የአማርኛ ምንጭ ከወደየት ነው?

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

የአማርኛ ምንጭ ከወደየት ነው?

Postby ጋንች. » Wed Sep 18, 2013 5:09 pm

የአማርኛ ምንጭ ከወደየት ነው?

በደረጀ ይመሩ

ታሪክ የሰውን ልጅ ማኀበራዊ ኑሮ፣ ድርጅቶቹን፣ ባህሉን፣ ሃይማኖቱን... ወዘተረፈ በተጨባጭ ማስረጃዎች ማለትም በጽሑፍ፣ ሰነድ፣ በጥንት ቅርስ ፍራሽና ቅሬት፣ በተውፌት (አፈታሪክ) ያለፈውን ክንውን ከጊዜና ስፍራ አንጻር አገናዝቦ የሚያሳይ የዕውቀት ዘርፍ ነው።

በመሆኑም የታሪክ ጥናት ሁለት ዓቢይ ክፍሎች አሉት። የመጀመሪያው ቅድመ ታሪክ ሲባል፣ ሁለተኛው ዘመነ ታሪክ ይባላል። የሥነ ጥንት ቅርስ ጥናት በምድር ውስጥ የተቀበሩ ፍርስራሽ ቅርሶችን፣ ቅሪቶችን የሚመረምር በአብዛኛው በቀደመ ታሪክ ክፍል ዘርፍ ላይ ያተኩራል። ታሪካዊ ማስረጃዎችን የጽሑፍ ሰነዶች፣ የሕንፃ፣ የእርሻ፣ የንግድ፣ የእደ ጥበባት ክንዋኔዎች፣ የሃይማኖት፣ የማኀበረሰብ መስተጋብራትን በጊዜና ስፍራ ተለይተው የሚታወቁበት ዘመነ ታሪክ ነው። ስለኢትዮጵያዊ ዐማራ ሕዝብ ታሪክ በተጠቀሰው የአጠናን ስልት መሠረት መረጃዎችን በማገናዘብ ይቀርባል። በሃይማኖት ሳቢያ፣ በይሆናል ግምትና መላ ምት የተጠናቀሩት አመለካከቶች ይቃኛሉ። ያማራው ሕዝብ ታሪክና ሥልጣኔ የአፍሪቃ አባይ ሸለቆ ሕዝቦች አካልና መሠረት ለመሆኑ በሰፊው ይገለጻል።

***

የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ረጅም ታሪክ በሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ በተመለከተ በዘመነ ኢምፔሪያሊዝም የምዕራብ አውሮፓ ቅኝ ገዥዎችና ተስፋፊዎች በተለይም የጀርመን፣ የጣሊያን፣ የፈረንሳይና እንግሊዝ ምሁር ተብዬዎችና አገር ሰላይ ሚሲዎኖቻቸው ሁሉ በነጭ ዘር የበላይነትና የአሰልጣኝነት ተልዕኮበፍጹም የዘረኝነት አስተሳሰብ እየተመሩ እጅግ ብዙ ትርኪ ምርኪ አጠናቅረዋል። የጥቁር ሕዝብ ዝርያዎችን በዝቅተኝነት ደረጃ መድበው በያለበት በአረመኔ ጭፍጨፋ፤ ወረራና ዝርፊያ ከምድረ ገጽ ላይ ለማጥፋት ሞክረዋል።

ለምሳሌ በአውስትራሊያ የታስማኒያ ጥቁር ዝርያዎች በጭራሽ ከወደሙት ሕዝቦች ወገን እንደሆኑ መጥቀስ ይቻላል። (Patrice Brantlinger: Dying races: rationalizing genocide in the nineteenth centaury (1995), PP. 43-56)

