ማርቆሶች ተሰብሰቡ

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 10:57 am

እኔም ስለተሸካሚው አየለ ሳይሆን፣ ስለተናጋሪው አየለ ነው የማወጋችሁ፡፡ የህዝቡን ከሰል ሳይሆን የህዝቡን በደል በትክሻው ይዞ ሲመላለስና ወደተፈለገው ቦታ ሲያደርስ ስለኖረው “ተናጋሪው አየለ” ነው የማጫውታችሁ። አየለ ማን ነበረ? እሱ በደል አንገብግቦት ውስጥ አንጀቱ ያረረ፣ ‘አቤት’ ይልበት ወኔም አንደበትም ያልነበረው የደ/ማርቆስ ህዝብ ‘አፍ’ ነበረ፡፡ የሹማምንትንና የባለጠጐችን ግፍ በየጓዳው ውስጥ ውስጡን ማጉተምተም እንጂ፣ ‘አቤት’ ብሎ አደባባይ ሊወጣ ያልደፈረን ተበዳይ ህዝብ መራራ ሀቅ፣ በበዳይ ሹማምንት ፊት ቆሞ በድፍረት ሲናገር የኖረ የአገር ‘አንደበት’ ነበረ፡፡ በቀልድ እየቀመመ፣ በፌዝ እያስታመመ፣ በስላቅ እያከመ በሚተነፍሰው የታፈነ የህዝቡ መራራ እውነት የሚታወቅ፣ የህዝብ ሃቅ፣ የህዝብ ሳቅ ነበረ አየለ፡፡ የከንቲባው ቦርሳ በደርግ መንግስት የመጨረሻዎቹ አመታት የደብረ ማርቆስ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ‘ጓድ እንትና’፣ እጅግ የሚፈሩና የሚከበሩ ባለስልጣን ነበሩ፡፡

ግርማ ሞገሳቸው ከሩቅ የሚያስፈራው ‘ጓድ እንትና’ የከተማዋን መሪ በሁለት እጆቻቸው ጨብጠው፣ ህዝቡን ባሻቸው አቅጣጫ የመምራት ፍፁም ስልጣን ነበራቸው ይባላል፡፡ ይሄም ብቻ አይደለም። በየጐዳ ጐድጓዳው ስለ ከንቲባው የሚወራውና የሚባለው ነገር ብዙ ነው፡፡ ህዝቡን ያለ አግባብ ስለመበደላቸው፣ ስለ ጉቦኛነታቸው፣ የህዝቡን ገንዘብ ያለ አግባብ በግል ካዝናቸው ስለማጨቃቸው … ብዙ ብዙ ነገር ይወራባቸዋል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን ወሬውም ሃሜቱም ውስጥ ውስጡን ነው፡፡ እኒህ የታፈሩና የተፈሩ ከንቲባ ‘እንዲህ አደረጉ’ ብሎ አፍ አውጥቶ መናገር፣ በገዛ እጅ በራስ ላይ መከራ መጥራት በሆነባት፣ አዋሻኪና አሳባቂ ጆሮ ጠቢ በሞላባት ከተማ፣ የልቡን ለመናገር የደፈረ አየለ ብቻ ነበረ፡፡ የአየለን ድፍረት የተለየ የሚያደርገው፣ በአደባባይ ስለ ከንቲባው አጉል ነገር መናገሩ ሳይሆን፣ ይሄን አጉል ነገር ለራሳቸው ለከንቲባው መናገሩ ነው፡፡ አንድ ዕለት ‘ጓድ እንትና’ ስራ ውለው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ፣ ከአየለ ጋር መንገድ ላይ ይገጣጠማሉ፡፡ ከንቲባው በእጃቸው ሳምሶናይት ቦርሳ ይዘው እንዳላዩ ሊያልፉት ሲሉ ታዲያ፣ አየለ ሆዬ ቆም ብሎ በፈገግታ ይመለከታቸዋል፡፡ “ደህና ዋሉ ጓድ እንትና?” በማለትም ሰላምታ ይሰጣቸዋል፡፡

“ሰላም ነህ?” ብለውት ጉዟቸውን ሊቀጥሉ ይዘጋጃሉ፡፡ አየለ ከንቲባው ወደያዙት ቦርሳ እያየ በትሁት አንደበት መናገሩን ቀጠለ፡፡ “እሷን ነገር ላግዝዎት ይሆን?” “አይ! … ደርሻለሁ … አመሰግናለሁ” ከንቲባው ነገሩን በአጭር ቋጭተው ከዚህ ነገረኛ ሰው ለመምለጥ ፈልገዋል፡፡ እሱ ታዲያ መች በዋዛ የሚለቃቸው ሆነ “ኧረ ግዴለም ትንሽ እንኳን ልርዳዎት?... የህዝብ ገንዘብ እኮ ይከብዳል” ብሏቸው እርፍ፡፡ ከንቲባው ምንም አላሉም፡፡ ለነገሩ ምንስ ማለት ይችላሉ? ሽሙጥ በሽጉጥ አይመለስ! ‘ጓድ እንትና’ ሰምተው እንዳልሰሙ ወደ ቤታቸው ቢገቡም፣ ወሬው ግን ሳይውል ሳያድር በየመንደሩ ተሰማ፡፡
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 11:08 am

አየለ እንዲህ እንደ ከንቲባው የማይደፈሩ የከተማዋ ጉቦኛ ሹማምንትና “ኪራይ ሰብሳቢ” ባለጠጐችን በሽሙጥና በነገር ወጋ ማድረግ ልማዱ ነው፡፡ በአብዛኛው በሽሙጥ እና በስላቅ ዘወርወር አድርጐ የልቡን የመናገር ልማድ የነበረው አየለ፣ አንዳንዴ ግን በየጓዳ ጐድጓዳው የተደበቀውን ሐሜት በአደባባይ ፍርጥርጥ አድርጐ ለመናገርም አያመነታም፡፡ እርግጥ እንዲህም ሆኖ ደረቅ ዘለፋ ብሎ ነገር አይነካካውም፡፡ “ሰርቋል”፣ “በድሏል”፣ “ዘሙቷል”፣ “አታላለች” አይልም አየለ፡፡ ባለ ሆቴሉ ጋሽ እንትና፣ ሆቴሉን ከመክፈታቸው ከጥቂት አመታት በፊት ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ የሚገፉ የትምህርት ቢሮ ተቀጣሪ ተራ የመንግስት ሰራተኛ ነበሩ፡፡ ድንገት የመንግስት ስራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው ባለሁለት ፎቅ ህንፃ የገነቡትንና የሚያምር ሆቴል የከፈቱትን ጋሽ እንትናን ህዝቡ ክፉኛ ያማቸዋል፡፡ አንድ ምሽት አየለ ወደ ሆቴሉ ገብቶ ለመዝናናት ሲሞክር፣ ጋሽ እንትና በዘበኛ ያሳግዱታል፡፡ “ይተውኝ እንጂ ጋሽ እንትና? ምናለበት እኔስ እንደሌላው ሰው ከፍዬ ብበላ ብጠጣ?” በማለት በትህትና ጠየቀ አየለ፡፡ “አይሆንም…ከዛሬ ጀምሮ እዚህ ሆቴል አትገባም ብያለሁ አትገባም!” ፈርጠም አሉ ጋሽ እንትና፡፡ “ምን ባጠፋሁ ጋሽዬ?” መልሶ ጠየቀ፡፡ “እየተሳደብክ አስቸግረሃል…ባንተ ምክንያት ደንበኞቼ እንዲርቁኝ አልፈልግም …ከአሁን በኋላ ሆቴሌ ውስጥ እየገባህ እንደፈለግህ መዘባረቅ አትችልም” ጋሽ እንትና ማምረራቸውን ገለፁ፡፡

