መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት - አሌክስ አብርሀም

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት - አሌክስ አብርሀም

Postby መንክር » Fri May 03, 2013 9:15 pm

የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት .....(ምናባዊ ወግ )
መግቢያ
‹‹ ለምን መግበያ አስፈለገ ››ካላችሁ መልሴ ‹‹ጥያቄ አታብዙ›› ብቻ ነው! እንደውም በቀጥታ ወደታሪኩ ልግባ.....
ሰማይ ቤት ነው ...ፀሃይ በደቡብ በኩል የሚያምር ‹‹ፒንክ›› ብርሃኗን ረጭታለች ..... ( አላያችሁትም አላየሁትም የፈለኩትን ብናገር እንዳትነተርኩኝ!!) እዚህ ሞቱ ብለን አይናችን እሰኪጠፋ ያለቀስንላቸው ሁሉ ዘና ብለው በቀን አስራ ሶስት ጊዜ እየበሉ እንደየምርጫቸው እየለበሱ በቅንጦት ይኖራሉ!! ድሮ የሞተ ዘንድሮ የሞተ የለም ! ማንም ሲሞት በቃ ይቀላቀላል.. እዛ ጥግ ላይ ቅደስት አርሴማን የመሰለች ቆኝጆ ብርሃን የመሳሰሉ ወንድና ሴት አሳላፊወች አጅበዋት በፍቅር ለቁርስ የተሰለፉትን ሙታን ትመለከታለች ....ቁርስ የሚታደለው ስም እየተጠራ ነው ...ቆንጆዋ ሴት ፈገግ ብላ ተናገረች ‹‹ አዲስ የመጣችሁ እንኳን ደህና መጣችሁ ይሄ የእግዚአብሄር መንግስት ነው... አሁን በዚህኛው አለም አቆጣጠር ከዘላለሙ አስር ቢሊየን ...ሶስት መቶ ሚሊየን ዘጠና ሁለት ሽ አራት መቶ ሰባኛው ሰአት ነው ....የዛሬው ቁርስ ክሮቶ ፐረሰኪ ነው ›› ስትል ሁሉም አጨበጨቡ፡፡ በሰማይ ቤት እጅግ ተወዳጅ የሆነና ፓስታ የሚመስል ምግብ ነው!! ብዙ ጊዜ ይሄ ምግብ የሚዘጋጀው እንግዳ(አዲስ ሟች) ሲመጣ መሆኑን ሁሉም ስለሚያውቁ ማን መጥቶ ይሆን በማለት ዞር ዞር እያሉ ተመለከቱ፡፡ በእርግጥም አንድ አዲስ እንግዳ መሃላቸው ነበር ‹‹ የምድራዊት ኢዮጲያን ለ21 አመት የመሩ አቶ መለስ ዜናዊ ›› አለ አንድ ግዙፍ ሰውነት ያለው መልአክ....ሁሉም ‹‹እንኳዋን ደህና መጣህ ›› እያሉ ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉ ለእንግዳው...ለአቶ መለስ!!
በዚህ ሁኔታ ቅድሚያ እንግዳው ቁርስ አንስቶ በግዙፉ መለአክ እየተመራ ኢትዮጲያዊያን ወዳሉበት ታላቅ መናፈሻ የሚመስል ቦታ ሄደ... ንጉስ ሃይለስላሴን ገና እንዳያቸው ነበር ያወቃቸው ምንም አልተቀየሩም ያኔ ዊንጌት በትምህርት ጥሩ ውጠየት አምጥቶ የሸለሙት ጊዜ እንዳያቸው!! ከጎናቸው ታላቁ ሚኒሊክ ለጣይቱ ‹‹ አፈር ስሆን እችን›› እያሉ ጉርሻ ዘርግተው በፍቅር ይስቃሉ ...ትንሽ ራቅ ብሎ ኮስተር ያለ ሰው ሹርባው ትከሻው ላይ ዘንፈል ብሎ በዝምታ ቁርሱን ይበላል! ዝምታው ያስፍራል ...መለስ በግርምት ይህን ሰው አየው ለራሱ ‹‹ቴውድሮስ ››ብሎ አንሾካሾከ፡፡ ሌላ ባለሹርባ ሰው ደግሞ ከቴድሮስ ጎን ተቀምጧል ...ይኋንስ ነበር ....መለስ ራመድ ብሎ ይኋንስ አጠገብ የነበረ ክፍት ቦታ ላይ ተቀመጠና ወደዩሃንስ እያየ ‹‹ከመይ›› አለ!! ድንገት ሁሉም በሳቅ ፈነዱ!! ቴውድሮስ ሳይቀሩ እግራቸውን አንስተው ሳቁ!! ሚኒሊክ ሳህናቸውን በግራ እጃቸው ይዘው በቀኛቸው አይበሉባ እንባቸውን እየጠራረጉ ‹‹ እመብርሃንን የትግሬ ሰው እንደሆነ ገምቸ ነበር›› ሲሉ ሳቁ የበለጠ ሞቀ!! ‹‹ወዳጀ›› አሉ ሚኒሊክ ‹‹...እዚህ ምድራዊ ቋንቋ የለም ትንሽ ስትቆይ ውስጥህ በአንድ ቋንቋ ይሞላል ...እሱም የፍቅር ቋንቋ እንለዋለን!! ›› መለስ ወደይኋንስ ተመለከተ እራሱን በመነቅነቅ የሚኒሊክን ቃል እውነት መሆኑን አረጋገጠለት፡፡
ሲፈራ ሲቸር ‹‹ እዚህ አለም ላይ የብሄሮች እኩልነት የለም ማለት ነው እንዴት አንድ ቋንቋ ብቻ ሌሎች ላይ ይጫናል››ሲል ኮስተር ብሎ ጠየቀ...›› ቴውድሮስ በአትኩሮት ሲመለከተው ከቆየ በኋላ ‹‹ፍቅር የማንም አይደለም ...ፍቅር ደግሞ የሁሉም ነው ስለዚህ ፊደል ሳትቀርፅ ... ቃል ሳትቀላቅል ድንበርም ሳታበጅለት የምትግባባበት ቋንቋ ካለህ ስለምን ሌላ ቋንቋ ትፈልጋለህ›› አለና ሰሃኑን ለአሳላፊው አቀበለው፡፡ምግቡ እምብዛም አልተበላለትም!!
መለስ ቴውድሮስን በግርምት እያየው ‹‹ ቋዋንቋ እኮ መግባቢያ ብቻ ሳይሆን ማንነትም ጭምር ነው.....›› አለ፡፡‹‹ ማን እንደሆንክ ለሚያውቅህ አለም ማንነትህን ማሳወቂያ እንቶ ፈንቶ ምን ያደርጋል›› ቴውድሮስ መለሰ!! መለስ ‹እነዚህ ሰወች የደርግ ርዝራዥ መሰሉኝ› አለና ከአፉ ላይ መለሰው!! እልህ ቢጤ ግን ሽው አለበት፡፡.ድንገት አንድ ወጣት እያፏጨ መጣና ተቀላቀላቸው‹‹ሀይ ጋይስ... ደግሞ እች መላጣ ማናት ›› አለ ወደመለስ እየጠቆመ፡፡ ሃይለስላሴ ባይናቸው ሲገለምጡት ዝም አለ ወጣቱ !! ‹‹ ልጅ እያሱ ይባላል›› ብለው ለመለስ አስተዋወቁት! ልጅ እያሱ ሳቅ ብሎ ወደመለስ እያየ ‹‹ እንዴት መጣህ; እንደሱ እራስህን አጥፍተህ ....›› ወደቴውድሮስ እያሳየ...‹‹ ወይስ እነደሸባው በካልቾ ብለው አባረሩሽ...ሂሂሂሂ›› ሃይለስላሴ ተበሳጩ!!
.ሚኒሊክ መለስ ነገሩ እንዳልተዋጠለት ገብቷቸው... ወደጀመሩት ወሬ ተመለሱና ‹‹ ሰማህ...መስቀል በፈረንጅ አፍ ጥራው በአበሻ ልሳን ሰይመው ቅድስናውን አትቀንሰውም!! ያው መስቀል ነው ፣ መስቀሉ ላይ ስለሁሉ የሞተው በቋንቋ መከፋፈልን ሽሮ ፍቅር ይሉት ቋንቋ አብስሯልና መስቀሉ በምንም ቋንቋ ቢጠራ ሁሉ ይግባባበታል ሁሉ ያከብረዋል!! አገርም እንዲሁ ነው!! ባንዲራው ቋንቋው ‹‹ብሄር›› ያልከው ሁሉ ቅዱስ መስቀል ነው መስቀሉ ላይ የአገር ፍቅር ይሉት እውነት ከሌለ ከንቱ ነው!! ፍቅር ነው ማንነት !
መለስ ቁርሱን መብላት ጀመረ...በውስጡ ‹‹ እነዚህ ሰወች የሚለቁኝ አይነት አይደሉም ›› እያለ ማሰብ ጀምሮ ነበር!!
‹‹ ያ ባለጌ የት ሂዶ ነው አንተ የነገስከው›› ሲሉ ሃይለስላሴ ድንገት ጠየቁ....
‹‹ማን›› አለ መለስ
‹‹ እኛን የደፈረን ያ መንግስቱ የሚባል ወሮ በላ›› አሉ ቆጣ ብለው!!
‹‹ እሱ የተከበረውን የኢትዮጲያ ህዝብ 17 አመት ሙሉ ሲያሰቃይ ሲያስርና ሲገድል ይሄ ግፍ እንዲቆም በሰላም ብንጠይቀው እንቢ ስላለ ለህዝብ መብት መከበር ስንል ጫካ ገብተን ድራሹን አጠፋነው ... እኛ ኢትዮጲያን ስንቆጣጠር ግፍና ጭፍጨፋው ቆመ›› ከማለቱ ከአጠገባቸው የተቀመጡ በርከት ያሉ ወጣቶች በሳቅ አውካኩ፡፡ መለስ ዞር ብሎ አይቷቸው ...ሲያበቃ እነማን ናቸው ብሎ ይኋንስን ጠየቀው ይኋንስ በረጅሙ ተነፈሰና ‹‹ በምድር አቆጣጠር 1997 በአንድ ላይ የመጡ ናቸው ›› አለው ባጭሩ!! ‹‹ እዚህም ጩኧት አለቻ›› ሲል አሰበ መለስ!! ከዛ በኋላ ዝምታ ነገሰ፡፡ የልጅ እያሱ ፉጨት ብቻ ነበር የሚሰማው .....
ይቀጥላል...
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby መንክር » Fri May 03, 2013 9:27 pm

by Alex Abreham part II
የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት .....(ምናባዊ ወግ )
ክፍል ሁለት


