ShyBoy wrote:ሰላም ሰዎች!
እኔ እንኳን አንባቢ ሰው አይደለሁም ሆኖም ግን ይሄ መጽሀፍ ካነበብኋቸው በጣት የሚቆጠሩ መጽሀፍት አልዱ ለመሆን በቅቷል:: መጀመሪያ ላይ ስጀምረው ለመጨረስ አልነበረም:: እዚህ ዋርካ ላይ ብዙ ሲወራለት ሳይ ምን አይነት መጽሀፍ ቢሆን ነው ብዬ ገረፍ ገረፍ ለማድረግ ነበር አጀማምሬ:: ግን መጽሀፉ ማግኔት ሁኖ ነው ያገኘሁት:: በጭራሽ አይለቅም! እጅግ በጣም የሚስብ ሁኖ ነው ያገኘሁት!!! ብራቮ ተስፋዬ ብያለሁ!!!
ወደ ይዘቱ ከተመጣ ብዙ ነገር ሊባልለት የሚችል መጽሀፍ ነው:: እኔ ግን ያን ያህል አንድን መጽሀፍ comprehend አድርጎ ትችት ለመስጠት ልምዱም ሆነ ብቃቱ ስለሌለኝ ዝርዝር ግምገማውን ለሚያውቁት ልተወውና በጥቅሉ ግን መጽሀፉን በማንበቤ ከልቤ ረክቻለሁ!!! ብዙ ትምህር ይሰጣል: ለማመን የሚያጠራጥሩ ነገሮችም አይጠፉትም:: በጣም ያዝናናል: ብሎም ያስተክዛል/ያሳዝናል:: በጣም ከማልረሳቸው እና ከልቤ ካሳቁኝ ሰዎች አንዱ ተክላይ ተክሉ......ነው ወይስ ተክሉ ተክላይ (ጸሀፊው ራሱ ትክክለኛው የቱ እንደሆነ ግራ እንደሚያጋባው ስለገለጸ ነው) ፍርፍር እስክል ነው የሳቅሁት:: የሲያትሉ ገጠመኞቹም በጣም አስቂኝ.......ሲሉም አሳዛኞች ናቸው: የኬንያውም አይረሳም:: የቁንድዶ ፈረሶች ታሪክ ደሞ የሚገርም ነው:: እኔ ስለዚህ ነገር ጭራሽ ሰምቸ አላውቅም ነበር:: ፖለቲካ ነኩ እና የውትድርናው ጊዜማ ምኑ ይወራል?
መጽሀፉን አንብቤ ከጨረስሁ በኋላ ስለ አቶ ተስፋዬ የተሰማኝ ነገር ቢኖር ግልጽነት እና ተንኮል የማያስብ አይነት ሰው ሁኖ ነው የተሰማኝ:: ድሮ ሳይወድ በግድ ያደረገቻውን ስህተቶች ሁሉ የተናዘዘ ሲሆን ላወጣቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ሳይቀር እርማት ሰጧል (ለምሳሌ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ስለሚለው መጽሀፍ የተናዘዘው ነገር...እኔ መጽሀፉን አላነበብሁም)::
የቡርቃ ዝምታ የሚል መጽሀፍ መኖሩንም ያወቅሁት አሁን ዋርካ ላይ ሲወራ እና እዚህ መጽሀፍ ውስጥ ነው:: ባላነበብሁት መጽሀፍ ላይ አስተያየት መስጠት ባልችልም እነ ሙዝ እና ሀሪከን መጥፎ መጽሀፍ (ኦሮሞን ከአማራ የሚያቃቅር) እንደሆነ ገልጸዋል:: ዛሬ ወሬ ስቃርም EMF ላይ የሆነ ነገር ተለጥፎ አየሁና ቀልቤን ስቦት ከፍቸ አዳመጥሁት:: ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር የተካሄደ ቃለመጠይቅ ነበር:: የቡርቃ ዝምታ ምንም አይነት ተንኮል ከጀርባው እንደሌለ ሰውየው ይገልጻል:: የልቁንም ያለውን እውነታ በማጋለጥ በፍትሄ እንዲፈለግለት ለማድረግ አስቦ እንደጻፈው አይነት ነገር ይገልጻል:: ቃለመጠይቁን እዚህ ጋ በመሄድ በግራ በኩል ካሉት "ቃለ-ምልልስ ከተስፋዬ ገ.አብ ጋር" የሚለውን ተጭናችሁ ማዳመጥ ትችላላችሁ http://www.ethioforum.org/wp/ (የዚህን ቃለ ምልልስ ብቻ ለይታችሁ ሊንክ ማቅረብ የምትችሉ ብትተባበሩ ጥሩ ነው የዌብሳይቱ ይዘት በየጊዜው ሊቀያየር ስለሚችል የቃለምልልሱ ማስታወቂያ ሊጠፋ ይችላልና)::
በሉ ሰላም ሁኑ!
