አስተያየት መስጫ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው አጭር ልብ ወለድ

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ሙዝ1 » Sat Nov 10, 2012 1:52 pm

ገጽ 137 ላይ ያሉ ሁለት የመጭረሻ አንቀጾችን ዘለልኳቸዉ --- ካሟሟቱ ጋ ምንም ግኑኝነት ያላቸዉ ስላልመሰለኝ ነዉ ....

ታህሳስ 15 ቀን 1941 ዓ.ም አረፈ ...

ስለ ተመስገን ገብሬ ህመምና አሟሟት የሚታወቀዉ ነገር የተመረዘ ነገር መብላቱ ነዉ:: ይሄን የተመረዘ ነገር በማን አቀነባባሪነት ነዉ የበላዉ የሚለዉ መሰረታዊ ጥያቄ ነዉ:: በወቅቱ ተመስገን ገብሬ የጠንቋዮችን ምስጢር እየዘከዘከ የሚያጋልጥ ስለነበር ጠንቋዮች ሰዎችን ተገን አድርገዉ የተመረዘ ነገር እንዲበላ አድርገዉታል የሚባል ወሬም አለ::ጠንቋዮችም ይገሉታል እየተባለ ይነገርም ነበር::

ከዚህ ሌላ ግን ህመሙ የጀመረዉ ቀን የበላዉ ምግብ ዋነኛ የበሽታዉ መንስኤ ነዉ:: በዚያች ቀን አብረዉት የነበሩት ደግሞ በዘመኑ ትልቅ ባለስልጣን የነበሩት ጸሀፌ ትዕዛዝ ናቸዉ:: ለመሆኑ ከኚህ ሰዉ ጋርስ የተለየ ጸብ ነበረዉ ወይ ብሎ መጠየቁ ተገቢ ጥያቄ ነዉ::

ተመስገን ሱዳን ዉስጥ በስደት በነበረበት ወቅት ከጃንሆይ ጋር እና ከጸሀፌ ትዕዛዙ ጋር ደብዳቤ ይጻጻፍ ነበር:: ለምሳሌ ጃንሆይ ጄኔቫ ዉስጥ ያንን ንግግር እንዲያደርጉ በርካታ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታዎችን በተመለከተ መረጃ የላከላቸዉ ተመስገን ገብሬ ነበር:: በተለይ ከተመስገን ገብሬ ለጃንሆይ የተላከላቸዉ ደብዳቤ በየካቲት 12 ስለተደረገዉ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ነዉ:: እያንዳንዱን ነገር በዝርዝር ጽፎላቸዋል:: ጃንሆይም ይህንን ደብዳቤ ሲያነቡ አለቀሱ ብለዉ ጸሀፌ ትዕዛዙ ለተመስገን ጽፈዉለታል:: ጸሀፌ ትዕዛዙ ከጃንሆን ጋር አብረዉ ወደ ለንዶን የተሰደዱ ናቸዉ::

ጣልያን ድል ሆነችና ስደተኞች ወደ ሀገራቸዉ ገቡ:: የኢትዮጵያ መንግስትም ወደ ዙፋኑ ተመለሰ:: ሀገር የማስተዳደር አቅምም ያላቸዉ አርበኞች ወደ ተለያዩ የመንግስት ስልጣኖች ላይ ተሾሙ: ተሸለሙ:: ጸሀፌ ትዕዛዙ አንድ ቀን ተመስገንን እንዲህ ይሉታል "" ላንተም ሆነ ለቤተሰብህ የሚሆን መሬት ጃንሆይ ይሰጡሀል"" ይሉታል:: ተመስገንም የሚከተለዉን መለሰላቸዉ:: ""ልጆቼ በእድላቸዉ ያድጋሉ:: እኔም የምፈልገዉን ቤት እገዛለሁ"" ይላል:: ይህ መልሱ በዘመኑ በጣም መጥፎ ለአደጋ የሚያጋልጥ ነበር:: ምክንያቱም ብዙ ሀብትና ንብረት የነበራቸዉ ባላባቶች ሳይቀሩ እንደ ቡራኬ ጃንሆይ ፊት እየቀረቡ መሬት እንዲሰጣቸዉ ይጠይቁ ነበር:: የተመስገን አካሄድ እንደ አፈንጋጭ የሚያስቆጥረዉ ሆነ:: ከናንተ ምንም አልፈልግም በራሴ መኖር የምችል ሰዉ ነኝ ማለት ነዉር ነበር:: እናም ይሄ ከጸሀፌ ትዕዛዙ ጋር የተቋሰለበት አንደኛዉ ነጥብ ነዉ::
አይን ሁሉን ቢያይም አጠገቡ ያለዉን ቅንድብ አይቶ አያዉቅም ...
ሙዝ1
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 3128
Joined: Wed Feb 22, 2006 9:25 am

