ኩሽ በእብራይስጥ ኢትዮጲያ በግሪክ አንድ ነው

Current political, socio-economic and human rights issues.

Moderators: ዘበኛ ፩, ዘበኛ ፫, ዘበኛ ፪, ዘበኛ ፬

ኩሽ በእብራይስጥ ኢትዮጲያ በግሪክ አንድ ነው

Postby እሰፋ ማሩ » Sat Dec 09, 2017 1:43 am

ኩሽ በእብራይስጥ ኢትዮጲያ በግሪክ አንድ ነው
ኩሽ በእብራይስጥ ኢትዮጲያ በግሪክ አንድ ነው በማለት ዶር ጌታቸው ያቀረቡት ምንም የሚጨመርበት የለም፡፡ሆኖም ግን በታሪክ ኢትዮጲያ ተብላ የተከበረች ሃገራችንን ለማዋረድ የእብራዊያኑን ኩሽ እንጠቀም የሚሉት ውስጣቸው በክፋት የተሞላ የጎሳ ልክፍት የያዛቸው ናቸው፡፡ሃገሪቱን የገዙት እስከወያኔ ድረስ የህዝቦቹን መብት ያላከበሩ ቢሆንም ኢትዮጲያ ተብሎ የምንታወቅበት ስማችን ለነበረው ግፍ ተጠያቂ ሊሆን አይገባም፡፡ኩሽም ሆነ ኢትዮጲያ ማለት በእብራይስጥና በግሪክ ለጥቁር ህዝቦች የተሰጠ ስም ሲሆን ቀዳሚ የጥቁሮች ሃገር ኢትዮጲያ የሚለውን ስም ይዛ መቀጠሏ በጎ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ወይስ ኩሽ
ጌታቸው ኃይሌ
አንድ ሰሞን “የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በሪቨረንድ በንቲ ቴሶ ኡጁሉ ተጽዕኖ የኢትዮጵያን
ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰርዛ በኩሽ ለውጣዋለች” የሚል ወሬ ተናፍሶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ
ክርስቲያን ምእመናንን አበሳጭቶ ነበር። ብዙ ተቃውሞም ተጽፏል። ይኼ ተጨማሪ ማብራሪያ ነው።
ከመጀመሪያው ለመነሣት፥ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው ቅድመ ክርስቶስ፥ ሁለተኛው ድኅረ ክርስቶስ
የተጻፉ ባለ ሁለት ክፍል ነው። የመጀመሪያው ክፍል ብሉይ ኪዳን ይባላል። ይህንን ክፍል በቋንቋቸው
በዕብራይስጥ ጽፈው የሰጡን አይሁድ ናቸው። ሁለተኛው ክፍል ሐዲስ ኪዳን ይባላል። የተጻፈው
በጽርእ (በግሪክ ቋንቋ) ነው። በግሪክኛ ጽፈው የሰጡን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ናቸው።
ብሉይ ኪዳን በመሠረቱ የአይሁድ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ግን የክርስትና ሃይማኖት በብሉይ ኪዳን ላይ
ስለተመሠረተ ፈላጊዎቹ እጅግ ብዙ ሆኑ። የአይሁድ ሃይማኖትም ምን እንደሆነ ለማወቅ ፈላጊው ስለበዛ፥
የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን የግብፁ ግሪካዊ ገዢ (በጥሊሞስ ፊላዴልፎስ (285-246 ቅድመ ክርስቶስ) ሰባ
(ሁለት) ሊቃናት ሰብስቦ ወደዓለም አቀፉ ቋንቋ ወደግሪክኛ አስተረጐመው። (ሕፃኑን ኢየሱስን በቤተ
መቅደስ ያቀፈው ሽማግሌው ስምዖን ከሰባ ሊቃናት አንዱ ነበር የሚል ተአምር በእኛ ዘንድ ይነገራል።)
አሁን እንግዲህ፥ ሐዲሱም ብሉዩም በግሪክ ቋንቋ ሊነበብ ቻለ። የግዕዙ መጽሐፍ ቅዱስ የተተረጐመው
