የዘመናችን ሲኖድ የቱን ይመስላል?

Issues and Articles of General Interests including topics related to religion

የዘመናችን ሲኖድ የቱን ይመስላል?

Postby እሰፋ ማሩ » Sun Dec 17, 2017 4:49 am

የዘመናችን ሲኖድ የቱን ይመስላል?
December 16, 2017
የዘመናችን ሲኖድ የቱን ይመስላል?

(ጥቅምት ሰባት ቀን 2010 ዓ.ም. ለተሰየመው ዓመታዊ ሲኖዶስ አባ ፋኑኤል ባቀረቡት የእግዳ አቤቱታ፤ ሲኖዶሱ ያሳለፈው የእገዳ ውሳኔ ባስነሳው ውዥንብር ምክንያት ለዋሸንግተን ዲሲ ህዝበ ክርስቲያን የቀረበ ነው።)

በዚህ ዘመን ያለው ሲኖድ (ሸንጎ)የቱን ይመስላል? የዮቶርን ሸንጎ? የአርዮስፋጎስን ሸንጎ? ወይስ የክርስቲያኖችን የቱን ይመስላል?

ይህንን ጥያቄ የፈጠረብኝ በጥቅምቱ ሲኖዶ ስብሰባ ላይ በተከሰተው ውዥንብር እንዴት ትመለከቱታላችሁ? በሚል ከህዝብ የቀረበ ጥያቄ ነው። በመጀመሪያ በዚህ ቅዱስ ስብሰባ ላይ ተሳሳቱ የተባሉ ወገኖች የሚታገዱበት የመነጋገሪያ አጀንዳ በሀራ ዘተዋህዶ ድረ ገጽ ተሰራጭቶ ተመለከትን። ቀጠለና አዲስ ተክል አባ ፋኑኤል በገንዘብ በገዙት ጵጵስና ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ሰርገው ገብተው በየደረሱበት ህዝብ በማተራመስ ላይ እንዳሉ ከፓትርያርኩ አንደበት ተሰማ። በወቅቱ የቀረበውን ለመረዳት ከፈለጉ በቀይ ቀለም የተጻፈችውን ዓዲስ ተክል የምትለዋን ይጫኑ።

በአባ ፋኑዔል ጵጵስና ላይ የሲኖዶሱ ሰብሳቤ የሰጡት ምስክርነት ውሳኔ አግኝቶ አባ ፋኑዔል ወደ መላኩነታቸው ተመልሰው በቀራፊነት እንዲሰማሩ ይታወጃል ብየ በጉጉት ስጠብቅ፤ አባ ፋኑኤል በገንዘብ በገዙት ጵጵስና በአባልነት እንዳሉ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአቡነ ማትያስ እየተመራ ጉባዔውን ቀጠለ። ቀራፊ ምን እንደሆነ ከዚህ ቀደም ያቀረብኩት ስልሆነ ማወቅ የፈለገ ይህችን ቀራፊ የምትለውን ቃል ተጭኖ በማንበብ ሊረዳ ይችላል።

ራሳቸው ፓትርያርኩ በመሩት አባ መላኩ በተሳተፉበት ሲኖድ፣ በአባ መላኩ ላይ ፓትርያርኩ ያረቡት “የጵጵስና ግዥ” ተከድኖና ተሸፍኖ፤ በገዙት ጵጵስና ህዝብ በማተራመስ ላይ ያሉት አባ ፋኑኤል በሌላ ሰው ላይ ይታገዱልኝ ብለው ለሲኖዶስ ክስ ማቅረባቸው ተሰማ። ሲኖዶሱ አባ ፋኑኤል ያቀረቡትን የክስ ሰነድ አይቶ ክስ የቀረበበት ግለሰብ ከኦርቶዶክሱ አተረጓጎም አፈንግጧል በማለት ያገደበት ውሳኔም ተሰራጨ።

ጵጵስናን በገንዘብ መግዛት ይቅርና ለመግዛትም ሆነ ለመሸጥ የሚያስብ ሰው በቅድስና ቅጽል በሚጠራው ሲኖዶስ ውስጥ መኖሩን ለመቀበል ለክርስቲያኖች እጅግ ከበደ ነው። ሲኖዶሱ በሻጮችና በገዥዎች ከተያዘ ሸጦና ገዝቶ ለመክበር ከማሰብ አልፎ በምን አቅሙና ቅድስናው ስለ ነገረ መለኮት ተረድቶና ተጨንቆ ሌላውን ሊከስና ሊያግድ ቻለ?የሚል ንግግር በህዝበ ክርስቲያኑ መካከል ተጧጧፈ።

ከፊደል እስከ ከፍተኛው ያብነት ትምህርት ያስተማሩን ሊቃውንት አበው እንደነገሩንና እያየን እንዳደግነውም፤ በየመንደሩ በየአደባባዩ የነበሩ ሸንጎዎች ይህን የመሳሰሉ አስጨናቂ ችግሮች በህዝብ መካከል ሲከሰቱ ምን ያደርጉ ነበር ? በማለት እኔም ከትዝታየ ጋራ መታገሌን ጀመርኩ።