በኢትዮጵያ ምድር የሚገኘውን ጥንታዊ የጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔ ከእሲያ የአረብ ሠርፀ ምድር የፈለሱ አበሻና አግአዚያን የተባሉ ‹‹ሴማውያን ነገዶች›› ፈጠራ ነው እየተባለ ተለፍፏል፣ ዛሬም እንኳ እንበለ እፍረት ያናፍሳሉ። የኢትዮጵያን ጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔ አፍሪቃዊ ምንጭና መሠረት ዓይናቸውን በጨው አጥበው ሸፍጠዋል። ተመሳሳይ ጽሑፍና ሕንፃ በየመንና በአክሱም ግዛት ውስጥ ስለተገኙ ብቻ የሳባውያን ቅኝ ገዥዎች የአክሱምን ሥልጣኔ ፈጠሩ የሚባል ከሆነ ስለምን የጥንት ግሪካውያን በጠቅላላው ከምድረ ግብፅ የአፍሪካ ኩሻውያን ጥቁር ሕዝብ ሥልጣኔ መቅዳታቸው ወይም ቅኝ ግዛት መሆናቸው በሰፊው መነገርና መታወቅ ይኖርበታል። ነገር ግን ከሁሉም በተቀዳሚ መታወቅ ያለበት ሃቅ በጥንት የመን ሳባውያን ሴማዊ ሳይሆኑ እንዲሆኑ ተደርጎ ውሸት መነዛቱን ነው። የሳባ፣ የሕማርያ፣ የቀጠባን፣ የሚናን ቋንቋዎች ከአረብኛ ይሁን ከዕብራይስጥ ጋራ በጭራሽ አይዛመዱም። በየመን የተገኙት አጭር የጽሑፍ ሰሌዳዎች እንጂ ረጀጅም የታሪክ ዘገባ ለምሳሌ እንደ የግብፅ ሄሮግሎፊስና እንደ አጤ ኢዛና ዓይነት ሰሌዳ አልተገኙም።

የአረብኛ ቋንቋ በየመን የተስፋፋው ከእስልምና ሃይማኖት ጋራ በሰባተኛው ክፍለ ዘመን ነው። ሁሉም የጥንት የመን ቋንቋዎች ከኩሻዊ ቋንቋ ቤተሰብ ሲሆኑ መነሻቸውም ከሰሜን ምሥራቅ አፍሪቃ ነው። በደቡብና ደቡብ ምዕራብ የሚኖሩት ሳባውያንና ሌሎቹ የየመን ጎሳዎች ሁሉም የጥቁር ዝርያ ኩሻዊ ነገዶች በቋሚ ሰፋሪነት መንደርና ከተማ ገንብተው ገበሬዎችና ነጋዴዎች ሆነው ሲኖሩ በአረቢያ በርሃማው ሰሜናዊ ምሥራቅ ክፍል እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ የሚኖሩት ሴማዊ ዘላኖች የአረብና እብራዊ ጎሳዎች ነበሩ። እንኳን ደቡብ አረቢያ ሠርፀ ምድር ይቅርና የባቢሎን፣ የከለዳውያን፤ የሱመሪያውን፣ የኢላምና የጥንት ሕንድ ሁሉ የጥቁር ሕዝብ ዝርያ የኩሻውያን ሥልጣኔ መሆኑ የታወቀ ነው። (http:www.sacred-texts.com/afr)

የ18ኛውና የ19ኛው ክፍለ ዘመን የምዕራብ አውሮፓ ልሂቃን ለቅኝ ገዥነትና ተስፋፊነት፤ ለነጭ ዘር ያሰልጣኝነት ተልዕኮ ምኞትና ቅዠት ተስማሚ ትርጉምና ግኝት አቀናብረዋል። ታሪክን አፋልሰው ቅራቅንቦ ተረት ፈጥረዋል። ኢትዮጵያ በአፍሪቃ አህጉር ያውሮፓ ኢምፔሪያሊስቶችን ወረራና ከበባ ተከላክላ፤ ነፃነቷን በልጆቿ የጋራ መስዋዕትነት ጠብቃ የቆየች፤ በዓለም ላይ ብቸኛ የጥቁር ሕዝብ አገር በመሆኗ ምክንያት የምዕራብ አውሮፓ ዘረኞች የጥንት ግብፅን ሥልጣኔ፣ ቋንቋና ባሕል ከአውሮፓ ነጭ ዘር ተብዬው ክልስልስ ወገን ለማዛመድ እንደጣሩት ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር የሚገኘውን ጥንታዊ ሥልጣኔ መካድ ስለማይቻላቸው ሌላው አማራጭ የአረቢያ ሴማውያን ሠፋሪዎች የአክሱምን መንግሥትና ሥልጣኔ ፈጠሩ ብሎ በታሪክ ስም መዋሸትን መርጠዋል። የኢትዮጵያ ምድርና ሕዝቡም ከጥንት ግብፅ፣ ከነቢያና ሌሎች አጎራባች ሕዝቦች ጋራ የነበረውን ቀጥተኛ መልከአ ምድራዊ ዝምድናና የረጅም ዘመናት የጠበቀ ግንኙነት ሸፍጠው ከአረቢያ ብቻ ፈለሱ ስለተባሉት አሰልጣኞች የውሸት ስንክሳር ደጉሰዋል። ዘረኞች ዓይናቸውን በጨው አጥበው ስለኢትዮጵያ ‹‹ታሪክ›› ሲጽፉ የጥንት ኢትዮጵያ በአፍሪቃ ከፈርኦን ግብፅ ጋራ ምንም አይነት ግንኙነት እንዳልነበራትና በሂግሮሊፕስ ጽሑፍ ስለ ፑንትና የቅመማ-ቅመምና አማልክት የአበሻ አገር ከ2500-600 ዓ.ዓ የተመዘገበውን እጅግ ብዙ ሰነድ ዋጋ እንደሌላቸው ጀርመናዊ አኖ ዲልማን ስለ አክሱም ግዛት አጀማመር /A. Dilmann: Ueber die Anfaenge det Axumitischen Reichs, Berlin 1879, P. 182)፣ የእንግሊዙ ዋሊስ ቡጄ (E.A.W Budge: Ethiopia and the Ethiopians, (Londor 1928), P. 130; የጣሊያኑ ኮንቲ ሮዘነ (Conti Rossini: Sugli Habashat, (Rome: 1906). PP.39-59)etc. የውሸት ዝባዝንኪ አጠናቀረዋል። በተለይ እንግሊዛዊው ዋሊስ ቡጄ በደቡብ ሸዋ በምድረ ጉራጌ ጥያ ከሰዶ እስከ ሲዳሞ ቱርካና ሐይቅ ድረስ ቆመውና ወድቀው የሚገኙትን የቁም ድንጋይ ሐውልቶችን በፈረንሳዩ ቄስ እዚያስ ተጎብኝተው የተመዘገቡትን፤

