''

''ግን ምን........?''
ዘካሪያስ እውነትም ያዘጋጀው ንግግር አልነበረም ስሜቱ ግን ሠባዊትን ብሎታል
''......ሠቢ ስለነጭ ፍቅር ከነጭ ጋር ተውዳጅቶ ስለመኖር ምንነት ብነግርሽ ላይገባሽ ይችል ይሆናል''

ሠባዊት ፈገግ ብላ እያየችው ሹካውን ወደሰላጣው ስታስጠጋ ዘካሪያስ ሎሚና ዘይት ጨመረላት
''...እሺ እሱ እኔን ምንም አያገባኝም እኔን ግን እንዴት ወደድከኝ.... ማለቴ ለምን?''

''ሠቢ የመውደድ ስሜት እኛ ባዘዝነውና ባልነው ሰሀት አይከሰትም እንዴት ወደድከኝ ላልሽው ብዘረዝራቸው የማያልቁ ብዙ ብዙ ምክኒያቶች አሉኝ በጣም ቆንጆ ነሽ: እርጋታሽ አመለካከትሽ ብቻ .....''

''ዘኪ አንተ የሠው ነህ ስለዚህ አሁን ያልከኝን ምክኒያቶች ለማድነቅ ብቻ መጠቀም አትችልም ነበር? የግድ የራስህ የማድረጉ የውስጥህን ፍላጎት ተቆጣጥረህ.......?''

''የምትቆጣጠሪያቸው እና የማትቆጣጠሪያቸው ስሜቶች አሉ ሠቢ በእርግጥ ሞክሬ ነበር ግን ደግሞ የማፍቅርን መስህብ የሚታገል ቢኖርም የሚያሸንፈው የለም ....ቆይ ስሜቶቼ ላንቺ እንዳዘነበሉ የኔን ስሜት አይተሽ አልገመትሽም?''
አላት እያጎረሳት

''ያው አንድ የሚገባህ ነገር ይኖራል ግን ደግሞ አንዳንዴ በምታሳየኝ ቁጥብነትህ ያንን ሀሳብ እንዳላስብ ያደርገኛል::''

''እሺ አንቺስ ምን ዓይነት አመለካከት አለሽ ለእኔ?''

''እ.........መጀመሪያ ሰሞናት በጣም ስትንከባከበኝ ያው የወንድ ተግባሩ ነው ብዬ ብዙም ቱክረት አልሰጠውትም ነበር በዋላ ግን በተለይ ከተወሰነ ሰሞን ወዲህ ....''
አልጨረሰችውም ዓይኖቿን ሰበረች ያፍንጫዎቿ ቅጠሎች ተንቀሳቀሱ እሷ ያልጨረሰችውን ንግግር ስሜቷ ቀድሞ ተናገረ
ሠላጣውን እንደጨረሱ ሁለተኛው ዋና ምግብ መጣ እየተጎራረሱ በዓይናቸው እየተፋጠጡ በስሜት ያለድምፅ እየጮዑ ምሽቱን ቀጠሉ:: ሁለተኛው ምግብ አልቆ ሶስተኛው ምግብ ቀረበ በክሬም የረጠበ የቸኮሌት ኬክ ተጎራረሱ እሱንም ያለ ቃል ያለ ምንም ድምፅ.... አንዳንዴ መውደድ ሲበዛ አፍ ይሎገማል አፍ ሲሎገም ስሜት ከስር ይጨፍራል ዋይ! ዋይ! እያለ::

ወደመፀዳጃ ቤት ደርሳ መጣች ዘካሪያስ በምግብ ቤቱ ህግ የማጨሱን ዕድል አላገኘም እሱም ሲጋራውን የሚያስረሱ ሌሎች ቅስፈቶች ውስጥ ነበር:: ስትመለስ ከናፍርቶቿ አልተቀባቡም ::

''ዘኪ መቼም ብዙ ታሪኬን በግልፅነት አጫውቼካለሁ ካለኝ ባህሪዬ በጣም ድብቅነት አይመቸኝም አይናፋርና ፈሪም ብሆን.....እና ወንድ እንደማላምን ነግሬካለሁ ልቤ በወንድ ላይ አቂሙዋል::''
አለችው ወይኗን እየተጎነጨች::

