እኔና እኛ ......

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

እኔና እኛ ......

Postby ሾተል » Wed Jun 21, 2006 2:33 pm

ህይወትን ተወለድኩዋት ጡትዋንና ጡጦዋና ጠብቼ ጭቃ አያቦካሁ በጉልበቴ እየዳሁ አብረያት አደኩ በደንብ አወቅኩዋት::ተለማመድኩዋት....የመኖር እቅዴን ስለወደፊቱ እኔነቴ ማሰቤን በታዳጊነት እድሜዬ ሳልጨነቅ ኩዋሱን,እቃቃውን, ቁማሩን, መቀማቱን,ማጨሱን,መቃሙን,ምናምኑን ሳደርግ እድግ አልኩና እራሴን መቻያ ጊዜዬ በእጄ የግድ ሲሰጠኝ ምን ይዋጠኝ::ተመክሮ አይኖረኝ ዘንድ ትበታዬ(መተበቴ)ወላጅ የሚለኝን አለመስማቴ ታላላቆቼ የሚሉኝን አለመቀበሌና ዘላለም በሰው ትከሻ ህይወትን አጣጥማታለሁ በሚል የጅል ብሂል መገንባቴ ይሄው ዛሬ ህይወት የምሬት እሬት ታግተኝ ገባ::እኔነቴ ከኔ ድሮም አልነበረምና በህሊና የአይኔ ብረት አይቸውም አላውቅ::የዛሬ እኔነቴ ኑሮ የኑሮ አቁፋዳ ስልቻውን አሸክሞኝ ዳገት አይሉት ተራራ ቁልቁለት አይሉት ዳገት ትንታግ ትንታግ እያስተነፈሰ በጉልበቴ እንድድህና ትንፋሼ እኔን እየተነፈሰኝ ጉልበቴ በክህደት ልስላሴ እንድባዝንና እንድንከራተት ይህእው ፈረደብኝ::

የኑሮ እዳሪ መውጣት አስፈለገኝና ጉልበቴን ልሞክር ጉራንጉር ስርቻ ስፈልግ ሰኮንዱ ወደደቂቃ ,ደቂቃው ወደ ሰአት,ሰአቱ ወደ ቀን,ቀኑ ወደ ወር,ወሩ ወደአመት,አመቱ ወደአመቶች እየተቀየረ ምንም ሳይሰማኝ የነበረኝን እንቡጥ የልጅነትና የታዳጊነት አልፎም የወጣትነት ፊቴን እያጨራመተ ከመልክ ጎዳና አውጥቶ ጊዜየን እሩህ በማጣት ሳልፈታተነውና ሳልሰራበት እየሰራብኝ ቀኑ እንደጉም እየበነነ አልጨበጥ ብሎ አንከላወሰኝ::

ስለት በስሜ ያለእምነቴ ለፈጠረኝ ይሁን ለሰራኝ ገባሁና ብሞክር ይደርሰኝ ዘንድ ሳለ ሳልሞክር ስለቴ ባይደርሰኝ የምከፍለውን ባዶነት ይጀ ሳላገኝ አጥቼ ሀትያት ላይ ህጥእና አክዬበት ሸክሜ ላይ ክብደት ዶየበት በራሴ ተሳስቼ ከሙክራቤ በባዶነቴ ተንበርክኬ ጸሎቴን ጮኬ ደግሜ ያለንጹህነቴ ሳላፍር ኑሮ ትሸውደኝ ዘንድ ይህእው የአለም የህይወት ዋንቻ ውድድር መዳ ስቴድየም ውስጥ ያለተቃራኒ ተቻዋች ብቻየን የኑሮ ሀላፊነት ኩዋሰን እመትራለሁ...አልሜ ያለአቅጣጫ ኩዋሴን አጥዛለሁ....ያለደጋፊ ለብቻየ አጨበጭባለሁ::

ጉም ነኝና እንደጉም መብነኔ አይቀርም...አፈር ነኝና እንደአፈር ከምስጥ ጋር እየተበላላሁ አፈር ሳልሆን አልቀርም...ቀኑ ይርዘም እንጂ...ማጠሩንስ መች አይምሮየ ተቀበለው....

ተስፋየን ከራሴ አለማብነኔ ይገርመኛል....ማነኝና ነው ዘላለም በዚች ምድር ላይ ተኮፍሼ የምኖረው....እረ ማነኝ ያለኝን እንደአጋሰስ ላመነጅግ ተንሰፍስፌ ያግበሰበስኩትን ሀብትና ባዶ ንብረት የጌጥና የማሳ ጎተራ ክምር ይጄ ወደአላየሁት ነገር ግን ወደምሄድበት ሌላኛው አለም ተሸክሜ የምህእደው::.ማካፈልን አብሮ ከትንሹና ትልቁ ከሌለውና ካለው ጋር እኩል ያለንቀት ተሰይሜ የምካፈለው??መጥኔ ለኔ......

