by ዋናው » Sun Jul 29, 2012 7:10 pm
ከበርካታ ዓመታት በፊት ከእዚች ገራገር ሃገር ጋር ብቻችንን ሆነን ስንማማል ትዝ ይለኛል እንደትላንትና ሁሉ ቅርብ ሆኖ እስካሁን ይታየኛል:: ግን ዓመታት ነጎዱ...
የመጀመሪያ ቀን ሰላምታ ልውውጤ ውስጥ ሁሉ "...ተቀየርክ አረጀህ አረጅሽ ትልቅ ሰው ሆንክ ሆንሽ..." የመባባሉ ጉዳይ የዕድሜዬን ዘለላዎች እርከን ላይ እንዳፈጥ ጋብዞኛል: በርግጥም ገመድ ሲዘሉ ትተናቸው የወጣናቸው ሕንስቶች ዛሬ በትዳር ውስጥ የራሳቸዉን የኑሮ ገመድ ይዘዋሉ
አዲሳባ ትልቅ የኮንስትራክሽን መንደር ሆና ጠብቃኛለች አስፓልት ይታረሳል ቤት ይፈርሳል አዋራ ከመኪና ጪስ እኩል ይጨሳል የአዲሱ ቤንዚል ሽታ የአዱገነትን ጠረን ቀይሮባታል... በርካታ ፎቆች በቅለዋሉ ቁመታቸው ተመዞ መስተዋት ለብሰው ከማዶና ማዶ ሆነው እርስ በርሳቸው ይተያያሉ አዋራ ለብሰዉም ከፈካችው ፀሃይ ብረሐን ወስደው ሙቀት ይተፋሉ...
ሁሉ ነገር እንግዳ ሆኖብኛል ... አዳዲስ ሰፈሮች አዳዲስ መንገዶች አዳዲስ ብራንድ ተሽከርካሪዎች እንዲሁም አዲስ ትውልድ... የቆመ ቀለጠ የሮጠ አመለጠ ምትለዋ አባባል እንጭጭ እንደሆነች ነበርና አዱገነትን ትቺያት የወጣዉት አሁን ያ ቃል እሁን ሆኖ ሁሉም ይሮጣል... "በጣም ቢዚ ነኝ!" የሚል የኔ ቢጤ ሁሉ ልታገኙ ትችላላችሁ:: ብቻ ሁሉም በፊናው ደፋ ቀና ይላል አላውቅም አልችልም የሚል ቃል ከአፉ የሚወጣ ሰው ማግኘት ይከብዳል ሁሉም ሁሉንም ነገር ይሰራል ይሞክራል::
አዲሳባ ተ'ምቦርቅቃለች ድሮ እምቧይና ሾላ ይብቅልባት የነበረ ጥጋጥጓ ዛሬ በኮንደሚኒየም ቤቶች ጫካ ተውጧላ አዳዲስ ጎረቤቶች አዳዲስ ማሕበረሰብ አዲስ ቀበሌ ውስጥ ትጎራብተው ብራንድ ኒው ጄኔሬሽን ተፈጥሮዋል:: እነኚህ ቀበሌ ውስጥ አዳዲስ ቃላትና አዳዲስ ስራዎች ተፈጥረዋል::
እነኚህ ሰፈሮች ውስጥ ባጃጅ በሶስት እግሯ እየተፈናጠጠች ከመንገድ ዳር እበር ዳር ታደርሳለች እየተገለበጠች ትዘወራለች እየተነዳች ትገለበጣለች ፍንግል ስትል ትንሽ ብረቶቿ እና ነጭ ሸሚዟ አፈር ከመቃሙ ውጪ ምንም አትሆንም:: ጥቂት ከዞርኳቸው ኮንደሚኒየም... ለቡ... ሚኪሊላንድ... ጀሞ... መብራት ኃይል ጥቂቶች ናቸው እነኚህ መንደሮች እንደጥንቱ ጂኦግራፊካል የጥቅም ትሥስር የላቸውም ነዋሪው አፈር ከለበሰ የትላንትና የአፈር ቤቶች ይዞ የመጣው ማንነቱ በዛሬ ፎቅ ውስጥ አልጠቀመዉም:: ግን አዲስ ሕይወት ሀ! ብሎ ጀምሯል
የእርሪ በከንቱዋ ሴተኛ አዳሪ ኮንደሚኒየሞች ውስጥ ወንደኛ አዳሪ ማግኘት አትችልም: የሰንጋተራው እንስራና ጋን ጠጋኝ ዛሬ 'ሚጠግነው ገል አይኖርም... አንዱ አገልጋይ ሌላው ተገልጋይ ሆኖ መንደርን የመጋራት ጉዳይ አሁን የለም ግን ሲሚንቶ ግድግዳ ተጋርተው ይኖራሉ::
