ላይመለስ ትላንት ሄዶ
ቀን ሲለወጥ ጎህን ቀዶ:
ፍንትው! ፏ! - ብላ ጸሃይ
ሞቆ ሲደምቅ - ምድር ሰማይ:
እኔ ገና’አንጎላጃለሁ
በእንቅልፍ ልብ’ናውዛለሁ
ሳልነቃ - እወዘወዛለሁ
በግብዳው አዛጋለሁ::
የተጨናበሱ አይኖቼን
እያሻሸሁ በእጆቼ
እወጣለሁ ተጎትቼ
ከአልጋዬ ተነስቼ::
ከዚያም ተደናብሬ
እያሸሁ ጸጉሬን - ተንጨብርሬ
እየተማታ እግሬ ከግሬ:
ጠጋ ነዋ ከመስኮቱ
ደጅ ደጁን ለመመልከቱ::
ስምገው በረዥሙ
የጥዋት አየር አይ መጣሙ
ንጽህናው ማስገረሙ::
ከዛፍ ላዩ ጎጆ መድረክ
ጣፋጭ መዝሙር ሲፈበረክ:
የወፎቹን ኦርኬስትራ
ያለዳንስ ያለዳንኪራ:
ያለጭብጨባ ያለ እስክስታ
ሳጣጥመው በዝምታ:
ጀመረች ልቤ ልትጨፍር
ደስታን ልትረጭ በደሜ ስር
መላ አካሌን ልታነዝር::
የጽጌረዳ መአዛ
አፍንጫዬን እያዋዛ:
ሆነኝ የጥዋት ፍስሃ ደስታ
ቀን አዋይ ስንቅ - ጣፋጭ ስጦታ::
ሰማዩን ብዬ ቀና
ሳይ ጥራቱን አንደንቅና:
መደመሜ ሳያልቅ ገና
ሃሳቤ ይዋልልና
ዱካሽን ይከተልና
ይፈልጋል ያንቺን ፋና
የወሰደሽን ያን ጎዳና::
ሲጥለቀለቅ አዕምሮዬ
ባንቺ ሃሳብ ህሊናዬ:
እኔነቴን እረሳና
ውበትሽን አልምና:
ድው ድው ትላለች ልቤ
ትረግጣለች አንዳች ጮቤ
ትመታለች የደስታ ድቤ::
ከዚያ ታዲያ ምናለፋሽ
መቁነጥነጥ ነዋ መረባበሽ
መጥተሽ እዚህ ባይን እስካይሽ
ከች እስክትይ አቆራርጠሽ
ጠረፍ ድንበሩን አሳብረሽ
በሰማይ ባቡር አየር ቀዝፈሽ::
ውርስ ትርጉም በእድል
(Source: ለጊዜው ያልታወቀ)