ያ ዘመን ፨ የመስቀል አደባባይ መዘዝ

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

ያ ዘመን ፨ የመስቀል አደባባይ መዘዝ

Postby password » Thu Oct 28, 2021 6:24 am

ያ ዘመን

ልቦለድ 1988

ምዕራፍ 1

ነሐሴ 1968 አ.አ

መስቀል አደባባይን ወደ አብዮት አደባባይነት ለመለወጥ የቤርቲኖ ህንጻና መንገድ ግንባታ ኩባንያ ሰራተኞች ደፋ ቀና ይላሉ። የክብር ትሪብዮኑን ሥፍራ ገንብተው ጨርሰዋል። አደባባዩን አስፍተውታል። የህዝብ መቆሚያና መቀመጫ እንዲሆን የተከለለውን ቦታ ደረጃ አውጥተውለታል። የሰልፍና የልዩ ልዩ አብዮታዊ ትርኢት ማሳያ እንዲሆን የተከለለው ቦታ ደግሞ አስፋልት እየለበሰ ነው። ግንባታው ግን ለመስከረም ሁለት ቀን በዓል የሚጠናቀቅ አይመስልም፥ ገና ብዙ ይቀረዋል። ካላለቀ የቤርቲነኖ ነገር አለቀ ማለት ነው። አሻጥረኛ ኮንትራክተር!

እችኑ አውቆ ቤርቲኖ ወደ ትውልድ አገሩ ሹልክ አለ የሚሉ ብዙ ሲሆኑ ውስጥ አዋቂዎች የሚያወሩት ሌላ ነው። ቤርቲኖ በርግጥ ወደ ትውልድ አገሩ ሄዷል ግን የሄደው ታምሞ እንጅ ፈርቶ አይደለም ነው የሚሉት። እዚህ አዲስ አበባ ያልደረሰበት ሃኪም ቤት አልነበረም። የሃበሻ ህክምና ሳይቀር ሞክሯል ነው የሚባለው ግን የሚፈውሰው አላገኘም።

አንዳንድ ሰዎች የበርቲኖ መታመም ሳይሆን የታመመበት ቀን ነው በጣም ያስገረማቸው። ወርኃ ሰኔ መሃል ላይ ነበር የታመመው፣ ያን ዕለት ነበር ቤርቲኖ መስቀል አደባባይን ወደ አብዮት አደባባይነት ለመቀየር ከደርግ ባለስልጣኖች ከነሻለቃው መንግስቱና ከመኢሶን ማለትም ከመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ አመራር አባላት ጋር ኮንትራት የተፈራረመው። ማታ ላይ ሆዱ ሲጮህ አመሸ፥ ለሊት ሲያስቀምጠው አደረ። ሰውዬው ከዚያን እለት ጀምሮ ጤና አላገኘም።

ሰው አልሰማ አለ እንጂ፡ መስቀል አደባባይን ሲነካኩ አንድ አባ ሰላማ የሚባሉ ባህታዊ መንፈሳዊ ማስጠንቀቂያ ተናግረው ነበር። በተለያዩ ጊዜያት መጥተው “ተው! አንዲት ጠጠር እንዳታነሱ ወዮ! ጉዳችሁ ይፈላል። መስቀል ቤዛዬ እያለ ህዝበ ክርስቲያን ጌታውን የሚያመሰግንበትንና ፀጋና በረከቱን የሚቀበልበትን የተቀደሰ ቦታ ስድስት ስልሳ ስድስትን አታከብሩበትም። እንዳትነኩ!” በማለት አስጠንቅቀው ነበር። ቢጮሁ ቢገዝቱ የሚስቅባቸው እንጂ የሚሰማቸው አላገኙም። “ተው በህዝብ ላይ መዓት ታስወርዳችሁ። ይህን የተቀደሰ ቦታ የሚነካ ሁላ ጉዱ ይፈላል! ይቀሰፋል!” እያሉ በፖሊስ ታፍሰው እስከተወሰዱበት ቀን ድረስ ያለማቋረጥ ጮኸዋል። የሰማቸው ግን አልነበረም።

ባህታዊው አንዳንድ ዘመናይ እንዳላገጠባቸው ሰካራም ወይም እብድ አልነበሩም። የታያቸው ነገር ነበር። ብዙ ሳይቆይ ልክ እሳቸው እንዳሉት በመስቀል አደባባይ መነካት የተቆጣ መንፈስ ተነቃነቀ መሰል የኢትዮጵያን ታሪክ ሰላማዊ ሂደት የሚበጠብጡ አበይት ክንዋኔዎች በተከታታይ ይከሰቱ ጀመር። ከነዚህ ክንዋኔዎች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የሻለቃ መንግስቱ ሃይለማርምን ስልጣን ለመደብ አልያም ሰውዬውን ጨርሶ ከሥልጣኑ ለማግለል በደርግ ውስጥ የተጀመረው እንቅስቃሴ ሲሆን ሌላው የኢትዮጵያ

ሙሉ መጽሓፉን በነጻ ያውርዱ

http://www.babile.wordpress.com
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 330
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 3 guests