ሞት ያልረታው የሃይማኖት መስራች

Issues and Articles of General Interests including topics related to religion

ሞት ያልረታው የሃይማኖት መስራች

Postby እሰፋ ማሩ » Fri Apr 06, 2018 11:58 am

ሞት ያላሸነፈው ብቸኛ የሃይማኖት መስራች ኢሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡
በመስቀል ላይ እንደ ብራና ተወጥሮ ተሰቅሎ፣ በደዌ ብዛቶ ደቆ የምታዩት ማን ነው? ለምንስ ተሰቀለ? ( ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
April 6, 2018 – በቆንጅት ስጦታው
ይህ እንዲህ በመስቀል ላይ እንደ ብራና ተወጥሮ ተሰቅሎ፣ በደዌ ብዛቶ ደቆ የምታዩት ማን ነው? ለምንስ ተሰቀለ?
እንኳን አደረሰን!!!
ይህ በአይሁድ ሐሰተኛ ክስ ያልተገባ የግፍ ፍርድ ተፈርዶበት ከመጽሐፍ ቅዱሱ ባሻገርም በወቅቱ የነበሩት የታሪክ ጸሐፍት እንደገለጹት ሌሊቱን ሙሉ በፈርጣማና ጨካኝ የጲላጦስ ወታደሮች ፊቱን በባልጩት ሲጸፋ፣ 6666 (ስድስት ሽህ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት) ጊዜ ብረት በተታታበት በባለስለታማ ጉጥ ጅራፍ ተገርፎ ሥጋው እላዩ ላይ ተበጣጥቆ አልቆ አጥንቱ እየታየ፣ አጥንቱን ዘልቆ የሚገባ የብረት እሾህ የተታታበት የእሾህ አክሊል እራሱ ላይ ጭነው ከዚህ ሁሉ አሰቃቂ መከራ በኋላ ደግሞ ደግሞ ለአንድ ሰው የማይቻለውን መስቀሉን አሸክመው እየወደቀ እየተነሣ ቀራኒዮ አደባባይ ድረስ ካመጡት በኋላ ተሸክሞ ባመጣው መስቀል ላይ እጅ እና እግሩን ወጥረው ቸንክረው ሰቅለው፣ ተጠማሁ ቢላቸው ሐሞትና ከርቤ (ቆምጣኔ) በማጠጣት፣ ጎኑን በጦር ወግተው በዚህ ሁሉ መራራ መከራ ገለውት በመስቀሉ ላይ የምታዩት ስለ እኛ ወይም ስለ የሰው ልጆች በደል፣ ኃጢአት፣ መተላለፍ፣ መርገም ሥርየት ሲል የታረደው ሰማይና ምድርን ከነግሳንግሱ የፈጠረው እግዚአብሔር ከሦስቱ አካል አንዱ ወልደ እግዚአብሔር ነው፡፡ አማናዊው በግ ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ዮሐ. 1 ፤ 1-14, ማቴ. 16 ፤ 16, ዮሐ. 20 ፤ 28, ሐ.ሥ. 20 ፤ 28, ሮሜ. 9 ፤ 5, ቲቶ 2 ፤ 13, 2ኛ ጴጥ. 1 ፤ 1, ዕብ. 1፤8

ምነውሳ ሁሉን ቻይ ኃያል ሆኖ ሳለ አቅም እንደሌለው እንደተሸነፈ በገዛ ፍጡሩ ይሄንን ሁሉ ግፍና መከራ ተቀበለ? ቢባል፡፡ የመጣው ለዚሁ በመሆኑ ያለ ተቃውሞ ወዶና ፈቅዶ ተቀበለው ማቴ. 26 ፤ 51- 54 ፡፡ መከራውን ግፉን ለምን መቀበል አስፈለገው? ቢባል፦

1ኛ. በአካል ተገልጦ በመሀከላችን በመመላለስ የቅርብ አምላክ እንጅ የሩቅ አምላክ አለመሆኑን ለማሳየት፡፡ ሮሜ. 1 ፤ 14- 25, 1ኛ ዮሐ. 3 ፤ 1-10

