የጥበብ እልፍኝ::

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

የጥበብ እልፍኝ::

Postby ቦቹ » Sun Dec 08, 2013 8:03 pm

ተመስገን ገብሬ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ አጭር ልብ ወለድ (የጉለሌው ሰካራም) ጸሀፊ እንደሆነ ይነገራል:: ህዳር 22, 1941 የታተመ ሲሆን አሳታሚውም ነጻነት ማተሚያ ቤት ነበር:: መልካም ቆይታ እንሆ በረከት::

የጉለሌው ሰካራም

በተመስገን ገብሬ

ክፍል አንድ

በጉለሌ የነበረው የታወቀ ዶሮ ነጋዴ ማነው ብለው ከገፈርሳ እስከ ደጃዝማች ይገዙ ሰፈር ለጠየቁ ሰዎች፤ ተበጀ ሰካራሙ ተበጀ ዶሮ ነጋዴው፤ ተበጀ ነው ብለው ይነግሯቸዋል፡፡

የሕይወቱ ታሪክ ፍፁም ገድል ነው፡፡ ጢም ያለው ሽማግሌ ሰው ነው፡፡ ራሱን ጠጉር ውሃ ወይም መቀስ ነክቶት አያውቅም፡፡ ማለዳ አይናገርም፡፡ በጠርሙስ የከመረውን ከጠጣ በኋላ ሲራገም ወይም ሲሳደብ ሲፈክር ወይም ሲያቅራራ ድምጡ ከፈረንጅ ውሻ ድምጥ ይወፍራል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም ላገኝው ሁሉ ማታ ሰላምታ ይሰጣል፡፡ ቢያውቀውም ባያውቀውም ካገኝው ሁል ጋር ማታ ይስቃል፡፡ ቢውቀውም ባያውቀውም የሰላምታው አይነት እንደ ወታደር ወይም እንደ ሲቪል ቢሆን ለእርሱ እንደተመቸው ነው፡፡ ከሰላምታው ጋር ድምጥ ትሰማለችሁ፡፡ ከአፉ ከሚወጣው ከሚወጣው ግን አንድ ቃል መለየት አትችሉም፡፡

ቡን በተፈላ ጊዜ በጉለሌ በየምድጃው ሥር የሰካራም ተረት በየተጫወተ ሰው ሁሉ የተናገረ በተበጀ ላይ ነው፡፡ መልኩን አይተውት ያላወቁት ባልቴቶች እንኳ ከፍንጃል ቡን ፉት እያሉ የሌላውን ሰካራም ተረት በተበጀ ላይ ያላክኩት ነበር፡፡ይህ እውነት ነበር፡፡ በጠባዩ ከተባለለት የባሰ ሰካራም ይሁን ወይም የጉለሌ ባህር ዛፍ ውስጥ ወጥቶ እንደ አዲስ እንግዳ ሰው ሆኖ ለአዲስ አበባ ታይቷል፡፡

ከዱሮ የእንጨት ጉሙሩክ አጠገብ ወደ ምሥራቅ ሲል ሲል ካለው ወንዝ ማዶ ድልድዩን ወደ ምሥራው ተሻግሮ መጀመሪያ የሚገኝው አነስተኛ ሳር ክዳን ቤት የተበጀ ቤት ማለት ያ ነው፡፡ በዚያ በቤቱ በዚያ በጉለሌ በሠፈሩ ኖረ፡፡ እንጨቱን ተሸክሞ አፈሩን ቆፍሮ ቤቱን የሰራው እርሱ ነው፡፡ ዋጋ ከፍሎ አስከድኖታል፡፡ ተበጀን ኩራት ተሰማው፡፡ ቆይቶ ደግሞ አይኖቹ እንባ አዘሉ፡፡ በጉንጩም የእንባ ዘለላ ወረደው፡፡ በግራ እጁ መዳፍ ከጉንጩ የተንከባለለውን እንባ ጨፈለቀው፡፡ ዓይኖቹ እንባ ያፈሰሱ ለራሱ ጎጆ ስላለው ነው፡፡ ሊነገር በማይችል ደስታ ልቡ ተለውስዋል፡፡

ዝናም ያባረራቸውም ከቤቱ ጥግ ሊያጠለሉ ይችላሉ፡፡ ቤት የእግዚአብሄር ነውና ውዥብ እንዳያገኛቸው ከቤት ውስጥ ዝናቡ እስኪያባራ ይቆያሉ፡፡ ተበጀን ‹‹ ቤትህን ይባርክ ›› ሊሉት ነው፡፡ እንግዲህ መንገደኛው ሁሉ ‹‹ ይህ የማን ቤት ነው ? ብሎ ሲጠይቅ የተበጀ ሊባል ነው ›› አለ፡፡ ቀጥሎ ደግሞ ‹‹ ተበጀ የትኛው ነው ሲባል ዶሮ ነጋዴው ሊባል ነው ›› አለ፡፡ ‹‹ ዶሮ ነጋዴው የትኛው ነው ›› ሲባል ያ የጉለሌው ሰካራም ሊባል ነው፡፡ አወይ፤ እኔ ተበጀ፤ ተበላሽቻለሁ አለና ደነገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ስለቤቱ ክብር እንኳ መጠጥ መተው ይገባኛል አለ ፡፡ መጠጥ ለመተው ያሰበበት የመጀመሪያ ጊዜው ይህ ነው፡፡ ሰካራምነት ጉዳት መሆኑ ተሰምቶት እንደሆን ይናገር ስለ ቤት ክብር ማለቱ ግን ወደ ዳር ይቆይ፡፡ ስለ ቤት ክብር ምን ያውቃል? ዶሮ ነጋዴው ተበጀ ሰካራሙ ተበጀ አይደለምን ? ሰካራሙ ተበጀ የሰራውን የገዛ ቤቱን ከፍቶ ገበና ኩራዙን አስቀምጦ ክብሪቱን ለመጫር ሲያወጣ በሐሳብ ተሰቅዞ እንደዚህ አሰበ፡፡

መምረጥ አለብኝ፡፡ ከዚህ ቤት ያለው መጠጥ ሁሉ አንድ ሳይቀር እየወጣ ይፍሰስ፤ ከዚህ በኋላ ክብሪቱም ኩራዙም
በቤት ይደር፤ በአዲሱም ቤት ብርሃን ይዙርበት፡፡ አለዚያም በአዲሱ ቤት መጠጥ ይዙርበት፤ ኩራዙም ክብሪቱ ከቤት ይውጣና ይፍሰስ፡፡ ሊደረግ የሚገባ ከሁለቱ አንዱ ነው እንጂ፤ በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት በአንድነት ይህች ውሸት አለና ሳቀ፡፡