እኔ እኮ ጎርፍ አመጣሽ ነኝ...ጎርፍም እንዳመጣኝ ደግሞ ለራሱ ሲል ይወስደኛል.....ታድያ መች የራሴን መኖርያ ቦታ አወቅኩና ነው የድንጋይ ክምር መጠለያ ሰርቼ አረፍ ብዬ የምኖረው::
Last edited by ሾተል on Wed Mar 03, 2010 9:53 pm, edited 5 times in total.
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Wed Jun 21, 2006 2:52 pm

ማኩረፉ,ማላዘኑ, የአይምሮየና የእኔነቴ ላንቃ እስኪሰነጠቅ ማፋሸጌ መች እራሴን ከተደበቀበት እረድቶ አገናኘኝ???ሌላውን በመሆን እራሴን በመርሳት ጠፍቸያለሁ::በጨረቃ በላምባዲና ሳር ውስጥ እንደወደቀ መርፌ ቢፈልጉኝ እንኩዋን መች እገኝና!ትላንት አመጣጤን ሳላውቀው ጊዜው ተሽመደመደብኝ::ዛሬን ደግሞ አላውቀው ዘንድ የጉዞ አቅጣጫዬ ተሰወረብኝ....ታድያ ነገን ወዴት እንደማመራ አውቀው???ወይኔ እኔ ምስኪን.....

በባዶነት መኮፈሱንማ አውቅበታለሁ::ውስጤ ባዶ ቅል መሆኑ ግን ተሰውሮብኝ በባዶነት አጊጬ ሊሰጠኝ የማይገባኝን ክብር ስቸር በፈገግታና ንቀት አሜን ብዬ እቀበላለሁ::እኔነቴን ሊያፋልጉኝ የራስ መሆን እውቀተ-ከረጢት የሆኑትን ሳይ ክብደታቸውን አሳምሬ ባውከውም እየናቅኩዋቸው ላለመማር ,ላለመገኘት ተስፈንጥሬ እሸሻቸዋለሁ....እነሱ ወድያው ባዶ መሆኔን ያውቁብኛላ....ሳስበው ባዶ መሆኔ ከታወቀብኝ ያ ሲቸረኝ የነበረው ሁሉ አክብሮት እንደ እንቡዋይ ካብ አንዴ ይደረመስና ውሀ እንዳረሰረሳት አይጥ ከስቼ መንምኘ ምጽዋት ፈላጊ ተመጽዋች እሆናለሁ....ኦኦ...መቸም መጋፈጥን ንክችም አላደርጋት
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Wed Jun 21, 2006 3:10 pm

የሚገርመኝ የህይወቴ ጸሀይ አላቃጥልም አለችኝ...አይበርደኝ ዘንድ ከላይ ምናምን ብደርብ ደግሞ በርዶኝ ስላልነበረ ሙቀቱ በላብ አደባየኝ::ከላየላይ የሰየምኩትን ባእድ ነገር ሳወልቅ ደግሞ የብርዱ ጥዝጣዜ የትንኞቹ ምጥማጤ ህሊናየን አሳተው.....ደሜ ተመጦ ተመጦ እኔነቴ በውሀ ብቻ ቢቀርም በአፍ እንደተነፋ ኡፉፋ ተነፍቼ ማስጠላቴ....

እራሴን አላጸዳ ዘንድ ጽዳት ለምኔ ነኝ....ውጭና ውስጤ ተግማምቶዋል....ክርፋት እከረፋለሁ....ቅርናት እቀረናለሁ...ያ ሁሉ ሽታ ኮ መጥፎ በሌላው ላይ መስራቴ,ህሊናየ መስራቱን አቁሞ መበስበሱ ነው::በለላው ችግር መደሰቴ,በሌላው ስቃይ ማላገጤ,በሀይል ረግጨ መግዛቴ,ለከርሴ ማደሬ,ለቀፈቴ መጨነቄ ነው...ለዚህ ነው ከርፍቼ የሌላውን ማሽተቻ ሴል አፍንጫ ያበላሸሁት::ሁሌም ያለኝ ሀይልና ጉልበት ከኔነቴ የማይከዳኝ ይመስለኛል መሰል መሰሎቼን ከአለሜ ስከላቸውና ደማቸውን ስጠጣና ስጋቸውን ስበላ አርካታየ አንዳች ነው::ቀኔ ደርሶ ከኔ የበላይ መጥቶ በስራዬ በግማቴ መብዛት አንጻር ትንሽ መቆያ ጎሬ ሲያዘጋጅልኝ ወይም ትንፋሸን እንደፈጠረኝ ሀላፊነቱን ተከናንቦ ትንፋሼን ሲያሳጥራት,ደሜን ሲጠጣት,ስጋየን ሲበላት....አቤት የህይወት ሽክርክሮሽ...አበት የመግማማት የቆሻሻነት ህይወት....
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Wed Jun 21, 2006 3:23 pm

ህይወቴ ልብ-ወለድ እንጂ ገሀድ አልሆን ብላኛለች::ስለራሴ ጠቅልዬ አለማወቄ እኮ ነው ከገሀድነት አመናጭቆ ያባረራት::የህይወት ብራማ ጨረቃዬ ስትበራ ልዘፍንላት ተንደርድሬ ስወጣ አቅጣጫዋን ስታ በተኮፈሰ አንዳች ተራራ ትሸሸግብኝና ስሙዋን ጤርቼ ዱምቡለቃ ልል ስል እፍር እልና ወደ ስግብግቡ እኔነቴ እከተታለሁ::የመአልት ምርኩዝ ይዤ እያነከስኩ በላምባዲና ኑሮየን ልኖር ስዳዳ ይችም ሰው ሰው ተሆነችና አይናቸው ደም የለበሰ እንደኔ ያሉ ምቀኞች የምንገዴን የምንገድ አፈር
እየሰረሰሩ ብዙ ጉድጉዋድ ሲሰሩበት ,ዘልየው አልሄድ ዘንድ ኩይሳ የሰራው እስኪመስል አፈሩን ከምረው አግደው ሲመልሱኝ ታድያ እንዴት ብዬ ከኑሮየ ጋር ልስማማ..
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Wed Jun 21, 2006 3:38 pm

የልጅነቴ,የታዳጊነቴና የወጣትነቴ ጀግና ሀብቴ ጸጋየ ስራውን ጠግቤ ሳልመገብ,እድንቄው ሳልጨርስ,አመስግኜው ሳልረካ ብእሩን አንጥፎ ከልቶ ክንዱን ሲንተራስ ሀዘኑ ጎድቶኝ ናፍቆቱ ህሊናየን አስቶኝ ምናለ ለኔ በሆነ እያልኩ እልከፈከፋለሁ::"ተስፋ ባጣ ምድረበዳ
የአንድ እውነት ይሆናል እዳ ነበር ያለው...?!

መች ለራሱ ኑሮ አወቀና ነው በቃኝ ኖረያለሁ ብሎ ጀግናው ከድቶኝ,ናፍቆቱን አሸክሞኝ የተለየኝ::አረመን አረመልኝ...ህመሜን አከመልኝ...ኑሮየን ኖረልኝ....እሱኮ ጸጋየ ነው...ጸጋየም ነበረ...ጸጋየ እንደሆነም በልቤ ውስጥ ውለታውንና ስራውን ተክሎ ይኖራል::ለሱ የሚሆን ቦታ ለሀውልቱ ማቆምያ ክልል በሰፊው በልቤ ውስጥ አለ ይኖራልም::በህልሜም አናግሬው አውቃለሁ እኮ....መክሮኝም ነበር...ድፍረቴ በሱሪዬ እንደሽንት ሆኖ ፈሶ አዋርዶኝ ሄደ እንጂ.......ጸጋዬ ግን እኔ እስከምኖር ድረስ ይኖራል...እናቱ ነኛ...የበቀለብኝ ስለእኔ ተቆርቁዋሪ ስለእኔ ተራኪ...ስለእኔ ታማሚ ነበርና....ስለእኔ አንብቶልኛል...የነን ልጆች አብቅሎልኛል...እኔን ተወነኝ....እኔን ሆኖ ተጋፈጠልኝ....ግን ህይወት ጉም ነበረችና በሱ በነነች.....ክንዱን ተንተራሰ::
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby sleepless girl » Wed Jun 21, 2006 11:40 pm

ሾተል ህምምምምምምምም ይጠጥራል የጻፍከው :roll: :roll: ...ከምር....እኔ ነኝ ወይስ......አማርኛህ??? ደግሜ..ደጋግሜ አነበብኩት...ግን.......ያው አልገባኝም::
እስኪ ቀለል አድርገህ ጻፈው: :wink:
Nothing is impossible!!
sleepless girl
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1510
Joined: Sun Feb 19, 2006 3:56 am
Location: near u!

Postby ዩፎ » Thu Jun 22, 2006 4:17 am

"አንዳንድ ነገሮችን የበለጠ ቀለል ማድረግ አይቻልም" - አልበርት አንስታይን

sleepless girl wrote:ሾተል ህምምምምምምምም
እስኪ ቀለል አድርገህ ጻፈው: :wink:
ዩፎ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 132
Joined: Sat Dec 25, 2004 10:29 pm
Location: united states

Postby ሾተል » Thu Jun 22, 2006 6:31 pm

ስሊፕለስ ገርል,
መኖር እኮ ይጠጥራል...ቀሎም አያውቅ::መስገብገቤን ሳላውቅ አግበሰበስኩና ሁሉም ነገር ቢኖረኝ አልረካ አልኩና ሌላ ልደርብበት ሳሰላ ሳወጣና ሳወርድ በላዩ ላይ ጨምሬ ተራራ ላስመስለው ሳስብ .እንደከበድኩ እንድቆይ ሳሰላ..አንዴ ቀማኛ መጥቶ አግበስብሶ ይሰወርብኛል ስል...አንዴ ለግብስባሶየ ብለው እኔን ቢከሉን ስል...አንዴ በዪ ሙጥጥ አድርጎ አጭበርብሮና አታሎ ይወስድብኛል እያልኩ ስጋየን ከነፍሰ ጋር ለማላቀቅ ስውተረተር... ቀፈቴን እንደታቀፍኩ አንዳች በሚያክለው አልጋየ ላይ የውፍረት ኪሎየን አልጋየ ሸክፎ ይዞልኝ በሀሳብ ስነጥር ይሄው እንቅልፍ ና ተወሰደኝ ብለው አሻፈረኝ ብሎ አይኔ ግልጥጥ ብሎ አደረ::ታድያ እንዴት የሀጥያት ቀፈቴን እንዴት ላቅለው::
እንዴው የማከብረው የአገሬ ጸሀፊ ሲሳይ ንጉሱ በመጽሀፉ የወለደውን ገጠ በሀሪ ይሄ መጥፎ ነገር የሚሰማው ጆሮውን ቆርጦ,አስጸያፊ ነገሮችን የሚያየው አይኑን ጠንቁሎ እንዲያጠፋው,ይሄ የሚሰርቀውና መጥፎ ነገር የሚሰራው እጁን ደሽድሾ እንዲጥለው,ይሄ የከረፋ ነገር የሚያሸተው አፍንጫውን መድምዶ እንዲያርፍ,ያ ያልተፈቀደለት ቦታ ጡል ጡል የሚለው እግሩን ሰይፎ እንዲጥለው,ያ የሚያመነዝረው ሴሰኛ ብልቱን ከናካተው ቖርጦት እንዲያርፍ በገጠ ባህሪው አፍ አናገረው....ለምን እንደዚህ እንዳለ ተፈላስሜ ስደርስበት ምክንያቱ ገባኝና እስቲ እኔ ልሞክረው ብዬ ማመንዘሬን ወድያ ወግድልኝ ብሽቅ ብዬ ብልቴ እንዳያመነዝር ተብልት ባርቀው ለስሜቴ የተገዛው ነበርኩ ለካ ስሜቴ አይምሮየን አልፎ በአፍንጫየ ሊወጣ.....እንደ ሚፈስ ፉዋፉዋቴ ተናግሮ,አምቶ,ተሳድቦ የማይጠግበው ምላሴን አደብ ላስገዛው ብሞክር ምላሴ የክቱን,የሱሱና የአውልያውን ሳያገኝ ቀረና ከአፌ ካልወጣሁ ብሎ እነዛ በአዋቂ ተስተካክለው የተደረደሩትን ጥርሶቼን ከቦታቸው,ከገደባቸው አነቃንቆ ገፍቶ ይሄው ገጣጣ አድርጎኝ አረፈው::
ታድያ እንዴት ብዬ እራሴን ላቅለው...ምንስ ጉልበት ኖሮኝ የጠጠረው ህይወቴን ላለስልሰው::[/url][/list][/list][/code][/quote][/u][/i][/b]
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Thu Jun 22, 2006 6:43 pm

ድሮ ድሮ ነው...ከናቴ ማህጸን ተሸፍኖ አድሮ ጸሀይ ሲያይና ሲነጋ እንደሚፈካና ሚከፈት አበባ ከናቴ ማህጸን ክፍትፍቱን አውጥቼ ወጣሁና የኪራይ አለሙን ባየው የሚቀዘቅዝና ንዳዱ የሚያሰክር ሆኖ በዛ ቅጽፈት አየሁትና ወይነ የዱሮው ዋሻ ይሻለኝ ነበር ብYእ ምርር ብዬ አለቀስኩ...አበጥ አሁን አሁን ሳስበው እናቴና አዋላጆቹ እንዴት እንዳባበሉኝና ይሄንን አዲሱን አለም በመፍራቴ ምን ያህል በፍርሀት እንደታዘቡኝ አሁን ብቻየን ሆኘ ሳስታውሰው ያሳፍረኛል::ለካስ እንሽጥ ነኝ::አሁን ምን አስፈራኝ???በርግጥ በሁዋላ በሁዋላ መሰሎቸን ሳይ ተጽናናሁ እንጂ ብቻየን ተፈጥሬ ቢሆንማ ታግዬ በዛ ጮርቃ የደም ጉልበቴ ከናቴ ጋር ተደባድቤም ቢሆን በማህጽኑዋ ውስጥ ገብቼ ተሸንቁሬ እቀር ነበር::ግን የሚሉኝን የምሰማ የተባረኩ ልጅ ነበርኩ::ቁንጠጣ የሚገባኝ,ምክር የሚያሳድገኝ,የበርበሬ መታጠን የሚያስተካክለኝ ልጅ ሆኘ አደግኩና አጥና ሲሉኝ ሳጠና,ሲያስተምሩኝ ሀሳቤን አካትቼ ስለምከታተል ያስተማሩኝ የሚገባኝ ሆንኩና ለላው እስኪቀናብኝ ድረስ ጎበዝና በአንደኛ ላይ አንደኛ ሆኜ ይሄው ኮሌጅ በጥሼ እራሴን ከራሴ አልፌ ለሰው ተረፍኩ....አቤት የዋህነቴ...ሲቸገሩ ደራሽ...ሲታመሙ አስታማሚ...ጥሩ ፈራጅ....ሁሉንም በአንድ የማይ ብሌነ ብሩክ ሆኘ ይህእው ሳልሞት አለሁ.::
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Fri Jun 23, 2006 12:45 pm