2ኛ. ለእኛ ያለውን የፍቅር መጠን ለማሳየት፡፡ ዮሐ. 3 ፤ 16,1ኛ. ዮሐ. 4 ፤ 8-16

3ኛ. ትሕትናን፣ ፍቅርን፣ ትዕግሥትን፣ የጾም የጸሎት የተጋድሎ ምግባርን፣ ጽናትን እራሱ አድርጎ በማሳየት “እንዲሁ አድርጉ!” ብሎ ለእኛ ለሰው ልጆች ለማስተማር፡፡ “ቀንበሬን በላያቹህ ተሸከሙ ከእኔም ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና!” ማቴ. 11 ፤ 29, ” እኔ ለእናንተ እንዳደረኩ እናንተ ደግሞ ታደርጉ ዘንድ ምሳሌ ሰጥቻቹሀለሁና!” ዮሐ. 13 ፤ 15, “የተጠራቹህት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉት ምሳሌ ትቶላቹህ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሏልና!” 1ኛ ጴጥ. 2 ፤ 21, “አኔን መከተል የሚወድ ቢኖር እራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ!” ማቴ. 16 ፤ 24, ሉቃ. 9 ፤ 23

4ኛ. ከዲያብሎስ አገዛዝ ነጻ ሊያወጣን፣ መርገማችንን ሊደመስስልን የሚችለው የእሱ ደም ብቻ በመሆኑ፡፡ ኢሳ 53 ፤ 1 – 12, ዮሐ. 1 ፤ 29, ኤፌ. 2 ፤ 14 – 19

5ኛ. ቀድሞ በገነት ማንነቱን ደብቆ እራሱን በእባብ ሥጋ ሠውሮ እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረውን አዳምንና ሔዋንን ያሳተውን ሰይጣን ጥበቡን በጥበብ ለመሻር እራሱን በሰው ሥጋ ሰውሮ ከሰው ተወልዶ አምላክነቱን ደብቆ ሰይጣን ሲጠረጥር እየሰወረበት ሰዓቱ ሲደርስ በመስቀል ላይ እያለ ሰይጣን እንደለመደው ሰው ሲሞት እንደሚያደርገው ሥጋውን በመቃብር ነፍሱን በሲዖል ለመቆራኘት ሲጠቃ በነፋሳት ወጥሮ ይዞ ለ5500 ዓመታት ሲዖል ሲያግዛቸው የኖሩትን ነፍሳት ተረክቦታል፡፡

ይሄንንም በምሳሌ ተናግሯል ማቴ. 12 ፤ 29, ማር. 3 ፤ 27 , እግዚአብሔር እግዚአብሔር ነውና ሰው ሆኖ መሰቀል ሳያስፈልገው ይሄንን ማድረግ ይችል ነበረ ነገር ግን በኃይል ማድረግ ቢችልም እግዚአብሔር እግዚአብሔር በመሆኑ መበለጥ የለበትምና በለጥኩ ያለውን ሰይጣን በለጥኩ ባለበት ጥበቡ ድል መንሣት ስለነበረበት ነው ሰው በመሆን አምላክነቱን ሠውሮ ከሰው በመወለድ ዲያብሎስን ድል መንሳት ያስፈለገው፡፡ በእነኝህ ምክንያቶች ሰው ሆነ በመከራውም አዳነን፡፡

ጥያቄው እኛ ክርስቲያኖች ነን ስንል፣ “የተዋረደልኝን፣ የቆሰለልኝን፣ የሞተልኝንና ሞቶም ያዳነኝን ኢየሱስ ክርስቶስን እወዳለሁ!” ስንል እሱ “እንድታደርጉት ምሳሌውን ተውኩላቹህ!” ብሎ ከተቀበለው መከራ የትኛውን በመፈጸም ለእሱ ያለንን ፍቅር ገለጽን? እሱን ተከተልን? በመከራው መሰልነው? የጌታን መከራ በሚገባ ማሰብ እንድንችል፣ ስለኛ የከፈለውን ውድ ዋጋ እንድናውቅ እንድንረዳ ታስቦ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን የሁለት ወራት ጾም አውጃ ጌታ ያደረጋትን እያንዳንዷን ነገር በእያንዳንዷ ቀን በቅዳሴው፣ በሰዓታቱ፣ በማኅሌቱ፣ በስብከቱ ቀምራ፣ አሰካክታና አዘጋጅታ ከጥንት ጀምራ አቅርባ በየዓመቱ ሥርዓቱን ትፈጽማለች፡፡

