ተወዳጁ ደምሴ ዳምጤ አረፈ::

ስፖርት - Sport related topics

ተወዳጁ ደምሴ ዳምጤ አረፈ::

Postby ጠና » Mon Nov 05, 2012 5:34 pm

በስፖርት ዓለም ታዋቂና ተወዳጅ የነበረው ደምሴ ዳምጤ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ:: ምንጭ http://sodere.com/profiles/blogs/ethiop ... essie-damt
Unity is Strength!
ጠና
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 143
Joined: Fri Dec 03, 2004 8:01 pm
Location: united states

Postby እንሰት » Thu Nov 15, 2012 3:41 am

ለጽኑዎቹ የደምሴ ወዳጆች
አንድ መጣጥፍ አነበብኩና በኮፒ ፔስት እዚህ አመጣሁዋት:: እርግጠኛ ነኝ እንደምትወዱት::

ደምሴ ዳምጤ - ከቅድመ ጋዜጠኝነት ዘመኑ ትዝታዎች
http://cyberethiopia.com/news/?id=196670

ተዘራ እሸቴ
በስፖርት ዘጋቢነት ድንቅ የሆኑ ባለሙያዎች ስራቸውን አስቀምጠውልን አልፈዋል። በርካቶች ደግሞ የነሱን ፈለግ ተከትለው ድርሻቸውን ተወጥተዋል። ደምሴም ከነዚህ ተርታ ይመደባል።

ደምሴና ታላቅ እህቱ እታአፈራሁ፤ ከአቶ ዳምጤና ከወይዘሮ እህተ በድሬዳዋ ከተማ ተወለዱ። ደምሴ ልጅ ሆኖ ሳለ አቶ ዳምጤ ከባለቤታቸው ተለያይተው በስራ ዝውውር ኑሮአቸውን በአዲስ አበባ አደረጉ። ሌላ ትዳርም መሠረቱ። ደምሴም ትምህርቱን ለመከታተል እንዲያስችለው በትዳር አለም ወደምትኖረው ታላቅ እህቱ ዘንድ ተጠግቶ መኖር ጀመረ። እኔም ከእህቱ የነበረኝ ጉርብትና ደምሴን በቅርበት እንዳውቀው እረዳኝ።
እራሱ ደምሴም ሆነ ሌሎች እንደሚመሰክሩለት ተሰጥኦውን ፈልጎ ለማግኘት ያጠፋው ጊዜ አልነበረም። አዎ! … የስፖርት ዘጋቢነት ሙያውን የመረጠው ገና በጠዋት ልጅ ሆኖ ሳለ ነበር። እኔም ዛሬ ድረስ ከተማሪነቱ ቅድመ ጋዜጠኝነቱ ጎሌቶ ይታወሰኛል። በሌላ መልክ የሚገለፅበትን የቆየ ሌላ ትዝታ ለመፈለግ ውስጤን ብፈትሽም ማግኘት አልተቻለኝም። ነገሩን አልኩ እንጂ ጠቅላላ ህይወቱ በዚሁ የተሞላች ነበረች።


ወደ እዚህ ሙያው ለመሳብ በድሬደዋ ከተማ አሸዋ ዳርቻ ይደረጉ የነበሩት የታዳጊ ህጻናትና የወጣቶች የእግር ኳስ ግጥሚያወች ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው። በርግጥ የኳስ ፍቅሩን በንቁ ተመልካችነት፥ ታዛቢነት፥ ደጋፊነት… ከመግልጽ ባለፈ እራሱን ያሳተፈበት የእግር ኳስ ቡድን አልነበረም። ለዘጋቢነቱም በወቅቱ ታዋቂ የነበረው የስፖርት ጋዜጠኛ ሰለሞን ተሰማ ዜና አቀራረብ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል።


