የዋናው አጫጭር ልቦለዶች

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ዋናው » Sat Aug 30, 2008 3:30 am

ጠጅ በትዝታ


ወይዘሮ ደብዚ የመጀመሪያ ልጇን እህምምን ስትድር የተበረከተላትን ጥለቱ ያማረ መልካም ጋቢ ደርባ ከጠጅ ቤቱ በር ፈንጠር ብላ ቁጭ ብላለች : ከወዲያ ማዶ ቅራሬ 3ተኛ ቡና ጥዳ የከሰሉን ፍም በማራገቢያ ታባብላለች ጀበናው ግን እንደሚያበሽቃት ሁሉ ሊፈላ ቀርቶ በድን ሆኗል ::
ቅራሬ የከፈተችዉን ጠላ ቤት ከስራ ዘግታው ከወ /ሮ ደብዚ ጋር ከተጠቃለለች መንፈቅ አልፏታል : አንዳንድ የሠፈሩ ሠዎችና የጠጅቤቱ ደምበኞች 'በጉዱ ካሣ ፍቅር ነፍሷን አጥታ ችላ ብላው ነው ቤቱን በራሷ ጥፋት የገደለችው '' ብለው ይኮንኗታል : የደብሪቱ ዶሮ ወርቃበባ ምታሰጣዉን ብቅል ስትቀልድባት ያየች ደብዚ ቤቱን ዘግታ ከርሷ ጋር እንድትኖር ሃሳብ አቀረበችላት ::

ደብዚ ገበያ የከዳው ቤቷን በምሬት እያየች ትንሽ ቆየችና በትዝታ ጭልጥ አለች :: ወደ ድሮው .... ወደ 2005

የቤቱ ግርግር ለጉድ ነው ደብዚ ወርቅ ጥርሷን ብልጭ እያደረገች ጠጇን እያደነቁ ሚያንቆረቁሩት ደምበኞቿ መሀል እየተሽሎኮለከች ከጠዋት ፀሐይ ማይተናነስ ፈገግታዋን ትለግሳለች :: ካሳው ሚባል ጠጅ ቀጂ ፈጣጣ ዓይኖቹን እያንቀዠቀዠ ቦርጫሙን ማንቆርቆሪያ ይዞ ይራወጣል ::

''እንዲያው አንተን ወጣት ሆኜ ባገኝህ ተክልዬን አልምርህም ነበር ''
ትላለች ወይዘሮ ባፈና የ SUAVEን ቀልድ እየሰማች SUAVE ከነ ኩሩቤልና ከነዘማች ጋር ሆኖ ያወራል አጠገባቸው ወይዘሮ ባፈና እና እሪኩም ተቀምጠው ብርሌያቸዉን ጨብጠዋል እሪኩም በወ /ሮ ባፈና ይታማ ነበር ወ /ሮ ባፈና ሱሳቸውን ካባታቸው ወይም ከድሮ ባላቸው ነው የወረሱት ይላል SUAVE ብርሌያቸዉን ቆንጥጠው አገጫቸዉን ቁልቁል ሲያሾሉ እያየ ::
ትምሕርት የሞቀ ሚሪንዳ በጠርሙስ ይዞ ስለዘመኑ ስልጣኔ ለመሪጌታ ዋኖስ ያወረዋል : መሪጌታ በወሬው ብዙም የተመሰጠ አይመስልም : ይልቅስ የ SUAVE ቀልድ እንደሳበው ሁሉ ደጋግሞ እየዞረ ወደነሱ ያያል :: መሪጌታ ደብዚ ማር እያስላሰች ምታቀርብለት ብርዝ አልኮል እንዳለው ሚያውቁት ሁለቱ ብቻ ናቸው :: ፀበል ለመርጨት ብሎ ረፋድ ላይ ደብዚ ቤት ሲሄድ ደብዚ የጉዱካሳን ቁርጥ ስለምታቀርብለት በየሳምንቱ ይሄድ ነበር : ዶማው እህምምን አስጠናለው እያለ ደብዚ ቤት ሲመጣ
''እኚህ ቄስ በየሳምንቱ ፀበል ሚረጩት ምን ዓይነት ሰይጣን ቤታቹ ቢኖር ነው ?'' እያለ እህምምን ያበሽቃታል ::
ደብዚ '' ገበያዋን በደስታ እያየች አረንጓዴ አግዳሚ ወንበርና ብርሌ ማስቀመጫ ጠረጴዛዎችን ቀሚሷን በመሰብሰብ እያለፈች
''ምን ይምጣ ?''
ትላለች : ባለሱቅ ሡቁን ዘግቶ ከነጉዱ ጋር ተሰይሟል :: የለስላሳ ጠርሙስ ብዛት የደመረበት የእጁ መዳፍ ላይ ያለው የእስክሪፕቶ ቀለም እንዳለ ነው ጉዱ ካሣ ጮማ ሲከትፍ ውሎ በወዛ እጁ ሞረድና መጥረቢያ ባዶለደመው ጣቱ ትትና የሸጠችለትን ገብስ ቆሎ እየዘገነ
''ትቴ ... መቼም ይሄን ቆሎ ያጣፈጠ ሙያ ....'' ይላታል ብምኞት እያያት አልፎ አልፎ ብፌስታል እየቋጠረ ቅንጥብጣቢ ያመጣላታል :: ጦጣው የማሲንቆዉን ጅማት እያከረረ ደጋኑን በመወደር አስቂኝ የአዋቂ ግጥሞቹን በዜማ ይደረድራል ::