አቶ መለስ የመጀመሪያ ቀን የመንግስተ ሰማይ ቆይታቸው የተሰጣቸው ክፍል እጅግ ሰፊና የኢትዮጲያ ቀደምት ነገስታት ጋር በጋራ የሚጠቀሙበት በመሆኑ ነገሩ እንግዳ ሆኖባቸው እንቅልፍ ሳይወስዳቸው ብዙ አምሽተው ነበር ... እንቅልፍ እምቢ ብሏቸው ሲገላበጡ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ አቶ መለስን ‹‹ እንግዳው አልተኛህም እንዴ?›› ሲሉ ጠየቋቸው
‹‹ አለሁ›› አሉ ድንገት ከንጉሱ በተሰነዘረው ጥያቄ ደንገጥ ብለው!!
‹‹...ማን አልከኝ ስምህን ››
‹‹ መለስ ...መለስ ዜናዊ ››
‹‹ መለስ.... ከፊቱም ከኋላውም ቅጥያ የለውም ስምህ ?››
‹‹ያው...ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ነበር የሚሉኝ››
‹‹ ሚንስትር ነሃ ...?!.››
‹‹ አይ ጠቅላይ ሚንስትር ነኝ ›› አቶ መለስ ጠበቅ አድርገው ተናገሩ....››
‹‹ታዲያ ንጉሱ ማነው ››
‹‹ንጉስ የለም››
‹‹ፕሬዝዳንቱ ማነው››
‹‹ፕሬዝዳንትም የለም...ይቅርታ ፕረዝደንት አለ...ክቡር ፕሬዝዳንት ግርማ ››ይባላሉ!!
‹‹እንቅልፍ እምቢ አለህ እንዴ...?››
‹‹ አይ በጊዜ መተኛት ስላለመድኩ ...ትንሽ ...››
‹‹ ፈርተኸን እንዳይሆን....ሃሃሃሃ ›› አሉ ንጉሱ ነገር ፍለጋ በሚመስል ድምፅ
‹‹ ለምን እፈራችሀዋለሁ? ሁላችንስ የሰራነው ላንዲት አገር አልነበር ...››
‹‹ እሱን እንኳን ተወው! ያ ዲቃላ ሻንቅላ ባለመምጣቱ እግዜርን አመስግን ....አሱ ቢኖር በትራስ አፍኖ ነበር በተኛህበት የሚያስቀርህ››
‹‹ማነው እሱ?›› አሉ አቶ መለስ ደንገጥ ብለው...
‹‹እኛን የካደን ይሁዳ...››
‹‹እ ...መንግስቱ?....››
‹‹ስሙን ቄስ ይጥራው....›››
አቶ መለስ ከት ብለው ሳቁና ‹‹ እሱስ ቢኖር ለእርሰወም ስጋት ነበር ›› አሉ !! ሁለቱም ሲስቁ ቆዩና ...አቶ መለስ ድንገት ሳቃቸው ጠፍቶ
‹‹ እኔ እምለው ድንገት መንግስቱ ቢሞት እዚህ ክፍል ይመደብ ይሆን እንዴ...?›› አሉ ለመልሱ ጓጉተው ከምኝታቸው ቀና እያሉ..
‹‹ ሌላ ቦታ የት ይሄድ ብለህ; እዚሁ መጥቶ ጉዱን ማየት ነው እንጅ .....›› አቶ መለስ ሳያስቡት አማተቡ! ለአፍታ ዝም ተባብለው
እንደቆዩ ሃይለስላሴ ‹‹ የሆነስ ሆነና አሁን በቦታህ ማን ተተካ..?.›› ሲሉ በጉጉት ጠየቁ...
.‹‹ሃይለማሪያም የሚባል ምክትሌ የነበረ ሰው ››
‹‹እሱ ነው የገደለህ?››
‹‹ኧረ እኔ የእግዜር ሞት ነው የሞትኩት›››
‹‹ ሃዲያ ይሄ ንግስና ያወረስከው ሰው ጋር ዝምድናችሁ እንዴት ነው የሚቆጠረው?››
‹‹የምን ዝምድና?››
‹‹ እችን ይወዳል ተፈሪ›› ብለው ከወገባቸው ቀና አሉና....
‹‹ የትም ለማታቀውቀው ሰው ነው አገርን ያህል ነገር ሰጥተህ የመጣሃው ;?›› አሉ ቆጣ ብለው...
የንጉሱ ድምፅ የቀሰቀሰው ልጅ እያሱ ‹‹ ይሄ ሸባ ሲለፈለፍብኝ ሊያድር ነው እነዴ....››አለ በምሬት ቀጥሎም እንቅልፍ ባጮነጮነው አይኑ መለስን እያየ ‹‹ አንተ አይደክምህም እንዴ ወደዛ አትተኛም ..››አለ እያመኛጨቀ ....
ንጉሱ እየሳቁ ‹‹ና ጉድህን ስማ ኢትዮጲያን ሃይለማሪያም ለሚባል የትም ለማላውቀው ሰው ሰጥቻት መጣሁ ይላል እንግዳው››
‹‹ይስጣታ ! እንተስ ለማንም ወታደር ሰጥተሃት መጥተህ የለ እንዴ›› ብሎ ንጉሱን በነገር ወጋ ካደረገ በኋላ
‹‹ ከምር ግን ለማታውቀው ሰው ነው የሰጠኻት አገራችንን ›› ሲል መለስን ተመለከታቸው...
‹‹ ዝምድና የለንም አልኩ እንጅ አላውቀውም አላልኩም ምክትሌ ነበር በዛ ላይ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ነበር ... በዛ ላይ የተማረ ነው ስለውሃ ጉደይ ምህንድስና ተምሯል ...›› እያሉ ሲዘረዝሩ
ንጉሱ ‹‹ ውሃ አስበላኋት በለን እንጅ›› አሉ !!
እያሱ ‹‹ አሁን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማነው›› አላቸው አቶ መለስን
‹‹ ቴድሮስ አድሃኑ የሚባል የጤና ሚንስትር የነበረ ይሁን ብየ ነው የመጣሁት ... ››
‹‹ እሱንስ ታውቀዋለህ››
‹‹ እ......ማለት ....ያው አንድ ብሄር ነን ››
‹‹ ታዲያ እሱ እስኪመቻች ሃይለማሪያምን አስቀመጥነው አትልም›› ካለ በኋላ
ወደመለስ እያየ ‹‹ ይልቅ ቁም ነገሩን ....ሚስቶችህን ለማን ጥለሃቸው መጣህ ? እንዴት ነበሩ .... ሳይህ አደገኛ ምላስ ነው ያለህ አሪፍ አሪፍ ሴቶች ሳትጠብስ አትቀርም››አለ
አቶ መለስ የዚህን ልጅ ጋጠወጥነት አልወደዱለትም ‹‹እኔ የነበረችኝ አንዲተ ህጋዊ ሚስት ነበረች ›› ሲሉ ሃይለስላሴም እያሱም በሳቅ አውካኩ እያሱ እየሳቀ....
‹‹ ወዳጀ ይሄ እኮ ሰማይ ቤት ነው የሚወቅስህ የለ የሚያመሰግንህ አንመርጥህም የሚል ህዝብ የለ ምን የለ እውነቱን አውራ ባክህ ...ሆሆ አንድ ሚስት ይላል እንዴ ሃሃሃሃሃ ሸባውም አተራምሶታል እንኳን አንተ!›› ወደ ኃይለስላሴ በአሽሙር እያየ..
‹‹ የት አየኸን ሴት ስናተራምስ አንተ? እኛ አንተን መሰልንህ ? " አሉ የውሸት ቁጣ እየተቆጡ!!

ልጅ እያሱ ወደ መለስ ቀረብ ብሎ አልጋው ጫፍ ላይ ቁጭ አለና ‹‹ ሚስትህ ቆን ጆ ነበረች?›› ሲል ጠየቀ
መለስ እንደመተከዝ አለና ‹‹ጀግና ነበረች ... ሲያስፈልግ እሳት የሚተፋ ብረት ይዛ .....››
‹‹ ኧረ ባክህ ባጭሩ መልስ ! አሁን ስለብረት ማን ጠየቀ ፡ ቆንጆ ነበረች አልነበረችም ... መልኳ .... አቋሟ ... ፍቅር ስትለዋወጡ....›› ልጅ እያሱ መልሱን ለመስማት በጉጉት መለስ ላይ አፈጠጠ
አቶ መለስ ኮስተር ብለው ‹‹ ደርግ ጋር በተደረጉ የተኩስ ልውውጦች ባንድ እጅዋ እየተኮሰች በሌላኛው እጇ የፍቅር ደብዳቤ ትፅፍ ልኝ ነበር ....››
‹‹ አንተ ሰውየ ለምን በቀጥታ አትመልስም... ›› ሲል ጮኸ እያሱ....
‹‹ ቆራጥ ነበረች ...››
ሁሉም ባንድ ላይ ረጅም ሳቅ ከሳቁ በኃላ ‹‹ ለምን ያንን ጓደኛህን አትጠራውምና አይነግረንም ›› አሉ ንጉሱ ፡ እያሱን እያዩ
‹‹አሪፍ ሃሳብ ›› ብሎ የሆነ ሰው ሊጠራ ወጣ እያሱ....
‹‹ ማነው ›› አሉ አቶ መለስ እያሱ ሊጠራ የሄደው ሰው ማንነት አስቧቸው!
‹‹በቅርቡ ወደዚህ የመጣ ኢትዮጲያዊ ነው .....እያሱ ጋር ሽርክ ናቸው ... በተለይ ስለሴትና ስለውድ ጉዳይ ሊቅ ነው!! እያሱ በሚገርም ፍጥነት ሰውየውን ይዞት ተመለሰ፡፡ ....ተጠርቶ የመጣው ሰው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ነበር!
‹‹ እንደምን አመሻችሁ ... ወዳጆቸ ›› ካለ በሀኋ ላ ፂሙን እየላገ .. እነዴ...መለስ እንዳትሆን ብቻ...›› አለ ስብሃት ተገርሞ !
አቶ መለስ ፈገግ አሉ ‹‹ ስብሃት እንዴት ነህ ....ስራ በዝቶብኝ ምድር ላይ ሳንገናኝ...››
‹‹እንኳን ከነዛ ብሽቅ ካድሬወችህ ገላገለህ ወዳጀ›› አሉ ስብሃት የመለስን እጅ እየጨበጡ....
እያሱ ... ተቻኩሎ መናገር ጀመረ ‹‹ ስብሃት ለምስክርነት ነው የተጠራሃው የመለስ ሚስት ቆንጆ ናት አይደለችም እስቲ ከነማብራሪያው ንገረን ..... ስንነዛነዝ ነበር ...››
‹‹ አዜብ አዜብ .... እስቲ መጀመሪያ ያችን ነገር አምጣ›› አለ ስብሃት ፡፡ እያሱ ከወደትራስጌው በትንሽ ጠርሙዝ አረቄ ለስብሃት ቀዳለት ለራሱም ያዘ ለንጉሱም አቀበላቸው ...ችርስ ተባባሉና
ስብሃት በረዥሙ ከአረቂው ሳብ አድርጎ በጎርናና ድምፁ
‹‹እነ አብረሃም እነማቱሳላ
ጠጡ ካቲካላ ....››› ብሎ የሚያምር ሳቁን ሳቀ.....ሓሓሓሓሓሓሓሓሓሓ!!
‹‹ እሽ ንገረና ›› አሉ ንጉሱ ‹‹ ከመጣህ አይቀር ንገረን፡፡ ስለሚስቱ ስለርስቱ ስለ መለስ አጠቃላይ ነገር ንገረን በል ጠሃፊ አይደለህም ስላገራችን ኢትዮጲያ ንገረን ያየኸውን የሰማሀውን ሁሉ..›› ስብሃት ግን ያቆማትን ግጥም ቀጠለ
‹‹.... ለማንም ምንም አላሉም
ጠጥተውም ዝም ዝምምምም!!.....›››
እነአዜብ እነ አባ ዱላ
ጠጡ ካቲካላ
ለማንም ምንም አላሉም
ጠጥተውም ዝም ዝምምምም!!....
ዝምምምም!
እነ አርከበ እነ ኩማ...እነ ስዩም መስፍን
እነ ገበረ ፂወን እነ አቦይ ስብሃት
እነ ሪድዋን እነ ካሱ ኢላላ
ጠጡ ካጢካላ
ጠጥተውም .......ዝምምምም
..በ አማራ በኦሮሞ ቤኒሻንጉል
ደግሞ በጋምቤላ
ጠጡ ካቲካላ
ለማንም ምንም አላሉም
ጠጥተውም ዝም ዝምምምም!!.... ኃኃኃኃኃኃኃኃኃኃኃኃኃኀኃኃ ዝምምምምምምም!!!!
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby መንክር » Fri May 03, 2013 10:10 pm

ጠቅላይ ሚንስተር መለስ በሰማይ ቤት ( ምናባዊ ወግ)
ክፍል ሶስት
....ጧት በተፈጠረው ነገር አቶ መለስ ተበሳጭተው እና አዝነው ነገስታቱም ሁሉ አቶ መለስን አኩርፈው እርስ በእርሳቸውም እንደወትሮው ከመጫወትና ከመሳሳቅ ይልቅ አልፎ አልፎ ብቸ ቃል እየተለዋወጡ ነበር የዋሉት! ልጅ እያሱም ሁኔታው አላምርህ ሲለው ገና በጧቱ ነበር ሹልክ ብሎ ወደስብሃት ገ/እግዚያብሄር የሄደው፡፡
በጧት የተፈጠረው ሁኔታ እንደቀልድ ተጀምሮ ነበር ለያዥ ለገናዥ ያስቸገረ የከረረ ፀብ ሁኖ ቁጭ ያለው......
******** **************** ***********************

