እኔን ደግሞ ባለሱቅ ናፈቀኝ:: በተለይ ዛሬ ይህንን ጽሁፍ ካየሁ በኋላ እንዴት ባለሱቅን አስታወሰኝ መሰላችሁ! የሱን ጽሁፍ ያነበብኩ ስለመሰለኝ በሩጫ ይዤው መጣሁ::
" የ#ET702 ከአዲስ አበባ ሮም-ሚላን ጎዞዬ ካለፈ በኋላ እንደዋዛ ሲነገር ይህን ይመስል ነበር፡፡
እንዴት ናችሁ ጓደኞቼ?አንዳንዶቻችሁ ትንሽ ስለሁኔታው እንዳብራራላችሁ በጠየቃችሁኝ መሰረት የአቅሜን እንዲህ አሰናዳሁት። ችለዉና በርትተው ለሚፈጠሩ ኣንዳንድ የፊደላት እና የቃላት ጉድፈቶች ይቅርታዬ ይቅደም።
እንዲህ ጀመርኩት………
ከዚህ በፊት በአጋጣሚ አርፍዶ በመምጣት የሚከሰተዉን እንግልት ስለማዉቀው ሲጠጋጋ በተባልኩት ጊዜ ነበር በቦታው የተገኘሁት ከምሽቱ 4 ሰኣት አከባቢ ማለት ነው. . . . .የጉምሩክን፣የአየር መንገዱን መስፈርት መለኪያ፣የኢምግሬሽኑንም. . . . ሌሎችንም ምርመራዎች ጨርሼ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ የደረስኩት ፕሌኑ ይነሳል ከተባለበት ሰዓት 50 ያህል ደቂቃዎችን ቀደም ብዬ ነበር፡፡
. . . . . .በመሃል በመሃል ስልክ ሳወራም ነበር. . . . . (ለምን ይዋሻል?). . . . ቤተሰብ፣ዘመድ፣ጓደኛ(ሙሌ፣ አሼ፣መንጌ፣ ዶ\ር አንዳርገው . . . . .ሌሎችንም). . ዉይ!እኔን ሞት ይርሳኝ! (ለነገሩ ለጊዜውም ቢሆን ቢረሳኝም ኣይደል !) ሆሆሆ!የሆሆሆነን ሰው በጣምም በተደጋጋሚም ሳወራ ነበር( (መቼም ‘ማነው?’ ብላችሁ ኣትጠይቁኝም ኣይደል?. . . .ብትጠይቁኝም ይነገራቹሃላ!ብርቃችሁ ነው?). . . . . .
ይልቅ ወደ ፕሌን ዉስጥ መግቢያ ሰዓት ደረሰና ወደ ውስጥ ዘለቅን። ለዚህ ስራ በተመደበች ሆስተስ መሪነት ቦታዬን ከሩቅ ኣየሁት. . . . . . በሁለት በእድሜ የገፉ ነጭ የቆዳ ቀለም ካላቸው ሰዎች መሃል. . . . . (በዚህ ጊዜ ፊቴን ብታዩት. . . .ቀን ላይ ረጅም መንገድ (ከሀዋሳ አዲስ አበባ) መንገድ ተጉዤ ስለነበር ባስ ውስጥ ከጎኔ ተቀምጠው የነበሩት ጠና ያሉ ሰዉ ነበሩ ወዲያው በዐዕምሮዬ ከች ያሉት. . . . እውነት ግን ሙዳቸው አልተመቸኝም ነበር።እና……አሁን ደግሞ ከቀኑ ሻ. . . ል ማለቱ ነው መሰል በሁለቱም ጎኔ።’ይሁና. . . .!’ ኣልኩና በዉስጤ ጠጋ ብዬ ከላይ ሻንጣ ማስቀመጫዉን ስከፍት በግራ በኩል የነበሩት በፊታቸው ፈገግታ ተሞልተው ብድግም ሻንጣዉን እንዴት ባስቀምጥ የላፕቶፕ ቦርሳም ኣብሬ ማስቀምጥ እንደምችል ነገሩኝ (በጣሊያንኛ መሆኑ ነው). . . . እኔም ፈገግ እያልኩ ምላሽ ሰጠሁ (Grazie!) አልኩኝ. . .’አመሰግናለሁ’ ማለት ነው።
ቆመው አሳልፈውኝ ቦታዬ ላይ ቁጭ ካልኩ በኃላ ወደ እኔ ዞረው ማዉራት መጫወት በሚፈልግ ዐይን ሲያዩኝ…..ፈገግ ስልላቸው ‘ዲ ዶቬ ሴይ?’ አሉኝ።።(‘ከየት ሀገር ነህ?’ ማለት ነው ኢትዮጵያዊ እንደሆንኩ ነገርኳቸው “ዱ ዩ ስፒክ ኢንግሊሽ?” ሲሉኝ አወንታየን በቋንቋው መለስኩላቸው ።መጀምሪያም የማዉቃትን የማዉቃትን ስለጠየቁኝ ነው እንጂ ጣልያንኛዉን ብዙም ኣይደለሁም።በእንግሊዝኛው ቀጠልን. . . . ሰማቸው ሪካርዶ እንደሚባል፣ጣልያናዊ. . . ዕድሜኣቸው 85…ከዚህ በፊት ወደ ኢትዮጵያ ሁለቴ እንደመጡ . . . በመጀመሪያው ወደ ሰሜን፣ሰሜን ምስራቅ እና ሰሜን ምዕራብ ያሉትን የቱሪስት መዳረሻዎችን ሁሉ እንዳዳረሷቸው . .. .በሁለተኛው ደግሞ ወደ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እንደጎበኙ ነገሩኝ።(በመሃል ፡ ‘ፒኣቼሬ’(‘ስላገኘውህ ደስ ብሎኛል’እንደማለት ነው) ብለው እጃቸዉን ዘርግተውልኝ እኔም አጸፋውን መልሼላቸዋለሁ በስርዓቱ፡፡
ኢትዮጵያን እንደወደዷትና አስካሁን ካዯቸው ሃገራት እንደምትለይ ኣከሉልኝ. . . ኣሁን ግን ከቡሩንዲ እና ታንዛንያ እየመጡ አንደሆነም እንዲሁ።እኔም ያለችኝን እያወራሁ የ ሀዋሳ ልጅ እንደሆንኩ ስነግራቸው “ሶ…ሶ…ቢውቲፉል” አሉኝ. . .ተመልሰው እንደሚመጡም አወሩኝ. . . . እንዲያ እንዲያ እያልን ፕሌኑ የሚነሳበት ሰዓት ደረሰ. . . የስልክ ቀፎዬ ሰዓት እንደሚያሳየው ከሆነ 7 ደቂቃዎችን ያህል ዘግይቶ ነበር::
አውሮፕላኑ ተነሳ።በረራው ተጀመረ አ…..ሉ።ኣማተብኩና 3 ጊዜ ጸጋን የተሞላሽ. . . . ።በሰላም እንደጀመርን በሰላም እንድናርፍ እርዳን ብዬ ከኪሴ ኣዉጥቼው የነበረዉን መቁጠርያ መለስኩ። ቀን ላይ ጸሃዩም መንገዱም ኣድክሞኝ ስለነበር ሃሳቤ ሁሉ ስለመተኛት ነበር።ከደቂቃዎች በኃላ ኣጠገቤ የነበሩትም ስዎች ለመተኛት ሲዘገጃጁ እኔም ለምን ይቅርብኝ ብየ የጫማዎቼን ማሰርያ በማላላት. . . . ወንበሩን ትንሽ ወደ ኃላ ዘንበል በማድረግ. . . የተሰጠኝን ፎጣ ልብ. . .ስ አደረኩና ላሽሽሽሽ።
በግምት ከ 1 ሰዐት በኃላ የሱዳን አየር ክልል ውስጥ ይሆናል ብዬ እገምታለሁ. . . መብራት ሲበራ የምግብ ሰዓት መሆኑን ነቄ ኣልኩና አኔም ከእንቅልፌ ነቃሁ።የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሰርቪስ ኣሪፍ ነው. . . ተሸላሚም ኣይደል።ምግባችዉም ኣሪፍ ነው።ሌላዋ በሌሎች አየር መንገዶች(ካየኃቸው) ያላየኃት ቀይ ዋይን አለች።።ከእንቅልፌም ስነቃ ሳስብ የነበረው ከምግብ በኃላ ቲኒሽዋን ዉስድ አድርጌ ተመልሼ የምተኛውን ጥሩ እንቅልፍ።
ወደ ፊት ኣሻግሬ ሳይ ሆስተሶቹ እያስተናገዱ ከእኔ ፊት 4ኛ ይሁን 5ኛ መደዳ ደርሰዋል።ሁሉም ተዘገጃጅቶ እየተጠባበቀ ይታያል።በዚህ መሃል የፕሌኑ ፍጥነት ሲጨምር ይታወቀኛል. . .ከፍታዉም ሲጨምር በጆሮዬ ላይ በሚሰማኝ ስሜት አስተዋልኩ።ሰው መረበሽ ጀመረ።የነበርነው ኢኮኖሚ ክላስ ስለነበር ከፊት ምን ኢየተካሄደ እንደነበር አላየንም።ለነገሩ ከፊት የነበሩት የቢዝነስ ክላሶችም ብዙም የተለየ ኢንፎ ኣልነበራቸዉም።ፓይለቱ እና ሆስተሶቹ ጉዳዩን አፍንው ይዘዉት ነበር።ከዛ……ተጀመረኣ!።
በመጀመርያ አውሮፕላኑ ወደ ላይ ወጣ ኣላልኳችሁም?።አሁን ደግሞ ድንገት ዘጭ አለ. . . ልክ ከአየር ላይ የሆነ ክብደት ያለው ነገር ሲወድቅ እንደሚሆነው ማለት ነው።በጣ….ም ነው የሚወርደው።ሰዉ ተደናገጠ።አንዳች ችግር እንዳጋጠመ ማጉረምረም ጀመረ።ሁሉም የየራሱን መላምት ይሰጥ ጀመች።እኔ በበኩሌ ምናልባት ያልተጠበቀ የአየር ንብረት ለዉጥ ይሆናል ብየ አሰብኩ።
ኣሁንም በጣም ወደ ላይ ከፍ አለ. . .የሆነ ድምጽ ተሰማ።የረዳት አብራሪው ድምጽ ነበር።”ሲት ዳውን!” “ሲት ዳውን!”). . . በተደጋጋሚ ይላል።አሁንም ከፍታው እየጨመረ ነው።ከመቅጽበት የ ኦክስጂን መሳቢያ ጭንብሎች ከ ፕሌኑ ጣሪያ ወረዱ። ‘የኦክስጂን መሳቢያ ጭንብሉን ኣጥልቁት’ ይላል በእንግሊዝኛ “ፑት ኦን ዘ ኦክስጂን ማስክ . . .አይ ዊል ጊቭ ዩ ሞር ኦክስጂን” ሲል ድጋሚ ወደታች ወረደ።ይኼኛው ይብሳል. . . ሰው ኦክስጂኑን ለማጥለቅ ግብግብ።ሆስተሶቹም መስተንግዶዉን ላሽ ብለው ወደ ቦታቸው ሄደው ጭንብላቸዉን ጥልቅ (ይሞታሉ ታዲያ?.....)አሁን ሰዉም መጮህ ጀመረ።የሚጸልይም መጸለይ…..እኔም የበኩሌን ልወጣ ብዬ ቅድም ከኪሴ ያኖርኳትን መቁጠርያ አውጥቼ…..አቡነ ዘ ሰማያት፣ ……ጸጋን የተሞላሽ፣.. .. …የሱስ ማርያም ዮሴፍ ልቤን ነፍሴን ህይወቴን ሰጣችኃለዉ፣…..በሞቴ፣….. ብቻ ምን ልበላችሁ? …..ጸሎት ሁሉ ከየ ኣቅጣጫው…….የራሴን ጭንብል ካጠለኩ በኃላ ከጎኔ የነበሩት ሰዎችም ኣጥብቄ አሰርኩላቸው።
በዚህ መሃል ምን ቢሆን ጥሩ ነው? በአማርኛ ”ዛሬ አምላክ ብቻ ነው የሚያድናችሁ” ሲል አልሰማሁትም?።ከዛ ከ ጥቂት ሲት ዳዉኖች በኃላ የምት ሰማዋም ድምጽ እየተቆራረጠች እየተቆራረጠች ጠፋች።ምን ይዋጠን? ጭንቀት. . . .የሞት ሽታ. . . ከየአቅጣጫው የጩኸት.. . . የጣር….የጸሎት ድምጽ ይሰማል።በጣም የገረመኝ እኚህ ቅድም አንኳን 85 ዓመታቸው ነው ያልኳችሁ አዛዉንት ሃባ አልደነገጡም።(ለነገሩ ለምን ይደንግጡ?።85 ዐመታት…..ሆ! ብታዩዋቸው አይመስሉም።አሁንም ጠንካራ ናቸው።ከዛ ምን ቢሉኝ ጥሩ ነው?።”ፈራህ ወይ?”። ወይ ጉድ! ምን ልበል?።’ኣዎን ፈርቻለሁ?’።አልልም።የነ አሉላ አባነጋ፣ የነ በላይ ዘለቀ ልጅ……የነ ካዎ ጦና የነ ተክሉ ዮታ ልጅ።እንዴት ፈራሁ ልበል?።ለዛዉም ለጣልያናዊ።ሄ ሄ ሄ ሄ!....
”አልፈራሁም አልኳቸዋ!”።የታባቱ!።አንድ ነገር ረሳሁ።የ አድዋው ላይ ኣይኖሩም።ለነገሩ ቢኖሩም ከጦርነቱ አያልፉም። ምናልባት የማይጨው ላይ።ምስኪኑ ህዝባችን ላይ አሲድ ሲደፋ ነበሩበት ይሆን?።እቃ አቀብለዉስ ቢሆን?።ሰልፍ ተቀላቅለው ደግፈዉትስ ቢሆን?።።አረ.. ይቅር።ከመጀመሪያው ኢትዮጵያን እንደሚወዱና እኔ ሃገር ቤት ሆኜ ያላየኃቸውን ቦታዎች እንዳዩ ሲነግሩኝ ይሄን ሀሳብ መተው ነበረብኝ። እና…እኔ ከነበርኩበት መደዳ ሶስተኛ መስመር ወደፊት በግራየ በኩል ሁለት ኢትዮጵያዊያን ነበሩ።ጠና ያሉ አለብበሳቸው ለዬት ያለ።በሁኃላ ላይ ስንተዋወቅ ኦኦኦኦኦ..ቴ…..!
አንደኛው በሀገረ ኢትዮጵያ የአንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ገዘፍ ያለ የዉሃ ማምረቻ ኩባንያ ባለቤት ነበሩ።ሌላኛዉም ነዋሪነታቸውን በሀገረ እንግሊዝ ያደረጉ፣ጠና ያሉ ረጋ ያለ አንደበት ያላቸዉ።እሳቸውም ቢዝነስ ማን ናቸው።ድምጻቸው ይሰማኝ ነበር።በተላይ የመጀመሪያው።ደጋግሞ “ጌታ ሆይ” ሲል ሰማው ነበር።ያው የሌላዉንም ጸሎት እኮ ሰምቻለሁ።ለምሳሌ ከፈትለፊቴ በስተቀኝ በኩል የሆኑ ሴትዮ “ኦ ሲኞሬ ጀሱ”(ጌታ ኢየሱስ ሆይ)።ደጋግማ ትል ነበር።ቀጥላም “ፕሬግያሞ ቱቲ”(ሁላችንም እንጸልይ)።ትል ነበር።
በስተቀኜ መተላለፊያዉን አለፍ ብላ የነበረች አንዲት ጣሊያናዊ ወጣት ‘አውሮፕላኑ የቴክኒክ ችግር ገጥሞት ነው’ አለች።ወሬው ተናፈሰ።በዚህ ጊዜ ስንት ነገር አሰብኩ።ግንባሬንና ጉንጮቼን አገላብጣ ስማኝ ኪዳነ ምህረት ትደግፍህ ብላ ጸልያልኝ የሸኘችኝ እናቴን. . . . ግንባሬን ዐይኖቼን አፍንጫዬን ከዛም ከናፍሮቼን በስሱ ሳም አድርጋ በስስትና በእንባ፣በአትሂድብኝ አይነት አስተያየት እያየችኝ በአንደበቷ በሰላም ደርሰህ ተመለስልኝ ብላ የሸኘችኝ እጮኛዬን…..