ከዚህ ከግሪኩ ቅጂ ነው። አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ፥ “ኢትዮጵያ ብሉይ ኪዳኗን የተረጐመችው በቀጥታ
ከዕብራይስጡ ነው” ይላሉ። ማስረጃቸው አርኪ አይደለም።
እነዚህ ሰባ (ሁለት) ሊቃናት ሲተረጉሙ፥ ዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ውስጥ የሀገርና የሕዝብ ስም
ሲያጋጥማቸው አንዳንዱን ዕብራይስጡ ውስጥ እንዳለው ይወስዱታል። አንዳንዱን፥ ለምሳሌ እንደ
“ኹሽ” እንደ “ፍልስጥኤም” ያሉ ስሞችን እንዳለ በመውሰድ ፈንታ፥ የግሪክ ተመሳሳይ ስም ይሰጡታል።
(ፍልስጤምን “ኢሎፍሊ”፥ ኩሽን “ኤይቲኦፕ” አሏቸው።) የዕብራይስጡ “ኩሽ” የሚያመለክተው
ጥቁርን ሕዝብ ነው። ግሪኮች ደግሞ ጥቁሩን ሕዝብ የሚጠሩት “ኤይቲኦፕ” ብለው ስለሆነ፥ “ኩሽ”
የሚለውን ስም “ኤይቲኦፕ” ቢሉት አይገርምም። ባጭሩ፥ ግሪኩ “ኤይቲኦፕ” የሚላቸው ዕብራይስጡ
“ኩሽ” የሚላቸውን ሕዝቦች ነው። “ስልቻ” እና “ቀንቀሎ” እንደማለት ነው፤ ሁለቱ ቃላት በምን
ይለያያሉ? እኛ ደግም፥ ከላይ እንደተናገርኩት፥ መጽሐፍ ቅዱሳችንን የተረጐምነው ከግሪኩ ስለሆነ፥
“ኤይቲኦፕ” የሚለውን “ኢትዮጵያ” አልነው። ከዕብራይስጡ ተርጕመነው ቢሆን ኖሮ ምናልባት “ኩሽ”
(ኩሳ) እንለው ነበር። “አለቀ ደቀቀ። ፓስቶሩ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የዛሬ ስድሳ ሁለት ዓመት
ባሳተሙት በግዕዝ መዝገበ ቃላታቸው ውስጥ “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም እንዴት እንደተቹት ቢያይ
ኢትዮጵያና ኩሽ ትርጕማቸው አንድ ሆኖ የሚያመለክቱት ኢትዮጵያንና ሱዳንን መሆኑን
እንደምናስተምር ይረዳ ነበር።
ጥያቄው መሆን ያለበት “የግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ ‘ኢትዮጵያ’፥ የዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን ‘ኩሽ’
የሚሉት ስሞች የሚያመለክቱት እነማንን ነው?” የሚል ነበር። መልሱ ቀላል ሆኖ ሳለ አስቸጋሪ
እናደርገዋለን። አንደኛ፥ እነዚህ ስሞች የሚያመለክቱት ጥቁሩን ሕዝብ ነው ብለናል። ሁለተኛ፥ በዓለም
ላይ ብዙ ጥቁር ሕዝቦች ቢኖሩም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ደራስያን የሚያውቋቸው ጥቁር ሕዝቦች በቅርባቸው
ያሉትን ኖባን (ሱዳኖችን) እና ኢትዮጵያውያንን ነው። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ አንድ ጥቁር
ሰው ከተነገረ፥ ያ ሰው ወይ ኢትዮጵያዊ ወይም ኖባዊ (ሱዳናዊ) ነው። ባጭሩ፥ ለግሪክ ደራሲዎች
“ኢትዮጵያ” የሚለው ስም የሱዳኖችና የኢትዮጵያውያን መጠሪያ ነበር። ኢትዮጵያን ያላንዳች ማስረጃ
ለኢትዮጵያ ብቻ ወይም ለሱዳን ብቻ መስጠት ስሕተት ነው። በዚያው አስተሳሰብ፥ ለዕብራይስጥ
ደራሲዎች “ኩሽ” የሚለው ስም የሱዳኖችና የኢትዮጵያውያን መጠሪያ ነበር። ኩሽን ያላንዳች ማስረጃ