''አዎ አውቃለሁ ይሄ አሁን የምልሽን የኔን ፍቅር እንድታስተናግጂ የሽንገላ ወይም ባራዳ የመጀንጀን አድርገሽ አትይቢኝ....እና ሠው ሁሉ ይለያያል ባለሽ ኤክስፒሪያንስ ይህንን ማሰብሽ ትክክል ነሽ ግን ደግሞ ልብሽ ቢያቄምም ስሜትሽ ...ሤትነትሽ...ጠቅላላ ሰዋዊ ፓርትሽ.... ወንድ ያስፈልገዋል እና ያንን ወንድ የማወቁ ወይም ባንቺ ሚዛን የመመርመሩ ዕይታሽ ምን አይነት እንደሆነ አላውቅም ግን ባንድ ነገር ሁለታችንም እርግጠኛ ነኝ ሰው ያስፈልግሻል::''
አላት ዘካሪያስ ሲያስረዳት የድምጹ አወጣጥ እርጋታውና የእጆቹ እንቅስቃሴዎች ሠባዊት ልብ ውስጥ ቦታ ነበራቸው::ከትንሽ የቃላት ምልልስ በዋላ አንድ የሚገርም የፍቅር አስማታዊ ክስተት ታየ::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው ___________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Wed Jul 26, 2006 9:01 pm

ሠላም ውድ አንባቢያኖቼ ሆይ
በሰሞኑን የዋርካ መዐበል ምክኒያት የጀመርኩትን ልብ-ወለድ መቀጠል አልቻልኩም: በተደጋጋሚ እየገባው ፖስት የማደርጋቸው ፅሑፎች በጊዚያዊው የዋርካ ችግር ምክኒያት ሊገቡልኝ ባለመቻላቸው ለጥቂት ቀናት ፅሑፌን አቋርጬ በትህግስት መጠበቁን መርጬያለሁ::
ጥቂት ቀናት ቆይቼ እሺ እንደሚለኝ ተስፋ በማድረግ ሰሞኑን ልቦለዱን እንደምቀጥል በአድናቂዎቼና በአንባቢዎቼ ስም ቃል እገባለሁ::

ከብዙ ብዙ ማክበር ጋር

ዋናው_________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Fri Jul 28, 2006 8:09 pm

.
.
.
ትኩስ ስሜት ያወረዛው የሁለቱም እጆቻቸው ተቆላለፉ:: የሠባዊት ዓይኖች ተስለመለሙ..... አፈሩ....የፍቅርን ስሜት ጨረር ሠሩ:: ዘካሪያስ ውስጡ እሷን ካለው ቆይቶ ነበርና የሻማውን ብርሀን የወይኖቹን መሰናዶዎች ከስሩ አድርጎ በደረቱ እየተሳበ ወደከናፍርቷ አመራ:: የመሳሳማቸው ቅስፈት በሷ እምር ብሎ መደንበር ተቋረጠ በ''ምነው?'' ዓይነት ጥያቄ ቅንድቦቹን ወደግንባሩ እያሰመረ አያት::

''ዘኪ ለምሰራው ነገር እርግጠኛ አይደለሁም::'' አለች የወይን ብርጭቆዋን እያነሳች

''ሠቢ ሁለታችንም'ኮ የሰራነው ነገር የለም ስሜቶቻችን ግን የሆነ የተግባቡበት ነገር እንዳለ ግን መናገር እችላለሁ::''
አላት በቀኝ እጁ ያንገቱን ጀርበ እያሻሸ

''ስሜቶቹ የእኛ ናቸው ዘኪ''

''አዎ የኛ ናቸው አውቃልሁ ግን እኛ ሠዋዊ ውሸታምነት አለብን ስሜት ግን መቼም አይዋሽም::''

''ስሜት ባይዋሽም ይቸኩላል::''

''ቢቸኩልም የሚፈልገውን ነው የሚያደርገው:''
በንግግር ዓይኖቻቸው ተቆላልፈው የሁለቱም ልብ ይመታ ነበር::

''ዘኪ ........?''
አለችው ድንገት አሳብ እንደመጣላት ፈገግ ብላ
''አቤት ሠቢዬ''
አላት በፍቅር ዜማ

''መጠጥ እንቀይር?''

''ምን ይምጣልሽ ነው ወይስ ቤቱንም እንቀይር ምን ይመስልሻል ?''

''እንደፈለክ ግን ትንሽ ሞቅ እንዲለኝ እፈልጋለሁ::''

''እሺ እውነትሽን ነው ወይን'ኮ ሲበዛ ጆሮ ከማጋል ሌላ መልህክት የለውም''
ሲላት ወደሳቅ ያጋደለ ፈገግታ አሳይታው

''ጆሮ ማጋል ብቻ የሆድህን ያወጣዋል...''
አለችው: ሁለቱም ሣቁ::

ከሻማጋ የተለኮሠው ትኩሥ ፍቅር....በወይን ጥዋ የተቀደሠው አዲስ ስሜት...ትዝታነቱ የዘካሪያስ የማፍቀር ዕጣው ሆነና ምሽቱ ሙጥጥ አለ:: ከቪክቶሪያ ተነስተው ወደ ዩስተን የተባለ ስፍራ ሄደው በምሽት ክበብ ሙዚቃ አህምሮዋቸውንና ስሜታቸውን አዝናንተው ነበር ወደ ዘካሪያስ ቤት ያመሩት::
ቤት ደርሰው መኝታን ሲያስቡ የለንደን ጭለማ ሆኖንጂ አዋፋት ተንጫጭተው መደበኛ ቋንቋቸውን ጀምረዋሉ ግን የደቀደቀ ጨለማ ነው:: ሠባዊት ሞቅታዋ ወደስካር ባይለወጥም ጉንጮቿ ፈመዋሉ ፈገታው አይቆምም::