አየለም የበለጠ ይምረራቸው ብሎ ቀጠለ፡፡ “እስቲ ይንገሩኝ ጋሽዬ…ምን ብዬ ዘባረቅኩ?...”የትምህርት ቢሮን ገንዘብ ዘርፈው ፎቅ ሰሩ” አልኩ? እንደማንም ሃሜተኛ “ከመንግስት በዘረፉት ብር ሆቴል ከፈቱ” ብዬ ተናገርኩ?...እስቲ ይንገሩኝ ምን ብዬ ዘባረቅኩ?” አለ፡፡ ከጋሽ እንትና አንደበት ቀድሞ መልስ የሰጠው የዘበኛው ዱላ ነበር፡፡ የደብረ ማርቆስ ህዝብ በአጉል ነገር ውስጥ ውስጡን የሚያማቸው እንደ ጋሼ እንትና ያሉ ባለጠጐች፣ የአየለን ምላስ እንደ ጦር ይፈሩታል፡፡ የሚያሳማ ጉዳይ ያለባቸው ሁሉ ‘እንዳያዋርደን’ በሚል ስጋት በቻሉት መንገድ ሁሉ አየለን ላለማስቀየምና ወዳጅ ለማድረግ ይጥራሉ፡፡ “አየለ … ና … እንጂ ሻይ ጠጣ” “እስቲ በቁምህ አንድ ሁለት ብለህ ሂድ” “እንካ እስኪ ይቺን … ባይሆን ለጠላ ትሆንሃለች” እንዲህና እንዲያ ባዩ ብዙ ነው፡፡
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 11:14 am

አንድ ዕለት ታዲያ… ጓደኛሞች የሆኑ ሰዎች አንድ ሆቴል በረንዳ ላይ ሰብሰብ ብለው ሻይ ቡና እያሉ ሲጨዋወቱ አየለን አልፎ ሲሄድ በቅርብ ርቀት ያዩታል፡፡ ከመካከላቸው አንዱ (የሚያሳማ ነገር ያለበት ሳይሆን አይቀርም) ጮክ ብሎ ወደ አየለ እያየ ይጣራል፡፡ “አየለ … ሰማህ ወይ አየለ?” “አቤት” አየለ ቆም ብሎ ወደ ሰዎቹ እያየ መልስ ሰጠ፡፡ “ና እንጂ የሆነ ነገር ብለህ ሂድ?” አለ ሰውዬው፡፡ ልጋብዝህ ማለቱ ነው፡፡ “አይ! … የለም ይቅርብኝ!” አለ አየለ - ትክሻውን በእምቢታ እየነቀነቀ፡፡ “አንተ ደ’ሞ … ሰው ሲለምንህ’ማ እሺ በል” አለ ሌላኛው፣ ‘አልጋበዝከኝም’ ተብሎ እንዳይታማ የፈራ ሰውዬ ወደ አየለ እያየ በልመና፡፡ “ኧረ እኔ እቴ!... የለም…ተውኝ ልሂድ!” ድርቅ አለ አየለ፡፡ “ምናለበት ገባ ብለህ አንድ ሁለት ብትል?...” ቀጠለ ሌላኛው “የለም … አልገባም!... እህል ቀምሻለሁ!” አለ አየለ ሆቴሉን የጐሪጥ እያየ፡፡ የሆቴሉ ባለቤት “ታቦትና የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳት” ዘርፈው በመሸጥ በህገ ወጥ መንገድ ሃብት ያፈሩ ናቸው’ በሚል በከተማዋ ህዝብ ክፉኛ የሚታሙ ናቸው (እህል ተቀምሶ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደማይገባ ልብ ይሏል)፡፡ በታቦት ገንዘብ የተሰራ ሆቴል፣ ‘ቤተክርስቲያን ነው’ ማለቱ ነው አየለ፡፡
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 11:21 am

“ወያኔ” እንደገባ “አየለ ጀምብ እግር” በሽሙጥ ጐንተል ከሚያደርጋቸው ሰዎች ከግልምጫ እስከ ጡጫ የሚደርስ ምላሽ ይሰነዘርበታል፡፡ እሱ ግን ይሄን ሁሉ መአት የሚመክትበትና ከጥቃት የሚያመልጥበት መላው፣ አሁንም ምላሱ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደብረ ማርቆስን የተቆጣጠረ ሰሞን እንዲህ ሆነ፡፡ አንድ ምሽት … አየለ ጠላ ቤት ውስጥ ቁጭ ብሎ እየቀመቀመ እያለ ከአንድ ወጣት ጋር ይጋጫል፡፡ ወጣቱ አየለን ለመደባደብ እየተገለገለ ‘ያዙኝ ልቀቁኝ’ ይላል፡፡ አየለ ግን ጠላውን እየደጋገመ ‘ኧረ እዲያ እቴ…’ እያለ በዚያች ደም የምታፈላ አብሻቂ ቅላፄው በጠበኛው ላይ ያሾፋል፡፡ የወጣቱ ፉከራም እያየለ ይመጣል፡፡ “አንተ ግንድ እግር! ገላጋይ አለ ብለህ ነው አይደል የምትቀባጥረው? … ወንድ ከሆንክ ውጭ እንወጣና ይለይልን” እያለ በንዴት ይንቀጠቀጣል - ወጣቱ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ጠጪው ሒሳቡን ከፍሎ ወደእየቤቱ ይሄዳል፡፡ ገላጋይ ይጠፋል፡፡ ወጣቱም ከጠላ ቤቱ በመውጣት ደጃፍ ላይ ቆሞ አየለን አፈር ድሜ ለማስገባት ይጠባበቃል፡፡ ባለ ጠላ ቤቷ ቤታቸውን ለመዝጋት ሲዘጋጁ፣ መቼም ባመሸበት አያድርምና በስተመጨረሻ አየለም ከጠላ ቤቱ ይወጣል፡፡ ወጣቱ ከጠላ ቤቱ በር ራቅ ብሎ ቆሞ ለድብድብ ሲዘጋጅ ያየዋል፡፡ አለፍ ብሎ ደግሞ ታጣፊ ክላሽ ያነገቱ “ወያኔዎች” ሮንድ እየጠበቁ ይመለከታል፡፡ ወጣቱ በንዴት እየጮኸ መዳፎቹን ለቦክስ አዘጋጅቶ ወደ አየለ ሲጠጋ ያዩት ሮንዶች፣ ክላሻቸውን አንቀጫቀጩና ወደ እነ አየለ ተንደረደሩ፡፡ “ቁም እንዳትንቀሳቀስ!...የምን ጭቅጭቅ ነው?” ጠየቀ አንደኛው ባለ ክላሽ፡፡ አየለ ወደ ወጣቱ እየጠቆመ ፈጣን ምላሽ ሰጠ፡፡ “ኧረ እኔ እንጃ እቴ!... ዝም ብሎ ይጨቀጭቀኛል!... እኔስ እሚለውም አልገባኝ፣ እስቲ እንግዲህ እናንተ ጠይቁት! … ‘መንጌ፣ አንተ ትሻለናለህ” ይላል!... ‘የማንም ጨብራራ መጫወቻ ሆነን ቀረን’ ይላል! …‘በአህያ ነው የመጡት’ ይላል … እነማንን እንደሆን እንጃ … እስቲ ጠይቁት” እያለ ቀጠለ አየለ፡፡ “እደባደባለሁ” እያለ ሲገለገል የነበረው ወጣት በክላሽ ሰደፍ እየተደቃ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወሰደ፡፡ አየለም ወደ ቤቱ!
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 11:27 am