የደምሴ ወደ አማተር ጋዜጠኝነት አመጣጥ በኔ ትውስታ

የሆነው ነገሩ እንዲህ ነበር። በወቅቱ የነበሩት የድሬዳዋ ስፖርት ኮሚቴ አባላት የስራና የቤተሰብ ሀላፊነት ጫና የነበረባቸው ነበሩ። ከዚህም የተነሳ የስፖርት ዘገባውን አጠናክሮ ለዜና ማብቃት ድክመት ጎልቶ ይታይባቸው ነበር። በዚህ ክፍተት ነበር ደምሴ የህይወት ጥሪውን ለማሳካት ብቅ ያለው። ህልሙን እውን ለማድረግ የነጻ አገልግሎት ለመስጠት እራሱን አቀረበ። አውንታዊ ምላሽ አገኘ። በሙያው ስልጠና ሳይኖረው ትምህርቱንና የስፖርት ዘጋቢነቱን አጣምሮ ያዘ። በእድሜ ክልሉ የነበሩት ባልሄዱበት ጎዳና ጉዞውን ቀጠለ። ነፃ የስልክ አገልግሎት እና ነፃ የስታድዮም መግቢያ ካርድ (ታሴራ) ተችሮት አገልግሎት መስጠቱን ጀመረ። በጥረቱም ስኬታማ ሆነ… የድሬደዋ ስፖርት አፍቃሪወችንም ቀልብ ገዛ። ደምሴን በየመንገዱ እየጠራ አድናቆቱን የሚቸረው የድሬደዋ ስፖርት አፍቃሪም በረከተ። ስሙ ገነነ። ወደፊት ጎልቶ የሚወጣ የጋዜጠኝነት ሙያ ችሎታ እንዳለውና ለሙያው የተሰጠ መሆኑንም አሳየ። በጊዜውም አማተር ጋዜጠኛ ተባለበት። በዚህ ጊዜም ያጎለበተው ልምድና እውቅና ለሁዋለኛው የጋዜጠኝነት ዘመኑ የማእዘን ድንጋይ ሆኖለት አለፈ።


ደምሴ በአንደበቱ ”በሙያው ተምሬ ያካበትኩት እውቀት ሳይኖረኝ ከህዝብ ተምሬ ነው ህዝብ ያገለገልኩት” ብሏል። እውነት ብሏል። በግለሰብ ደረጃም ለእውቁ የስፖርት ጋዝጠኛ ሰለሞን ተሰማ አስተዋጽኦም ትልቁን ስፍራ ሰጥቷል። ይሄ እኔም በቅርበት ሳየው የነበረ በመሆኑ ዛሬም ይታወሰኛል። ሰልሞንን የምሆን ምኞት በሁለንተናው ተናኝቶ፤ በሰለሞን ስራወች ውስጡ ገዝፎ፤ ለሰለሞን ያለው አድናቆት ጣሪያ የነካበት ወቅት ነበረ። በጥቅሉ በሰለሞን ቀልቡ ተሰርቆ ነበር።


በቅርበት ለምናውቀው የደምሴ ቅድመ ጋዜጠኝነት ጉዞው እንዲህ ቀላል አልነበረም

ደምሴ ታላቄ ስለነበር በሄደበት ሁሉ ተከትየው አልሄድኩም፤ በዋለበትም ቦታ ሁሉ አብሬው አልዋልኩም። ነገር ግን ዘወትር በምሳ ሰአት በቅጥር ግቢያችን በሚገኘው ትልቅ ዛፍ ስር አብረን እንታደም ነበር። በዛ ቆይታችን አባቱ ከሚልኩለት መደጎሚያ ላይ ቆጥቦ ዘወትር የሚገዛውን ጋዜጣ እናገለብጣለን። ደምሴ ጋዜጦቹን የሚገዛው ለመረጃነት ብቻ ሳይሆን የሙያ ብቃቱንም ከፍ ለማድረግ ነበረ። ድምፁን ከፍ አድርጎ እንደ ሰለሞን ተሰማ በፍጥነት ለማንበብ ጥረት ያደርጋል። እኔም አንዱን ገጽ ለማንበብ ስንት ደቂቃ እንደፈጀበት እመዘግባለሁ። ለማንበብ የስፖርት አምድ ካለ ያስቅድማል። ከሌለም ሌላውን ያነባል። ሰኞ ሰኞ ደግሞ እሁድ እለት በስታድዮም የተካሄደውን ስፖርት ለማታው የሬድዮ የስፖርት ዘገባ በዛችው ዛፍ ስር ያጠናቅራል። በስልክ ለማስተላለፍ የማያደርገውን የንባብ ልምምድም አዳምጣለሁ። በዚህ አያበቃም። ማታ ደግሞ የዘገበውን ዘገባ ከሬድዮ አብረን እናዳምጣለን። በዛ ምሽት ከኔ ሌላ ስሜቱን የሚጋራ በአካባቢው ስላልነበረ ብተኛም ይቀሰቅሰኝል። ሀሳቤንም እንድሰጥ ይጠይቀኛል። እኔም ሙያው ባይኖረኝም ከውስጤ የተሰማኝን አድናቆት እቸረዋለሁ። በርግጥም ደግሞ ከማንም በላይ አድናቂው ነበርኩ።


ታድያ ከዚህ ምሽት የስፖርት ዘገባው ማግስት ወደ መሀል ከተማ ብቅ ሲል የሚገጥመውን ያውቅ ነበር። ጨዋታውን እንዳየው ለዜና በማቅረቡ ከተመልካች አድናቆትን ሲቸር፤ ከእግር ኳስ ተጫዋቾች በተለይ በተከላካዮችና በበረኞች እርግጫና ጥፊን አልፎ አልፎ ይቀምስ ነበር። ለዱላ የሚዳርጉት ጉዳዮች አጥቂው ተከላካዩን እንዴት ሸውዶት እንዳለፈው...ግብ አግቢው በረኛውን አንጠልጥሎት ኳስዋን ከመረብ እንዴት እንዳዋህዳት... ለምግለጽ የሚጠቀምባችው ቃላቶች ነበሩ። ይህ አገላለፁ ለአድማጩ ቢጥምም በተከላካዮችና በበረኞች አይወደድለትም ነበር። ብዙ ጊዜ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል። ያንን ሳይፈጽም እየቀረ ያየውን በተሰማው መንገድ ገልጾ ለሙያው ሲል ዱላ ይቀምሳል።


በስም እየጠቀሰ ይነግረኝ ስለነበር የምድር ባቡርና የከነማ ተከላካዮች፤ የስሚንቶው በረኛ፤ በኔም ትዝታ እስካሁን አሉ። አንድ ቀን ካድያ የምሰማውን ሊያሳየኝ የገዛውን ጋዜጣ እቤት እንዳድርስልት አስከትሎኝ ይሄዳል። አጋጣሚ ሆኖ የባቡር ተከላካይ በመንገድ ላይ አግኝቶን ሲመታው አይቻልሁ። ደምሴ ዐይኑ እንባ ሲያቀር እኔ ግን እንባ አውጥቼ አልቅሼለታለሁ። ለኔ ልዩ ነበር። ድምሴን ዛሬም ሳስበው በመውደድ ነው።


ደምሴ በባህሪው ተግባቢና ሰላምተኛ፤ ፈገግ ሲል ሁለቱም ጉንጮቹ ስርጉድ የሚሉ፤ አዘውትሮ በእጁ ፀጉሩን የመደምደም ልምድ የነበረው፤ ቀጭን ነበር። ቅጥነቱን ለመሸፈን ሁልቱንም የህዋላ ኪሶቹን በጋዜጣ ይሞላቸው እንደነበር ይታወሰኛል። በጊዜው "ሊያልፍ" እየተባለ የሚጠራውን ሱሪና ጥሩ ሸሚዝ፤ ተረከዝ የሌለው ጫማ ያዘወትራል። ደምሴ ድሬደዋ ተወልዶ ይደግ እንጂ ከጫትና ሲጋራ ከመሳሰሉት ሱሶች የተጠበቀ፤ ውሎውም ከእሱ በእድሜ ከፍ ካሉ የስፖርት አፍቃሪወች ጋር ነበር።

ደምሴ የስፖርት ጋዜጠኛስ እንዴት ሊሆን ቻለ?