''መኝታዬ ተዘጋጅቷል?''
አለችው የሲጋራውን ጪስ በመታዘብ እያየችው

''አዎ!''
አላትና ተነስቶ ጥርሱን ቦርሾ መጣ ዘካሪያስ አጠገቧ ሲቀመጥ የስሜቱ ያንን ያህል መሆኑን እየታዘበው ነበር

''ዘኪ አንድ ነገር ልንገርህ አልዋሽህም ስሜቴ ብቻ ሣይሆን ልቤም ከጅሎሀል ግን እኔ የመዋደድ ዕድሉ የለኝም ባልጠበቅኩት መንገድ ታስቀይመኛለህ ''
አለችው እጆቿን አጣምራ አንጋጣ ከጎን እያየችው

''ሠቢ ገና ለፍቅር ወለል ብሎ የተከፈተውን ልቤን ያልሰራውትን አጢያት እየተነበይሽ ውስጤ የበደለኛነት ስሜት አትፍጠሪብኝ...''

''ማስጠንቀቄ አይደለም ዘኪ.....ምነው ዘባረቅኩኝ ሞቅ አለኛ ለዛ ነው ....በስንት ጊዜዬ ብጠጣ....''
ብላው ለማቀፍ የሶፋው መደገፊያ ላይ የተዘረጋ ክንዱ ላይ ተንተራሰች ::

ሥሜት ጓዙን ጭኖ በፍቅር ዘመቻ ላይ ሆይ!! አለ መዋደድ ከእንብጡ ወደ አበባው እየጎለመሰ እያው ሆነ ሠባዊት ወንድ ላይ ብታቄምም ወንድነት እንደናፈቃት ሁሉ በወሲባዊ ስሜት ግልቢያ ላይ ታስታውቅ ነበር:: ዘካሪያስም ሽንጡ በጎመጃቸው ጭኖቿ መሀል ሲዋዥቅ ልቡ በደስታ እየፈነጠዘች ነበር::
በከፋው የለንደን ብርድ በሙቀት ሲቀልጡ ሌላ ዛሬ ለመወለዱ የመስኮቱን መጋረጃ የገለጥች ደብዛዛ ጀንበር ተላከች::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sat Jul 29, 2006 9:01 pm

(-26-)
.
.
.
አንተነህ ሶፋው ላይ በጀርባው ተንጋሎ ጠቅልሎ የሎከሳትን ሲጋራ ያጨሳል አገጩ ላይ ብትን ብለው ያደጉት ፂሞችን ባንድ እጁ ጣቶች እየፈተለ ዘካሪያስን አየውና

''እና በማን ይፈራል ሞት እያዜምክ በፍቅር ዘመትካ....?''
አለው

''ምን ላድርግ ፒካሶ ያንተ ምክር ነው ስሜትህን አዳምጠው አላልከኝም አዳመጥኩት ሠባዊትን አለኝ አደረኩት ልቤ ፍቅር ሸተተው የሠባዊትን መሀዛ ሠጠውት::''

''አሪፍ ነው ሠባዊት ደስ ያለችኝ ዘረኛ ሆኜ አይደለም ዘኪ ቫኒንም እወዳታለሁ ታውቃለህ ብዙ ነፃነቶች ከእርሷ ተምሬያለሁ ሠባዊት ግን አንድ የተለየ መለኮታዊ ሀይል አላት ያንን ውብ ዓይኖቿ እያየህ ውስጧ ትገባለህ ውስጧ ደግሞ ፍቅር...ሀዘን....ርሕራዔ....ሕይወት ህይወት የሚሸቱ ሕያውነት....ብቻ የተለየች ነች:: ጓደኛዬ ስለሆንክ አሰብኩልህ ባለፈው በቻርኮል ስስላት ዓይኖቿ አንተ ላይ ነበሩ በፍቅር ቅልጥ ማለቷ ያስታውቅ ነበር::''