‹‹የታሪክ ሰነድ አይሆኑም፤ የተሰሩትም በአረቦች ነው፣ ኢትዮጵያውያን ምንም ነገር አልፈጠሩም። ላሊበላና አክሱምንም ወዘተ ሁሉ የሠሩት ከግብፅና ግሪክ የመጡ ሥልጡኖች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ከወታደርነት ሥራ በስተቀር ለምንም ነገር ችሎታ የላቸውም›› እያለ ጽፏል።

ሌላው ወሻካች ስፔንሰር ትሪሚንግሃም (1952) የተባለውም እንግሊዛዊ የአረብ ታሪክ ሊቅ ተብዬ ትርክምርኪውን ሲያራግብ አኖ ሊትማንም (1875-1958) የተባለውን የዘረኝነት አመለካከት ዋና አቀንቃኙን በመጥቀስ አናፍሷል። የሴማውያን አበሻና አጋአዚያን ተብዬ ነገዶች ከረቢያ ሠርፀ ምድር ፈልሰው በኢትዮጵያ አምባ ምድር የመስፈር የፈጠራ ተረት- ተረት በዘመናዊው የሥነ ቋንቋና በጥንት ቅርሳ-ቅርስ ፍርስራሽ ጥናት ውድቅ ተደርጓል። በዚህም መሠረት አሜሪካዊው ዩሴፍ ግሪንበርግ የቋንቋ ምሁር የአፍሪቃን ቋንቋዎች እ.ኤ.አ 1955 ዓ.ም ባደረገው ምደባ የአንዱ ዘርፍ አፍሮ-እስያ የሚገኘውና ምንጩ ኢትዮጵያ መሆኑን እንዲሁም ሌሎች የአፍሪሲያ ቋንቋ ቤተሰብ ተመራማሪዎች እነ ጄ ሁስዶን (Geolingustic evidence for Ethiopian Semitik Prehistory. Abbay No 9 (1978), PP. 71-72) ወዘተረፈ እንዳረጋገጡት በኢትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ከቅደም ታሪክ በፊት ቢያንስ 2ሺህ ዓመታት በላይ ሴማዊ ቋንቋ መነገሩ ተረጋግጧል። በመሆኑም አገውኛ፣ ግዕዝ፣ ዐማርኛ፣ ጉራግኛ፣ ጋፉትኛ በዚሁ ስፍራ በአፍሪቃ የስምጥ ሸለቆና የኢትዩጵያ አምባዎች የተፈጠሩ ናቸው። እንዲያውም የጉራጌኛ ቋንቋዎች የቅድመ ሴማዊ መነሻ (proto semitic) ምንጮች እንደሆኑ ተገምቷል። (Appleyard, 2003)