''ተቀበል ...''
አለ ጉዱ እንደሚያርደው ሠንጋ ትከሻዉን ነፋ ለማድረግ እየሞከረ

''የኔማ ደብዚቾ የዋርካዋ አድባር ...''
ጦጣው በቅላጼ ይቀበለዋል : ቀጠለ ጉዱ ብርሌዋን ቆንጠጥ አድርጎ
''... አንቺ ባትኖሪ ምን ይውጠን ነበር ...?''
ጭብጨባ ተሠማ

''ተቀበል ...''
አለ መሪ ጌታ ዋኖስ ብርዙን ወደ አፉ እየሠደደ ... ከዛም ቅኔ አዘል ስንኙን ለ ጦጣው ያቀብላል ::

ጌታ ሲመጣ ከፊሎቹ ተነስተው እጅ ነሱ :
''ኸረ ሃኪም ጌታ እድሜዎ ማቱሳላ ነው እንዲያው ሳነሳዎ መጡ ...!''
አለች ደብዚ እንቁላል ቅቅል በዳንቴል ሸፍና ገበያ ምትማፀነዉን ፉፊን እንድትወጣ እየነገረቻት : ፉፊ ዓይኖቿ ነፍሴ ላይ እንደተተከሉ ዞር አለች
''ምነው በሠላም ?''
አለ ጌታ በኩራት አግዳሜው ላይ ቁጭ ብሎ እጅ እየነሳ
''እንዲያው መቼም መዳኒት አዋቂ ነህ ........ወጣት ሚያደርግ ኪኒን የለህም ?''
አለች ደብዚ በቁሟ ወደ ጠጅ ቀጂው ካሳው እየተጣራች

''ዛሬ ደግሞ ወጣት መሆን አማረሽ ?''

''ምን ላድርግ እኛ እድሜያችን ከፈጀ እነ 'ነፍሴ ' ተፈጠሩ እኔም እንደ ባፈና ወጣት ሆኜ ከነሱ ጋር መቅበጥ አማረኛ ... አበስኩ ገበርኩ .... መቼም ልብ አያረጅም ነው ያለው ያ ዘፋኝ ...''
ሳቋ ጠጅ ቤቱን ይሞለዋል :: ነፍሴ ፈገግ አለና
''አይ ወ /ሮ ደብዚ አኪም ጌታ ሚያስረጅ እንጂ ወጣት ሚያደርግ መድሀኒት የለዉም ::''
አለ :: ይሄኔ ወ /ሮ ባፈና የከናፍርቷን ጎኖች በሁለት ጣቷ ቁልቁል እያለበች
''እንግዲያውስ SUAVEን አስረጅልኝና አፈፍ ላድርገዋ .....''
ስትል ሳቁ በረከተ ::
እሪኩም እየተነሳ ባረጀ የራሺያ ካሜራው ፎቶ ሲያነሳ ያየው ባቲ ከጥግ ሆኖ ከዝምታው ድንገት እንደነቃ ሁሉ
''እኔ 'ምለው አንተ ምታነሳው ፎቶ ሚደርሰን ሠማይ ቤት ነው ? ሁሌም ምታሳየን የእርኛና የወንዝ ፎቶ ነው ''
አለው : አጠገቡ ደጉ ሚሪንዳ ይዟል : ከውቃው ጋር ኃይለኛ ክርክር ላይ ናቸው : ውቃው ለፍልሰታ ፍቺ መንደር ውስጥ 8 በግ ገፍፎ እንደመጣ በጀብደኝነት ሲያወራ ደጉ ደግሞ
''እንዴት ነፍስ ያለዉን ነገር ታርዳለህ እስቲ አንተ በግ ሆነህ አስበው ....''
ይለዋል ::
.
.
.

ወ /ሮ ደብዚ እንዲያ የደመቀ ጊዚያትን እያስታወሰች ዓይኖቿን እምባ ሞላው ዛሬ ቤቷ ''እንዴት ዋላቹ '' ብሎ ሚመጣም ጠፍቷል ደጋግማ ለሽያጭ ብታቀርበው አልተሳካላትም :: ከማዶ ሠፈር ያሉት መሸታ ቤቶች ድምቀዋሉ እሷም በጊዜ እየዘጋች ባልቻ ግሮሠሪ ቁንድፍቱ /አረኼ ይዛ መቀመጥ ጀምራለች ::
''አበስኩ ገበርኩ አይ አንቺ ዋርካ .... እንዲያው መጨረሻሽ ምን ይሆን ...?''
አለች ድንገት ከሕልሟ እንደነቃች ብንን ብላ ኦና ቤቷን እያየች

''እትዬ .... ዛሬ መልስ አለብኝ ብለው አልነበር ?''