“አየለ ጀምብ እግር” በነገር ወጋ እያደረገ ያስቀየማቸው አንዳንዶች፣ “አፉ ባለጌ ነው” ይሉታል፡፡ እርግጥ አየለ ተሳዳቢ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይሄም ሆኖ ግን “ተሳደበ” ቢባል እንኳን ልብ የሚያቆስል ሽሙጥ እንጂ፣ የብልግና ቃል እምብዛም ከአፉ ሲወጣ አይደመጥም፡፡ ይልቁንም ህፃን አዋቂው ወደ አየለ የሚወረውረው የብልግና ቃል ይበልጣል፡፡ የጤና ችግሩ መጠሪያው ሆኖ “አየለ ጀምብ እግር” ሲባል ምን እንደሚሰማው መገመት አያዳግትም፡፡ አንድ ወጣት ነው አሉ፡፡ ከሰል ተሸክሞ የሚጓዘውን አየለን ከበስተኋላው እየተከተለ በግጥም ይወርፈዋል፡፡ “ፍየል በግርግር አየለ ጀምብ እግር” እያለ፡፡ አየለ መልስ ሳይሰጥ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ወጣቱ ግን አሁንም መሳደቡን አላቆመም፡፡ “አየለ ወሸላ (ይቅርታ)” ይለዋል ጮክ ብሎ፡፡ ስድቡ ከተሸከመው ከሰል በላይ የከበደው አየለ፣ ተሳዳቢውን ወጣት ዞር ብሎ በንቀት እየተመለከተ የመልስ ምት ለመስጠት ተዘጋጀ፡፡ “አየለ ወሸላ!” ደገመ ወጣቱ፡፡ “አይ!...የሰው ነገር!...ያቺ እናትህ ይሄንንም ሚስጥር ብላ ነገረችህ?!” አለ አየለ፡፡ እንዲህ ነው አየለ፡፡ እንዲህ ያለውን አይን ያወጣ ዘለፋ በሰምለበስ ምላሽ ነው የሚመክተው፡፡


ምንም እንኳን ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት አየለ የሚተዳደረው በሸክም ቢሆንም፣ ከሌሎች ተሸካሚዎች በተለየ እንዲታወቅና ተፈላጊ እንዲሆን ያደረገው ጠንካራ ጉልበቱ ሳይሆን ጠንካራ አንደበቱ ነበር፡፡ በስላቅ እንዳይዳብሳቸው ሰግተው የሚሸሹት የመኖራቸውን ያህል፣ በሳቅ እንዲያፈርሳቸው ሽተው በየሄደበት የሚከተሉት ብዙ ነበሩ፡፡ የአየለን ንግግር ለመስማት የሚጓጉና ዱካውን ተከትለው የሚያፈላልጉት ብዙዎች ነበሩ፡፡ ‘አየለ አለበት’ የተባለ ጠላ ቤት፣ ከአፍ እስከ ገደፉ ነበር የሚሞላው፡፡ ይህን ስለሚያውቁ ነው ጠላ ጠማቂ ሴቶች አየለን ሳይነጋ የሚያፈላልጉትና እንጀራ በአዋዜ ቁርሱን አብልተው ዘመራ ጠላ ሲያስኮመኩሙት የሚውሉት፡፡ ታዲያ በነፃ ነው፡፡ ሲጠጣ ውሎ ሲጠጣ ቢያድር ‘ሒሳብ’ ብሎ የሚጠይቀው የለም፡፡ ለእሱ የሚቀዳው የነፃ ጠላ፣ እሱን ተከትሎ ሳቅ ፍለጋ ወደ ጠላ ቤቱ ለሚጐርፈው ጠጪ የተከፈለ የማስታወቂያ ወጪ ነው፡፡ በጠላ ጠማቂዋ ስፖንሰርነት በነፃ ሲጠጣ ስለሚውል ከጠጪዎች የሚያገኘው ግብዣ በቀጥታ ወደ ኪሱ የሚገባ የዕለት ገቢው ይሆናል፡፡ በዝሆኔ በሽታ የተጠቁ ሁለት እግሮቹ፣ ችግሮቹ ሳይሆን መጠሪያዎቹ ሆነው ልጅ አዋቂው “አየለ ጀምብ እግር” እያለ ነው የሚጠራው፡፡