አቶ መለስ ምሽቱን ልጅ እያሱና ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ ጋር ሲጫወቱ ስላመሹ ድክም ብለዋቸው ነበር ፡፡ ጧት ታዲያ አርፍደው ሲነሱ ክፍሉ ውስጥ ማንም ሰው አልነበረም፡፡ ከምኝታቸው ተነስተው በመስኮት ወደውጭ ሲመለከቱ የኢትዮጲያ ነገስታት በሙሉ አንድ ጉብታ ላይ ቆመው ወደሆነ ቦታ በጉጉት ሲያዩ ተመለከቱ፡፡ ነገሩ ገሟቸው እየተቻኮሉ ወደነገስታቱ ሄዱ፡፡
ነገስታቱ በሁኔታው ከመመሰጣቸው የተነሳ አቶ መለስ አጠገባቸው ሂደው ሲቆሙ እንኳን አላየዋቸውም ነበር፡፡ የሁሉም ወደአንድ አቅጣጫ መመልከት የገረማቸው መለስ ወደዛው አቅጣጫ አይናቸውን ላኩ .....አድማስ ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀስተ ደመና ተዘርግቷል የሰማይ ቤት አድማስ የኢትዮጲያ ብቻ አድማስ መስሏል ....ባንዲራው በዛ ሁኔታ፣ ያውም ከሞቱ በኋላ ሲታይ አይንን በእንባ ይሞላል ...ውስጥን በልዩ ስሜት ያናውጣል ... አፄ ሚኒሊክ በሲቃ መናገር ጀመሩ
‹‹ አገራችን እግርዋ ምድር ላይ ቢሆንም እራሷ ሰማያዊ ነው ....የፈጣሪ ግዛት ናት ....ይሄው ምልክቱ ...ይሄው የጦጲያችን ባንዲራ ...ተዚህ በላይ ምን እማኝ አለ ››
ነገስታቱ ሁሉ በወኔ ተናገሩ ‹‹ እውነት ነው! ውሸትም የለበት ....መጠርጠሩስ ...››
‹‹ ኮከቡ የታለ?>> የሚል ጥያቄ ድንገት ሁሉንም አስደነገጣቸው ፡፡ አቶ መለስ ነበሩ የጠየቁት
‹‹የምን ኮከብ›› ሚኒሊክ ጠየቁ
‹‹ የኢትዮጲያን ህዝብ አንድነትና ተስፋ የሚያመለክተው ኮከብ›› አቶ መለስ በተገረሙት ነገስታት ተገርመው ጠየቁ!!
ሁሉም የአቶ መለስ ጥያቄ ስላልገባቸው እርስ በእርስ ሲተያዩ ልጅ እያሱ ወደመለስ ጠጋ ብሎ ‹‹ ስማ እንቅልፍህን አልጨረስክም እንዴ›› አለ ፈገግ ብሎ...ሁሉም በሳቅ አውካኩና ወደቀስተደመናው ሲዞሩ አቶ መለስ ከመጀመሪያው የበለጠ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው
‹‹ ይሄ የምታዩት አረንገዋዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ብቻውን የኢትዮጲያ ባንዲራ አይደለም›› አሉና የነገስታቱን ቆሌ ገፈፉት...
‹‹ ታዲያ ለማን ልትሰጠው ነው ወዳጀ›› አሉ ሚኒሊክ የመለስን ጤነኝነት በጠርጣሬ እየተመለከቱ
‹‹ የማን እንደሆነ አላውቅም !! የኢትዮጲያ ባንዲራ ህገ መንግስቱ ላይ እንደተቀመጠው መሃሉ ላይ በሰማያዊ መደብ የህዝቦችን አንድነት የሚያመለክት ኮከብ እና ......››
‹‹ዝም በል!!›› አፄ ቴውድሮስ አንባረቁ ሁሉም በድንጋጤ ሽምቅቅ አሉ!!
‹‹ ለምን ዝም እላለሁ...ኮከቡኮ...››
‹‹ መይሳው .....!! አፍህን ዝጋ አልኩኮ አንተ ሁርጋጥ!! ይሄ ሞት የሚሉት የሚያመጣው ያጣ ይመስል የማንንም ሁርጋጥ ይሰበስባል እዚህ ሲሞቱ ከሰው እኩል የሆኑ ይመስላቸዋል....›› አሉና በእልህ ተንጎራደዱ....
‹‹ ሞት የማንኛውም ሰው ዲሞክራሲያዊ መብት ነው ትንሽ ትልቅ ሃብታም ደሃ የለም›› አሉ አቶ መለስ ሁርጋጥ መባላቸው አበሳጭቷቸው ....
‹‹ ኧረ በማምላክ ዝም በል አንተ ሰው ምን ነካህ›› አሉ ሚኒሊክ መለስን እያዩ...
‹‹ አልልም! ዝም አልልም ....እኔ መለስ እንኳን እናንተ ፊት ይቅርና የአፍሪካ ህብረት የጂ ኤት ስብሰባ ላይ ማንም አላስቆመኝ...እናገራለሁ ያመንኩበትን ከመናገር ማንም ዝም በል ሊለኝ አይችልም.....››
‹‹የአፍሪካ ህብረት ...ሃሃሃሃሃሃ ባቀናነው ስካር ተወላገዱበት ....አሉ.... የአፍሪካ ህብረትኝ የተከልነው እኛ አለም በፋሽስት ፍቅር ሰክራ ጥቁርን እንደደዌ ተጠይፋ ባለችበት ወቅት ነጮች እየተሳለቁብንና እየሰደቡን እየተሳለቁብን እራሳቸው መድረክ ላይ ቁመን ልክ ልካቸውን የተናገርንም እኛ ምኑ ነው ብርቅና ድንቁ ምኑስ ነው ዘራፍ የሚያስብለው ....›› አሉ ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ መለስን በቁጣ እያዩ
‹‹ ስማ ...ደማችንን አፍስሰን አጥንታችንን ከስክሰን በዘመናት የገነባናትን አገር እንደድፎ ቆርሰህ .....እነደፀበል የምናመነውን ውሃ እንካችሁ ብለህ ለጅብ አስረክበህ መምጣትህን ያልሰማን መሰለህ ...ጅብ የማያውቁት አገር ሂዶ አጎዛ አንጥፉልኝ እንዳለው መሆኑ ነው ...እንዳሻህ የምትቀባጥርበት ሂድና ቀባጥር እንግዳ ነህ ቀድመን ሙተናል ብለን አንኮራም ብለን ብናስጠጋህ ምድር ላይ የለመድከውን አርቲ ቡርቲ ድስኩር በለመደ አፍህ እኛ ላይ..... ›› አሉ ሚኒሊክ
‹‹ እንነጋገራ...›› አሉ አቶ መለስ እንደቀላል ያዩት ጉዳይ ተራዝሞ እዚህ መድረሱ አስደንግጧቸው
‹‹ ሂድ ወዲያ የሚያነጋግርና የማያነጋግር ጉዳይ ለይ መጀመሪያ›› አሉ ቴውድሮስ ...
‹‹ አንተ ሰውየ ከኔ ጋር ችግር አለብህ ከመጣሁ ጀምሮ በክፉ አይንህ ነው የምታየኝ ላንተ ስል በሂወት ልኑርልህ ›› አሉ አቶ መለስ ቴውድሮስ ፊት ላይ የሚነበበው ንቄትና ጥላቻ አንገሽግሷቸው "
‹‹ ለቴድሮስ ብለህ ለምን ዘላለም ቁመህ አትቀርም ደግሞ ካንተ ብሎ ንጉስ ....ሰላቢ ! ዘር ማንዘርህ ከሃዲ .....›› አሉ ቴውድሮስ አጼ ይኋንስ እያዩ...
አቶ መለስ በብስጭት ቴውድሮስን እያዩ እንደተፋጠጡ ድንገት ኃ/ስላሴ ተናሩ‹‹ ባንዲራ የአንደኛ ክፍል የስእል ደብተር መሰለህ ከመሬት ተነስተህ ኮከብ የምትስልበት ››
እያሱ ወደ ንጉሱ እያየ ‹‹ ሸባው ተው እንጅ አንተስ ባንዲራው ላይ ወልጋዳ አንበሳ እየለጠፍክ የእንስሳት ማቆያ ባንዲራ አስመስለኧው አልነበር ›› አለ፡፡
በቀልዱ የሳቀ አልነበረም!! አቶ መለስ በነገስታቱ ግትርነት ተበሳጭተው ወደክፍላቸው ገቡ ነገስታቱ መለስን እንት እንደሚያባርሩት መመካከር ጀመሩ ድንገት ኃ/ስላሴ የሆነ ሃሳብ በለጭ አለባቸው.......(ይቀጥላል)
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby ፓፒዮ » Mon May 06, 2013 2:03 am

ሰላም መንክር
እባክህ ቀጥልልን
ፓፒዮ ነኝ
ከ እናርጅ እናውጋ
ፓፒዮ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 41
Joined: Tue Apr 17, 2012 8:28 pm
Location: agere mariyam

Postby መንክር » Mon May 06, 2013 6:56 am

ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት ( ምናባዊ ወግ
ክፍል አራት
በክፍል ሶስት የኢትዮጰጲያ ባንዲራ ላይ ባለው ኮከብ አቶ መለስና አጼ ቴውድሮስ ከፍተኛ ፀብ ውስጥ እንደገቡና ቴውድሮስ መለስን ‹ሁርጋጥ› ብለው መሳደባቸውን እንዲሁም ቀዳማዊ ኃ/ስላሴ የአፍሪካ ህብረት ላይ አቶ መለስ ሰራሁ ባሉት ስራ ተባስጭተው ‹ እኛ ባቀናነው ስካር ማንም ተወላገደበት ›› ብለው እንደተረቱ አይተናል ....ሚኒሊክም ቢሆኑ የአቶ መለስ ነገር አልዋጥ ብለዋቸው ነበር ልጅ ሰለሞን የነገስታቱ ንትርክ ሰልችቶት የልብ ጓደኛው ደራሲ ስብሃት ገ/እግዚአብሄር ዶርም መሄዱን ስናወራም ነበር ከዛስ......
አቶ መለስ የነገስታቱ ግልምጫና ኩርፊያ የነገሰበት ክፍል ውስጥ ተቀምጦ ከመፋጠጥ ይሻላል በማለት ሰማይ ቤትን ዞር ዞር ብለው ለመጎብኘት አሰቡና ከክፍላቸው ወጥተው እጅግ በተዋበው መንገድ መጓዋዝ ጀመሩ .... ሰማይ ቤት ዛፎቹ አበቦቹና ኮረበረታወቹ በደስታ ያሰክራሉ ... ሁሉም ሰው ጤነኛ ነው ሁሉም ሰው አይራብም ማንም ሰው በጥላቻ አይተያይም .... ሁሉም በሚያየው ነገር እየተደሰተ በተመሳሳይ ቋንቋ እያወራ ያለምንም አላማና ምኞት በሰላም ይኖራል.....
አቶ መለስ አረፍ ማለት ስለፈለጉ ቅርንጫፎቹ ዘርፈፍ ካሉ ዝግባ የሚመስል ዛፍ ስር ቁጭ አሉ ግንዱ በጣም ወፍራም ከመሆኑ የተነሳ አስር ሰው እጅ ለእጅ ቢያያዝ እንከዋን ሊከበው አይችልም፡፡ ከተቀመጡበት ራቅ ብሎ ቁልቁል የሚወርድ ፏፏቴ ይታያል፤ ውሃው ንፁህ ከመሆኑ ብዛት የወተት ጎርፍ ይመስላል ፡፡ ወዲያው አባይ ትዝ አላቸው ግድቡ ....!! እስካሁን እንዴት እንደረሱት ለራሳቸውም ገርመዋቸው እያለ አንድ ሰው ‹‹ጭስ አባይን አይመስልም ›› አለ !! በድንጋጤ ዞር ዞር ቢሉ ማንም ባከሰባቢው የለም ! ሊያማትቡ እጃቸውን ሲያነሱ ሌላ ድምፅ
‹‹ አባይ ብትል ትዝ አለኝ ...ቦንድ ገዝተህ ነው የሞትከው ወይስ...›› ሲል ሰሙ
‹‹ ቦንድ ገዝቸ ወለዱን ስጠብቅ አይደል አንድ ክልፍልፍ ሹፌር ገጭቶ የገደለኝ ወይኔ የአንድ ወር ደመወዜ›› አለ ሌላኛው በቁጭት...
አቶ መለስ በሰወቹ ወሬ ተገርመው ማዳመጣቸውን ቀጠሉ...ሰወቹም ወረያቸውን ቀጠሉ....
‹‹ ....ባክህ ለትውልድ ይሆናል ልጆቻችን በደስታ ይኖራሉ....››
‹‹ተው እንጅ ....የእነማን ልጆች ...ከመሞትህ በፊት ወያኔ ነበርክ መሰል.... ›› አለ ሌላኛው ....በሳቅ አውካኩ ....
‹‹ ማነው አባይን የወያኔ ያደረገው ›› ሲል ሳቁ ጋር እየታገለ ጠየቀ ሌላኛው
‹‹ ያ ሰላቢ መላጣ ነዋ!! እንደወያኔ ባለስልጣኖች ሆድ የማይሞላ አቅማዳ አስቀምጦ ሞተ ....ይሄው ቦንድ ብናስገባ ደመወዝ ብንሰጥ ቅምም አላለው .....ወይ ግድብ.....እንደው ይሄ ቢሊየን የሚባል ብር 666 ይሆን እነዴ አካውንት ቁጥሩ ሰይጣን!! ...በቃ ተዋጥቶ ተዋጥቶ አሁን ሞላ ....ሲባል 3 ቢሊየን ደርሰናል ይሉናል...ያውም አላሙዲን ሳይቀር ሰጥቶ!! ይብላኝለት ለኗሪው እኛስ ቦንድ የለብን ደሞዝ የለን .... የገደለን አምላክ ይክበር ይመስገን!! ›› አለ ሌላኛው በምሬት!! አቶ መለስ ተበሳጩ !! ቢሆንም የሰወቹን ወሬ ላለማቋረጥ ዝም ብለው መስማታቸውን ቀጠሉ!!
‹‹ እኔ እምልህ አንተ ስትሞት ግድቡ ምን ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር...›› አለ አንድኛው ፤ አቶ መለስ የሰውየው ጥያቄ ደስ አላቸው መልሱን ለመስማት ገዋጉተው ተመቻቹ እንደሩቅ ሰው ስላስጀመሩት ግድብ ተደብቀው ሪፖርት መስማታቸው ለራሳቸውም እየገረማቸው.....
‹‹ ግድቡ አሁንም ይቆፈራል ....ስመኘው በቀለ የሚባል ኢኝጅነር በቴሌፊዥን ብቅ እያለ እየቆፈርነው ነው ...ይሄን ያህል ሜትር ኪዩብ አፈር ቆፈርን ይላል ....ሌላ ቀን ደግሞ ብቅ ብሎ ጓጉተን ‹ለሰማኒያ ሚሊዮን ህዝብ ብርሃን ፈጠርን› ሊል ነው ብለን ስንጠብቀው
‹ለ ስድስት ሽ ኢትዮጲያዊን የስራ እድል ፈጠርን › ብሎ... ይሄ ስመኘው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሃላፊነቱን ትቶ የሰራተኛና ማሃበራዊ ጉደይ ስራ አስኪያጅ ሆነ እነዴ እስክንል ግራ ያጋባናል!! ››
‹‹ ....እና አሁንም እየተቆፈረ ነው ....›
‹‹ አወ! እኔ ልሞት አካባቢ ቁፋሮው 2 አመት ሊሞላው ነው እያሉ በአል ሊያከብሩ ሽ ር ጉድ ሲሉ ነበር...›› አቶ መለስ ተገረሙ ‹‹ እንዴት ነው ሁለት አመት የሞላው ጊዜው እንዴት ይሮጣል›› ሲሉ አሰቡ! ሰወቹ ወጋቸውን ቀጠሉ....
‹‹ ሰውየው ከሞተ በኋላ አገሪቱን የሞላት የእርሱ ፎቶና መፎክር ብቻ ነው ! ወደየትም ብትዞር .....›› አቶ መለስ ደነገጡ ይሄን ወሬ ማመን አልቻሉም ...ከተቀመጡበት ብዲግ አሉና ወደሰወቹ ሂደው ‹‹ የኔ ፎቶ ነው አገሩን የሞላው ›› አሉ በቁጣ!!....ሰወቹ በድንጋጠየ በርግገው ተነሱና እያማተቡ አቶ መለስ ላይ ባለማመን አፈጠጡ አፋቸው ተያያዘ ‹‹ መለ ....ክክክክክ ቡር ጠቅላይ ሚንስትር እንዴ እዚህ ምን ይሰራሉ ›› ሰወቹ በድንጋጠየ የሚናገሩት አጡ ....
‹‹ተረጋጉ ድንገት እዚህ አረፍ አልኩና የምታወሩትን ስሰማ ገርሞኝ ነው›› አሉ አቶ መለስ ሰወቹን ለማረጋጋት እየሞከሩ፡፡
ሰወቹን ለማረጋጋት እረዥም ጊዜ ወሰደባቸው !! እየቆየም አሁን ያሉት ሰማይ ቤት መሆኑ ትዝ ሲላቸውና የአቶ መለስ ስልጣን ምድር ላይ እንደቀረ ሲታወሳቸው ተረጋግተውና ተግባብተው አቶ መለስ ጋር ሞቅ ያለ ጨዋታ ጀመሩ.......እንደሚከተለው...
‹‹ እና እርሰወ ከሞቱ ጀምሮ ....››
‹‹አንተ በለኝ ባክህ››
‹‹ እሽ ...ያው አንተ ሞትክ ተብሎ ህዝቡ አውርቶ በሃሳቡ አርባህን ሊበላ ሲዘጋጅ እንደገና ሞትክ ተባለ››
‹‹ እንዴት እንዴት....›› አሉ አቶ መለስ ግራ ገብቷቸው
‹‹ አንተ ለህክምና ከሄድክ በኋላ የበላህ ጅብ አልጮህ አለ!! ስላንተ ህዝቡ ያወራል ሚስትህን ጨምሮ ባለስልጣኖችህ ዝም ጭጭ አሉ
ኧረ የት ሄደ መለስ ሲባል ‹በመልካም ጤንነት ላይ ነው› እያሉ ህዝቡ በቃ የማያተርፈው ይዞት ነው .... እያለ የማይወደውን ኢቲቪ ጧትና ማታ እየከፈተ ስላንተ ሞትህንም ሽረትህንም ሲጠብቅ እግረ መንገዱን እንደሞትክ ሲያወራ....››
‹‹ ገፊ ሁሉ ›› አሉ አቶ መለስ በብስጭት....
‹‹....ከዛ አቶ በረከት መስከረም ላይ ተሸሎህ ስራ እንደምትጀምር ለህዝቡ ሲናገር ህዝቡ በቃ ትንሽ ተረጋጋ...››
‹‹ በረከት... እሱ ምናለበት !! እኔ እምለው ...ህዝቡ የኔ መኖር የኔስ ደህንነት ከመቸ ወዲህ ነው ያስጨነቀው...›› አሉ አቶ መለስ ግርም ብሏቸው
‹‹ኧረ ህዝቡስ በጣም ነው የሚገርመው .... የኢትዮጲያ ህዝብ የትዳር አጋሩን ብቻ አይደለም እወድሻለሁ አፈቅርሻለሁ ብሎ በአንደበቱ የማይናገረው ጠ/ሚንስትሩንም በግልፅ እወደሃለሁ አይልም ! ግን ይወድህ ነበር !! ....››
‹‹ እሽ ቀጥል....››
‹‹ መስከረም ላይ ፓርላማ ውስጥ ሊያይህ ቀጠሮ ለያዘው ህዝብ ነሃሴ አጋማሹ ላይ በኢቲቪ .... ያ ሰላምታ ሲያቀርብ ግንባሩ ጠረንቤዛውን ሊነካ የሚደርሰው ጋዜጠኛ ሞተወን ለኢትዮጲያ ህዝብ በጧቱ አረዳው...››
‹‹ ...እንደው ምን ብሎ ተናገረ ... አፈር ስሆን ንገረኝ ...›› አሉ አቶ መለስ
‹‹ ለሃያ አመታት ኢትዮጲያን በቆራጥነት ሲመሩ የነበሩት ቆራጡ መሪ አቶ መለስ .........ከዘህ አለም በሞት ተለዩ!!›› በቃ ልክ እንደዚህ ነው ያለው!!
አቶ መለስ ትክዝ አሉ ፡፡ዜናው ጠላቶቻቸውን ምን ያህል እንደሚያስፈነድቅ አሰቡ .... ዒሳያስ አፈወርቂ ውስኪ አስወርዶ በድፍን ኤርትራ ያሉ ከበሮወችንና ክራሮችን አሰብስቦ ኤርትራን የሚያክል ክበብ በሰራ ጨፋሪ ተከቦ እስክስ ሲል ታያቸው..... ሳዋ ሃያ ሽ ጊዜ መድፍ ስትተኩስ ምድር ቃጤ ስትሆን ታያቸው....ብርሃኑ ነጋ ወገቡን ታጥቆ ጉራጌኛውን ሲያስነካው ...ለድፍን የግንቦት ሰባት አባላት ዛሬ የክትፎ ቀን ነው ብሎ ሲያውጅ ታያቸው ....መራራ ጉዲና‹‹ ሰው ቢሄድ ሰው ይተካል ችግሩ ኢትዮጲያን አጥፍቶ መጥፋቱ ነው›› እንደሚሉ ገመቱ...አቶ ቡልቻ ‹‹ጠላታችን ሰው አይደለም መለስ ለልጆቹ ቢኖር ለሚስቱ ቢኖር....›› እያሉ አባታዊ አስተያየት ሲሰጡ አሰባቸው....ልደቱ አያሌው ‹‹ እኛም በማኒፌስቷችን ያልነው ይሄንን ነው ....ሰው ሰው ሟች ነው....›› እያለ ሲፈላሰፍ በለጭ አለባቸው
ስየ አብርሃ ‹‹ እስካሁን የሞትኩት እኔ ብሆን ድፍን ትግራይ ማቅ ለብሶ አመድ ነስንሶ ነበር የሚቀመጠው›› እያለ ጉራውን ሲነሰንስ ታያቸው ...ታማኝ በየነ ሞታቸውን ለአለም ለማወጅ ከአሜሪካ ቻይና በእግሩ ሲሄድ ታያቸው ብቻ ውስጣቸው በዜናው አዘነ.......
‹‹ እሽ ከዛስ በኋላ ምን ተፈጠረ ህዘቡ ምን አለ አለም ምን አለ .....›› አሉ አቶ መለስ
ሰውየው ግን አቶ መለስ የጠየቁትን ከመመለስ ይልቅ ፈርፍር ብሎ መሳቅ ጀመረ ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ......
(ይቀጥላል)
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby መንክር » Mon May 06, 2013 11:15 am

ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት ( ምናባዊ ወግ
ክፍል አምስት
አቶ መለስ እግሬን ላፍታታ በዛውም ስማይ ቤትን ዞር ዞር ብየ ልይ ብለው ወጣ እነዳሉና ለእረፍት አንድ ዛፍ ስር ቁጭ እንዳሉ ሁለት ኢትዮጰያዊያን ስለአባይ እያወሩ እግረ ወጋቸውን አቶ መለስን በሃሜት ሲቦጭቁ በክፍል አራት አይተን ነበር በኋላም እነዚህ ስወች ጋር አቶ መለስ ተዋውቀው ኢትዮጲያ ውስጥ የእርሳቸውን ሞት ተከትሎ ስለጠፈጠረው ሁኔታ እየጠየቁና እየተገረሙ እንደነበር እያወጋን ነው ያቆምነው ክፍል አምስት እነሆ....
****************************************************************************************************************
በቅርቡ በመኪና አደጋ የሞተው ኢትዮጲያዊ ለአቶ መለስ ስለቀብር ስነስረአታቸው በዝርዝር እንዲህ ሲል አወጋቸው
‹‹..... ኢትዮጲያ ጭጭ አለች !!ብዙ ሰው ቀድሞ ሙተሃል እያለ ሲያሟርት የነበረው ሳይቀር መሞትህን ማመን አልቻለም ‹ኢቲቪ እንከዋን ዘንቦበት እንደውም ጤዛ ነው › ሙሉ ቀን ስላንተ ሞት ሲያውራ ሲደጋግም ዋለ ዋሽንቱ ሆድ ይበላ ነበር አስከሬንህ ማታ 3 ሰአት ይገባል ተብሎ ሲነገር ህዝቡ ወድዛው ጎረፈ....››
‹‹ ሟርተኛ ሁሉ ምን ሊሰራ ነው የሚጎርፈው መሞቴን ለማረጋገጥ....›› አሉ አቶ መለስ....
‹‹ ኧረ አይደለም አቶ መለስ ህዝቡ በቃ ጎረፈ ....ቦሌ መንገዱ በሰው ተሞላ ሴቶቹ ከምን ጊዜ ጥቁር ልብስ እንደለበሱ ቢያዩ ይገረማሉ .... አስከሬንህ ቦሌ እስኪደርስ ህዝቡ እየተላቀሰ ደረቱን እየደቃ መልየ እያለ.......››
‹‹ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ......የኢትዮጲያ ህዝብ ነው መልየ የሚለው አጭበርባሪ የዝናብ ፀሃይ አትክኖ አትክኖ ከደፋኝ በኋላ መልየ.....ወይኔ መለስ ኑሬ በነበር ታንክ ነበር የማዘምትበት ››
‹‹ ኧረ በስማም በል ያከበረህ ህዝብ አልቅሶ አስለቅሶ ቤተሰብህን አስተዛዝኖ በቀበረህ ህዝብ ላይ ታንክ......››
‹‹ዝም በል !! ቀጣፊ!! የኢትዮጲያን ህዝብ መች አጣሁት በተለይ ያዲስ አበባ ሰው ...እስስት ነው ! በውስጡ እየሳቀ ነው ድራማ የሚሰራው አስመሳይ!! ደሞ መልየ አሉ ይለኛል ....መለመላቸውን ያስቀራቸው....ሌባ ሁሉ!! ››
‹‹ኧረ ከልቡ ነው ህዝቡ ያዘነው ....እንደውም እሳቸው የጀመሩትን እንጨርሰዋለን እያለ እኔ እስክሞት ድረስ ሲፎክር ነበር ህዘቡ›› አለ የአቶ መለስን ቁጣ የፈራው ተናጋሪ
‹‹ እሳቸው የጀመሩትን ....ጥገኛ ሁሉ እኔ የጀመርኩት ላይ እንደዝንብ ከሚሰፍር የራሱን አይጀምርም የተጀመረ መጨረስ ምኑ ነው የሚያስፎክረው ወሬኛ አስመሳይ ሁሉ!! በንጉሱ እንደፎከረ በደርግ እንደፎከረ ደሞ በእኔ ሊፎክር አፉን ይከፍታል ክፍታፍ ሁሉ!
ይሄ ሳቀ ሲሉት የሚያለቅስ አለቀሰ ሲሉት የሚስቅ የተቀዣበረበት ህዝብ እሱን ልመራ ያቃጠልኩት እድሜ ጉልበት.... የአዲስ አበባ ህዝብ በየበረንዳው ተኮልኩሎ ድራፍቱን ሲግፍ እኔ በመኪና ታሽጌ ስብሰባ ኮንፈረንስ ስሯሯጥ ካንዱ አገር አንዱ አገር ስራወጥ ኖርኩ
ደግሞ አለማፈሩ ....መለስ ሞተ ብሎ ሲያለቅስ ሆዳም ሁሉ››
‹‹አቶ መለስ ምነው የአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ወረዱበት ትግሬ ብቻ ነው ለእርሰወ የአገር ፍቅር ያለው.....›› አለ ተናጋሪው ተበሳጭቶ ተወልዶ ያደገባት የተማረባት በመኪና ተገጭቶ የሞተባት አዲስ አበባ ስትወቀስ ቆርቁሮት.....››
አቶ መለስ በፌዝ ፈገግ ብለው ‹‹ትግሬ አልክ ....እነሱ እንጂ እንደመዥገር ተጣብቀው በስሜ ሲነግዱ በተሰጣቸው ስልጣን ሲጨማለቁ ለዚህ ያበቁኝ ወይ አይማሩ ወይ አያነቡ የትግል ተረት እየተረኩ ተወዝፈው አገራችንን የወዘፏት...የትግራይን ሚስኪን ህዝብ በጦርነት በተጠበሰ በእርሃብ በተሰቃየ ባልዋለበት ስሙን ያስነሱ ከወንድሙ የኢትዮጲያ ህዝብ የለዩ ሆዳሞች መሃይሞች ስግብግቦች ....››
‹‹ ታዱያ መሪያቸው አንተ አልነበርክ ስታደርግ ያላዩትን አያደርጉ....›› አለ ዝም ብሎ የቆየው መዋች ኢትዮጲያዊ
‹‹ ልክ ነህ ይህን ስም ያሰጡንም እነሱ ናቸው!! አልሙ ብለን ኢፈርትን ብንመሰርት ቦጥቡጠው ቦጥቡጠው ቀፎውን አስቀሩት...ስሩ ብለን ፊት ብንሰጣቸው ኮንትሮባንድ የለ ስርቆት የለ የታገሉለትን ህዝብ በጠራራ ፀሃይ ዘረፉት ››
‹‹ እኮ እነማን ›› አለ አቶ መለስን እያየ ጠያቂው...
ከትግረይ ህዝብ አብራክ የወጡት አምነናቸው የነበሩት ...›› ብለው ትክዝ አሉና ‹‹ለመሆኑ አባ ዱላ ገመዳ ደህና ነው ›› ሲሉ ድንገት ጠየቁ
‹‹ አወ እሳቸው አምሮባቸዋል›› ቀብርህ ላይ ሲያለቅሱ የሁሉንም ኢትዮጲያዊ ሆድ ነው የበሉት....
‹‹ ማን አባዱላ አለቀሰ ›› ሲሉ ጠየቁ አቶ መለስ
‹‹ ምን ያላለቀሰ አለ በታሪክ እንዲህ ተለቅሶ አያውቅ ም ...ቁመህ ካስለቀስከው ይልቅ ሙተህ ያስለቀስከው ነበር የበዛው ›› አለ ተናጋሪው ....
አቶ መለስ አሽሙሩን ያልሰሙ መስለው አለፉት እና ‹‹ አቶ ግረማ ወልደ ጊወርጊስ ደህና ናቸው ›› ሲሉ ጠየቁ
‹‹ ደህና ናቸው እሳቸው ምን አለባአቸው አልባሌ ቦታ ከመዋል ብለው አላፊ አግዳሚውን ሰላም እያሉ ቁጭ ብለዋል››
‹‹መሞቴን ሲሰሙ ምን አሉ›› አሉ አቶ መለስ ፈገግ ብለው ...
‹‹ ልጅ ይሮጣል እንጅ አባቱን አይቀድምም ›› አሉ እየተባለ ሲወራ ነበር!!
አቶ መለስ ሁኔታውን ሲያስቡት ገረማቸው ...መሞታቸውን ማመን አልቻሉም ኢትዮጲያ በጣን ናፈቀቻቸው ! ወደክፍላቸው ከመመለስ ብለው ወደደራሲወች መንደር ጉዟቸውን ቀጠሉ.... ሲያወራቸው ከነበሩት አንዱ አቶ መለስ ‹‹ ምናይነት መኪና ገጭቶ እንደገደለኝ ታውቃለህ ›› ሲል ጠየቃቸደው እራሳቸውን በአሉታ ወዛወዙ
‹‹ የመከላከያ መኪና ነው ጭፍልቅ አድርጎ የገደለኝ››
‹‹ዳር ዳሩን መሄድ ነበረብህ ›› አሉ አቶ መለስ
‹‹ መንገዱን ስቶ በእግረኛ መንገድ ላይ ገብቶ እኮ ነው የገደለኝ›› አለ በስጨት ብሎ
‹‹ለመሆሙ ስራህ ምን ነበር ›› ሲሉ ጠየቁ አቶ መለስ
‹‹ ተቀዋሚ ነበርኩ››
‹‹ እናንተማ የእገረኛ መንገድ መጠቀም አትወዱም ››
‹‹ምናልከኝ አቶ መለስ››
ጠላትህን መንገድ ላይ ካላገኘኧው በመንገዱ ሂድና ፈልገው የሚል የትግራ ገበሬወች ተረት ትዝ አለኝ ....ሃሃሃሃ ስላም ዋሉ›› አቶ መለስ ሲሄዱ ሁለቱ ሰወች ከኋላቸው ቁመው ሲያዩአቸው ቆዩና ‹‹ይሄ መላጣ ያንድ ወር ደመወዜን አስበላኝ›› አለ አንዱ
ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት (ምናባዊ ወግ)
ክፍል ስድስት
አቶ መለስ ሰማይ ቤት በማንም አንገታቸው እየታነቀ እየተወቀሱና እየተከሰሱ መኖር ዲሞክራሲያዊ አይደለም ሲሉ አሰቡ!! በዛ ላይ እስካሁን ድረስ የኢትዮጲያ ነገስታትና በርካታ ኢትዮጲያዊያን ሙታኖች ጋር በምንም ነገር ሊስማሙ አልቻሉም ፡፡ ያገኛቸው ኢትዮጲያዊ ሁሉ ከንፈሩን እየነከሰና እየዛተ አልፎ ተርፎም ፀያፍ ስድብ እየሰነዘረባቸው ተቸገሩ፡፡ በአንድ በሆነ መንገድ ከዚህ ሰማይ ቤት ከሚሉት ቦታ መውጣት አለብኝ እያሉ ሲያስቡ ሰነበቱና ይህን ሃሳባቸውን የሚያካፍሉት ሚስጥር ጠባቂ ጓደኛ ማፈላለግ ለመጀመር ወሰኑ...... ‹‹ስንት የማይደፈር ነገር የደፈርኩ ነኝ ›› አሉ ለራሳቸው....
ይህን ከሰማይ ቤት የማምለጥ ዘመቻ ሊደግፍ የሚችል ኢትዮጲያዊ ሟች ለመፈለግ የመጀመሪያ ምርጫቸው የቀድሞ ታጋዮች መንደር ነበር ...ለራሳቸውም በማያውቁት ምክንያት የቀድሞ ታጋዮችን ማግኘት ያስፈራቸዋል ... በእርግጥ ብዙ ወዳጆቻቸው እንዳሉ ቢያውቁም በምድር የነበረው አንዳነድ የፖለቲካ ሽኩቻና መጠላለፉፉ ቅሬታ ያሳደረባቸው ታጋዮች ሊኖሩም ይችላሉ ፡፡ ሰማይ ቤት ነገሮችን በመነጋገር መፍታት ከባድ ነው ....ኢትዮጲያ ውስጥ እያሉ ‹‹መነጋገር›› ቀላል ነበር : ካመነ ያምናል ካላመነ አቶ መለስ ሁልጊዜም ልክ ይሆናሉ ! እዚህ ሰማይ ቤት ግን ማሳመን ካልቻልክ ማመን አለብህ !! ለማሳመን ደግሞ የመናገር ጥበብ ሳይሆን እውነት ብቻ ነው መንገዱ ....ቢሆንም ታጋዮችን ማሳመንና በእርሳቸው መስመር ማሰለፍ አማራጭ የሌለው ምርጫ ሆነባቸው ለአቶ መለስ .....
*********************************************
የታጋዮች መንደር ሲደርሱ ያጋጠማቸው ነገር ግራ አጋባቸው ፡፡ ‹‹እንኳን ሲታገል የሞተው ታጋይ ድፍን የትግራይ ህዝብ ቢቆጠር ይህን ያህል ቁጥር ይኖረዋል ብሎ መገመት ያስቸግራል ›› አሉ አቶ መለስ የሚርመሰመሰው ህዝብ ብዛት ተገርመው፡፡‹የኔን መምጣት የሰሙ ታጋዮች ሰማይ ቤቷን በደስታና በጭፈራ ቀውጢ ያደርጓታል› ብለው ያሰቡት አቶ መለስ ረጋ ባለና ግርማ ሞገስ ባለው እርምጃ ወደአንድ ትልቅ አዳራሽ ገቡ .... ፊት ለፊት ትልቁን የካራንቡላ ጠረንጲዛ ከበው የሞቀ ጨዋታ የሚመለከቱ በርካታ ታጋዮች አቶ መለስን ከመጤፍም አልቆጠሯቸው ...አላዩኝም ማለት ነው ብለው ያሰቡት መለስ ጉሮሯቸውን ጠራረጉ እህ አህህህሀ...ማንም ዙሮ አላያቸውም !! ተበሳጩና ‹‹ ምድረ ቁማርተኛ›› አሉ በውስጣቸው!!
በሰወቹ መሃል በውልብታ ሲመለከቱ ሃየሎም የካራሙቡላውን ድንጋይ ሊወረውር ሲያነጣጥር አዩ ....ሊጮሁ ምንም አልቀራቸው
‹‹ ትጋዳላይ ሰላም ናችሁ›› አቶ መለስ ውስጣቸው እየፈራ ጮህ ብለው ተናገሩ!! ማንም ስላምታቸውን የመለሰ የለም!
ፍርሃታቸው ወደ ስጋት ተቀየረ ‹‹ ታጋይ ሲሰዋ ደንቆሮ የሆናል እንዴ›› ሲሉ አሰቡ!!
‹‹ ሃየሎም›› ቤቱን በሚያናጋ ድምፅ ተጣሩ ፡፡ መልስ የለም !!
‹‹ ሙሴ›› ዝም!!
ወደፊት ተራመዱና የተሰበሰቡትን ታጋዮች ገፈታትረው ሃየሎም ፊተ በቁጣ ቆሙና...
‹‹ስማ ምን ይዘጋሃል? ›› ሲሉ በብስጭት ጠየቁት ...
ሃየሎም በሚያስፈራ እርጋታ እና ቅዝቅዝ ባለ ድምፅ ‹‹ እንጫወትበት ዘወር በልልን›› አላቸው
‹‹ ዞር በልልን? ...ሃየሎም... መለስ እኮ ነኝ! ...እንዴት ነው እንደዚህ የምትናገረው ባክህ?...››
ሃየሎም አቶ መለስን ከመናገር ይልቅ ክጎኑ ወደቆመው ተጋጣሚው ዞሮ
‹‹ ያንተ ተራ ነው ተጫዋት››አለው ፡፡
አቶ መለስ ሃየሎም ጋር ካራንቡላ የሚጫወተውን ሰው ለመጀመረያ ጊዜ ተመለከቱት ...‹.የሃየሎም ገዳይ› ተብሎ በምድር ሞት የተፈረደበት ሰው ነበር! የሰማይ ቤት ነገር ግራ አጋባቸው !! ‹‹ በሬ ካራጁ›› ብለው ተረቱ!! በመቀጠልም ታጋዮቹን ሁሉ ተራ በተራ ካዩ በኋላ
‹‹እስቲ እንነጋገር ምንድን ነው በውስጣችን ያለው ቅሬታ ምንድነው ያሳዘነን ነገር በትግል ባህላችን በግልፅ እንወያይ የእናንተን የነፃነት ችቦ ተቀብሎ 21 አመት ሙሉ ሲለፋ ሲደክም ለኖረ ጓዳችሁ ይሄ ነበር የሚገባው አቀባበል? .....›› እያሉ በተለሳለሰ አነጋገር ግኡዝ የሆኑት ታጋዮች ላይ እስትንፋስ ሊዘሩባቸው ጣሩ! ወይ ፍንክች!! ዝምታ ብቻ!!
ቀጠሉ መለስ ‹‹ የሞታችሁለት ህዝብ የታገላችሁለት ህዝብ ኑሮው ተቀይሮ በየቀኑ ያመሰግናችኋል ...ንፁህ ውሃ ሲጠጣ ያመሰግናችኋል ...በቀን ሶስት ጊዜ ሲበላ ...በነፃነት ሲናገር ...በነፃነት የፈለገውን የፖለቲካ ፓርቲ ሲመርጥ ...ያስታውሳችኋል ...የሞታችሁለት የኢትዮጲያ ህዝብ!!...››
ዝም!! ሃየሎም ዝም ! ሙሴ ዝም! ስበሃት ገ/እግዚአብሄር ትዝ አላቸው መለስ
እነአብርሃም እነማቱሳላ ጠጡ ካቲካላ
ለማንም ምንም አላሉም ...ጠጥተውም ዝም...ዝምምምምም!!
እነሙሴ እነማርታ እነሃየሎም ....
ሲጫወቱ ካራምቡላ
እየጠጡ ካቲካላ....ዝምምምም!!
አቶ መለስ ቀጠሉ ‹‹ የአፈናና የዝምታን ቀንበር በደማችሁ የሰበራችሁ እናንተ እንዴት በባርነት እንደተያዘ ህዝብ ዝም ትላላችሁ?....››
ዝም ! ቄሱም ዝም መፀሃፉም ዝም !!
አቶ መለስ የሚያደርጉት አጡ ዝም ብለው ሃየሎምን አዩት፡፡ የሃየሎም ፊት የሞናሊዛን ፊት የሚያስንቅ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት እየተነበበት ፊታቸው ቁሟል ...
‹‹ስላም ዋሉ›› ብለው ውልቅ አሉ ...አቶ መለስ ፡፡ ማመን ግን አልቻሉም....‹‹እንዴ የህወሃት ጉባኤ ላይ ለመናገር እድል ይሰጠን ብለው እጃቸውን እንደጭራሮ የሚያንጨፈርሩ ታጋዮች ምን ነካን ብለው ነው .... ወይ ጉድ ››
ከታጋዮች ሰፈር ወጥተው ወደነገስታት ሰፈር የሚየስኬደውን ረዥም ጎዳና እያዩ ወገባቸውን ይዘው ቆሙ ....ትእይንቱ አሳዛኝ ነበር ፡፡ አራት ኪሎ ናፈቃቸው....ፓርላማው ናፈቃቸው ....አዲስ አበባ ናፈቀቻቸው ....ሁሉም ቦታ ሁሉም አለም ናፈቃቸው ከሰማይ ቤት ውጭ!! ከዚህ እስራት ለመውጣት ሰው ማፈላለግ አለባቸው ....‹‹እንደውም ሰማይ ቤትን ሰብሮለመውጣት የሰማይ ቤትን መነሻና መድረሻ የሚተነትን መፀሃፍ ማግኘት አለብኝ›› አሉና ጉዟቸውን ወደደራሲያን መንደር አደረጉ!! የስብሃት ግጥም በአይምሯቸው እየተብላላች....
እነአብርሃም እነማቱሳላ
ጠጡ ካቲካላ ............
ለማንም ምንም አላሉም....
ዝም ዝምምምምምም!!
ዝም ባለ አፍ ዝምብ አይገባም ...
.ዝምታ ወርቅ ነው .....
ዝም አይነቅዝም...............
‹‹ ነቀዝ ሁሉ›› አሉ አቶ መለስ ምድርና ሰማይን የሚያናጋ በሚመስል ድምፅ ....( ይቀጥላል)
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby መንክር » Mon May 06, 2013 12:08 pm

ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ በሰማይ ቤት ( ምናባዊ ወግ)
ክፍል ስምንት
ከሰአት በኋላ ልጅ እያሱ ጫት ከምታመጣለት የሃረር ልጅ ጋር ሊያስተዋውቃቸው መለስንና ስብሃትን ይዟቸው ሔደ!! ልጅቱ ቤት ሲደርሱ ቀድመዋቸው የደረሱ አንድ ሁለት ሰወች ነበሩ ! አንዱ አቶ መለስን ሲያይ ‹‹ አጅሬው በመጨረሻ ተገናኘን ››አለ ነገር ፍለጋ በሚመስል አነጋገር ፡፡ ይሄ አረብ የሚመስል ሰው አቶ መለስን ጠጋ ብሎ ‹‹ ስማ አባይን መገደብ የማይታሰብ ነገር ነው እኛ ግብፃዊያን በአባይ የመጣብንን ችላ ብለን አናልፈውም ታሪክ አንብብ›› አላቸው ...ልጅ እያሱ ‹‹ አቦ አትወግመና አባይ ምናምን ...እኛ የመጣነው ጫት ልንገዛ ነው ›› አለው!
ሰውየው ነዝናዛ ቢጤ ነው አቶ መለስን ‹‹ የግብፅ ህዝብ በህልውናው አይደራደርም እንኳን የውጭ ጠላት ደፍሮን አይተሃል ሙባረክን 18 ቀን ሙሉ ታህሪር አደባባይ ላይ ሳንበላ ሳንጠጣ እንደገለበጥነው .... ››እያለ ይደነፋ ጀመረ
አቶ መለስ ‹‹ 18 ቀን ሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃሃ እኛ የኢትዮጲያ ህዝቦች 5 አመት ሳናቋርጥ የኢጣሊያን ፋሽስት ድራሹን አጥፍተነዋል ....እኛ የኢትዮጲያ ህዝቦች ሳንበላ ሳንጠጣ 17 አመት ተዋግተን ደርግን አስወግደነዋል ....18 ቀን ይላል እነዴ...ሃሃሃሃሃሃ›› ግብፃዊው ተሸማቀቀ ::አገሩ ላይ ለስራ የሚሄዱ ኢትዮጲያዊያንን እንዳሻው የሚናገር የግብፅ አርሶ አደር ‹ ከአገሩ የወጣ አገሩ እስኪመለስ › እያሉ ዝም ይሉት ስለነበር እንዲህ አይነት ኢትዮጲያዊ ይገጥመኛል ብሎ አላሰበም ነበር
‹‹ እና አባይን ልትገድቡት ነው ....›› አለ እንባ እየተናነቀው
‹‹ ግጥም አድርገን ›› አለ ልጅ እያሱ ስብሃትና መለስ በሳቅ አውካኩ..... በመጨረሻም ለግብፃዊው የጫቱን ሂሳብ ከፍለውለት እየተሳሳቁ ወደሰፈራቸው ተመለሱ!!
*****************************************************
መለስ ፣ስብሃት፣ በአሉ ግርማ እና ልጅ እያሱ በአቶ መለስ አጀንዳ ላይ ለመነጋገር አንዲት ጨለምለም ያለች ጥግ ላይ ተቀምጠዋል ... ይሄ ሁኔታ አቶ መለስን የመጀመሪያውን የህወሃት ጉባኤ አስታወሳቸው ውስጣቸው በትግል እና በአቢዮት ስሜት ተሞላ፡፡ በዛ ላይ የገዘዋትን ጫት ሲጀምሩ በቃ ነገሩ ሁሉ ተገላለጠላቸው .... ሰማይ ቤት በአቢዮታዊ ዴሞክራሲ መርህ መመራት አለበት ሲሉ አሰቡ! ከሰማይ ቤት ማምለጥ ብቻ ሳይሆን መላውን ጭቁኑን የሰማይ ቤት ህዝብ ከዚህ የአፈና ስርአት ነፃ ማውጣት አማራቸው .....እናም የእለቱን አጀንዳ ደራሲ ስብሃት ከፈቱት....
‹‹ በአሉ እንዲሁም እያሱ ወንድማችን መለስ አንዲት ሃሳብ ተከስታለታለች እናንተ ጋር እንመካከርባት ብለን ነው.....››አሉ
‹‹ ምን ችግር አለው እንነጋገርበታ .... ›› አለ በአሉ በእርጋታ
ስብሃት ከገነት ስለማምለጥ መለስ ያወረዋቸውን በዝርዝር ከተናፈሩ በኋላ ‹‹ የሚጨመር ካለ መለስ ተናገር››
‹‹ ሁሉንም ነገር በሚገባ ገልፀኸዋል ....አሁን ደግሞ ምን አሰብኩ ብቻችንን ከምናመልጥ ለምን እዚህ ያለውን ስርአት አንቀይረውም ››
በአሉ ከትከት ብሎ ሳቀና ‹‹ወይ መመሳሰል !›› አለ
‹‹ ማን ጋር ?›› አሉ አቶ መለስ ይሄን ሃሳብ ቀድሞኝ ያሰበ ይኖር ይሆን ብለው
‹‹ ሳጥናኤል ጋር ነዋ!! ....እሱም ወደምድር ከመወርወሩ በፊት ልክ እንዳንተ ነበር ያሰበው ሃሃሃሃሃሃሃሃ››በአሉ ሳቁን ማቆም አልቻለም!!
‹‹ ሳጥናኤል ..... ሰይጣኑ? ›› አቶ መለስ በግርምት ጠየቁ
‹‹ ታዲያስ...እሱ ነበር የእግዜር መንግስት ላይ አብዮት ያስነሳው ከዛ በኋላ ደግሞ ይሄው አንተ ተነሳህ ሃሃሃሃሃ ››
‹‹መቸ ›› አቶ መለስ ጠየቁ በጉጉት
‹‹ የዛሬ ብዙ ሚሊየን አመት አካባቢ›› ካለ በኋላ የሳጥናኤልን አመፅ ይተርክላቸው ጀመረ......
*****************************************************************

ሳጥናኤል ለድፍን ሰማያዊ ግዛት የእግዜር ወኪል የግዜር ጋራጅና አራጅ ሁኖ ተመርጦ ነበር ! ውበቱ ወንዳወንድነቱ ግረማ ሞገሱ ...ባጠቃላይ ሙሉ ሁኖ የተፈጠረ ...ማንም ‹የማይሳፈጠው› ታላቅ መለአክ ነበር !! እግዜርን ፊት ለፊት ማየት የተፈቀደለት ብቸኛ መለአክ !! እንግዲህ እግዚአብሔር ከፀሃይ 7 ሽ እጅ የደመቀ ስለነበር እሱን ቀጥ ብሎ ማየት የማይታሰብ ነው ወላ መለአክት ወላ ሌላው ፍጥረት ፈጣሪን ፊት ለፊት አየሁት የሚል አልነበረም ፡፡ ሳጥናኤል ግን አይቶታል ፡፡የእግዜር ኪሩብ ነበር .....እግዜር በችሎቱ ሲቀመጥ ሚሊን ቢሊየን ትሪሊየን ከዋትሪሊየን መለአክት በግንባሩ መሬት ላይ ተደፍቶ ቅዱስ ...ቅዱስ... እያለ ይሰግዳል ....
ሳጥናኤል ፊቱን ወደሰጋጁ መለአክት ጀርባውን ለእግዚአብሔር አድርጎ ከምድር ጥግ እስከጥግ የሚደርስ ክንፉን ዘርገቶ ይቆማል፡፡ የፈጣሪ ሃያል ብርሃን እንደጥቁር መነፀር ከፊቱ በቆመው ሳጥናኤል ክንፍ ውስጥ ያልፍና ሃይሉ ተቀንሶ ብርሃኑም ተለሳልሶ ለሌሎቹ ይታያል እንዲህ እየሆነ ብዙ ሚሊየን አመት እንደተቆጠረ አንድ ቀን ሳጥናኤል ክፉ ሃሳብ ሽው አለበት ... መለአክቱ ለኔ ነው ወይስ ከሀዋላየ ለቆመው ፈጣሪ የሚሰግዱት ሲል አሰበ!! ‹‹ አይ ለኔ ነው ....ባይሆንም ለኔ መሆን አለበት ››አለና በልቡ ያሰበውን ጩሆ ተናገረው ‹‹ አዋጅ አዋጅ ....ከዛሬ ጀምሮ የምትሰግዱት ለኔ ለታላቁ ሳጥናኤል መሆኑን አውቃችሁ ስግደታችሁን አጠናክራችሁ ቀጥሉ››
ሲል በታላቅ ድምፅ አንባረቀ ፡፡ እግዚአብሄርም እስቲ ጉዱን ልየው ብሎ ዝም!! ግማሹ መለአከክ ለሳጥኛኤል በግንባሩ ተደፋ ሚካኤል ግን ‹‹ ምናልክ አንተ ›› ሲል በቁጣ ጮኸ!! ‹‹ ምንስ ብል ምን ያገባሃል ዝም ብለህ ስገድ ›› ሲል ሳጥናኤል በትእቢት ተናገረ ‹‹ ‹‹እኮ ላማን ነው የምሰግደው›› አለ ሚካኤል ደሙ ፈልቶ
‹‹ ለኔ ለታላቁ ሳጥናኤል ነዋ››አለ ሳጥናኤል ከዛ በፊት ባልታየ ወደፊትም በማይታይ ትእቢት
‹‹አላደርገውም ...ለታለቁ ፈጣሪ ብቻ ነው የምሰግደው ››
‹‹ ከእኔ በላይ ታላቅ የለም››
‹‹ እንዲህ ነኝና ሚካኤል ›› ብሎ እሳት ለብሶ እሳት ጎርሶ የእሳት ሰይፉን መዥረጥ ሲያደርገው ሳጥናኤልም አስፈሪ ሰይፉን መዘዘ እልፍ አእላፍ መላእክት ለሁለት ተከፈሉ ፡፡ግማሹ ከሚካኤል ግማሹ ከሳጥናኤል ..... ያሁሉ የእሳት ሰይፉን እያንቦገቦገ ተፋጠጠ .....
እግዜር ጉዱን አያለሁ ብሎ ዝም!!!!!!
እነአብርሃ እነማቱሳላ
ጠጡ ካቲካላ .....
እነሰይጦ እነሚኪ ተማዘዙ ሻሙላ....
ለማንም ምንም አላሉም ጉዱ እስኪለይ ዝም ዝምምም!!
በዛ በኩል እነገብረኤል እነፋናኤል የግዜር ጦር ....በዚህ በኩል እነኩሽካኩ እነማናኩ የሳጥናኤል ጦር ......
ተጀጀመረ !!
የሚካኤልና የሳጥናኤል ሰይፍ ሲጋጭ ፀኃይ ተፈነካከተች ፣ኮከቦች ረገፉ፣ ዘጠኝ ትናንሽ አለማት ተፈጠሩ ፣ ሰማይ ቤት ተደረማመሰ ፣ ምድረ መለአክ ተጠዛጠዘ...ድሉ ወደሳጥናኤል አደላ ከእልፉ እሩብ እልፍ በሰይፍ አለቀ .... ሳጥናኤል አሁን ሜርኩሪ የምንላትን ፕላኔት አንስቶ ሚካኤል ላይ ወረወረበት ለትንሽ ሳተው ....ሚካኤል በተራው ማርስን አንስቶ እንደአለሎ ወደሳጥናኤል ወረወረበት ...የቀራቸው ፕላኔት የለም ተወራወሩ!! የሚካኤል ጦር ተዳከመ ከዛ ሁሉ መለአክ ጥቂት ቀሩ ...የሳጥናኤል ጦር ግን የመፋለም ወኔው እየጨመረ ጭራሽ እነሚካኤልን መክበብ ጀመረ ..... በመጨረሻ ሚካኤል ጦሩን ሊያይ ዞር ባለበት ቅፅበት የሳጥናኤል ክንድ አረፈበትና ወደቀ!! ሳጥናኤል በፍፁም ትእቢት ሚካኤልን ቁልቁል እያየ ሰይፉን ከፍፍፍፍፍ አደረገና በሚካኤል ልብ ትክክል ቁልቁል ሊሰካበት ሲያነጣጥር ሚካኤል የቀኝ ክንፉን ለመነሳት ዘረጋ..... በዚች ቅፅበት ሚካኤል ክንፉ ላይ በደማቅ ቀይ ቀለም የተፃፈው የፈጣሪ ስም የሳጥናኤልን ሰይፍ እጁ ላይ አሟሟው ....አይኑ ጨለማ ጉልበቱ ቄጤማ ሆነበት ...... ነገር ተገለባበጠ በቃ!! ሳጥናኤል የፊጥኝ ተጠፍሮ ቁልቁል ወደጨለማ ተጣለ ግብረአበሮቹ በምድር እንደትቢያ ተበተኑ እነጅኒ እነ መተት እነቡዳ .......›› አለና በአሉ ግርማ ትረካውን ጨረሰ !!
አቶ መለስ በጥሞና ሲያዳምጡ ቆዩና ‹‹ በጣም ጥሩ ሳጥናኤል የተሸነፈበትን ምክንያት ስንገመግም
1. ሳጥናኤል ህዝባዊ አልነበረም ሰራዊቱም የተሳሳተ መነሻ ይዞ ነበር የተዋጋው
2.ሳጥናኤል በቂ እና አሳማኝ ቅስቀሳ አላደረገም ! ቅስቀሳው ቢደረግ ኖሮ በቀላሉ የቀሩትን መላእክት ከጎኑ ማሰለፍ ይችል ነበር
3. ባጠቃላይ የዚህ ጦርነት ጥሩ ጎን ቢሸነፍም ወደምድር ተወርውሯል ፡፡ እኛም የምንፈልገው ተወርውረንም ይሁን በክብር ተሸኝተን ወደምድር መመለስ ነው ስለዚህ በዚህ ጦርነት ተሸናፊ የለም››
‹‹ አለቻ ወኔ ›› አሉ ስብሃት!!
(ይቀጥላል)
ጠ/ሚንስትር መለስ በሰማይ ቤት (ምናባዊ ወግ)
ክፍል አስር
ልጅ እያሱ በበአሉ ግርማ ትረካ በታም ተበሳጨ ‹‹ ስለሳጥናኤል ይሄ ሁሉ ተረት እና ዝብዘባ ለምን አስፈለገ ....ወይ በአሉ...›› አለ፡፡
ስብሃት እያሱን እያየ ‹‹ እንኳንም አብዮትን ከስር መሰረቷ አየናት...በአሉ! የሆነስ ሆነና እች ሰማይ ቤት ተመችታሃለች ››ሲሉ ጠየቁት
በአሉ እግሩን ለማፍታታት ቆመና‹‹ በበኩሌ ተመቸኝም አልተመቸኝም ተመልሸ ወደኢትዮጲያ መሄድ አልፈልግም››
‹‹ደርግ እኮ የለም ብትፈልግ እነደገና ኦሮማይን ብትፅፍ ዝንብህን እሽ የሚል የለም ›› አሉ አቶ መለስ በአሉን በአቢዮቱ ለማሳተፍ እየገፋፉት
‹‹ ሃሃሃ እሱን እንኳን ተወው መለስ ... የመፃፍ ነፃነት .....ሃሃሃሃሃሃ.......›› አሉ ስብሃት
‹‹ ተው እንጅ ስብሃት ደግሞ አንተ ምንህ ተነካ ...ያሻህን ስትፅፍ ኑረህ በክብር አይደለም የሞትከው ....አሁን ማን ይሙት ኢትዮጲያ ውስጥ የመፃፍ ነፃነት የለም የምትልበት አፍ አለህ...›› አሉ አቶ መለስ በትዝብት ስብሃትን እያዩ፡፡
ስብሃት መለስን በግርምት እያዩ ‹‹ እየውልህ መለስ !ደራሲ አንተ የምትሰጠውን የመፃፍ ነፃነት እንደምፅዋት አይጠብቅም ያሻውን ይፅፋል የድርሰት ቆሌው እንጅ ወላ የደርግ ወላ ያንተ በጎፍቃድ አይደለም ፃፍና አትፃፍ የሚለው›› አሉ ለወትሮው ታይቶባቸው የማይታወቅ ቁጣ አይናቸው ላይ እየነደደ ቀጠል አረጉና ‹‹ ቢበዛ ማሰርና መግደል ነው የሚችለው ባለስልጣን!! ለዛውም ደራሲውን ብቻ ....ደራሲው የፈጠራቸው ገፀ ባህሪያት ግን ዘላለማዊ ናቸው ፡፡ አንተ የፈጠርካቸው ወታደሮች ይሞታሉ ይቆስላሉ ....አንተ የፈጠርካቸው ነጋዴወች ይከስሉ ይነስራሉ....አንተ የፈጠርካቸው ሞዴል አርሶ አደሮች ዝናብ ቢጠፋ ወንዝ ቢደርቅ ይደርቃሉ...ኮፈዳቸውን ይዘው ከተማ ይገቡልሃል አንተ የፈጠርካቸው ዲያስፖራወች ፊትህ ቢጠቁርባቸው ጣጥለውህ ይሄዳሉ ወደመጡበት ...
የደራሲው ፍጡራን ግን ዘላለማዊ ናቸው ....ጉዱ ካሳን ጃንሆይ ምን አደረጉት ....ፀጋየ ....ፊያሜታ ምን ሆኑ ... ሰብለ በዛብህ ምን ሆኑ ...
አየህ የገዥን ግፍ እየተናገሩ ጉድህን እየዘከዘኩ ያውም አገራቸው ላይ በክብር የሚኖሩ ፍጥረታትን ስለሚፈጥር ነው ደራሲን የምትፈራው ›› ስብሃት ተንተገተጉ
መለስ የአቢዮቱ ነገር እንዳይበላሽ ነገሩን ለማለዘብ ፈለገ ‹‹ በርግጥ ልክ ነህ ስብሃት ግን በአሉ በኢሃዴግ አገዛዝ ቢፈጠር እስካሁን የት ይደርስ ነበር ››
‹‹ ቃሊቲ ነበራ የሚደርሰው ዘብጥያ ....››
‹‹ትንሽ አጋነንከው ስብሃት ....››
‹‹ መለስ ትሰማኛለህ....እያንዳንዱ አገዛዝ ጥሎበት ፊዳ የሚያደርገው ዜጋ አያጣም በተለይ ደራሲ እና ጋዜጠኛ ከመንግስት ጋር እሳትና ጭድ ናቸው ...ሁነውም አይራራቁም በከፉም በደጉም! አንተም አስርሃል ...ገርፈሃል...ገለህም ከሆነ ቀስ በቀስ እዚሁ እናገኛቸዋለን ›› አሉ ስብሃት ትክዝ ብለው !! መለስ ስብሃትን በአትኩሮት እያየ ‹ይሄ ሰው ግን በእርግጥ የተወለደው አደዋ ነው እነዴ› ሲሉ አሰቡና
‹‹ እንደደርግ ግን በግፍ አንገድልም በዚህ እንተማመን ›› አሉ
በአሉ አንድ ሁለት ጊዜ አሳለና ‹‹ ይቅርታ ስለደርግ ባናነሳ›› አለ
‹‹ለምን..... በግፍ ስለገደለህ አረመኔ ለምን አናነሳም ..ለምን አንወቅሰውም ›› አሉ አቶ መለስ ለበአሉ የተቆረቀሩ ይመስላሉ
‹‹ ምክንያቱም መንግስቱ እዚህ የለም በሌለበት ደግሞ እርእሳችን ሊሆን አይገባም ›› አለ በአሉ
‹‹ አንተ ሳጥናኤል በሌለበት ታሪኩን ስታወራልን አልነበር...›› መለስ ጠየቁ
‹‹ ሳጥናኤል እማ አለ ....ሃሃሃሃሃሃሃሃሃ››
‹‹የታለ ....›› አሉ መለስ ደንገጥ ብለው
በአሉ ትቂት የጫት ቀጠል ጠቀለለና ‹‹ይህን የማጎርሰው እሱ ሳጥናኤል ነው›› ብሎ ወደመለስ የጫት ጉርሻውን ዘረጋላቸው .... ቤቱ ባሳቅ ተሞላ ...መለስ የቅሬታ ፈገግታ ፊታቸው ላይ እየታየ ! ከቀልዱ ባሻገር በአሉ በአቢወቱ ሃሳብ መስማማቱ ቁልጭ ብሎ ታያቸው!!
ጫቱን ተቀበሉት !!
‹‹ ለአቢዮቱ ስም ማውጣት አለብን ›› አለ ልጅ እያሱ.....
መለስ ቀደም ብለው‹‹... እንግዲህ እዚህ ሁለት ሰው ከአድዋ አለ ....እኔና ስብሃት ! አድዋ ታሪካዊ የጥቁሮች ተምሳሌት ነው ...አደዋ ባርነት ድል የተመታበት ቦታ ነው ....አድዋ የማይቻል የሚመስል ገድል የተፈፀመበት ቦታ ነው .......››
‹‹ ባክህ ነገር አታንዛዛ ! ባጭሩ የአብዮቱ ስም ምን ይሁን ›› አለ በአሉ መለስን እያየ
‹‹ዘመቻ ሰማያዊት አድዋ›› አቶ መለስ ባጭሩ መለሱ
‹‹እስቲ ከተለመደው ነገር እንውጣ ›› አሉ ስብሃት ‹‹ አድዋ ማይጨው ...ለምን ከጦርነት የራቀ ስም አንሰጠውም ለምሳሌ ....እእእ .....››
ድንገት በር ተንኳኳ ....የገባውን ሰው መለስ አላወቁትም እነስብሃት ሞቅ ባለ ሰላምታ ተቀበሉት
ስብሃት እንግዳውንና መለስን አስተዋወቋቸው ‹‹ ዳኛቸው ወርቁ›› አለ ድምፁ የታፈነ ይመስላል፡፡
በአሉ ድንገት ጮኧ ‹‹ ለዘመቻው ስም ተገኘ ....በቃ ተገኘ ‹ዘመቻ አደፍርስ› ዳኛቸው አደፍርስን ተከራይተንሃል !! ››
አቶ መለስ ተበሳጩ እነዚህ ደራሲወች አፋቸው ሚስጥር አይቋጥርም ለመጣው ሁሉ ይሄን የሚያክል ከባድ ሚስጥር ይዘረግፋሉ ሲሉ በውስጣቸው ተማረሩ!!
ዳኛቸው ‹‹ለመሆኑ የምን ዘመቻ ነው ›› አለ
ስብሃት በአሉና ልጅ እያሱ እየተፈራረቁ አንዱ ካንዱ አፍ እየነጠቀ ለዳኛቸው ስለዘመቻው እየተሸሙ ሲነግሩት መለስ በግርምት ይመለከቱ ጀመር....
‹‹የዘመቻው መሪ ማነው....›› አለ ዳኛቸው ሲሰማ ከቆየ በኋላ ......
ሁሉም ወደመለስ ጠቆሙት .....
.(ይቀጥላል)
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby ዛዙ » Tue May 07, 2013 4:34 pm

ብሪሊየንት......በስማም እንዲህ አይነት ምናብ ያለው ሰው እዚህ ዋርካ ላይ ገጥሞኝም አያውቅም:: መንክር አሉህ? ስምን መላክ ያወጣዋል:: ቀጥልልን በናትህ:: ደራሲ እናት ወልዳለች:: ስንት አይነት fertile imagination አለ በናታችሁ!!!! ቀጥልልልልልልን.....ቀጥልልልልልልን...የአንድ ሰው ሰላማዊ ሰልፍም ቢሆን ወጥቻለሁ:: ያነበቡት ሁሉ እንደሚወዱት አረጋግጥልሀለሁ:: ብቻ ህሊናህንና ኢማጅኔሽህን ተከትለህ የመጣልህን ጻፍልንና ቀጥል::
ዛዙ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 199
Joined: Sat Oct 09, 2004 12:46 pm
Location: ethiopia

Postby ቦቹ » Tue May 07, 2013 6:59 pm

በጣም በጣም አሪፍ የተጨበጨበለት ፁሁፍ:: ዋርካን በከፊል መንጥሬ ልወጣ ስል መረቅ የሆነ ፁሁፍ ስመለከት እግሬን ዘርግቼ ባንድ ትንፋሽ አነበብኩት:: ይመችህ ያራዳ ልጅ እንደዚህ ፀዳ ያለ ነገር ስላካፈልከን::
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ሓየት11 » Wed May 08, 2013 12:00 am

ድንቅ ደራሲ:: የምናብህ ስፋትና ጥልቀት ብቻ አይደለም ...ውስጠ ወይራህም ለጉድ ነው:: ... እንሆ ...ከዘመናዊያን ድንቆች ተርታ ሰይምንህ:: ... ከነ አዳም ረታ ተርታ :!:

ከምስጋና ጋር!

ሓየት
ሓየት11
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 2945
Joined: Sun Apr 06, 2008 7:34 pm
Location: ላን'ሊይ

Postby ክቡራን » Wed May 08, 2013 2:15 am

...ሀሪፍ ነው የሰማይ ወጎች ደስ ይሉኛል , ያራዳ ልጆች "ይመቸኛል" ይላሉ:: ጥልቀት ያለው መነባነብ ነው.....ይሄ ጽሁፍ ግን የመንክር የራሱ አይመስለኝም እሱም ይሄን አላለም:: ካሌክስ አብርሀም ያለ መሰለኝ;; ማንን ፈርታይል ማይንድ እንበል ? ጽሁፉን ያመጣልንን መንክርን ወይስ ደራሲውን..? በተረፈ አሁንም እላለሁ... ውብ ስራ ነው::

ዛዙ wrote:ብሪሊየንት......በስማም እንዲህ አይነት ምናብ ያለው ሰው እዚህ ዋርካ ላይ ገጥሞኝም አያውቅም:: መንክር አሉህ? ስምን መላክ ያወጣዋል:: ቀጥልልን በናትህ:: ደራሲ እናት ወልዳለች:: ስንት አይነት fertile imagination አለ በናታችሁ!!!! ቀጥልልልልልልን.....ቀጥልልልልልልን...የአንድ ሰው ሰላማዊ ሰልፍም ቢሆን ወጥቻለሁ:: ያነበቡት ሁሉ እንደሚወዱት አረጋግጥልሀለሁ:: ብቻ ህሊናህንና ኢማጅኔሽህን ተከትለህ የመጣልህን ጻፍልንና ቀጥል::
ክቡራን
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 8546
Joined: Tue Mar 04, 2008 4:24 pm

Postby መንክር » Wed May 08, 2013 6:35 am

ይሄን ድንቅ ስራ ጓደኛዬ ልኮልኝ አንበብኩት እና ምናልባት ያላነበቡት አንብበው እንድኔ እንዲደሰቱ ብዬ ወደ ዋርካ አመጣሁት:: ስለዚህ ጽሁፉ የኔ አየደለም:: አሌክስ አብርሀም ነው ይላል:: አሌክስ አብርሀም ማን እንደሆነ አላቅም:: ልክ እንደናንተ እኔም አንብቤው ከምቀምቅጫዬ ተንስቼ አጨበጨብኩለት:: ጽሁፉንም ለናንተ አካፈልኩት:: ሰለዚህ የጻፋችሁት ምስጋና ለዚህ ድንቅ ደራሲ ይድረሰው::
መንክር
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 28
Joined: Fri Feb 15, 2008 9:23 pm

Postby ቀዳማይ » Thu May 09, 2013 6:06 am

በጣም ጥሩ ቀጥልበት :D
ቀዳማይ
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 60
Joined: Thu May 09, 2013 6:02 am

Postby ዛዙ » Fri May 10, 2013 5:11 pm

ክቡራን ስለእርማቱ አመሰግናለሁ:: መንክር ራሱ አሌክስም መስሎኝ ነበር ብኋላ ደግሞ::

ክቡራን wrote:...ሀሪፍ ነው የሰማይ ወጎች ደስ ይሉኛል , ያራዳ ልጆች "ይመቸኛል" ይላሉ:: ጥልቀት ያለው መነባነብ ነው.....ይሄ ጽሁፍ ግን የመንክር የራሱ አይመስለኝም እሱም ይሄን አላለም:: ካሌክስ አብርሀም ያለ መሰለኝ;; ማንን ፈርታይል ማይንድ እንበል ? ጽሁፉን ያመጣልንን መንክርን ወይስ ደራሲውን..? በተረፈ አሁንም እላለሁ... ውብ ስራ ነው::

ዛዙ wrote:ብሪሊየንት......በስማም እንዲህ አይነት ምናብ ያለው ሰው እዚህ ዋርካ ላይ ገጥሞኝም አያውቅም:: መንክር አሉህ? ስምን መላክ ያወጣዋል:: ቀጥልልን በናትህ:: ደራሲ እናት ወልዳለች:: ስንት አይነት fertile imagination አለ በናታችሁ!!!! ቀጥልልልልልልን.....ቀጥልልልልልልን...የአንድ ሰው ሰላማዊ ሰልፍም ቢሆን ወጥቻለሁ:: ያነበቡት ሁሉ እንደሚወዱት አረጋግጥልሀለሁ:: ብቻ ህሊናህንና ኢማጅኔሽህን ተከትለህ የመጣልህን ጻፍልንና ቀጥል::
ዛዙ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 199
Joined: Sat Oct 09, 2004 12:46 pm
Location: ethiopia

Postby ዛዙ » Fri May 10, 2013 5:24 pm

መንክር አሌክስን አመስግንልና::

እኔ ግን ሁለት ለጊዜው የታዩኝ ቴክኒካዊም ባይባሉ ታሪካዊ ወይም ዳራዊ እርማቶች እንበላቸው አሉ:: ለደራሲው ብትነግረው ይህ ድንቅ ሥራ ነው:: በመጽሀፍ መውጣት ያለበት ሥራ ነው:: ሓየት እንዳለውም በጣም ውስጠ-ወይራ (suggestive) የሆነ ጽሁፍ ነው::

1ኛው: መለስ ዜናዊ እኔ እሰከማውታውሰው ድረስ "የኢትዮጵያ ህዝብ" ብሎ አያውቅም:: የ'ኢትዮጵያ ህዝቦች' ነው የሚለው:: በሁለቱ አጠራር መሀል ያለው ልዩነት በተላይ መለስን በተመለከተ ቀላል ዲቴል መስሎ ሊታየው የሚችል አይመስለኝም ይሄን አይነት ኢማጅኔሽን ላለው ደራሲ:: ሰለዚሀ አላስተዋለውም ወይም ዘንግቶታል ብዬ ሰላሰብኩ ቢያርመው ነው::

2ኛው: "አጼ ሀይለስላሴ ኢያሱን ተቆጡት" የሚለው ትንሽ ደራሲው እዚህ ጋር ከታሪክ ጋር ይጣረሳል:: ተፈሪ መኮንን ለኢያሱ የነበረውን አክብሮት ከዘውዴ ረታ እና ተክለሀዋርያት የታሪክ መዛግብትና መጻህፍት የሁለቱን ግንኙነት ለተረዳ ሰው ይሄ ትንሽ ግር የሚያሰኝ ነው:: ደራሲው የበለጠ የታሪክ መጻህፍትን አንብቦ ግንኙነታቸውን ከታሪክ ጋር እንዳማይጣረስ አድርጎ ቢቀርጸው የበለጠ ሥነ-ጽሁፋዊም ታሪካዊም ውበቱም ጎልቶ ይወጣል የሚል ግምት አለኝ::

ደራሲውን አመስግንልና አሁን.....መች ነው ታዲያ የሚቀጥለው ቁራጭ የሚወጣልን:: እኔ በጉጉት መሞቴ ነው እባክህ ቶሎ ቀጥልልልልን...........

አክባሪህ
ዛዙ
መንክር wrote:ይሄን ድንቅ ስራ ጓደኛዬ ልኮልኝ አንበብኩት እና ምናልባት ያላነበቡት አንብበው እንድኔ እንዲደሰቱ ብዬ ወደ ዋርካ አመጣሁት:: ስለዚህ ጽሁፉ የኔ አየደለም:: አሌክስ አብርሀም ነው ይላል:: አሌክስ አብርሀም ማን እንደሆነ አላቅም:: ልክ እንደናንተ እኔም አንብቤው ከምቀምቅጫዬ ተንስቼ አጨበጨብኩለት:: ጽሁፉንም ለናንተ አካፈልኩት:: ሰለዚህ የጻፋችሁት ምስጋና ለዚህ ድንቅ ደራሲ ይድረሰው::
ዛዙ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 199
Joined: Sat Oct 09, 2004 12:46 pm
Location: ethiopia

Next

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 6 guests