አለች ቅራሬ ሢኒዎቿን ከነመሰናዶው እየሰበሰበች


''ኸረ አዎ ያ ዶርዜው በዚህ ሳልፍ አብረን እንሄዳለን ብሎኝ'ኮ ነው ድሮስ ሸማኔ ማመን...''
አለች ጋቢዉን ወለቅ አድርጋ ከስር ዶርዜው ተጨንቆ የሠራዉን ጥበብ በፈገግታ እያየች

ይሄን ጊዜ ከደነበረ በግ ጋር ጦምኔው እየተራወጠ ወደጠጅ ቤቱ ገባ ::
''የጊሸኗ ድረሽ .... ምን መጣ ?''
አለች ደብዚ ደምብራ : ጦምኔው ከደነበረ በጉ ጋር ሲተራመስ ስራ ያጡ አግዳሚ ወንበሮች ተናዱ :
''ይሄ ነው የቀራቹ በምንምን የቤቴን ገበያ ጥርግርግ አድርጋቹ ወስዳቹ አሁን ደግሞ በዚህ ኦና ቤት ቀንታቹ በበግ ልታፍርሱት ነው ?''

''ኸረ ደብዚ .... በግ አይደለም ''

''ምን ?''

''ወይፈን ነው ... አባፈረዳ ለ ናቲሜሽን መልስ ባልቹ ቤት እንዳደርስ የላከኝ ወይፈን 'ኮ ነው ''

''ይሄ ?''
አለች ደብዚ ወደ ወይፈኑ እያየች : ውይፈኑም በመናቁ የተናደደ ይመስል በግ አለመሆኑን ለማብሰር ፋንድያዉን አንጠባጠበ

''አዎ ከስቶ 'ኮ ነው ....''

''አበስኩ ገበርኩ ''
አለች ደብዚ እያማተበች

ተ ፈ ፀ መ

ማስታወሻነቱ ለወ /ሮ ደብዚ ጠጅ ቤት ይሁንጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby Debzi » Sat Aug 30, 2008 3:57 am

ዋናው!!! በጣም ግሩም ነው:: እንዲሁ ከመጀመሪያው እስከሚያልቅ ድረስ እንደሳኩ ጨረስኩት ሰው ጉድ እስከሚል:: ደሞ ከምኔው ይህ ሁሉ ሀሳብ መጣልህ ባክህ???

በጣም ነው የወደድኩት:: ትልቅ ምስጋና:: እፎይ:: ያሰብኩት ተሟላልኝ::
Ke akbrot selamta gar!!
Debzi
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1918
Joined: Sun May 02, 2004 12:34 am
Location: Los Angeles, CA

Postby እሪኩም » Sat Aug 30, 2008 10:09 am

ሠላም ልጅ ዋናው!

መልካም ጭውውት ነው:: ከክፍል አንድ ወደ ክፍል ሁለት እንደምትሸጋገር ተስፋ አደርጋለሁ::

በዬት በኩል መጣህ እኔ ሳላውቀው:
ዘኒት ካሜራዬ ስንቱን እንዲህ ልትችለው::

ደብዚ ጠጇን ጥላ አህሪቡ ስትለን:
ዘውትር ደንበኛ ነኝ ወድጄ ባፈናን::

ፓን ሪዚኮ ዘሎ ብርቄን ሲስም:
በጣም አኮረፈች ፈረንጇ እህምም::

የከንፈር ወዳጄ ባፈና ባትኖር:
መንገዱ ወልጋዳ ምን ይውጠኝ ነበር::

ታሪኩ ረጅም ነው በዚህ አያልቅም:
ደብዚ ቤት ሂደን ጠጅ እንኮምኩም::


መልካም ሰንበት
እሪኩም ከቦሩ ሜዳ
Image
መሸፈት ያለ ነው ይጠየቅ ልብሽ :
ሥንድድ እና ድንብል አሸን ክታብሽ ::

http://www.cyberethiopia.com/warka5/vie ... hp?t=23129
እሪኩም
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 853
Joined: Fri Apr 01, 2005 1:20 am
Location: ወሎ

Postby ዋናው » Tue Sep 16, 2008 2:29 am

እሪኩም wrote:ሠላም ልጅ ዋናው!