ለኢትዮጵያ ብቻ ወይም ለሱዳን ብቻ መስጠት ስሕተት ነው።
“የጀርመን ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን በሪቨረንድ በንቲ ቴሶ ኡጁሉ ተጽዕኖ የኢትዮጵያን ስም
ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰርዛ በኩሽ ለውጣዋለች የሚለው ወሬ ውሸት ነው። ውሸቱ እንዲፈጠር
ያደረገው መርጋ ዮናስ ሪቨረንድ በንቲ ቴሶ ኡጁሉን አነጋግሮ ያወጣው ጽሑፍ ነው። መርጋ ጽሑፉን
ሲጀምር “An Oromo pastor has taken up the mantle by translating or changing biblical words deemed
erroneous” (አንድ የኦሮሞ ፓስተር [በንቲ ቴሶ ኡጁሉ] የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላትን በመተርጐም ወይም
ስሕተት የመሰሉትን በመለወጥ [የማርቲን ሉተርን] አጽፍ አነሣ) ይለዋል። ነገሥት ለተከታያቸው አልጋ
እንደሚያወርሱ ነቢያት ለተከታያቸው አጽፍ ያወርሳሉ--ኤልያስ አጽፉን ለኤልሳ እንዳወረሰው። መርጋ
ሪቨረንድ በንቲን እንዲህ ሲሸነግለው ሪቨረንዱም አላስተባበለም። በመቀጠል፥ “Among the most notable
changes or corrections in the new bible is the term Ethiopia, which was changed to Cush. Rev. Benti
Ujulu Tesso is one of the scholars behind some of the latest changes.” (እመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዋናዎቹ
ለውጦች ወይም እርማት መካከል ያስፈለገው ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ነበር፤ ወደ ኩሽ ተለውጧል።
ሪቨረንድ ኡጁሉ ቴሶ ከለውጡ በስተጀርባ ካሉት ምሁራን አንዱ ነው) ይላል። በለውጡ ብንስማማም
ባንስማማም፥ አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር የጀርመንን ሊቃውንት አማከረ ሲባል ማንም ኢትዮጵያዊ ሊኮራ
ይገባዋል። ግን የጀርመን ሊቃውንት ብሉዩን ከዕብራይስጥ፥ ሐዲሱን ከጽርዕ (ከግሪክ) ወደጀርመን ቋንቋ
ሲተረጕሙ እንደ በንቲ ያለ አንድ ሰሞነኛ ካህን አማከራቸው ማለት የሚያስቅ ነው። ምክንያቱም፥
ከመርጋ ጽሑፍ እንዳገኘነው፥ በንቲ የአንድ የወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን ምእመናንን በክህነት እያገለገለ
ገና የዶክትሬቱን ድርሰት ይጽፍ የነበረ ሰው ነው። ለመመረቂያ የሚጽፈውም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ
ሳይሆን፥ ግሪክኛና ዕብራይስጥ ማወቅ በማያስፈልገው “ሰማይ አምላክ ነው” በሚለው በኦሮሞ ቅድመ
ክርስትና ሃይማኖት ላይ ነበር። (“Oromo Indigenous Religion and Oromo Christianity: Contradiction and
Compatible.”)
ጀርመኖች ማርቲን ሉተር መጽሐፍ ቅዱሱን ወደጀርመንኛ እስኪተረጕምላቸው ድረስ የሚጠቀሙት
በላቲኑ ቅጂ ነበር። የተረጐመውም ሐዲሱን ከግሪክኛ ብሉዩን ከዕብራይስጥ ነበር። በንቲ ስለጀርመንኛ
መጽሐፍ ቅዱስ ብዙም ስለማያውቅ ማርቲን ሉተር የተረጐመው ከላቲን ነው ይላል። የጀርመን ቤተ
ክርስቲያን አሁን ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሷን እንደገና ለ2017 ዓ. እ. እንዲደርስ አድርጋ ተርጕማለች።
የትርጐማው ግብረ ኀይል ሊቀመንበር፥ ፕሮፌሰር ዶክተር ክሪስቶፍ ኬለር (Professor Dr. Christoph
Kähler, Bishop Emeritus) በጽሑፍ እንደገለጠው፥ ጀርመኖቹ መጽሐፍ ቅዱሳቸውን ትርጐማ ሲከልሱ፥
ሪቨረንድ በንቲ እንኳን የማርቲን ሉተርን አጽፍ ተጐናጽፎ በትርጐማ ሊሳተፍ ቀርቶ፥ አጠገባቸውም
እንኳን አልነበረም።
ሁለተኛውና ዋናው ውሸት “ኢትዮጵያ” የሚለውን ስም ፓስቶር በንቲ በ “ኩሽ” አስለወጣቸው ማለቱ
ነው። የጀርመን መጽሐፍ ቅዱስ ዱሮውንም “ኢትዮጵያ” የሚል ስም አልነበረበትም። ያልነበረ
አይለወጥም። የነበረውና አሁን ወደ “ኩሽ” የተቀየረው Mohrenland/Mohren ነው። ታዲያ ሌሎቻችንስ
ብንሆን የቀድሞው Mohrenland/Mohren ሳያስቆጣን ወደ Cush/Cushite ቢለወጥ ምኑ ነው የሚስቆጣን?
Mohrenland/Mohren እንዳለ ቢቆይ እንመርጥ ነበር ማለት ነው? እንዲያውስ እኛ እጀርመን መጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ እስከዛሬ ሳንገባ ዛሬ ምን አስገባን? ጀርመኖቹ Cush/Cushite ን የመረጡት Mohrenland/Mohren
ስድብ ስለሆነ የጥንቱን ስም ብንይዝ ይሻላል ብለው ነው። ወይስ ምን ምክንያት ሰጥተን
Mohrenland/Mohrenን ወደ Cush/Cushite መለወጣችሁን ትታችሁ ወደ ኢትዮጵያ ለውጡ እንበላቸው።
መቈጣት ካስፈለገ፥ Cush/ Cushite ያለውን የዕብራይስጡን ብሉይ ኪዳን ነው።
“ፈረንጆች ስማችንን ለወጡብን፤ የአንድን አገር ስም መለወጥ የሚችል የሀገሬው ሕዝብ እንጂ ፈረንጅ
አይደለም” የሚል ቁጣ ይሰማል። የሀገር ስም መለወጥና ለአንድ ስም አዲስ ትርጕም ማምጣት የተለያየ
ነገር ነው። የሀገራችንን ስም ማንም አለወጠውም። ሁለት አንድ ነገር ቢሆኑ ኖሮ THE GIDEONS
የሚባሉት ፕሮቴስታንቶች በእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱሳቸው ውስጥ ኢትዮጵያ የሚለውን ወደ Cush
ከለወጡበት ጊዜ ጀምሮ ኩሽ እንባል ነበር። ግን አልተባልንም። አንድም ፈረንጅ “ይድረስ ለኩሽ
መንግሥት ፕሬዚዴን . . .” ብሎ ሲጽፍም አላየንም። ቢልም ፖስተኛው አያደርስለትም።
ሆኖም አንድ ጥያቄ ማንሣት እንችላለን፤ ዕብራይስጡ ብሉይ ኪዳን “የካም ልጆች ኩሽ፥ ሚስራይም፥
ፉጥ፥ ክናዐን ናቸው” ይላል። ይኸንን ዐረፍተ ነገር አዲሱን የጀርመን ትርጕም አዘጋጆች ምን ብለው
ተረጐሙት? ስሞቹን እንዳለ ገልብጠዋቸዋል ወይስ “ምስራይም” የሚለውን ስም Ägypten (Egypt ግብፅ)
ብለውታል? “ምስራይም” የሚለውን ስም እንዳለ መገልበጣቸውን ትተው እንደ ግሪኩ Ägypten ብለውት
ከሆነ (ባላየውም እንዳሉት አልጠራጠርም)፥ ለምንድን ነው “ኩሽ” የሚለውን ስም እንደግሪኩ Äthiopien
(Ethiopia ኢትዮጵያ) ያላሉት?
