የደራሲው ስቃይ

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

የደራሲው ስቃይ

Postby Jossy1 » Mon Nov 25, 2013 8:45 am

በጠዋቱ ያነቃው የሞባይሉ ጥሪ ነበር:: ከእንቅልፉ ጋር እየታገለ ጥሪውን ተከትሎ በዳበሳ ስልኩን አነሳው

<<ሄሎ..>> አለ እንቅልፍ ባደከመው ድምፅ
<<የደላህ ነህ ወንድሜ:: አገር ምድሩ ነቅቶ ይቦጭቅሀል አንተ እንቅልፍህን ትለጥጣለህ>> የቅርብ ጓደኛው ደጀኔ ነበር የደወለው::
<<ተኝቻለሁ እኮ ደጁ... ምንድን ነው በጠዋቱ የምትረብሸኝ...?>>
<<አንተ ነህ እኮ አገር የረበሽከው:: እቤት ከሆንኩ አሁኑኑ እመጣለሁ::>> ብሎ ጆሮው ላይ ዘጋበት::

ያሬድ እየተነጫነጨ ድጋሚ ለመተኛት አልጋው ላይ መገላበጥ ጀመረ:: እንቅልፍ ግን ድጋሚ ሊወስደው አልቻለም:: ከአልጋው ላይም መነሳት ከበደው:: ማታ አብዝቶ የጠጣው ጅን ጭንቅላቱን በጠበጠው:: እራሱን እየወቀረ ህመም ሆነበት:: ካልተኛ ደግሞ ህመሙ እንደማይበርድለት ስለገባው ደጀኔን ደጋግሞ እየረገመ ለመተኛት ሞከረ:: አልቻለም::

ሲተኛ ስልኩን መዝጋት ውይም ድምፁን ማጥፋት አይወድም:: ማንም ሰው ያለምክንያት አልባሌ ሰአት ላይ አይደውልም የሚል እምነት ስላለው ነው ስልኩን የማያጠፋው:: የደጀኔ መደወል ግን አናደደው:: አጥፍቼ በተኛሁ ኖሮ ብሎ እንዲያስብ አደረገው:: ሰአቱን ሲመለከት ከጠዋቱ 4.30 ሆኗል:: ማታ 9.00 ላይ ነበር ከጓደኖቹ ጋር ሲጠጣ አምሽቶ ወደ ቤቱ የገባው:: አልጋው ላይ ቢገላበጥ ; ራሱን እያባበለ ለመተኛት ቢሞክር አልሆነለትም:: ቢጨንቀው እንደምንም ከአልጋው ተነስቶ ወደ ሽንት ቤት ሲሄድ በሩ ተንጓጓ:: ደጀኔ ነበር::

<<አንተ እንቅልፍ የለህም እንዴ? ለምንድን ነው በጠዋቱ ምትረብሸኝ?>> አለው በሩን ከከፈተለት በኋዋላ

<<ይሄን ጋዜጣ አንብበው::>> ብሎ ሲሰጠው ተቀብሎት ወንበር ላይ ወርውሮት ወደ መፀዳጃ ቤት ሄደ::

<<ልክ ነህ መጀመሪያ ጣጣህን ብትጨርስ ይሻላል>> አለ ደጀኔ የፌዝ ሳቅ እየሳቀ:: ያሬድ ከሽንት ቤት እስኪመለስ ደጀኔ ሶፋው ላይ ተቀምጦ ይቁነጠነጣል:: የያሬድን ስሜት ጋዜጣውን ካነበበ በኋላ ለማወቅ ጓጉቷል::

<<ምንድን ነው በጠዋቱ ያመጣህ?>> ብሎ ጠየቀው ደጀኔን
<<ይሄ ነው ያመጣኝ?>> ብሎ ጋዜጣውን ከወንበሩ ላይ አንስቶ አቀበለው::
<<ደግሞም ምን ተፈጠረ በዚች መከረኛ አገር ላይ>> እያለ ጋዜጣውን ተቀብሎት ተቀመጠ
<<ስታነበው ምን እንደተፈጠረ ትረዳለህ>>

ያሬድ ጋዜጣውን ሲዘረጋ የራሱን ፎቶ በትልቁ ከአንዲት ሴት አጠገብ ተመለከተ:: <<ደግሞም ፎቶዬ እዚህ ጋዜጣ ላይ ምን ያደርጋል:: እቺስ ሴት ማነች?..... እንዴ!..... አውቃታለሁ... ምን ተፈጠረ!>> ብሎ ግራ በመጋባት አንዴ ጋዜጣውን ቀጥሎ ደጀኔን እያየ ጠየቀው::