ዘረኞች የአክሱምን ጥንታዊ ሥልጣኔ ዘመናት እጅግ በጣም ቀናንሰው በአራተኛው ክፍለ ዘመን ተጀመረ እያሉ ለፈጠራ ውሸታቸው እንዲስማማ አድርገው ቀምረውታል። ነገር ግን የአረብ ሠርፀ ምድር ጥናት ሊቅ የሆኑት ወይዘሮ ጃክሊን ፒረን (1956) በትክክል እንዳስቀመጡት በተቃራኒው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ወደ አረብ የመን እንደተሻገረ፣ የሳባ አሰልጣኞችን ቀይ ባሕርን ተሻግሮ በሰሜን ኢትዮጵያ የመስፈር ተውኔት የነ ኮንቲ ሮዘነና ብጤዎቹን ተረት- ተረት በተጨባጭ ሰነድ በጊዜና በስፍራ ለይተው ዘቅዝቀውታል።

ያውሮፓ ዘረኞች ተረት ባፍጢሙ ተደፍቷል። ከፐረነም ሌላ ምሁር ሮጀር ሽናይደር የተባሉት በኢትዮጵያ ምድር የተገኙት የሳባ ጽሑፍ በየመን ከተገኙት ጋር በዕድሜ እንደሚበልጡ እንጂ እንደማያንሱ አረጋግጠዋል። ለምሳሌ በሰሜን ኢትዮጵያ ጥንታዊ ከተማ የሃ የተገኘው የጽሑፍ ሰሌዳ በየመን ከተገኙት ሁሉ በዕድሜ ይበልጣል። (Encyelopaedia Brititanica, Cambridge 1911, Volume 24, P.628)

ኢትዮጵያዊው ሊቅ አስረስ የኔ ሰው ‹‹ግእዝ የካም መታሰቢያ›› በተሰኘው ርእስ የዘረኞች ሴራና ተረት-ተረት የሳባውያን የአሰልጣኝነት ተልዕኮ በአበሻ ምድር ውድቅ አድርገውታል። በደቡብ አረቢያ የሚገኙት ሐውልቶችና የጽሑፍ ሰሌዳዎች በኢትዮጵያ ነገሥታት ግዛታቸው የተመዘገቡ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። የሳባ ፊደልና የሳባውያን ያሰልጣኝነት ተልዕኮ በአፍሪቃ ልፈፋ የጥቁርን ሕዝብ ታሪክና ሥልጣኔየለሽ ለማስመሰል የተሸረበ ያውሮፓ ቅኝ ገዥ ተስፋፊዎች ሴራ መሆኑን አስምረውበታል።

ስለሆነም ወደ ኢትዮጵያ ምድር ከደቡብ አረቢያ የፈለሰ ‹አበሻ› የሚባል ነገድ የለም። ይልቅስ በተቃራኒው በዘመነ አክሱም አበሾች በየመን ስለመስፈራቸው በታሪክ ተመዝግቦ ይገኛል። የኢትዮጵያን ምድር በጥንት ዘመን አገሩ ፑንት፣ ሕዝቡን ደግሞ አበሻ ተብሎ የሚጠራውና የሚታወቀው በምድረ ግብፅ የፈርኦን ሥርዎ መንግሥት ታሪክ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ መሆኑ ቀደም ብሎ ተገልጿል።

ዐማርኛ የግዕዝ እኽት

ያማርኛ ቋንቋ የግእዝ ልጅ ነው ተብሎ በቤተ ክህነት ሰዎችና አንዳንድ የቋንቋ ሊቃውንት ሲነገር ቆይቷል። ዳሩ ግን መቼ እንደተጀመረ ጊዜውን ለይተው ሳያሳውቁ ዐማርኛ በላስቶች ዘመነ መንግሥት ከብዙ ዓይነት ቋንቋ ተመርጦ የመንግሥት ቋንቋ እንደሆነና ‹ልሳነ ንጉሥ› መባሉን ይገልጻሉ።

የቤተ መንግሥቱ የመነጋገሪያና የሕዝቡ መግባቢያ ቋንቋ ዐማርኛ ሲሆን፤ ግእዝ ግን የሥነ ጽሑፍና የቤተ ክህነቱ ዋና ቋንቋ ሆኖ እስከ 19ኛ ክፍለ ዘመን መቀጠሉ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም ግን የቤተ መንግሥቱ ዜና መዋዕልና ታሪክ እንዲሁም የክርስትና ሃይማኖት መገልገያ የነበረው ግእዝ ከዳግማዊ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ ዐማርኛ እየተካው እንደመጣ ይታወቃል። ቀደም ብሎም የግእዝ ቅኔና ሰዋሰው ትርጉም ማስተማሪያው ቋንቋ ዐማርኛ እንደነበር ሊቀ መዘምራን ሞገስ ዕቁብ እግዚ (1961 ዓ.ም) ዘግበውታል።