ከሁለቱ አንዱ ለማድረግ ሳይቆርጥ መብራቱን አቃጠለና ተቀመጠ፡፡ እንደገና ደግሞ እንደዚህ አሰበ፡፡ አያድርገውና ዛሬ ሰክሬ ይህ ቤት ቢቃጠልብኝ አመዱን አይቶ በሰካራሙ ተበጀ ላይ ለመሳቅ ድፍን ጉለሌ ነገ ከዚህ ነው የሚቆም ! ጉለሌ ምን ባለኝ? ወሬ ከማቡካት በቀር ጉለሌ ምን ሥራ አለው; ለአዲስ አበባም የስድስት ወር መሳቂያ በሆንኩ ነበር፡፡ መንገድ አላፊዎችም ነገ በዚህ ሲያልፉ አመዱን አይተው ይህ የተቃጠለው ቤት የማን ነበር ሲሉ የተበጀ ሊባል ነው፡፡ በሰካራሙ ተበጀ ቤት መጠጥና እሳት ባንድነት ይህች ውሸት ! ወደ ውጭ እንደ እርም ወርውሮት የነበረውን የመጠጥ ጠርሙስ ሁሉ በጨለማው ዳብሶ አንድ በአንድ ለቃቀማቸው፡፡ አንዱን ግን ቀና አደረገና ከአፍንጫው አስጠግቶ አሸተተው፡፡ በጠርሙሱ ቅርፅ የመጠጡን አይነት አወቀው፡፡ ዊስኪ ነበርና ስለዚህ ነው ሰው እንዳይሰማ ቀስ ብሎ የሳቀ፡፡

የጠርሙሱን ግማሽ ከጠጣ በኋላ ግን በአፉ ቡሽ ቢወትፍበት ለሳቁ መጠን የለውም፡፡ ‹‹ ጉለሌ ተኝቷልና ከዚሁ ከባሕር ዛፍ ሥር ቁጭ ብየ ብጠጣ የሚታዘበኝ የለም›› አለና አሰበ፡፡ እውነቱን ነው፡፡ ጉለሌስ ተኝቶ ነበር ነገር ግን አሁን እርሱ ጠጥቶ የሰከረ እንደሆነ ጉለሌን ሊቀሰቅሰው ነው እርሱ ከጠጣ በጉለሌ ማን ይተኛል? ጠርሙሱን ከከፈተው በኋላ ብርጭቆ ያስፈልገው እንደነበር ትዝ አለው፡፡

ሶስት የሚሆን ደኅና ጉንጭ ጠርሙሱን ከአፉ አስጠግቶ ጨለጠ፡፡ ከዚያ በኋላ የሚጠጣበት ብርጭቆ ሊያመጣ አሰበ ከዚያ በኋላ ደግሞ በሶስት ጉንጭ ምን ያህል ጠርሙሱን ቀና አድርጎ በጨረቃዋ ተመለከተ፡፡ ‹‹ግማሹን ያህል ሰርጉጀዋለሁ›› አለና በሳቅ ፈነዳ፡፡ ‹‹ ለዚህችስ ብርጭቆ ማምጣት አያሻም›› እያለ ጠርሙሱን አምቦጫቦጨው፡፡ በቀኝ ክንዱ መሬቱን ተረክዞ የቀረውን ጅው አድርጎ ወደ ውስጥ ወረወረው፡፡ ባዶውን ጠርሙስ ደግሞ በጁ እየጠነቆለ ‹‹አንተን ደግሞ ለአንድ ዶሮ ለውጩ ሞያ እይዛለሁ የዊስኪ ቅርፍቱም ዋጋ አለው አይጣልም›› አለ፡፡ ‹‹

እንዲሁ ሲጠጣ ሌሊቱን አጋመሰው፡፡ ቀጥሎ ከእግሩ በታች የወደቀውን ጠርሙስ እየቆጠረ ይህን ሁሉ እንደጠጣሁት አላምንምና በጉለሌ አፈርሳታ ይደረግልኝ እነናቄ እነተሰማ አጎቴም ይጠጣሉ›› አለ፡፡ የጠርሙሱ መጠጥ ሁሉ እስኪያልቅ ድረስ ከዚያ ከዛፉ ሥር ተቀምጦ ያን ጠንካራ ትምባሆውን ከአፉ አላየውም፡፡

በሳቅ ጊዜ ብቻ መልሶ ዝም እስኪል ድረስ መጠጡ ወይም ትምባሆው ከአፉ ያቋርጣል፡፡ የመጠጥና የትምባሆ ጊዜው ተበጀ ይህ ነው፡፡ማለዳ በቀዝቃዛ ውሃ ታጠበ፡፡ ቋንጣም እንቁላልም ጠበሳና በዳቦ በላ፡፡ የጦም ቀን ነበር ‹‹ ለአባ ተክለ አረጋይ አልናገርምና ነፍሴ ሆይ ግድ የለም አለ››፡፡

የነፍስ አባቱን ማለቱ ነው፡፡ ምናልባት በዓመት እንኳ አንድ ጊዜ ጠየቋቸው ወይም ጠይቀውት አያውቁም፤ እርሱንም አያደርሰውም፤ እርሳቸውም ከበዓታቸው አይወጡም፤ አንዳንድ ጊዜ የዛሬውን እሑድ ዕረፍት አደርገዋለሁ ያለ እንደሆነ እግሩን ደኅና አድርጎ የሚታጠብበት ቀን ማለት ነው፡፡ ደክሞት ነበርና ደኅና እንቅልፍ ተኝቶ ነበር፡፡ ዝናሙን ነጎድጓዱን ጎርፉን ውሃ ምላቱን አልሰማም፡፡ አንዳች ነገር ሰማ፡፡ ዘፈን እና እልልታ የሰማ መሰለው፡፡ ትናንት ከጠጣው መጠጥ ኃይል መሰለውና ይህስ ዕብደት ነው እንጂ ስካር አይደለም አለና ተመልሶ ተኛ፡፡ እንደገና አዳመጠ፡፡ የእርዳታ ጥሬ ጩኸት ሰማ፡፡ ከ አልጋው ዘልሎ ከወረደ በኋላ ቤቱን ለመዝጋት ጊዜ አላገኝም፡፡ በትልቁ ወንዝ ዙሪያ ቁመው ይጮሁ የነበሩ ሰዎች የውሃው ምላት

የሾገሌን ገረድ እንደጠለፋት ነገሩት፡፡ ጉርፍ የወሰደው ሾገሌን ራሱን ቢሆን ወይም የሾገሌን ገረድ ለተበጀ ማዕረግ ምኑም አይደለም፡፡ ‹‹ ገረዲቱን እናንተ በመጨረሻ ያያችኋት ወዴት ነው? ›› ብሎ ጠየቀና እየጠለቀ በዋና ይፈልግ ጀመር፡፡ ስለ ሾገሌ ገረድ በትኩስ ውሃ ምላት ለመግባት አንሠዋም ያለው ጉለሌ በዳር ተሰልፎ ቁሞ ተበጀን ይመለከት ነበር፡፡ ብዙ ጠልቆ ከቆየ በኋላ ብቅአለና ‹‹ አገኝኋት መሰለኝ ›› ብሎ በዳር ላሉት ጮሆ ተናገረ፡፡

ለሰው ሁሉ ደስታ ሰጠው፡፡ ከሁሉም ይልቅ እርሱን ደስ አለው፡፡ የጠለቀውና የዋኝው ረጅም ጊዜ ስለሆነ ደክሞት ነበር፡፡ ነገር ግን ሊያወጣት ይገባዋል፡፡ ጠለቀና አገኛት፡፡ በአሸካከሙ ላይ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ አለዚያስ ውሃው ምላት እንደገና ይነጥቀዋል፡፡ እንደተሸከማት ውስጥ ለውስጥ ዋኝና ከዳር ብቅ አለ፡፡ ከሸክሙ ክብደት ኃይል የተነሣ ወዲያው ወደቀ፡፡ እርዳታ ተነባበሩለትና ጎትተው እርሱንም እርሷንም አወጧቸው፡፡ ተበጀ ተንዘራግቶ በብረቱ ውጋት እያቃተተ የጉለሌ ሰው በሳቅ ሲፈነዳ ሰማ- ከራሱ ነኩል ቀና አለና ‹‹ ሴትዮዋ ድናለች? ›› ብሎ በርኅራሄ ድምፅ ጠየቃቸው፡፡ አንዱ ቀረበና ‹‹ አሳማ ነው ያወጣሃው ›› አለው፡፡ የሚያቃትተው ተበጀ ከወደራሱ ቀና አለና ‹‹አሳማ?›› ብሎ ጠየቀው፡፡ ‹‹ ለመሆኑ ከእናንተ ውሃ ወሰደባችሁ ሰው ነበር ወይስ አሳማ ኑርዋል? ›› ብሎ ተበጀ ጠየቀና ያቃትት ጀመር፡፡

ጎረቤትህን እንደነፍስህ ውደድ ቢባልም ሰዎችን እነ እቲላን ነበር እንጂ የእቲላን አሳማዎች አልነበረም፡፡ እቲላ ጎረቤቱ አሳማ አርቢ ነው፡፡ ውሃው ምላት ነጥቆ ወስዶ የነበረ የእቲላን አሳማ ሳለ ያላዩትን ቢያወሩ ግድ የሌላቸው ሰዎች የሾገሌን ገረድ ውሃ ወሰዳት ብለው አውርተው የተበጀ ነፍስ ለአንድ አሳማ ነፍስ ሊያስለውጡት ነበር፡፡ መልካሙ የሰማዕትነት ሥራው ሁሉ ደግሞ እንዲሁ ርካሽ ሆኖ የሚቆጠር የሆነበት ዘወትር የሚሰክር ሆኖ ስለታወቀ ነው፡፡

በሞራልም (ግብረ ገብነት) መሠረት አደረግሁት የሚለውን ሁሉ ሳያውቀው እንደሚያደርገው ይቆጥሩበታል፡፡ ‹‹ በጎሥራህን ሁሉ በትኩስ መቃብር ውስጥ አፈር አልብሰው አንተ ሰው ሁን ሚስት አግባ ልጆች ይኑሩህ›› ይሉትና ይዘልፍት ነበር፡፡ ድኃ ቢሆን ወይም ባለጠጋ ሰካራም ቢሆን ወይም ትኅርምተኛ ሁሉም የጉለሌ ልጆች ነን አባታችንም ጉለሌ ነው ብሎ ራሱን ሚያኮራ እርሱ ተበጀ ብቻ ነው፡፡

ክፍል ሁለት

ከሚያሰክር ሁሉ ትኅርምተኛ ለመሆን ብዙ ጊዜ አስቦ ነበር፡፡ ሰክሮ ያደረበት ሌሊት አልፎ ብርሃን በሆን ጊዜ ከእንግዲህ ወዲህ ‹‹መጠጥ አልቀምስም›› እያለ እየቀኑ በብርሃን ተበጀ ምለዋል፡፡ በነጋዉ የበለጠ ጠጥቶ የባሰ ሰክርዋል፡፡ ለመስከር ይጠጣል፡፡ ደስ ያለው እንዲመስለው ይጠጣል፡፡ ብስጭቱን የሚረሳ መስሎት ይጠጣል ይህ ነው ተበጀ፡፡ ‹‹ ይህን መስከርህን ካልተውህ ላንተ አበ ነፍስ አልሆንህም›› ብለው የመጀመሪያ ንስሐ አባቱ ብዙ ከመከሩት በኋላ መንፈሳዊ ልጅነቱን ከርግመት ጋራ አስወግደውታል፡፡

ገረዶቹም ለርሱ ተቀጥሮ መሥራትን ከውርደት ቆጥረውት እየነቀፉት ሂደዋል፡፡ ‹‹ መጠጥ ካልተውህ አናገባህም›› ብለው እየጊዜው ለጋብቻ ጠየቋቸው የነበሩ በቁመናው አሰናብተውታል፡፡ በሰምበቴ በማኅበርም ማኀበርተኛ ለቦሞን የጠየቃቸው ነፍሱን ሳይቀር ንቀውታል፡፡ ይህ ሁሉ በእርሱ ዘንድ ከኢምንት አይቆጠርም፡፡ ያሉትን ቢሉ እርሱ ምን ቸገረው ገንዘብ እኮ አለው፣ ገንዘቡም ጥሬ ብር ነው፡፡ ባለጠጋ ነው፡፡ መስከረም የባለጠጎች ነው፡፡ ትኅምርተኛ መሆንም የድሆች ነው፡፡ እንደ ልዩ አመፅ አድርገው ለምን በእርሱ ይቆጥሩበታል? እንዲህ በተከራከረ ነበር፡፡ ነገር ግን ልዩነት አለው፡፡

