ልባቸው እንደ ከበሮ
በትዕቢት ተወጥሮ
ያበሻ ሴቶች ሥራ ዘንድሮ
መሹለክለክ እንደበረሮ::
ጨዋነቱ ተሽቀንጥሮ
በጥብቆ ተወጥሮ
መንከላወስ ተሽቀርቅሮ
እንደ ሥልጣኔ ተቆጥሮ
ብር እንደቢራቢሮ::
በውበት አንደኛ ከሁሉም
የሆኑ ይመስል ባለም
ጉራቸው አያስቀምጥም::
የፍቅር ክቡርነቱ
በጭራሽ የማይገባቸው ከቶ
ናቸው ጥርቅም ያጭበርባሪ
የበሉበትን ወጭት ሰባሪ
መሽቁቅ ሌባ መሰሪ::
አበሣ ነው መቼም ኑሮ
ካበሻ ሴቶች ዘንድሮ::
አለኝ አንዱ - ሞኝ ተላላ
አንጀቱ እርር ብላ
በቁጭት ፍም ተንቀልቅላ
ደሙ በንዴት እየፈላ:
አፉን ሞልቶ ብግን ብሎ
ሴቶቼን አጣጥሎ
ወገኖቼን አቅልሎ::
አንድ አይቶ ባንድ ደንባሪ
ጰርጳራ ቶስቷሳ ፈሪ
ዝንተ -አለም አማራሪ:
መጥፎ ክፉው ብቻ ጎልቶ
ለሚታየው ለዛ ድሪቶ:
አዘንኩለት ለሰውዬው
ማፍቀር ውል ላላለው
መፈቀር ላልታደለው::
ከልቤ በጣም አዘንኩ
ባያገኝ ፍቅር በልኩ:
የምትወደው ስፍስፍ ብላ
ንጹህ አፍቃሪ ሸበላ
ያበሻ ቁም ነገረኛ
የውበት ባለአዱኛ
ጸባየ -ወርቅ መልከኛ:
ለኑሮዋ ተጣጣሪ
ኮስታራ ሰርታ አዳሪ
ወይ ቆራጥ ትጉህ ተማሪ
ታታሪ እጅግ ታታሪ
ባለማግኘቱ I'm sorry!
ያ ፈገግታዋ ደማቁ
የኔ ቆንጆ ጠይም ዕንቁ
አትጠገብ እሷ ታይታ
ያበሻ ሴት የኔ ሽታ
ልዩ ቀለም ቸኮላታ
ሰላሜ እሷ ናታ::
አይኗን ሳየው ከፊት ለፊት
የታዘብኩትን ልዩ 'ውበት
ሳልቀንስ የምገልጽበት
ምናለ ቢኖረኝ አስማት::
ምትሀታዊ ቋንቋ ዜማ
ከየታባቴ ላግኝማ:
እንዳሳየው ለዚያ ገልቱ
እንዳድነው ከዕንግልቱ::
ይሄ ደሞ ምን ያወራል ?
በሕልም አለም ይዋልላል
ዝም ብሎ ይቀዣብራል::
የሉም እንዲህ - አይነት ሴቶች
ቢኖሩም በጣም ጥቂቶች
የማይገኙ ሕልም እንጀሮች ::
አውቃለሁ እንደማይጠፋ
ብሎ የሚደነፋ
ጥሩንባውን የሚነፋ::
እኔ ግን እላችኌለሁ
አፍጥጬ እጠይቃለሁ:
ፍጹም 'እንዳ -ትስቱብኝ
አይሞሉም ብላችሁ እፍኝ::
አልቆጥራቸው በበኩሌ
ናቸውና የትዬለሌ::
ለነገሩ ያ አማራሪ
ቦቅቧቃ ፈሪ ፍርፋሪ
እጣ ፈንታው በምርመራ
ከመሰረቱ ቢጣራ
ከርግብግቢቱ አሻራ
የተጻፈለት መከራ
ዳርጎት ነው ጅሎን ለካ
ከአጭበርባሪዋ ጮካ
ከዛች እንክርዳድ አራሙቻ
ስም አስጠፊ ግትቻ
ቅብዝብዝ ሆዳም ሥልቻ::
ሞኞ ታዲያ የኔ ደንዛዞ
ይለኛላ ይቺን ይዞ
ሁሉን በአንድ ላይ ጠርዞ
ያበሻ ሴት ! ውይ ! ጨካኝ አዞ !
ተጻፈ በ እድል
(ቀደም ብሎ በሌላ ገፅ የቀረበ)