የዳሞት ግጥሞች

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

አይ

Postby ዋኖስ » Wed Nov 03, 2010 10:27 pm

አይ የደረሰበት!ከሠው መሃል ተቀምጦ፣

በሃሳብ ባሕር ተሰርቆ፤ በሠመመን ተዉጦ፣

ጋያ-ሳቢ ይመሥል የሓሳብ ጅረት ሰልቅጦ፣

ወደ ሰማይ ሶስቴ ንሮ፤ ብሩሕ-ዓይኑን ገልጥጦ፣

አንዴ ስሟን፤ አንዴ መልኳን፣ አንዴ ፀጉሯን፤
በእዝነ-ሕሊናዉ ቀውጦ፣

ተመስጦ፤ ተመስጦ፤ ደግሞ ደግሞ ተመስጦ፣

በረቂቅ ምስጢር ተዉጦ፤ እንደቂቤ ዉስጡ ቀልጦ፣

ከዚያ በኋላ ሲመለስ፤

የልቡን ዓይን ይገልጣል። የዓለምን ዓይን አፍርጦ።


ዳሞት ከዳሞት!
ዋኖስ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1552
Joined: Tue Nov 16, 2004 2:39 pm
Location: Mars

Postby ኦኑፈያሮ » Mon Nov 08, 2010 12:15 pm

ብልጭ ብሎ ጠፋ !


ተኝቷል እንበል ወይም አንቀላፋ

ተጥሏል እንበል ወደቀ ተደፋ

ምራቅ ነው እንበል በምላስ ተተፋ

የሳት ራት መብራት ታይቶ እንደሚጠፋ

በወግ በማይረግ ተወግቶ በይፋ

የብርሀኑ ጮራ ሊያበራ ሊስፋፋ

የጨለማው ግርዶሽ ሊቀደድ ሊጠፋ

እኛም ደስ ብሎን ስንጠብቅ በተስፋ

ዲሞክራሲ እሚሉት ብልጭ ብሎ ጠፋ

በማለት አረዱን መርዶ የሚያስከፋ

መች አለልን እና እንዲህ ያል ማይረግ

ባህላችን ሆኖ ለውሼት ማደግደግ

መች አለልን እና ለመኖር ተስማምተን

የውሼት ማነቆ እየተጠናወተን

እኔ አውቅልሀለሁ አንተ አታውቅም ከኔ

ማንም አያገባው በገዛ ስልጣኔ

ፈረንጅ ይሁን አበሻ አይቆምም ከጎኔ

በማለት ሲፎክር በግፍ በጭካኔ

ፈረንጁም አበሻም ነጩም ሆነ ጥቁሩ

ሁሉም መብት አለው በገዛ ሀገሩ

አገሬ ለፍፊ ልፈፋ ድምጽሽ ከፍ ይበል ይሰማ በይፋ

የዲሞክራሲ አይን ብልጭ ብሎ ጠፋ

የዋሼ ምላሱን የሰረቅም እጁን መቆረጥ ቢጀምር

የዲሞክራሲ እይታ አይጨልምም ነበር

እራሱን ማታለል አቤት ማደናገር

በችሎት ስንቀርብ ለመሆን ምስክር

በየእምነታችን ማህላ መደርደር

በውነት እምላለሁ ሃሰት ላልናገር

እያሉ ለዳኛ ብለው በመደስኮር

እውነትንም ትቼ ለሃሰት ብናገር

ፍርዱን ይፍረድብኝ አምላክ ብሎ ነበር

ፈጣሪም ተረሳ እውነትም እረክሶ

ውሼት ውድ ሆነ ለገዜውም ነግሶ

እውነት ሰሚ አግኝቶ ያሼነፈለታ

ያኔ እሱን አያርገኝ የማታ የማታ

አንገቱን ቢደፋ ደረቱን ቢመታ

ምንዳውን ያገኛል ለዋለው ውለታ

ቢከመር ቢቆለል የውሼት ጋጋታ

ሃቅ ሰሚ አግኝቶ ብልጭ ያለ ለታ

ክምሩም ይናዳል የለውም መከታ

እልም ብትን ይላል ማሰሪያው ሲፈታ
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Sun Nov 14, 2010 8:14 am

ተው ቻለው ሆዴ !

ያለ ሥም ሥም ሠጥቶ ቢልህ አመለኛ

ለማየት ቢጠየፍ ቢርቅህ ጓደኛ

ለበጎ ነው ብለህ ናቅ አርገው ግዴለም

ሁሉም አላፊ ነው አይኖር ለዘላለም

አሉባልታ ወሬ ስላንተ ቢያወሩ

ቢያድሙ ቢያብሩ አንድነት ቢያሴሩ

በቀል የግዚያብሄር ነው እየው በቀላሉ

አልፋን ኦሜጋ ይፈጸማል ቃሉ

አለቃህ በተንኮል ሊጎዳህ ቢሞክር

እማኝ ቢሰበስብ የሃሰት ምስክር

አትፍራ በጭራሽ በፍጹም አትስጋ

የዘራውን ያጭዳል የስራውን ዋጋ

ወጭህን መጥነህ በእቅድ ስትሰራ

ከደባል ሱስ ወጥተህ ጫት አልኮል ሲጋራ

ከምሽት ዳንስ ቤት ስትቀር ከጭፈራ

የሆነ ያልሆነው ስላንተ ቢወራ

ቢጥምም ባይጥምም አድምጥ በጥሞና

ጉድ አንድ ሰሞን ነው አንተ ብቻ ጤና

ንፉግ ነው ስስታም ቢሉህ ለነገሩ

ያርግልኝ በላቸው መልሰው ይፈሩ

ጥረህ ተጣጥረህ ገንዘብ ስትይዝ ገና

ቤተሰብ መስርተህ ህይወትህ ሲቃና

እንዳሼን ቢፈላ ምቀኛ ቢበዛ

ለፈጣሪ ሰጥተህ እለፍ እንደዋዛ

አይበላ አይጠጣ አይውል ከሰው ጋራ

የቅርብ ወዳጅ ያልከው እያለ ቢያወራ

ጸያፍ ንግግሩ ውስጥህን ቢያደማ

ናቅ አርገህ ተወው ሰምተህ እንዳልሰማ

መለወጥ ስትጄምር አለ ብዙ ጣጣ

ዙሪያህ ይታጠራል በሾህ በጋሬጣ

አብሮ አደግ ጓደኛህ ይሆናል ባላንጣ

የሥራ ጓደኛህ ተበለጥኩኝ ብሎ

አሰት ቢደረድር እውነት አስመስሎ

ጥላሼት ቢቀባህ ሥራህን በክሎ

በትግስት ተቀበል አትናደድ ቶሎ

ምርቱ ተበጥሮ ሲለይ እንክርዳዱ

የሰራዊት አምላክ አይቀርም መፍረዱ

ቀና ደፋ ስትል ለሥራ ሥትሰጋ

ከፊትህ ቢደቀን ያልታሰበ አደጋ

በቀል የጌታ ነው ተቀበል በጸጋ

ልፋትህ ድካምህ ከንቱ ቢቀር መና

አይደለም ሽልማት ቢነፍግህ ምስጋና

ሳትለግም ሳታኮርፍ ሥራ ለህሊና

አፈጮሌ ቢገኝ ቀድሞ በምላሱ

ብዙም አትጨነቅ አታስብ ስለሱ

እውነትና ንጋት እያደር ሲጠራ

ላንተ ያለው አይቀር ተቀምጧል እንጀራ
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Sat Nov 20, 2010 10:50 am

ክብር ለአፈር!ሕይዎት ለታደገች ለሰው ልጆች ቤዛ

ምነው ይች ምድር እንዲህ ጠሯ ይብዛ

እስቲ እናዳምጥሽ ምድሪቱ መስክሪ

ማን ይሆን ዘብ ቆሞ ላንች ተቆርቋሪ

ውስጥሽ ተሰርስሮ ላይሽ ተቦርቡሮ

ውበትሽ ተገፎ ሲመስል አሻሮ

የቱ ነው ባላንጣሽ ቀንደኛ ጠላትሽ

ማነው ተጠያቂ ማነው ተወቃሽሽ

መንጥሮ መንጥሮ አርጎ ምድረ በዳ

ለመጭው ትውልድ ሲያስተላልፍ ዕዳ

በቦንብ በመትረየስ በፈንጅ እያረሰ

መቼ ተጠየቀ መቼ ተከሰሰ

በተፈጥሮ ሚዛን ባየር መዛባቱ

ወንዙ ከደረቀ ምንጭና ጅረቱ

ማነው ወንጄለኛ የማነው ጥፋቱ

የሚበላ ጠፍቶ እየከፋ ድርቁ

ህፃናት ጎልማሶች አዛውንት ካለቁ

ደመናው ባይዳምን ቢጠፋ ዝናቡ

ምንድነው መንስኤው ምንድነው ሰበቡ

በረኻው ተስፋፍቶ ቢበዛ ንዳዱ

ማነው ወንጄለኛ በማን ላይ ነው ፍርዱ

የዱር እንስሳቱ ካገር ቢሰደዱ

ሽሽቱን ቢመርጡ ቆመው ከሚነዱ

ቁጥራቸው ቢቀንስ ጉዳቱ አይሎ

ማነው የጠየቀ የት ደረሱ ብሎ

የፋብሪካው ዝቃጭ ቆሻሻ አይሙላ

አይበክል መሬቱን ከዛሬ በኋላ

እንገስግስ ወደፊት ይብቃ ማለት ዳዴ

ተራራ እና ሜዳው ይልበስ አረንጓዴ

ይገንባ እርከኑ ይሰራ ክትር

ዛፎች ይተከሉ ይብቀልበት ሳር

ትልቅ ዋጋ ይሰጥ ክብር ለሃገር
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Sun Nov 28, 2010 8:27 am

