የዋናው አጫጭር ልቦለዶች

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

የዋናው አጫጭር ልቦለዶች

Postby ዋናው » Sun Sep 16, 2007 4:18 am______ሚሊሊም_______

እትዬ ዙሪያሽ አረኼ (አረቄ) ቤት ናቸው:: ታከለ ወላቃ ጥርሱን ብልጭ እያደረገ መለኪያዋን በሶስት ጣቱ ወደአፉ ይሰዳታል ሙጥጥ ያለ ቀጭን ፊቱ ገና ሳይናገርበት ያስፈግጋል:: ሠፈሩስጥ ሚታወቀው የጋሽ ልሣኑ ወፍጮ ቤት 16 ዓመታት ሙሉ ጥሬዉን ዱቄት እያደረገ ኖሯል:: ወፍጮቤቱ ሚጠራዉም ታከለ ወላቃው ተብሎ ነው:
ከርሱ ትይዩ ባሕሩ ሽበታም ፀግሩን እንደአደባባይ ፅድ አጎፍሮት ሙሉ ሠውነቱን ጥምልምል ከዘራው ላይ አስጎንብሷል: የቀበሌው ፅሕፈትቤት ዘበኛ ነው ቀን ቀን ሚያነግተው ጠብመንጃ በሰፈሩ እንዲፈራ እንዳረገው ሁሌም በጀብዱኝነት ያወራል: ከጎኑ ታዴ አንካሣው ቁጭ ብሏል ቀይ ፊቱ ኑሮዉን አሳብቃበታለች ላዩ ላይ የጠመጠመው ጋቢ እንደእትዬ ዙሪያሽ አረቄ ቤት ቡዝዝ ብሏል ታዴ አንካሤ የሠፈሩ ዕድር ጥሩንባ ነፊ ነው:

ታከለ ሙጥጥ ብላ ጭፏ የተድበለበለ አገጩን አንጓው ብቻ ወፍሮ በቀጣጠኑ ጣቶቹ እየፈተለ
'' ዙሪያሽ እስቲ ባክሽ ቅጂልኝ የማትናገረዋን....ዛሬ ደግሞ ምነው አረኼሽ እምባ እምባ አለችኝ?''

''እሕሉ ተወዶባት ይሆናላ ምን ዘንድሮ ለዚ ሚሊሊም ያልጨመረ አለ'ንዴ?''
አለ ባሕሩ ደመና የመሠለ ሸበቶዉን በከዘራው ቁልምም እያከከ
''ምን የሷ አረኼ በበርበሬ ነውንዴ ሚጠመቅ?''
አለ ታከለ ከቡጥሌው ወደመለኪያው ሚንዶቀዶቅለትን አረቄ በጥልቅ ዓይኖቹ እያፈጠጠ

''ይሆን ይሆናላ እኔንስ እንደዛ በጡርንባው እንድቃጠል ሚያደርገኝ የዙሪያሽ አረኼ አይደል....?''
አለ ታዴ አንካሴ የጠየመ ጋቢዉን ሽቅብ እያስተካከል
'ትዬ ዙሪያሽ ግዙፍ ወገባቸዉን በመቀነታቸው እያጠበቁ ታዴን ገልመጥ አደረጉና

''ያቃጥልህ የናት ያባቴ አምላክ ቱልቱላ ታዲያ ምን ልታደርግ መጣህ አረኼው በርበሬ ከሆነብህ ይሄ ሙት ሚቀሰቅስ ጥሩንባህን ዛሬ አልነፋህም መሰለኝ ሟርተኛ''
ብለው ወረዱበት

''እስቲ አደብ ግዢ አንቺ ምን የሚሊሊም ኑሮ ቢያሰክርሽ ታዴ ላይ ትንጣጪያለሽ'ንዴ ዘላለም በዚ ስራዬ እንደቀናሽ አንቺማ የእድሩ አላፊ ቢያደርጉሽ ጥሩንባዬን ቀምተሽ ሳልሞት በቀበርሽኝ ....''
ቤንቱን በጭቅጭቅ አተራመሱት: ይሄኔ ታከለ ፍቅፍቅ ብሎ እየሳቅ
''...እስቲ ዝምበሉ ሁልሽም ከጥንትም ፀሐይ የውጣልሽ ይመስል ኑሮሽን በሚሊሊም ታላክኪያለሽ... አሁን አንቺ ምን ከዚህ የተሻለ ኖረሽ ታውቂና ነው ድሮም ጠላና አረቄሽን ትሸጪያለሽ አሁንም ትሸጪያለሽ እነ ጋሽ ልሣኑ ይቆጩ ድሮ ያቺ ወፍጮዋቸው የማታግበሰብሰው አልነበረም አሁን ግን ሰዉ ቤቱ ይፈጨው ወይም ገበሬው ዱቄቱን ማጨድ ጀምሮ ይሆን......ገበያው ጠፍቷል.... ወይም አዳሜ ጥሬዉን መዋጥ ጀምሮም ይሆናል ቅቅቅ አንተም ብትሆን ኑሮ ኑሮ እያልክ ባዲስ አመት አታላክክ ጥሩንባህ እንደሆን ጾሟን አታድር....''

ባሕሩ እየሳቀ
''አዬ የታዴ የጥሩንባ ሱስማ የሞተ ሰው ቢያጣ ለሞተ ውሻ ሁሉ ሳይነፋ ይቀራል ''
አለ :
ታዴ አንካሴ ንድድ ብሎት ወደባሕሩ እያየ
''ምን ይመስላል ይሄ ደግሞ ወናፍ....ያንን ጥይት ያልጎረሰ ብረት እንደአራስ ታቅፈህ ወና የመንግስት ቤት ትጠብቃለህ በቃ ባንተ ቤት አርበኛ የሆንክ ሁሉ መስሎህ ጸጕርህን አጎፍረህ ትንዘባነናለህ ''

'' ይሻላል እንዳንተ እንደሰላቢ በየደጁ ሄጄ እርርርርሪ ከማለት''

''ተው ተው ተው ባሕርሸት...'' አለ ታከለ

''.... ያንን ብረት ይዘህ ሳይ'ኮ እንዴት አንጀቴን እንደምትበላኝ ለመሆኑ ግን አተኳኮሱን ታውቅበታለህ?''

''አቶ ልሣኑ ከበጎቻችቸው ጋር ይሄንን ዱቄት ያስቅሙሀል በቃ መስተሳሰቢያህ ላይ ተመርጎ ሁሉም ነገር እንደወፍጮ ቋት ይመስልሀል....''

ይሄኔ ሌላ ሠው
''እንደም አመሹ 'ትዬ ዙሪያሽ?''
ብሎ ገባ በእጁ ክላሠር ይዟል ከነስርሱ ጋር ሲተያይ እሱ ልጅ እግር ነው ቀጭን ትከሻው ለብሶም ለፀበል እራቁቱን እንደተሰለፍ ይመስላል::

''ሄይ አምታታው... ግባ እስቲ ''
አሉ እትዬ ዙሪያሽ የጠላዉን ጋን አፍ በእርጥብ ጨርቅ እያፈኑ

''እቸኩላለው..... ለጉዳይ ፈልጌዎት ነው''
አለ ቀጭኑ ሠው ጠይም ፊቱ ስር ብልጭ ሚሉት ሁለት ወፋፍራም ጥርሶቹ የመወፈራቸው ጉዳይ ሚበላዉን ከሠውነቱ በኃይለኛው የተሻሙበት ይመስላል::

''ምን ምን ገጠመህ...?''
አሉ እትዬ ዙሪያሽ የረጠበ እጃጅቸዉን በቀሚሳቸው አደደራርቀው የያዘውን ክላሠር እያዩ

''ከውጪ አገር የመጡ እንግዶች ይጠብቁኛል የሚከራይ ቤት ካልሆት ብዬ ነው ለ15 ቀን ''
ታከለ ከከት ብሎ ሳቀና የወፍጮቤት ዱቄት የጠገበ ግማሽ ፀግሩን እያከከ
''ዙሪዬ ዛሬ ወግ ደረሰሽ ....አይ አንቺ ሚሊሊም አታሰሚን የለ ''
አለ ወደጣሪያው እጆቹን ዘርግቶ
''እስቲ ዝምብለ ታከለ አንተ ደግሞ ትንኝ ይመስል ጥልቅ ማለት ትወዳለህ .....''
አሉ እትዬ ዙሪያሽ
''ዝምበል እስቲ ብዝንስ እኮ ነው''
አለ ባሕሩ አፉን ከፍቶ ዓይኑን አሞጭሙጮ ልጁን እያየው

''ስማ.....'' አሉ 'ትዬ ዙሪያሽ ''....ብቻዉን ነው ሚኖረው?''