መልካም ጭውውት ነው:: ከክፍል አንድ ወደ ክፍል ሁለት እንደምትሸጋገር ተስፋ አደርጋለሁ::

በዬት በኩል መጣህ እኔ ሳላውቀው:
ዘኒት ካሜራዬ ስንቱን እንዲህ ልትችለው::

ደብዚ ጠጇን ጥላ አህሪቡ ስትለን:
ዘውትር ደንበኛ ነኝ ወድጄ ባፈናን::

ፓን ሪዚኮ ዘሎ ብርቄን ሲስም:
በጣም አኮረፈች ፈረንጇ እህምም::

የከንፈር ወዳጄ ባፈና ባትኖር:
መንገዱ ወልጋዳ ምን ይውጠኝ ነበር::

ታሪኩ ረጅም ነው በዚህ አያልቅም:
ደብዚ ቤት ሂደን ጠጅ እንኮምኩም::


መልካም ሰንበት
እሪኩም ከቦሩ ሜዳቅቅቅ እነኚህን ስንኞች አላየዋቸዉም ነበር እሪኩም

ደብዚቾ ያንቺ ጠዥ ቤት ታሪክ ብዙ'ኮ ነው..... ጠፋሽ ደግሞ ምነው?

ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Thu Nov 20, 2008 4:09 pm

እስቲ እቺንም ቤት ሽርፍራፊ ምናቦችን አጥልዬ አቆንቆረቁር ዘንዳ ሣሎን ይሁን::
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

መካሪዎቹ

Postby ዋናው » Fri Nov 21, 2008 10:40 pm

__
ፍቅር ምትለዋን የሚቲቱን ቤት ከጎበኘው በኌላ እቺን ነገር ጣፍ ጣፍ ቢለኝ ነው የጣፍኩት
___________ __________መካሪዎቹ___ _________

ብቻዉን ሲሆን እሷን ማሠብ ከጀመረ ቆይቷል ሠሞኑን ግን ለየት ያለ ስሜት እየተሰማው ነው: በተለይ ትላንትና ከምትሠራበት ግሮሠሪ ሄዶ የከፈተችለትን 2ተኛውን ሚሪንዳ ተጎንጭቶ ሲያያት ከውጪ የገቡትን አዲስ ተስተናጋጆች ምታይ መስላ ገርመም ስታደርገው አፉ ውስጥ ያለው ሚሪንዳ ትን እስኪለው ነበር የደነገጠው
ዛሬ እዚሁ ዋርካ ሠፈር ውስጥ ጓዋደኛው የሆነው ሀሪከን ምን ማድረግ እንዳለበት ምክር ቢጤ ሊሠጠው ቀጠሮ የያዘበት ቦታ ደረሰ: ዝናቡ ካባራ ቢቆይም የዋርካው ቅጠሎች በዶፉ ረግፈው ከመሬቱ ጪቃ ጋር ተለውሠዋል... ዋርካዉን ጥቂት ዋርካዊያን ከበዉት ሁሉም በራሳቸው ዓለም ውስጥ ናቸው ጌታ,ጦምኔው,ጋሎ,መንፌው, ክብ ሰርተው በጦምነው የአራዳ ትዝታ ተመስጠዋል::

ሻይ ቦይ ሠዓቱን ለማየት የለበሠዉን ባለመስመር ሸሚዝ ሲሰበስብ ከጎኑ አንዲት ጉብል መጥታ
''ፍቅር ማለት ምን ማለት ነው?''
ብላ ተየቀችው ሻይ ደንገጥ ብሎ
''ከሩብ ሆኗል ''
አላት: ልጅቷ ከጆሮዋ ጥግ ያፈተለከ ፀጉሯን በጣቶቿ ጫፍ መልሳ እየሸጎጠቻቸው ፈገግ አለችና
''እኔ የጠየቅኩህ'ኮ ሌላ ነው''
አለችው ስትስቅ የግራ ድርብ ጥርሷ ከንፈሯን ገፋ አድርጎ አንዳች ለዛ ይሰጣታል: ሻይ ተደናቅጦ እጁን ለትውውቅ ሰነዘረላት: ድፍረቱ ለራሱም ገረመው::

''ሚቲቱ... ''
አለችው የርሱን ስም ከነገራት በኌላ
''ማን?''
''ሚቲቱ....''
ሻይ ቦይ ፈገግ አለና
''ምን ማለት ነው?''
አላት: ሚቲቱ ግን ሳቋን ለመቆጠብ ልዝብ ባለ ፈገግታ የሻይን ዓይናፋር ዓይኖች እያየች
''መጀመሪያ የኔን ጥያቄ መልስልኝ ፍቅር ማለት ምን ማለት ነው?''
''ከምር ግን ሚ2 ማለት ነው ወይስ...?''

''መጀመሪያ መልስልኝና እነግርኻለው አልኩህ'ኮ''
አለች እሷም ቀጠሮ እንዳላት ሠዓቷን እያየች ሻይ ተንፈስ አለና ጥብቅ አድርጎ የታጠቀዉን ቆዳ ቀበቶ ከጎንና ጎኑ እንደመነካካት አድርጎ ቀጠለ
'እሽ የራሴ ትርጓሜ ልስጥ ............