እንደገና ደግሞ ድሮ ነው....ብጣሽ ሙጭቅላ ንፍጡን የሚበላ ዝርክርክ ህጻን እያለሁ...የወረሩኝን ዝንቦች እንኩዋን እሽ ለማለት ጉልበቱ ለምኔ ባልኩበት በዛ የጨቅላ ሰሞን.....እዚህም ይፎከርልኛል...እዚያም ይነበነብልኛል እንዲህ እየተባለ::"ምርጥ ምርጡን ለሙጭቅላ ህጻናት"ከዛ እኔም በዛች የዋህዋ ጭብጦ ልቤ ምርጥ ምርጡ ሊሰጠኝ ነው ብዬ በደስታና በተስፋ ጮቤ ስረግጥ የጠበኩት ተስፋ ከቀን ጅቦች አልፎ ገደቡን ጥሶ መጥቶ እንዴት ይድረሰኝ::እኔም ተስፋ ሳልቆርጥ ሆዴን መማጉዋጉዋት አሰይቸው መስክ ላይ ውላ ልጁዋ እንደናፈቃት እናት ላም ሳስጮሄው....ላንቃዬን እሳተ ጎመራ እንዳጎረጎደው ከርሰ መቃብር ሳዛጋው...ተስፋዬን አይቸው የማላውቀውን ብሩህ ብርሀን ሳበራው.....ምርጡን ተዉና ገና በጨቅላነቴ እየተንሰፈሰፉ በጉልበታቸውና በተገረሰሰው ሀይላቸው ይመርጡኝና ይመለምሉኝ ገባ....እኔም እባካጩ ገና ሙጭቅላ ነኝ ጭጋር አጥንቴን አስረዝሞት ተስፋ ሆደንና ቂጠን አሳብጦት እንጂ ገና ኢምንት ነኝ ብላቸው ከየት ሰምተውኝ...ከዛ በማላውቅበት ሀሩር የምድር ሲኦል ዶሉኝና ያላቅሜ አንዳች ክብደትና እርዝመት ያለውን ነገር ሲያጫምቱኝና ልኬ ያልተገኘለትን ነገር ሲያላብሱኝ ከዳር ሆኖ ላየኝ በመጫምያና መላበሻ ውስጥ የሚዋኝ አጽመ ምስሎ ነበር የምመስለው....እኔም በዚሁ ያልፍልኛል ብዬ የያዝኩትን የሲኦል ትንፋሼን ገና እያላመድኩት ሳለ ይሄ አይበቃህም ብለው ከቁመቴ ጋር የማይተናነስ ክብደቱ ግን አንዳች የሆነ ብረት አስታቀፉኝና በል እራስህን አድን አሉኝ::እርሳስ በላዬ ላይ ይዘንባል....እንደፍልፈል ቆፍሬ የገባሁት በሸሸጊያ ጎሬዬ ላይ እርሳሱ እየጮሄ ዱብ ዱብ እያለ ነፍሴን ከስጋየ ሊያላቅቅ ይመሳጠራል....ከዛ ተስፋ ሳልቆርጥ ትንፋሸን ላቆያት እየተጣጣርኩ ዘወር ስል መሰሎሸ ክንዳቸውን ሳይንተራሱ ተቆራርጠው ተከታትፈው,ተተልትለው ትንፋሻቸውን ልከዋት አየሁ.....ያነ ነው ተስፋየ በእኔ ላይ ተሽመድምዶ የጠፋው...ያኔ ነው የናቴ ማህጽን ምን ያህል ከልሎና ሸክፎ ጠብቆኝ እንደነበረ የተረዳሁ...ያኔ ነው መኖሬ ትርጉምዋን አጥታ በወንድነት እኔን ማሰየሙዋን ያወቅኩት::ያኔ ነው ውሥጤ ቢሸናም ውጬ እራሴን ጠብቆ የማዳኑ ሀላፊነት እንዳለኝ የተረዳሁት....ያኔ ነው በስንት ማሳመን እራሴን በብረቴ በጣጥሼ ከዚች ጭካኔ አለም ልከላ የነበረውን እቅዴን ትቼ ቃል የተገባልኝንና የተፎከረልኝን ምርጥ ምርጡን ለኔ የተባለውን ነገር ለማየት የግዋጉዋሁ...የዛኔ ነው ከተሸሸግኩበት ጎሬ ማንም ሳያየኝ ተሽሎክሉኬ በእሳት ውስጥ እንደወርቅ ተቃጥዬ ተፈትኜ ከተመደበልኝ ቦታዬ ጠፍቼ የመኖር ውዳሴየን ለራሴ ደግሜ ደጋግሜ እራሴን አመስግኘ የሰላም አየር ተነፈስኩ ስል ተይዤ እራሴን መክዳቴ ወንጀል መሆኑ በወንጀለኞችና ሀያል ሀይለኞች ተረጋግጦብኝ ወደ እርዴ ወስደው አንዴ በነገራቸው ቢቀሉኝ አንገቴ ከኔ ተላቀቀና በደስታ እያሽካካ እንደኩዋስ እየተንቡዋለለ ደሜን ማቆያየን ከምድር ጋር አላልሶት በድክመቱ ጉዞወንና ማፋሸጉን ቢገድብ እኔም ወደዘላለማዊው ቤቴ እንደንፋስ አካላቴን ለክርፋትና ግማት,ለምስጥ እራት አደራ ሰጥቼ በማይታየው ንፋስ አምሳያ በቀለለው ቀሪው እኔነቴ በመላክ እርዳታነት እየተመራሁ በነንኩ::ጠፋሁ::ተለየሁ::ዳግም ላልከሰት ተደበቅሁ::በርግጥ አሁንም አለሁ::መች ያ ብቻ አበቃልኝና::
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

አማርኛህ ሀይለኛ ነው

Postby ሳምኪት » Sat Jun 24, 2006 11:48 am

ግን የምትፅፈው ከጭንቅላትህ ነው ወይስ ከመፃሀፍ ላይ ነው እሄ ይብራራለኝ በተረፈ አሪፍ ድርሰት መፃፍ የምትችል ነው የሚመስለኝ ወይንም ልብ ወለድ በርታ.............
What Is Your Idea About Ethiopia?
ሳምኪት
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 12
Joined: Tue Jan 18, 2005 6:44 pm
Location: united states

Postby ሾተል » Sat Jun 24, 2006 11:56 am

ሳምኪት,

እራሴን ልሁን አልኩና እራሴን ጎርጉሬ በሀሳቤ,በተወለደው እኔነቴ የባዶ ጣር አግስቸ ነው እንጂ ምኑ ሊገደኝ የሰው አሻግሬ አያለሁ አለሜ::እንዴው ስንቱን ዘመን ኖሬ ላልፈው ነው የሰው አንጋጥጬ አይቼ በሰው ውልደት ቅናትና ሀብት ለራሴ ማስታውቀው????የሰውን ጣረ ምጥ የምኮርጀው??ምነው የድሮው የትምህርት ቤቱ ኩረጃ አይበቃኝም???ዛሬስ ትልቅ ነኝ....የተራራ ስባሪ ስለዚህ አምጨም ቢሆን ደም እወጣታለሁ እንጂ የሰውን እንደራሴ ለማድረግ አልዳዳም::
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Tue Jun 27, 2006 11:21 am