''አዎ እንዲህ እያጃጃልከኝ አስከንፈኝ አንተ በጨ የሆንክ ሠው....''
አለው ዘካሪያስ ወደአንተንህ ስቱዲኦ እየገባ የጨረሰውን የመጨርሻ ፔንቲንግ ኢዝሉ ላይ ተሰቅሎ ዘካሪያስ ቢያየው ፈዞ ቀረ:: ሠባዊት ነች: ዓይኖቿ ቅርዝዝ ብለው ፊትለፊት ያያሉ ከውሀላዋ ፀጉሯ ንፋስ እንደበተነው ሁሉ ተንሳፏል:: ሠማያዊ ቀሚስ ለብሳለች ካማረ የፊቷ ገፅ ስር የሚታየው ቅስት አንገቷ ላይ የጠለቀው ያንገት ጌጥ ግራና ቀኝ እንደ ቀስት ከተጋደሙት የደረቷ አጥንት መሀል ወርዶ ለሠፊ ትከሻዋ መሀልነቱን 'ሚመሰክረው ስፍራ ላይ ተንጠልጥሎዋል በወርቅ የተሸለሙ የቁልፍ እና የሌንስ ምልክት ያላቸው ቅርጾች በሀብሉ ላይ ተንጠላጥለው ይታያሉ: በእጇ ትኩስ ያልፈነዳ ቀይ የፅጌሬዳ አበባ ይዛለች ከውሀላዋ ዳመና ይታያል መዝነብ የሚፈልግ ሠማይ
አንተነህ ስራውን ከሚያደንቅለት ጓደኛውጀርባ ሆኖ እሱም እንደአዲስ እያየው ነበር

''ፒካሶ ሙት ይሄ ድንቅ ስራ ነው እንዴት ያምራል.....ዋው...!!!!''

''አመሰግናለሁ ዘኪ አንተ ፍቅር ስትሰራ እኔ ይሄንን ሸራ ሠባዊትነትን እየከተብኩበት ነበር::''

''እስቲ ማብራሪያ ይስጡበት የተከበሩ አአርቲስት አንተንህ''
አለው ዘኪ ለአንተነህ ስፍራውን እንደመልቀቅ ብሎ

''ሠባዊት ለእኔ የገባችኝ በዚህ መልኩ ነው ዘኪ አንገቷ ላይ የምታየው ጌጦቿ ምክኒያት አላቸው ሌንሱ የወንድሟን መፈለግ ለመግለፅ ሲሆን ቁልፉ ለእራሷ እና ለቤተሰቧ አብት ያላትን ታኣማኝነት ነው:: የለበሰችው ሠማያዊ ቀሚስ ደግሞ ተስፋዋን ያሳያል ሠማያዊ ቀለም ሁሌም ህያውነትና ንፅሑ ተስፋን ይወክላሉ ...በእጇ የያዘችው እንቡጥ አበባ ምንነት ላንተ መንገር አያስፈልግም ዘኪ....''
አለው አንተነህ ፈገግ ብሎ

''ትኩሥ ፍቅር....?''
አለ ዘካሪያስ እጆቹን አጣምሮ ወደ ስዕሉ እንዳፈጠጠ:: አንተነህ ነገ እግዚብሽኑ ለህዝብ ይታያል ካቀረባቸው ስራዎች መካከል ሁለቱ በሠባዊት ታሪክ ተነሳስቶ የሰራቸው ናቸው አሁን ይሄ የሚያዩት እና አንደኛው እዛው ጋለሪ ያለው ሌላ ዘመናዊ የቀለም ቅብ /ምደርን ፔንቲንግ/ ከቀናት በፊት ነው ስራዎቹን ያስረከበው ይሄንን የመጨረሻውን ስራውን ካቀረባቸው ስዕሎች የተለየ በመሆኑ እንደ ርሀዊነቱ ሪያልስትክነቱ ያማረ ፍሬም ስለሚያስፈልገው እሱን ለማስተካከል ነበር::

''ቫኒ ትላንት ደውላልኝ በርካታ የእግዚብሽኑ ታዳሚያንን ከምጸራበት ስፍራ ይዛ እንደምትመጣ ነግራኛለች''
አለው አንተነህ::

''አዎ ባለፈው እኔጋ ከነበሩት የኤግዚቢሽኑ ግብዣ ካርድ ብዙ ወስዳ ነበር.....ዛሬ አዳሬ ወደ እሷው ነው አይለኛ ጦርነት አለብኝ ፒካሶ''

''ቀይ መስቀል ካስፈልገህ ደውል'ንግዴ...''
አለው አንተነህ እያሾፈበት

''ቀልድ አዎ አንተ ምን አለብህ...... ነገ ሠባዊትም ቫኒም አሉ ምንድነው የማደርገው?''

''ሠባዊት ታውቃለች አይደልንዴ ...?''

''እሱማ ታውቃለች...''