መርጋ “ሌላ ምን ለውጥ ተደርጓል?” ብሎ ሪቨረንድ በንቲን ቢጠይቀው፥ “ሌላውን አሁን ልነግርህ
አልችልም” አለው። እውነቱን ነው፤ የማያውቀውን፥ ያልዋለበትን እንዴት ሊነግረው ይችላል?
ሦስተኛ፥ “ኢትዮጵያ የሚለው ስም ስድብ ነው” ይላል ፓስቶሩ፥ ኦሮሞ የሚለው ስም ስድብ ነው
እንደተባለው ማለት ነው። “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ስድብ ከሆነ፥ “ኩሽ” የሚለው ስም እንዴት ስድብ
አይሆንም? እንደእውነቱ ከሆነ፥ “ኢትዮጵያ”ም ሆነ “ኩሽ” የኛ ስም ከሆነ ቅዱስ ስም ነው። አንዳን ሰዎች
የሚሉትማ ሌላ ነው፤ ኩሽ የኖኅ እርግማን ስላረፈበት እርጉም ነው ይላሉ። ስድብ ማለት ይህ ነው። ኖኅ
ሦስት ልጆች ነበሩት፤ ሴም፥ ካም፥ ያፌት። ጥፋተኛው ካም አራት ልጆች ወለደ፤ ኩሽ (ኩሳ)፣
ምስራይም (ግብፅ)፥ ፉጥ፥ ከነዓን። ቢጐዳም ባይጐዳም፥ የተረገመው ከነዓን ነው። ሌሎቹ
አልተረገሙም።
አራተኛ፥ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ወደ ኩሽ ቢለወጥ ፥ “ኢትዮጵያ” የሚለው ስም ያገለላቸውን “ኩሽ”
የሚባሉትን ኦሮሞችን ሲዳሞችን፥ . . . ያቅፋል ይላል።ይኸ አስተሳሰብ “አባቶቻቸው ከጣና ባሕር የመጡ
ወንድማማቾች ናቸው” ከሚለው ተረት ይሻላል። ግን ሁሉም አለማወቅ ያመጣብን ስሕተት ነው። አገር
ቤት ሄደን አንዱን የኦሮሞ ወይም የሲዳማ ገበሬ፥ “ደስ ይበልህ፤ ኢትዮጵያዊ መባልህ ቀርቶ ኩሳዊ
ተብለሃል” ብንለው፥ እብዶች ያደርገናል እንጂ በደስታ ጮቤ አይመታም። ዕውቀቱ ካለው፥ “ኩሽ”
መባል የሚወድ ሕዝብ “ኢትዮጵያ” ቢባል አይጠላም?