ብዙ የቋንቋ ሊቃውንት ለምሳሌ ዲልማን፣ ሮዲጀር ወዘተረፈ ዐማርኛ የግእዝ የቅርብ እኽት እንጂ ልጅ እንዳልሆነ ጽፈዋል። ይህም ትክክል ነው።

የዐማርኛ ቋንቋ ባህርይ ከአገውኛና ሌሎች መሰሎች ጋር 70 በመቶ እጅ ይዛመዳል።

የኢትዮጵያን ሕዝብ ሴማዊና ካማዊ ብሎ መከፋፈል የአውሮፓውያኖች የቅኝ ገዥነት ተስፋፊዎችና ከፋፍለህ ግዛ ስልት ነው።

በሃይማኖት ሳቢያ የመጽሐፍት ቅዱሱን የብሉይ ኪዳን ዘፍጥረት የጐሳዎች ትውልድ ሐረግ ትረካ ማለትም የኖህን ሦስት ልጆቹን የካም፣ የሴምና የያፌትን ትውልዶች አስመልክቶ በቋንቋና የጎሳ ጥናትና ምርምር ሽፋን የኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ነገዶችና ቋንቋቸውን የሚከፋፍሉበት ዘዴ ፍጹም የተዘባረቀና የተወናበደ ሆኖ ለፖለቲካ መሳሪያነት በጥንቃቄ ታስቦኖ ተሰልቶ የተደረገ እንደሆነ ግልጽ ነው። ነገር ግን በኢትዮጵያ ባሕልና እምነት ከጥፋት ውሃ በፊት የኦሪ ወይም የአራም ነገድ ከ4470 እስከ 3244 ዓ.ዓ ከኖረ በኋላ የነገደ ካም በኢትዮጵያ ከ2635 እስከ 1013 ዓ.ዓ ሲገዙ መኖራቸው ይተረካል። ከሁሉም በላይ ግን የግእዝ ቋንቋም በክብረ ነገሥት ሆነ በአንቀጸ ሃይማኖት ከቤተ ካም ግን እንደሆነ ተመዝግቧል። አለቃ ታዬ የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ (አስመራ 1920) በተባለው መጽሐፋቸው ለምሳሌ ምዕራፍ 6 ላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ዋና ባላባቶች የሴም ዘሮች 7 ወገን ናቸው። እነዚህም አማራ፣ አገው፣ አስገዴ፣ ትግሬ፣ በቅላ፣ በደውና ሐባብ ናቸው።

በኢትዮጵያውያን ባሕል ነገደ አገው ሴማዊ ነው። ግእዝ፣ ሳባ፣ ቅብጥርስ ወዘተረፈ ሁሉ ኩሻዊ ቋንቋዎች ናቸው። ስለሆነም የኢትዮጵያን ቋንቋዎች ‹‹ሴማዊና ኩሻዊ›› ብሎ መሸንሸንም ፖለቲካዊ ነው።

ታዲያ የመምሩ ሚስት አወቅሽ አወቅሽ ቢሏት መጽሐፍ አጠበች እንዲሉ ምድረ የቋንቋ ሊቅ ተብዬ ጽዩናውያን ዘረኞች እነ ሊዎን በንዲርና ግብረ በላዎቹ አገር በቀል ጋጋኖዎች እነ ኃይሉ ፉላስና (1983) ብጤዎቻቸው ሁሉ ስለ ዐማርኛ አመጣጥ የቀባጠሩትን መመልከት ያስፈልጋል።

የበንዲር መላምት ዋናው ይዘት ዐማርኛ በ4ኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም መንግሥት ግእዝ ተናጋሪ መኮንኖችና ከአገውኛ ተናጋሪ ብዙ ወታደሮች እንዲሁም ከአባይ ሳሃራዊና ከኦሞዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች ወደ ደቡብ ሲዘምቱ በተደረገው የዝነቃ መስተጋብር (Pidginization) የተገኘ ነው ብለዋል። ያማርኛን ልዩ ባሕርያት ሁሉ ከተጠቀሱት ቋንቋዎች የተዘነቁ ናቸው በማለት አቅርበዋል። ያማርኛን ኢሴማዊነት በዚህ አይነት ከገለጹ በኋላ ደግሞ ዐማርኛ በግድ ሴማዊ አድርገው ይመድቡታል። ለምን?