<<ፎቶህ ላይ ከምታፈጥ ዜናውን አንብበው>> ሲለው ጋዜጣውን ማንበብ ጀመረ::

ቀስ በቀስ ፊቱ መለዋወጥ ጀመረ:: በድንጋጤ ከተቀመጠበት ወንበር ተነስቶ ዜናውን ደጋግሞ አነበበው:: የሚያነበውን ማመን አቃተው:: ከዚያም ደጀኔን እያየ <<እቺ ልጅ.... እቺ ልጅ..... እውነት ራሷን አጠፋች!!!!!? ወይኔ እዳዬ...!>> ሶፋው ላይ ዘፍ ብሎ ተቀምጦ ጭንቅላቱን በሁለት እጆቹ ያዘ:: ያነበበውን ዜና አምኖ መቀበል አቃተው:: እንዳቀረቀረ ሟች ፊቱ ድቅን ብላ መጣችበት:: ፀፀት ውስጡን አነደደው:: ጋዜጣውን አንስቶ ወረወረው:: መሬቱ ላይ እንዳቀረቀረ እንባዎቹ ዱብ ዱብ አሉ:: ደጀኔ ያሬድ ፊት ላይ ሀዘን; ፀፀት ከድንጋጤ ጋር ነግሰው ሲያይ ደነገጠ:: ዜናው ሊያሳዝነው እንደሚችል ቢገምትም ይሄን ያህል ያስደነግጠዋል ብሎ አልጠበቀም::

ጋዜጣው በፊት ገፁ ላይ <<ፍለጋ በተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ አጨራረስ ያልተደሰተችው ወጣት ርብቃ ተሾመ ራሷን አጠፋች::>> የሚል አርእስት በትልቁ ተፅፏል:: ከስሩ የፍለጋ ድራማ ደራሲን የያሬድ አለሙ ፎቶ እና የሟች ርብቃ ተሾመን ፎቶ አስቀምጧል:: ከአርእስቱ ስር በዝርዝር ስለ ህይወት ታሪክዋ ሲተርክ ; ሟች ርብቃ በትምህርትዋ ጎበዝ በባህሪዋ ምስጉን ; ለቤተሰቦችዋ ደግሞም ብቸኛ ልጅ እንደሆነች ያትታል::
ራስዋን መርዝ ጠጥታ ካጠፋች በኋላ መኝታ ቤትዋ ውስጥ በተውችው ደብዳቤ ላይ <<የተፈጥሮ ጭካኔ ሳይበቃ ; ሰዎችም ራሳቸው በፈጠሩት ጥሩ ገፀ-ባህሪ ላይ ሲጨክኑ ማየት እጅግ ልብ የሚሰብር ነው:: በተለይ የሚወዱት ደራሲ ; ተፈጥሮን እና ፍቅርን ያሰተማረ ደራሲ; ውስጤ ሰርፆ የገባውን ጥሩ ገፀ-ባህሪ ላይ ርህራሄ ማሳየት አለመቻሉ አሳዝኖኛል:: ሀዘኔን መርሳት ስላልቻልኩ መገላገሉን መረጥኩ:: አንድ ደራሲ ስራዎቹ ህዝቡን ለማስተማር ብቻ ሳይሆን ለማስደሰት እየፃፈ እንዴት ተወዳጅን ነገር አጨራረሱን ላለማሳመር እምቢ ይላል? መልሱን ለደራሲው ትቻለሁ:: ድርሰት ምናባዊ እንደሆነ ቢገባኝም <ፍለጋ>ን ግን እንደምናብ አላየውም:: ለእኔ ህያው የሆነን ነገር ማጣት ከባድ ስለሆነብኝ መገላገልን መረጥኩ:: ወላጆቼ ልለያችሁ ባልፈልግም ስቃዬን መቻል ስላልቻልኩ መገላገልን መረጥኩ::>> ይላል ጋዜጣው ላይ በአጭሩ በርብቃ የተፃፈውን ደብዳቤ ሲጠቅስ::

ያሬድ ሀዘን እና ድንጋጤ አደንዝዞት በሀሳብ ወደ ኋላ ተመለሰ::

