ይድረስ ለናቴ
እትዬዋ ይሄንን ደብዳቤ ስጥፍልሽ ያዩኝ እዚህ ከሃገሬው የተመሳሰሉ ሃበሾች በሳቅ ሆዳቸው ንፍር ነው ያለው:: በዚህ ዘመን ብህር ከወረቀት አገናኝቶ ደብዳቤ ሚጥፍ ሰው ማየት ብርቅ ነው አሉ:: ሚገርመው ገጠር የኮምፕተር ደብዳቤ መነበብ እንደማይቻል ሊገባቸው አለመቻሉ ነው::
እስቲ ተያቸው ስለነሱ ኋላ እመለስበታለሁ... አንቺ እንዴት ነሽ? ይሄው እንግሊዝ ኣገር ከገባው የፊታችን ባለግዚያር ለት ሁለት ወር ሊሞላኝ ነው እንዲያው የናንተ ናፍቆት ደርሶ ትክዝ እያደረገኝ መቆዘሜን ያዩ ሃገሬዎቹ ድፕሪሽን ይዞክ ነው እያሉ እንደወንጀለኛ በጥያቄ ያደክሙኛል... እትይዬ አንቺ እንዴት ነሽ? መቼም ይሄ በልግ ሲመጣ ያ አስምሽ ተነስቶ ያሰቃይሻል እያልኩ ሁሌ ነው ማስብ... እስቲ ባይሆን ወቅቱ እስኪቀየር ትልቋ እማማጋ ሂደሽ ክረሚ... የኔ ነገር ዳሩ ከብቶችን ለማን አደራ ብለሽ...? ጊደሬ እንዴት ነች? አደገች? የጋሽ አምሳሉ ኮርማ እንዳይደፍርብኝ አደራ እትይዬ...
እስቲ ስለኔ ላጫውትሽ ... አየ ፈረንጅ ሃገር... ምን ጉድ ነው እትየዋ....? ገና ቀትር'ኮ ነው ሚጨልም... ፈጣሪ ምን ሲል ጀምበር እንደሰሰተባቸው? በዚህ ላይ ውርጩ ክምር ልባሽ ተሸክሜ ውዬ ክምር ብርድ ልብስ ሰሸከም ተኝቼ ይነጋል ጠአይቱን እዚህ ከመጣው ሁለት ቀን ነው ያየዋት እሱንም አየዋት አይባልም እንደ እጅ ባትሪ ብልጭ ብላ ጥፍት ነው ያለችው እረ እስቲ ለብርዱ ሠው ከተገኘ ጥሩ ካቲካላ ስደጂልኝ
እዚህ ካየር መሳፈሪያው ወርጄ ጆሮዎቼ በነጎድ እንደነጎሉ ጓዜን ይዤ ስቅበዘበዝ የጋሽ አዘነ ወንድም ልጅ ደርሶ ተቀበለኝ ብረሓኑ ነው ስሙ ባለንጀሮቹ ግን ቡርኖ እያሉ ነው 'ሚጠሩት እንዴት ያለ ደግ ሠው:: 15 ዓመት ሙሉ ታክሲ ሲሾፍር ነው የኖረ ግን ክፉ ሚስት አለቸው መቼም እሱ አሟልቶ አይሰጥ... እና እልሻለሁ በማግስቱ እጅ ስጥ ብሎ ቢያማክረኝ... እኔ ያንቺ ልጅ ዘራፍ አልኩልሻ ዘርማንዘሬ አዳፍኖ ላሶጣው ነጫጭባ ደጁ ድረስ መጥቼ እንዴት እጅ ልስጥ ብዬ ዘራፍ አልኩልሽ.... ኋላ ለካስ ነገሩ ሌላ ነው... እዚህ ሃገራቸው እንድቀር መላው ሂዶ ለነሱ የውሸት ማልቀስ ነው... እትይዬ... እስቲ ባክሽ የነፍስ አባትሽ አባ ወ/ዮሓንስ ጋር ሂደሽ ይቅር ይለኝ ዘንድ አስለምኝሊኝ... መቼም የዋሸዉት ውሸት እትይ... መቼም አስተርጓሚ ተብዬው ሳያውቅብኝ የቀረ አይመስለኝም...