ስደት ባረብ ምድር !አይኔም አለቀሰ የልብን ስቃይ አይቶ

እኅኅኅ ብሎ ውስጡ ተንገላቶ

እንዴት ሊዘልቅ ነው ተብከንክኖ ከቶ

እርቆ እንዳልሄደ ባህርን ተሻግሮ

እብሮ እንዳልቆመ ከኔ ጋር ኖሮ

ሆዴ እንደ እሳት ጋየ በናፍቆት ተማሮ

ይህ ናፍቆት የሚሉት አገሩን ወረረ

በጥንድ በነጠላ ባንድ አርጎ እያሰረ

የተከበረው ህዝብ አበሻ ተዋርዷል

እድሉ ሆነና ምድረ አረብ ተሰዷል

አንተም አይዞህ በርታ እጣ ወጥቶልሀል

ካገርህ እርቀህ ይህው ተሰደሀል

መታመም ይኖራል መሞትም እንደዚያው

ከዚህም የከፋ ስላለ እምታየው

ከንግዲህ ሞተሀል ቀድመህ ተቀበለው

በኋላ እንዳታዝን ከዛሬው እወቀው

ፍፁም ሌላ አይደለም አረብ አረብ ነው

የያዝኩትን ዳቦ መብላት ልተው ሁሉን

ማስተዋል ልጀምር የነገው እጣየን

እምባዬ ወረደ በጥፍ በጥፍ ጎርፎ

ዛሬ ሁሉ አልቆ ለነገ ምን ተርፎ

ጉልበቴም ራደ መብረክረክ ጄመረ

ተስፋዬ ጠፋብኝ ውስጤ ሁሉ አረረ

አላሳየኝ አለ አይኔ መመልከት

ተደነባበረ ጥቁር ነሽ ጠፍቶበት

አእምሮየ ካደኝ የኔ እንዳልነበረ

በምትኩ ገባ እብደት ተጨመረ

ሩጥ ሩጥ አለኝ ቅደድ ልብስህን

አፈትልክ አፈትልክ አድን አንተነትክን

እንደ አረብ የለም ገርግሮ አስገርጋሪ

አንድ ሰው ብቻውን ለሽህ አደናጋሪ

ሀሳብ አደከመኝ መፍትሄው ቸገረኝ

እኔ እዚህ ቁጭ ብየ ሀሳብ አሻፈረኝ

ብቻ ሲያጨካክን ለሁልጊዜ ላይኖር

ሁሉ እያስቀመጠ ቀሪ የቂም ብድር

እባክህ ጌታየ በጥበብ በመላ

ዜጋ ተቸግሮ ወጣቱ ተሰዶ መከራ እንዳይበላ

አገሬ ኢትዮጵያን አርጋት የሀብት ክምር

ከንግዲህ እንዲቀር ስደት ባረብ ምድር
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Tue Nov 30, 2010 2:17 pm