''አይደለም ከዳላስ ከጓደኛው ጋር ነው የመጣው''

''ከየት...ከየት አለ...ከዲላ....ነው ያለው?''
አለ ታከለ የልጁን ዓይን እያየ

''ከዳላስ....አሜሪካ''
አለ ልጁ ክላሠሩን እጥፍ ዘርጋ እያደረግ

''የለኝም ልጄ አንድ ቢሆን እንደምንም እዚዉ አስጠጋው ነበር ሁለት ከሆኑ እንኳን ጫጫታቸዉም መከራ ነው''
አሉ እትዬ ዙሪያሽ የወይራ ጪስ የጠገበ መጋረጃ በአፍረት የተሸፈነ ጓዳቸዉን የጎንዮሽ እየጠቆሙ

''ለነግሩ እንደሌሎት አውቃለው ግን አዩ ቢዝነሱ የሁሉም ስለሆነ እግረመንገዴን ልጠይቅዎ ብዬ ነው ''
አለና ልጁ እነኚያን ጥርሶቹን ፈልቅቆ ሳቀባቸውና ሄደ::

''አዬ ዙሪያሽ ጫጫታቸው አልሽ ....''
አለ ታከለ አረቄዉን ወደአፉ እየዶላት

''ለነገሩ'ኮ መንግስት እንግዳ ተቀባይነታችን ሚታየው ዘንድሮ ነው ቤት ያላቹ ሁሉ እንግዳ አስጠጉ ብሎ ተናግሯል:''
አለ ባሕሩ ከፋይ ኮቱን ትከሻው ላይ እያስተካከላት ንጥት ብላለች::

''ምነው እዚሁ እኛ ጋር ሆኖ አላሙዲ..... አገር ሚያክል አዳራሽ ከውጪ አገር አስመጣ አላሉም... ምነው ታዲያ ካማሪካው ዲላ ባዶ እጃቸዉን ተንከርፍፈው ከሚመጡ ቤታቸውን ይዘው አይመጡም ነበር...?''
አለ ታከለ ሡሪዉን ከፍ አድርጎ የጉልበቱን ሎሚ እያሻሸ

አሁንም ድጋሚ ሌላ ሠው ብቅ አለ

''ዙሪዬ.....''
ይሄኛው ደግሞ ሰክሯል መላጣው ሳይቀር ወዝቷል

''ዛሬ ይጠጣል እ ን ደ...ጉድ ይጠ..ጣል ''
አለና ድብዳብ የለበሠ መዳቡ ላይ ሄዶ ዘፍፍፍ! አለ

''ዙር...ዬ ጋብዢልኝ ወላ ጥሩንባ ነፊ....ወላ ዘበኛ ወላ....ወፍጮ...ምናምን...''
ዝብንን ያለ ስካሩ ሲናገር ስቅ እያስባለው ነው::

''ምን አገኘህ ደግሞ ?''
አሉት እያፈጠጡበት

''ኤጭ....ለሚለነም ያልሆነ ብር ይ..በጣ...ጠስ.....''
አለና ከኪሱ አንድ ብር አውጥቶ ቀዳደው::ሁሉም በድንጋጤ አፈጠጡበት

''አሕያን ምግባሯን አውቆ ቀንድ ነሳት አለ ያገሬ ሰው...''
አለ ታዴ አንካሣው

''ዙር...ዬ መንጌን ታውቂው...የለ በቀደም ካማሪካ የመጣው የጋሽ አሰፋ ልጅ .... አገኘኝና ይሄንን ውስኪ ሲጠምቀኝ ዋለ በዋላ እናንተ ትዝ ብላችሁኝ ደሀ ጓደኞቼ ናፈቁኝ ...ስለው አምሳ ዱላር አሳቅፎ ላከኝ ቅቅቅ ''
እትዬ ዙሪያሽ ገና አሁን ወርቅ ጥርሳቸው ታየች::

''ረስቼው ረስቼው....ዙርዬ....ላቶብ ትገዢያለሽ? ጠይቅልኝ ብሎኝ ነው?''

''ምን?''

''ላ....ቶብ..... ውይ አውንስ ከቲክኑሎጂየ ከራቅ ሰው ጋር አብሮ መጠጣት ነው የሰለቸኝ''

''ደግሞ ምንድነው እሱ ወይ ዘንድሮ ሚሊሊም አታመጣብን የለ መቼ ''
አለ ታከለ ለተጋበዘው ቡጥሌ ሙሉ አረቄ ወላቃ ጥርሱን እየቸረ

''ታክ'ዬ... እኔም አላውቀዉም ቅቅቅ ቦርሳውን ሳየው ግን ግን ዶሴ መሰለኝ ...መንጌ አይለኛ ነው ምናልባት ካማሪካን መንግስት የግምጃ ቤት ሰነዱን ሰርቆት ይሆን...ንንዴ? ቅቅቅ''
'' ኸረ እኔ ምን በወጣኝ ደግሞ የሌባ ተቀባይ ተብዬ ሆ ሆይይይ እቺኑ አረኼዬን በሰላም ልቸርችር''
አሉና 'ትዬ ዙሪያሽ ሂሳባቸዉን ማወራርደ ሲጀምሩ

መላጣው በተቀመጠበት ነፋስ እንደሚወዘውዘው ዛፍ እየተነቃነቀ
''ዙሪ...ዬ ዛሬ ምከፍልሽ በዱላር ነው መልስ አለሽ....?''

''ምን?''
አሉ እትዬ ዙሪያሽ

''ዱላር አታውቂም....? ውይ አሁንስ ከደሀ ጋር ብቻ መኖር ሰለችኝ አቦ...''
አለ

''ምንዛሪዉን አታውቀዉም ''
አለ ታከለ::

እትዬ ዙሪያሽ በንቅሳት የተሸለም ክንዳቸዉን ወገባቸው ላይ በቄንጥ አድርገው እየጠበቁት ነው
መላጣው ኪሱ ገብቶ ዶላሩን መዝዞ አወጣና ለ 'ትዬ ዙሪያሽ ሠጠ

''ምን ሆነሀል አንተ ሰው ዛሬ ይሄ'ኮ አንድ ብር ነው''
አሉት ዓይኖቻቸው እንደተወደደው በርበሬ ፍም መስለው

''ምን?''
አለና ቀዳዶ የጣለዉን ዶላር ከግሩ ስር ተመለከተው::


ተፈፀመ::


መጪው ዘመን የሠላምና የደስት ይሆንላቹ ዘንድ ምኞቴ ነው

ዋናው_______________________________________________________________________________::

Last edited by ዋናው on Fri Aug 23, 2013 1:10 am, edited 16 times in total.
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby sleepless girl » Wed Sep 19, 2007 4:45 am

ቕቕቕቕቕቕቕቕቕቕ
ቕቕቕቕቕቕቕ ዋንቾ ከምር አሪፍ መጣጥፍ ናት..........ተረባቸው በጣም ያስቃል...........አይ ሚሊሊም ቕቕቕቕቕቕቕቕቕ ችሎታህን እንደልማዴ አድንቄልሀለው........አራት ነጥብ ::

አድናቂህ
Nothing is impossible!!
sleepless girl
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1510
Joined: Sun Feb 19, 2006 3:56 am
Location: near u!

Postby ቅራሪ » Wed Sep 19, 2007 3:52 pm

ዋንቾ ሰላም ነህ ቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅ በጣም እሚመች መጣጥፍ ነው ቅቅቅቅቅቅቅቅቅቅ በጣም ነው ያሳቀኝ እስቲ ቀጥልበት ቅቅቅቅቅቅ

ያንተው ቅራሪ
ቅራሪ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 247
Joined: Wed May 10, 2006 4:42 am
Location: adiss abeba

Postby ደያስ » Mon Sep 24, 2007 4:19 am

አሁን ይሄ ያስቃል ደስ ይላል እንጂ!!!!!!!!!!!!
ደያስ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 19
Joined: Sun Sep 23, 2007 12:12 am
Location: Addis Abeba

Postby ፓን ሪዚኮ » Mon Sep 24, 2007 9:40 am

አባ ነብሶ ....ይቺ ...ንጉስ ቢኖር ..... ታሸልማለች ................