መልሱ ለትንሳሔ አካባቢ ነው ሚደርሰው ብለዉኝ እየጠበቅኩኝ ነው:: እስከዛው ጎተራ ምታክል ክፍል ሰጥተዉኝ እዛ እኖራለሁ ግን ጸአዳ ነው ምግባቸዉን ግን ልለምደው አልቻልኩም እሳት ያልመታው ነጭ እንቁላል ንፍሮ ከመሰለ ነገር ጋር እየሰጡኝ ወስፋቴ ዝግት ብሎልሻል 'ንዲያው ለአጭ ለአጭ'ኮ ነው 'ሚለው ይልቅ ብረሓኑ እየመጣ አንዳንድ ጊዜ ያገሬ ምግብ ያለበት ሆቴል ወስዶ ይጋብዘኛል... እንጀራቸው ንጣቱ እንደበረዶ ነው ማባያዉን ግን ብዙም አልለመድኩት ብቻ ከምኖርበት ቤት ምግብ ይሻላል:: እትዬዋ ሳልረሳው ልንገርሽማ እዚህ ሃገር ከመጣው ዶሮዎቹን ፈጀዋቸው አልኩሽ: መቼም የዶሮ ግፍ ካለ እኔኑ ፈንግል ይዞኝ ፍንግል እንዳልል ፈራው አንዳንዴ ለኪስ ብለው ከሚሰጡኝ ሳንቲም ሁቴል ሄጄ በወረቀት ቁና ሙሉ ዶሮ ገዝቼ እበላለው... የብዛቱ ነገር ተዪኝ... በዚህ ላይ ብቻዉን ነው 'ሚበላው ሽንኩርት የለ በርበሬ የለ አንዳንዴ እንደገንፎ አፍ ውስጥ ከሚላወስ ድንች ጋር ይሰጡኛል
የመሳፈሪያዉን ነገር አታንሺው እንደቤታቸው ባለፎቅ አውቶብስ አላቸው እሱ ላይ መስታወቂያ ነገር ሹፌሩ መዘውር ላይ እያስነካን ነው ምንሳፈር አያምኗቸዉም መሰለኝ ሳንቲሙን ሌላ ቦታ ነው ምንከፍል ታዲያ ተንደርድሬ ፎቅ ላይ እወጣና ከተማይቱን ቁልቁል እየቃኘው ስዞር ይመሻል ሹፌሮቹ ከውካዋ ቢጤ ናቸው ተሳፋሪ መቀመጫ ሳይዝ ስለሚያበሩ ስንት ቀን የፈርንጅ አሮጊት ላይ ወደቅኩ መሰለሽ? ደግሞ አሉ እዚህ ሃገር ሰው መንካት ነውር ነው አንድ ቀንማ አንዷ እንደቄብ ዶሮ ስታስካካብኝ ግንፍል ብሎኝ አደብ ግዢ ብዬ በቋንቋዬ ዘራፍ አልኩባታ... መቼም ያንን ውሸት ያስፈታልኝ ተርጓሚ አግኝቼው ቢተረጉምልኝ አጥንት ሚነካ ስድብ እንደሰደበችኝ ቀልቤ ነግሮኛል
የባቡሩን ብዛት አታንሺው እትይዋ... ሃገሩን ቀፎ አስቀሩትኮ እንደፍልፈል ከስሩ ፈልፍለው ፈልፍለው ደግሞ ሲበሩ እንደጥይት ነው::
እትዬ አሁን ቋንቋ መማር ጀምሪያለው ሃገሬ እስከ5 የተማርኩት ጠቅሞኛል ብቻ ያስተማሪዋ አፍ አልያዝ አለኝ እንጂ መጻፉንስ ደሕና ነኝ ሁለት መንፈቅ ከተማርኩ የነብርሓኑ ዓይነት አፍ እንደማወራ ተስፋ አለኝ:: ቋንቋ ተማሪ ቤት ስሄድ መንገድ ላይ ያገሬን ልጆች ሳይ እጅ ነስቼ ሰላምታ ስሰጣቸው ልክ እንደጸበኛ ገላምጠዉኝ ያልፋሉ ካንድም ሁለቴ ብረሓኑን ምነው ሰው ሃገር ፍቅር ነሳን ብዬ ጠየቅኩት... "እዚህ ሃገር 'ማታውቀዉን ሠው ሠላም ማለት ነውር ነው" አይለኝም እረ እውቅና ይንሳቸው እትዬዋ ምጽዋት አልጠየቅኩ አሳድሩኝ አላልኩ የግዜር ሰላምታ ማንን ገደለ?