''እና ታዲያ ምን ችግር አለው?''
ዘካሪያስ ግራ በተጋባ መንፈስ

''እንዴት ምን ችግር አለው? ፒካሶ የፈለገ ቢሆን ሠባዊት ደስ አይላትም::''
ሊፈጠር ስለሚችለው ነገር ትንሽ ተወያዩ:: የዘካሪያስ ስልክ አቃጨለች

''ሄሎ....'' አለው የሴት ድምፅ
ኤልሳቤት ነበረች::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

ዋውውውውው

Postby ሚላት11 » Sat Jul 29, 2006 10:47 pm

ዋው እንዲት ደስ የሚል ልብ ወለድ ነው በናትህ አብሶ ስለ ካምደን አካባቢ ምናምን ሳነብ ሰዋቹን እየሳልካቸው ነበር ሳነብ የነበረው በጣም ደስ የሚል ነው እና የለንደንንም ንሮ በጥሩ አስተውለከዋል አሪፍ እንግዲ ምን ታረገዋለክ የለንደን ኑሮ ሁሊም እንደ ጨለመ ነው አይደል ቅቅቅ

መጨረሻውን አሳወቀን እባክህ.

ሚላት ከለንደን
ሚላት11
መንገደኛ
መንገደኛ
 
Posts: 1
Joined: Fri May 19, 2006 10:33 pm

Postby ዋናው » Sun Aug 06, 2006 11:08 am

.
.
.
ሠሞናቱን ሁሉ አንተነህና ጓደኞቹ የኢግዚቢሽኑን የመጥሪያ ካርድ በየአበሻ ቤቶች ሲበትኑ ነበር:: ዮሐንስ ለጥበብ ግድ ያሌለውን የለንደ ነዋሪዎች አበሾችን ፊታቸውን ወደዚህ ቢያዞሮ ሊዝናኑና ሊኮሩ እንደሚችሉ በምሳሌ አጣቅሶ ነበር ፍላየሩን /የግብዣውን ወረቀት/ ያዘጋጀው::
አበሻዊ ለንደኖች ብዙ ብዙ እስራቸው ያለውን ተስተውሎት የጎደለውን ነገር ቁብ ሳይሰጡ የኖሩ ናቸው ::አብዛኛው የረገጠውን ምድር ተፈናጦ ነገን የሚያራውጥበትን መንገድ ብቻ ነው የሚያየው መደሰት....መኖር....ለነርሱ ዛሬ ላይ ሆኖ ወደነገ አጮልቆ ማየት ብቻ ነው በእርግጥ አገራዊ ዜማን በመጠጦች ስሜት እያዜሙትም ይሁን እየደነቆሩት ጭፈራ በተባለ የምሽት ስም ይታድማሉ:: ከፊሉ በዓይማኖታዊ ቃል ስም ከሰንበቶች መንፈሳዊ ምስጋናና አምልኮ ውጪ ዘመድ ጥየቃ ካልሆነ የትም አይሄድም:: ለንደን ብዙ ብዙ የሚታይ ቦታዎች አሏት ግን አብዛኛው አበሻ በጣት ከሚቆጠሩ ታሪካዊ ስፍራዎች ውጪ ያዩት ነገር የለም እንግድነት ለመጣም ሰው ምናልባት ለንደን አይ ወይም ብሪቲሽ ሙዚየም ከወሰዱት በዋላ የተለመደውን የአበሻ ቤት ጭፈራ ነው ይዘውት የሚወጡት::

የአንተነህ ኢግዚቢሽን በብራውን ስቶን ጋለሪ እየታየ ነው:: ከሚማርበት የትምሕርት ተቋም በርካታ ሰዎች ተገኝተዋሉ ማስታወቂያው የደረሳቸው ያገሬው ስዕል አፍቃሪያን....በሰው በሰው የአንተነህን ችሎታ የሰሙ....እንዲሁም ጓደኞቹ ስፍራው ተገኝተዋሉ:: የአበሻው ቁጥር ግን በጣም ያነሰ ነበር:: አንተነህ በዚህ ነገር ይበሳጫል ...'ለምንድነው ስዕል የቲያትርን እና የሙዚቃን..ያህል ያገሬን ሰዎች ስሜት ያልሳበችው?' ብሎ::

''አንተነህ ተዋወቃት ቪኪ ትባላለች የቴት ሞደርን ዎርክ ሾፕ ስራ አስኪያጅ ነች::''
አለው የብራውን ስቶን ጋለሪ ባለቤት ኬቨን ረጅም ነው ግራጫ ፀጉር አለው የድምፁ ውፍረቱ ደስ ይላል:: የክራባቱን ቋጠሮ በቀኝ እጁ ጣቶች እየነካካና ትከሻውን ለማኮፈስ ወደውሀላ እየሳበ
''...በስራዎችህ በጣም ተደንቃለች::''
ብሎት ከቪኪ ጋር እንዲያወሩ ትቷቸው ሄደ::

''ጥሩ ችሎታ አለህ ...ይቅርታ ከየት ልበል አንተነህ?''
አለችው ስሙን ተንተባትባ እየጠራችው

''ኢቲዮጲያ''

