ያልታደለ ሕዝብ “የቀብር ቀን” ሲጠብቅ “የፍቅር ቀን” ይመጣበታል! – ስዩም ተሾመ
ሳተናው
By ሳተናው
September 1, 2017 06:
ስዩም ተሾመ
ነሃሴ 26/2009 ዓ.ም “የፍቅር ቀን” ነው። ቀኑ “በፍቅር የተሳሰረ ሕዝብ እናት ኢትዮጲያ” በሚል መሪ ቃል በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ተገልጿል። በመርሃ ግብሩ ከተጠቀሱት ዝርዝር ተግባራት ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡- “ሁለት ታዋቂ ሞዴሎች በባህላዊ ልብስ ተውበው በሁሉም ክፍለ ከተሞች እየዞሩ የአበባ ስጦታ ያበረክታሉ። በሆስፒታል ለሚገኙ ሕሙማን፣ ለሕግ ታራሚዎች፣ ለሕፃናት፣ እናቶችና አዛውንቶች “የፍቅር ስጦታ ፖስት ካርድና አበባ ያበረክታሉ…” እነዚህ ተግባራት እንግዲህ የሚፈፀሙት በኢህአዴግ መንግስት ነው። ሌላው ቀርቶ አምና እና ዘንድሮ ብቻ በሰራው ስራ እጅግ ብዙ አዛውንቶች ረግመውታል፣ እናቶች አልቅሰውበታል፣ ሕፃናት እንደ ጭራቅ ይፈሩታል። “የሕግ ታራሚዎች’ማ…” የፈፀመባቸውን በደል ራሳቸው ያውቁታል።
“የህግ ታራሚዎች” ስትሉ አንድ ነገር ትዝ… አለኝ። በነገው ዕለት “የፍቅር ስጦታ” ከሚበረከትላቸው ውስጥ፤ እንደ እስክንድር ነጋ፣ ተመስገን ደሳለኝ፣ ዮናታን ተስፋዬ፣…ወዘተ፣ ወይም ደግሞ በፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተንገላቱ ያሉትን እነ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ በቀለ ገረባ፣ ንግስት ይርጋ፣…ወዘተ፣ በማዕከላዊ፥ ቃሊቲ፥ ቂሊንጦ፥ ዝዋይ፥ ሸዋ ሮቢት፥… በአጠቃላይ በታወቁና ባልታወቁ እስር ቤቶች መከራና ስቃይ እየደረሰባቸው ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ይገኙበታል? ኧረ ለመሆኑ፣ ከእነዚህ ሰዎች ፊት ቆሞ “ኑ እስኪ ዛሬ ‘የፍቅር ቀን’ እናክብር?” የሚል የኢህአዴግ ባለስልጣን አለ? ይህን ለማድረግ የሚያስችል ከፀፀት የፀዳ ሕሊና ያለው ባለስልጣን ይገኛል? በእርግጥ የለም! እንዲህ ያለ ስብዕና ያለው የኢህአዴግ ባለስልጣን በባትሪ ቢፈለግ አይገኝም። የኢትዮጲያ ሕዝብን “‘የፍቅር ቀን’ እናክብር?” ለማለት ደፍረቱን ከየት አገኛችሁ? ነው ወይስ በሕዝቡና በፖለቲካ እስረኞቹ መካከል ያለው ግንኙነት በግልፅ አልታያችሁም?
ሕዝባዊ ተቃውሞ
በአሁኑ ግዜ በሀገራችን በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞች ይገኛሉ። እነዚህ እስረኞች ተራ ወንጀለኞች አይደሉም። ሁሉም በሞያቸው የተከበሩ፤ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ ፀሃፊዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥…ወዘተ ናቸው። ከሞላ-ጎደል ሁሉም በአሸባሪነት ወንጀል ተከሰው የተፈረደባቸው፣ አሊያም በተንዛዛ የፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተንገላቱ ያሉ ሰዎች ናቸው። ዋና ጥፋታቸው ደግሞ “የሕዝብ መብትና ነፃነት ይከበር!” ማለታቸው ነው። ስለዚህ፣ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች የሕዝብ ድምፅ እና አሌኝታ ናቸው። አዎ…በእነሱ መታሰር የሕዝብ ድምፅ ነው የታፈነው። እንግዲህ ነገ በዚህ መልኩ ካፈናችሁት ሕዝብ ጋር “የፍቅር ቀን” ልታከብሩ ነው።
ሕዝብ ያሰበውን የሚናገረው፣ ፍቅርና ጥላቻውን የሚገልፀው በግልፅ መናገር ሲችል ነው። የኢትዮጲያ ህዝብ ግን እንኳን መናገር መተንፈስ ተስኖታል። በፍርሃት ልጓም አንደበቱ ተለጉሟል። ድምፁን የሚያሰሙለት፣ ብሶትና አቤቱታውን የሚገልፁለት የፖለቲካ መሪዎች፥ ጋዜጠኞች፥ ፀሃፊዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥…ወዘተ ለእስርና ስደት ተዳርገዋል። ሕዝቡ የኢህአዴግን የፍቅር ስጦታ ለመቀበል ወይም ለመተው የሚናገርበት አንደበት ያስፈልገዋል። የህዝቡ አንደበት ግን ከፖለቲካ እስረኞቹ ጋራ አብሮ ታስሯል። እነሱ ከእስር ካልተፈቱ ሕዝቡ የእናንተን “የፍቅር ስጦታ” በአክብሮት ይቀበለው፣ አሊያም አሽቀንጥሮ ይጣለው በፍፁም ማወቅ አትችሉም።
የፖለቲካ መሪዎች፣ ጋዜጠኞች፥ ጦማሪያን፥ ፀኃፊዎች፥ የመብት ተሟጋቾች፥ የሃይማኖት መሪዎች፥ …ወዘተ በሌሉበት ሕዝብ አፍ አውጥቶ እውነቱን አይናገርም። ምክንያቱም፣ በኢህአዴግ ካድሬ ጋር መጣላት፥ መጠቆር አይሻም። “ለምን?” ቢባል፤ ነገ ልጆቹን በሰላም ማሳደግ ይፈልጋል! ነገ በስራው መቆየትና ማደግ ይፈልጋል! ነገ ስኳርና ዘይት ይፈልጋል!… በአጠቃላይ፣ እውነቱን ከተናገረ የኢህአዴግ ጋሻ-ጃግሬዎች ነገ መውጫ-መግቢያ ያሳጡታል። ስለዚህ፣ ሕዝቡ የይመስል ውሸቱን ለኢህአዴግ ይነግረዋል። እውነተኛ ብሶትና ምሬቱን ግን፤ ለተቃዋሚ መሪዎች፣ ለታማኝ ጋዜጠኞች፣ ለሃቀኛ ፀሃፊዎች፣ ለመብቱ ለሚሟገቱ ወይም ለነፍስ አባቱ ይነግራል። እነዚህ ሁሉ በአሸባሪነት ከተከስሰው ሲታሰሩ እውነት ነው የታሰረው፣ የብዙሃን ድምፅ ነው የታፈነው። ሕዝቡን መተንፈሻ ነው ያሳጣው። እንዲህ በፍርሃት ከታፈነ ሕዝብ የመከራ ሲቃ እንጂ የፍቅር ሳቅ መጠበቅ ፍፁም አላዋቂነት ነው።
በአጠቃላይ፣ ሕዝብ የእናንተን የፍቅር ስጦታ ለመቀበልና ላለመቀበል የሚናገርበት አንደበት ያስፈልገዋል። በማዕከላዊ፥ ቃሊቲ፥ ቂሊንጦ፥ ዝዋይ፥ ሸዋ ሮቢት፥…በመሳሰሉት እስር ቤቶች መከራና ፍዳ እያዩ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች ሲፈቱ የህዝቡ አንደበት ይፈታል። የእናንተን የፍቅር ስጦታ በአክብሮት መቀበሉን አሊያም በንቀት አሽቀንጥሮ መጣሉን በግልፅ ይነግራችኋል። ይህ ካልሆነ ግን በፍርሃት የተለጎመ ማህብረሰብ ቢያፈቅሩት አያፈቅርም፣ ሲጠላም አይታወቅም። ለምሳሌ፣ ነገ የምትሰጡትን “የፍቅር ስጦታ” የተቀበለ እናንተን ፈርቶ፣ ያልተቀበለም እናንተን ሸሽቶ ነው። ከነገ ወዲያም በየስብሰባው ስትጠሩት የሚመጣው፣ የእናንተን የተለመደ ወሬ የሚሰማ መስሏችሁ ነው? አይደለም! ብሶትና ምሬቱን ለፈጣሪ እየነገረ ነው። አሁን ነገ “የፍቅር ቀን” ስትሉ ሕዝቡ “’የቀብር ቀን’ አርግላቸው” እያለ ፈጣሪውን ይማፀናል፡
ከመቼ ከትል ያነስን ቦንደኞች-በላይነህ አባተ
August 12, 2017
በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
ለገሰ ዜናዊ በወቅቱ በነበረው ያረቦች አመፅ መክንያት በእስራኤሎችና በምዕራባውያን ትዕዛዝ እንደዚሁም ሲወለድ በተነቀረበት የአማራ ጥላቻ የአማራን ጥቅም ለመንጠቅ ዓባይን ተሱዳን ደጃፍ ሊገድብ “ሕዳሴና ቦንድ” እያለ ቃዠ፡፡ የመለስ ቅዥት እንደ ዛር ተኮፍሷችሁ የሰይጣን ቁራጩ ለገሰ ቦንድ እንዲሳካ ስንክሳር እሚያካክል ጥሑፍ የጣፋችሁ ሆዳምና ዘልዛላ “ምሁራን”፣ የቦንድ ስብሰባዎችን ለማዘጋጀት መቀመጫችሁን ያማታችሁ አዘጥዛጮች፣ ቦንድ ለመግዛት ሆዳችሁን እንደ ቅንቡርስ እየገፋችሁ ያረጠረጣችሁ ህሊና ቢሶች፣ ልማት፣ ህዳሴና ታድሶ እያላቸው ያክላላችሁ ዘፋኞችና ሌሎችም ቦንደኞች! የቦንድ ገንዘባችሁ ወገኖቻችሁን እንደ ደን ከማስጨፍጨፍ በተጨማሪ ለገዳዮቹ መሳከሚያ፣ ሰርግ መደገሻ፣ መዝናኛና ለሌሎችም ቅንጦቶች መዋሉን ከእነዚህ በህሊናቸው ከተገዙ ወይዛዝርት ውይይት ተረዱ፡፡ (የወይዛዝርቱን ውይይት ይህንን ተጪነው ወይም ቆርጠውና አጣብቀው ይመልከቱ) https://ethsat.com/2017/08/esat-menales ... gust-2017/ ወይዛዝርቱ እውነት አልተናገሩም እያላችሁና ከተሞክሮዋ ትምህርት ከቀሰመችው የአባ የሻነው ትል እያነሳችሁ እንደ ልማዳችሁ አትንዘላዘሉ፡፡
አባ የሻነው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የትል ታሪክ ደጋግመው ይተርኩልን ነበር፡፡ አባ የሻነው “ተትሏ እንማር!” ይላሉ ራሳቸውንም እንደተማሪ በመቁጠር፡፡ “ትሏ ዛፍ ለመውጣት ስትሞክር ወደቀች፤ አንድ በሉ፡፡ እንደገና ሞክረች ግን ነጠረች፤ ሁለት በሉ፡፡ አሁንም እንደገና ስትንጠለጠል ዘች አለች፤ ሶስት ብሉ፡፡ ዘች ታለችበት ተነስታ እንደገና ተንጠለጠለች፤ ግን ተመልሳ እርፉቅ አለች፤ አራት በሉ፡፡ እርፉቅ ታለችበት ተነስታ አሁም ግንዱን በትንሹ ወጣች፤ ግን እንደገና ተንደባለለች፤ አምስት በሉ፡፡ ተተንደባለለችበት ተነስታ ተበፊቱ የበለጠ ርቀት ዛፉን ወጣች፤ ግን ተመልሳ ነጠረች፤ ስድስት በሉ፡፡ ተነጠረችበት ተነስታ ለሰባተኛ ጊዜ ስትሞክር ሰማይ የደረሰውን ዛፍ ምንም እንከን ሳይገጥማት ወጣችው” እያሉ ይተርካሉ ጨረቃ የመሰለ ፈገግታ እያሳዩና ሻሽ የመሰለ ጺማቸውን እያፍተለተሉ፡፡
ከትረካው በኋላም አባታችንና መምህራችን አባ የሻነው “በሰባተኛው ዙር ትሏ ለምን የተሳካላት ይመስላችኋል?” ብለው ሲጠይቁ “በሰባት ስላሴ ስለሚውል፣ ተስፋ ስላልቆረጠች …ወዘተርፈ” እያልን እንመልሳለን፡፡ እርሳቸውም “እርግጥ ነው ተስፋ ያልቆረጠን ስላሴም ይረዳል!” ብለው የምንሰጠውን መልስ ሳያጣጥሉ “ትሏ የተሰካላት ተልምዷ ትምህርት በመውሰድዋና ያደናቀፏትን መንገዶች ትታ ሌላውን በመከተልዋ ነው” ብለው ተልምድ የመማርንና የተለያዬ መንገድ የመከተልን ጠቀሜታ ያስተምራሉ፡፡
የአባ የሻነው ትል ያህል ተልምድ መማር ተስኗቸው ስለ ቦንድ እጃቸው ውሀ እስቲቋጥር የጣፉት፣ ላንቃቸው እስቲደርቅ የሰበኩት፣ ልሳናቸው ጥረቅም እስቲል የዘፈኑትና መቀመጫችርውን እስቲያልባቸው ያረጠረጡት ህሊናቸው የሸጡ አለዚያም የተንዘላዘሉ የለገሰ ቦንድ ካድሬዎች ናቸው፡፡ አለዚያማ ሰይጣንና ለገሰን እንኳንስ ቆመው ሞተውስ ከዘልዛላ በቀር ማን ያምናቸዋል?
የሚያዝ የሚጨበጥ ጭራ የሌለው ለገሰ፤ የሰፈሩን ባንክ በመዝረፍ ባደባባይ ውንብድናውን የጀመረው ለገሰ፤ በአስር ሺ የሚቆጠሩ የመንደሩን ጎረምሶችና ኮረዳዎች እንደ ሳር አሳጪዶ አገራችንን የባህር መተንፈሻ የነሳት ለገሰ፣ በርሃብ የረገፈውን ሕዝብ ስንዴ እየሰረቀ ኬሻውን ባሸዋ የሞላው ለገሰ፤ ለፖለቲካ ፍጆታ የቅዬውን ሕዝብ በቦንብ ያስጨረገደው ለገሰ፣ አማራን ለማዳከምና ለማጥፋት ድንጋዩን ብቻ ሳይሆን ጠጠሩን፣ አሸዋውንና አፈሩን የፈነቀለው ለገሰ፣ በአያቶቻችን ደምና አጥንት የከበረውን መሬታችንን ለሥጋና ለነፍስ አባቱ ሱዳን የሰጠው ለገሰ፣ ሕዝብን በቋንቋ ጎራዴ ያቃላው ለገሰ፤ ስንቱን ባልታወቀ ወህኒ ያሰቃየው ለገሰ፣ ስንቱን እያሰደደ ባባህር ያስበላውና በጭራቆች ያሳረደው ለገሰ “ቦንድ” ብሎ ሲጮህ ቦንደኞቹም ተከትለው እንደ ገደል ማሚቶ “ቦኦ…ንድ…ቦኦ..ንድ” እያሉ አስተጋቡ፡፡ ሳጥናኤል የእግዚአብሔርን ቃል እየተናገረ እንደሚያታልለውም ለገሰ “ራዕይ፣ ታድሶ… ህዳሴ” እያለ ጫቱን እየቃመ ሲጀነጅን ቦንደኞቹም ተከትለው “አዎ ልማት፣ ታድሶ፤ ህዳሴ! ያገር ጉዳይ! የሕዝብ ጉዳይ!” እያሉ ተሽኮረመሙ፡፡
መሽኮርመሙ ከሞቀ ውሀ እንደ ገባ ጨው ፍርክስክስ አርጓቸው ነፈሰ-ገዳዩንና ከሀዲውን ለገሰን እንቃወማለን እሚሉት ሁሉ የቦንድ ካድሬ ሆነው ቁጭ አሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ ሕዝብ እንደ ጫካ ሲጨፈጨፍ ድምፃቸው ተሰምቶ እማይታወቅ ተሽኮርማሚ ዲዳዎች በጥሑፍና በራዲዮ ቦንድ፤ ታሐድሶ፤ ህዳሴ በሚሉት ቃላት አፋቸውን ፈቱ፡፡ ስንቶቹ ከንቱ ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች ከስማቸው ዳር ፒኤች ዲ፣ ኤም ዲ ወዘተርፈ እሚሉ ማእረጎች እያስቀመጡ ድጓ እሚያካክል ዝባዝንኪ እየጣፉ አንባቢን አባተሉ፡፡ ስንቶች አቀንቃኞች “ህዳሴ፣ ራዕይ፣ ታድሶ፣ ልማት” እያሉ መስክ ግጦ እንደ ጠገበ አለሌ አክላሉ፡፡ ስንቶቹ ዘፋኞች ሙሴ የተሻገረውን ባህር የሸጠውን ለገሰን “ባህር አሻጋሪው ሙሴ!” እያሉ በሌለ ባህር አፋቸውን እንደ ሰማይ ከፍተው ተሕዝብ፣ ተእግዚአብሔር፣ ተህሊና፣ ተእውነትና ተታሪክም እስከ መጨረሳው ተቀያየሙ፡፡ ስንቶች ከርሳሞች የለገሰን ቦንድ ለመግዛት እንደ ቡችላ ጅራታቸውን ወትፈው ተንጦሎጠሉ፡፡
ይህ ብዕራቸውን እንደ ሰሃራ ያደርቁለት፣ አፋቸውን እንደሰማይ የከፈቱለት፣ እንደ አሳላፊ ወገባቸውን የሰበሩለት፣ እንደ ቡችላም የተንጦለጦሉለት የቦንድ ገንዘብ ለነፍሰ-ገዳዮች ቅንጦት ሲውል ለምን ብሎ የሚጠይቅ የመለስ ቦንድ “ምሁር”፣ ካድሬ ወይም ቦንድ ከፋይ ቡችላ የት አለ? ሕግና ሥርዓት በሌለበት አገር ልማትም ሆነ ቦንድ የማይሰራ መሆኑን ተረድቶ ጸጸቱን በአደባባይ የገለጠ ቦንድ ሰባኪ “ምሁር” የት ይገኛል?
ይኸንን እያየን ለገሰ በቅዠቱ እሚመራው የነፍሰ-ገዳዮችና የዘራፊዎች ቡድን ላገር ያስባል፣ ለግድያና ለዘረፋ የዘረፈውን ሥልጣን በምርጫ፣ በእርቅና በሽምግልና ይመልሳል እያልን እንደ አህያ ጅራት ተመንዘላዘል የተቆጠብን ስንቶቻችን ነን? የአባ የሻነው ትል ተስድስት ልምዶች ስድስት ትምህርቶች ስትቀስም እኛ በወልቃይት አማሮች የተጀመረው መታረድ በደኖን፣ አርባ ጉጉን፣ ጉራፈርዳንና መተከልን ጎብኝቶ ጎንደርና ባህርዳርን ካዳረሰበት አርባ ዓመታት ልምዶች ስንት ትምህርት ቀሰምን? የአባ የሻነው ትል በሰባት ሙከራዎች ሰባት መንገዶችን ስትሞክር እኛ በአርባ ዓመታት ውስጥ ስንት መንገዶችን ፈትሸናል? “የህዳሴ ግድብ፣ የከተማና ገጠር ልማት፣ የብሔሮችና የሲኖዶስ እርቅ፣ አገራዊ ወይም ኤፍሬም ይሳቃዊ ሽምግልና” በሚሉ የለገሰ የጫት ጅንጀናዎች እየተሽኮረመምን ስንት ተጨማሪ ዓርባ አመታት ተመሳሳይ መንገድ ልንከተል አስበናል? እስከ መቼስ ከትል ያነስን ቦንደኞች ልንሆን ተረግመናል?
ዓባይን ማን መቼ ይገድበው? http://www.zehabesha.com/amharic/wp-con ... 6/Abay.pdf
ሐምሌ ሁለት ሺህ ዘጠኝ ዓ.ም.