ፓን አባ ፈርዳ
Imageኢትዮጲያ ትቅደም
ፓን ሪዚኮ
አለቃ
አለቃ
 
Posts: 2044
Joined: Tue Aug 03, 2004 3:35 am
Location: ጎሃ ጽዮን

Postby ዋናው » Wed Mar 26, 2008 3:39 am

ሠላም ዋርካዊያን /ያት

እቺን ልቦለድ ለቫልንታይን ቀን ፅፌያት ኢቲዮ ዋርካ ላይ እተርካታለሁ ብዬ ነበረ የቀዳዉትን ድምፅ ስሰማው አስጠላኝ ፎረም ላይ ሲነበብ ይሻል ይሆን ? ብዬ ዛሬ ለናንተ አበረከትኳት ብትረፍድም እስቲ በሞቴ አንቡልኝማ ::የቀፍቅረኛሞች ቀን

ለወራት ከብዶ የቆየው ብርድ አሁንም ጆሮን ሊቀነጥስ ምንም አልቀረዉም : ንፋሡ ከዛፍ ዛፍ እየሮጠ ሚያራቁተው ቅጠል ባለማግኘቱ የተናደደ በሚመስል የሠዉን ልብስ እየገለበ ይከንፋል :: ዮናስ የገዛዉን የወይን ጠጅ በቄንጠኛ የወረቀት ከረጢት አንጠልጥሎ አውቶብስ ይጠብቃል :: የአውቶብስ ማቆሚያው ሚቀጥለው አውቶብስ ለመምጣት ሚቀረው ደቂቃ 7 መሆኑን አየ :: ብዙ የቆመ መስሎት ነበር ግን እዛ ሲደርስ 9 ደቂቃ ነበር ሚቀረው

''እንዴት ለንደንን ሚያክል ከተማ አንድ አውቶብስ ለመጠበቅ 10 ደቂቃ እንቆያለን ...?''
አለ ሠኣቱን ገልመጥ እያደረገ በላስቲክ ውስጥ ሆነው የፍቅርን ቀን ጮክ ብለው ሚዘምሩ ሚመስሉት በእጁ የያዛቸው የፅጌሬዳ አበቦች ብርዱንም ዳመናዉንም ድል የነሡ ይመስላል ::

''መልካም የቫላንታይን ቀን ወጣቱ ... ለፍቅር ለሚቸኩሉ ሠዎች 10 ደቂቃ 10 ቀናት ነው ...''
አሉ አንዲት በእድሜ ብዛት ፊታቸው የተሸበሸበ አሮጊት በቀበቶ አንገቱን ያሠሩት ውሻ ዓይን ዓይናቸዉን ያያቸዋል የውሻው አፍ ቅጥነት እንደ ዓይጥ የሾለ ነው እግሮቹም እንደ ማማሣያ የቀጠኑ ሶሎግ ውሻ ነው :: እነኚህ እንግሊዞች ለውሻቸዉም ዳይት ያውቃሉ :

''አመሠግናለው እናቴ የልቤን ስለተረዱልኝ ደስ ብሎኛል ...''
አለና ፈገግ ብሎ በአፍረት ወደውኃላው ፊቱን መለስ ሲያደርግ አንዲት የቀይ ዳማ አበሻ በሃሣብ ተውጣለች :: በጥልቅ ሃሳብ ውስጥ መስጠሟ በመቆዘሟ ያስታውቃል ድንገት ብርዱ እንደተሠማት ያደረገችዉን ጃኬት ዚፕ ወደላይ ስትሻጠው ዓይኖቿ ከብለል ሲሉ ከዮናስ ዓይኖች ጋር ተገጣጠሙ : ልክ አንዳች ነገር ስትሠራ የተደረሠባት ዓይነት ደንገጥ አለች :: ወዲያው አንገቷን ሠበረችና የሞባይል ስልኳን አውጥታ ሠኣቷን ተመለከተች ::

''ለ 5 ሠዓት ሩብ ጉዳይ ሊል ነው .... ''
አላት ዮናስ ጠጋ ብሎ ቁልቁል ከተቀመጠችበት የፕላስቲክ ቀጭን አግዳሚ ወንበር ላይ እያያት

''አመሠግናለሁ ....''
በሃዘን ውስጥ የተነከረ ትንሽዬ የፈገግታዋ ብልጭታ አንዳች ልዩ ስሜትን ይሠጣሉ

''አንቺም እንደኔ አበባ ለመስጠት ወይም ለመቀበል የቸኮልሽ ትመሲያለሽ ...''
አላት የአሮጊቷን ሚቁነጠነጥ ውሻ አይቶ በከፊል ፍራቻ ወደውኃላው እያፈገፈገ

''እመስላለሁ ?''
ድምጿ በቀዘቀዘ ስሜት ሆኖ ግን ሚያዜም ይመስላል

''ዛሬ መምሠልና አልመምሠል አያስፈልግም ቀኑን ዝም ብሎ መዘከር ነው የኔ እሕት ....''
አላት ዮናስ ያንጠለጠለዉን ወይን ያዘለ የወረቀት ቀረጢት ከጉልበቱጋ እያማታ

''በውሸታሞች ቀን ሁሉም አይዋሽም ....... በአባቶች ቀን ደግሞ ሁሉም አባት አይሆንም ..... ሁሉም የመታሠቢያ ቀኖሽ ራሡን የቻለ ባለቤት አላቸው ....''

'' ንግግርሽ ፍቅረኛ እንደሌለሽ ምስክር ሚሆን መሠለኝ ...ይቅርታ ግን ዮናስ እባላለሁ ....''
አላትና ወይኑን አበባ በያዘበት እጁ በጥንቃቄ አሸጋገረና ለመጨበጥ ዘረጋ

''...ሚስጥረ ...''
አለችው እሷም እጇን ዘርግታ አሁን ፈገግታዋንም ሙሉ መልኳንም ሲያስተውለው ስለቁንጅናዋ የመማል ያህል እርግጠኛ ሆነ ::

''ሲንግል ነኝ ነው ምትዪው ...?''

''ለጊዜው ...''
አለችው የአውቶብሷ መምጪያ ደቂቃ በመድረሡ ቆማ እየተዘጋጀች ጅንስ ሡሪዋ ውስጥ በነፃነትና በጉራ ኮርቶ ቀጭን ወገቧን የንቀት የያዘው መቀመጨዋ የዮናስን ዓይን ሠረቀው

''እንዳቺ ዓይነት ቆንጆ ሤት ሲንግል የመሆኗ ነገር ....እኔ ...ንጃ ትንሽ ይከብዳል ?''

''ስለማድነቅህ አመሠግናለው እንግዴ እኔ ላጤነቴን ነው ማውቀው ሳታውቀኝ ካጋባሕኝ መቸስ ምን አደርጋለሁ ...''
አለች :: ሚስጥረ ከሠጠመችበት የሀዘን ድባብ ውስጥ እየወጣች እንደሆነ ሚያስታውቅ ዓይነት ፈገግታና ዘና ማለት ይነበብባታል ::

አውቶብሡ ሢመጣ መጀመሪያ ውሻው ከዛ አሮጊቷ ገቡና ዮናስ ሚስጥረን አስቀደመ :: የአውቶብስ ማለፊያው ቲኬቱን ቦርሣው ውስጥ እንዳለ ለሹፌሩ የማግኔት ማስነኪያ ጋር አስጩኾ ሚስጥረ ወደተቀመጠችበት ስፍራ ተከትሏት ጎኗ ቁጭ አለ አውቶብሷ መንደር መንደሩን ምትዞር አነሥ ያለች ስትሆን ብዙዉን ጊዜ ተጠቃሚዎቿ በእድሜ ገፋ ያሉ ናቸው ::

''ወዴት እየሄድሽ ነው ?''

''እኔንጃ .... እኔም አላወቅኩትም የዛሬ ዓመት ጣፋጭ የፍቅር ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት ዝም ብዬ ቤቴ ሆኜ ሳሰላስል እስቲ ብቻዬን ልዝናና አልኩና ወጣው ''
አለችው ሁለት መዳፎቿን አጋጥማ ጉለበቶቿ መሀል እንዲሞቃት እያፋተገች

''የዛሬ ዓመት ፍቅረኛ ነበረሽ ?''

''አዎ .... ''
አለች በረጅሙ እየተነፈሠች

''ተለያይታችሁ ነው ?''

''እሡ ተለየኝ .... እኔ እያፈቀርኩት እሱ ፍቅር አለቀበት እኔ ደግሞ ያለኝን ፍቅር በሙሉ እሱን ብቻ ስላፈቀርኩበት ...እሱ እኔን ሚያፈቅርበት ተጨማሪ ፍቅር ላበድረው አልቻልኩም ስለዚህ ተለያየን ....''
አለች በመስኮቱ ያረጁ የሠሜናዊ ለንደንን መኖሪያ ቤቶች እያየች

''ሆ .... አዝናለሁ ... አገላለፅሽ ትንሽ ይከብዳል ... ግን ያው በፍቅር ዓለም ውስጥ ሁሌም ያጋጥማል ''
አላት ዮናስ ሠኣቱን እያየ

''ፍቅረኛህን ትወዳታለህ ?''
አለችው ...ፈገግ ለማለት ስትሞክር የላይኛዋ ከንፈር ትንሽ ጠመም ለማለት ሚፈልግ ይመስላል ::

''አዎ በጣም ''

''እሷስ ትወድሀለች ...?''

''እ .... ይመስለኛል ሚስጥረ ትንሽ ግን ቅናተኛ ነች እንጂ ''
አላት ፈገግ ብሎ ... በጥንቃቄ የቀረፀው የከንፈሩ የፂም መስመር ፈገግታዉን አጅበው ዘርጠጥ ይላሉ

''ስለምትወደህ ነዋ ምትቀናው ..... እድለኛ ነህ ''
አለችው ::

''አንቺ በድሮ ፍቅረኛሽ ትቀኚ ነበር ...?''