ለታላቁ ሠው !
በአሉን የበላው አልጮህ ቢልም ጅቡ

ህያው ነው ታሪኩ አይረሳውም ህዝቡ

ዘላለም ይኖራል ከመቃብር በላይ

የቀይ ኮከብ ጥሪ እድሜ ለኦሮማይ

ማለፊያ ድርሰቱ የብዕር ጠብታ

ከአድማስ ባሻገር ጮራዋን አስፍታ

እንደ ንጋት ኮከብ ታበራለች ጎልታ

ለዎዳጅ ለዘመድ ጎረቤት ጓደኛ

መሪር ሀዘን ትቶ እውቁ ጋዜጠኛ

እንደወጣ ቀረ አልመጣም ዳግመኛ

ሰላም አሳጥተው እሱን ያሳደዱ

በሰፈሩት ቁና ይግቡ በገመዱ

የዘራውን ያጭድ የጁን ያግኝ ሁሉ

አሜን ሀሌሉያ ያንተ ነው በቀሉ

አልፋና ኦሜጋ ይፈጸማል ቃሉ

በስሙ ለምኘ ያውም በበአሉ

ሀጢያት ወንጄል ሳይኖር ለሰው ልጆች ብሎ

ህይዎት ቢታደግም ጌታችን ተሰቅሎ

የደራሲም ባህል አለው ተመሳስሎ

እራሱን ሰውቷል እውነት ትኑር ብሎ

የገሀዱን አለም ሀቅ እና ገጽታ

ከትቧል በብዕሩ በደሙ ጠብታ

ዋስ ነው ነገረፈጅ ለድሆች ጠበቃ

ግፍና በደልን ጭቆና ሰቆቃ

የለውም ደራሲ የሚሸከም ጫንቃ

እስራት እንግልት ግርፋት ህመሙ

መልካም አስተዳደር ፍትህ ለተጠሙ

እንደ ሻማ ቀልጦ ነዶ እንደ ጧፍ

ጮራ ፈንጣቂ ነው ካጥናፍ እስካጥናፍ

በወረቀት ከትቦ ከሽኖ ሰንቆ

የልብ ትርታውም ወደ ህዝቡ ዘልቆ

ያሳያል ደራሲ ችግሩን ፈልቅቆ

እከከኝ ልከክህ ደግፈኝ ልደግፍ

አያሻም በጭራሽ ያልሰራውን ሊዘርፍ

ባገር በወገን ሃብት ለግል ብልጽግና

ነቅቶ ይታገላል ለመጣል ሙስና

የናት ጡት ነካሹን ይዋጋል በብርቱ

ብዕሩ ናት ለሱ ጠመንጃ ጦር ቀስቱ

አያውቅም ማስመሰል ማለት እሽሩሩ

ውሃን ከምንጩ ነው ነገርን ከስሩ

የመሸበት ማደር እውነቱን ተናግሮ

አይወድም መልፈስፈስ ለሆድ ለከርስ አድሮ

አይፈራም በጭራሽ ዘጠኝ ሞት ቢነዳ

የታሪክ ተወቃሽ አይሆንም ባለእዳ

የተደበቀውን በዘዴ በመላ

ታወጣለች ብዕሩ ጎልጉላ ጎልጉላ

ለወገኑ ክብር ላገር ብልጽግና

ይሰርቃል ብዕሩ ለህዝብ ልዕልና

ይደርሳል በቶሎ ፍጹም ጊዜ ሳይፈጅ

የድገት ማነቆውን በብዕሩ ሊፈጅ

ግንባር ቀደም ሆኖ ራሱን ሰውቶ

ለወገኑ ታምኖ ለወገኑ ሞቶ

ደሙ ቢንቆረቆር ከውስጡ ተሟጦ

መጋፈጥ ነው እንጅ አይሸሽም ፈርጥጦ

ውጋት ነው ነቀርሳ ልክፍት ነው አባዜ

ሰንከፉ ካልወጣ ስቃይ ነው ሁልጊዜ

አይከደን አይኑ አይመጣ እንቅልፉ

ምጥ እና ነው እኅኅ የደራሲ ትርፉ

ጽንሱ ቢቀያየር ጽንሱ ቢለዋወጥ

እስከሚገላገል ዛሬም ምጥ ነገም ምጥ

ብዕር አስቀይማው ከብዕር ተጣልቶ

ይቅር ለግዜር ይላል በደልን እረስቶ

መከራው ቢበዛም እንዲያው ለነገሩ

ክንዱን ሳይንተራስ አትነጥፍም ብዕሩ
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ሾተል » Tue Nov 30, 2010 5:26 pm

መቼም አንዳንድ ጊዜ የነገሮች መገጣጠም ሲያጋጥሙን በጣም ግርም ይለናል::ሰሞኑን ስለበአሉ ግርማ ማወቅ አስፈለገንና ስለሱ የተነገሩና የተጻፉ ነገሮችን ሰርሰር ጎርጎር አድርገን ለማወቅ ያኽል ስንማስን ሰነበትንና ለምን ያወቅነውን ያላወቁ ካሉ አናሳውቅም ብለን ሳለ እንደሚታወቀው ዛሬ ራድዮ ፕሮግራም ስላለን ለዛሬ ስለበአሉ ያወቅነውን ለማካፈል ፕሮግራም ይዘን ሳለ እናንተ ገጣሚ ዳሞት ስለበአሉ ግርማ ጽፋችሁ ብናይ ወይ የነገር መገጣጠም አልንና ግርም አለን::

ይገርማል::

እና እናንተ ዳሞት ግጥማችሁን ለፕሮግራማችን ማጀብያ ብናነበው ምን ይመስላችሁዋል?ፕሮግራሙ ሊጀመር የቀረው ሰአት ቢኖር 1 ሰአት ከሰላሳ ሲሆን ልክ በቭየና የሰአት አቆጣጠርክ ከ 19 እስከ 20 ሰአት ድረስ ነው::

ፕሮግራማችንን በቀጥታ መስማት ከፈለጋችሁ ማለታችን ግጥማችሁን ስናነብና ስለበአሉ ግርማ ያለንን ዱቅ ዱብ ስናደርግ ለማዳመት ከፈለጋችሁ

www.o94.at/live

ብላችሁ ከገባችሁ በሁዋላ
LIVE MP3-STREAM unseres Sendungssignals

የሚለውን ተጫኑና አድምጡን::

ግጥማችሁን እንድናነብ እንደተፈቀደልን ተስፋ በማድረግ ነው::

በቅድሚያ ምስጋናችንን ልከናል::