እርሱ ብዙ ጊዜ ሰክሮ አውቶሞቢል በላዩ ላይ ሒዶበታል፡፡ ሰክሮ በበነጋታው ከእንቅልፉ ሲነቃ
ብዙ ጊዜ ከእስር ቤት ውስጥ አድሮ ራሱን አግኝቶታል፡፡ በጉለሌ መንገድ ዳር ባሉት በብዙ የውሀ ጉድጓዶች ሰክሮ ገብቶባቸው እየተጮኸ ጉለሌ አውጥቶታል፡፡ ሰክሮ የጎርፍ ውሀ ከወሰደው በኋላ ብዙ ጊዜ እሳት አደጋ ደርሶለታል፡፡ ሰክሮ ከቤቱ መድረስ እያቃተው ከወደቀበት ባቡር ምንገድ ሳይነሳ ብዙ ጊዜ ጎርፍ በላዩ ላይ ሲሄድበት አድርዋል፡፡ ይህ ሁሉ ውርደት እና ርክሰት ነው እንጂ ክብር ከቶ አይደለም፡፡ እንግዲያውስ ክቡር ደሃ ነው ገንዘብ ስለሌለው ራሱን መግዛት ይችላል፡፡ ባለጠጋ ደግሞ መናኛ ተራ ነው፡፡ ገንዘብ ስላለው ራሱን መግዛት አይችልም፡፡ ይህን ሁሉ አሰበ፡፡ ስለኖረ ባይማር እንኳ ብዙ ከማወቅ ደርሰዋል፡፡ ‹‹ ባለጠጋ ሆነ ወይም ደሀ፣ ሰው ከራሱ የበለተ መሆን ይገባዋል››፡፡ አለ፡፡

ቤቱን ከሠራ ከአምስት ወራቶች በኋላ ጀምሮ ተበጀ መጠጥ ከቶ አልተጠጣም ስለቤቱ ክብር መጠጥ እርም ነው ማለት
ጀምሯል፡፡ ያለፈውንም ዘመን መራርነት እያሰበ ተንገፍግፈዋል፡፡ አንድ ብሎ ለመጀመር ከወደቀበት ትቢያ አንስቶ ዕድሉን ሲራግፍ እነደ ራዕይ ያያል፡፡


ያበላሸው እድሉ አሳዘነው ‹‹ በዚህ እድሜየ ሁሉ ሚስትም አላገባሁ ልጅም የለኝም›› አለና አዘነ፡፡ ውሾቹ እየተባሉ ሲጫወቱ ተመለከተና ‹‹አመሌ ውሻ ነበርና ከውሾች ጋር ኖርኩ›› ብሎ ራሱን ረገመ፡፡ በውሾች ፈንታ አሁን በዚህ እድሜው ልጆቹ ዙሪያውን እየተጫወቱ ሲፈነጩ ባየ ነበር እንዲሁ አሰበ፡፡ ቀልድና ወዘበሬታ ስለሚያውቅ እንደዚህ እያለ ይቀልድ ነበረ፡፡ ጉጃም የአበባውንና የግራር ማሩን ይጭናል፡፡ የተጉለትና የአምቦ ወረዳ ጌሾውን ያቀርባል፡፡ የሆላንድ የቢራ ፋብሪካ ቢራውን ያወጣል የኢጣሊያ ፋብሪካ ወይን ጠጅ (ነቢት) ያፈላል፡፡ መደቅሳና ዘቶስ በግሪክ አገር ይጣራል በስኮትላንድ ዊስኪ
ይጠመቃል፡፡

ይህ ሁሉ የሚደረገው በአራዳ የሚቀመጡትን እንዳይተማቸው ነው፡፡ በዚህም ምክንያት መዋሻዋ እንደምትጮህ ጉጉት ሰካራሞች በከተማይቱ ይጮሃሉ፡፡ ‹‹በደብረ ሊባኖስ ግን ድምጡን ዘለግ አድርጎ የሚናገር ወፍ እንኳ የለም፡፡ ውሃ እንኳ የሚጠጣ በመቅነኑ ነው፡፡ በአራዳ አሁን ወይም በገዳም ምንም ገንዘብና ቢስቲን ለሌለው ውሀ ደግሞ እጅግ አድርጎ ይጣፍጣል፡፡›› ይህን የመሰለ ቀልድ
ይቀለድ ነበር፡፡

ሰካራሙ ተበጀ ግን ገንዘብ እያለው ወሀ ጣፍጦታል፡፡ ልዩ በሆነው በዚያ ማታ ወደ አልጋው ወጥቶ በተኛ ጊዜ መጠጥን እርም ካደረገው አንድ አመት ከዘጠኝ ወር ከዘጠኝ ቀን እንደ ሆነው ጊዜውን ቆጥሮ አወቀው፡፡ ጊዜውንስ ማወቅ ለምን አስፈለገው? ‹‹ እንደ ጉድፍ ( ጥንብ) መጣያ ትንፋሼ ተበላሼ፤ አፌም እነደ እሬት መረረኝ ሹልክ ብየ ዛሬ ብቻ፤ ጥቂት ብቻ፤
አንድ ጊዜ ብቻ፤ እኔ ብቻ፣ ብጠጣ ምን ይጎዳል›› ብሎ ተመኝቶ ስለመበረ ነው፡፡ ነገር ግን ወደ አልጋው ወጥቶ ተጋደመ

ከተጋደመም በኋላ ተነሥቶ መጠጥ ቤት ለመሄድ ከባድ ከነበረው እንቅልፉ ለበላቀቅ ታገለ፡፡ በመጨረሻ ወደ መጠጥ ቤት በሄደ ጊዜ በውኑ ወይንም በሕልሙ እንደነበረ ራሱን ተበጀ አላውቀውም፡፡ የጠጣም እነደሆነ ከሁለት መቶ ዓመት በፊት ይደረግ በነበረው የአረመኔ ቅጣት እጁን እግሩ ከመቆረጥ ይደርሳል ብሎ አላሰበም፡፡ አናጢ የጠረበው እንጨት ከቅልጥሙ ይቀጠላል ብሎ ክፉ ሕልም አላለመም፡፡ አንድ ሰካራም አንካሳ በአንድ ዓመት ስንት የእንጨት እግር ይጨርሳል ብሎ ስለዋጋው አልተጨነቀም፡፡ ደኅና ምቾት ያለው አንካሳ ለመሆንም ገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አንካሳው ሰው ሰካራም እንደሆን በእንጨት እግሩ በሰላም ጊዜ ይሄድበታል፡፡ በሁከት ጊዜ ደግሞ ይማታበታል፡፡ ሲማታበት
ይሰበራል ሲሰበርም ሌላ የእነጨት እግር መግዛት ያስፈልገዋል፡፡ ስለዚህ የእንቸጥ እግር የሚሰሩ አናጢዮች ለደንበኞቻቸው ትርፍ መጠባበቂያ እግር በሜንጦ ሰቅለው ያስቀምጡላቸዋል ይባላል፡፡