''በጭራሽ .... እንዲያዉም እኔ ላይ ደርቦ ሌሎች ሤቶች ሲይዝ ሁሉ እያወቅኩኝ ፍቅር ስላለብኝ አብሬው እንዳልሠማ እንዳላየ እሆን ነበር .... ሚገርምህ እንደሠማው እኮ ያውቃል ስለፍቅር ብዬ ሁሉንም ችዬ ዝም እንዳልኩም ያውቃል ....''
አለች ወደሣቅ ሚያደላ ፈገግታ እንቡጥ ከናፍርቷን ሢገልፁት ከድርድር ጥርሶቿ መሃል አንዱ እንደመደረብ ብሎ ፈገግታዋን ለማድመቅ ሚሞክር ይመስላል ::

''እንዴት ያስችልሻል ... እሱስ እንዴት ያን ያህል ይጭክንብሻል ...?''

''አየህ አንዳንዴ እንዲህ ነው ፍቅር እውር ነው ሲሉ ... አንደኛው እውር እንደኔ ዓይነቱ አውቆ ሚታወር ወይም ልቦና እያየ ዓይን የማያይ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በፍቅር ብዛት በማመን ሚታወሩ ናቸው ...''
አለችው :: ወዲያው ሁለቱም እኩል የማቆሚያ ደውሉን ተጫኑና ባጋጣሚው ተሣሳቁ
''እኔ 'ኮ ስልክ ስጭኝ መውረጃዬ ደርሶዋል ልልሽ ነበር ...''
አላት ዮናስ ::ስልክ እንዲቀያየሩ ሲጠይቃት
''እንዲሁ አንድ ቀን አውቶብስ ላይ እንገናኝ ይሆናል ... ደግሞ ከእኔ ጋር ስትደዋወል ቅናተኛ ሚስትህ ትሠማና ....''
ብላው በሣቅ አድበስብሳ አለፈችው ::
ከአውቶብሡ ሢወርዱ ባለውሻዋ አሮጊት እግራቸው ስር ጥቅልል ብሎ የተኛዉን ውሻቸዉን ዝቅ ብለው እያሻሹ

''ለትክክለኛዋ ፍቅረኛህ እንደምትደርስላት እርግጠኛ ሁን ...''
ብለው ቀለዱበት ይሄን ጊዜ ሁሉም ተሣሣቁ

''እውነታቸዉን ነው እኚህ አሮጊት ... በል ቶሎ ድረሥላት ...''
አለችው ሚስጥረ ማዶዉን አሻግራ እያየች

''ሠርፕራይዝ ስለሆነ ማደርጋት ችግር የለዉም ለነገሩ ደርሺያለው ቤቷ ያ ነው ...''
አለና አበባ በያዘበት እጁ ጠቆማት : የሚስጥረ የሞቀ ሥንብት ፈገግታ ፍቅረኛው በር እስኪደርስ ውስጡ ነበር ::

መጥሪያዉን ሲያቃጭል የፍቅረኛው ድምፅ ከውስጥ ተቀበለው ::
ከዚህ በኌላ ዮናስ በቅጡ ያስተዋለው ነገር ብዙም አልነበረም ብቻ አንድ ሥደትና ዕድሜ የራስቅሉን ፀጉር የሞለጨው ጎልማሣ የአንገት ልብሡን እያስተካከለ ዮናስ በተደገው በር ሢወጣ አስተዋለ :: ፍቅረኛው ምታባብልበትም ቃላት ... ምትቆጣበትም ቁጣ ... ይቅርታ ምትልበትም አፍ አልነበራትም እጁ ላይ የያዘዉን አበባ እያየች ፊቷን በእጆቿ መዳፍ ሸፍና ጀርባዉን ሠጠችው

''ዮናስ በሆነ መርፌ ያደነዘዙት ያህል ሚያየዉም ሚያስተውለዉም ነገር ብዥ አለበት የወይን ጠርሙሡን ወደቤቷ ወረወረና ደረጃዉን ቁልቁል ሢወርድ መላጣው የመኪናዉን ቁልፍ በእጁ እያሽከረከረ የማብሸቅ ፈገግታ አሳይቶት ወደውጪ ወጣ
ዮናስ የሚስጥረ ንግግር ጆሮው ላይ አቃጨለበት
''አየህ አንዳንዴ እንዲህ ነው ፍቅር እውር ነው ሲሉ ... አንደኛው እውር እንደኔ ዓይነቱ አውቆ ሚታወር ወይም ልቦና እያየ ዓይን የማያይ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የፍቅር ብዛት በማመን ሚታወሩ ናቸው ...''

ዓይኑ ላይ የቀረው ፈገግታዋ ድንገት ውስጡን እንደእሣት ከሚለበልቡት አውጥቶ ያቀዘቀዘው ሁሉ መሠለው :: ወደወሄደችበት አቅጣጫ ሩጫዉን ቀጠለ ከፍቅረኛው ሽሽት ይሁን ሚስጥረ ላይ ለመድረስ ብቻ ራሱም ለምን እንደሚሮጥ አላወቀዉም እጁ ላይ ያሉት ፅጌሬዳዎች ግን በሩጫውና በንፋሡ ቀንበጣቸው እየተገነጠለ ወደውኃላው እየፈረጠጡ ነው :: ምናልባት ላለቀ ፍቅሩ ሽኝት ይሆን ...

ተፈፀመ ::

Last edited by ዋናው on Sat Aug 30, 2008 4:06 am, edited 3 times in total.
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Wed Mar 26, 2008 3:42 am

________ያልጠፉ መብራቶች _________ቤቱ በሠዎች ጢም ብሎ ጠጠር ቢወረውሩ ሚወድቅበት ቦታ አይገኝም : ሢጋራው ሽቶው የሠዉ ላብና የጫማ ሽታ አንድ ላይ ተዋሕዶ ለየት ያለ መሃዛ ፈጥሮዋል :: የቤቱ ሤቶች በትርምሱ መዓል ተሠግስገው ስሜቱ በመጠጥ የጋለዉን ወንድ እየተሻሹ ወዲያ ወዲህ ይላሉ : ሙዚቃው ከጣሪያው በላይ ይጮኻል : እንደምንም ቦታዉን አብቃቅተው ሚደንሱት ወንዶች እየተውረገረጉ ጉልበታቸዉን አጥፈው ወደጀርባቸው እየተኙ መሬት ሊነኩ እያሉ ብድግ ይላሉ :: አንዲት ሴት መሀላቸው ከነርሱ እኩል ትውረገረጋለች ለዓመል ጡቶቿን ብቻ የሸፈነው ልብሷን ትከሻዋን ሚጠላልፈዉን ገመድ በአውራ ጣቷ ሳብ እንደማረግ ትልና ወደጀርባዋ መቀንጠስ ትጀምራለች እስከ ሡሬዋ ባተሌት ድረስ ሚታይ እርቃን ሆዷ ካለው እንብርቷ ላይ ሎቲ ተንጠልጥሎዋል :: ከወገብ ቅጥነቷ ጋር ማይመጣጠን መቀመጫዋ በርከክ ብላ ዲጄው በለቀቀው ዳንስ ሆል ሙዚቃ ስታገላብጠው የወንዱ ዓይን ሁሉ ተጎልጉሎ እሷው ላይ ይከመራል :: ድግሞ ብድግ ትልና ወንዶቹ መሀል ሆና ቀጫጭን እጆቿን እያጠፈችና እየዘረጋች በትከሻዋ ትወዛወዛለች : ዓይኖቿ በተራቸው ይጣቀሳሉ የተቀለሙ ከናፍርቷ ስሜትን ሚያዜም በሚመስል የአፍ አከፋፈት ሆኖ ከእንቅስቃሴዋ ጋር ያዜማል ::
ኤፍሬም እቺን ልጅ ፍለጋ ብሎ እዚህ መጠጥ ቤት መምጣት ከጀመረ ከራርሟል :: ሠሞኑን ከጓደኞቹ ጋር የዘጋው ጥሩ ዝግ ነበር ታዲያ በርግጠኛ ኪሡን አወፍሮ ጎራ ሲል መቅዲ ግን አልነበረችም :: ጓደኛዋን ጠራትና ጠየቃት አንዱ ሀብታም ለሣምንት እንደተከራያት ነገረችው :: ኤፍሬም በንዴት እንደጨሠ ሢጠጣ አድሮ ከዛችው ጋር አነጋ :: እሱ ግን መቅዲን ብቻ ነበር የፈለገው ::
ኤፍሬም ራጉኤል የተሠኘው የንግድ ስፍራ አክባቢ አገር ያወቀው ሌባ ነው :: 4 ወር ታስሮ ከተፈታ በኌላ ብሶበታል : ግን ሚሠርቅም ጠፋንጂ
'' ከሚሠረቀው ... ሌባው የተሻለ ብር ሆነኮ ያለው ''
ይላል ከጓደኛው ኤርሚያስ ጋር በየሠዉ ቦርሳና ኪስ ገብተው የረባ ሳንቲም ሲያጡ ...