ሌሎች አዳዲስ ነግሮች
ድሮ ድሮ አዲሳባ ውስጥ ብዙ ነግሮች አይኖሩም'ንጂ ፌክ ነገር የለም ነበር ለምሳሌ ድሮ መኪና እምብዛም የለም'ንጂ ፌክ መኪና የሚባል ነገር አይታወቅም ዛሬ ስማቸው እንደዓይነታቸው የበዙ መኪናዎች በመዲናይቱ ይታያሉ:: ሴሜትሪካል ያልሆነ መኪና ልታዩ ትችላላችሁ ከኋላው በ BMW ተጀምሮ ከፊትለፊቱ በMERCEDES የሚያልቅ መኪና ታያላችሁ ከሁለቱ አንዱን ስም ስትፈልጉ መኪናው ኋላ ላይ የወንድማችሁን ወይም የእሕታችሁን ስም ልታገኙበት ትችላላችሁ:: ግን ይሄዳሉ ያገለግላሉ ምንም ያገልግሎት አቅማቸው 'ሚፈተሽበት የራሳቸው ዕድሜ ክልል ደርሰው ለመወደስና ለመወቀስ ባይበቁም ክንድ አውጥቶ በቄንት ሚዘውራቸው ጩፌሮች እንዳሸን ናቸው::
ከውጪው መልኩ ያማረ ፎቅ አይታችሁ ውስጡ ስትገቡ ግር ሊላችሁ ይችላል መጠኑ እኩል ያልሆኑ ድረጃዎች ሊያወላክፋችሁ ይችላል... የፀሐይን መውጪያና መግቢያ ያላተኮረ የመስኮት አቅጣጫ ሕንጻ ውስጥ ያልተለመደ አየርና ጠረን ፈጥሮ "ምነው መልክ ብቻ ሆነ" ብላችሁ አሜት ልትጀምሩ ትችላላችሁ... አናቱ ላይ ትኩስ ሲሚንቶ እየፈሰሰበት ምድርቤት ያለው ባንክ ስራዉን ሲያቀላጥፍ በርካታ ቦታ ታያላችሁ:: ሲሚንቶ ጠብ ቢልባችሁ ሚስማር ቂው ብሎ ቢያስደነግጣችሁ ትራንስፎርሜሽን ምትለዋን ቃል እያስታወሳችሁ ታልፋላችሁ... መቼም ኤልሚት(መከላከያ ቆብ) አትጠይቁም::
አንድ ጊዜ የቀለበት መንገድ ሲሰራ ያጋጠመኝ ቻይናው አንጸባራቂ ሰደርያዉን, ብረት ጫማና ኤልሚቱን አድርጎ ሲቆጣጠር የድልድዩን ፌሮ በሽቦ የሚቋጥሩና በዙሪያው ደፋ ቀና የሚሉ ምስኪኑ ያገሬ ባተሌዎች ደግሞ በሲልፐር ጫማና መላጣ ራሳቸዉን አጋልጠው በነተበ ካናቴራ አስተውያቸዋለሁ:: ይህ ግርምቴ የኢትዮጵያን እና የቻይናን አዲስ ፍቅር ምን ይሆን ወደሚለው አሻግሮኝ ከባልንጀሮቼ ጋር ብዙ ተወያየንበት::
አዎ ለውጥ ፈላጊ ነን እና አዲስ ለውጥ በርካሽ ለማግኘት እንዳቅማችን ቻይና ጋር መሄድ (ግድ ብሎናል) <= /የዘመኑ አባባል/ አቅም ኖሮን ወደምሕራቡ ብናቀና ጣጣው ብዙ ነው ኪስም ይጎዳል ቻይና ግን "ስንት ይዘሻል?" ብላ ነውን'ጂ ምትጠይቀው ስለአካባቢ ደሕንነት ስለ ሕዝቦች ምቾት ስለወደፊት ጉዳትና ጥቅም ግድ የላትም::
