by ትርንጎ* » Fri Sep 28, 2018 3:44 pm
<<<<<<<<<<<<<<<<<<<<<<<ወጣት ልጆች ላላችሁ>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>>
እንዴት ናችሁልኝ፡፡ መቼም ለብቻዬ ማውራት ጀምሬያለሁ፡፡ በቀደም የራሴኑ ቤት ወደሁዋላ ሄጄ ሳነብ ዋልኩና እንዴት የሚጥም ጊዜ ነበረን ...ድሮ፡፡ የነዳሞቴ፡ ዋንሽ፡ ውቅሽ፡ ሙዝሻ፡ ቆንጂቴ፡ ደብዚ፡ ሞኒካ....ሌሎቻችሁ ሁሉ እንደው የት ትሆኑ? በአይን ባላውቃችሁም ናፈቃችሁኝና በያላችሁበት ፈጣሪ ይጠብቃችሁ ካማለት ሌላ ምን አረጋለሁ፡፡ እኔስ የህይወት ማራቶን ይዞኝ ጠፍቼም አልነበር፡፡ በነገራችን ላይ ለዋርካ አባላት በሙሉ እንኩዋን ለመስቀለ ብርሃኑ አደረሳችሁ!!!
ሰሞኑን አንድ ልቤ ውስጥ ተሰንቅሮ አልወጣ ያለኝ ነገር አለና እንደው ከጠቀመ ብዬ ልጫጭር መጣሁ፡፡ ድሮ የማውቃት ደርባባ የአገሬ ሰው ነበረች፡፡ የሙት ልጆችዋን ለብቻዋ አሳምራ አሳድጋ ለኮሌጅ አበቃቻቸውና በመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁላት፡፡ አንደኛው ወደስራው አለም ሲሄድ ትልቁ ዶክተር ለመሆን በታዋቂ ዩኒቨርሲቲ ተቀብለውት ጀምሮ ሳለ ጭንቀት የሚባል ነገር ከሚገባው በላይ ይበጠብጠው ገባ፡፡ እናት ደጉዋም ስብስብ አድርጋ ወደቤትዋ ታመጣዋለች...ስሰማ ህክምና ሁሉ ጀምሮ ነበር፡፡ ተዲያ ባለፈው ሳምንት ይቺን ሰፍሳፋ እናት ላለማሳፈር ይሁን፡ ወይም ትምህርቱን መቀጠል ባለመቻሉ ተበሳጭቶ ከስራ ስትመጣ ራሱን አጥፍቶ አገኘችው፡፡ ገና ስታየኝ "ይኸውልሽ ያ ሁሉ መንሰፍሰፍ ለዚሁ ነው" ስትለኝ ምን ውስጥ ልግባ፡፡ ድሮ ስልክ ደውላ ሁለቱም ካላነሱ ተነስታ የስንት ሰአት መንገድ እንደምትነዳ እየነገረችኝ ስስቅ ትዝ ይለኛል ፡፡ የራሴውም ልጅ ትዝ እያለችኝ ሆዴ መንሰፍሰፉን ሊያቆም አልቻለም፡፡
ልጆቻችን እኛ ጎብዘው ጥሩ ቦታ እንዲደርሱልን በጣም የምንገፋቸው ብዙዎች ነን...ለክፋት አይደለም፡፡ ግን ደግሞ ቆም ብለን በነሱ ቦታ ሆነን ለማየትም መሞከር ሳይበጅ አይቀርም፡፡ በተለይ በውጭው አለም የወለድናቸውም ሆኑ በልጅነታቸው መጥተው እዚህ ያደጉትን የግድ "እኔ እንዲህ ነው ያደኩትና"...እያልን መንገታገቱ እያዋጣን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ይኸኛው ከፋ እንጂ የት ይደርሱ ይሆን የተባሉ ሌሎች ሁለት ልጆችም በአይምሮ ህመም መቀሰፋቸውን ከእናታቸው አፍ ሰምቻለሁ፡፡ አገሩ የፉክክርና የውድድር አገር ነው...በዛ ላይ ጉዋደኛ አለ...ብዙ ወጣት የሚያጠምዱ እንቅፋቶች አሉ፡፡ ታዲያ ይኸንን በቁጣና በማስፈራራት የሚዘለቅ ይመስላችሁዋል?
አንቺስ ምን እያደረግሽ ነው ለምትሉ እኔም ዞሮብኛል፡፡ ግን ልጆቼን ስሜ ስሜ ልጨርሳቸው ነው...በአጠገቤ ባለፉ ቁጥር... የነሱ ደግሞ ዝም ብሎ መሳም ፡) እኔን መቶ ጊዜ አንስቶ ለምን አያፈርጠኝም...ስለ ልጆቼ ግን ከአምላኬ ጋር ስበላም ስጠጣም ስነዳም ድርድር ሳምንቱን ሁሉ ይዣለሁ...እንደው ቢቸግረኝ፡፡ እርቃ ያለችውንም ልጄን ሳሞጋግስና ሳበረታታ ነው የከረምኩት፡፡ ለምን መሃይም ሆና የበላሁትን በልታ አብራኝ አትኖርልኝም? እንደው ፈጣሪ ከእንዲህ አይነቱ ሰቀቀን ይሰውረን ወገኖቼ፡፡
በሉ አላሰልቻችሁ፡፡ እንደው ወጣት ልጆች ያላችሁ እንደው ቆም ብላችሁ ግንኙነታችሁን ብትገመግሙና እኔም ሃዘኑ ቢወጣልኝ ብዬ ነው የሞነጫጨርኩት፡፡ ቸር ይግጠመን!
Last edited by
ትርንጎ* on Tue Oct 09, 2018 11:30 pm, edited 1 time in total.