''ቅድም 'ኮ ስትጠራኝ ሀይለኛ ቢዝነስ እያበሰልኩኝ ነበር ሶሪ እሺ ...''
አለችው በጄል ግንባሯ ላይ የተለጠፈ ቢጫ ፀግሯን በረጃጅም ጣቶቿ ነካ ነካ እያደረገች የውሸት ኩርፊያውን ለማባረር ድራፍት ያሊያዘ እጁን ከፍታ እቅፉ ስር ገባችለት ::
''እኛንማ መች ዞር ብለሽ ታይናለሽ መቅዲ ...?''
አላት ኮራ ብሎ አንገቷ ስር ያለዉን ጠረኗን ባፍንጫው እየማገው ... ሽቶ ላብ ... ተደባልቆ አፍንጫዉን አልፎ አናቱ ላይ ሲወጣ ታወቀው

''ኤፊ አንተንማ እንዴት አላስታውስህ ስንት ቀን እየጋበዝከኝ ...''

''ግን ሁለት ቀን ብቻ ነው አብረን ያደርነው ...''
አላት ድራፍቱን አስቀምጦ ሆዷን እያሻሸ ::

''ምን ላድርግ አቅም ለያይቶ ያሳድረናል እኔ ደግሞ ሸሌ ነኝ ብር ነው ሚያስተኛኝ ''
አለችው የለኮሠዉን ሲጋራ ነጥቃው እያጨሠች ሳቋ ውፍረቱ ከርሷ ትንሽነት ጋር አይሄድም

''ፍቅር አይዘኝም ለማለት ነው ?''
ረጅም ሳቅ ስቃ

''እሡን ነገር ምንነቱን ሳላውቀው 'ኮ ነው ዕቃዬን ሸጬ መተዳደር የጀመርኩት ...''
አለች በመዳፏ ጭኖቿ ስር እየገባች ምትሸጠዉን ዕቃ ልታሳየው እየሞከረች ::

''ግን 'ኮ ስንት ቀን ብር ይዤ ስመጣ አላገኝሽም ...''
አላት ::

''ትላንትና እስከዛ ሠዓት አብረከኝ ስትቆይ 'ኮ እኔ ደግሞ ይዘህኝ ምትሄድ መስሎኝ ስንት ገበያ አባረርኩኝ ደግነቱ የንጋት እንጀራ ጣለልኝ አንተ ከሄድ በኌላ አንዱ ጥምብዝዝዝ ብሎ መጣና ይዞኝ ሄደ ገና ሡሪዉን አውልቆ አንድ ዙር እንደ ሄደ እንቅልፉን አይለጥጠዉም ....? ይሄ ተገላብጦ ቢያጣኝም ምንም አይለኝም ብዬ ብሬን ይዤ ወደማደሪያዬ ፈድ አልኩልሀ .... ''
እየተላፉ እየተሳሳቁ መጠጡን እየጠጡ በሙዚቃው እየደነሡ ቆዩ ::
ኤፍሬም ዛሬ በመቅዲ ገላ ውስጥ ሢቀልጥ እየታየው በድስታ ይፈነድቃል አጠገቡ ያለው ጎረምሳ በሙዚቃው እጁን እያወናጨፈ ይደንሳል ድንገት ኤፍሬም ሲያየው ዓይኖቹን ይሰብርና በዳንሱ እንደተመሠጠ ሁሉ አንገቱን ክንዱ ስር ቀብሮ ይጎብጣል : ኤፍሬም አንድ ቦታ ሚያውቀው ይመስለዋል ግን አሁን ስለሱ ግድ አልነበረውም ኪሡ ቀስ ብሎ ይገባና የያዘዉን ብር ስለመኖሩ ያረጋግጣል ::
ዛሬ የሠራው ስራ አልነበረም አንድ የሤት ቦርሳ ሠርቆ ሢፈትሸው ያገኘው 2ብር ከ 35 ሳንቲም እና የቤት ቁልፍ ብቻ ነበር ከቁልፎቹ ጋር አብሮ ያለው የጆሮ መኮርኮሪያ ጫፉ ላይ የያዘው ቆሻሻ ትዝ ብሎት ፈገግ አለ ::

ሆዱን ሞርሙሮት ወደናቱ ቤት ሲገባ ድንገት ያእናቱን ሳጥን ክፍት ሆኖ ያገኘዋል ከራሱ ጋር ተሟገት :: ትላንትና ከመቅዲ ጋር እንደዛ በስሜት ነፍዞ ስሜቱን እንደተሸከመ ቤት ገብቶ እንቅልፍ ማጣቱን አስታወሰ :: ከዛም ያእናቱን ቁጣ .... ቀስ ብሎ መበርበር ጀመረ 400 ጥሬ ብር በአደራ ሊሠጥ እንደታሰረ አገኘ : ኮቴዉን አጥፍቶ ሲወጣ ታናሽ እሕቱ ብቻ ነች በረንዳው ላይ ስንዴ እየለቀመች ያየችው :

''ዛሬ እስኪበቃሽ ጠጪ መቅዲ ....''

''ዛሬ እንዴት ነው ጭነሻል መሠለኝ .....?''
አለቸው ኪሱን በመዳፏ መታ መታ እያደረገች

''ነገርኩሽ 'ኮ ...''
ጉትት አድርጎ አንገቷ ስር ይስማታል ረጃጅም ክንዷን እንደእባብ ዙሪያዉን ጥምጥም ታደርግበታለች ከዛም ጡቶቿን ደረቱን ታስነከዋለች :
የቤቱ ትዕይንት ቀጥሎዋል መብራቶች እየተትረገረጉ ጨለማዉን ክፍል በቀለማት ብረሀን ያደምቁታል :

''እንውጣ ?''
አላት ከጭኑ ስር እንደእሳት ሚፋጅ ስሜቱ ልክ በሠዓት እንደሚፈነዳ ቦንብ ጢጥ ጢጥ ሲል እየታወቀው

''ትንሽ እንቆይ መደነስ አምሮኛል .... ከፈልግክ ክፈለኝና ሾርት ገብተን እንምጣ ....''
አለችው በስሜት መቅለጡን አውቃ ጭኗን እሱ ጭን ውስጥ አስገብታ ትር ትር ሚል ስሜቱን መጠን ለመጨመር እያሻሸች
ኤፍሬም ግሏል ትር ትር ትር ጢጥ ጢጥ ጢጥ እያለ ነው ::

''ኖ መቅዲ ዛሬ ሌሊቱን ሙሉ አቅፌሽ ነው ማድረው ...''
ይላታል

''ኤሺ አንድ ሠዓት ያህል ታገሠኝ ...''
አለችው : እየተነጫነጨ እሺ አላት : መጠጧን ተጎንጭታ በግንባሯ ጉንጩን ገፋ አድርጋ ጆሮ ግንዱ ስር ገባችና
''ሂሣብ ስጠኝ መውጪያ መክፈል አለብኝ ...''
አለችው : ሠጣት ቀስ ብላ ቆጠርችዉና በሹክሹክታ
''መጣው ...''
ብላ አንገቱ ስር ስማው ሄደች
: ኤፍሬም 1 ሠዓቱ እንዴት እንደሚሄድለት ግራ ገባው : መጠጥ ደገጋመ ሢጋራ አጨሠ ደነሠ እንደምንም ሠዓቱ ፎቀቅ አለለት :: መቅዲ ግን አልመጣችም መጣው ብላው ከሄደች 45 ደቂቃ አለፋት : አንገቱን ስግግ አድርጎ ወደሄደችበት ያያል የለችም :: 50 ደቂቃ 55..... አንድ ሠዓት አለፋት :: ተነሳና ፈለጋት የለችም .... አንዲት ጓደኛዋን ሲያገኛት

''መቅዲስ .....?''
አላት ዓይኖቹ ፈጠው

''መቅዲ ያ ሀብታም ሠውዬ መጥቶ ወሰዳት ''
አለችው ስካሯ በሚያስታውቅ ንግግር : ኤፍሬም ተርገበገበ ቅድም አጠገቡ ይደንስ የነበረ ጎረምሳ እየሳቀበት ጊቢዉን ጥሎ ወጣ ::
ኤፍሬም የሠጣትን ብር ልክ ኪሡ ሚያገኘው ይመስል ልብሱን መዳበስ ጀመረ ትዝ ሲለው ለካ የቀረዉን ብር ደግሞ ያስቀመጠው ጃኬቱ ውስጥ ነው እየተንደረደረ ሲገባ ጃኬቱ የለም :: ጃኬቴን ብሎ ሲጮኽ ያስተናግደው የነበረ አሳላፊ የመጨረሻዉን ዙር ሂሣብ ሊጠይቅ መጣ : ትዕግስቱን ስለጨርሰ አሳላፊዉን በቡጢ ለመምታት ሲሰነዝር አንድ ለየት ያለ ነገር ተቀበለው ከዚህ በኌላ ግን ለሠዓታት ብዙም ሚያስታውሰው ነገር የለም ::

ጎጃም በረንዳ አልመሸም ሳይመሽ ሌሊት ሳይሆን ሊነጋ ነው ሕይወት ዝውውሯን ቀጥላለች : ሌባው መስረቅ አለበት ማጅራት መቺው መውጋት አለበት ሴተኛ አዳሪዋ ራሷን መቸርቸር አለባት .... አንዱ ባንዱ ተጠላልፎ ዛሬን ያልፋል : ነገን ደግሞ በሌላ መጠላለፍ ይቀጥላል : ስለነገ ማንም ግድ የለዉም : ምክኒያቱም ስለዛሬ ትላንትና ማንም ግድ አልነበረዉምና :