ተበጀን እንደዚህ ያለ ሕይወት አያጋጥመውም፡፡ በበቀለች ዓምባ መጠጥ ቤት ደረጃውን ተራምዶ ተበጀ በገባ ጊዜ የጥንት ወዳጆቹ ስካሮች በእቅፍ ልይ ተነባበሩ፡፡ እንደተወደደ መሪ በጫንቃቸው ላይ ተሸክመው እየተቀባበሉት በዕልልታ ጮሁ፡፡ ከመጠጥ ቤት ጠፍቶ የነበረው ተመልሰዋልና በስካሮች ሁሉ ዘንድ ደስታ ሆነ፡፡ እንኳን በደኅና ገባህ! የመጠጥ ጠርሙሶቹን እንደ ዘንባባ ይዘው ተቀበሉት ቁማርተኛው ያረጀ ግሪክ እየሳለ ተናገረ ሁሉም በደስታ ይጮሁ ስለነበረ አንድም የሰማው የለም፡፡

ረስቶት የነበረው መጠጥ ጣዕሙን ገና ሳያውቀው ገና ከጫብቃቸው ሳይወርድ በጩኸቱም በመጠጡም ተበጀ ሰከረ፡፡ ከጫንቃቸው ወደ ቁልቁል ጣሉት ፡፡ የሕፃንነት ዘመን አልፉልና ራስህን ችነል መሄድ ይገባሃል አሉት፡፡ ሰማህ? አቅም አንሶህ መሄድ አቅቶሃልና እንደኩብኩባ እየዘለለህ መሄድ ትችል እንደሆነ ምርኩዜ ይኸውልህ ብሎ አንካሳው በየነ አቀበለው፡፡ ምረኩዙን ለመያዝና ለመጨበጥ እጁን ሲዘርር በግምባሩ ከበሬት ላ ተደፋ፡፡ እንደ ወደቀም ሳለ፤ እስኪነቃ ድረስ በመካከሉ ስንት ሰዓት አልፎ እንደነበረ ለማስተዋል አልቻለም፡፡ የመጠጥ ቤቱ እመቤት ጊዜ አልፏልና ከውጭ ጣሉትና ቤቱን ዝጉት ብላ አዘዘች፡፡

ወደቤቱ የተመለሰ መስሎት ሄደ፡፡ ማወቅ አልቻለምና ወዴት እንደሄደ ግን አላወቀም፡፡ አንድ መንገድ ሲያቋርጥ ተሰናከለና ወደቀ፡፡ ከወደቀበትም ምድር ላይ በዳሰሰ ጊዜ ለእጁ የገጠመው የባቡር ሀዲድ ነው፡፡ ቤቱ ያለ በጉለሌ ነው፡፡ የሰከረበት ደግሞ የበቀለች መተጥ ቤት ነው፡፡ መጠጥ ቤቱም ከዩሃንስ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ ነው፡፡ ምን ያህል ቢክር ነው የጉለሌ መንገድ ጠፍቶት እስከ ባቡር ሀዲድ ድረስ ተሳስቶ የሄደ; ራሱን ይዞ ለመጮህም ራሱ ወዴት እንዳለ ማወቅ አቃተው፡፡ እንደ ቤቱ መንገድ ጠፋበት፡፡ ጥቂት መስማት ከቻለ በኋላ ጩኸት በስተ ኋላው የነፋ ነበረ የእሳት አደጋ ወይስ ባቡር ኑርዋል; እያፎደፎደ ሲሄድ ከወደ ኋላው በኩል ምን እንደገፋው አላወቀም፤ ከኋላው በኩል ትልቅ ሀይል መታው፤ ከፊቱ በኩል ቀበሮ ጉድጓድ ተቀበለው፡፡ እግሩ እንደ ብርጭቆ ነከተ፡፡ ከወደቀበትም ሌሊቱን ሁሉ ደም ከእግሩ ዘነመ፡፡ ትንኝም እንደ ንብ በላዩ ሰፎ ደሙን መጠጠው፡፡ ቀና ብሎ በአጠገቡ የወደቀውን የአህያ ሬሳ አሞራዎች ሲግጡት አየ፡፡ የቀረው ልቡ በድንጋፄ ተመታ የእርሱ እድል ከአህያው
ሬሳ ዕድል ቀጥሎ ሆነ፡፡ በስካሩ ምክንያት እስከ ዘላለም ድረስ ከአህያ ሬሳ እንደ ማይሻል ተረዳው፡፡ ነገር ግን የአሁኑ መረዳት ለምን ይበጀዋል? ማወቅ የሚያስፈልግበት ጊዜ አልፏል፡፡

በሕይወቱ ሳለ እንደ ወደቀ ያህያ ሬሳ መነሳትአልቻለምና በተራው አሞራዎቹን ዓይኑን ሊመነቁሩት ነው፡፡ ሥጋውን በልተው ከጨረሱት በኋላ አጥንቱን ሊግጡት ነው፡፡ሌሊት ደግሞ ቀበሮዋች ሊረፈረፉበት ነው፡፡ ይህን እንዲያመልጥ ለመሸሽ ከወደቀበት ሊነሣ እቃተተ ሞከረ፡፡ ባልተቻለው ጊዜ ግን ተጋደመ፡፡ በደሙ ላይ እነደተጋደመ አራት ቀኖች አለፉ፡፡ እግሩ እንደቀረበታ ተነፋ፡፡ እንደ ቅጠልያ ያለ እዥ ወረደው፡፡ ከወደቀበት ያነሳው የመንግስት አምቡላንስ ባገኝው ጊዜ ፈፅሞ በስብሶ ነበር፡፡ ዶክቶር ክሪመር ባዩት ጊዜ ከሰማይ በታች ሊደረግለት የሚችል ሕክምና ምንድር ነው; ደሙ አልቅዋል፡፡ በሽተኞችን
ለመርዳት በጎ ፈቃድ ካላቸው ሰዎች የተለገሰውን ደም ለሚሰክር ጥጋበኛ አልሰጥም፡፡ እርሱን መንካት መርዙን ያስፈራል ከዚህ በፊት ይህ እንዳይደርስበት እንዳይሰክር ብዙ አስጠንቅቀነው ነበር አሉ፡፡

ከንፈሩ ተንቀሳቀሰ፡፡ ላብ በፊቱ እንደ ውሀ ፈሰሰ፡፡ ለመናገር ጣረ፡፡ በመጨረሻ ግን መናገም ስይሆንለት ቀረ፡፡ ሐኪሞችም የገማውን ልብሱን ገፈፉት፡፡ እንደ ቅባትም ያለ መድኃኒት ቀቡት፡፡ ከግማሽ ሊትር የበለጠ ደም ሰጡት፡፡ በመጠጥ ከተጉዳው ከልቡ ድካም የተነሣ ኤተር ለመቀበል አለመቻሉን ከተረዱ ዘንድ የሚያፈዝ መድኃኒት ጀርባውን ወግተው ሰጡት፡፡