ፍቅር አንድን ነገር (ወይም ሰው ) ስናስበው ደስ እንዲለን የሚያደርግ ስሜት ነው !!! የጾታ ፍቅር ሊሆን ይችላል : የናት ፍቅር ሊሆን ይችላል : የሀገር ፍቅር ሊሆን ይችላል ...........ግን ብቻ ስለዚያ ነገር /ሰው ስናስብ ደስ የሚል ስሜት ከተሰማን ያ ስሜት ፍቅር ይባላል :: ስሜቱም እውነተኛ እና ከልብ የሚመነጭ : አስበነው እና ፈልገነው ሳይሆን በራሱ ጊዜ የሚፈጠር ነው :: የኔ ትርጉም ይህ ነው ::''
አላት በመልሱ ራሱ እንደረካ ሁሉ ራሱን ነቅነቅ አድርጎ: ሚቲቱ ምንም አስተያየት ሳትሠጠው
''ኦኬ ... ሚቲቱ ማለት ደግሞ በወላይትኛ ፍቅር ማለት ነው''
አለችው:: ይሄን ጊዜ ከጎን ሆና ትሰማ የነበረችው ትትና ጣልቃ ገባችና
''ዋው በወላይትኛ ደስ ይላል ልበል? .... በናትሽ ሚቲቱ ያዘኝ ሚለውን ቃል ፍቺዉን ፈልጊልኝና አብሬ ልበለው?''
አለቻት:ሻይ ዓይኖቹን እንደሰበረ ሠዓቱን ሲገላምጥ ጌታ ሚያነበዉን የጤና ሞግዚት የሚል መፀሐፍ ከደነና ከተቀመጠበት ተነስቶ
''እኔ'ኮ ስትኮላተፍ ምስሎኝ ነበር ሻይ... ያው ሚጡ ለማለት ሞልቀቅ ልትል ያሰበች መስሎኝ ስትጠይቃት የሻይቦይ ነገር እያልኩኝ ስታዘብህ ነበር:''
አለ:: ትትና ስለፍቅር ምንነት በሀገር ምሳሌ አድርጋ ለሚቲቱ ታስረዳታለች ሚቲቱ ግን አሻግራ የጌታን የሽርደዳ ንግግር ለመስማት እየሞከረች ነበር::
ጌታ ከሻይ ጋር ሲሳሳቅ ጦምኔውና መንፌው ሚቱ የሕንድ አክተር ነው ብለው ክርክር ጀመሩ በተለይ መንፌው ትዝታው መጥቶበት ሚያውቃቸዉን የሕንድ አክተሮች አንድ ባንድ ሲዘረዝር ሚቲቱ ሳቀችና
''ሞክር...''
አለችው ሚቲቱ ስለፍቅር ምንነት ጥያቄ ብላ ማታውቀው ሠፈር መጥታ የራሷ ስም ትልቅ ጥያቄ የመፍጠሩ አጋጣሚ ገርሟታል:: የሁሉንም ቀልደናነት ስታስተውል የእንግዳነት ስሜቷ ከላይዋ እየሸሸ በቀልድ ልትቀርባቸው በመፈለግ..

'' የስሜን ትክክለኛ ትርጉም ያወቀ ካለ በፍቅር ልስመው ፍቃደና ነኝ:''
አለች ረዘም ያሉ ቃላት ስትናገር ግን ኮልታፋነቷ ይስተዋላል::
ሻይ ወደ ትትና ቀረበና....
''ትቴክስ ስታስረጂ ስሰማሽ ስለፍቅር ብዙ ምታውቂ ትመሲይኛለሽ .... እስቲ ባክሽ ምክር ቢጤ ስጪኝ ሠሞኑን እዛ ባልቻ ግሮሠሪ አንድ ያፈቀርኳት እንስት አለች... ገና ሳያት ድንብርብሬ ነው ሚወጣው በዚህ ላይ ያልበኛል: ስንት ቀን ልጨብጣት እልና የጄን ላብ አይታ ታውቅብኝ ይሆን? እያልኩ እተዋለሁ... አያ ዋኖስ ከዳሞት አንድ የላብ መከላከያ መድሐኒት አስመጥቶልኝ ነበር ግን አልሰራም....''
ትትና በሻይ ንግግር እየሳቀች ልስልስ ባለ አንደበቷ እንዲህ አለችው
''ሻይቦይዬ...... ፍቅር እንደተርጓሚው ነው ወይም እንደተመካቹ / እንደተጠቃሚው ይመስለኛል :: የኔ አመለካከት ግን ብዙ ጥረት የሚጠይቅ እንደ ተተከለ አበባ እንክብካቤ የሚፈልግ , በፍጹም ኢጎ የሚባል ነገር የማይስማማው , መቻቻልና ቀና አመለካከት የሚያስፈልገው ግዙፍ ግን የማይጨበጥ ረቂቅ ነገር ነው ::