አሁን አሁን አብሮ የመጣ አንዳንድ ነገር መስተዋል የተጀመረ ይመስለኛል ግን ስሙ "ለውጥ" ይባላል አፍሪካ ውስጥ የራስን ምሶ የሌላዉን ምሶሶ አድርጎ መኖር ለውጥ ተብሎ መነገር ከተጀመረ ቆይቷል... እና አዲሳባም የዛሬ 10 እና 15 ዓመታት የነበረን የራሳችን ስልጣኔ ዛሬ በሌላ ተቀይሯል አንተ ቅደም አንቺ እለፊ ይሄን ልርዳህ ይሄን ላግዝሽ ተባብሎ ችግርን ተናቦ የመፍታቱ ባህላችን ቀርቷል የራስህ ደም አምሳያ የሆነው ዛሬን ጥቅም ካገኘ ደሙን ቀርቶ ሰብህናዉን ሁሉ ይረሳል:: ሃብታሙና ደሃው ተፋጦ ይኖራል ድሮ ባለጸጋው በመስጠቱ እንደሚደሰት ሁሉ ተመጽዋቹም ለባለጸጋው ዕድሜና ጤንነት ይመኝ ነበር... አሁን አሁን ግን ከላይ ያለዉም የታቹን ላለማየት ፊቱን በመኪና መስታወት ጋርዶ ሲሄድ የታቹም "ይድፋው!" ይላል::
ካስደሰቱኝ ለውጦች አንዱ የሬዲዮ ጉዳይ ነው: አዲሳባ ውስጥ ብዙ ዓይነት ኤፍ ኤም ራዲዮዎች አዳምጪያለሁ: ትርካው, ትምሕርታዊ ውይይቱ, ቀልዱ, ሙዚቃው በርካታ ነው እንደድሮው ለፍላፊና አድማጭ ብቻ ሳይሆን ዛሬ ሁለቱም ባንድ መንፈስ ሆነው የማየቱ ዕድል አጋትሞናል:: በርግጥ በርካቶች ቀኑ ሙሉ ስለስፖርት ብቻ ሲዘክሩ ይውላሉ:: እኔም ከንግሊዝ በመምጣቴ ብቻ ስለበርካታ ኳስ ተጫዋቾች ሕይወትና ቤቶቻቸው ተጠይቂያለሁ... ዕድሜያቸው አስራዎቹ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ባብዛኛው በምንፈስ እንግሊዝ ሃገር ውስጥ ይኖራሉ ብል ማጋነን አይሆንም ራዲዮ ቀኑን ሙሉ ስለስፖርት ሳይሆን ስለስፖርተኞቹ የግል ሕይወት ሲሰብክ ይውላል... እናም ላንድ አዲሳባዊ ወጣት ሩኒ... ሚስቱ ምን ዓይነት መኪና እንደምትነዳ ለልደቷ ሩኒ ምን እንዳደረገላት ቤታቸዉን በስንት ብር እንደገዙት ለሆሊዴይ ምን ያህል ፓውንድ እንደሚያጠፉ... ማውቀ ራስን ከዘመኑጋ እንደማራመድ ስልጣኔ ይቆጠራል :: የዳኛቸው ወርቁን አደፍርስ መጽሓፍ አፋልጉኝ ያልኳቸው ወጣቶች አደፍርስ በሚለው ስም ተሳልቀዉብኛል::
እናም ቅኝቴን ልቀጥልና አዲሳባ የአፍርካን ቀንድ አየር እየተነፈሰች በሩቅምስራቅ ጨርቅና ማቅ እያጌጠች እና እያዘነች በዱባይ መስታወት ራሷን እየፎተተች በምሕራባዊ ሕልም ውስጥ ራሷን እየቃኘች ኑሮዋን እየገፋች ነው:: don't mind the dust የሚል ጥቅስ ለጥፋ ውስጥ ድረስ ከርሷን እንዳይ ስትጋብዘኝ የናፍቀኝ ወዟን ለማየት ባለኝ ጊዜ ውር ውርታዬን ቀጠልኩኝ::
እንደ እነአባቱ ልጅ ትላልቅ የ villa ብረትበሮቿ እና ጥርብ ድንጋይ ቤቶቿ ወይም ሃመርና ካዲላክ መኪናዎች ሳይሆን እነሙዘይድ የሚያሽኮረሙሟቸው እንስቶች ዓይኖቼን ሞሉት:: ውበትና ደምግባት ተሸክማ በሴትነቷ ተሽኮርምማ አንገቷን የምትደፋ ሴት ሳይሆን ዛሬ ያለችው ያላትንም የሌላትንም ውበት ለማሳየት አንገቷን ሰግጋ ደረቷን ምትነፋ ናት... አንድ ሁለት ቦታ "ካት ወክ እናሰለጥናንለን" የሚለው ማስታወቂያ ምንኛ ገቢያ እንደቀናው በአስትውሎቴ ታዝቢያለሁ:: አዱገነት ድሮም የቆንጆዎች መነሃሪያ ናት ዛሬም ብሶባታል:: የምሽት ክለቦች ውስጥ በቡድን ሆነው የሚጠጡ የሴት ጎረምሶች አይቶ መደነቅ ፋራ ሊያስብል ይችላል ባንድ መዳፍ ጣት የሚቆጠሩ እንስቶች አንድ ጠርሙስ ስቶልችኒያ ወይም ሺቫስ አውርደው ቢደንሱ ብርቅ አይደለም
አንድ ምሽት ከ H2O የምሽት ክለብ ቆይታዬ ስወጣ ቺቺኒያ 'ሚባለዉን ሰፈር ለመጀመሪያ ጊዜ አየዉት:: የሃምቡርጉን ሴንት ፖውል ወሲባዊ መንደር ነው ያስታወሰኝ:: በመብራት ገመድ ራሳቸዉን የተበተቡ ትናንሽ ቡና ቤቶች ውስጥ ውር ውር የሚሉ ጭኖች ሙሉ ቅያሱን ሞልቶታል ከየበራፉ በርካታ ጠረኖችና ሙዚቃዎች ወጥተው ቺቺኒያን አድምቀዉታል... የሰራተኛ ሰፈር, የሰባተኛና የድሮዉን ውቤ በረሃ የስራ ልምድና ጸባይ ባንድ አቀናጅቶ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ፈጣጣነትን የወረሰ አዲስ የተፈጠረ ሰፈር ነው:: እሙሙ ለተለያየ ሃገር ዜጋ በተለያዩ ሃገራት ቋንቋ ይሸጣል ቋንቋ እንደወረደ ይነገራል ገጠመኝ እንደወረደ ይደሰኮራል እንጭጭ እሙሙም እንደወረደ ለአረብና ሌላ አፍሪካ ወንዶች ይሸጣል::
ከውጭ ምንዛሪ ጋር ባለመስታወት ፎቅ ስር በኒዮን መብራት ባናየዉም የእሙሙ ምንዛሪ በየቦታው እንደትንግርት ይወራል:: ወቅቱ የአፍሪካ መሪዎች ስብሰባ ነበር ታዲያ ምሽት ላይም ኮንኮርድ, ሜሞ እና ጋዝላይት የራሳቸዉን ስብሰባ ጀምበርን አስተኝተው ይቀጥላሉ እናም የውጪ ምንዛሪው ግብይት ይቀጥላል:: እነኚያ የጸሓይ ነጸብራቅ የጨረቃ ፍልቃቂ የመሰሉ የምሽት ንግስቶች እንደገቢያው ይመነዘራሉ::
አዲሳባ እንደበፊቱ ሁሉ ዘንድሮም ምሽቷ አቅፎ ያባብላል ጥሩ ጥሩ ክለቦች ተከፍተዋል በርካታ ላውንጅም እንደዚሁ ሄጄ ከወደድኳቸው ጥቂቶቹ
ላውንጅ እና ባር=> ሱባ (አንደኛ ነው) ላዩም ታቹም ያምራል /የመደብ ልዩነት አለው/ የተም, ብላክ ሮዝ, MKS እና ፋራናይት ሲሆን.... ከክለብ ደግሞ=> H2O, እና ኢሉዥን ምርጥ ቤቶች ናቸው
ምርጥ ክራውድ (ጥሩ ታዳሚ) በኔ ዕይታ 1ኛ ብላክ ሮዝ ሲሆን ይቅርታና ዲቄት የሆነ ታዳሚ ያለው ደግሞ ኢሉዥን ነው:: ከጃዝ ባር ካቡን ብዙም አልወደድኩትም ጣይቱ ጃዝ አምባ ግን አንደኛ ነው ከሸበሌዉም ይበልጣል what a wonderful poetic jazz ብዬ 6 የሞኒካን 6 ኳክብት ደርድሬላቸዋለሁ::
እስቲ ደግሞ ብሬክ እውስድና እመለሳለሁ ገና ብዙ ያልተዳሰሱ አሉ
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::