አንድ ቀን ደግሞ የማሪያም ንግስ ቀን ብረሓኑ ቤተስኪያን ይዞኝ ሄዶ ሕጣናቱ ሁሉ ሂሳብ መደመሪያ ማሽን መሳይ ነገር ይዘው ነፋስ እንደሚወዘውዘው ዛፍ ግራ ቀኝ ዘመም ሲሉ ይውላሉ በዚህ ላይ ስጋዎ ደሙን ሲቀበሉም ያቺ ማሽን ከጃቸውና ካይናቸው አትነቀልም... ክብረ-በዓሉ አልቆ ምዕመናኑ ሲበተን የኮረዶቹን አለባበስ አይቼ ማሪያምን ይቅር በዪኝ ብዬ ከደጇ ተመለስኩ... እትይዬ መሰልጠን እንዲህ ነው'ንዴ?
መቼም ብዙ አወራሁብሽ ምን ላድርግ እዚህ ከመጣው ከልብ ያዋራዉት ሰው የለም ሁሉም ወተት እንደጣደ ጥድፍ ጥድፍ እንዳለ ነው... የብርሓኑ ባለንጀሮች ቤት አንድ ሁለት ቀን ሄጄ ነበር ሙሉ ቤተ-ሰብ ተኳርፈው ቴሌቭዢን ላይ ያፈጣሉ ዓይኖቻቸው ከቴሌቭዢን ሲነቀሉ ልጆቹ ቅድም የነገርኩሽ ነገር ላይ ... አዋቂዎቹ ደግሞ ስልኮቻቸው ላይ አንገታቸዉን ይደፋሉ:: እትይ ከምር ሰው ከሰው ማያወራበት ምድር'ኮ ነው የመጣዉት::
ሳልረሳው ላውራልሽማ... እዚህ ሃገር ሚሽቲቱ ሶፋ ላይ ጥፍሯን እያሾለች ባልየው ማጀት ገብቶ ዓይኖቹ በሽንኩርት ያነባሉ... ተደብቄ "አበስኩህ ገበርኩህ" ብዬ አማተብኩኝ::
በይ እስቲ ልተዉሽ እትይዋ... ለሚቀጥለው እኔም ካገሬው ሃበሻ ጋር ለመመሳሰል በዛዉም ቋንቋዉን ለማወቅ በጉራማይሌ እጥፍልሻለው እስከዛው ሰላም ሁኚ ከዘመድ እስከ ጎረቤት ሳሚልኝ:: ብዙ ምታዋራ ካርድ ብረሓኑ ሲጠቁመኝ አዲሳባ እነአንዳርጌ ጋር ደውዬ ድምጼን አሰማለሁ::
ሰላም ሁኚ ውይ ዬኔ ነገር ብረሃኑ ሰው ሲሰናበት "ችርስ" ነው ሚባል ብሎኝ ነበር