ጥረትና /እንክብካቤ :- አንዴ ከተጀመረ በኃላ በፊት ይደረጉ የነበሩት ነገሮች ለምሳሌ በጣም መቀራረብ , አንዱ ለአንዱ ማሰብ (መጨነቅ ), ነገሮችን በቀላሉ ማየት , ከምንም በላይ ቅድሚያ መስጠት , የተለመዱ ቃላቶችን ወይም "እምጷን " አለማስቀረት , በተለይ መነጋገር , ግልጽ መሆን የመሳሰሉት የሚያስፈልጉት ከተሟሉለት ያንን ሰው ያለ አንዳች መመዘኛና ቅድመ ወይም ድህረ ዝግጅት ማፍቅር ማለት ይመስለኛል ::

ኢጎ /ፉክክር :- ለፍቅር ወይም ለአፍቃሪዎች የማይስማማ ስለሆነ በተቻለ መጠን ምን ተደረገልኝ ሳይሆን ምን ማድረግ አለብኝ የሚለው ላይ እያንዳንዱ ሰው ማተኮር ያስፈልገዋል :: ደስታን ከሌላሰው እጅ መጠበቅ ሳይሆን ምን አይነት ደስታ ላበረክት እችላለሁ ብሎ ስለራስ ማሰብ ::

ቀና አመለካከት ለሁሉም ነገር ቢያስፈልግም ለአቶ ፍቅር ግን በጣም በጠንካራው ያስፈልጉታል :: ፍቅር ደስታ ማለት ስለሆነ ቀና ካልተሆነ ደሞ ያደስታ አይገኝም ::''
ትትና የድምጿ ዝግ ማለት የሻይቦይን ጆሮ ዘረጋጋው: ራሱን ከፍና ዝቅ እያደረገ ካዳመጣት በኌላ

''ትቴክስ በጣም ነው ማመሰግንሽ ብዙ እንድታብራሪልኝ የምፈልገው እንዴት "አፕሮች " ማድረግ እንዳለብኝ እና መጠየቅ እንዳለብኝ ነው :: ከዛ በኋላ ላለው ነገር : አያያዙን እንዴት እንደሆነ ልምዱ ባይኖረኝም በጣም ምቹ እንደምሆን ይሰማኛል ለጉራ አይደለም :: አንች የጠቅስሻቸውን ነገሮች በሙሉ ብቻ ሳይሆን አስበልጦ ማሟላት የሚያቅት አይመስለኝም :: ችግሩ ያለው መጀመሪያ አቀራረቡ ላይ ነው ......... ''
አላት:: ይሄን ጊዜ ሀሪከን ቁና ቁና እየተነፈሰ ደረሰና መንፌዉን በተረብ ወጋ ወጋ አድርጎት ትትና እና ሻይ መሀል ገብቶ
''....ሻይ በጣም ይቅርታ ሌት ስለሆንኩኝ... ደግሞ ትቴክስ ምትመክርህን ሰምቼዋለው ...የምር ግን ሴትን ልጅ ስትቀርብ ልክ ወንድን ጋ እንደምትቀርብ ሆነክ ቅረብ ሴት ጋ ቀርበክ ትንሽ እንኴን የመደናገጥ እና የመረበሽ ስሜት ካሳየክ በቃ ነገሩን አበላሽህው ማለት ነው
በተረፈ በምንም መልኩ ሴትን ልጅ እንዲህ ሁኝልኝ እንዲህ ላድርግሽ ብለህ አትጠይቅ መጠየቅ እንኴን ለሀበሻ ለነጭም ልምድ ከሌለህ በጣም አደገኛ ነገር ነው