ወንድሞቼን፣እህቴን፣ የወንድሞቼን ባለቤቶች፣ልጆቻቸውን፣ አክስቶቼን፣ ጓደኞቼን……ሆ ሆ ሆ ኧረ ስንቱን አሰብኩት….. ከሀዘናቸው ላጽናናቸው ብመጣ ለቤተሰቤ ሌላ ሀዘን ልፍጠር?.... በቃ ልሞት ነው?።መልሼ ደግሞ እንዴት ሆኖ?።በፍጹም አልሞትም።ያስጀመረኝን ሳያስጨርሰኝ አይወስደኝም እልና….ሳላዉቅ ያቋረጥኩትን ጸሎቴን መቀጠል።ጠባቂየ የሆንክ የእግዚኣብሔር መልዓክ ሆይ………ብቻ ዉዝግብግብ አልኩኝ።
በዚህ መሃል ነበር ሶስተኛው ወደ ታች መውረድ የተከሰተው።በዚህኛው ጊዜ ትንሽ ወደጎንም እንደመንገጫገጭ ብሎ ነበር።።እስካሁን የታየ አንድም ሆስተስ አልነበረም።እነሱም የኦክስጂን ጭምብሉን ኣጥልቀው ነበራ!....ኣሁን ትንሽ ረገብ አለ።እንግዲህ ያ ከፍታ መጨመርም ሆነ ድንገት ዝቅ ማለት….ዋናው አብራሪ ወደ መጸዳጃ ቤት ደርሰው ሲመለሱ የፕሌኑን ጋቢና(በራሴ ቋንቋ) የውጥ በር ተቆልፎ ሲያገኙት ለመክፈት አልያም ለመስበር ሲያደርጉ የነበረዉን ሙከራ እንዲያቆሙ ማስፈራርያ መሆኑ ነበር።
እንዲያዉም አንዳንድ በቢዝነስ ክላስ የነበሩ በኃላ ላይ ሲያወሩ የረዳት ፓይለቱ ድምጽ ሲቆራረጥ እኛ ያልሰማናቸው ከረዳት ፓይለቱ ጋር የቃላት ልውውጦችም ነበሩ።ጥቂት የማስፈራርያ የአማርኛ ቃላት ይሰሙ ነበር ብለዋል።ልብ በሉ, የኦክስጂን መሳቢያ ጭምብሉ አሁንም በአፍና በ አፍንጫችን ላይ ነው።አንዳንድ ሰዎች ከአፋቸው ላይ ሲያነሱት አየሁና እኔም አነሳሁ።ለነገሩ ሆስተሶቹም ከፊትለፊት ራቅ ብለው መታየት ጀመሩ።አሁን ሁኔታዎች የተረጋጉ ይመስላሉ።ግን ምንም ድምጽ ኣልነበረም።ሰውን ለማረጋጋት ምንም የተደረገ ነገርም አልነበረም።የተላለፈ መልዕክትም እንዲሁ።ተሳፋሪው የየራሱን መላምት ያስቀምጣል።ግን አንድም ሰው ፕሌኑ መጠለፉን ያወቀ አልነበረም።ብቻ ዋናው መረጋጋቱ ነው የተፈለገው።የሚተኛም ተኛ።ሆስተሶቹ አይታዩም ነበር።ምግባችንም ቀረች።እኔም ትኝት አልኩዋ!።የታባቱ!...............ይቀጥላል….
ክፍል ሁለት ይቀጥላል"
አቦ ዋርካችንም ይቀጥል መሰለኝ:: ሰላም ብያለሁ::
https://www.facebook.com/DireTubeFans/p ... 6554506957
We must learn to live together as brothers or perish together as fools.
Martin Luther King, Jr.