ተምስገን ገብሬዎች

Postby እንሰት » Mon Nov 19, 2012 6:40 am

ሙዝ እጅህ እና ጊዜህ ይባረክ እያልን እንዳለጌታ ደግሞ ተመሰገን ካጭር ልቦለድ ጀማሪ በላይም ነው:: ይህንን ገጽታውን ላሳያችሁ ይለናል:: የአባ ፈርዳውም አቢቹም አልቀረም ሲነሳ::

Addis Times መፅሄት
እንዳለጌታ ከበደ

እነሆ! ስለተመስገን ገብሬ አሁንም ልተርክ ነው፤ ከዚህ ቀደም ‹ከማደንቃቸው ሰዎች አንዱ› ስለመሆኑ በሌላ አጋጣሚ፤ ለአድማጮች አውርቼ ነበር፤ ተመስገን ገብሬ፤ ብዙ ያልተባለለት፤ የኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዘመናዊ አጭር ልቦለድ ደራሲ፤ የመጀመሪያው ያሰኘውን ብቸኛ እና ነጠላ አጭር ልቦለዱን ‹የጉለሌው ሠካራም›ን ለማየት ሁለት ሦስት ወራት ሲቀሩት ሞት የቀደመው፤ ከ63 ዓመት በፊት ግብዓተ ሕይወቱ የተፈፀመ፡፡


ከአምስት አመት በፊት፤ የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር፤ አጫጭር ልቦለዶች ብቻ የሚነበቡበት አንድ ጉባዔ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አሠናዳ፤ መታሰቢያነቱም ለተመስገን አደረገው፤ ‹የጉለሌው ሠካራምም› ተተረከ፤ ስለ የሕይወት ታሪኩም ብዙ የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ተነገረ፤ መድረክ ላይ የሆነው ሁሉ፤ በኢቲቪ ተላለፈ፤ ይህን ያዩ የደራሲው ቤተሰቦች፤ አባታችንን እናንተ በምትሉት ልክ አናውቀውም፤ ሳናውቀው ነው ሞት የቀደመው አሉና፤ እናታችን አደራ በማለት የሰጠችን፤ በእርሳስ የተፃፈ፤ ያልተጠናቀቀ፤ ከመቶ ገፅ የበለጠ፤ 60 ዓመት ያስቆጠረ ረቂቅ ድርሰት ይዘን መጥተናልና እዩት እስኪ አሉንና፤ ሳይሸጥ የቀረ፤ ቤት ውስጥ የተቀመጠ ‹የጉለሌው ሠካራም› አለና ማኅበሩ ይረከበን ብለው ይዘው መጡ፡፡


ከዚያ በኋላ፤ በእርሳስ የተፃፈችዋ፤ ‹ሕይወቴ› ታተመች፤ ተመስገንን ብቻ ሳይሆን፤ የዘመኑን መንፈስ ቃኘንበት፤ የአተራረክ ብቃቱን ብቻ ሳይሆን፤ እሱና ሌሎች አርበኞች፤ በየካቲት 12/1929 ዓ.ም.፤ ስለተጐነጩት የመስዋዕትነት ፅዋ አወቅንበት፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ የዚያን ዘመን ትውልድ አባላት፤ ሀገር እና ባንዲራ የሚባል መስቀል ተሸክመው፤ ምን ያህል ጊዜ እንደተገረፉ፤ ምን ያህል ጊዜ እንደተወገዙ፤ ምን ያህል ጊዜ ቀራኒዮ ተራራ ላይ ወጥተው ለነፃነት ብለው በፋሽስት ምስማር እንደተቸነከሩ አየንበት፡፡