አንዱ ሐኪም ከጉልበቱ ይቆረጥ አለ፡፡ ሌላው ግን ሁለተኛ እንዳይሰክር ከቂጡ አስጠግቼ እቆርጠዋለሁ አለና ከቂጡ አስጠግቶ ቆረጠው፡፡ የተቆረጠውን እግሩን ከፊቱ መዝናችሁ አስታቅፉት ብሎ አስታማሚዎችን አዘዘ፡፡ እግሩን ከፊቱ መዘኑትና አሥር ኪሎ የሆነው እግርህ ይኸውልህ ታቀፈው ብለው አስታቀፉት፡፡ በዚህ ጊዜ በአጥንት የተጣሉት ውሾች በላዩ ላይ ተረፈረፉበትና በድንጋፄ ከእንቅልፉ ነቃ፡፡ ይህ ሁሉ የደረሰበት በሕልሙ እንደነበር ማወቅ አቃተው፡፡ ከአልጋው ላይ ወረደና ገረዱን ወይዘሮ ጥሩነሽን ከመኝታቸው ቀስቅሶ እየጮኸና እየተንዘረዘረ ስንት እግር ነው ያለኝ ብሎ ጠየቃቸው፡፡

ወይዘሮ ጥሩነሽም ‹‹ድሮ ስንት እግር ነበረዎ ጌታ?›› ብለው ጠየቁት፡፡ እየጮኸ ሶስት ጊዜ ‹‹ ሁለት ሁለት ሁለት ነበረኝ›› አላቸው፡፡ ሶስት ጊዜ ሁለት ስድስት ማለት ነው፡፡ ልጆቼን ያሳደገች ላም ካራት እግር የበለጠ አልነበራትም ሰለዚህ የእርስዎም እግሮች አራት ናቸው አሉት፡፡ ‹‹የምሬን ነው የምጠይቅዎት;›› አለና ጮሆ ተንዘረዘረ፡፡ ‹‹

በእርግጥ ሁለት እግሮች አሉዎት ጌታ›› አሉት፡፡ ተበጀ እግሩን አጎንብሶ ለመሳም ሞከረና ራቀው፡፡ ወደ ሰማይ እያየ መጠጥ ማለት ለእኔ ሞት ማለት ነው አለ፡፡ ጊዜውም ሌሊት ነበር፡፡ እንደዚህ የማሉበት ሌሊት ያልፋል ብለው ወይዘሮ ጥሩነሽ መለሱለት፡
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Mon Dec 09, 2013 8:36 pm

ራሴን በላውት
(በደበበ ሰይፉ)

ገብቼ ሱባዔ
ገብቼ ጉባዔ
ላያሌ አመታት
በነኔት ማሳ ተመላልሼበት
ወጥቼ ወርጄበት
አዝመራ ባጣበት
ራሴን በላውት
እየመነዘርኩት
እያመናዘርኩት::
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby varka911 » Tue Dec 10, 2013 12:25 am

እናመሰግናለን ወንድማችን ቡቺ :D
ስምህን ሳየው ማንደፍሮት ትዝ ይለኛል: የበዓሉ ግርማ ድርሰት ላይ ያለው ማለቴ ነው :P
እንግዲህ ይልመድብህና ከቡቺ ማስታወሻስ እየቀንጨብክ አስደብረን :wink:

ቦቹ wrote:ራሴን በላውት
(በደበበ ሰይፉ)

ገብቼ ሱባዔ
ገብቼ ጉባዔ
ላያሌ አመታት
በነኔት ማሳ ተመላልሼበት
ወጥቼ ወርጄበት
አዝመራ ባጣበት
ራሴን በላውት
እየመነዘርኩት
እያመናዘርኩት::
Get your second chance On my First Aid!
varka911
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 101
Joined: Tue Oct 22, 2013 2:30 pm

Postby ቦቹ » Tue Dec 10, 2013 1:06 am

varka911 wrote:እናመሰግናለን ወንድማችን ቡቺ :D
ስምህን ሳየው ማንደፍሮት ትዝ ይለኛል: የበዓሉ ግርማ ድርሰት ላይ ያለው ማለቴ ነው :P
እንግዲህ ይልመድብህና ከቡቺ ማስታወሻስ እየቀንጨብክ አስደብረን :wink:

ቦቹ wrote:ራሴን በላውት
(በደበበ ሰይፉ)

ገብቼ ሱባዔ
ገብቼ ጉባዔ
ላያሌ አመታት
በነኔት ማሳ ተመላልሼበት
ወጥቼ ወርጄበት
አዝመራ ባጣበት
ራሴን በላውት
እየመነዘርኩት
እያመናዘርኩት::


ቅቅቅ ይመችህ ፍሬንድ:: ይቀርባል ባይነት ባይነት:: :)
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Tue Dec 10, 2013 1:14 am

እሳት ወይ አበባ በpdf ሙሉው መጽሀፍ

http://upload.wikimedia.org/wikipedia/a ... sAbeba.pdf
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Tue Dec 10, 2013 1:49 am

ግድ የለም ሰምታለች
(ከመስፈን ወልደ ማርያም)

ባል ያላገኘች ሚስት
ያልወለደኝ እናት
እግዜር ደስ ያለው ለት
ያለ እንከን የሰራት
መልኬ በቃኝ ብላ አለምን የናቀች
አንዲት ሴት ነበረች::

ዝም አልል አልቻልኩም
የልቤን ነገርኳት ብትወደም ባትወድም
''አንቺ ሴት አንቺ ቆንጆ
ለምን ትኖሪያለሽ በዚ ትንሽ ጎጆ
በባሕር ማዶ ጡብ ቤት መስራት ሲቻልሽ
ደሳሳዋን ጕጆ ምን ዕድል አስመኘሽ?
እስከ መቼ ድረስ ትከናነቢያለሽ?
እስከ መቼ ድረስ ትሽኮረመሚያለሽ?
መስታወት ግዢና መልክሽን እወቂው
ጉድለትሽ ምንድን ነው? ውበትሽስ የት ነው?
በመጎሳቆልሽ ማነው የሚጎዳው?
ማንስ ነው የሚያዝነው?
ጠይቂ መርምሪ ተረጂው እውነቱን
ራስሽ ለራስሽ አስተካክዩው ፍርዱን
ሀዘን ነው ስንፍና ወይስ ድንቁርና?
የሚያኮራምትሽ በአለም በጤና
በቅናት ሲያሽካኩ ጎረቤቶች ሁሉ
እንብረጥ እንብለጥ እየተባባሉ
ካቅማቸው ፉንጎቹ ሲመጣደቁብሽ
ማን ይድላው ብለሽ ነው አንቺ እንዲህ መሆንሽ?
ሣጥንሽን ክፈቺው
ጌጥሽን እስቲ አውጭው
ይውረድ ክንብንብሽ
ቀና በይ ካንገትሽ
ተራመጂ በእምነት
ኩሪ ባለሽ ውበት!