ውስጠትን ጠልቀን መርምረን ቀለው የምናገኛቸውን ነገሮች ቀድመን ብናቀላቸው ለነገሮች አለመጨነቃችንንና ለነገሮች ክብር አለመስጠታችንን ስለሚያሳይ እንዲቀሉልን ከመዋተትና ከመወትወት ይልቅ ምትአተ አይምሯችንን ለማሰራት በሳንባችን ሙሉ ትንፋሻችንን ስበንና ሞልተን ለጥልቁ የምርምር ውቅያኖስ ዋና መዘጋጀትና መስመጥ አለብን::ለምን ቢባል ከሁሉም በላይ የእራካታ ጫፍ የተደበቀን ነገር በራስ ጥረት አግኝቶ የግል ማድረግ ነው::
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Tue Jun 27, 2006 11:57 am

በጣም ደካማ መሆኔን ያወቅኩት አሁን ነው.....ነገሮች ካልገቡኝ የገባው ካለ መጠየቅ እንጂ ቀድሜ አቀብ ወጥቼ ለስድብና ለማሽሙዋጠጥ እራሴን ምጥለው ባዶነቴን በራሴ ላይ ማወጅ አይሆንብኝም???
ሾተል ያየውን የሰማውን,ያደረገውን,ነክቶት ያለፈውን በሚገባው ሁሉም ሊግባቡበት በሚችሉት ቁዋንቁዋ አገሳ...ታድያ ይህ ምን ሀጥያት ሆኖ ነው አንዴ እብድ በጬ አንዴ ከመጽሀፍ ነው ኮርጀህ በቃላቶች መነባነብ ያስታቀቅከው የምንለው::የተኮረጀበት ደራሲና የተኮረጀበት መጽሀፍ ካለ ሾተል ከዚህ መጽሀፍ ነው የኮረጅከው ይባልና አፍረቱን ተከናንቦ ዳግም ለጸሀይና ነፋስ ሾተል እራሱን ላያሳይ እስከምጽሀት ቀን ድረስ ይሸሸግ....ካልሆነ ግን ምንም የሾተል ሞራል ባይሞትም ሞራሉን የገደልን መስሎን በሚገባው ቁዋንቁዋ ባንጎነትለው ጥሩ ነው::
ይህ ንጹሁና ክርፋቱ አይምሮዋችን እኮ ለማበላሸት,ለማስተካከል,ለመፍጠር ነው የተወለደልን....ስለዚህ ሰውን መፍጠር ይክበድ እንጂ ለላ ለላውንማ መፍጠር የሚከብድ አይመስለኝም:ጥሁፍማ ቀላል እኮ ነው ለመፍጠር....ያየነውን ከሽነን አሳምረን ማቅረብም እንደመፍጠር ይቆጠራል...ሾተል እየገለጸ ያለው የሱንና የነሱን የኑሮ ስንክሳር,የፍጥረተ ሂደት ክንዋነዎችንና እውነታዎችን ነው::እራሱን ጠልቆ ገብቶ ማየት ፈለገና አጋጣሚ ያየውን ነገር አይረሳው ዘንድ በማስታወሻ ነገር አትሞ አስታወሰውና ለላኛው እሱነቱ እንዲያየው ገላልጦ ታይፑን ተመተመው....በቃ ያ ነው::ሾተል ደሞ እራሱን እንጂ ሰውን አይደለም ስለዚህ እራሱን ሆኖ በተከፈተለት የመማማሪያ መድረክ እራሱን ቢገልጽ አንዴ ከመጽሀፍ ነው አንዴ አበድክ ቲርኪ ሚርኪ የሚባለው...