‹የጉለሌው ሠካራም›
ውስጥ ተበጀ የተባለውን ገፀባህርይ የሚገልፅበት አንድ ዐረፍተ ነገር፤ ራሡ ተመስገን ገብሬን ይገልፀዋል ብዬ አምናለሁ፤ ‹የሕይወቱ ታሪክ ፍፁም ገድል ነው› ተመስገን ገብሬ፤ በአክብሮት እንደሚያነሳው፤ የልጅነት መምህሩ፤ እንደ ኑሬ ነው ‹…ኑሬ እውር ነው፤ ግን ለተማሪዎች ሁሉ የሚያስደንቅ ብርሃን ነበር፡፡ እኛ ጭቃማ በሆነው በጠባቡ መንገድ መራነው፡፡ እርሱ ግን በተሻለው በእውቀት መንገድ መራን፡፡ ምሽት የለውም፤ ግን የሁላችን አባት ነበር፡፡ ወላጆቻችን ገንዘብ ስላልከፈሉት ይርበው ነበር፤ እና ግን ብዙ በሆነ ጊዜ ረሃብን ይረሣው ነበር….(ገፅ 21- ሕይወቴ) ተመስገን ስለራሱ ሲፅፍ አፅድቶ እና አንፅቶ አይደለም፤ በ15 ዓመቱ ኮከብ እየቆጠረ፤ የጥንቆላ መጻሕፍት እያነበበ፤ ጉቦ እየተቀበለ፤ ራሱን ያስተዳድር እንደነበር ሲፅፍ፤ ግልፅነቱ እንጂ ችሎታው አይመስጠንም፡፡ ‹…ምንም እንኳን አሁን ድሆችን በጉቦ በማስጨነቅ ብጨክን፤ ምን መሆኑን ለማላውቀው አንድ ታላቅ ነገር ሰማዕት ለመሆን ከልጅነቴ አብሮኝ ምኞት አድጐአል› ይለናል-ራሱ፡፡


ይህቺ ከልጅነቱ ጀምሮ አብራው ያደገችው ምኞት ብዙ ዋጋ አስከፍላዋለች፤ ‹…ለታላቅ ተጋድሎ ይልቁንም ሌሎችን ለመታደግ ራሳቸውን ለመስዋዕትነት አሳልፈው ለመስጠት ታላቁን የእሳት ነበልባልና የተሳለውን ሰይፍ ለመገናኘት በመድፈር ባደረጉት ሌሎችን በማሰማው በሰማዕታት ታሪክ ደስ ብሎኝ ከእነርሱ እንደ አንዱ ለመሆን ተመኝቼ ነበር (ገፅ 41)› ብሎ የተጓዘበት መንገድ አሁን ስሙን እንዳነሳው ምክንያት ሆኖኛል፡፡


ተመስገን ተናጋሪ ነው፤ እሱና ወዳጆቹ ባቋቋሙት ማሕበር፤ በየቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ እየተገኘ፤ ስለሰማያዊ ሕይወት በሚነገርበት መድረክ፤ ስለምድራዊ ኑሮ በመተረክ፤ ብዙ አድናቂዎችን ቢያተርፍም፤ የእንግሊዝ ሰላይ ነው ተብሎ፤ በሚከተለው ሃይማኖት ሰበብ መወገዝ ሆኖ ነበር ዕጣ ፈንታው፤ ያደነቁት አናናቁት፤ ያከበሩት አዋረዱት፤ እሱና ጓደኛው በጃንሆይ ትዕዛዝ ከአደባባይ ራቁ ከመድረክ ወረዱ፤ ‹በሃገር ላይ ሁከት የሚሰሩ…› ስለመሆናቸው ተነግሮ አንደበታቸውን እንዲቆልፉ ተደረገ፡፡


ተመስገን፤ በጣሊያን ወረራ ጊዜ፤ ብዙ ተንገላትቷል፤ ወገኖቹ ተማርከው በውሃ ጥም ምክንያት ደም የተቀላቀለበት ውሃ ሲጠጡ አይቷል፤ በእሱ እና በወገኖቹ ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ለጃንሆይ በሚፅፍላቸው ጊዜ፤ ጃንሆይ በስደት አገር በለንደን ሆነው ያለቅሱ እንደነበር ተፅፏል፤ ጣሊያን ድል ከሆነች በኋላ ግን፤ ሀገር የማስተዳደር አቅም ያላቸው ተብለው አንዳንድ አርበኞች ሲሾሙ እና ሲሸለሙ፤ ተመስገን ጃንሆይ ፊት ቀርቦ መሬት እንዲሰጡት እና የቡራኬው ተቋዳሽ እንዲሆን፤ በሹማምንት ግፊት ቢደረግበትም፤ ግብዣውን ሳይቀበል በመቅረቱ መንግስት ጥርስ ውስጥ ገባ፡፡