ማለትም በየዕለቱ ሰባት የጸሎት ሰዓታት መድባ በሌሊቱ 9 ሰዓት የጌታን በአይሁድ ተይዞ ስለኛ ሥጋው ከላዩ ላይ አልቆ አጥንቱ እስኪቆጠር ድረስ የተገረፈውን 6666 የጭካኔ ግርፋቱን እያሰብን፡፡ በንጋቱ እንደዚያ ሲገረፍ ሲደበደብ አድሮ በደከመ ሰውነቱ በፍርድ አደባባይ ቆሞ ሰዓታት ማሳለፉን እያሰብን፡፡ በጠዋቱ 3 ሰዓት በጲላጦስ ፊት ለፍርድ መቆሙን፣ በግፍ ተላልፎ መሰጠቱን፣ ልብሱን ተገፎ ከለሜዳ መልበሱን፣ በማኅበራነ አይሁድ ከትንሽ እስከ ትልቅ ሲተፋበት መዋሉን እያሰብን፡፡ የቀትር 6 ሰዓት እጆቹና እግሮቹ በመስቀል ላይ ተቸንክረው ስለኛ ለተዋረደና መራራ ሞት መብቃቱን እያሰብን፡፡ የቀን 9 ሰዓት ነፍሱን ከሥጋው መለየቱን፣ ተጠማሁ ቢላቸው ይግደለው ብለው ሐሞትና ከርቤን ቀላቅለው በሰፍነግ እንዲጠጣው ማድረጋቸውን፣ ክብርት ነፍሱ ከቅዱስ ሥጋው መለየቷን፣ ጎኑን በጦር መወጋቱን እያሰብን፡፡ የሰርክ 11 ሰዓት አዳምንና ልጆቹን ለማዳን የማይሞተው ሞቶ በበፍታ ተገንዞ ወደ ሐዲስ መቃብር መውረዱን እያሰብን፡፡ የመኝታ 3 ሰዓት “ይህች ጽዋ ከኔ ትለፍ!” እያለ በሰውነቱ መከራን ተሰቅቆ ተጨንቆ መጸለዩን እያሰብን እንድንጸልይ እንድንሰግድ በማድረግ ቅድስት ቤተክርስቲያን ሥርዓት ሠርታ ጌታችንን አምላካችንን መድኃኒታችንን ኢየሱስ ክርስቶስስን እንዲህ በየሰዓቱ ትሰብካለች ታስባለች ትዘክራለች፡፡ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ነው ኢየሱስ ክርስቶስን የምትሰብከው የምታስተምረው የምታስበው በባዶና አስመሳይ የለበጣ ጩኸት አይደለም፡፡ የሚማር ካለ ከራሷ አልፋ ለሌላው ብዙ ታስተምራለች አርአያ ትሆናለች እንጅ ይሄ ቀረሽ ተብላ የምትነቀፍ የምትተች አይደለችም፡፡

በዓመት አንድ ጊዜ በሚመጣ ጾም ብቻ ሳይሆን የጌታ ሕማምና መከራ የሚታሰብባቸው የሚዘከርባቸው የዘወትር እሮብና ዓርብ ጾም ደንግጋም የጌታን መከራ ሕማምና መሥዋዕትነት እንድናስብና እንድንካፈል ታደርጋለች፡፡ ምን ያህሎቻችን ተጠቀምንበት? ለመሆኑስ ምን ያህሎቻችን ይሄንን ታላቅ ጾም ጾምን? ስንቶቻችን ነን ገና በመጀመሪያው ሳምንት ላይ ጌታ ለእኛ የከፈለውን ውድ ዋጋ ማሰብና ለዛም መታመን ተስኖን ጾሙን ያቋረጥነው? እንደ ጌታ አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ያለ ምንም ምግብና ውኃ መጾም ባንችል እንኳ ቢያንስ ግን መከራውን ለማሰብ በሚያስችለን ደረጃ ጥቂት እንኳ ድካምና ሕመም እስኪሰማን ድረስ ጾመን በመከራው እሱን ማሰባችንን፣ መምሰላችንን፣ መከተላችንን፣ መውደዳችንን ማረጋገጥ አልነበረብንም ወይ? ይሄንን ሳናደርግ ለማድረግም ጨርሶ ሳንፈቅድ “ኢየሱስ ክርስቶስን እንወዳለን! ለከፈለልኝም ውድ ዋጋ ክብርና ዋጋ እሰጣለሁ! በደሙ የተገዛሁ ውድ ልጁ ነኝ!” ብለን ብንመጻደቅ እራሳችንን ካልሆነ በቀር ልላ ማንን መሸንገል ማታለል እንችላለን? ፍቅራችንስ እውነተኛ ነው ወይ? ሆዳችን በልጦብን በጾም፣ በጸሎት፣ በሥግደት ለእግዚአብሔር መገዛት ያቃተን፣ ለጌታ ያለንን ፍቅርና መታመን ማረጋገጥ ያልቻልን ክርስቲያን ነኝ ባይ ወገኖች በእውነት ልናፍር ይገባል!፡፡