አሁን የቡርቃ ዝምታን አንብቤያለሁ:: የአቶ ተስፋዬ አጻጻፍ ችሎታ በዚህም መጽሀፍ በጣም አስደምሞኛል!!! (ምናልባት ብዙ መጽሀፍ አንብቤ ስለማላውቅ ይሆናል ግን መጥፎ ነገሮቹ እንደተጠበቁ ሁነው አጻጻፉን በጣም ነው ያደነቅሁት........አንባቢን ልብ እየሰቀለ ቁንጥጥ አድርጎ የሚይዝ አይነት ነው-ለኔ)::
መጽሀፉ ልብ ወለድ ቀመስ በመሆኑ እውነትነቱን ማረጋገጥ ባልችልም ሀየሎም አራያ እውነት በዚህ መጽሀፍ እንደተገለጸው አይነት ሰው ከሆነ ከምር እጅግ በጣም ተወዳጅ ሰው ነበር ማለት ነው!!! ግን እውነትነቱን እጠራጠራለሁ:: ምክንያቱም ህወሀት ሰውን አስሮ አያሰቃይም: አይገርፍም እያለ ባንድ በኩል ግን እኔ ባደግሁበት አካባቢ ወያኔዎች እንደገቡ (ከገቡ በኋላ ያለውን እንኳን ሁሉም ያውቀዋል) መሳሪያ አለው የተባለውን ሁሉ ሰው ቤቱ እየገቡ እንዲሁም እስር ቤት እየወሰዱ በጣም ይገርፉ እና ያንገላቱ ነበር::
መጽሀፉ ጥላቻን ለመዝራት የተጻፈ ነው ወደሚለው ስመጣ......... በመሰረቱ እኔ ብዙም የታሪክ አንባቢ እና አዋቂ ስላልሆንሁ "ነፍጠኛ" ስለሚባለው ስርዓት ብዙም የማውቀው ነገር የለም:: ማንም ሰው የመሰለውን እና የተገነዘበውን ነገር በፈለገው መልኩ መጻፍ መብቱ ነው ብዬ ስለማስብ አቶ ተስፋዬ ለምን የቡርቃ ዝምታን እንዲህ አድርጎ ጻፍ ብየ መውቀስ አልፈልግም:: የጻፋቸውን ነገሮች እውነትም ከሚያውቃቸው ኦሮሞዎች ያየው እና የሰማው ከሆነ: መጽሀፉ ላይ ያንጸባረቀው ስሜት በሚያውቃቸው ኦሮሞዎችም ውስጥ ካለ ስለዛ ነገር መጻፍ መብቱ ነው.......ጥፋተኛ ሊያስብለውም አይገባም::
አቶ ተስፋየን የምቃወምበት ግን አንድ ነገር አለ:: ይሄን ያህል ሴንሲቲቭ የሆነ ነገር በሚጽፍበት ጊዜ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አለመመልከቱ:: በኢትዮጵያ ህዝብ ያለው አመለካከት (በአማራው: በኦሮሞው: በትግሬው ወይም በሌላው) እሱ ባስቀመጠው መልኩ ብቻ ነው ወይ? መጽሀፉ ላይ ያሉት ባህሪያት በትክክል ያሉ (የነበሩ) ሰዎችን ባህሪ ከሆነ ምንም ችግር የለም ይጻፉ:: ግን ትግሬው እና ኤርትራዊው ሁሉ ቆራጥ እና በምግባር የታነጸ ብቻ ነው? ፈሪ እና ምግባረ ብልሹ የለም? ኦሮሞው ሁሉ ቂመኛ እና በኦሮሞው ክልል ሌላ ብሄር እንዳይኖር የሚፈልግ ነው? ተከባብሮ መኖርን የሚያስብ: ኢትዮጵያዊነት የሚሰማው ኦሮሞ የለም? ባለስልጣን የሆነው ሁሉ አማራ (እንዲሁም ተራው አማራ) ሆዳም: ጨካኝ: ለሌላው ብሄር ዴንታ የሌለው ነው? ሩህሩህ: አርቆ አሳቢ: ሰላም ወዳድ: ሌላውን ብሄር የሚያከብር የለም? ፖለቲካ ክፍል ወሮበላው እንዳለው መጽሀፉ ላይ ከአማራው አካል የወጣው አንድ ጥሩ አረፍተነገር ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ሊለያዩ ሲሉ ነው (እኛ አማሮች ከማንም አንበልጥም: ከማንም አናንስም የሚል አይነት):: ከኦሮሞዎች ለአማራው ጥሩ ነገር የሚንጸባረቀው በጣም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ከሀወኒ ብቻ ነው:: የቡርቃ ዝምታ ይሄንን ሚዛናዊነት ባለማሳየቱ በጣም ቅር ብሎኛል:: በተረፈ ግን ጸሀፊው ካንዳንድ ሰዎች ያየውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ስሜት በመሰለው መንገድ ማንጸባረቁን አልቃወምም:: መብቱም ነው:: አንድ ሰው ደሞ ይሄንን መጽሀፍ ስላነበበ ብቻ ልቡ በጥላቻ ይሞላል የሚል እምነት የለኝም::
ቸር ያሰማን!!!