የሆነው ሆኖ፤ ‹ኒው ታይምስ ኤንድ ኢትዮጵያን ኒውስ› የሚል ጋዜጣ፤ ‹ኢትዮጵያን ከራሱ አብልጦ የሚወድ…. ስራዬ ከቶ በሕዝብ ዘንድ ይታወቅልኝ ባይ ያልሆነ… እግዚአብሔርንና ሰውን ለማገልገል የተፈጠረ… የተወደደ ባል እና አስተዋይ አባት› ብሎ የገለፀው ተመስገን ገብሬ፤ እነማን እንደሆኑ ያልታወቁ (የጃንሆይ ወዳጆች ወይም ሕዝቡን በዘበዛችሁት ብሎ ያጋለጣቸው ጠንቋዮች ወይም ሌሎች ሊሆኑ ይችላሉ) የተመረዘ ምግብ አብልተውት ሞተ፡፡


…ተመስገን ገብሬ ከርቀት ይኼ ነው፤ በቅርበት ለማወቅ ‹ሕይወቴ›ን ማንበብ ግድ ነው፡፡ እንደ ተመስገን ገብሬ ያሉ ሰዎች ጥቂቶች ናቸው፤ ተመስገን ገብሬዎች የምላቸው፤ እውነተኞችን ነው (እስካሁን ድረስ ይርጋ ዱባለዎችን ስፅፍ፤ ወልደጊዮርጊስ ወልደዮሐንሶችንና ሰለሞን ተካልኞችን ስፅፍ፤ ቴዲ አፍሮዎችን ስፅፍ፤ ራሴን ከትቼ እኔን አስገብቼ ነበር፤ በድክመታቸው ውስጥም ሆነ በብስለታቸው ውስጥ ራሴን አግኝቼው አውቃለሁና፤ በከፊልም ሆነ በጨረፍታ እነሱን የሚመስል ነገር በሕይወቴ ውስጥ አልፎ ያውቃልና፤ ስለተመስገን ገብሬዎች ስተርክ ግን፤ ራሴን ከዚህ ቅጥር አስወጣለሁ) …እና ተመስገን ገብሬዎች፤ ለአገራቸው ደህንነት እና ለወገናቸው የተሻለ ሕይወት በብዙ ይደክማሉ፤ የድካማቸው ፍሬ ግን አይከፈላቸውም፤ ሹመት ሽልማት አይቸራቸውም፤ እንኳንስ አገር ውለታ ቆጥሮ፤ ‹አሁን እንደዚህ እንድኖር ደምና አጥንት ከከፈሉት ወገን አንዱ ነህ!› ሊለው ቀርቶ፤ በሥጋ እና በደም የሚዋለዱት እንኳን ‹ጠንቅቀው› አያውቁትም፤ ሕይወቱ በፍፁም ገድል የተሞላ መሆኑን አይመሰክሩም፡፡ ተመስገን ገብሬዎችን ተከትለው፤ እሱን ፊታውራሪ አድርገው ከኋላ የሚሰለፉ ሰዎች፤ ብዛታቸው ጥቂት ነው፤ ጥቂት ቢሆኑም ለአገራቸው ምሰሶዎች ናቸው፤ ምሰሶ እንደነበሩ የሚታወቁት ግን ዘግይቶ ነው፤ እድሜያቸው ከሄደ፤ የልጅ ልጆቻቸው ከመጡ፤ 50 እና 60ኛ የሙት ዓመታቸው ሲከበር… (የሀበሻ ጀብዱ ላይ ያነበብነው፤ የሰላሌ ኦሮሞ ተወላጅ የሆነው፤ ምኒልክ ይሙት ብሎ ለማንም ወደኋላ የማይመለሰው፤ በአፄ ኃይለሥላሴ ዘንድ እንኳን የተፈራው አቢቹን ልብ ይሏል?) ተመስገን ገብሬዎች መንገዳቸው የጨዋ ነው፤ አነጋገራቸው የጭምት ነው፤ በገድላት እና በድርሣናት ውስጥ እንደምናገኛቸው ሰማዕታት፤ ራሳቸውን ለተከበረ ነገር ያጩ ናቸው፤ ለተከታዮቻቸው ግድ አላቸው፤ የሆነ ሰው፤ የሆነ ቦታ ሆኖ፤ ለአርአያነት ሊመርጣቸው እንደሚችል ግምት አላቸው፤ ተከታዮቼ ወዴት ናችሁ ብለው ግን አይፈልጉም፤ የሚታመኑት ለሃሳባቸው ነው፡፡