አየለ ግን በእግሮቹ ሲሳለቅ እንጂ ሲሳቀቅ አይታይም። ሲጠጣ ውሎ ወደ ቤቱ እየተጓዘ ነው፡፡ ሚዛኑን ስቶ መንገዳገድና እግሮቹም እርስበርስ መጋጨት ጀምረዋል፡፡ አየለ እንደምንም ቆም ብሎ እግሮቹን እያየ በግርምት ተናገረ፡፡ “እኔ'ኮ የሚገርመኝ…ምን ሆንን ብላችሁ ነው የምትጋጩት?...የማበላችሁ እኔ!...የማጠጣችሁ እኔ!...ምናለ ተስማምታችሁ ብትኖሩ?!” በማለት፡፡ ከትላልቅ እግሮቹ ጋር በተያያዘ የነበረውን ሌላ ገጠመኝ ላክልላችሁ፡፡ አንድ ምሽት ጨለማን ተገን አድርጐ ወደ ሴተኛ አዳሪ ጐራ ይላል አሉ፡፡ መብራት ስላልነበር ሴተኛ አዳሪዋና አየለ ጨለማ ውስጥ ነበር ስለ ጉዳዩ ተነጋግረው የተስማሙት፡፡ ድርድሩ ተጠናቅቆ አየለ ቀደም ብሎ አልጋው ውስጥ ገብቶ ሴተኛ አዳሪዋን መጠበቅ ጀመረ፡፡ ጥቂት ቆይቶ እሷም ጣጣዋን ጨርሳ መጣችና ብርድልብሱን ከፍታ ከጐኑ ተኛች፡፡ ነገሩ ከመጀመሩ በፊት ግን፣ ሴተኛ አዳሪዋ ከግርጌዋ የሆነ ከበድ ያለ ነገር ሲጫናት ተሰማት፡፡ ደንገጥ ብላም አማተበች፡፡ “ኧረ የምን ጉድ ነው፣ አልጋው ስር የተጋደመው አንቱዬ?” አለች ሴተኛ አዳሪዋ በእግሮቿ የከበዳትን ነገር ለመሸሽ እግሮቿን እያጣጠፈች፡፡ ነገሩ የገባው አየለ ፈጥኖ መለሰላት፡፡ “አይዞሽ አትደንግጭ!...ጫማዬን ሳላወልቅ ተኝቼ ነው!” ወደማደሪያው ያቀናል - ደ'ሞ በራሱ እየቀለደ፡፡
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 11:34 am

ኢህአዴግ ደ/ማርቆስ መግባቱን ተከትሎ … ከዚህ በፊት የጠቀስኳቸውና አየለ በነገር ወጋ ያደረጋቸው የደርግ ባለስልጣን (የደ/ማርቆስ ከንቲባ) እንደሌሎች ኢሰፓዎች ሁሉ ተይዘው ወደ እስር ቤት ገቡ፡፡ ኢህአዴግ ከንቲባውን ያሰራቸው በስልጣን ዘመናቸው በሰሩት ግፍ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ አየለን ያሰረበትን ምክንያት ግን የሚያውቅ ያለ አይመስለኝም፡፡ የሆነው ሆኖ በአንድ ወቅት ከንቲባውና አየለ እስር ቤት ተገናኙ፡፡ አንድ ዕለት ታዲያ እስረኞች በተወሰነ ሰአት በሰልፍ ወደ መፀዳጃ ቤት ሲወሰዱ አየለና ከንቲባው በአጋጣሚ ጐን ለጐን ይቀመጣሉ፡፡ አየለ ከከንቲባው ጐን ቁጭ ብሎ እየተፀዳዳ በዚያች አሽሟጣጭ ቅላፄው እንዲህ አለ፡፡ “ወይ ጉድ እናንተዬ!...ወያኔ እመጣ ብሎ፣ እኔና ጋሼ እንተናም አብረን ያልበላነውን አብረን እናስወጣው ጀመር?!”


የቀልድ ህይወት ፣ የምር ሞት! ተረበኛው፣ ቀልደኛው፣ ዋዘኛው፣ ፌዘኛው አየለ በ1980ዎቹ መጨረሻ አንድ ማለዳ ከመንገድ ዳር ሞቶ ተገኘ፡፡ ሲጠጣ አምሽቶ በስካር ናውዞ ወደ ማደሪያው በመጓዝ ላይ እያለ የጣለው ሃይለኛ ዝናብ ክፉኛ ደብድቦት፣ ቱቦ ስር ወድቆ በላዩ ላይ ጐርፍ ሲሄድበት አድሮ ጧት ላይ አስከሬኑ ደለል ሰርቶ ታየ።

የአየለ ሞት በመላ ደብረ ማርቆስ ተሰማ። ይሄን ተከትሎ በከተማዋ የሚታወቁ በርካታ ባለሃብቶች በተለያዩ ጊዜያት ከአየለ የተቀበሉትን አደራ ይዘው ወጡ፡፡ “እኔ ጋ 2 ሺህ ብር አለው” “ይሄው…1ሺህ 200 ብር” “ሶስት መቶ ብሩ ይሄውላችሁ” የሚለው የባለሃብቶች ያልተጠበቀ ንግግር ተደመጠ፡፡ አየለ በኑሮው እንጂ በሞቱ ቀልድ እንደማያውቅ የታወቀው በዚህ ጊዜ ነው፡፡ በህይወት እያለ ስለ ቀብሩ እንጂ ስለ ኑሮው አይጨነቅም ነበር። በጉልበቱም በአንደበቱም የሚያገኘውን ገንዘብ እያጠራቀመ፣ ለባለሃብቶች በአደራ ይሰጥ ነበር፡፡ “መቼም መሞቴ አይቀርም… ማስቸገር አልፈልግም። እኔን ለመቅበርም የከተማው ህዝብ መጉላላት የለበትም፡፡ ባይሆን ለቀብሬ እንኳን ራሴን ልቻል እስኪ እቺን ብር አስቀምጡልኝማ” ከሚል ቀልድ የሚመስል የምር አደራ ጋር፡፡ አየለ እንደተመኘውም “ራሱን ችሎ” ተቀበረ፡፡ የደብረ ማርቆስ ህዝብ አስከሬኑን ወደ መቃብሩ የሸኘው በመንታ እንባ ነው፡፡ ለቀልደኛ ህይወት እና ለምር ሞት!
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ገልብጤ » Wed Jun 05, 2013 2:17 pm

ሙዝ እግር በአሪፉ ትጽፋለህ ለካስ
ኧረ እኔ እቴ !... የለም…ተውኝ ልሂድ !” ድርቅ አለ አየለ፡፡ “ምናለበት ገባ ብለህ አንድ ሁለት ብትል ?...” ቀጠለ ሌላኛው “የለም … አልገባም !... እህል ቀምሻለሁ !” አለ
አየለ ሆቴሉን የጐሪጥ እያየ፡፡ የሆቴሉ ባለቤት “ታቦትና የቤተ ክርስቲያን ንዋየ ቅዱሳት” ዘርፈው በመሸጥ በህገ ወጥ መንገድ ሃብት ያፈሩ ናቸው’ በሚል በከተማዋ ህዝብ ክፉኛ የሚታሙ ናቸው (እህል ተቀምሶ ቤተክርስቲያን ውስጥ እንደማይገባ ልብ ይሏል )፡፡ በታቦት ገንዘብ የተሰራ ሆቴል፣ ‘ቤተክርስቲያን ነው’ ማለቱ ነው አየለ፡፡

:lol: :lol: :lol: :lol: አራዳ ይግደለኝ ማለት እንደ አየለ አይደል
ዋው ብያለሁ ሙዝ ...የአየለን ነብስ ይማር
ያልበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ምርጫ ሲያስብ
የበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ትውልድ ያስባል
James freeman clarke
ገልብጤ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1680
Joined: Sat Jun 26, 2010 11:24 pm

Postby ሙዝ1 » Wed Jun 05, 2013 2:31 pm

ሙዝ1 wrote:ለሚቾ ሰላም ነዉ? እዚህ ቤት የሆነ ወቅት ስለ አየለ ጀምብ እግር አዉርተን ነበር:: ያለፈዉ ቅዳሜ አዲስ አድማስ እትም ላይ ስለ አየለ ጀምብ እግር .... የአገር ሳቅ .... የአገር ሀቅ በሚል ፊያሜታ የሚባል ሰዉ የጻፈዉን ነዉ ፖስት ያደረኩት ....