እብድ እኮ በሰላም የሚኖር ነጻ ፍጡር ነው.....ያሻውን ያስባል,ያሻውን ያደርጋል,በውስጡነቱ መሪ የለው ህግ የለው,ገደብ የለው,...የፈለገውን ያደርጋል በፈለገበት ይኖራል.....ነገር ግን ድርጊቱ ሳይገባን ከብዶ ና ተሸፍኖ የታየን ነገር ከአይምሮ አይናችን ላይ የተጋረደብን ነገር ከግርደቱ ሲጠራና የተጋረደው ነገር ግልጽ ሆኖ ሲታየን በራሳችን እንደምንስቅ አልጠራጠርም::
ሾተል ነኝ....ከአማርኛ ጣፋጭ ማሳ
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ሾተል » Thu Jul 06, 2006 12:01 pm

ለትናንሾቹ ተብሎ ትላልቆቹን መጉዳት እንደሆነ ከተለያየ ቦታ ቢወሳልኝ እኔም ትላልቆችን የማክበር የዘር ማንዘር ባህል ውራጅ ስላለብኝ ወርሴን ሳይሞት ለማቆየትና ለእኔ የዘር ጠብታዬ ሚጠቅመውን ባህሌን ማውረስ እንዳለብኝ ሳውቅ ለምን ብዬ ጽሁፌን ላቁም አልኩና ትላልቆቹን በማክበር ካለኝ የህይወት ፍልስምና ላካፍል ዳግም መጣሁ::በርግጥ ትናንሾቹስ ማን አላቸው??እኔና እኛ ካላከበርናቸው ማን ሊያከብራቸው???ስለዚህ እኔም ከእኛ ጋር አከብራቸዋለሁ::

አንድ ነገር ተገነዘብኩ::እኔ እራሴውና እኛው ለካስ ሰውነት የማይለቀን ሰዎች ነን::አንዱ በሞከረው ቁጭ ብዬ የምነድ የምቃጠል.....ቀዬው ተስማምቶት,ደክሞ ባገኘው,ያለውን በወረወረው ለጋሽ ውስጤ የሚነድና እንደአንዳች የማር የሰውን ሰውነት የተሸከምኩ ሰው....ይብላኝ ለኔ.....እስቲ ምናለ በራሴው መንገድ ብጉዋዝና ሌላውን ባላይ??እስቲ ሌላኛው ቢደሄይ እደሰትበት ዘንድ ምኑ ሊተርፈኝ ነው ባይሆን ቢትረፈረፍለት ጭብጦ እንኩዋን አገኝ ነበር አዙሮ የሚያይ ህሊና ቢኖረኝ::አቤት መጥኔ ለኔ......የቁርጡ ቀን ምን ሊውጠኝ ይሆን??አቤት ክፋቴ ክርፋቴ....


በርግጥ እኔው ለራሴው ነኝ::ማንን ከመጤፍ ልቁጠር ብዬ እንጂ በራሴው ዛቢያ የምሾር ብቻ ብሆንማ በንዳድ ጊዜም ቢሆን አፍረቴን መሸፈኛ ክልባሽ ጨርቅ ባላስፈለገኝ ነበር....ለድፍረቱ ምን ጉልበት ኖሮኝ ነው እንጂ::

እስቲ እስክፈላሰም አለሁ ለማለት ነውና የሚመጠምጡ ትንኞች አካባቢዬን ቢወሩትና የማይቆረጠው ተስፋዬን መስሎዋቸው ሊመጡት ቢታገሉም እኔ ሁሌም አለሁና ግባቸውን ከትልማቸው ጋር ይዘው ይሰያሉ እንጂ ዳግም እል ዘንድ ከዛሬ ጀምሮ እመላለሳለሁ::

ተመለስ ላላችሁኝም ትላልቆች ከአክብሮት ጋር ተመልሻለሁ,ቃላችሁንን የመጠበቅ ግዴታ ስላለብኝ::

አይገቦ ዘንድ ያላችሁም የቱጋ አልገባችሁ እንደሆን በነጻነት ጠይቁኝ.....እመልስ ዘንድ መዘጋጀቴ መልኬ ጥርት ብሎ ያስታውቃል::አለመጠየቅና አለመመለስ ግምኛ ነው አይገባም::በርግጥ በርግጥ የሚያሳጣ እኔነት የለብኝም ምስጋና ለፈጣሪ ይግባውና

በሌላነቴ ተበርዞ እኔነቴ ስለጠፋ እኮ ነው ነገር በሽክና ቢግቱኝም አልገባ ያለኝ ቢሆንም ቢሆንም ነው ያሉት 50 አለቃ ገብሩ የ ታገል ሰይፉ ውልደት???አቦ ቢሆንም ቢሆንም እኔነቴ እንዳይረሳ ከበደም ቀለለም ዘላለም ይቆይ ዘንድ ሰርስሬ እያወጣሁ በኔነቴ ወርቃማ ቃላት እዋባለሁ....ያም ደግሞ እራሴን ስላስፈለገኝ ነው....በቃ ምን ይጠበስልኝ:.
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Next

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: Bing [Bot] and 2 guests