''ኢ ትዮፒአ....?''
አለች በመገረም ዜማ

''አዎ ምነው ?''
ሳቀችና
''ምንም ...ከዚህ በፊት በጥበብ ዙሪያ የናንተ አገር ሰዎችን ሰምቼ አላውቅም...በጣም ድንቅ ነው::''
አለች የዓይኖቻ ሽፋሽፍት ላይ የተጠቅመችው ማስካራ ሽፋሽፍቷ ሲከደንና ሲከፈት ከውስጥ የሚንቀዠቀዡትን ሰማያዊ ያይኖቿ ብሌኖች የሚቀረጥፉ የመስላሉ

''ኢቲዮጲያ ቀለምና ብርሀን የለም ብለሽ ነው ?''
አላት እሱም በቀልድ እያስመሰለ

''እንደዛ ማለቴ'ንኳን አልነበረም ለአስር ዓመታት የስዕል አስተማሪ ነበርኩኝ የብዙ አገር ሰዎችን አስተምሬያለሁ ግን ካንተ አገር ያጋጠመኝ አልነበረም የገረመኝ አውን ያንተን ባይ ከማናቸውም ተማሪዎቼ የበለጠ ችሎታ አለህ ምናለበት ተማሪዬ ሆኖ ቢሆን ብያለሁም ቅቅቅቅ''

''ላድናቆትሽ አመሰግናለሁ ቪኪ በታሪክ አምናለሁ እኔ ደግሞ ያወቅኩት ታሪክ አገሬ የጥበብ ጀማሪ መሆኗን ነው ምናልባትም ልጠቁምሽ እችላለሁ ስለአክሱም ሲቪላይዜሽን ...''

አላት አንተነህ ዛሬ ትንንሽ ጠቃጠቆ ያለበት ሰፊ ነጭ ሸሚዝ አድርጎዋል ፀጉሩን ቆጣጥሮታል ከወትሮው ትንሽ ዘነጥ ብሎዋል:: ቪኪን በይቅርታ ትቷት ወደ ደሰባዊት ሄደ::
ማታ ዘካሪያስ ወደቫኔሳጋር ከመሄዱ በፊት ተፈራግጦ ተሯርጦ ኦክስፎርድ ሰርከስ ሄዶ ለሠባዊት ልብስ ገዝቶላት ነበር:: ያረፈችበት ቤት ሄዶ በድቅድቅ ጨለማ ስጦታውን ሲሰጣት ምክኒያቱን ጠይቃው ነበር
''ማፍቀሩን እንደሆነ ነግሬሻለሁ ልቤም እንደወደደሽ ስሜቴም እንደሰገደልሽ ሁለቱንም ያንቺ ልብ ጠይቋቸው ነግረውታል ....ግን የነገው የፒካሶ ኢግዚቢሽን ላይ ይሕእንን ቀሚስ አድርገሽ እንድትመጪ ፈልጌ ነው''
ነበር ያላት

አንተነህ ሠባዊትን ሲያያት ተደነቀ በስዕል ያስቀመጣት ሠባዊት ነፍስ የዘራች እስኪመስለው ድረስ ሁሉ ፈዞ ነበር የተመለከታት::

''ዘ-አርት ኦፍ ሴክ ወይስ ዘ-ሴክ ኦፍ አርት.....ዋው እንኳን ደህና መጣሽ ::''
ጨበጣት:: ተፈለቅልቃ ጉንጩን ሳመችውና ማድነቋን የጋለሪውን ዙሪያ ገባ ቃኝታ ነገረችው::

''አመሰግናለሁ...ያጋጣሚ ነገር ነው ወይስ...ይሄንን ቀሚስ እንድትለብሺ ዘኪ ነግሮሽ ነበር?''

''ምነው ወደድከው...ዘኪ ነው ማታ ያበረከተልኝ::''

''ያንን ስዕል አይተሽዋል ሠባዊት?''

''የቱን ገና መምጣቴ ኮ ነው''
አለችው ወደጀርባዋ ያላትን ስዕል ለማየት ስትዞር ዘካሪያስ ከቫኔሳ ጋር እጅ ለእጅ ተቆላልፈው ገቡ::
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው_________________________________::

wannaw@cyberEthiopia.com
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Sun Aug 06, 2006 11:41 pm

.
.
.
ሠባዊት ዘካሪያስን ስታይ ውስጧ ያለው ፍቅር ውርር ቢያደርጋትም ከቫኔሳጋር ስታየው ግን ደስተኛ አልወነችም:: ቫኔሳ ተፍለቅልቃ አንተነህን ስማው ከውኃላዋ የተከተሏትን የምትሰራበት የስራ ባልደረባዎቿን ለማስተዋወቅ ተጣደፈች: ይሄን ጊዜ ዘካሪያስ ወደ ሤባዊት ተጠጋ::

''...ሠቢ ዛሬ በጣም አምሮብሻል''
ብሏት አንተነህ ጠቁሟት ውደነበረው ስዕል ይዟት ሄደ

''አመሰግናለሁ ዘኪ ''
መልሷ አጭር ነበር: ተከፍታለች ልክ እንደተሳለው ስዕል አንተነህ በቡሩሹ ዳግም በገፅ የፈጠራትን የራሷን ምስል ስታይ ደነገጠች ችሎታውንም አደነቀችው ደጋግማ እያየች

''በጣም ያምራል ዘኪ አንገቴ ላይ ያጠለቁትን ግን አብሎች አላውቃቸውም ቀሚሱስ ይሄ ነው ....''