ይቀጥላል


ለገልቤX
ጸሀፊዉ እኔ አይደለሁም ... በነገርሽ ላይ አየለ ጀምብ እግር አፉ ብቻ ሳይሆን አይኑም በጣም ያወራል .... አስተያየቱ የሆነ ሸር ነገር እንዳለዉ አስታዉሳለሁ .... አንተ ኮት ካደረካት ሌላ ጸሀፊዉ (ፊያሜታ) ያላካተተዉ ... በታቦት ብር የተገዙ የህዝብ ማመላለሻ አዉቶብሶች አሉ ተብሎ ይታማ ነበር .... አዩ ጀለሴ ታዲያ ቤተክርስትያን ሄዶ አያዉቅም ..... ለምን አትሄድም ሲባል .... "ምን ማለትህ ነዉ ጌዎርጂስ .... ሚካኤል ... ገብሬል " ... እዚህ እያለልኝ ባዶ ድንጋይ ሄጄ የምስምበት ምክንያት ምንድን ነዉ? ይል ነበር አሉ ... አሉ ነዉ ታዲያ
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ገልብጤ » Wed Jun 05, 2013 3:40 pm

እድለኛ ሰው ነው ..ሽር እንኳን እኔ አልለውም ምክኒያቱም ...ሲናገር የነበረው የመልስ ምት እንጂ ...ሰው ሳይደርስበት የሚደርስ አይመስለኝም ...ሁሉም ሰው በስራው ስም ይወጣለታል አይደል..አየለም በተካነው ምላሱ ያስነካዋል እንጂ ..
ያልበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ምርጫ ሲያስብ
የበሰለ ፖለቲከኛ ስለቀጣዩ ትውልድ ያስባል
James freeman clarke
ገልብጤ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1680
Joined: Sat Jun 26, 2010 11:24 pm

Postby ለማ12 » Sat Jun 08, 2013 9:31 am

ሙ ሰላም ነው ?
ስለ አየለ አውርተን ነበር አሁን ስልሱ የጽፍከው በጣም ብዙ ትዝታዎችን አስነስቶብኛል:
አዩ በጣም ነገር አውቂና ተናጋሪ ነበር እስኪ አንድ ጊዜ ያለውን ላስታውስህ እርግጠኛ ነኝ አጎቶችህ በከፊል ሳያወሩህ አልቀሩም:


አንድ አባ ታደ´ሰ የሚባሉ ትልቅ ሰው ነበሩ ታዲያ በጣም መቀመጫቸው ሰፋ ሰፋ ያሉ ልጆች ነበሩአቸው:
አንዲቱ በጣም ደግ ስልነበርሽ አባ አደምንና ሁለቱን ልጆቻቸውን አስተናግዳለች እየተባለች ትታማ ነበር

ታዲያ አንድ ቀን ተስብስበን እያወራን ሳል ከገብያ ዘንቢል ተሸክማ ስትመጣ አጠገባችን ስትደርስ አየለ አብሮን ነበረና ያዝላት ያዝላት አሉት:
ከዚያ በፊት አዩ ከሰል ተሸክሞ ትንሽ ሳንቲሞች ተቀብሎ ኖሯል
ዝም አለ ታዲ ያዝላት ብሎ በካልቾ ሲለው ምን አለ መሰለህ አንተ ተው ሲል አሁን ተሸክሞ ሳንቲም ስላገኘ አይፈልግም አለ አንዱ አዎ ሁሉም ነው እንደ እስላም የለቀቁብኝ ብሎ ጸጥ አደረጋቸው የሚናገራቸው ነገሮች አጥንት ዘልቀው ይገቡ ነበር

በተለይ ጠላ ቤት ገብቶ ይጠጣና እንክፈልልህ ስንት ነው የጤጣሀው ስንለው ምንም አልጠጣሁ አምስት ብቻ ነው የቀመስኩት ይለን ነበር:

እማማ ቁራ ገደል ቤት እኔን ነበር የሚአስከፈለኝ እኔም ሳላንገራግር እከፈል ነበር የመፈራበት ምክንያት ስላለኝ እንዳይናገረኝ ብዬ: ዝም ብዬ ነበር የምከፍለው:


ስለጋሽ ከንቲባው ያለኝን የግል ትዝታ ብነግርህ እዚህ ላይ ብዙዎች ስለሚያውቁኝ እንግደልህ ይሉኛል
ከአሁኑ ሁኔታ ስታወዳድረው በጣም ጉቦኛ ነበር ማለት ይከብዳል አሁን ላይ ሆኖ ማለቴ ነው በወቅቱ ልክ ነህ ይባልና ይታማ ነበር:
ከ2 አመት በፊት አማኑኤል አግኝቸው ነበር ብዙ ትዝታዎን አንስቼ በጣም ነው የትጫወትነው:


ሰላም ሁን እስኪ እንደዚህ አጫዉተኝ:

ገልቡ ልክ ነህ ያልከው አዩ ካልነኩት አይነካም ነበር:
ለማ12
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1103
Joined: Sat Jun 16, 2012 9:46 am

Postby እምቢ ለሀገር » Sat Jun 15, 2013 5:13 pm

ዋርካ ላይ ብቅ ብዬ አያ ለማን እና ሙዝነትን ሰላም ሳልል ብሄድ አይቀናኝም...እዴት ባጃችሁ 'ደርቢዎቼ'? :lol:

አያ ለማ..ሙዝነት.. ሰሞኑን በሸገር fm ሬዲዬ የጨዋታ ፕሮግራም ጨዋታ አዋቂዋ መዓዛ ብሩ እና ታላቁ የሙዚቃ(የዜማ) ደራሲ አበበ መለሰ ለዛ ያለው ወጋቸውን አዳመጥኩ:: አበበ መለሰ በኩላሊት በሽታ እየተሰቃዬ ነው::ኢትዬጵያዊያንም እርሱን ለማሳከም እየተረባርቡ ነው::እኔም ያቅሜን ብያለሁ...ዛሬ ውለታ የሙዚቃ ድግስ በአዲስ አበባ ለዚህ ታላቅ ሰው ውለታ ለመክፈል ተዘጋጅቷል::...በጨዋታ ፕሮግራሙ ላይ አበበ መለሰ ደጋግሞ ማርቆስን ሲያነሳት ሰማሁ እና እናንተ ትዝ አላችሁኝ..ከሙዝነት ቢዘል እንኳ አያ ለማ ስለ አበበ አንድ ነገር እንደሚለን አስባለሁ:: የአበበ ሚስት እሱ እንደ ሚጠራት አድዬ(አዳነች)ም የማርቆስ ልጅ ናት...የጠይም ቆንጆ..የማርቆስ ኪነት አባል የነበርች..እሱ ጊታር ሲጫወት እሷ እየዘፈነች..ማርቆስ ላይ ፍቅር እንደጀመሩ...የአበበ ቤት ቤተመንግስት ግቢ እንደነበር(የእህቱ ባል አስተዳዳሪ ነበሩ)...የኤፍሬም 'የኔ አደይ አባባ" ዘፈን ለሷ እንደተዜመ....ብዙብዙ ነገሮችን አበበ አጫወተን:: እርግጠኛ ነኝ...አያ ለማ በአበበ ዙሪያ የምታጫውተን ነገር ይኖራል::ሙዝነትም ..ፍንጣሪ አይጠፋህም :: እስኪ አውጉን :lol:


እምቢተኛው!
ከሉማሜ
ETHIOPIA ETHIOPIA ETHIOPIA
እምቢ ለሀገር
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 262
Joined: Mon Feb 13, 2012 5:08 pm

Postby ሙዝ1 » Tue Jun 18, 2013 2:46 pm

ለሚቾና የሉማሜዉ እምቢ ለሀገር

እንዴት ናችሁ ባያሌዉ? ሁሉም አማን ነዉ ....

ሸገር ኤፍ ኤም ላይ የአበበ መለሰን ዉይይት እየኮመኮምኩ ነዉ .... በጣም ግልጽ .... ሳያካብድ .... ሳይፈላሰፍ ... የመአዛን ጥያቄዎች በቀጥታ እየመለሰ ነዉ ...

ስለ ቤተመንግስትና ስለ 15ኛ ሻለቃ (የነ አዳነች ሰፈር) ሲያወራ እኔንም በሀሳብ ይዞኝ ፈሰሰ ... ህምምም እዚህ አዲስ በአሁን ሰዐት ዝናብ እየዘነበ ነዉ ... ዝናቡን በመስኮት እያየሁ ነዉ የአቤን ጨዋታ የምሰማዉ ... 15ኛ ሻለቃ የወታደሮች ሰፈር ነዉ ... ... ስለሱ ሰፈር ከኔ በላይ የዋርካዉ ሾተል በደንብ ሊያጫዉተን ይችላል ... በጣም ጉልበተኞች ... በግሩብ የሚደባደቡ የወታደር ቤተሰብ ናቸዉ ... ሁሉም ማለት በሚቻል መልኩ ከሌላ አካባቢ የመጡ ወታደሮች ናቸዉ .... ምናልባትም ትንሿ ኢትዮጵያ ... አንድ ቄስ ብቻ እዛ ካምፕ ዉስጥ ይኖሩ ነበር ... ሌላዉ ግን ወታደር ... ቄሱም የነ ሸዋዬ አክሊሉ አባት ... እስኪ እኔም አድዬን (አዳነችን) ባላዉቃትም ስለነበሩኝ ቺኮች ላስታዉስ ...

ሰርክ አዲስ
የልጅነት ፍቅር ---- ምን እንደምንፈልግ በትክክል ያላጠራነዉ ግኑኝነት ... እድሜዬ ከ 15 በታች በዛ ላይ ለቫኬሽን የመጣሁ መጤ ...ሰርካዲስ ... ስሟ ራሱ ደስ ሲል አሁን እንኳን ስጠራት የሆነ የሁልጊዜ አዲስነቷ ይመጣብኛል .... አባቷ --- አይደለም እኛ የሲቪል ልጆች ... የወታደር ልጆችም ይፈሩት ነበር .... ኮሚሳር ነዉ ይባል ነበር .... ኮሚሳር ምናልባት ደህንነት ነገር ይሆን? አላዉቅም!!! ብቻ ከሌሎች ወታደሮች በተለየ ይፈራ ነበር ... .... እናም ግኑኝነታችን ይህንን የፍርሀት ድባብ ተሸክሞ ነበረ የምንገናኘዉ ከፈንጅ ቤቱ በታች ካለ የተኩስ መለማመጃ ጉድጓድ ዉስጥ ... አብዛኝዉም ወሪያችን ስለ ቆቅ አደን ሀሀሀ .... አሪፍ ጅንጀና ነዉ አይደል? ታዲያ ጀግንነቴን በምን ላሳይ ... ... ከኔና ከሷ ግኑኝነት እስካሁን የማልረሳዉ .... የክረምት ጭቃ ስለሆነ ትንሽዬ ዳገት ነገር ከሆነ አዳልጧት እንዳትወድቅ እጇን ይዤ የምጎትታት ....ሀሀሀ . ደስ የሚል የእጅ ንክኪ ነበር.. በደንብ ከጎረመስኩ በሗላ ድብዛ በተማርኩባቸዉ ሁለት አመታት ... 15ኛ ሻለቃ የሰርካዲስ ትዝታ ብቻ አልነበረም .... እሷ ከአባቷ ጋ ኢህአዴግ ሲገባ ወደ ሀገራቸዉ ሂደዋል --- ሀገራቸዉ የት ይሆን? ጠይቂያት አላዉቅም ነበር .... ሌላዉ ትዝታዬ ሌላዋ ቆንጆ አይንዬ ....

አይንዬ የዉነት ቆንጆ ነች .... ጠይም ... ሰልካካ አፍንጫ ... የሚያምር የሰዉነት ቅርጽ (እሱን እኔ ብቻ ነኝ ያየሁት -- ሁሌ በቀሚስ ነበረች) ... በጣም ሴት .... አሁን አሁን ሴት የሚመስል ሴት ሳጣ .... እነ አይንዬ አይኔን አባልገዉት አይነት ወቀሳም እወቅሳታለሁ ... የምንገናኘዉም ማርቆስ ቤተክርስትያን ጀርባ ካሉ የመቃብር ቤቶች አልያም አባ ገና ተራራ ... ደስ የሚሉ ክረምቶች ከነአይንዬ ጋ ... ዋዉ ... በምን ምክንያት እንደተለያየን ግን አላዉቀዉም ... ...