ሴትን ልጅ እነ ትትና መተው በሚመክሩክ ፎርሙላ ተከትለህ እጠብሳለሁ ብለህ የምታስብ ከሆነ የሚሳካልክ አይመስለኝም
ለሁሉም ስራክ ያውጣክ
''
አለው:: ጦምኔው ወመንፌው ጆሮ ጠጋ ብሎ
ዓይናፋሩ ያቺን ናርዶስ ምትባል ዌይተር ወዶ ሾቁዋል'ኮ አታየውም'ንዴ? እንዴት እንደከሳ''
ሲለው ጌታ ጣልቃ ገብቶ
''እሷ ልጅ'ኮ የመንደራው ሚባል ቦይፍሬንድ ነበራት....''
አለ::
ሻይ ቦይ ምን ማድረግ እንዳለበት ግራ እንደተጋባ ማሕደረ ቅልቅል እያለች መጥታ የትትናን ምክር በመንቀፍ የራሷን ምክር ልትሠጠው ሞከረች::ተንጨባሮ የቆመ ፀጉሯ(ፍሪዝ) ከእንቅስቃሴዎቿ ጋር አብሮ ይዘላል ስትናገር ሲያይዋት ታፍራለች:: ንግግሯ ውስጥ ማያቋርጥ ፈገግታ አለበት...
'1ኛ አትፈር ....ደፈር ደፈር በል .....
2ኛ የምትፈልገው ልጂቷን ለትዳር ከሆነ እንግዲህ በቀደም ስታወራው እንደነበረው አይነት የግብጦ ታሪክ አጫውታት (በነገራችን ላይ ግብጦ እንዴት እንደምወድ ) .......ከቻልክ አረቂውን አስመጥተህ ቀማምስና ወደ ሁለተኛው ጉዳይ ተረማመድ ...
3ኛ እንዲሁ ጊዜያዊ ነገር እና ወንዳ -ወንድነት ማፍታቻ አይነት ነገር ከሆነ የፈለከው ባጭሩ '____ስጭኝ ' በልና እርፍ በቃ ...አለቀ ...ከዚያ በኋላ አይን ማውጣት ብቻ ሳይሆን አይን የበላህ ሰለምትሆን ምንም አትልም ......እንደውም ለእኔ ቢጤ ምክር ሰጪ ሆነህ ታርፈዋለህ ....ግን የትትና መንገድ ከተከተልክ ዙሪያ ጥምጥም ስትሄድ መኖርህ ነው .............እንግዲህ የእኔን ምክር አልቀብልም ካልክ ግን ከልቤ እቀየምሀለሁ ...''

ሻይቦይ የመሐደረን ምክር ሰምቶ ሲጨርስ .....
''አይ መሐዲ ሁሉ ነገር በአፍ እንደሚያወሩት ቀላል ቢሆንማ ..... እዚ ሠፈር ከመንፌው የባስኩ ባለጌ ሆኜ በተገኘው ''
አላት እየሳቀ ሻይ ሲያወራ ካደገበት ቀዬ ይዞት የመጣው የንግግር ዜማ ይስተዋላል::
ይሄን ጊዜ እንግዳዋ ሚቲቱ ወደሻይ ቀረብ አለችና
''ከዚ ሁሉ ሠው የተመቸህኝ አንተ ነህ:''
ስትለው ግማሽ አፍረት ግማሽ ደግሞ የዋርካዊያን ጓደኞቹ መሠባሰብ ድፍረት እየሠጠው
''እንግዲያውስ ከሁሉም የመሐዲን ምክር ልጠቀምበት....?''
ሲል ስፍራው ላይ ሣቅ በረከተ ውቃው ጮክ ብሎ እየዘፈነ ማጭብጨብ ጀመረ

'አሃይ ቡና አሃይ ቡና
አሃይ ቡና አሃይ ቡና


አቅፎና ደግፎ ..... ስሞ እንደመለመን
አቅፎና ደግፎ ...... ሰሞ እንደመለመን
እስኪ ስጪኝ ይላል እንደናቱ ጎመን

አሃይ ቡና አሃይ ቡና ''

ጦምኔው እያጨበጨበ ካጀበው በኌላ
''እንዴ .....ቡና ስትል ትዝ አለኝ ...ሞኒካ ቤት አንዲት ቺክ ቀጥሬ ነበር''
አለና መሮጥ ጀመረ
የሻይ ቦይ ጊዚያዊ ድፍረት ግን አልበረከተም ፅጉሩን እያሻሸ አንገቱን ደፋ::

አ.ለ.ቀ


ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby Debzi » Fri Nov 21, 2008 11:29 pm

እዝጋቤር ይስጥህ, አቦ!

አዎን....ዋርካን እምናውቃት እንዲህ ጥሩ ሙድ ውስጥ ስትከተን ነው:: በጣም ነው የወደድኩት!!
Ke akbrot selamta gar!!
Debzi
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1918
Joined: Sun May 02, 2004 12:34 am
Location: Los Angeles, CA

Postby ሚቲቱ » Sat Nov 22, 2008 1:01 am

ዋናው በጣም በጣም ነው ከልቢ የማመሰግንህ አሪፍ ነው የጳፍከው በዚሁ ቀጥል አጳጳፍክ ድርሰት ነው የሚመስለው በርታ የኔ ወንድም አሺ ............. ሚቲቱ
ሚቲቱ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 101
Joined: Sat Nov 15, 2008 5:04 am

Postby ሚቲቱ » Sat Nov 22, 2008 1:18 am

shy boy ትትና የሰጠችህ አስተያየት አኔም አደግፈዋለው በጣም አሪፍ ነው ግን ነገ አኛንም አንደሱ አንዳታደርገን. በበበበበበበበበበበ............ሳሳሳሳሳሳሳሳሳ.................ቅቅቅቅቅቅቅቅቅ
ሚቲቱ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 101
Joined: Sat Nov 15, 2008 5:04 am

Postby ShyBoy » Sat Nov 22, 2008 2:44 am

እንዴ ዋናው!!! ከምር ከምኔው እንዲ ከሸንሀት? ደሞ እኮ የትትናን ምክር ውድቅ አድርጌ የማህደረን ምክር ልቀበል ስል አንተው ራስህ ጨረስኸው? የኔ ስሜት እንዴት አወቅህ ግን?