******************************

አዘውትሮ ቡና ከሚጠጣበት ካፍቴሪያ ብቻውን ቁጭ ብሎ መፅሀፍ ሲያነብ <<ሰው አለው እዚህ ጋር?... መቀመጥ ይቻላል?>> የሚል ድምፅ ከንባቡ አነቃው:: ልጅ እግር ጠይም ሴት ከፊቱ ቆማለች::

<<ማንም የለም ተቀመጪ::>> ብሏት ወደ ንባቡ ተመለሰ:: ከጥቂት ደቂቃ በኋላ <<ያሬድ ነህ አይደል?>> አለችው አጠገቡ የተቀመጠችው ልጅ

<<አዎ ነኝ>> አላት ቀና ብሎ በፈገግታ
<<የድርሰቶችህ አድናቂ ነኝ:: ርብቃ እባላለሁ::>> ብላ እጇን ዘረጋችለት:: ፈገግታውን ሞቅ ባለ ፈገግታ እየመለሰ <<አመሰግናለሁ::>> ብሎ ጨበጣት::

<<አንተን ለማግኘት ያልገባሁበት ቦታ የለም:: አንከራተኸኝ በመጨረሻ አገኘሁህ::>>

<<አመሰግናለሁ:: ስለተንከራተትሽ ይቅርታ:: ግን እንዴት አገኘሽኝ?>> አላት:: በድርሰቱ ምክንያት በአካል ብዙ ሰዎች አያውቁትም:: ለህትመት ባበቃቸው መፅሀፎች ላይ የሚለጥፈው ፎቶው ወጣት እያለ የተነሳውን ነው:: ከዚያ በኋላ ፀጉሩ ተመልጧል:: ወፍሮ ቅላቱ ደብዝዞ ፊቱ በመጠጥ ወይቧል::

<አንተን በቅርብ የሚያውቅ ሰው አግኝቼ ነው እዚህ የመራኝ::>>

<<ሻይ ቡና ልጋብዝሻ! ምን ይምጣልሽ?>> ብሎ አስተናጋጅ በጭብጨባ ጠራ::

<<የመጣሁት አንድ ነገር ልጠይቅህ ነው?>> አለችው ፊትዋን ቅጭም አድርጋ

<<ትችያለሽ:: ምንድን ነው?>>

<<ፍለጋ ድራማ ላይ ያለውን ሲራክ ከሞት እንድታስነሳው ነው::>> ስትለው ደነገጠ:: የግርምት ፈገግታ ፈገግ ብሎ

<<ድራማው ካለቀ እኮ ሶስት ሳምንት ሆኖታል:: ያማ አይቻልም::>>

<<ለምን አትችልም:: ዝነኛ ደራሲ ነህ:: አንተ ከፈቀድክ አያቅትህም::>> አለችው ኮስተር ብላ

<<ከስነ-ምግባሩ ውጪ ነው:: ድራማው አልቋል::>>

<<መሞት ያልነበረበትን ሰው ነው የገደልከው:: ለምን ያን ያህል ጨከንክበት ግን!?>> አለችው የሚወቅስ በሚመስል አስተያየት እያየችው

<<በድርሰት ላይ happy ending ብዙም ደስ አይለኝም::>>

<<ለምን?>>

<<ተፈጥሮ እንደዛ አይደለችማ:: ሁሉም ነገር በበጎ አያልቅም:: ድርሰት ደግሞም የነባራዊው አለም ነፀብራቅ ስለሆነች መፃፍ ያለበት እንደ ነባራዊው ሀቅ ነው::>>

<<አንተ እንዳልከው ተፈጥሮ ሁሌም ላታስደስት ትችላለች:: ምክንያቱም በአምላክ ተፅእኖ ስር ነው ያለችው:: እኛም ምንም ማድረግ አንችልም:: ግን! አንተ ድርሰቱ በተፅእኖህ ስር ስላለ ;ፈጣሪውም ስለሆንክ ሲራክን ድጋሚ እንድታስነሳው እፈልጋለሁ:: ሲራክ ለእኔ ሁሉ ነገሬ ሆኗል:: እሱ ሞቶ እኔ መኖር አቅቶኛል:: እንደ ክርስቶስ አስነሳው:: የሲራክ እግዚአብሔር አንተ ስለሆንክ አሁን ከሶስት ሳምንት በኋላ አስነሳው:: ያሬድዬ አሺ በለኝ::>> ብላ እንባ በሞላቸው አይኖችዋ እያየችው ተማፀነችው::