ለሚቾ ...
የካንቲባዉም ጓደኛ ነበርክ? ሎል .... ያ የምታዉቀዉ የኢንሹራንስ ኩባንያ ዉስጥ ስንት ሸር ይኖራቸዉ ይሆን? ... ቂቂቂ ልጃቸዉ አሪፍ ጓደኛዬ ነዉ ... የባንክ ባለቤት እንደሆነ መቸም ሳትሰማ አትቀርም ሎል የ 35 አመት ጎልማሳ የባንክ ትልቅ ድርሻ ሲኖረዉ አትቀናም .... ቂቂቂ
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ለማ12 » Fri Jun 21, 2013 12:46 pm

ሙ ሰላም ነው ?

ምን ያልሆንኩት አለኝ ግን ሁሉም አለፈና እናወራዋለን:


ጋሼ ከንቲባው ድሀ ነው ለማለት አይደለም ከወቅቱ ጋር ሲነጻጸር ማለቴ ነበር:

እላይ እንዳልኩህ አማኑኤል ተገናኝተን ብዙ አሳቀኝ:


እናቱ ያሉት እዚያ ነው በጣም ስላረጁ በጣም ይረብሻሉ

ደጁን አትዝጉት ብለው በጣም ስላስቸገሩ ምን አደረገ መሰለህ


መጀመሪያ ሚስቱን ላክና እንድታስተዳድራቸው አደረገ እሳቸውም ሚስቱን ምን አሉአት መሰለህ ሄደሽ ግደያት ብሎ ነው የላከሽ እያሉ በጣም አስቸገሩ ይህን መሸከም ያቃታት ሚስት ተመልሳ አዲስ አበባ መጣች:
ቀጥሎ ሴት ልጁን ላከ ደግሞ ልጅቱን ምን አሉአት መሰለህ በቁሙአ ውረሻት ብሎ ነው የላከሽ ብለው አሻፈራኝ አሉና መልሰው ሰደዱአት:
መጨረሻ ሲጨንቀው ጅብ ይበላታል ብሎ ራሱ ሄደ በዚህ ጊዜ ነው ወደ ጎንደር ሳልፍ የተገናኘነውና ያጫወተኝ::_
ወንዱን ልጁን አላውቀውም መኖሩን ነግሮኛል ሀብታም ሆኖለት ከሆነ መልካም ነው ግን ጎጃሞች ሀብታም ሆነዋል የሚለውን በመጠኑም ቢሆን አልደግፈውም ዝም ብለው በብድር ነው የሚጫወቱት:
በጣም አዝናለሁ መሆናና መደረግ የሌለበት ነገር ነው እያደረጉ ያሉት:


እስኪ አንድ ነገር ልጠይቅህ ለመጫውቻ እንዲሆነን


ማርቆስ እሆድፒታሉ ፊት ለፊት የነበሩ ጠላ የሚሸጡ ሴትዮ ነበሩ ልጃቸው ነጻ ነው የምትባል የናንተ እድሜ የነበረች ትመስለኝ ነበር አሁን ያለች አይመስለኝም እስኪ ስለዚህ አካባቢ አጫውተኝ: አ15 ሻለቃ አካባቢ ጉልበት የነገሰበት ሰፈር ነበር እኔም ስንዴ ጎም ትምህርት ቤት አጠገብ ደፋ ቃና እል ነበር መጥፎ አልነበረም:


እምፒ ሰላም ብያለሁ:
እናንተ ሰፈር አቶ ጫኔ የሚባል ትንሽ ሀብት ያለው ሰው ነበር ታውቀዋለህ የሚል ግምት አለኝ ቤቱ ሉማሜ እውሀው ዳር ነው ልጁ አብሮን ይማር ነበር ግን ደካማ መሳይ ነበር አንድ ወሮበላ ታናሽ ወንድም ነበረው ስሙ ጠፋብኝ ያም ሆነ ይህ ስለዚያ አካባቢ ስታጫውቱኝ በጣም ደስ ይለኛል
ስለ አበበ መለሰ የሆነ ነገር በል ነው ያልከኝ ?

ያው እንዳላችሁት ነው በህመም ላይ ነው የሚገኘው ታክሞ ይሻለዋል የሚል ሙሉ ተስፋ ነው ያለኝ
እነ አቶ ይሁኔ በተቻላቸው እየታገሉ ነው እኔም በዚያ በኩል ነው የምሰለፈው የምትችሉትን ማድረጋችሁ በጣም ጥሩ ነው ሚስቱን አንስተሀል አዎ ልክ ነህ ግን አሁን እዚህ ላይ ብዙዎቹ ስለሚከታተሉ የምለው የለኝም

ለመሆኑ ሰላም ናችሁ?

በየአላች ሁበ ሰላም ሁኑልኝ::
ለማ12
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1103
Joined: Sat Jun 16, 2012 9:46 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jul 10, 2013 3:31 pm

እስክ ትንሽ ደግሞ ወዳጄ አበቢና (አበባየሁ ገበያዉ) የጻፈችዉን አንብቡት

የገጠር ወግ ፍለጋ!!

ከጓደኞቼ ጋር አዝማሪ ቤት ዘለቅን ‹‹የገጠር ወግ ፍለጋ›› እዚሁ አዲስ አበባ፡፡ የባላገር ወግ፣ የባላገር ጨዋታ ይናፍቃል፡፡ ታዳሚውን በዓይኔ አማተርኩና ፈታ... ብዬ ግጥም ከዜማ እያዋደዱ የሚጫወቱ ሰዎችን እያደመጥኩ፤ ሰምና ወርቁን እየፈታሁ፤ ከራሴም፣ ከጓደኞቼም ጋር ስወያይ ቆየሁ፡፡ ከእኛ ፊት ለፊት አንድ ሴትና አራት ወንዶች በጋራ ያውካካሉ፣ ይጫወታሉ፡፡ አልፎ አልፎ ሳያቸው፤ ወደ እኛ እያዩ የሚያወሩ መሰለኝ፡፡ አይነ ውሃቸው ዲያስፖራ ነገር ይመስላል፡፡ ከጓደኞቼ መካከል አንደኛው፣
‹አታውቁትም፣ የቀበሌ አስር ልጅ እኮ ነው› አለ፡፡ ከፊት ለፊታችን ወደ ተቀመጡት ዳይስፖራ ቅብ፤ ወደ ሆኑት ሰዎች እየጠቆመን፡፡
‹ማርቆስ?› ጠየቀነው፡፡
‹‹አዎ፡፡ ከአቡኑ ቤት ጀርባ?›› የመኖሪያ ሰፈሩንም ሳይቀር አመላከተን ከመካከላቸው የአንደኛውን፡፡
‹እረግ! እረግ! አወኩት፡፡ የእነንትና ታናሽ ወንድም› አለ አንደኛው ጓደኛዬ፣ በጋራ የምናውቀውን ሰው እያስታወሰን፡፡
‹አዎ!›
‹እረ! ከተስፋይቱ ምድርም እንደሚኖር ሰምቻለሁ- እየሩሳሌም› ሌላኛው ጓደኛዬ ቀበል አድርጎ፡፡
ጓደኞቼ ወደ እኛ ያጣብሩ የነበሩ ልጆችን ማንነት አወቁ፡፡ እኔም ብሆን በስሱ አስታወስኩት ከአራቱ አንደኛውን ወንድ ልጅ፡፡ ትኩረታቸውን ከእኛ አልነቀሉም፡፡ ይሳሳቃሉ፣ ከተስፋይቱ ምድር መጣ የተባለው ልጅ የአንደኛውን እጅ በመሃላ መልክ ደጋግሞ ይመታዋል፣ ልጁም ዘወር እያለ እኛን ያያል፡፡
‹‹እናውቃቸዋለን እያለ ነው፤ ወይንስ ምንድን ነው?›› እኔም ነገር ገባኝ፡፡ አዝማሪው ኮተት እያለ ከተስፋይቱ ምድር ወደ ዚችኛዋ ተስፋይቱ ምድር(ኢትዮጵያ) የዘለቁትን እንግዶች ሊያጫውት ተጠጋ፡፡ ‹‹እኔስ እሄዳለሁ እየሩሳሌም...›› ‹‹ውዳሴ ለእናተ ይገባችኋል!!›› አይነት ሙዚቃ፡፡ የተስፋይቱ ምድር ሰዎችን ያሞካሽ ይዝዋል፡፡ ከየኪሳቸው የያዙትን አውጥተው ግንባሩ ላይ በምራቃቸው ለጠፉለት፡፡ ብር በምራቅ ቀባ ቀባ ተደርጎ ግንባር ላይ መለጠፍ እንደቀረ አላወቁም!! ዛሬማ በደረት ኪስ፣ በእጅ ማስያዝ ነው እንጂ፡፡ ከዘመኑ ጋር አብሮ መሻገር መሰልጠን መሰለኝ(ሳቅ)፡፡
‹ከተስፋይቱ ምድር ናቸው› ከተባሉት መካከል ሴቲቱ ወደ መፀዳጃ ደርሳ እንደ ተመለሰች የተቀመጠችበትን ዱካ ወደ እኛ ትይዩ አስተካክላ አንገትዋን እንደ መቀርቀር፣ መሬቱን በእግሩዋ እንደ መቆርቆር አድረገችና አዝማሪውን ‹ና ወዲህ› አለችው፡፡
‹ግጥም ልትሰጠው በሆነ› ብየ በልቤ ተመኘሁ፡፡ የዋዛም አይደለች፡፡

ይቀጥላል
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

Postby ሙዝ1 » Wed Jul 10, 2013 3:38 pm

‹ተቀበል› አለችው፡፡
ባሌ አይን አበዛ፤ ምን አየ በዋዛ፣
ያላገባው ይዞት፤ አንገቱ ጠምዛዛ፣
ያማትር ጀመረ፤ ከዚህና ከዛ፡፡
ድሮም ጠርጥሪያለሁ፤ ካገሩ ሲገባ፣
የቀይ ዳማ ወዳጅ፤ አካለ ደርባባ፣
ትሄጅ እንደሁ ሂጁ ነገር ሆዴ ገባ፡፡ በአድናቆት አጨበጨብንላት፡፡ ይህችማ አይነተኛዋ ባላገር አይደለች ግጥም ከስንኝ ፍለጋ አትንጓለል፤ እዚያው ፈጥራ፣ እዚያው ተቀኝታ..በቃ ጨዋታ አዋቂ(ሳቅ)
የማስንቆው ጌታ፣ አዝማሪው የገባው ነገር አለ መሰለኝ ወደኛም ያማትራል፡፡ ‹ተቀበል እንጂ› ‹ፉት› አለች በመለኪያ ከያዘችው የአገር ቤት አረቄ(ፎከት)፡፡
አንቺማ ብልጢቱ፤ ከበባሽ መብዛቱ፣
እረ የትኛው ነው፤ ከዚህ ከስድስቱ፣
ጓዳ ማጀትሽን፤ የሰራው ካንጀቱ፡፡
ጎጃም ግራ ገባው፣ ድንበር ያዘ ምነ፤
ባሌን አስጠልቶኝ፤ አንቺን ያስወደደኝ፣
ቀን ያለ ቀን መጥተሸ፤ ምታስለፈልፊኝ፣
በእንዲህ ያለ ሰዓት፤ ምታስቀባጥሪኝ፣
ብትበይኝ ነው እንጂ ብትቆረጣጥሚኝ፡፡ ብላ እርፍ፡፡ እንዴት እንዴት ነው አያ ነገሩ!!
‹‹ጓዶቼ ይሄ ነገር እንዴት ነው?›› ስላቸው ተሳስቀው
‹እህ! እንግዲህ በይ ተወጪው፡፡››
‹‹ጉዳዩ ለእኛ ነው?›› ስላቸው
‹‹ከታደሚው ሁሉ መካከል፤ ከስድስታችን ወንዶች፤ አንዷ፣ ሰባተኛዋ ሴት አንቺ!!››
‹እና እኔን ነው?› ደግሜ ጠየኩ፡፡
‹‹እህ...ሌላ አለ?!!› አለኝ አንድ ነገር የሻተው የሚመስለው ጓደኛዬ፡፡ የተስፋይቱ ምድር እንግዶች እንግዲህ ወደ እኛ እየጠቆሙ ሲጨዋወቱ ይህቺን ‹ጠብ ያለሽ በዳቦ› ሴት ግምኛ አስከፍተዋታል፡፡ እንግዲህ የቀበሌ አስሩ ልጁ ባልዋ መሰለኝ(ሳቅ) እስዋን ያበሳጨ ነገር ተናግርዋል(አይታበታለች) ‹ተቀንቼ፣ ተሙቼ!!› ነው ነገሩ፡፡ ‹‹ናማ፣ ናማ›› አለችው አዝማሪውን መልሳ ‹‹እረግ ውሃው በላኝ፤ አሁን ይለያል›› አልኩ ጆሮየን ይባሱን አቅንቼ፡፡
የልጅነት ልቤን የወሰደችቱ ያቻትና ቢለኝ
ህልሙን አጉድፈሽው ማንሳቴ ትዝ አለኝ
ቀኑ ጨላልሞበት መንገዱ ጠፍቶበት
ምን ይውጠው ነበር እኔ ባልደርስለት
ከልቡ ስር ገብተሸ ብትቆረቁሪው
በጉብዝናው ወራት ዕምባ አስገበርሽው
እያለ ሲነግረኝ ድፍን ሰባት ዓመት የባታ አለፈኝ
መገናኘት አይቀር የተባለው ተረት ታንቺ አስተያየኝ
የአንቺስ ልብ ምን ይላል
ትዝታውን ቀብርዋል
ጠቅለሽ ግቢልኝ ላውጣ የቁም ተዝካር
የኔም ልብ እንደሱ ይሂድ አሰቅሏል፡፡
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

PreviousNext

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 2 guests