የምክር የተግሳጽና የጥበብ መዝገብ እያሉ የቅኔ መምህራን ይናገሩለት የነበረው ዮቶር በትዝታየ መጣብኝ። አባቶቻችንና እናቶቻችን ችግር ሲፈቱባቸው የነበሩት የጽዋዕ፣ የሰንበቴ ማህበራት የመሳሰሉት ሸንጎዎች፤ በሌሎች አገሮች የነበሩት እንደ አርዮስፋጎስ፤ እንደ ሲኖድና የመሳሰሉት የክርስቲያኖች ሸንጎዎች ከፊቴ ተደረደሩ። ለኛ ከሚቀርበን ከዮቶር ሸንጎ ጀምሬ ተመሳሳይ ሸንጎዎችን ዳስሼ በዘመናችን ያለው ሲኖዶስ ምን እንደሚመስል በግሌ ለማየት ሞከርኩ። በሙከራየ ህሊናየ የዋኘባቸውን በዘመናችን ያለውን ሸንጎ እንድታዘብ ያደረጉኝን ሸንጎዎች ከዚህ በታች አቀርባቸዋለሁ።

1ኛ፦የዮቶር ሸንጎ

2ኛ፦ አርዮስፋጎስና ሲኖድ

3ኛ፦የመጀመሪያ ክርስቲያኖች ሸንጎ

4ኛ፦በአገራችን ያለው ሸንጎ

5ኛ፦ኧረ ለመሆኑ ነገረ መለኮት ምንድነው?

ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት አበው የዮቶርን ሸንጎ ለነጻነት እንደምሳሌ ስለሚጠቅሱት ለኛ ይቀርበናልና በኢትዮጵያዊው ዮቶር በሚባለው ሸንጎ እጀምራለሁ።

1. የዮቶር ሸንጎ

የኢትዮጵያ ሊቃውንት የዮቶርን ሸንጎ ለብዙ ምሳሌዎች ይጠቅሱታል። የዮቶር ሸንጎ በሙሴ አማካይነት እስራዔላውያንን ከመሪር አገዛዝ ነጻ እንዳወጣበት፤ እነ መላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬም የዮቶርን ዘዴ በመጠቀም በነ በላይ ዘለቀ አማካይነት ኢትዮጵያን ከጣሊያን ነጻ እንዳወጡበት መምህሮቻችን በቅኔያቸው ነግረውናል። በስፋት መረዳት ከፈለጉ የመላከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ የዓምስቱ ዘመን ተጋድሎ በሚል ርእስ የተጻፈውን ጦማር ተጭነው ይመልከቱ።

ሙሴ የሸንጎ ጥበብ ጎድሎት በተቸገረ ጊዜ፤ ሙሴ በሚከተለው አመራር እስራኤላውያንን ከተጫነባቸው መራራ አገዛዝ ነጻ ሊያወጣቸው እንደማይችል ዮቶር ተመልክተ። ዮቶር ለሙሴ የሰጠውን ምክር ተግሳጽና ጥበብ ከዚህ በታች የሰፈረውን ከራሱ ከሙሴ መጽሀፍ እየጠቀሱ መምህሮቻችን አስተምረውናል። ሙሴ ሆይ? “የምታደርገው ነገር መልካም አይደለም። ይህ ነገር ይከብድብሀልና አንተ ከአንተም ጋራ ያለው ህዝብ ትደክማላችሁ፤ አንተ ብቻህን ልታደርገው አትችልም። አሁንም እመክርሀለሁ። ቃሌን ስማ። እግዚያብሔር ካንተ ጋራ ይሆናል። አንተ በእግዚያብሔር ፊት ለህዝቡ ሁን። ነገራቸውንም ወደ እግዚያብሔር አድርስ። ስርIኣቱን ህጉን አስተማራቸው። የሚሄዱበትን መንገድ የሚያደርጉትን ስራ ሁሉ አሳያቸው። ከህዝብ ሁሉ አዋቂዎችን እግዚያብሔርን የሚፈሩትን የታመኑ የግፍንም ረብ የሚጠሉትን ሰዎች ምረጥ . . . . . ይህን ብታደርግ እግዚያብሔር እንዲሁ ቢያዝህ መቆም ይቻልሀል። ደግሞም ይህ ህዝብ ሁሉ በሰላም ወደ ስፍራው ይደርሳል“(ዘጸ 18፡17᎗23)እያለ እንደመከረውና የነጻነት ማውጫ መንገዱን እንዳሳየው፤ በጎሳ፣ በጎጥ፣ በዘር፣ በቋንቋና በሃይማኖት እየከፋፈለ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከውስጥና ከውጭ የሚነሱትን ወራሪወች ሁሉ፤ አርበኞች አባቶቻችን በዮቶር መርሆ ሲገስጹበትና ሲያሳፍሩበት እንደነበር ስለዘላለማዊው ነጻነታችን ያስተማሩን የኢትዮጵያ ሊቃውንት ነግረውናል።

