ሰላም ዋርካውያን እና ዋርካውያት
ዛሬ የማስተዋውቃችሁ ድረ ገጽ ስንክሳር ይባላል:: ሐይማኖት ተኮር ድረ ገጽ ሲሆን ወደ ታሪካዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ያዘማል:: አንብባችሁ እንድትፈርዱ እነሆ ብያለሁ::
http://www.melakuezezew.info/
ስያሜ እና ባለቤትነት
ስንክሳር- የዲያቆን መልአኩ እዘዘው ገጽ
የቤተክርስቲያን መዓዛ የሆኑ ጻድቃን ፤ ሰማዕታት ፤ ሊቃውንት እና የታሪክ ሰዎች ፤ ለሀገር መልካም የሰሩ ሰዎች ዜና መዋዕል ፤ ብሂል የሚዘከርበት ፤ የሀገራችን የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ፤ በዓላት፤ ዕሴቶች እና ሌሎችም የሚዳሰሱበት ታሪካዊ ቦታዎች ፤ ገዳማት ፤ አድባራት ፤ አብነት ት/ቤቶች ፤ የፀበል ቦታዎች ፤ ቤተመዘክሮች ፤ አብያተ መጻሕፍት ፤ ሰንበት ት/ቤቶች አጠቃላይ ገጽታ የሚታተትበት ገጽ በመሆኑ ስንክሳር ተብሏል::
አላማውና መነሾው
ምክንያተ ጡመራ ( My Reason For Blogging )
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
በእግዚአብሔር አጋዥነት ጦማር ( ጽሕፈት ) እንጀምራለን
ረድኤተ እግዚአብሔርን አጋዥ ካላደረጉ
ልማር ላስተምር ፤ አነብ እተረጉም ፤ እጽፍ እደጉስ ቢሉ አይቻልምና
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማደግ በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚከናወኑ ድርጊቶችን በመረጃ መረብ (Internet) አማካይነት ከአንዱ ክፍለ ዓለም ወደ ሌላው ክፍለ ዓለም ሀሳቦች ፣ አመለካከቶች እና አስተሳሰቦች ይንሸራሸራሉ፡፡
በሀገራችን በኢትዮጵያ ይህ ቴክኖሎጂ ከሌሎች ሀገሮች ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ ያደገ ባይሆንም ቁጥሩ አነስተኛ የማይባል ተጠቃሚ በሀገር ውስጥ ይገኛል፡፡ በውጭው ዓለም ደግሞ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎች መኖራቸው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
በዚህ ዘመን የበርካታ ሰዎች ዓይኖች ከኮምፒውተር መስኮት (Monitor) ፊት ለፊት ተደቅነው፣ በወገባቸው ደግሞ ተንቀሳቃሽ ስልክ (Cell Phone) ታጥቀው እንደመኖራቸው እነኚህ የቴክኖሎጂ ግኝቶችን ለመንፈሳዊ ሕይወት ጥንካሬ በመጠቀም ዘመኑን የመዋጀት ሥራ መሥራት ግድ ይለናል፡፡
በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች የጡመራ መድረኮች (Blogging Sites) ቢኖሩም ከ50 ሚሊዮን በላይ ለሚደርሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምዕመን ግን ከ5 ወይም ከ6 በጣት የሚቆጠሩ የጡመራ መድረኮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም በማኅበራዊ ሕይወት፣ በግዕዝ ቋንቋ፣ በትምህርተ ሃይማኖት፣ ዜና ያተኮሩ የቤተክርስቲያኒቱ ፍሬዎች በሆኑ ልጆች የሚዘጋጁ ናቸው፡፡
በሀገራችን ኢትዮጵያ ከ36,000 በላይ ገዳማትና አድባራት፣ እንዲሁም በርካታ ታሪካዊ ቦታዎች ከመኖራቸው በተጨማሪ አኩሪ ሥራ ሠርተው ያለፉ ስማቸው በወርቅ ቀለም የተፃፈ ፤ ከመቃብር በላይ የገዘፈ የታሪክና የእውነት ባለቤት አባቶች እና እናቶች ነበሩን፣ አሉን ወደፊትም ይኖራሉ፡፡ የእነኚህን ቅዱሳን መካናት እና ቅዱሳን ሰዎች ሕይወት በመዘከር ትውልዱ ከእኔ ምን ይጠበቃል? ብሎ እንዲጠይቅና ታሪካዊ ኃላፊነቱን በመረዳት ይህም ትውልድ በተራው ታሪክ ሠሪ ትውልድ እንዲሆን የቀደሙ አባቶችን ሥራ እና ሕይወት መካፈል እንችል ዘንድ ይህ ስንክሳር የተባለው የጡመራ መድረክ (Blogging Site) ተከፈተ፡፡
በዚህ የጡመራ መድረክ ገዳማት፣ አድባራት፣ አብያተ ክርስቲያናት፣ የአብነት ት/ቤቶች፣ የፀበል ቦታዎች፣ ታሪካዊ ቦታዎች ፤ ቤተ መዘክሮች፣ አብያተ መፃሕፍት፣ ሰንበት ት/ቤቶች እና ሌሎችም መካነ ታሪኮች እንዲሁም የቤተ ክርስቲያን መዓዛ የሆኑ የቅዱሳን፣ ፃድቃን፣ ሰማዕታት፣ ደናግል፣ መነኮሳት፣ ነቢያት ሐዋርያት፣ አበው ወእማት፣ መምህራን፣ ሊቃውንት፣ ጳጳሳት፣ ወንድሞችና እህቶች አርአያነት ያላቸው ሰዎች ዜና መዋዕል፣ ገድል፣ ትሩፋት፣ ብሒል የሚዘከርበት የሀገራችን የሚንቀሳቀሱ እና የማይንቀሳቀሱ ቅርሶች ፤ በዓላት፤ ዕሴቶች እና ሌሎችም የሚዳሰሱበት ይሆናል፡፡
በዚህ የጡመራ መድረክ (Blogging site) የሚወጡትን የተለያዩ ጽሁፎችን፣ ሥዕሎችን፣ ቪዲዮዎችና የተለያዩ መረጃዎች የጡመራ መድረኩ ባለቤት በተለያየ ጊዜ ታትመው የወጡ መጻሕፍት፣ መጽሔት፣ ጋዜጣ፣ ዜና መዋዕሎች፣ በራሪ ወረቀቶች እና ድረ ገጾች (websites) በዋቢነት ከመጠቀሙም ባሻገር የተለያዩ ቦታዎችን በአካል በመሔድ የሚያደርጋቸው ቅኝቶች ግብዓቶች ናቸው፡፡
የጡመራ መድረኩ ተሳታፊዎች ወደፊት በሚሰጡት፣ የነቃ፣ የጎላ፣ እና የሰላ ምክር እና አስተያየት ለሁላችንም መልካም የትምህርት መድረክ እንደሚሆን ተስፋዬ ነው፡፡ የጅማሬም የፍፃሜም ባለቤት እግዚአብሔር ሁላችንም ያጽናን፡፡
የአባቶቻችን ዕምነታቸው ፀጋ በረከት ረድኤታቸው
ጥርጥር የሌለባት ንጽሕት ተዋሕዶ ዕምነታቸው በእኛ ዘንድ ፀንታ ትኑር
ዲያቆን መልአኩ እዘዘው የኔነህ
melakuezezew@gmail.Com
www.melakuezezew.info
Cell Phone +251-918-774646
ጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን