የዛቲ ግጥሞች

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

የዛቲ ግጥሞች

Postby ዛቲ » Mon Dec 02, 2013 5:54 pm

የበሬ[/u] ምስጋና

የበሬን ምስጋና ቢወስድም ፈረሱ
አይገፋ መሬቱን አያርስም እንደሱ
ሰዉ ሞኙ ምን ያውቃል
በመልክ ይታለላል
ሞፈሩን የሳበን በሬን የሚከዳ
ፈረስን የሚያሞግስ በጦርነት ሜዳ::
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Mon Dec 02, 2013 6:10 pm

እኔ እሷን ስከጅል እሷ ደሞ እሱን
እሱ ደሞ ያቺን ያቺ ደሞ እኔን
በንግልት ገደልነው ፍቅር የሚሉትን::
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Sat Dec 21, 2013 6:06 pm

ወራጅ ወንዝ

መች እፎይ ይል ይሆን
ይሄ የኛ ወገን?
መከራን አርቁልኝ እያለ ሲለምን
የዘመን ንጉሶች
እየተተካኩ አንዱ በአንዱ ላይ
ዳንኪራ ሲመቱ ቀና ብሎ ሳያይ
ሲማጸን ይኖራል የመጣውን ጌታ
ባላገር ገራገር የሌለው መከታ::
ያልሰማ ሲመጣ የሰማ ሲያዘግም
ሆነበት ወገኔ ለወራጅ ወንዝ ማዜም::


[/u]
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Sat Dec 21, 2013 6:29 pm

እንደ ገጣሚ

ወረቀቴን ይዤ ብዕሬን ጨብጬ ልክ እንደ ገጣሚ
ሆሄያት ገጣጥሞ ቃላትን ቃራሚ
የት ኣለህ እላለው የቅኔ መደዳ
ከገጠመ ብዬ የሃሳቤ ናዳ
ብሰርዝ ብደልዝ ብሞነጫጭር
ወረቀት ጨምድጄ ወዲያ ባሽቀነጥር
ገጣሚን ለመምሰል ባለ ብዕሩን
ነጋ ጠባ ባስብ ሌት ተቀን
ስንኝ ኣልሰራሁም ቤት ኣልመታ ብሎኝ
ተረት ምሳሌዎች ቢያፈነግጡብኝ
ገጣሚን ለመምሰል ሳስብና ሳልም
ጊዜ ትቶኝ ሄደ ቃላት ስለቃቅም።

***************
ሰው

ኣያችሁት ብያ የሰዉን መርከስ
ከእቁብ ሳይቆጠር ከሞት ጫፍ መድረስ
ኣንተ ሰው ኣንተ ሰው
መከራን በላይህ ሌላው እሚያከብደው
እሱም እንዳንተው ሰው ኣንተም እንደሱ ሰው


****************************

ከሁሉ ሰው ራቅኩኝ ብዬ ኣንቺ ኣለሺኝ
እነሱን ጠልቼ ወዳንቺ ብሸሽ
ባይኖችሽ ላታዪኝ ምነው ኣፈር ኣልሽ?

**************************
ጠላት ሲሞት

ኣትጥላው ጠላትህን
ኣትመኘው ሞቱን
ጠላት ከሌለማ
ፈተናም ከጠፋ የሂወት ኣላማ
ትርጉም ያጣል ምክንያት
ማንን ኣሸንፈህ ልትሰይማት ህይወት
መግጠሙን ማወቅ ነው ደምቆ ለመታየት
መለመኑን ትተህ ጠላትህ እንዲሞት።

****************
ከንፈርሽን ላኪው

ስስምሽ
ከንፈሬ ገጥሞ ከከንፈርሽ
ኣይኔ ክድን ይላል ከሰመመን ገብቶ
ወገብሽን እቅፍ እጄም ተዘርግቶ።
ልቤ እየደቃ ኣታሞ እየመታ
ማር በዝቶ ተጋግሮ ከከንፈር ቦታ
ቢቀመስ ቢበላ ኣላልቅ ብሎብኝ
ይብቃኝ ብዬ እንዳልተው ወለላ ሆኖብኝ፣
ስስም ውዬ ባመሽ
ይህ እንቡጥ ከንፈርሽ
ኣታውሪ ኣትሳቂበት
በከንፈርሽ ኣድርገሽ ከንፈሬን ሳሚበት።
ስትስሚኝ
መስማት ይሳነኛል ጆሮዬ ተደፍኖ
የልቤ ትርታ ከልብሽ ተዳብሎ
ኣዲስ ዜማ መዝሙር ኣዚመው ቀልጸው
እስክስታ ዳንኪራ ልቦቻችን ወርደው
ጉሮ ወሸባዬ ኣርፈራም ጋም ኣሉ
በሃሴት ተሞልተው ጨፈሩ ዘለሉ።
ስስምሽ መንፈሴ ይረካል
የደስታ ብርሃን ህይወቴን ያደምቃል
ኣናውራ ይቅርብን ወሬ ምን ያደርጋል
ከንፈርሽን ላኪው ከከንፈሬ ይዋል።
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Mon Dec 30, 2013 12:46 pm

ምድር ስትታመም ስትሆን ስቃይ ብቻ
ሰው በሰው ሰልጥኖ ሲነግስ ጥላቻ
ሆዳም ከርሰ ብዙ መአድ የሚነጥቅ
ሽፍታ ባለ ጓንዴ ረግጦ የሚሳለቅ
ወሬኛ አላርፍ ባይ ስም የሚያብጠለጥል
ደራሽ ባለ ጊዜ 'ሚያነሳና እሚጥል
ሳይደርሱበት ደርሶ የሚለቀው ምላስ
በነገር ርክፍካፎ የሚተነኳኩስ
ያስጠላል ትእይንቱ ምንስ ልበላቹ
ጥሩ ሰው ጥሩ ሰው የታለ ብላቹ
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Mon Jan 27, 2014 7:27 pm

ውብ

ውስጤን ላትሰሙት አፍ ከፍቶ ላይነግር
እንደሃውልት ቆሞ ባይመሰክር
ኣንዲያው በደፈና መች እድል ሰጣችሁኝ
አስቀያሚ ትርኢት መልከጥፉ አላቹኝ
የት ያያል አይናቹ አላስተዋላቹኝ
እኔነቴ ውብ ነው የቆንጆ ቆንጆ ነኝ።

****************************
ይቻላል ወይ?

ኣንገቴ ቢሰበር ጭንቀት ሲበዛበት
ውስጤ ሲደክምብኝ መቆዘም ታክቶት
ፊቴ ቅጭም ቢል መፈገግ ተስኖት
ብርቱ እንደተወጋ ቁስለኛ ሳቃስት
በል ቻለው ይሉኛል ይቻላል ወይ ናፍቆት?
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Wed Feb 05, 2014 7:22 pm

ግጥሜን ኣፋልጉኝ

ግጥሜን ያያቹ ሰዎች እባካቹ
ግጥሜን ያያቹ ስለ ፍቅር ብላቹ
ስለሷ ያወጋል ስለወደድኳት ልጅ
ስላስጠናችኝ ደጅ
ኣበክሮ ይነግራል ያውጃል ያበስራል
በወርቅ ቃሎች ደምቋል
በተመስጦ ስሜት የቋጠርኩት ስንኝ
ኣጣሁት ከውስጤ ባዶነት ተሰማኝ
ግጥሜን ኣፋልጉኝ ነግ በኔ ነውና
ትዝታ እንዳላጣ ልቤ እንዳይሆን ወና።

*****************************************
ቆንጂትና ነብር(ከ እንግሊዘኛ የተወሰደ)

ከዛ ማዶ ዱር ቆንጂትና ነብር
እሷ ስትጋልበው እሱ ሆኖ ከስር
ፈገግታ ከፊቷ ነበረ ሲሄዱ
ተመልሰው መጡ ገብታ እሷ ከሆዱ
ፈገግታን ወስዶ እሱ።
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ወርቅነች » Thu Feb 06, 2014 2:40 am

የዛቲ ግጥሞች በጣም ያምራሉ
ከሩቅ ሆነው ይጣራሉ
የሰውንም ሴሜት ይሰባሉ

ጀሚላ ከችርችል ጎዳና :lol: :lol: :lol:
ወርቅነች
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 967
Joined: Sun Oct 03, 2010 10:05 am

Postby ወርቅነች » Tue Feb 11, 2014 2:53 am

የዛቲ ግጥሞች ልብ ይሰባሉ
ለጆሮም ጤንነት ይመቻሉ :lol:
የሰውንም ልጅ አንደበት ይማርካሉ

ጀሚላ ከችርችል ጎዳና :lol: :lol: :lol:
ወርቅነች
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 967
Joined: Sun Oct 03, 2010 10:05 am

Postby ዛቲ » Tue Feb 11, 2014 7:32 pm

ጀሚላ ከቸርችል አመሰግናለው
ከድፍረት ሳትቆጥሪ ግጥሜን ላነበብሽው
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ዛቲ » Tue Feb 11, 2014 7:57 pm

ተናገር ማቱሳላ

ኦ ማቱሳላ!
እንዴት ብለህ ኖርከው ይህን ሁሉ አመት
በደስታ በተድላ?
እንዴት ብልህ ቻልከው ገፋኸው ምእቱን
ስቃይ መከራውን?
ብትገባም መሬት ብትሆንም አፈር
ብትችል መናገር
ይችን የኛን እድሜ አሰርት እማትሞላ
ቆንጥረን ልንኖራት እንደማቱሳላ
የመኖር ትርጉሙ ምክንያት ፋይዳ ጠፋ
እድሜያችን አጠረ ሞታችንም ከፋ
በዚች ቤሳቤስቲ የእድሜ ጥርቃሞ
ስቃያችን ብሶ ህሊናችን ታሞ
ከአፋችን ገብቶ እንደ እሬት ሲመር
ማቱሳላ እንዳንተ ምእቱን ብንኖር
ምን እንሆን ነበር?!
******************
ስላንቺ

ዳገቱን ብወጣ ተራራውን ብወርድ
ስላንቺ የኔ ውድ
በፀሃይ በረመጥ
በሙቀቱ ብላጥ
በብርድ በቸነፈር
በንፋስ ውሽንፍር
ብወጣ ምስቅልቅል
ላንቺው ነው የኔ ፍቅር
ባህር ከባህሩ ብጠልቅ እንደ መልህቅ
ከውቅያኖስ ሩቅ ጥልቅ
ብል ስጥም ስጥምጥም
ስላንቺው ነው ይሄም
በሰማይ ሰማያት በከፍ በከፍታው
ክንፌን ባራግፈው
ተመልከች ላንቺው ነው
ምን ልበልሽ ውቢት
እሰጥ አገባውን ከተፈጥሮ ሙግት
ስላንቺ ገጠምኩት
*********************
ሰው ባያፈቅር

ዓለም በምህዋሯ ብትዞር እንደ እንዝርት
ፀሃይ ፈገግታዋን ሙቀቷን ብትሰጥ
ጨረቃም በምሽት ብትል ሄድ መለስ
ዳመና እርጥበቱን ዝናቡንም ቢያፈስ
ወንዙ ቢንቆረቆር ሸለቆውን ቢያዳርስ
ተክል በልምላሜው ቢመስል ቀጠልያ
በእንስሳት ሁካታ ደስታ ፈንጠዝያ
ሁሉም ውበት ነበር ዳሩ አለማማሩ
ማፍቀር ቢሳነው ነው ሰዉ እንደ እግዜሩ
*********************
የላብ ጌታ

እንደ ኮከብ አምሽቶ ንጋት ላይ አልጠፋም
አንድ ነበር ለሱ ብርሃንም ጨለማም
አይኑ በክፍተቱ ለእንቅልፍ ሳይገዛ
ጎኔ ይረፍ ብሎ ሳያነጥፍ አጎዛ
ድካም ማርኮ ይዞት በቅቶኛል ያላለ
በላቡ ያደረው የላብ ጌታ የታለ?
***************************


ጭንቀቴ አስጨነቀኝ

ባልተሳካው ነገር ስጨነቅ
በጎደለው ሁሉ ስሳቀቅ
መጪው ሲጨልም ስተክዝ
እምባ በጉንጬ እንደ ወንዝ
በከንቱ እንዲያ ሲያደክመኝ
ብዙ መጨነቄ መልሶ አስጨነቀኝ
************************
አባት

ያኔ ባፍላነቴ በጨቅላ አእምሮ
ውስጤ የተሰነደ እንደእሳት ተዳፍኖ
ያኔ ለጋ እያለው ያኔ ድሮ ድሮ
ወደዚህ አለም ወደኔነት
ያመጣኝን አባት ተጋድሞ ያየሁ እለት
ያቺ እለት ያቺ ድባበ ክፉ
ያሳየችኝ አብዬን ከነክንብንቡ
በቁመናው ግርማ የሞላ በዙርያው
ከእግዜር በታች ለኔ እንከን ያልነበረው
የበኩር መምህሬ በሂወት ጎዳና
አይኖቼ እምባ ኣዘሉ ተንተርሶ አዩና
እንዴት ካልጋ ዋለ እሱም ደከመና?
እንዴት ተሸነፈ ግጥሚያ ገጠመና?
እንዴት ብዬ ነበር ያኔ በአፍላነት
ሰው ኖሯል የኔ አባት ተፈጥሮን ረሳሁት
በዛች ሰአት ከሂወት ጋር ሙግት
ገጥሞ ሲታገላት
ካልጋው ጠርዝ ቁጭ ብዬ
እምባ ኣቅሮ ኣይኔ
ሲቃ ይዞት ውስጤን
አይኖቹ ተከድነው እያየው አባቴን
ተው ባክህን አልኩት ሞትን ተማፀንኩት
ጨልፌ ኣልጨረስኩም ቆንጥሬ ከሂወት
ተወት አድርገው ላሁን ችላ በል አንዳንዴ
ባዶህን ብትሄድ ምን አለበት እንዴ?
ይሰማኝ ይመስል ብሶቴን ስጋቴን
ይራራ እንደው ብዬ ተሰምቶት ሃዘን
ወይ ፍንክች አለ እሱ አወየው እዳዬ
ካልጋው ጠርዝ ከጫፉ እያለው ቁጭ ብዬ
የተሸከሙኝን እኒያ እጆቹን ሳስስ
አይኖቹ በግርብብ ድምፁ በለሆሳስ
ተረፍኩ ወይ ላንተው?
የመጨረሻው ቃል አፉ ያፈለቀው
የኔ አባት ከዛ አልተመለሰም ተጓዘ አራቀና
ቀዝቀዝ አለ እጁ ከእጄ ሆነና
ልቤን ወጋው ላፍታ የሃዘን ስለት
ውስጤን ስቃይ ጎዳው ተሰማኝ ባዶነት
ግን ለምን እንዳልል በእግዜር ስራ ቦታ
እሱ ከፈቀደ ጠያቂ የለምና
ፅናት ይስጥህ አለኝ ሰውም ማፅናናቱ
ቻለው ነበር ያለኝ ናፍቆት ኧረ ስንቱ
ኧረ ስንቱን ልቻል አባትነት ጠፍቶ
ህላዌው አብቅቶ ከመቃብር ገብቶ
ይሁና ልበለው ከሆነ ርግጥ ውነት
ያምላክ ሆኗል በቃ አባቴን ሸኘሁት
የለጋ ወቅት ነበር ያፍላነት
አባት አለኝታዬን የተሰናበትኩበት።
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ወርቅነች » Thu Feb 13, 2014 1:37 am

ዛቲ wrote:ጀሚላ ከቸርችል አመሰግናለው
ከድፍረት ሳትቆጥሪ ግጥሜን ላነበብሽው


ዛቲ እኔም አመሰግናለሁ ምሰጋናው ደርሶኛል
የዛቲም ግጥሞችና ቤት ተመችተውኛል

ጀሚላ ከችርችል ጎዳና
ወርቅነች
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 967
Joined: Sun Oct 03, 2010 10:05 am

Postby ዛቲ » Mon Feb 17, 2014 1:46 pm

ከቁርጡ ከዱለት ከመረቁ ፍትፍት
እየመራረጠ ያደርገዋል እንክት
መች ሊመለስ ሆነ የሰው ስጋ ጥሞት
እየሸረከተ በምላሱ ስለት
ዛቲ
አዲስ
አዲስ
 
Posts: 13
Joined: Thu Oct 03, 2013 12:59 pm

Postby ወርቅነች » Sun Mar 02, 2014 3:54 pm

ዛቲ wrote:ከቁርጡ ከዱለት ከመረቁ ፍትፍት
እየመራረጠ ያደርገዋል እንክት
መች ሊመለስ ሆነ የሰው ስጋ ጥሞት
እየሸረከተ በምላሱ ስለት


የሰው አፍ አያርፍ አይጠግብ ልክ እንደ ሆዱ
አፉ ዝም የሚለው የደረሰ ለት ነው ሞቱ
ካልሞተ አፉ ዝም አይልም
ሆዱም አፈር ካልሞላ አይጠግብም

ተቀነጨበ ከ ምክክር ግጥሞች...ተለገሰ መሀል ለዋለሉ :lol: :lol: እንደነ ዘእግዚኒ ቄሶች...ሰላም ነው ዛቲ ባለ ምርጥ ግጥሞች ትላለች ጀሚላ ከችርችል ጎዳና :lol: :lol:
ወርቅነች
ዋና ኮትኳች
ዋና ኮትኳች
 
Posts: 967
Joined: Sun Oct 03, 2010 10:05 am

Postby ምክክር » Tue Mar 04, 2014 8:56 am

ቅምጥሏ
ቅምጥል አፍቅሬ:
ለሷ ተቸግሬ::
ኩሽና እንዳትገባ ካልጋ እንዳትነሳ:
ምግብ አብሳይ ቀጠርኩ ሳስብላት ለሷ::
የእንጀራ ጠርዝ ጣቷን እንዳይቆርጣት ብዬ:
አጉራሽም ቀጠርኩኝ አሳቢ መስዬ::
ቅምጥሏን ፍቅሬን ድንገት ቢያስነጥሳት:
ይማርሽ የምትል ሌላም ቀጠርኩላት::
የሞልቃቃ ነገር መጨረሻው አያምር:
ቅጥ ያጣዉን ፍቅሬን ውሥጡን ስላየችው::
ባል ቀጥረህ አምጣልኝ ብላኝ አረፈችው::

መውደቅና መነሳት
ሁሉም በመውደቄ ሳቁ ተሳለቁ:
ሳያረጋግጡ ነገ እንደሚወድቁ::
መውደቅ መሞት አይደል ለተገነዘበው:
ዳግም ትንሣኤ አለ የጸና እምነት ላለው::
ጨለማን ያላየ መብራት አያደንቅም:
መውደቅን ያላየ መነሣት አያውቅም::

(ከፌስ ቡክ ያገኘዄቸው)
ምክክር
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 303
Joined: Thu Jun 26, 2008 10:10 am
Location: Super Earth

Next

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 7 guests