ኢትዮጵያውያን አባቶቻችንና እናቶቻችን በሙሴ በተሰየመው በ12 ሀዋርያትና በ12 አዕዋደ ወርህ በ12 ሰዓተ መአልት ልክ በጽዋዕ ማህበራትና በሰንበቴ በመደራጀት በየመንደሩ የገጠማቸውን ችግር ሲፈቱበት፤ እንደወያኔ ሰብሮ ገብ ወራሪ እያስፈነጠሩ ሲጥሉባቸው የኖሩባቸው የጽዋዕና የሰንበቴ ሸንጎዎች ከኢትዮጵያዊው ከዮቶር እንደ ፈለቁ ያብነቱ መምህራን አስተምረውናል። ኢትዮጵያ በገረቤቶቿ አገሮች ከደረሰባቸው ቅኝ አገዛዝ ተጠብቃ ታፍራና ተከብራ የኖረችው በዮቶራዊው ባህሏና ሸንጎዎቿ እንደሆነ ከኛ መምህራን ብቻ ሳይሆኑ በተሳተፍንባቸው ኮሌጆችና የንቨርስቲዎች መምህሮቻችን ሰምተናል። ጥንታዊት ኢትዮጵያ ስትጠበቅባቸው የነበሩት እነዚህ ሸንጎዎች፤ ግሪካውያንን የመሳሰሉ ጥንታውያን አቻዎቿ ይጠቀሙባቸው ከነበሩት ሸንጎዎች አርዮስፋጎስንና ሲኖድ ከሚባሉት ጋራ እንደሚመሳሰሉ ያብነቱ መምህራን ነግረውናል። ከዚህ ቀጥለን እንመልከታቸው።

2ኛ. አርዮስፋጎስና ሲኖድ

አርዮስፋጎስ የሚባለው ሸንጎ በግሪክ ህዝብ መካከል ግጭት ሲፈጠር የግጭቱን ምክንያት እያጠና ችግሩን በመፍታትና ትውልዱን በሞራል እያነጸ የሚያሳድግ የዮቶርን ሸንጎ የሚመስል የጥንታውያን ግሪኮች ሸንጎ ነበር።

ይህ ሸንጎ ከውጭ ሰርገው የሚገቡትን አዳዲስ ነገሮች ከነበረው የኑሮ ዘይቤ ጋራ እያነጻጸረ ጎጅ የሆኑ ነገሮች በዜጎች መካከል ገብተው በመለያየትና በመከፋፈል ወደ ብጥብጥ እንዳይመሩ እያረመ ጠቃሚ ጠቃሚውን እያለማና ከነበረው ጋራ እያዋሀደ ህዝቡን ወደተሻለ ህይወት የሚመራ ባለቅኔዎችና ጠበብቶች የሚሰበሰቡበት የኛን የጽዋዕ ማኅበር የሚመስል የግሪኮች የሸንጎ ነበር። (የሐዋ 17፡18-28)።

ሲኖድ የሚባለውም ”journeying together” coming from two Greek words (syn hodos) that mean “with (someone) and road” ተብሎ እንደ ተተረጎመው፤ ግሪኮች ከክርስትና በፊት ችግር ከሚፈቱባቸው ሸንጎዎች አንዱ ነበር። ይህም ማለት ከጽውዕ ማህበራችን ጋራ ጎን ለጎን ከሚካሄደው ሰንበቴያችን ተመሳሳይ ብቃት ችሎታ ያላቸው በተመሳሳይ መንገድ ለተመሳሳይ አላማ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ ሸንጎ ነበር።

ግሪኮች እምነታቸውችንና አኗኗራቸውን ወደ ክርስትና ሲያዞሩ በክርስቲያናዊ ህይወታቸው ለሚገጥማቸው ችግር መፍቻ አድርገው እስካሁን ይጠቀሙበታል። ዓለም አቀፋዊ ሆኖ የጥንት አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ተቀባብለውታል። ከጵጵስናው ጋር በግብጽ በኩል ወደኛም ተሻግሯል። የጫነብንን ሸክምና ያተረፈልንን ጥቅም፤ በቦታው ለማየት ከዚህ ላይ አቆይተን፤ ወደ መጀመሪያ ክርስቲያኖች ሸንጎ እንሻገር።

3ኛ. የመጀመሪያ ክርስቲያኖች

ዛሬ የኛ ቤተ ክርስቲያን የገጠሟትን የመሰሉ ችግሮች የመጀመሪያ ክርስቲያኖችን ገጥመዋቸው ነበር። የመጀመሪያ ክርስቲያኖች በቁጥር እየበዙ ሲሄዱ በመካላቸው ማህበራዊ ችግር ተፈጠረ። የተፈጠረውም ችግር፤ በይሁዳ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ከግሪክ በመጡ ሰዎች ላይ የጫኑት የተዛባ የአመራር በደል ነበር። ሐዋርያት ችግሩን መፍታት የሚችሉበትን የሞራልና የጥበብ ሰዎችን የሰበሰበ ሸንጎ ፈጠሩ። (የሐዋ 6፡1᎗ፍ)።

ሸንጎውን ከፈጠሩ በኋላ “የእግዚአብሔርን ቃል ትተን ማዕድ አገልጋዮች አይደለንም” በማለት የራሳቸውን አቋም ጭምር የገለጹበት ሸንጎ ነበር። ይህ የሐዋርያት ሸንጎ ሙሴ እስራዔላውያንን ከባርነት ነጻ ካወጣበት ከዮቶር የሸንጎ ዘይቤ ጋራ የሚመሳሰል ነው።