ለዚህም ትውስታ አለኝ። ”ሁሉም ነገር የሚፈጠርበት የራሱ አጋጣሚ አለው” ወቅቱ ኢትዮጵያ 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫን የምታስተናግድበት ጊዜ ነበር። ገዜጠኛ ሰለሞን ተሰማና ይንበርበሩ ምትኬ የተወሰኑትን ጨዋታወች ተከታትለው ለመዘገብ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ገብተዋል። አጋጣሚ ሆኖ ደምሴ ሀይለኛ ትኩሳት የተቀላቀለበት ጉንፋን ያመውና ሲጠብቀው ከነበረው ታላቅ ጨዋታ ቀርቶ በቤት ይውላል። ቀልቡን ከሰረቁት እውቅ ጋዜጠኞች ጋርም ሳይታደም ይቀራል። ሰለሞንና ይንበርበሩም ከጨዋታው ፍጻሜ በህዋላ የሙያ ባልደረባቸውን ለመጠየቅ አድራሻውን ያጠያይቃሉ። ጉርብትናዬን ከሚያውቁ ሰወች በተደረገ ጥቆማ እንደምፈለግ ከስታድዮሙ ድምጽ ማጉያ እሰማለሁ። እኔም በጊዜው የደምሴ ጉዳይ እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም ነበር። በተባለው ቦታ ፈጥኜ ተገኘሁ። ከዚያም በቀረበላቸው መኪና ተያይዘን ወደ ደምሴ ታላቅ እህት ቤት አመራን። እኔም በጉዞአችን ላይ በደምሴ ህይወት ውስጥ ዘልቀው የገቡትን ጋዜጠኞች ትክ ብዬ እያየሁ ሳይታሰብ ደረስን።

ደምሴ ታላቅ እህቱ ከባለቤቷና ከሶስት ልጆቿ ጋር ከምትኖርበት አንዲት ክፍል ቤት እንደተኛ ደረስን። አልጠበቀም ነበር። ሰለሞንና ይንበርበሩም ባጋጠማቸው ነገር ተደናግጠዋል። በፈገግታቸው ሊሸፍኑት ቢሞክሩም በፊታቸው ላይ እየተገለጠ ይወጣል። አዎ! ... ያልጠበቁት ነገር ተከስቷል። ጠይቀውት ሲወጡም በመሀላቸው ፀጥታ ሰፍኖ ነበር። ሰለሞን ዝምታውን ለመስበር ይመስላል "እንደዚህ አልጠበቅኩም ነበር ይላል" ይንበርበሩም በሀሳቡ መስማማቱን ፊቱን አቀጭሞ እራሱን በመነቅነቅ ይገልጻል። ወደ መኪናቸው ሲገቡ ለእኔ አጭር ጥያቄ አቀረቡልኝ። ”ከማን ጋር ነው የሚኖረው?” ከታላቅ እህቱ ቤተሰብ ጋር እንደሆነ አጠር ያለ መልስ ሰጠሁ። ደምሴ እራሱን ከሱስ ጠብቆ ከአባቱ ከምትደረግለት ድጎማ ላይ ቆጥቦ፤ አለባበሱን አሳምሮ፤ መታየቱ ደህና ገቢ ያላቸው ቤተሰብ ልጅ እንደሆነ ሳያስጠረጥረው አልቀረም። እነ ሰለሞንም ባዩት ሁኔታ ውስጣቸው ሳይረበሽና ጥርጣሪያቸው ከእውነታው ሳይጋጭባቸው አልቀረም። ብቻ በዚህ ሁኔታ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ይሄዳሉ።


