ያገሬ ሰው
የወንዜ ሰው
ተድጦ ተደፍጥጦ - ወኔ ሃሞቱ
ተገምሶ ተደርምሶ - በቃኝ እምቢ ባይነቱ
ኩሩ ልባም እሱነቱ
ስብዕናው
ሕልውናው
በራስ መኩርያ- መመክያው
ኩራት ክብሩ- ተገፎ
ሞገስ ግርማው -ተጨልፎ
የድህነት -ኋላ የመቅረት- አብነት
የጭቆና- የፍትህ እጦት- ተምሳሌት
የአህዛብ መሳለቂያ - ሆነ ቢሉኝ- ምጽዋተኛ
የውራጅ ውራጃቸው - የእዳሪ ትራፊያቸው- ምርኮኛ
በሕይወት ሳለ - ከሞተ እኩል -ትብያ ሆኖ- ምድር የተኛ
ተፍሮ ተቆፍሮ -ከርሰ ምድሩ
ተነግሮ- ተለፍፎ -የቁም ቀብሩ............
ሙሾ ላወርድ -ደረት ድቅያ- እርም አውጥቼ
ስሰናዳ -ካሳብ ጓዳ -ገብቼ...
የሕልሜን ለቅሶ -ሳልጨርሰው አንብቼ.....
የትንሳዔው ዋዜማውን አየሁኝ
ጋሻው ሲመለሰለት አለምኩኝ!!......
ከእንግዲህማ- አልኩኝ
ከእንግዲህማ -በቃ አበቃ
የዘመናት ጭንቅ ሲቃ
የዝንተ ዓለም ሰቆቃ
ከእንግዲህማ- ጠላቱ ምን ቢዳክር
ፍላጻውን ቢቀስር
ወጨፎውን ቢወረውር
የት ሊደርስ ምን ሊፈጥር?
ከእንግዲህማ
ድህነቱን ይመክታል - ረሃብና እርዛቱን
ከአፈር ያደባየዋል - የጭቆና ስራዓቱን
መክኖ አይቀርም አደራው -የአባ ታጠቅ ምኞቱ
ጋሻው ከተመለሰማ -አብሮ ይመጣል ሃሞቱ
ብዬ ሳልም -ስባዝን
ድንገት ብንን!!
አይ ሕልም?
ደህና ቆዩ