ኤፍሬም ፊቱን በቀስታ ሲዳብስ አንዳች ክምር ያህል ከበደው ልብሱ በደም ቀልቷል :: ወደቤቱ መሄድ እንደማይችል ያውቃል : ብርዱ ደግሞ አንዘፈዘፈው :: የሡሪ ኪሡን ሲዳብስ 20 ብር አገኘ :: መቅዲ ያጋለችው ስሜቱ ከመጠጡ ስካር ጋር ሆኖ ያረፈበት ቡጢ አላበርደዉም አሁንም ከስሩ የሴት ያለ ሚል ስሜቱ እንደቁስሉ ሁሉ ይጠዘጥዘዋል ::

ያልጠፉ የሌሊት መብራቶችን ከጀርባቸው አድርገው ገበያ ሚጠብቁ ሤተኛ አዳሪዎች ጀርባቸዉን በወይራ ለታጠነ ጎጆዋቸው አቀብለው ፊታቸዉን ብርድ ያስለበልባሉ : ሠካራም ያሰድባሉ ::
''አዳር ስንት ነው ?''
አለ ኤፍሬም ያንገቷን ንቅሳት እያስተዋለ : በቫዝሊን የተወለወለ ፊቷ ፈገግ አለ ... ብርድ ያሰመረው ሽብሽብ ሳይቀር ሚስቅ ይመስላል ::

''25 ብር ''
አለች ከፈገታዋ ጋር ገልመጥ ብላ

''20 ብር ነው ያለኝ ''
አላት ጠጋ ብሏት ከስሯ ከእንቅልፏ መነሳቷ በመንጠራራቷ ሚያስታውቅ ድመት ሠውነቷን ታፍታታለች ::

''ተፈንክተሀል እንዴ ...?''
አለች ደሙን እያስተዋለች
''... በል በል ሂድልኝ ወንድሜ ጥምብዝ ብላቹ ስትሰክሩ ወደኛ ትሮጣላቹ የስሜት ማራገፊያ የሆንነው አነሠና ደግሞ ... የስካራቹ ማራገፊያ እንሁን ... ሂድልኝ ሠውዬ ሂድልኝ ሳትዋረድ ...''
አምቧረቀች : አነጋጋሯ የአዲሳባ ሠው እንዳልሆነች ያስታውቃል ::

''የተፈነከትኩት እኔ አንቺ ምን አገባሽ ያን ያህል ደግሞ ራሴን እስክስት አልሠከርኩም ሌቦች ጃከቴን ለመውሰድ ሲሉ ነው የደበደቡኝ ...''
አላት ተጠግቷት እንድታዝንለት በሚጋብዝ ዜማ

''እሺ ግባ .... ግን ይሄ ደምህን እጠብ እኔ የሠው ደም አልወድም ምን እንዳለብህ ምን አውቃለሁ ...''
አለችውና በሩን ለቀቀችለት ::
ኤፍሬም ወደውስጥ ሢገባ ለየት ያለ ጠረን ተቀበለው አፍንጫው ስር የነበረዉን የመቅዲ ጠረንና ሽቶ ስለወሰደበት ተናደደ :: ወይራው ቤቱን ጉም አስመስሎታል :
ባቀረበችለት ውሃ ፊቱን ታጠበ የልብሱን ደም አጠበና ወንበር ላይ አሠጣው :

''ስምሽ ማነው ?''
አላት የአፍረት ቀና ብሎ እያያት ቁመቷ ረጅም ነው

''ፈለቁ ...''
አለችው ኮንጎ ጫማዋን ለማውለቅ ግብ ግብ ይዛ : ድመቷ ከአልጋው እግር ጋር እየተሻሸች በራሷ ዜማ ታዜማለች :

''ኮንደም አለሽ ?''
አላት የሠጣትን ብር ከቁም ሳጥኑ ላይ በረጅም ቁመቷ ተንተራርታ ያወረደችው ጣሣ ውስጥ ስትከት አይቷት :: አልመሰችለትም በቀይ ፓኬት የታሸገ የኮንደም ጥቅል አምጥታ ልብሱን ካሠጣበት ወንበር ላይ አደረገች :: ከዛኛው ክፍል ወንድና ሤት ሲጨቃጨቁ ይሠማል ሚለያቸው ሣጠራ እንጂ አንድ ቤት ነው :: አልጋው ከተጠጋበት ግድግዳ ላይ የሽማግሌ ሠውዬ ፎቶ በጥቁርና ነጭ ተሠቅሏል : ሠውዬው ቀጭን ትከሻቸዉን ለማሳበጥ ሞክረው የተነሡት ፎቶ ነው :: ከሡ አጠገብ የቅዱስ ገብሬል ምስል ዳንቴል ለብሷል ::

ኤፍሬም ፈለቁን ሲያያት መቅዲ እየሳቀች ምታየው ይመስለዋል :: የመቅዲን ጡቶች በመዳፉ ሚዳብስ ይመስለዋል .... ለመጀመሪያ ቀን ይዟት ሲያድር ወገቡ ላይ ጭኖቿን ከፍታ የጋለበችው የስሜት ግልቢያ ትዝ አለው :: ያ ሎቴ ያንጠለጠለ ወገቧ እንደዘንዶ ሲሳብ እየታወሠው .... ስሜቱ ጨፈረበት :: ከዛም ፈለቁ ...... ስር ገብቶ ትር ትር ትር ማለት ጀመረ መቅዲ ያላት እሷም ነበራት መቅዲ ያረገችዉን ሁሉ ፈለቁም የማድረግ ተፈጥሮዋዊ ድርሻ ነበራት ::

ጠዋት ላይ የጎጃም በረንዳ ወፎች ተንጫጩ የአውቶብስ ተራ ማይክራፎን ንግግሩን ጀመረ : የታክሲ ወያላዎች እሪታቸዉን ጀመሩ :: ጎጃም በረንዳ የሌቱን አፍረት ሳትሽኮረመመው የቀን ፈጣጣነቷን ጀምራለች ::

''ሁ ሁ ሁ ሁ ሁ ሁ ......''
የፈለቁ ጩኸት እንኳንስ በስካር ተኝቶ የነበረዉን ኤፍሬምን ቀርቶ የሞቱትንም ይቀሰቅሳል ::

''ውይኔ አባቴ ወይኔ አባቴ ......''
ፈለቁ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ነው :: ኤፍሬም ግራ ገብቶታል ራቁቱን ሆኖ ሚያደርገው ግራ ገባው : ልብሱን በዓይኑ መፈላለግ ሲጀምር በርካታ ሴቶች ገቡና ከፈለቁ ጋር እዬዬያቸዉን ቀጠሉ :: ኤፍሬም እንደምንም ራቁቱን ሆኖ ልብሱን ይዞ ሲወጣ ድንገት ዓይኖቹ ከሌላ አምሳያው ሁለት ዓይኖች ጋር ተጋጭቶ ውሃ ሆነ ::
ከቤቱ በራፍ ላይ መርዶዉን ሊያረዱ ከተሠበሠቡት ሌሎች ሴትች መሀል አንደኛው እናቱ ነበሩ

ተፈፀመ


ተፃፈ በዋናው

ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby መልከጻዲቅ » Wed Mar 26, 2008 6:59 am

ያልጠፉ....መብራቶች.... :arrow:

ባንድ....ትንፋሽ...ነው....አንብቤ...የጨረስኴት.....መቸቱና...ገጸ-ባህርያቱ...ያልተለያዩበት....ተገጣጥመው....የሚታዩበት....ውብ....ስራ...ነው... ውድ.. ዋናው :idea: ኤፍሬምን...ጥሩ...ስለኅዋል....የሌባ...ልብ...ለመስረቅ...አይራራም...:!:እናቱ...ቌጥረው....ያስቀመጡትን...ገንዘብ....ከመቀነት...ላይ...በመፍታት....
የፋንታዚ...አለም...ሌባ....ሳይሆን....ታማኝ....ሌባ...መሆኑን....አሳይቷል::"መቅዲ.."ብለህ...የሰየምካት....ሌላዋ....የታሪኩ...ገጸ-ባህሪይ...ስራዋን...በደንብ...ተወጥታለች:: "ቃብድ...ቀድሞ...መቀበል.......ጨመር...አድርጎ....የሰጠ....ከተገኘ...ደግሞ...ላፍ..ማለት...የቡና...ቤት...ሽሌዎች....ባህሪይ...ነው...
የቡና...ቤትን...ህይወት...የሚያሽከረክራት...ብር...እንጂ.....""ፎንቃ..""...የሚባል...ያራዳ....ብሂል....አይደለም::እናም...ኤፍሬም...የራጉኤል....ሽፍታ...ለናቱ....
ያልተመለሰ...ወሮበላ...በሌላዋ...የቡና ቤት...ወሮበላ....የጁን...አገኛታ.. :D ብድር...በምድር...አይነት:: :lol: ""ጄል""...ለምትለዋ....ቃል...ግን...ተመሳሳይ....የአማርኛ...ቃል...ብትመደብለት....የበለጠ....ውብ...ይሆን...ነበር...ብዬ....አስባለሁ....ምናልባት...."የፈረንጅ....ቅቤ...ተቀብታ..." ብንል...ያስኬድ...ይሆን... :wink: ይሄ.ነገር...የኔም...ችግር...ስለሆነ...ነው:: የሴተኛ...አዳሪዎቹ...የምሽት...ሰልፍ...ወደ...ጎጃም...ተራ..ዘለቀ...እንጂ......የጌሾ ተራንም....የሰባተኛንም...የዶሮ...ማነቅያንም...ሰራተኛ...ሰፈርንም...ወ..ዘ..ተ..የምሽት..ውሎ...ያመላክታል:: ..በጣም...ግሩም...ድርሰት...ናት...ብዬአለሁ::
መልካም....ምሽት.... 8)
መልከጻዲቅ
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 899
Joined: Wed Aug 08, 2007 11:45 pm