በሌላ ወቅት በጥንቆላ ንግድ የከበረ ሲሞን የሚባል ሰው መንፈሳዊውን ጸጋ በገንዘብ ገዝቶ የበለጠ ንብረት ለማካበት ፈልጎ ሽጡልኝ ብሎ ወደ ሐዋርያት ቀረበ። የሀዋርያትን ጉባዔ ይመራ የነበረው ጴጥሮስ “የእግዚአብሄርን ስጦታ በገንዘብ ለመግዛት አስበሀልና አንተም ገንዘብህም አብራችሁ ጥፉ” (የሐው 8፡20)ብሎ አሰናበተው። ፓትርያርኩና ሲኖዶሱ ይህን ምሳሌ በመከተል ተባብረው አባ ፋኑኤልን፤ ጵጵስናውን በብር ገዝተህ የከበርክ፤ ከብረህም የማትጠግብ ነህና ከፊታችን ጥፋ አለማለታቸው፤ ከፊደል እስከ ዓብነቱ ጉባዔ ትምህርት ቤት ያለፍነውን ምን ያህል እንዳስጨነቀን መገመት የሚያቅተው ያለ አይመስለኝም።

እነዚሁ የመጀመሪያ ክርስቲያኖች ሀዋርያት ለሁለተኛ ጊዜም ሌላ ማህበራዊ ችግር ተፈጥሮ ያደረጉት ሸንጎ ነበረ። ለዚህ ሸንጎ የቀረበው ችግርና የፈቱት መንገድ ከመጀመሪያው የተለየ ነበረ። የመጀመሪያው የምጣኔ ሀብት መዛባት ሲሆን በዚህኛው ሸንጎ የፈቱት ችግር ግን በስነ ልቡናና በባህል ልዩነት የተፈጠረ ውዝግብ ነበር።

ለዚህ ስብሰባ ምክንያት ከሆነው ህዝባዊ ችግር ይልቅ፤ ህዝቡን ከከፋ ችግር ላይ የሚጥል ፋታ ሊሰጠው የማይገባ የበለጠ ነገር ታያቸው። “ለጣዖት ከተሰዋ ከደም ከታነቀም ከዝሙት ትርቁ ዘንድ ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናል። ከዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ”(የሐዋ 15፡29)። ብለው ወሰኑ።

ሐዋርያት ውሳኔያቸውን የደመደሙት “ከዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ” በማለት ነበር። ከላይ የተመለከትናቸው የሸንጎ ዓይነቶች በወቅታውያን ህዝባውያን ችግሮች ላይ ያተኮሩ ከዚያም ራቅ በማለት ለህዝቡ ያልተከሰተውን ችግር አስቀድመው በማያት እየፈቱና “ከዚህ ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ” እያሉ ህብረተሰቡ የከበበውን ሁሉ ችግር እያየ እንዲጠነቀቅ በማሳሰብ ወሰኑ። “ሰላም ነው! ሰላም ነው!” የሚለው የዘመኑ የዱርዬወች ቃል በህዝባችን ህሊና ከመስረጹ በፊት “ጤና ይስጥልኝ” የሚለው የመገናኛና የመሸኛ ቋንቋችን ከመጀመሪያዎች ክርስቲያኖች ሸንጎ እንደተወረሰ መምህራን ይናገራሉ።

ከአርዮስፋጎስ ጀምረን ሲኖድና የመጀመሪያ ክርስቲያኖች ሸንጎዎች በሀገራችንም በሙሴ ስም የተመስረቱት የጽዋዕ ማህበራት ይሰሩት የነበሩትን ያብነቱ መምህራን አባቶቻችን ከነገሩን በጥቂቱ ተረድተናል። አሁን ደግሞ በዘመናችን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚካሄዱትን የሸንጎ አካሄዶች ቀጥለን እንመልከት።

4ኛ፦በአገራችን ያለው ሸንጎ

በዚህ ዘመን በአገራችን ያለው ሲኖድ ከላይ ከዘረዘርኳቸው ጥንታውያን ሸንጎዎች በላቀ እውቀትና ጥበብ ከውጭና ከውስጥ የሚፈጠረውን ችግር የሚፈታ እንዲሆን ይጠበቅ ነበር። ይህ ሳይሆን ቀርቶ መነጋገሪያ አጀንዳውና ውሳኔው ከህብ የራቀ እንዲያውም ጭራሽ በኢትዮጵያ ምድር የሌለ ከፈረንጅና ከዓርብ አገሮች ካሉ ሰዎች የሚመነጭ ይመስላል።

የችግሩ ፈጣሪና ችግሩ የታወቀ ሲሆን፤ ሲኖዶሱ ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚነጋገረውንና የሚለዋወጠውን የጥሪ ድምጽ እንኳ መስማት ከማይማይችልበት በሩቅ የሚኖር ይመስላል። “ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ” እንደሚባለው፤ ከችግሩ ፈጣሪ አንዱ የነበሩት ወንድማችን ዶክተር አረጋዊ በርሄ እንደነገሩን የችግሩ ፈጣሪ “የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር” ሲሆን ችግሩም ይኸው ወያኔ የሚያፈልቀው እንደሆነም እንዲህ ሲሉ አርድተውናል።

“የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጭ ግንባር በ1979 ዓመተ ምህረት አስተሳሰብ ለዋጭ የፕሮፓጋንዳ መርኃ ግብር ለሚመለምላቸው ቀሳውስት ዘረጋ። የማሰልጠኑ ዓላማ ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብና በትግሬአዊነት ላይ ብቻ የተመሰረተ ስሜት በትግራይ ተወላጆች ጭንቅላት መክተት ነው። ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትተቀርጸው የኖረችውን ብሄራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በጠባቡ ትግሬአዊነት ስሜት በመተካት የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት ነው። የወረዳ ስልጠና የተጀመረው በጠንካራ ትግሉ የታወቀው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በነገረ መለኮት ትምህርት የተመረቀው ገብረ ኪዳን ደስታ ነው። የስልጠናውም ይዘት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጠቅላላ መዋቅራዊ አስተዳደር በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባለሟሎች መተካትና በቤተ ክርስቲያኒቱ አካባቢ የትግርኛ ቋንቋ እንዲሰፍን ማድረግ ነው”