በዛን ሰሞን በስም የማላስታውሰው አንድ የስፖርት ጋዜጠኛ ከሀገር ወጥቶ አልተመለሰም ነበር። እነ ሰለሞንም አዲስ አበባ እንደተመለሱ የደምሴን ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተውት ነበር። በወቅቱ የነበሩት ባለስልጣንም ከሀገር ወጥቶ ባልተመለሰው ጋዜጠኛ ቦታ የወሎውን አማተር ጋዜጠኛ ለመቅጠር ዝግጅት አጠናቀው ጨርሰዋል። በዚህ ጊዜ ነበር እነኚህ ተደማጭነት የነበራቸው እውቅ ጋዜጠኞች፤ ደምሴ ለአመታት በነፃ ሲያገለግል በአስቸጋሪ ህይወት ውስጥ ሆኖ እንደነበር አለቃቸውን አስረድተው ያሳመኑት። ሀሳቡንም እንዲቀለብስ የተማፀኑት። ለጉዳዩም ክብደት ለመስጠት ደምሴን በአስቸኳይ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ ይደውሉለታል። ደምሴም ከመቻኮሉ የተነሳ የትምህርትመረጃወቹን እንኳን ሳይዝ ተነስቶ ውልቅ ይላል። በአስቸኳይ የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መረጃውን አውጥቼ እንድልክለት ደወለልኝ። እኔም ላኩለት። እሱም በዛው ሳይመለስ ቀረ።

ከአማተር ጋዜጠኝነት ወደ ጋዜጠኝነት ተሸጋገረ። ጋዜጠኝነትም ሙያው ሆነ። በርቀት ሲያደንቃቸው ከነበሩት ጋዜጠኞች ጋርም በቅርብ ሆኖ ደሞዝ ተከፍሎት ለመስራት በቃ። እነ ሰለሞንም ፈለጋቸውን ሲከተል የነበረውን ደምሴን እጁን ይዘው ከደርሱበት አደረሱት። ደምሴም እንደ እነሱ የሙያ ግዴታውን ተወጣ። ከኢትዮጵያ ስፖርት አፍቃሪ ህዝብም አድናቆትን አተረፈበት። በሙያውም አንቱ ተባለበት።


ሁሌም ለማከብረውና ለምወደው ታላቅ ወንድሜ ደምሴ ይችን ካልኩ ቀሪውን ደግሞ በስፋትና በቅርበት ለሚያውቁት እተዋለሁ። ብርታቱና አለመሰልቸቱም ትውስታዬ ሆኖ አብሮኝ ይቆያል። ተግባሩምያኮራኛል።
ለቤተሰቦቹና ለአድናቂዎቹ ጽናናትን ይስጥልኝ!!!
እንሰት
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1213
Joined: Sun Jan 30, 2005 1:14 am
Location: united states

Postby ተድላ ሀይሉ » Sat Nov 17, 2012 2:46 am

ወንድማችን ጠና :-

ይህንን መድረክ ስለከፈትክልን እግዚአብሔር ይባርክህ::

እንሰት:- አንተ በተግባር እንዳሣየኸን እንግዲህ ስለ ሟቹ ወንድማችን ደምሴ ዳምጤ ያገኘነውን መረጃ ሁሉ ወደዚህ ቋት እያመጣን ለትውልድ መማሪያ : ለማያውቁት እንዲያውቁት : የሚያውቁትም እንዳይዘነጉት ለማድረግ እንጣር::

ምንጭ:- PeaceMind2011, Published on Nov 6, 2012. Demissie Damte - Rest In Peace.

ተድላ
የወያኔ ሕገ -አራዊት አንቀፅ 39 ኢትዮጵያን የመበታተኛ ፈንጂ ነው !
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር !!!
ተድላ ሀይሉ ዘብሔረ -ኢትዮጵያ ::
ተድላ ሀይሉ
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 4903
Joined: Fri Mar 17, 2006 2:45 pm
Location: ኢትዮጵያ


Return to Warka Sports - ዋርካ ስፖርት

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 3 guests