የቋንቋ ተመራማሪዎች “ሴማዊ፥ ኩሻዊ” የሚሏቸው ቋንቋዎች አሉ። ይህ አከፋፈል የተመሠረተው
በቋንቁዎቹ ላይ እንጂ፥ በተናጋሪዎቹ ዘር ላይ አይደለም። የሁለቱም ዘራቸው አንድ ነው። በቋንቋ
“ሴማዊ” እና፥ “ኩሻዊ”፥ በዘር “ኢትዮጵያ” እና “ኩሽ” የሚያመለክቱት ያንኑ አንዱን ሕዝብ ነው።
“ኩሽ የሚለው ስም በይበልጥ ያቀራርበናል” ማለት ኢትዮጵያን አንቀበልም ለሚሉ ወገኖች የተፈጠረ
ፖለቲካዊ አስተዋፅኦ ነው--የሃይማኖት አስተማሪን ሳይቀር የተተናኰለ በሽታ።
አምስተኛ፥ የሀገሪቱ ስም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ Abyssinia ነበር፤ ወደ ኢትዮጵያ የተለወጠው አሁን
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ነው ይላል ፓስቶሩ። አለማወቅ ካልቀረ እንደዚህ ነው። በየትኛው ዘመን ነው
ኢትዮጵያ ራሷን በእንግሊዝኛ Abyssinia ትል የነበረው? የትኛው ንጉሥ ነው “እኔ እገሌ ንጉሠ ነገሥት
ዘብሔረ Abyssinia” ያለ? ከ1307 እስከ 1336 ዓ.ም. በነገሠው በአፄ ዓምደ ጽዮን እንኳ ብንጀምር፥ ራሱን
የሚጠራው “ንጉሠ ጽዮን፥ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ” እያለ ነበር። የውጭ አገር ጸሐፊዎች አገራችንን
Abyssinia ይሏት ነበረ። በእኛ በኩል ግን አገራችን መንግሥት ከሆነችበት ጊዜ ጀምሮ ያለው ሰነድ
የሚያመለክተው ኢትዮጵያ መባሏን ነው። ሰነዶቹ ሜዳው ሁሉ ናቸው። አነጋግሯቸው
አታኵርፏቸው።
ስድስተኛ፥ ሐበሻ ማለት ድብልቅ ማለት ነው ይላል። ከየትኛው መዝገበ ቃላት ነው እንዲህ ያለ ትርጕም
የሚገኘው? ወይስ ዐዋቂ መስሎ የተራ ሰው አነጋገር ከሰው ፊት ማቅረቡ ነው? ሐበሻ የነገድ ስም ነበረ።
የነገድ ስም ስድብ ሊሆን አይችልም። ሁለተኛም አንድ ሀገር በአንድ ነገድ ስም መጠራት በኢትዮጵያ
አልተጀመረም።
ለማጠቃለል፤ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ከመተዋወቃችን በፊት ጀምሮ ሀገራችንን የምንጠራው “ኢትዮጵያ”
ብለን ነው። በሌላ ስም ትጠራ ማለት ተንኮል ነው። ስማችንንም፥ መጽሐፍ ቅዱሳችንን አናስነካም።
ሆኖም፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጐማ አይቆምም፤ ይቀጥላል። ወደፊትም ብዙ ዛሬ ያልታወቁ የግሪክና
የዕብራይስጥ ቃላት በምርምር ብዛት ይታወቃሉ፤ አዲስ ትርጐማን ያስገድዳሉ። ተቀባዩ ቋንቋም
ያረጃል፤ በዛሬው ሰዎች ቋንቋ የተተረጐመ መጽሐፍ ቅዱስ ለነገ ሰዎች እንግዳ ይሆንባቸዋል። የመጽሐፍ
ቅዱስ ማኅበር የሚቋቋመው እነዚህ ምክንያቶች አዲስ ትርጐማ ሲያስገድዱ ተዘጋጅቶ ለመገኘት ነው።
እሰፋ ማሩ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1504
Joined: Mon Sep 12, 2016 8:47 pm

Return to Warka Politics - ዋርካ ፖለቲካ

Who is online

Users browsing this forum: Bing [Bot] and 7 guests