ሾተል ነን
እሰይ ተመስጌን አምላኬ ለካስ በክብርነቴ እራሴን ሆኜ እኔነቴን ፈልጌ አግኝቼዋለሁ !?
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9647
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby ወለላዬ » Wed Dec 01, 2010 5:01 am

- በአሉማ ባይሞት

በአሉማ ባይሞት ቢኖር የሱ እስትንፋስ !
በጊዜው ያለውን ጠልቆ በመዳሰስ
ሁሉንም አጣርቶ በግልጽ አማርኛ
ባቀረበ ነበር በጻፈልን ለኛ
ያን ደፋር ጸሀፊ ባይወስደውማ ሞት
በግፍ ባይገደል ትንሽ ቢሰነብት

ባቀረበ ነበር ሌላ አዲስ ኦሮማይ
ፊት የቀነሰውን ድብቅ ሴራ እንድናይ
ሆኖም ትቶልናል ከአብራኩ ልጆች
የማንዘነጋቸው ልብ ወለድም ሰዎች
እነአበራ ወርቁ እነ ሀይለማሪያም
ኖረው ባናውቃቸው ባካል ባይታዩም
አዲስ አስተማሪው ያ ታፈሰ ብሩ
መስለው ይታያሉ ባገር የነበሩ
የቀይ ኮኮቦቹ ደርቤና ሂሩት
የአድማስ ባሻገርዋ የኮሜርሷ ሉሊት
የተረት ሰፈሩ ያ ደራሲው ሲራክ
ከሀሳብ አይጠፉም ይታወሳሉ ሰርክ
ስለዚህ በአሉ ቢኖርማ ባይሞት
የኦሮማይ ሰዎች በአጭር ባያስቀሩት
አውቦ አሳምሮ በሱ እይታ አንጻር
አዳዲስ ጽሁፎች ያቀርብልን ነበር
ወለላዬ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 403
Joined: Wed Jan 26, 2005 11:20 am
Location: united states

Postby ኦኑፈያሮ » Thu Dec 09, 2010 6:37 am

ፍርሃት በእንጉርጉሮ !


እንባዬ በል ውረድ ፊቴ ይሁን ጅረት

ውሃ በሆንኩ ነበር የተጸነስኩኝለት

በል እንባዬ ውረድ ፍሰስ በደረቴ

ተመልካች ነህና ቆማ ስታጣጥር ደራሽ አጥታ እናቴ

አንጄቴ ተቃጠል ብለህ እርር ኩምትር

የት ይገኛል ብለህ ከእናት በላይ ፍቅር

የታባህ ልታገኝ ከእናት ወዲያ ክብር

አንደበቴ ዝጋ ትንፋሽ አትናገር

ፈርተህ ዝም ብለሀል እማዬ ስትደፈር

ፈሪ ጮማ አይበላም ይባላል ተረቱ

ሠው ሠው አይባልም ካልሆነ ለናቱ

እንባዬ በል ፍሰስ ሆነህ መንታ መንታ

አልከፈልክም እና የናቴን ውለታ

አልመለስክም እና የናቴን ወሮታ

እናቴ አለቀሰች እጅግ ተንሰቅስቃ

ባህር ሆዷ ደርቆ ከሰው በታች ወድቃ

ያን ባህር ሆዷ ጄግኖችን ያፈራ ወንዶች የሞቱበት

ማተቧ ተቆርጦ ሆኖባት የሠው ቤት

አሻግራ እምታየው ሆኖባት ጎረቤት

እናቴ ተጎዳች ማህጸኗን ደክሟት

ጠላቷ ቀን ቆጥሮ ከጄርባዋ አጠቃት

እማዬን አጠቃት ጠላቷ ቀን ቆጥሮ

ሲያነክስ ቆይቶ በሆዱ ቂም ቋጥሮ

ይኽው ተሳካለት አምናና ዘንድሮ

እናቴ አለቀሰች እጅግ ተብከንክና

በልጅ ሳትታደል ወልዳ መካን ሆና

መካንነት መካን ወልዶ አለመሳም

ደርቆ መቅረት ይሻል ከማፍራት ሆዳም

ከጅብ ሆድ አምላኩ ግሳንግሱ ከርሳም

በገንዘብ ብደለል ይሁን አይደንቀንም

ድሮም ጅብ ሆድ እንጅ ክብር አይገባውም

ጥንትም ጅብ ከርስ እንጅ ወንድነት አያውቅም
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Thu Dec 09, 2010 7:44 am

ታዘቢኝ !


የዕድገትሽ ገች አሜከላ

ቀስፎ የያዘኝ አሸክላ

አሽቀንጥሬ ካልጣልኩት የጊዜ ጉዳይ ሆኖ እንጅ

ከሱ ጋር እየተያየሁ

እማማ ታዘቢኝ እታገላለሁ

የሙስና አራማጆች እንደጸር ቢያሳድዱኝ

ያለስም ስም ቢሰጡኝ ያለስራዬ ሊያጠምዱኝ

የትግሌን ወላፈን ላንቃ

ፈጽሞ አላቆምም በቃ

ምናባክ ቢሉኝ አፌን እንድዘጋ

እሽ አልልም እኔ እከፍላለሁ እንጅ ዋጋ

ከእናቴ ማህጸን ወጥቼ ካንቸ ማረፊያ እስክገባ

ወትሮም አልቀድም ይህን የታዘልኩበትን አንቀልባ

የድገትሽ ገች አሜከላ

የቆዬ ነቀርሳሽን አፈር ከድሜ ሳላበላ

ከምድረ ገጽ ሳላስወግደው

እኮ እንዴት ሆኘ ነው እማርፈው

ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል

ከንቱ ብሂሉም እነሱ ላይመለሱ ሊነቀል

እንዲባል ተለውጦ ያለፈው ሻጋታ ተረት

ባጭር ጊዜ ሳያስቆጥር ዘመናት

ያለችሎታ መረጃ ያለልምድ ሥራ ግብር

ባነስተኛ ወረቀት ቢጤ ሀብትሽ ሲመነዘር

ዘርና ቤት ተቆጥሮ ባምቻ በጋብቻ

በእከክልኝ ልከክልህ ተገንዞ በጥቅም ብቻ

የሚሆነውን ዝም ብዬ ማየት ከቻልኩኝ

ይህን ነቀርሳ ተጋፍጨ ካልታገልኩኝ

ታዘቢኝ እማማ የድገትሽን ገች አሜከላ

ቀዝፎ የያዘሽን ክፉ አሼክላ

አሽቀንጥሬ ካልጣልኩት

ላይመለስ ካልቀበርኩት

ታዘቢኝ እማማ ካቀፍኩት

ለመኖር ብዬ ከዋሼሁ

ካለፍኩት አይቸ እንዳላየሁ

ልማትሽ ተጨናግፎ ላላይ ላልሰማ ያንችን ስቃይ

እነሳለሁ በራሴ ምዬ ሌላ ሰውም አልጠብቅ አላይ

ትምህርት ጤና ጣቢያ ድልድይ እና የህጻናቱ መዋያ

ክሊኒክና አስፋልት የገጠር መንገድ የድገታችን መለያ

አንድነታችን ጠንክሮ በፍቅር ጀባ አምሮና ደምቆ

እናስወግደው በፍጥነት ሙስና ነውና የድገታችን ማነቆ

ደሀው ወገን ተርቦ እህል በገፍ ሲነጥቁ

ህዝብ ታሞ ፈውስ አጥቶ መድሃኒት አፍሰው ሲሰርቁ

ወንድሜ እዛ ሲሞት ዳስ እዚህ ሲቀለስ

ባስረሽ ምችው ድግስ ሻፓኝ ተደርድሮ ኬክ በሰይፍ ሲቆረስ

ጎረቤት በጠኔ ሞት ቀርቦት ሲያጣጥር

እዚህ ጮማ ቁርጡ ተርፎት የሚታደር

ለራስ ጥቅም ብዬ አንችን ከረሳሁኝ

አውሬ ልባል እንጅ ሠውም አይደለሁኝ

በሰበብ ባስባቡ መሰሌን ጠልቼ

ለራሴ ለብሸ ለራሴ በልቼ

ዬኔ ያልሆነ ወረት ላቤ ያልሆነውን

አንድ ቀን እንኳን ያልለፋሁበትን

ስዘርፍ ከኖርኩማ ያየሁትን ሁሉ

ላጠፋው ከወሰንኩ ለኔ ያላደሉ

በሀሰት ከስሼ ስልጣን ተንተርሼ

መሰሌን ከጎዳሁ ለራሴ ቆርሼ

ባሰተኛ ሰነድ ገንዘብ አጭበርብሬ

አብልጨ አባዝቸ ቀንሼ ደምሬ

ጥቅም ላልተገባው ልሰጥ ከቋመጥኩኝ

ማግኜት የሚገባው ምንም እንዳያገኝ

አድርጌ ከሰራሁ ሳይወቅሰኝ ሕሊና

ምንም ሠው አይደለሁ ባዶ ቤት ነኝ ወና
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Thu Dec 09, 2010 8:06 am