አፈስ አፈስ አርጊው እርምጃሽ ይጣደፍ
በድን አትምሰይ ይቅርብሽ መንከርፈፍ

ቀሚሶች አሰሪ ሰፋ አርጊው ጥበቡን
ጸጉርሽም ይበጠር ተይው ክንብንቡን::

ቤትሽንም አጽጂው ተባዮቹ ይጥፉ
ምሰሶው ይቃና ይጠረግ ምድራፉ::

ኧረ ምን ጎደለሽ? ካካል ከአእምሮሽ
ለጋ ነሽ መልካም ነሽ ሙሉ ነሽ ትርፍ ነሽ::
ሕይወት ያለተስፋ ኩራትስ ያለ ክብር
ወግ ያለ መአረግ ምኞትስ ያለ ግብር
ከንቱ ነው መና ነው ሕልም ነው እወቂው
መካንነት መርጠሽ ዘር ልታጠፊ ነው::
ለስጋ ነው? ለነብስ?
ሕያው ለሙት መንፈስ!
ጤንነት ነው? እብደት?
ሕይወትን መሰዋት!

በትካዜ ፈዛ አይን አይኔን እያየች
ሳወርደው መዓቱን ጭጭ ብላ አዳመጠች::
ነግሬአት ነግሬአት አተኩራ እያየች
' አዬ የልጅ ነገር!" ብል ጥላኝ ሄደች::
ትካዜ ሐዘንዋን ጭንቅና ስቃይዋን
አጋብታብኝ ሄደች ቀረሁኝ ብቻዬን::
ሀሳቤን ጠልታ ነው? ወይስ ልጅነቴን?
ሳልጠይቃት ሄደች
ግድ የለም ሰምታለች
ግድ የለም ሰምታለች::
Last edited by ቦቹ on Tue Dec 10, 2013 11:47 am, edited 1 time in total.
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Tue Dec 10, 2013 5:47 am

ክልክል ነው

ማጨስ ክልክል ነው
ማፍዋጨት ክልክል ነው
መሽናት ክልክል ነው
ግድግዳው በሙሉ ተሰርቶ በክልክል
የቱ ነው ትክክል?
ትንሽ ግድግዳና ትንሽ ኃይል ባደለኝ
"መከልከል ክልክል ነው"፤ የሚል ትዕዛዝ አለኝ፡፡

(በእውቀቱ ስዩም፣ የ፣ሣት ዳር ሐሳቦች፣ 2000)
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Tue Dec 10, 2013 5:56 am

በጠራ ጨረቃ

በጠራ ጨረቃ በእኩለ ሌሊት
አይኖቿ እያበሩ እንደ ከዋክብት
«ሳማት ! ሳማት !» አሉት
«እቀፍ ! እቀፋት።»
አላወላወለም ወጣቱ ታዘዘ
ወገቧን አንገቷን እጇን በእጁ ያዘ
ምንም እንኳ ጡቷ እንደሾህ ቢዋጋ
ጣቷ በመሆኑ የጉማሬ አለንጋ
ጆሮ ግንዱን ሰማው በጥፊ ሲናጋ።
ዋ ጀማሪ መሆን ! ዋ ተማሪነት
ዋ ትእዛዝ መፈጸም ዋ ምክር መስማት !
በጠራ ጨረቃ በኩለ ሌሊት...

መንግስቱ ለማ
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 3:32 am

ዳዊትና ጎልያድ

እግዜርና ዳዊት አብረው ተቧደኑ
ብቻውን ታጠቀ ጎልያድ ምስኪኑ
አንዳንዱ ለሽንፈት ተገዶ ሲፈጠር
በጥቅሻ ይወድቃል እንኳንስ በጠጠር

ከበእውቀቱ ስዩም
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 6:41 am

ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ሚሊዮን መሰለኝ
ፍቅሬ አንችን ስወድሽ ቀኑ ረዘመብኝ።
እኔ እወድሻለሁ
የሰማይ መሬቱን
የባህር ስፋቱን
የዓለም ዳርቻ የርቀቱን ያህል
እንደ ፅጌ-ረዳ
እንደ አደይ አበባ
እንደ ሎሚ ሽታ፡፡
እንደ እጣን ጢስ እንጨት፣ እንደ ከርቤ ብርጉድ፣
እኔ እወድሻለሁ፣
አበባ እንዳየ ንብ፡፡


እንደ ቢራቢሮ ጫካ እንደሚያስሰው
ፍቅርሽን በፍቅሬ በፍቅርሽ ልቅመሰው
ማር ወለላዬ ነሽ ከረሜላ ስኩዋር
አማርኛ አይበቃ፤
ወይ ጉድ!
ባለም ቋንቋ ሁሉ ቢወራ ቢነገር፣
እኔ እወድሻለሁ
እንደማታ ጀንበር።
እንደ ጨረቃ ጌጥ፣ እንደ ንጋት ኮከብ፣
እኔ እማልጠግብሽ
ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፣ ስወድሽ፡፡
ጡት እንዳየ ህፃን ወተት እንዳማረው
ጠጋ በይ ዘመዴ አፍሽ ህይወቴ ነው።
ጣይ እንዳየ ቅቤ
ገላዬ ገላሽን ሲነካ የሚያልቀው፣
አፈር መሬት ትቢያ ውሃ እንደሚበላው፣
ፍቅሬ አንቺን ስወድሽ
ብዙ ሺህ ዘመናት
እልፍ አእላፍ ሌሊት
ውድ እወድሻለሁ፣
ዐይኖችሽን ባይኔ ተዳክሜ እያየሁ
ስወድሽ ስወድሽ
እኔ እወድሻለሁ።

16/9/1960ዓ.ም የኢትዮጵያ ድምጽ ጋዜጣ
ገብረክርስቶስ ደስታ
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 6:48 am