ወንድማችን አረጋዊ እንደነገሩን የችግሩ ፈጣሪ ወያኔ” ቤተ ክርስቲያኗ ለረዥም ዘመናት በህዝቡ አዕምሮ ላይ ስትቀርጸው የኖረችውን ብሔራዊ የኢትዮጵያነትን ስሜት ከትግራይ ህዝብ አዕምሮ ጠራርጎ በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባለሟሎች መተካትና በቤተ ክርስቲያኒቱ አካባቢ የትግርኛ ቋንቋ እንዲሰፍን ማድረግ ነው” ብሎ የዘረጋውን ተግባራዊ ለማድረግ ለ26 ዓመታት በመታገል ላይ እንዳለ ችግሩን የተሸከመው የኢትዮጵያ ህዝብ ይቅርና ዓለም ተረድቶታል።

”የቤተ ክርስቲያኒቱን ይዘት እያጠበቡ ራሷን ቤተ ክርስቲያኒቱን መምታት” መሆኑን አረጋዊ እንደገለጹት በዘርና በዲኖሚኔሽን ጥላቻ የሰከሩ ወያኔዎች ትግራይን ከተቆጣጠሩ በኋላ የራሷን ህዝብ ለማጥፋት ቤተ ክርስቲያናችንን ለበጎ ነገር ስትጠቀምባቸው የነበሩትን እንደ ጽዋዕና ሰንበቴ የመሳሰሉትን ሸንጎዎች መልካቸውን በመለወጥ ለጥፋቱ መሳሪያ አድርጓቸዋል። በየጠረፉና በመሀል አገር የሚኖረውን ዜጋ እየደመሰሱ መሬቱን ንብረቱን መንደሩን ለመዝረፍ እንዲያመቻቸው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ለረዥም ዘመናት በመላ ኢትዮጵያውያን ስትቀርጸው የኖረችውን ኢትዮጵያዊነትን ከሁሉም ጭንቅላት ጠራርገው ለማውጣት ያላቸውን ሁሉ ኃይል ተጠቅመዋል።

“በትግራይ ነጻ አውጭ ድርጅት ባለሟሎች መተካት” እንዳሉትና በቅርቡም እንደተገለጸው፤ ኢትዮጵያ የቆመችባቸውን አዕማድ ተቋማት ሲደመሰሱ ማየት የማይፈልጉትን ዜጎች እየመነጠሩ በማጥፋት፤ በቤተ ክህነቱ ካሉት ከ16 መመሪያዎች 14ቱን መምሪያወች ከማጥፋት ወደ ኋላ በማይሉትን ራሳቸው ባሰለጠኗቸው ሰዎች ሞልተዋቸዋል።

ዶክተር አረጋዊ “ቤተ ክርስቲያኗን ከህዝብ ለይቶ በመምታት ስፋቷን ማጥበብ” እንዳሉትም ከዋልባ ገዳም ጀምሮ አድባራቱ ገዳማቱ ከመጥፋታቸው ነዋየ ቅድሳቶቻቸው ከመበዝበዛቸው ባሻገር ከ8 ሚሊዮን በላይ ክርስቲያኖች የት እንደደረሱ እንዳልታወቀ በራሳቸው በፓትርያርኩ አንደበት ሲነገር ተሰማ። በጠፉት ክርስቲያኖች ህይወት ተጠያቂ መሆን የሚገባው ኦርቶዶክስንና አማራውን ሰበርነው ካሉት ከአቶ ስብሀት ነጋ ሌላ ሰው እንዳለ ፈልጎ ማግኘት ከሲኖዶሱ የተሻለ ሸንጎ ባላስፈለገ ነበር። ይህም በፓትርያርኩ የተሰጠው ምስክርነት ራሱን ሲኖዶሱን ከህዝብ ህሊና አውጥቶ ጥሎታል።

ወያኔ መሬት ይቅርና ያላቸውን ሁሉ ንብረት እየተካፈሉ በኖሩት ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ በቋንቋና በድንበር ተከልለው እርስ በርሳቸው እንደ ባእድ እንዲተያዩ የሚያደርግ መርሆ በህዝብ ላይ ከጫነና ድንበር ተሻግሮ የኢትዮጵያን ጭንቅላት ከነከሰ በኋላ፤ ራሱ ያወጣውን የክልል ህግ ጥሶ ራሱን በፌድራል ስም ሰይሞ መላ ኢትዮጵያን ተቆጣጠረ። በጎረቤት አዋሳኝ በጎንደር በወሎ በጎጃም የሚኖሩትን ዜጎች እያፈናቀለ መሬቱን ለባእድ ቸረቸረ። ተቃቅፎና ተደጋግፎ የመኖርን መንፈስ ከሰፊው ኦሮሞና አማራው ህዝብ ጭንቅላት ጠራርጎ ካወጣ በኋላ፤ መሬቱን ለራሱ ደጋፊዎች ሰጠ። በጽሁፋቸው ባንደበታቸው የሚቃወሙትን ማሰር ማሳደድ መግደል ጀመረ። ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያናችን ከህዝቡ ጎን በመሰለፍ ድንበር ሲፈርስ በሚል በቀረበው መልእከት ወያኔን መገሰጽ የሚገባው ሲኖድ ራሱን ከህዝቡ አገለለ። ራሱን ከህዝብ ማግለል ብቻ አይደለም፤ እንዲያውም ከወያኔ ጋራ በመወገኑ ስርየት የሌለው በደል በህዝብ ላይ ፈጸመ። ሲኖዶስ ወያኔን ባይመስል ይህን ሁሉ ደባ በመላ ዜጎች ላይ ሲፈጸም የሚከተለው ምሳሌ ነበረው። ሀናንያ መሬቱን ለባእድ ከሸጠ በኋላ፤ የሽያጩን ገንዘብ ከራሱ ህሊናና ከህዝብ ደብቆ በሸፍጥ በመቅረቡ የክርስቲያኖች ሸንጎ መሪ ቅዱስ ጴጥሮስ “ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለምን ሞላ ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥከውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለምን በልብህ አሰብክ እግዚአብሔርን እንጅ ሰውን አልዋሸህም” (የሐዋ 5፡3-6)። ብሎ በሀናንያ ላይ የመንፈስ ቅዱስን እሳትነትን ለብሶና ጎርሶ እንደ ተነሳበት፤ ሲኖዶሱም በወያኔ ላይ ይነሳበት ነበር። በዚህ ወቅት ይህ ሲኖዶስ የሚከተለው ምሳሌና መመሪያው ምንድነው? በማለት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሰዎች አነጋግሯል፤ አሁንም እየተነጋገረ ነው።

ሀናንያ የሸጠው የራሱን መሬት ነው፤ እንደወያኔዎች የሰው ድንበር ጥሶ ነጥቆ ለባእድ አልሸጠም። ሀናንያ መሬታችንን ነጠቀን በላያችን ለባእድ ሸጠብን መንደራችን በላያችን አፈረሰብን ብሎ የከሰሰው የለም። ለመሆኑ የትኛው ይከፋል የራሱን መሬት ሸጦ የሸጠበትን ገንዘብ የደበቀውን ሀናንያ? ወይስ መሬታችንን ነጠቀን ለባእድም ሸጠብን፤ መንደራችን በላያችን አፈረሰብን እየተባለ የሚከሰሰው የወያኔ በደል ይከፋል?

“ዘምሉእ ጥውእየተ ወስፍጠተ ወዛቲ ስፍጠት ዘረሰየቶ ለአዳም ይትመየጥ ውስተ መሬት። ወባህቱ ዘያሜክር ጎየ ርኍቀ ተሀፊሮ ወተመዊዖ ሶበ ቀርበ ሀበ አምላክነ ወሀቤ ሲሳይ ለኩሉ ዘሥራ ”(ሃይ ምእ 87፡35) ማለትም፦ “አዳምን ወደ መሬትነት የመለሰውን የህሊና ጥመትና ሸፍጥ የመከረውና አመራር የሰጠው ዲያብሎስ አፍሮና ግንባሩን ተመቶ ወደቀ፤ “እያሉ እነ ቅዱስ ሳዊሮስ የመንፈስ ቅዱስን እሳትነት ለብሰውና ጎርሰው ያሰሙትን የቤተ ክርስቲያናችንን ድምጽ ይህ ሲኖድ ለምን አፈነው?

በተቃራኒው ወያኔ በልማት ስም የቀረጸውን ማታለያና ማዘናጊያ ዘዴ ሲኖዶሱ ተቀብሎ በተደጋጋሚ በሚያደርገው አደንቋሪ ጩኸት፤ ክርስቶስ በተራበ ጊዜ ድንጋዩን ዳቦ ነው ብሎ ሰይጣን ለክርስቶስ ካቀረበለት ፈተና ይልቅ፤ ወያኔ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እጅግ የከበደ ፈተና ሆኖበታል። ሲኖዶሱ ወያኔ በህዝቡ ላይ የሚጭነውን ፈተና ባለመቃወሙ። ይልቁንም በመደገፉ ትዝብትና ንቀት ተጸይፎ ከሚመለከተው ሲኖዶ የሚሰነዝረውን እግዳም ሆነ ውግዘት ሊቀበል ቀርቶ በራሱ በሲኖዶሱ የነበረውን ታማኝነትና ተቀባይነት ከመሬት ጥሎታል። ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ጀምሮ 26 ዓመት ሙሉ በገደለው ባስገደለውና እርስ በርስ ባገዳደለው በወገን እሬሳ ዙሪያ ዘመድ ወዳጅ የልቅሶ ምሾ እያወረደ በሚያለቅስበት ወቅት፤ ወያኔ “ስብር ስብር ስብር አረጋት እንጅ………አሸበል ገዳየ” እያሉ የሙሽራ ዘፈን እየዘፈነና ህዝቡንም በማስገደድ እያዘፈነ ነው።