Postby ውቡ » Wed Mar 26, 2008 8:45 am

ትንፋሼን ሳላቃርጥ ነው አንብቤ የጨረስኩት መጨረሻው ደሞ በጣም ነው ያስደነገጠኝ ለማንኛውም ያንተን ጽሁፍች ሳነብ ፊልም የማይ ነው የሚመስለኝ በጣም ቆንጆ ነው ብእርህ ይባረክ
አድናቂህ
ውቡ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 24
Joined: Thu Jan 03, 2008 11:42 am

Postby እቴነሽ » Wed Mar 26, 2008 9:42 am

ሰላም ዋናው........(ያልጠፉ መብራቶች) ይቺ እጥር ምጥን ያለች ጽሁፍህ እንዴት ትጥማለች ባክህ? ሰሞኑን እዚህ ሰፈር ለጠፋህበት ጥሩ መካሻ ነች ብዪ እገምታለሁ.....

አቦ ተባረክ አንተ ሰዉ....

አክባሪህ
እቴነሽ
እቴነሽ
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 91
Joined: Thu Mar 17, 2005 4:19 am

Postby ዋናው » Fri Mar 28, 2008 12:13 am

መለከፃዲቅ ለሠጠህኝ በጎ አስተያየት ከልብ አመሠግናለሁ:: ያቺ የፈረንጅ ቅቤ አሳቃኛለች ... እስቲ እንጠቀምባት ይሆን የፈረንጅ ቅባት ብንል ትርጉሙ ሊንሻፈፍብን ሆኖ'ኮ ነው እንደወረደ ምንጠቀማት ወይም ወልዲያ ቤት ወስደን ትርጉም እንዲተነተንላት እንደርጋለን::
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Fri Mar 28, 2008 12:14 am

ውቡ እና እቴክስ ለሠጣችሁኝ የተለመደ አስተያየት ከልብ አመሠግናለሁ:
እቴክስ በጣም ጠፍተቻል በሠላም ነው ግን?
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ዋናው » Tue Apr 22, 2008 11:36 pm

ሚጢጢ መዳፍ


ንፋሱ የፒያሳን ጎዳናዎች ከጥግ እስከጥግ አዳርስ ተብሎ ከላይ እንደተላከ ሁሉ የላስቲክና የኮተት መዐት እያንኳኳ ያልፋል:: ቀሚስ ይገልባል... በእድሜ ብዛት የተጣፈ ሻንጥላን እያወላገደ ይታገላል:: ሚጡ ዓይኖቿ ውስጥ የገባዉን አዋራ በትናንሽ ጣቶቿ እንደጨፈንች እያሸችው በእንባዋ ታሟሟዋለች: ከዛም ዓይኖቾ ይቀላሉ:: ቀይ ፊቷን በብርድ ፊርማ ተዥጎርጉሮም ውብ ገጿ እንዳለ ነው:: ካፍንጫዋ ስር የደረቀው የንፍጧ ቅርፋፊ እርብትብት ከናፍርቷን ያመላክታል::
ሚመጸወት ሲመጣ ልክ እንደፒያሳው ነፋስ እሷም በሚጢጢ ባዶ እግሯ እየሮጠች ትንሽ መዳፏን ትዘረጋና አንገቷን ዘመም ታደርጋለች:: ከተጎነጎነ መቆየቱን በመቦዘዙና በመበታተኑ ሚያስታውቅ ፀጕሯን ባንደኛው እጇ እያከከች በኮልታፋ አንደበቷ ትለምናለች: ግን አልተሳካላትም እንደሠውም የቆጠራት የለም:: እሷም ሆድ አይብሳትም ወዲያው ወደጨዋታዋ ትሮጣለች የተንከረፈፈ ቀሚሷን እያዘናፈለች ወደሞነጫጨረችው መሬት ላይ ድንጋይ እየወረወረች እናጣጥ እንጣጥ ትላለች... ወዲያው ደግሞ መዳፏን ዘርግታ ራሷን ጋደድ አድርጋ አላፊ አግዳሚዉን ትለምናለች::

''ዛሬ ምነው አንቺም እንደመስከረም ንፋስ ቅልብልብ አደረገሽ ሚጡዬ...?''
አሏት ጋሽ አስቻለው የተወረወረላቸዉን ሣንቲም ባንድ እጃቸው እየቆጠሩ አንደኛው እጃቸው የለም... ወይም አልነበረም:: ሁለቱ እግራቸዉም እንደዚሁ... የመጸዋቹ አንጀት ጨክኖ ሚቆጥሩት ቀርቶ ብድግ ሚያደርጓት ሳንቲም'ንኳን ሲያጡ የተሸበሸበ የፊታቸው ቆዳ ላይ ሚንጠባጠበዉን እንባ በትከሻው አንገታቸዉን ቆልመመው እየጠረጉ
''አይ ፈጣሪ ለዚች ግማሽ በስባሳ ስጋዬን'ንኳን መሆን አቃተህ...?''
እያሉ ያለቃስሉ::
ከርሳቸው ፈንጠር ብላ የሚጡ እናት ሎሚዎቿን ዘርግታ ገቢያ ትጠብቃለች:: ቀጫጫ ሠዉነቷ እጥፍጥፍ ብሎ ትንሽ ሆናለች: በጊዜ ጠባሳ የተደበቀ ውበቷ ዳመና እንደጋረደው የማታ ጀንበር ሆኗል::

''ምነው ዛሬ ደግሞ ልጅሽ እንዲያ ስትፈነጥዝ አንቺ መተከዝሽ...?''
አሉ ጋሽ አስቻለው ወደሚጡ እናት እያዩ: ቀሚሷን ለመግለብ ከሚታገላት ንፋስ በክንዷ እንደመመንጨቅ ብላ ያጠፈች እግሯ መሀል ሸጎጠችና

''አይ አባት... መቼ ሳልተክዝ ውዬ አውቅና ነው...? ነው ወይስ ዛሬ ነው በመስከረሙ ብረሐን ያስተዋሉኝ...?''
ፈገግ ለማለት ስትል ብልጭ ያሉ ጥርሶቿ እውነትም በቁጠባ ብቻ እንደሚከፈቱ... ለክት ብቻ እንደሚታዩ ሁሉ በረዶ ናቸው::
''ኤዲያ ምን ቢተክዙ ቢያብሰለስሉ አይሞላ..... እንዳስቻለው ገላ ጎዶሎ ለሆነ ሕይወት ደግሞ...''

መፅዋቹ ጠብ ሚያደርግላቸዉን ሣንቲም አይተው ቀና ይሉና የምርቃት መዐቱን ያወርዱታል:: ሚጡ ለርሳቸው የመፀወተዉን እየተከተለች ስትለምን መፅዋቹ10 ሣንቲም ትንሽ መዳፏ ላይ አቀበላት ሳንቲሙን በስስት አይታው ወደናቷ ስታመራ
''ምነው ሚጡዬ አሳሳሽ እንዴ?''
አለቻት በአዋራው የቀሉ ዓይኖቿን አይታ
''ከለሜላ ልግዛበት...?''
አለቻት ሣንቲሙን ወደጀርባዋ እንደመደበቅ እያደረገች

''ግዢበት...''
አለቻት እናትየው በከረሜላ ጉጉት የበሩ ድፍርስ ዓይኖቿን በሀዘን አይታ: ሚጡ ሮጣ ማስቲካ ሲጋራና ከረሜላ ወደሚቸረችረው ጫማ ጠራጊ ሄደች::

''ይሄ ከረሜላ አይገዛም...''
አላት ድንገት ጉልበቱ መሀል አጣብቆ የያዘዉን ያረጀ ጫማ በጅማት ወስውሶ በወረንጦ መጎልጎሉን ገታ አድርጎ እጇ ላይ ያለዉን ድፍን አስርሣንቲም እያየ..
ሚጡ ሣንቲሙን አገላብጣ አየችዉና ሸንኮራ ወደሚሸጠው ደግሞ ሄደች