ተመስገን ገብሬዎች አሟሟታቸው ሁሉ ምስጢራዊ ይሆናል- አንዳንድ ጊዜ፤ የሞቀ የደመቀ ስርዓተ ቀብር አይፈፀምላቸውም፤ ስለራሳቸው ገድል እና ስለስራቸው ድል የመዘመር አባዜ ስላልተፀናወታቸው፤ ስማቸው የተደበቀ ነው፤ በመጋረጃ የተከለለ፡፡ በተቀናቃኞቻቸው እጅ ነው የሕይወት ገመዳቸው የሚያጥረው፤ የቆሙለት እውነት ነው ጠላት የሚያፈራባቸው፡፡


…የሆነ ነገር ጀማሪዎች ናቸው፤ ‹ማንም ባልሄደበት መንገድ እንሂድ› ብለው ግን አይደለም ጉዞአቸውን የሚጀምሩት፤ እነሱ ስለፈለጉ፣ የሚያስፈልግ ስለመሰላቸው እና ልባቸው ስለፈቀደ አንድ አዲስ ሀሳብ አምጠው ይወልዳሉ፤ የወለዱትን የሃሳብ ፍሬ ግን አያዩትም… እንደዚህ ዓይነት ሰዎች፤ ደግሜ እነግራችኋለሁ፤ በቁጥር ጥቂቶች ናቸው፤ አስፈላጊነታቸው የሚገባን ዘግይቶ ነው፤ ለመታየት በሚጓጉ እናሌላውን ዝቅ አድርገው ከፍታ ቦታ ላይ ለመቆም በሚታትሩ ሰዎች ይሸፈናሉ፤ አርበኝነታቸው ጦር ሜዳ ሄዶ ተጋድሎ ለመፈፀም ብቻ
የሚዘከር አይደለም፤ አንደበታቸውም፤ ብዕራቸውም ለሃቅ የቆመ እና ለእውነት የተገራ ነው፡፡ እንዲህ ናቸው ተመስገን ገብሬዎች፡፡
እንሰት
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1213
Joined: Sun Jan 30, 2005 1:14 am
Location: united states

Re: ተምስገን ገብሬዎች

Postby ዲጎኔ » Tue Nov 20, 2012 4:10 pm

እንሰት wrote: እሱና ወዳጆቹ ባቋቋሙት ማሕበር፤ በየቤተክርስቲያን ቅፅር ግቢ እየተገኘ፤ ስለሰማያዊ ሕይወት በሚነገርበት መድረክ፤ ስለምድራዊ ኑሮ በመተረክ፤ ብዙ አድናቂዎችን ቢያተርፍም፤ የእንግሊዝ ሰላይ ነው ተብሎ፤ በሚከተለው ሃይማኖት ሰበብ መወገዝ ሆኖ ነበር ዕጣ ፈንታው፤ ያደነቁት አናናቁት፤ ያከበሩት አዋረዱት፤ እሱና ጓደኛው በጃንሆይ ትዕዛዝ ከአደባባይ ራቁ ከመድረክ ወረዱ፤ ‹በሃገር ላይ ሁከት የሚሰሩ…› ስለመሆናቸው ተነግሮ አንደበታቸውን እንዲቆልፉ ተደረገ፡፡ እነማን እንደሆኑ ያልታወቁ (የጃንሆይ ወዳጆች ወይም ሕዝቡን በዘበዛችሁት ብሎ ያጋለጣቸው ጠንቋዮች ወይም ሌሎች ሊሆኑ ይችላሉ) የተመረዘ ምግብ አብልተውት ሞተ፡፡
ዲጎኔ
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 4752
Joined: Fri Aug 19, 2005 2:03 am
Location: united states

Previous

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 5 guests