''አንገትሽ ላይ ያለው አብል ምክኒያቶች አሉት ሁሉንም ከአርቲስቱ ብትርጂው ይሻላል....የኔ ቆንጆ''
ቀና ብላ አየችውና መልሳ ዓይኖቿን ሰበረች ወደመሬቱ ጥቂት አይታ ድጋሚ ቀና ስትል የጋለሪው ባለቤት ኬቨን በመገረም እሷንንና ሥዕሉን እያየ መጣ

''ከካንቫሱ የወጣሽ ሁሉ ነበር የመሰልሽኝ ....በጣም ቆንጆ ነሽ::''
አላት እየጨበጣት ጠንቃቃነቱና ለታዳሚው የሚሰጠው ፈገግታ ደስ ይላል:: ወዲያው በርካታ ታዳሚያን የሠባዊት እና የስዕሉ መመሳሰል እየገረማቸው እሷን መመልከት ጀመሩ ይሄን ጊዜ ሠባዊት አፈረች ፈገግታዋ ፊቷ ላይ ቢታይም በአፍረት ፍማለች :
ቫኔሳ ወደዘካሪያስ ስትቃኝ ሠባዊትን አስተዋለቻት
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው_______________________________::
wannaw@cyberEthiopia.com
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Mon Aug 07, 2006 11:59 pm

.
.
.
''ቫኒ...ሠባዊት ...ሠባዊት ቫኒ..''
አለና ዘካሪያስ በየተራ ወደ ሁለቱም እየዞረ አስተዋወቃቸው ለመልካም ትውውቅነታቸው በፈገግታ ተያዩ

''ቆንጆ ነሽ አንተነህ ጥሩ ሞዴል አግኝቷል በዚህ አጋጣሚ አንቺም እድለኛ ነሽ በአርቲስት አንተነህ መሳልሽ::''

''አመሰግናለሁ::''
ሁለቱ ሲያወሩ ዘካሪይስ በመሳቀቅ ነበር የሚያቸው::
የኢግዚቢሽኑ ታዳሚዎች ተበራክተው ጋለሪው ሞላ አንተነህ ያቀረባቸው ስዕሎች አብዛኞቹ ዘመናዊ ቅብ የሚባሉት ዓይነት ናቸው የካንቫሶቹ ግዝፈት ትንሽ የጎሉ ነበር በእስኴር ካንቫስ ላይ ቀለማትንና የምስሎችን ቅርጽ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ ማስቀመጥ ብዙ ሠዐሊያንን የሚፈትን ነው:: አንተነህ እነዚህ ነገሮች አስታርቆ ከማስቀመጡም በላይ ማንኛውም ግንዛቤው ላለው ተመልካች በምስልነቱ ብቻ ዓይንን ያንከራትታል :: ዛሬ ወዳጆቹ ሁሉ አብረውት ነበሩ ስለሺ ፂሙን እየፈተለ ባልጠገበ ስሜት ደጋግሞ ያያል ዮሐንስ /ጆኒ ዘ-ገዳም የቀሉ ዓይኖቹን እያሻሸ ማድነቂያ ቃላት እንዳጣ በሚያስታውቅ ዕይታ ለአንተነህ ፈገግታ ይሰጠውና ራሱን በመገረም ይነቀንቃል: ሌሎች ጥቂት አበሾችም አብዛኛው ስዕሎች ባይገባቸውም ቢያንስ የሠባዊትን ምስል አይተው እያደነቁ ነው::

አጭር ፀጉር ያላት መልከ ቀና አበሻ ወደአንደኛው ካንቫስ ለረጅም ደቂቆች ያህል አንጋጣ ስታይ አንተነህ አያት ከዴቪድ ጌ'ው ጋር እያወራ ነበር ልጅቱ ጥያቄ ሊኖራት በሚችል ስሜት ወደርሷ አመራ

''ይቅርታ አንተነህ?''
አለችው እሱነቱን ለማረጋገጥ ወደጋለሪው ከገባች ማንንም አላገኘችም ከበሩ ላይ ብቻ የስዕሉን ካታሎግ አንስታ ቁጥሮችንና ካንቫሶችን አመሳክራ ርዕሳቸውን ታይ ነበር::

''አዎ ነኝ ''
ጨበጣት::

''ጥያቄ መጠየቅ ይቻላል ?''