ህዝባችን በዚህ ሁኔታ ላይ እያለ፤ ከሲኖዶስ ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን አገልጋይ ነኝ የሚል ሁሉ የሰላምና የመረጋጋት እንቅልፍ እንዴት ሊኖረን ይችላል? አንዳንዶቻችን ቀደሞ በሽምግልና በሩቅ ልምዳቸው ለጥቂት አረጋውያን የሚሰጠውን ቁምስና ተላብሰን፤ ብዙዎቻችን ደግሞ ባልዋልንበት ባልደከምንበት ብዙ ዘመን ባላሳለፍንበት ነገረ መለኮት ውስጥ እየገባን፤ የሂንዱ፤ የሮማን ካቶሊክ፤ አንዳንዶቻችሁ ደግሞ የጀሆቫና የየሱስ ብቻ የእስልምናውን ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ጋራ እየቀላቀልን የነገረ መለኮት ተቆርቋሪ ጠባቂና አስጠባቂ መስለን፤ ግማሾቻችን አፍራሽ መስለን በምንፈጥረው ጫጫታ በወያኔ ዱላ በመደብደብ ላይ ያለው ህዝብ የሚያሰማውን ዋይታ እያፈንበት መሆናችንን ማን በነገረን?

5ኛ. ኧረ ለመሆኑ ነገረ መለኮት ምንድ ነው?

“ንግበር ሰብአ በአርያነ ወበአምሳሊነ”(ዘፍ 1፡26)ብሎ ወዶና አክብሮ በአርአያው ከፈጠረው ከሰው በላይ የላቀ በዚህች ምድር ላይ ለመለኮት ሌላ ምን ነገር አለው?። “ርኢኩ ሥቃዮሙ ለህዝብየ። ወሰማእኩ ዘአውአየቶሙ እምነዳእተ ገባር ወወረድኩ ከመ አድህኖሙ” (ዘጽ 3፡7)ማለትም፦ የህዝቤን ስቃይ አየሁ። ከሚያስጨንቋቸውም ሰዎች በሚደርስባቸው መከራና ግፍ የሚያሰሙትን ዋይታ ሰማሁ ለመታደግም ወረድኩ” ከሚያሰኘው በመላ ኢትዮጵያውያን ላየ እየተፈጸመ ካለው የከፋ ለመለኮት ምን ነገር አለው?

በህዝቡ ሁለንተና ችግር ሳይሳተፍ ራሱን ደብቆ፤ በነገረ መለኮት እያሰበበ ከህዝቡ ጩኸት የተለየና ባእድ ድምጽ የሚያሰማ፤ በወያኔ እጽፍ ድርብ መሪር አገዛዝ ህዝብ የሚያሰማውን ጩኸትና ዋይታ እንዳይሰማ ለማፈን የተቀነባበረ የወያኔ ነገረ ሸፍጥ መሆኑን የሚስተው ይኖራል ብሎ የሚገምት ካለ እንስሳ ይመስለኛል።

ህዝባችን ወያኔዎች በሚፈጽምብን መከራ የምናሰማውን ዋይታችንን ለቅሷችንን ለፈጣሪ አድርሱልን ለዓለም አሰሙልን እያለ በሚጠይቅበት በዚህ ወቅት ፤ ወያኔ አዳዳሲ መከራ እየፈጠረ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በላይ በላይ ማሸከሙን እንዳይቀጥል መታገል፤ አምላክ የመከራውን ዘመን እንዲያሳጥርልን ተግቶ መጸለይና ዓለምም ከኢትዮጵያ ህዝብ ጎን እንዲቆም የህዝቡን ድምጽ ማሰማት ሲገባ፤ ግማሾቻችን ለክርስቶስ አምላክነት ለእመቤታችን ቅድስና ጠበቃና ተቆርቋሪ በመምሰል፤ ግማሾቻችን ደግሞ ከኦርቶዶክሱ ያተረጓጎም ስልት አፈንጋጭ እየመሰልን በምንፈጥረው ጫጫታ ወያኔ በህዝቡ ላይ የሚፈጽመውን በደል እንዲቀጥል እየረዳነው ነን። ህዝቡም ግማሹ እየተሰደደ በየደረሰበት እንዲታረድ ለባርነት ሽያጭም እንዲዳረግ ተባብረናል ። በአገር የቀረው ህዝብ ዘርም ሳይተካ በማነኛውም መንገድ ኢትዮጵያ የምትባል አገር መክና እንድትጠፋ ከሚየደርገው ወያኔ ጋራ ተሰልፈናል።

ህዝብ ይህን በመሰለ ክፉ ሁኔታ ላይ ሳለ፤ እንደ አባ ፋኑኤል ጠልቃችሁ ላልተረዳችሁት ነገረ መለኮት ጠበቃና ተቆርቋር መስላችሁ፤ ግማሾቻችሁ ደግሞ በነገረ መለኮት ቅናትና ክብር ካባ ፋኑዔል ይልቅ በተቃጠለ መንፈስ ላይ መሆናችንን ለህዝብ ለማሳየት በመቃተት ላይ ያላችሁ፤ የቀረነው ያባትህ ቤት ሲበዘበዝ አብረህ በዝብዝ በሚል መመሪያችን እኛ ምናገባን በማለት በዝምታና በገለልተኝነት ማለፍ ነው የምንል፤ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ነገረ ወያኔን በመፈጸምና በማስፈጸም ከነገረ መለኮቱ ጋራ በመጋጨት ላይ መሆናችንን ልንረዳ ይገባናል። ከጠረፍ እስከ ጠረፍ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተባብሮና ተቆጥቶ ከዳር እስከዳር በወያኔ ላይ ሲነሳ፤ እኛም ከህዝብ ጋራ ተባብረን ወያኔን እንደበድባለን የምትሉም፤ የምትከተሉት የሰይጣን ሸፍጥ እንጅ ነገረ መለኮት፤ ነገረ ማርያም ነገረ ሐዋርያትና ነገረ ሊቃውንት አይደለም።