ከዚያች ዕለት ጀምሬ ሁልጊዜ የማስበው

እንግልትሽ አይደለም ባይምሮዬ የሚላወሰው

እርሀብሽም አይደለም አንጄት አንጄቴን የሚልስው

ይልቁንም አልጠፋ ያለው በልቤ ላይ የታተመው

ካባትሽ ከአብራሃም ጋር የተጋራሽው ታሪክ ነው

አብራሃም ልጁን እንዲያርድ ሲመጣለት ትዛዙ

እሽ ማለት አልከበደውም በቅጽበት ካራ መምዘዙ

ግን አልቻለም ወዲያው ማረድ ተባለ ሦስት ቀን ተጓዘ

የልጁን አይን አይን እያየ ውስጥ ውስጡን ተመዘመዘ

ልጁ በዚህ አባ ሲለው ያባት አንጄቱ ሲራራ

በዚያ ደግሞ አምላኩ በታላቅ ድምጽ ሲጣራ

በሁለት ገመድ ተወጥሮ ቃሉን እንዳይክድ ሲፈራ

በተሰጠውም ሦስት ቀናት አብራሀምን የገጠመው

በመርመጥመጥ የማይታለፍ የቃል የእምነት ፈተና ነው

ዛሬም በሰው ተመስሎ ጊዜ አንችን ሲፈትንሽ

ከማያልቅ ቀን ቀንሶ ሶስቱን ብቻ ሲያኖርልሽ

በዬት በኩል ሹክ ብላ ኢትዮጵያ አበራታችሽ

ልጅሽ ካሌ በዚህ በኩል እማማዬ ስትልሽ

በዚያ ደግሞ አዛውንት እናት አንድያ ልጅ ተይ ሲሉሽ

ያለተስፋ ስትቃትቺ ዙሪያውን ገደል ሲሆንብሽ

እንዴት ሆና በየት ደርሳ ኢትዮጵያ አጸናችሽ

እርግጥ እውነት ያጸናል እውነት የማይፋቅ ነውና

ጽናትሽ ጽናት ይሆናል ጠብቆናል ከፈተና

ቃል እምነትሽ ወህኒ ወርዶ ሥጋሽ ብቻ እሚፈታ

ከእውነትሽ ጋር ስትቆሚ ስትሆኝ ከራስሽ አለኝታ

ፈታኝሽ ተፈተነ ሊረታሽ ያለው ተረታ

የኔ ቢጤውም አውታታ በገዛ ፍራቱ የታሰረው

በእስራትሽ ተፈትቶ በንግልትሽ ነው የበረታው

አራያ መሆን እንዲህ ነው እንዲህ ነው እራስን መምራት

አሰትን በውነት ገድሎ ጥላቻን በፍቅር መርታት

እንዲህ ነው እራስን መምራት

ከማደንቀው ሠው
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Thu Dec 09, 2010 8:13 am