የሴማዊነት ምደባ ያገኘው ከደቡብ አረቢያ ሥልጡን ሳባውያን ሴማዊ ቋንቋ፣ ፊደል፣ ሃይማኖት፣ ግብርና፣ ሕንፃ ግንባታ ወዘተረፈ ይዘው ቀይ ባሕርን ተሻግረው ጨለማውንና ኋላ ቀር ሥልጣኔ የለሹን ጥቁር አፍሪቃን አሰለጠኑት፣ ወይም ሰፍረው ቅኝ አደርጉት ከሚለው የዘረኞች ርዕዮት ነው። እንደሚናፈሰው በእርግጥ ሳባዊያን በአፍሪቃ ስልጣኔ አምጪ ከሆኑ ለምን በመርዌ፣ በበርበራ፣ በዘይላ፣ በሞቃዲሾ፣ በሞምባሳ፣ በዛንጅባር ወዘተረፈ የሳባውያን ሕንፃ፣ ፊደል፣ ሃይማኖት፣ ግብርና ጥንታዊ ቅርሳ- ቅርስ አልተገኘም።

አክሱምን ብቻ ለይተው የመረጡበትና በዚያ ሰፈሩ የተባለበት የፈጠራ ውሸት ምክንያቱ በኢትዮጵያ ከየመን የቀደመ፣ ከጥንት ግብፅና አፍሪቃ ጋራ የተዛመደ ሥልጣኔ ሳያቋርጥ በመገኘቱ ብቻ ነው።

በዚህ ዓይነት በግእዝ ቋንቋም ላይ የሚታየው ‹‹ኢሴማዊነት›› በአፍሪቃ ምድር ከኩሻዊ ቋንቋ ጋር ስለተዘነቀ ነው ይባላል። ይህም ማወናበጃ የግእዝን ቀዳሚነትና አፍሪቃዊነት ለመሸፈን ታስቦ ነው። ግዕዝና ዐማርኛ አረብኛንና እብራይስጥን፣ ሱርሱርትን፣ ከለዳዊን ይቀድማሉ።

የአፍሮ እሲያ ቋንቋ ምንጭ አፍሪቃ ነው። የደቡብ አረቢያም የአፍሪቃ ክፍል የኢትዮጵያ ጥንታዊ ግዛት ነበር።

የአረብኛ ፊደል ከግዕዝና ከሳባ ጋራ ምንም ዝምድና የለውም። ያረብኛ የጽሑፍ ሰነድ ሰሌዳ የተገኘው በ512 ዓ.ም መሪ ከተባለው ከደማስቆስ በስተደቡብ ምሥራቅ ነው። የእብራውያን የሙሴ ሕግና ሃይማኖት በቃል ብቻ ሲተላለፍ ቆይቶ በአክሱም ዘመነ መንግሥት በአምስተኛው ክፍለ ዘመን ነው ይይሁዲዎች ታልሙድ በጽሑፍ በፍልስጥኤምና በፋርስ ግዛት ውስጥ የተከተበው። የእብራይስጥ ቋንቋ አናባቢ ምልክት ያገኘው በ9ኛው ክፍለ ዘመን የአክሱም መንግሥት በዘላን ቤጄዎች ተወሮ ከወደቀ በኋላ ነው።

ግእዝ ማለት ቀዳሚ አንደኛ ነው፤ ፊደሉም እንዲሁ ቀዳሚነት ያለው ከጥንት ሂሮግሊፕስ በቀጥታ የወረደ እንጂ ከሳባ ተብዬ የተቀዳ አይደለም። በተቃራኒው ሳባ ከግእዝ ፊደል የተወረሰ ነው።

በየመን የነበሩት ሳባውያን ሚናናውያን ሒማራውያን ሁሉ ከነገደ ኩሽ ወገን የሆኑ በቋሚ ሰፋሪነት በግብርና የሚተዳደሩ ነበሩ እንጅ ዘላን ሴማዊ ጎሳዎችና ቋንቋ ተናጋሪዎች አልነበሩም።
ጋንች.
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 96
Joined: Fri Dec 16, 2011 6:25 pm

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 1 guest