ያሬድ ሁኔታዋ አሳዘነው:: ግን ከፈጠረው የፍለጋ ድራማ ገፀ ባህሪ ጋር ሳይሆን ከተዋናዩ ጋር ፍቅር ይዟት ይሆናል ብሎ አሰበ::

<<ሲራክን ሆኖ የተወነው ዳንኤል እኮ በህይወት አለ:: የሚቀጥለውን ድራማዬ መሪ ተዋናይ ራሱ ዳንኤልን ስለማደርገው ሲራክን ያኔ ታገኚዋለሽ::>> አላት

<<ዳንኤልን አግኝቼ አናግሬዋለው:: አንተን የት እንደማገኝ የጠቆመኝ አሱ ነው:: እኔ የምፈልገው የፍለጋውን ሲራክ ነው:: ከየትኛውም ድርሰቶችህ ገፀ-ባህሪ በላይ እኮ ነው ሲራክ:: በፍፁም መሞት የለበትም! በፍፁም>> ኮስተር ብላ አለችው::

<ልጅትዋ አምርራለች> አለ ለራሱ እና እንዴት እንደሚያስረዳት ካሰላሰለ በኋላ

<<ይኸውልሽ የኔ እህት.... ይቅርታ ስምሽን ረሳሁት....>>
<<ርብቃ>>
<<ይኸውልሽ ርብቃ..... ድራማው በጣም ስለረዘመ ቶሎ መጠናቀቅ እንደነበረበት የቴሌቪዥን ጣቢያው ባለቤቶች ማሳሰቢያ ስለሰጡን የነበረን አማራጭ ድርሰቱን ማሳጣር ነበር:: ለድርሰቱ አጨራረስ የመረጥኩት ትራጀዲ ቢሆንም አሁን አልቋል ድራማው:: ፋይሉ ተዘግቷል:: ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም::>>

<<ፍለጋ-2 ብላችሁ እንደገና ጀምሩት:: በህዝብ ዘንድ እስከተወደደ ድረስ ተንዛዛ አልተንዛዛ ጣቢያው ምን አገባው!? በማስታወቂያ ገንዘብ እያፈሱበት አይደለ እንዴ?>>

<<እንደዛ ሳይሆን ሌላ ድርሰት ; ሌሎች ደራሲዎች እና ሌሎች ተዋናዮች እድል ማግኘት አለባቸው:: በቀና ታስቦ ነው ድራማው እንዲያልቅ የተደረገው::>>

<<ሌላ ቀን ሌላ አዲስ ድራማ ማቅረብ አይችሉም? ቴሌቪዥኑ እንደሆነ ህዝቡን ያሰለች ፕሮግራመ 24ሰአት ሲቀርብበት ነው የሚውለው:: አሁን ለዚህ መላ ጠፍቷቸው ነው?>>

<<ይኸውልሽ ለመዝናኛ ፕሮግራም ጣቢያው የመደበው ሰአት አለ:: ለሌሎች ፕሮግራሞችም እንደዚሁ:: ጣቢያው ከሁለት ተከታታይ ድራማ በላይ ለማቅረብ የሚችል በቂ የመዝናኛ ሰአት የሉትም::>>

<<የማታውን ፕሮግራም በሌላ ቀን ከሚደግሙት ለሌላ ድራማ ሰአቱን መስጠት አይችሉም? መቼም አመል ሆኖ ጥሩ ነገር እንዲበረክት ስለማይፈግ ነው እንጂ ዘዴስ አልጠፋ!... ሲራክ ግን እንዲነሳ እፈልጋለሁ.... ካለ ሲራክ መኖር አቅቶኛል:: ቢያንስ አስነሳው እና ሳትገድለው ጨርሰው!!... ያሬድዬ ደራሲ ስለሆንክ የሰው ሀሳብ ይገባሀል:: ሲራክን ገድለኸው እኔ መኖር አልችልም:: እውነቴን ነው:: አስብበት:: ከሳምንት በኋላ መጥቼ እጠይቅሀለሁ::>> ብላ ተነስታ ቻው ሳትለው ሔደች:: የመጣላትንም ሻይ አልጠጣችውም::

ቀልዷን እንዳልሆነ አውቋል:: ከሁኔታዋ እንዳመረረች ገብቶታል:: የግርምት ሳቅ ስቆ መፅሀፉ ላይ ድጋሚ አቀረቀረ::

ይቀጥላል
Freewill
Jossy1
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 215
Joined: Sun Aug 28, 2005 6:37 am
Location: qatar

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 4 guests