''እናትሽን 10ሣንቲም ጨምሪ.... በያት::''
አላት ሸንኮራ ሻጩ:: በጨርቅ እንደቁስለኛ የተበተበ ቢላዉ የሸንኮራ ፍርፍሪ በመያዙ ዝምቦች ሊወሩት ያንዣብባሉ:: ከሻጩ ይልቅ ያልተነኩት አገዳዎች በኩራት የመዘጋጃ ጊቢን ግንብ ተደግፈዋሉ:: አሁንም ሚጡ 10ሣንቲሙን አይታው ወደመፋቂያ ሻጩ ሄደችና ቀልቧ የወደደዉን መፋቂያ ስታነሳ ሻጩ እጇን ቀብ አደረጋት::

''... ልገዛ ነው....''
አለች እንደማልቀስ ብላ
''ለየትኛው ጥርስሽ እስቲ እኝኝኝኝ በይ::''
አላት መፋቂያ ሻጩ: እጇን ሳይለቃት የጉንጩ ከፊቱ አጥንት ላይ መለጠፍ የዓይኖቹ መጎድጎድ የከንፈሩ መድረቅ... እሕል ቀምሶ ሚያውቅም አይመስልም ::

''እኝኝ''
አለች ሚጡ ትንንሽ ጥርሶቿን ለማሳየት ቀይ ድዷን እያበራች
''... ለኔእኮ አይደለም ለእማዬ ነው...''
አለች እኝኝ በማለቷ እንዳፈረች ሁሉ አንገቷን ደፍታ

''ለናትሽ ወተት ጥርስማ እኔ በነጻ እሰጥሻለው ታዲያ ንገሪያት እሱ ነው የላከልሽ ብለሽ...''
አላት የተከናነበችዉን ሎሚ ሻጭ እናቷን እያየ

ሚጡ መፋቂያው ቢሰጣትም ለምና ያመጣችው ሣንቲም ምንም የመግዛት አቅም እንደሌለው አይታ ተናዳለች...

''ልመዘን...?''
አለች ሚዛን ስሩ አኑሮ ቀጫጫና ወፍራም በመለካት ዳቦዉን ሚጠብቀዉን ወጣት.... 10ሣንቲሟን እያሳየችው: በቁጣ
''ሂጂ ወደዚያ እቺ ሳትፈለግ ተፈልፍላ...''
ከተናገረ ሣምንት ያልፈው ሚመስል ድምፁን ትንሿ ሚጡ ላይ ሞረደ ... በሞረድ ዓይኖቹም እያፈጠጠባት.... ሚጡ እንደንፋስ በርግጋ ወደናቷ ሮጠች

''እማዬ መፋቂያ አመጣዉልሽ...''
አለቻት ለናቷ ቅርፊቱ በቄንጥ የተቀረፀ ረጅም መፋቂያዉን እያቀበለቻት
''አይ ሚጢዬ.... ላንቺ ከረሜላ ብለሽ... ለኔ መፋቂያ ገዛሽ?''
አለቻት አቅፋ አንገቷ ስር እየሳመቻት እንዲህ አድርጋ ስትስማት የሚጡ አባት ትዝ ይላታል እሱም በፍቅራቸው ጊዜ ተላፍቷት ካደከማት በኌላ አንገቷ ስር ነበር ሚስማት
''እስቲ... ባክህ... ምን እንደድመት አንገቴን...''
ትላለች ስሜት ባወረዛው ፊቷ የውሸት ቁጣ እየሞከረች
''ለዛሬ ድመት ብንሆን ምን አለበት ውሻ እያረጉን ስንት ጊዜ እንኖር የለ...?''
ይላታል በቀን ስራ የጠነከረ መዳፉን ወገቧ ላይ እየጠመጠመ...
አንድ ቀን እንዲሁ በድሕነት ፍቅራቸው ሐሤትን እያገኙ በመዋደዳቸው ድሕነትን ድል እየነሡ እንዲህ አለችው
''እኔ ያንተ ልፊያ በቃኝ አሁንማ ምትላፋው ላመጣልህ ነው...''

''አልገባኝም...?''
አላት ዓይኖቹን አፍጥጦ

''አሳድገህ ምትላፋው ላመጣልህ ነዋ...''

''አሁንም አልገባኝም...''
አላት

''ኡፍፍፍፍ አንተ በቃ ይሄ ሢሚንቶ ጆሮህን ደፍኖታል አይደል?''
አለችው በነኚያ ጥርሶቿ ፈገግ ብላ የጎን እያየችው

''ጆሮዬማ እየሠማ ነው ግን ....''
ይሄኔ መዳፉን ይዛ ሆዷ ላይ አኖረችው: ፈነጠዘ
''እውነት እርጉዝ ነሽ?''

''እና በቅሎ መሰልኩህ ....?''
ፈነጠዘ ማንቆርቆሪያ ጠላ አስልኮ ዋንጫዉን አጋጨ::

''ግን ሤት መሆን አለባት...''

''እሱን አንተ አትወስንም እኔ ደግሞ ምፈልገው ወንድ ነው...''
ትላለች እሷም
''በጭራሽ... አቤት.... ፓ! እንደምንም ጥሩ አድርጌ ነው ማሳድጋት''

''እስቲ ልጁ ይምጣ መጀመሪያ... እሳቸው በመጡና አፈር በበሉ አለች አክስቴ....''

ግን ልጁን አላየም:: ሚጡ ልትወለድ 3 ሣምንታት ሲቀረው ከሚሠራበት ፎቅ ላይ ድንጋይ ወደቀበት... ያ ቀን የጣለው ድንጋይ የሚጡ አባትንም ሕይወት ጣለው::

''እማዬ... ያ ከቻቻው ልጅ'ኮ ነው የሰተሽ የኔ 10ሳንቲም ምንም አልገዛ አለኝ...''
አለቻትና ሳንቲሙን እንደመደበቅ እያደረገች አሳየቻት እናትየው ፊቷ በሀዘን ቀጭሟል

''... አስል ሳንቲም ምንም አይገዛም?''
አለች ሚጡ ለማትሠማት እናቷ

''አባባ አስል ሳንቲም ምን ይገዛል?''
አለች ለጋሽ አስቻለው

''አዬ ልጄ ትንሽ አርፈድሽ ተፈጠርሽ እንጂ... ብዙ ነገር ይገዛ ነበር...''
አሏት::
ከማዶ የጊዮርጊስ ቤ/ቲያን ቅዳሴ ከታክሲዎች ጥሩንባና ከአውቶብስ ፍሬን ቡጥጫ ጋር እየተሻማ ይሠማል::

''አባባ... በካ ምንም አይገዛም?''
አለች ሚጡ: ሁሉም ዝም ብሏል ያ ሣንቲም የመግዛት አቅሙን ሊነግራት የቻል የለም:: እናቷ ወደትላንትና ትዝታዎቿ ነጉዳለች

ሚጡ ሣንቲሙን ጋሽ አስቻለው ግማሽ እግሮች ስር ወርውራ ወደ እናቷ ሮጠች

''ለምን ታልክሺያለሽ መፋኪያውን ልመልስለት....?''
አለቻት እንባዋን በሚጢጢ እጇ እያበሠች

''ሚጡ...''
አሉ ጋሽ አስቻለው: ሚጡ ዞር ብላ አየቻቸው

''10 ሣንቲም ምርቃት ይገዛል...''
አሏት

''ምንድነው ምንድነው...?''
ብላ ሮጠች

''እግዚያብሔር ፊቱን አያዙርብሽ...''
አሏት:: ሚጡ ሣንቲሙን መስጠቷን ረስታው ሚጢጢ መዳፏን አየች:

የጊዮርጊስ ደወል.... የመዘጋጃ የሠዓት ደወል.... ይሠማል ጊዜ በማንኛዉም ቅስፈት ስልጣን እንዳለው ለመናገር ሚያሾፍ መሠላቸው ጋሽ አስቻለው::

______________________////__________________________

መጀመሪያ
ተፃፈ በኢት አቆጣጠር 19 91
አዲስ አበባ

ዋናው
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Postby ፈትያ » Wed Apr 23, 2008 1:27 am

wow ዋናው እጅህ ይባረክ በጣም አሪፍ ሚጡዬ አንጀት ስትበላ:cry: :cry: :cry: :cry:


ዋናው በዚህ አጋጣሚ ጥላን አልባን አስታውሳት
ፈትያ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 17
Joined: Thu Jan 29, 2004 11:38 pm
Location: ethiopia

Postby ዋናው » Wed Apr 23, 2008 11:40 pm

ፈትያ wrote:wow ዋናው እጅህ ይባረክ በጣም አሪፍ ሚጡዬ አንጀት ስትበላ:cry: :cry: :cry: :cry:


ፈቲ ስለወደድሽው ደስ ብሎኛል:
ምስጋናዬ ይድረስሽ::
ጥበብ ከእኔ የበለጠ ጠንካራ ናት እኔ እንደምፈልገው ሳይሆን እሷ እንደፈለገችው ታደርገኛለች::
ዋናው
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2799
Joined: Tue Dec 16, 2003 5:29 pm
Location: ሕልም ዓለም

Next

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 2 guests