ቢወራ ቢሰላ ቢደመር ቢቆለል

የሒሳብ ስሌቱ ለእኛ ምን ጠቀመን

ልማድ ሆኖባቸው ወሬ ወራሽነት

ይኖራል ይሉናል ህዝቡ በነጻነት

አየር ላይ ነው ያለው ነጻነት ተንሳፎ

አልወረደም ገና አጣብቂኙን አልፎ

ከወሬ ያለፈ የሚታይ ሳይኖር

ሠው የለም ይላሉ ከኛ ሌላ በቀር

እራሳቸው ክበው እነሱ ለናዱት

ምንድነው ትርጉሙ ምንድነው ነጻነት

ወይ ኤርትራ
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

Postby ኦኑፈያሮ » Thu Dec 09, 2010 4:37 pm

መራሄ መንግስቱ !አንድ ጊዜ ባገሬ ውይይት ሲደረግ

መመሪያ ተሰጠ ሁሉም እንዲዘጋጅ

ባለስልጣኖቹም ተሰበሰቡና

ጠቅላይ ሚኒስተሩ ሰጧቸው መመሪያ

ስሙኝ ሚኒስትሮች እስቲ እንነጋገር

ስለጉብኝቱ ምናም እንፍጠር

በጆሯችን ሰምተን እንደተረዳነው

በድህነት ሆኗል እኛ የታወቅነው

ስለዚህ መዘየድ መላ ማፈላለግ

ዘዴው ከተገኘ ይቀራል ስማችን

ድህነት የሆነው የኛ መለያችን

አሉና አንጋጠጡ ጠቅላይ ሚኒስተሩ

ፈልገው ለማሰብ የሚሉትን ሁሉ

ከዚያም ቆያየና ጸጥታ ሲተካ

መላ ለመጠቆም አንዱ እጁን አወጣ

ጥሩ ጥሩ ቃላት እየተመረጡ

ሪፖርት ይደረግ ይቅር መጨነቁ

በማለት ሐሳቡን ሰጠ ተናገረ

ከሀሜት ያድናል ያለው ጠቆመ

ሌላ እጁን አወጣ እየተገረመ

እንዲህም ተናግሮ ያንን ተቃወመ

እውነቱን መናገር ይሻል ነበር እንጅ

በሽታን መደበቅ እንደምን ይበጅ

እርሃብ ቢደበቅ መልክ ይመሰክራል

ካንገትም ቢያነጥፉት ወደ ልብ አይገባም

ይልቅስ ይሻላል ውነቱን ሳንደብቅ

ሁሉን አሳይተን እርዳታን እንጠይቅ

ብሎ እንደጨረሰ ሦሥተኛው ጄመረ

ይጠቅማል ያለውን እንዲህ ተናገረ

በገሃድ ለሚታይ የህዝባችን ኑሮ

መላ ማፈላለግ አልፎበታል ድሮ

ለራት የማይበቃ እርዳታም ቢጠየቅ

መፍትሄ አይሆንም ይህንን እንወቅ

ተመዝግበው ያሉ በሌላው የሌሉ

በኢትዮጵያ ምድር በገፍ ይገኛሉ

ከሀረር ተነስተን ወለጋ ለመድረስ

ለምለም ነው ሃገሩ መንፈስን የሚያድስ

በተለይ ከቡናው ፉት እማ ካላችሁ

የከፋ ታሪክን በደንብ ታውቃላችሁ

ጥንት ድሮ ገና ቡና ሳይታወቅ

ያውሮፓ ነጋዴ ከፋን ሲተዋወቅ

ከፋ እላለሁ ብሎ ከፋ በማለቱ

መጠሪያው ያው ሆነ አሁን በየቤቱ

እናም እንዳትረሱ ከፋ ኮፊነቱን

ነገሩ ለአለም ጥንታዊ ስማችን

አሉ ጨማመሩ ጠቅላይ ሚኒስተሩ

በጎሪጥ እያዩ ታዛቢውን ሁሉ

እንግዳው ባንክሮ ሁሉን አዳመጡ

ከዚያም ቃላቸውን እንዲህ ብለው ሰጡ

እንዲህ በብዛት ሃብትማ ካላችሁ

ለኛም ለሌሎችም መርዳት አለባችሁ

በማለት ነገሩን ትንሽ ጨማመሩ

በሰሙና ባዩት እየተጉረመረሙ

ከዚያ ወደ ግብዣው ተነስተው አመሩ

እስቲ እንጠያየቅ እንዲያው ለነገሩ

እናንተ ብትሆኑ ጠቅላይ ሚኒስተሩ

ምን ይሆን መልሳችሁ ምን ትመሰክሩ
ኦኑፈያሮ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 170
Joined: Thu Aug 04, 2005 1:52 pm

ነፋስ ና ሙድ

Postby ዋኖስ » Sat Dec 18, 2010 5:23 pm

ነፋስና ሙድ


ነፋስ መዉጫ ላይ የተቀመጠች ሻማ፣

ሕያዉ-ፍቅር፤ እምነት ፅናት-የተጠማ፣

እድለ-ቢስ ሰዉ አንድ ናቸው፤

ተዉት ሰዉ አይስማ፤ ያሳዝናል ሕይወታቸው።

ሁለቱም “አይለፍላችሁ!” እንደተባሉ ሁሉ፣

ብልጭ-ድርግም! ብልጭ-ድርግም! ይላሉ፣

የነፋስና የሰዉ “ሙድን” እያጠሉ።

ዳሞት ከዳሞት
ዋኖስ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1552
Joined: Tue Nov 16, 2004 2:39 pm
Location: Mars

አካሌ

Postby ዋኖስ » Sat Dec 18, 2010 5:30 pm

የቅማል-ስደት፤ ከራስ ወርዶ አንገት፤

አካሌ!

ሔደሽ ላትሄጅ፤ ላትርቂ ከቤቴ፣

ላትጠይኝ፤ ላልጠላሽ፣ ላትወጭ ከአንጀቴ፣

ላትረሽኝ፤ ላልረሳሽ፤ ላይላላ ማተብሽ፤ ላይቀንስ እምነቴ፣

ያለኔ መኖሩን ላይለምደዉ አዕምሮሽ፤ ላይቀበል ዉስጤ፣

አዋጅ አስጎስሞ ገላችን ቃል-ገብቶ፤ አፋችን ከፈራ፣

ሽሽት መሰለብሽ ከራስ-ወርዶ-አንገት ላይ የቅማልን ሥራ።

ስለዚሕ ሔዋን ሆይ፤ ስሚኝማ አካሌ፤ ሥደት ለአንችም ለኔ፣

ላይመች ለአጥንትሽ፤ ላይደላዉ ለጎኔ፣

ጣት-መቀሠር ይቅር፤ መፍትሔም አያመጣ፤ አይሆንም ብያኔ።

ፅናት፤ እምነ-በረድ ዘልቆ እንደሚገባ ሆድሽ ቢያዉቀዉ ኖሮ፣

“ስንት የፈጀ-ትዳር!” በአሽሙር-በአሉቧልታ ባልቀረ ተሠብሮ።

ሠማሽኝ? ፅኝ!

ዳሞት ከዳሞት
ዋኖስ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1552
Joined: Tue Nov 16, 2004 2:39 pm
Location: Mars

PreviousNext

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 2 guests