ነገረ መለኮት “ሶስት ቀናት ሳይበሉ የዋሉ ያደሩ ሰወች ወደፊትም የሚበሉት ስለሌላቸው አዝንላቸዋለሁ። ጦማቸውን ላሰናብታቸው አልወድም” (ማቴ15፡32)። እያለ ክርስቶስን እንዲናገር ያደረገው የህዝብ ችግር ነው።

የማርያም ነገር፦እነ ቅዱስ ዮሀንስ “ከመ ትኩን መራሂተ ለሃይማኖት ዐባይ”(66፡32) እያሉ የነገሩን አምላክን በድንግልና ጸንሳ በድንግልና በመውለዷ ብቻ አልነበረም። ስለ ህዝብ የነበራትን ጭንቅ “ገዥዎችን ከዙፋናቸው አውርዷቸዋል። ትሁታንን ከፍ ከፍ አድርጓቸዋል። የተራቡትን በበጎ ነገር አጥግቧቸዋል። ሀብታሞችን ግን ባዷቸውን ሰዷቸዋል”(ሉቃ 1፡52)እያለች በመናገር ለህዝብ በሰጠችው ክብር ነው።

የሐዋርያት ነገርም የመጀመሪያ ክርስቲያኖች ሸንጎ በሚለው አንቀጽ ከላይ እንዳየነው ህዝባውያን የሆኑትን ችግሮችን የፈቱበት የህዝብ ነገር ነው።

የሊቃውንቱ ነገርም፦“ኮነ አምላክ ሰብአ ወአንሶሰወ መእከለ ሰብእ ግፉዕ፤ ምስለ ግፉዐን ወዘንተ ኩሎ ገብረ ከመ ያድህኖሙ ጼዉዋነ ወይኩን ረዳዔተ ለእለ አልቦሙ ረድኤተ”(114፡20) ። እያሉ ርዳታ ተነፈጎት በመቃተት ላይ ካለ ህዝብ ጋራ መቆም ነው።

የክርስቶስም፤ የማርያምም፤ የሐዋርያትና የሊቃውንቱም ነገር “ወለኩሉ ዘአለወ ወተቃረነ ንባበ መንፈሳዌ ወተግህሰ እምነ ጽድቅ ውስተ ኩሉ መካን ሀበ ሀለወ ወለኩሎሙ ከሀድያን ወሰብእ እኩያን ወህጉላን እለ አልቦሙ ሃይማኖት ወዘዐለው ሃይማኖተነ ወእለ ሴሙ ላዕሌሆሙ መገብተ ከሀድያነ ንኴንኖሙ በግዘት በኩሉ መዋዕል” (102፡ 23)ሲል ሊቁ በተናገረው ይደመደማል። ይህም ማለት፦ “ነገረ መለኮትን፤ ነገረ ማርያምን፤ ነገረ ሐዋርያትንና ነገረ ሊቃውንትን የሚቃረን ከእውነት የራቀ ነው። በዚህ ላይ እውቀትና እምነት የሌላቸውና አስመሳይ ባህርይ ያላቸውን በህዝበ ክርስቲያን ላይ የሰየመ የተወገዘ ይሁን” ማለት ነው። ይህ የጥንታዊት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያናችን መመሪያ ነው።

ታዲያ መመሪያችን ክርስቶስን ካስጨነቀው፤ ማርያምን ካስጨነቃት ሀዋርያትን ካሳሰባቸውና ቅድሚያ ከሰጡት፤ ሊቃውንትም ይህን የሚቃረን ይባረር አትቀበሉት ካሉ፤ የተቀደሰውን ሁሉ ያለ ቦታውና ያለ ወቅቱ እያመጡ በህዝብ ላይ በመድፋት የህዝቡን ድምጽ የሚያፍኑትን ጳጳስ፣ ቄስ፣ ቆሞስና ሰባኪ ብሎ እንዴት መቀበል ይችላል?እነ አባ ፋኑኤልን የመሳሰሉ ሰዎች ያቀረቡለትን እየተቀበለ አገድኩ አወገዝኩ የሚለውን ሲኖድ ከላይ ከጠቀስኳቸው ሸንጎዎች በየትኛው እንመስለው? ይህን ስል ህዝብ መከራው ከብዶት በገነፈለባቸው ወቅቶች ሁሉ ከሲኖድ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያችን የተሰማራን የምናደርገውን አፈና በተደጋጋሚ ስላየሁት፤ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ ወያኔ በሚፈጥረው አፋኝ ሸፍጡ እንዳንተባበር ለማሳሰብ እንጅ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ይህንንም አትተው”(ማቴ ፡ ) እንዳለው ስለምናምነው እምነት እንድንመሰክር ከተጠየቅን፤ ምን አገባን በማለት እንለፈው ማለቴ አይደለም። ሰውናታችንን አክብሮና ወዶ በአርአያው የፈጠረን አምላክ ዓይነ ልቡናችንን ያብራልን!

ቀሲስ አስተርአየ ጽጌ nigatuasteraye@gmail.com

ታህሳስ 7 ቀን 2010 ዓ.ም.
እሰፋ ማሩ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1526
Joined: Mon Sep 12, 2016 8:47 pm

Return to Warka General

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 3 guests