''በሚገባ ''

''በመጀመሪያ በጣም የሚደነቅ ችሎት እንዳለህ ልነግርህ እወዳለሁ......አብዛኞቹን አብስትራክቶች በእራሴ መንገድ አንደርስታንድ አድርጌያቸዋ ለሁ:: ይሄኛው ስራህ በጣም የወደድኩት ነው...''
ቀጠለች ልጅቷ: የቀለመ አጭር ፀጉሯ ፊቷን አጉሉቶታል ሳትስቅ ገና ጉንጯ ሊሰረጉድ ይፈልጋል::

''.....እና ይሄኛው ፔንቲንግ ፊቷን ያዞረች ሴት ትታየኛለች ከፊት ለፊቷ ያለው ግድግዳ ላይ የተሰቀለው ሙሉ ሰማያዊ ቀለም ያለው የካንቫስ ምስል ምንን ሪፕረዘንት ያደርጋል ...ፕሊስ ታብራራልኛለህ አንተነህ?''

ጥያቄዋ ገረመው

''በመጀመሪያ ማን ልበል ስምሽን የእኔ እመቤት?''

''ኤልሳቤት::''
.
.
.
ይቀጥላል

ዋናው____________________________________::[/list]
Last edited by ዋናው on Wed Aug 09, 2006 11:11 pm, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Wed Aug 09, 2006 9:23 pm

.
.
.
ሁለቱ ሲያወሩ ዘካሪያስ መጣ

''ትመጪያለሽ ብዬ አላሰብኩም ኤልሳቤት''

''ጥበብ እንደምወድ ስነግርህ አላመንከኝም ማለት ነው?''
አለችው ስማው ስትጨርስ:

''እኔንንጃ አላመንኩሽ ይሆን ብቻ....ለማንኛው ተዋውቀሽዋል አይደል አነተነህ ማለት እሱ ነው... ፒካሶ ብለን ነው የምንጠራው ......ፒካሶ በደንብ አስተናግዳት የሰፈሬ ልጅ ናት::''
አላቸው ፈገግታው ከፊቱ ቢታየም የምደንገጥ ስሜት እንዳለው ያስታውቃል:: በዓይኑ ወደ ሠባዊት ሲያማትር ዘካሪያስ አንድ ጥግ ሆና ተክዛ ቆማ አገኛት

''ሠቢ እንዴት ነው ኤግዚብሽኑ?''

''በጣም ቆንጆ ነው ፎቶግራፈሩ ካነሳቸው ፎቶዎች የተወሰኑትን እፈልጋቸዋለሁ ባለፈው ለአንተነህ ካደረግኩት የቃለመጠይቅ ዘገባ ጋር አዲሳባ ጋዜጣ ላይ እንዲታተም የምሰጠው ነው::''
አለችው ወደ መሬት እንዳቀረቀረች

''ምንም ችግር የለውም ሠቢ''
ጥቂት ዝምታ መሀላቸው ሰፍኖ ሠባዊት
''ዘኪ....?''
አለችው:: ዘካሪያስ ያጠራሯ ዜማ ቢያስደነግጠውም በመንሰፍሰፍ በዓይኑ የጋለሪውን ዙሪያ ገባ ቃኝቶ

''ወዬ...?''
አላት

''ምናልባት የእኔ እዚ መገኘት አላስፈላጊ ከሆነ ይቅርታ''

''ለምን እንደዛ አልሽኝ ሠቢ?''
አላት: ዓይኖቹን በፍርሃት እያርገበገበ

''እኔንጃ ...ባንተና በቫኔሳ መሀል መግባት አልፈልግም ::''

''ሠቢ ሲጋራ ማጨስ ፈልጌያለሁ ውጭ እንውጣ?''

''አስፈላጊ ነው?''

''ፕሊስ?''
ተከታትለው ሲወጡ ቫኔሳ ከእሩቅ ተመልክታቸው በደመቀ ስሜት ከሚያዋሯት ሰዎች መሀል ብይቅርታ ተለይታ ተከተለቻቸው
.
.
.
ይቀጥላ[/list]....

ዋናው__________________________________::
Last edited by ዋናው on Sun Aug 13, 2006 1:33 am, edited 1 time in total.
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ወንዳታ » Thu Aug 10, 2006 12:48 pm

ሰላም ዋናው እጅግ መረቅ ያለው ጨዋታ ነው... ጉድ ፈላ ዘንድሮ.... በናትህ ሰባዊትን አታበሳጫት ወንድ የምትቅማ ሰት ደስ ትለኝአለች በሶስቱ ሰዎች መሀከል የሚፈጥእረውን ጭቅጭቅ ማየት ናፍቆኝኣል....... WELL DONE BROV
LOVE AND RESPECT FOR ALL
EVEN IF THEY ARE LOSERS LIKE VANI
ወንዳታ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 46
Joined: Mon Jan 31, 2005 3:23 pm
Location: united kingdom

PreviousNext

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: Google [Bot], Majestic-12 [Bot] and 2 guests