I am the first Earth Mother of all fertility
I am the Source I am the Nile I am the African I am the beginning
O Arabia, how could you so conveniently have forgotten
While your breath still hangs upon the threads of my springs
O Egypt, you prodigal daughter born from my first love
I am your Queen of the endless fresh waters
Who rested my head upon the arms of Narmer Ka Menes
When we joined in one our Upper and Lower Lands to create you
bosom of my being
How could you so conveniently count down
In miserable billions of petty cubic yards
The eternal drops of my life giving Nile to you
Beginning long before the earth fell from the eye ball of heaven,
O Nile, that gush out from my breath of life
Upon the throats of the billions of the Earth's thirsty multitudes,
O World, how could you so conveniently have forgotten
That I, your first fountain, I your ever Ethiopia
I your first life still survive for you?
I rise like the sun from the deepest core of the globe
I am the conqueror of scorching pestilences
I am the Ethiopia that "stretch her hands in supplication to
God"
I am the mother of the tallest traveler on the longest journey on Earth
My name is Africa I am the mother of the Nile.
O Nile, my prodigal daughter on the wilderness of the desert
Bringing God's harmony to all brothers and sisters
And calming down their noises of brass in their endless nakednesses
O Nile, you are music that restore the rhythm of existence
Into the awkward stampeding of these Middle Eastern blindnesses
You are the irrigator that cultivate peace
From my Ethiopian sacred mountains of the sun
Across to nod on the East of Aden and across Sinai
Beyond Gibraltar into the heights of Mount Moriah
O Nile, my chosen sacrifice for universal peace offering
Upon whose gift the heritages of Meroe and Egypt
Still survive for the benefit of our lone World
You are the proud daughter O Nile, who taught
The ancient world how to walk in upright grace
You are my prodigal daughter who saved and breast fed
Little lost Jacob whose brothers sold for food
You, who nurtured, fed and raised
The child prophet called Moses on your cradle,
You, who stretched out your helping hand and protected
The baby Christ from the slaughtering swords of their Herods,
O Nile, my infinite prodigal daughter
At whose feet mountains like Alexander bent
Their unbendable heads to drink from your life giving milk,
O Nile, at whose feet giants like Caesar Knelt
Conquerors like Napoleon bowed
Their unbowable heads to partake from your immortal bounty.
O Nile, you are the majestic blood line of my African glory
That shower my blessings upon the starved of the world
You are the eloquence that ring the Ethiopian bell across the deaf world You
are the gifted dancer of graceful rhythms
That harmonize with your sisters Atbara and Shabale
With your brothers Awash and Juba
To fertilize the scorched sands of Arabia
O Nile, without your gift Mediterranea shall be a rock of dead waters
And Sahara shall be a basket of skeletons
You are Africa's black soil that produce life
You are the milk that quench the thirsty multitudes
You are the messenger of my gospel, O Nile
That bring my abundant harvest to the mouth of the needy
You are the elegant pilgrim of my mercy.
You are the first fountain you are the first ever Ethiopia
You are the appeaser of the lustful greeds
You are the first Earth Mother of all fertility
Rising like the sun from the deepest core of the globe
You are the conqueror of the scorching pestilence
You are the source you the Africa you are the Ethiopia you are the Nile.

- Tsegaye Gebre-Medhin, Ethiopian Poet Laureate, August 1997
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 7:00 am

ተይ አይሆንም ነብሴ

የቱ ይሆን ኩነኔው የትኛው ነው ፅድቁ?
የምድሩ የቅርቡ የሰማዩ የሩቁ?
በእንጀራ በጠላ በሥጋ ሢሣይ
አካል ብቻ እንጂ ነብስ አታድግም ወይ?
ነብስ እንደነበልባል ሥጋ እንደእንጨት
አይደል ባንድ ዕጣቸው መዳፈን መብራት?
መክሰል ወይስ መፍካት?
የት ነው የሥጋ ደብሩ ደሞ የነብስ ቤት?
መች ነው ለየብቻ የተካለሉት ጎጆስ የወጡት?

ልሂድ ልሂድ አለች ወደ ሕልሟ ኬላ
ሥጋ ሐር ልብሷን ነብሴ አውልቃ ጥላ
ከፅድቁ ገበታ ከአብርሀም ልትበላ::

ተይ አይሆንም ነብሴ ሥጋሽ ይታሠብሽ
ተመከሪ ነብሴ ምድሩም ይታወስሽ
አልፋ ወ ዖሜጋ ጭቃው ነው ገነትሽ
የዘላለም ቤትሽ::

ደበበ እሸቱ
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 7:17 am

በመላ ዕድሜያቸው

በመላ ዕድሜያቸው
በገማ አፋቸው
የሌላውን ስጋ
ቆርጠው እሚያደቁ
እሚቦጫጭቁ

ለሰከንድ ቁርጥራጭ
ለደቂቃ ፍላጭ
ዘግተው አፋቸውን
ከፍተው ራሣቸውን
ትተው የውጭውን
ውስጡን ቢያስተውሉ
የልብን ጉድጓድ

በድማሜው ብቻ
ባደሩ በዋሉ
ቀሪ ዕድሜያቸውን
ሲያሙ ራሣቸውን::

ደበበ እሸቱ 1968
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 7:26 am

ያገረሸ ፍቅር

የሰማይ
አሞራ
ላዋይህ
ችግሬን፡፡
ብረር ሒድ ንገራት”.
ከትልቁ
ዛፍ
ሥር፣
ዱሮ በልጅነት
ከተጫወትንበት
ከትልቁ ዛፍ ሥር አታጣትም ፍቅሬን
ብረር
ሒድ ንገራት፣
ንገር መናፈቄን፣

(ገብረ ክርስቶስ ደስታ፣ 1998)
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Postby ቦቹ » Thu Dec 12, 2013 7:36 am

ያልተማረ ይግደልህ

ትናንትን አፈቀርኩት" ዛሬን ግን ጠላሁት
አፌን ለሆድ ብቻ ሲጮህ አገኘሁት፡፡
ትንሽ መግፋት ቢቻል ጊዜን ወደ ኋላ
እኔስ በተሰየምኩ ካባቴ ፊት ለፊት ከአያቴ በኋላ
ወይ ታሪኬ ሊፃፍ ወይ ግፌ ሊሰላ፡፡
አባባ ገድልህን ለምን ነው የነገርከኝ?
ለትናንት አሻቅለህ ዛሬ አስጠላኸኝ
ብትከፍተው ገለባ
ሕይወት ትግል አልባ፣ ትግሉም ሕይወት አልባ
የተማረ ይግደለኝ ብለህ አጓግተኸኝ
ፊደል ከቆጠረ ቁጥርን ከደመረ ለሆዱ ካደረ
መንጋ መሀል ጣልከኝ
እኔም ተማከርኩልህ" ተመራመርኩልህ
የመብት አቡጊዳ ትግሌን ጀመርኩልህ
መብሌን አትንኳት ብዬ ፎከርኩልህ
ኧረ በሞትኩልህ
ይልቅስ ልንገርህ" ሞትክን በተማረ መመኘትክን እርሳው
ጽድቁን ከፈለግከው
ፊደል ያልቆጠረው ያገሬ ገበሬ ተኩሶ ይጣልህ፣ ይግደልህ ከማሳው፡፡

(ቼበለው መኩሪያ፣ ማለዳ፣ 1993)
ያ ተፈሪ - በንቲ!
ጀበሲ ኦፍኤጊ!
ኢትዮጵያን ነመገንቲ!
ተፈሪ በንቲ!


ኢጆሌ! ወረ አድአ
ቦቹ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 357
Joined: Fri Dec 31, 2004 1:26 am

Next

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 2 guests