ለማንኛውም እግዜር ይስጥልን!!!!
ShyBoy
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1118
Joined: Tue Apr 04, 2006 10:36 pm
Location: Gojjam

Postby ShyBoy » Sat Nov 22, 2008 3:36 am

ሚቲቱ wrote:shy boy ትትና የሰጠችህ አስተያየት አኔም አደግፈዋለው በጣም አሪፍ ነው


ሚቲቱ: በቅድሚያ በቤትሽ እንደዛ እንድንጫወት ስለፈቀድሽ አመሰግናለሁ!!! ሆኖም ግን የትትና ፕሮሲጀር እንደ አባይ መንገድ ስለሆነብኝ በትግስት የምወጣው አልመሰለኝም::

ግን ነገ አኛንም አንደሱ አንዳታደርገን.


አልገባኝም...........ልታብራሪው ትችያለሽ?

በበበበበበበበበበበ............ሳሳሳሳሳሳሳሳሳ.................ቅቅቅቅቅቅቅቅቅ

የእናትዬን አሳሳቅ ሪሚክስ አደረግሽው ማለት ነው? :lol: :lol: :lol:

በነገርሽ ላይ: ጥሩ ግጥሞች ትጽፊያለሽ!!! ያው አማርኛ ግድፈቶችሽን በልምድ እንደምታሻሽይው ተስፋ አለኝ.........ሁላችንም ተኮላትፈን ነው የለመድነው:: Hahu help የምትለዋን ተጠቀሚባት::

በሉ መልካም ዊኬንድ ይሁንላችሁ!!! ያው እንደተለመደው ነገ እዛ ቤትህ እንገናኛለን አይደል ዋናው?
ShyBoy
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1118
Joined: Tue Apr 04, 2006 10:36 pm
Location: Gojjam

Postby TrueObserver » Sat Nov 22, 2008 5:24 am

ስዎች ቀላል ይቀደዳል እንዴ እዚህ ቤት ውስጥ....Shyboy..ስታይልህ ተመችቶኛል ...አፋርታም ነህ ብዬ አላምንም ነገር ግን ጥሩ አክተር ነህ:: ከሆንክም ሻይ ቦይ ትትና እና ማህደረ በነካ እጃቸው አይንህን ይግለጡልህ..::

ማህደረና ትትና--- የተግባር ክፍለጊዜ የላችሁም? ከቲዎሪው ባሻገር:: የአለውን የሰጠ ንፉግ አይባልም :wink: ....ኢፍ ዩ ቦዝ ኦረዲይ ቴክን..ሻይቦይ ለአንተ አዝናለሁ :)

ቺርስስ
Wise
TrueObserver
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1011
Joined: Tue Sep 26, 2006 3:17 am

Postby Senayte » Sun Nov 23, 2008 7:11 am

ሎል አንተ ዋናው .....".ግብጦ " ማለት ምን ማለት ነው ድግሞ?

እንዳንዶች ቃላቾች ትርጉማቸውን ይቅርና አማርኛ ቃላት የማይመስሉኝን ዋርካ ውስጥ እስማለሁኝ ሎል ::

መልሱን በቶሎ ዋናው ...ከምር አንድ ቦታም የሆነ ቃል ትርጉሙን ጠይቄህ ኢግኖርን ገጭተህኛል ሎል ::

ፍርዶብኝ ነገሮች ሳይገቡኝ ማለፍ ...... አልችልበትም ::
" Every problem has a solution. If it doesn't ,it isn't a problem but a fact ,and you must learn to live with it."
Senayte
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 241
Joined: Thu Nov 18, 2004 5:00 am
Location: Lieville.....

Postby sarandem » Sun Nov 23, 2008 2:53 pm

:lol: :lol: :lol: ዋናው አላበዛከውም እንዴ :?: ሰው ሲያስነጥሰው ሁላ ወደ ድርሰት እየቀየርክ አስቸገርክ::
አሪፍ መጣጥፍ ነው ይምችህ አቦ :wink:
sarandem
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 674
Joined: Tue Jul 11, 2006 8:59 am
Location: Nomad Cafe

Postby ShyBoy » Mon Nov 24, 2008 4:58 am

Senayte wrote:ሎል አንተ ዋናው .....".ግብጦ " ማለት ምን ማለት ነው ድግሞ?


ሰኑ: ዋናው መጦ የሱን ማብራሪያ እስኪሰጥ ይችን አንብቢ ስለግብጦ::
http://www.cyberethiopia.com/warka4/vie ... ht=#308905
ShyBoy
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1118
Joined: Tue Apr 04, 2006 10:36 pm
Location: Gojjam

PreviousNext

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 3 guests