ክርስትና በአፍ ብቻ የሚወራ ድርሰት አይደለም! በሥራ የሚገለጥ ሕይዎት እንጅ፡፡ ክርስቲያኖች ነን እያልን ክርስትናውን የማንኖረው ከሆነ ሳያምኑ አምነናል ከሚሉት፣ መከራ የተቀበለላቸውን፣ የቆሰለላቸውን፣ የሞተላቸውን ክርስቶስን ሳይወዱት እንወደዋለን እንደሚሉትና ለዐመፃ ሥራቸውና ላለመታዘዛቸውም ድርጅታዊ ሽፋን አበጅተው ከላይ በጠቀስኳቸው ጥቅሶች ላይ ክርስቶስ ምሳሌነቱን እንድንከተል ደጋግሞ ያሳሰበውን ቃል አሽቀንጥረው ጥለው ክርስቶስ የመጣው የሰው ልጆችን ለኃጢአት ሥራ የተፈቱና እንደፈለጉ እንዲሆኑ ነጻ የተለቀቁ ለማድረግ የመጣ ይመስል “እኔ ጾሜላቹሀለሁ እናንተ አትጹሙ፣ እኔ ደክሜላቹሀለሁ እናንተ አትድከሙ፣ እኔ መከራን ተቀብየላቹሀለሁ እናንተ አትቀበሉ፣ እኔ ሕግን ፈጽሜላቹሀለሁ እናንተ አትፈጽሙ!…” እንዳለ አድርገው “በጸጋው ድነናል! እራስን በጾምና በተጋድሎ ማሰቃየት፣ መከራ መቀበል አያስፈልግም!” እያሉ ያልገባቸውን ቃል እየጠቀሱ ልቅነትን፣ መረንነትን፣ አልጫነትን፣ አለመታዘዝን፣ ዐመፃን እየሰበኩ እንደዚያም ሆነው ከሚኖሩት ቃሉ “ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው!” ሮሜ. 16 ፤ 15 -23, 2ኛ ቆሮ. 11 ፤ 13, 1ኛ ጢሞ. 4 ፤ 1 – 2, ዕብ. 13 ፤ 7 – 9 ከሚላቸው ከንቱዎች በምንም እንለያለን???

ሐዋርያት “አምናለሁ እምነት አለኝ!” የሚሉትን ነገር ግን ከጾም፣ ከጸሎት፣ ከሥግደት፣ ሕግጋቱን ከመጠበቅና ከመጋደል ውጭ የሆኑትን ሰዎች እምነታቸውም ሆነ እራሳቸውም ከንቱና የሞቱ እሬሳዎች እንደሆኑ አስተምረዋል ያዕ. 2 ፤ 14 ፤ 26 አምናለሁ የሚል ክርስቶስን በመከራው ይመስለው ዘንድ ግድ ነው “ሞቱን በሚመስል ሞት ከእርሱ ጋር ከተባበርን ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእርሱ ጋር እንተባበራለን!” ነውና የሚለው ቅዱስ ቃሉ ሮሜ. 6 ፤ 5 እግዚአብሔር በቅዱስ ቃሉ ከጥንት ጀምሮ እንድንጾም ሲያዘን የኖረው ከጾም የምናገኘው በርካታ ዓይነት ጥቅም ስላለ እንጅ እኛን ለመጉዳት፣ በእኛ ላይ ቀንበር ለመጫን አይደለም፡፡ ጾም ከእግዚአብሔር ምሕረትን ከማግኘት ጀምሮ ከአጋንንት ቁራኝነት እስከመላቀቅ ድረስ በርካታ ጥቅሞች አሉት፡፡ ዘጸ. 34 ፤ 28, ዕዝ. 8 ፤ 21-23, ኢሳ. 58 ፤ 1-12, ኤር. 14 ፤ 11-12, አስ. 4 ፤ 16, ዳን. 10 ፤ 2-3, ዘዳ. 9 ፤ 9-19, ዘሌ. 16 ፤ 29-31, ዘካ. 8 ፤ 19, አስ. 9 ፤ 31, 2ኛ. ሳሙ. 12 ፤ 22, መሳ. 20 ፤ 26, ኢዩ. 1 ፤ 14, ነህ. 1 ፤ 4, 1ኛ. ሳሙ. 7 ፤ 6, መዝ. 69 ፤ 10, ሉቃ. 2 ፤ 37, ሉቃ. 18 ፤ 12, ማቴ. 4 ፤ 2, ማቴ. 6 ፤ 16-18, ማቴ. 9 ፤ 14-17, ማር. 9 ፤ 29 ሐ.ሥ. 13 ፤ 2-3, 14 ፤23, 27 ፤ 9

ጾም ሃይማኖታዊ ግዴታችን ሆኖ እያለ ለዚህ ሃይማኖታዊ ግዴታ ጆሮ ባለመስጠት አገኘሁ ብለን ያለ ልጓም እንደፈለገን እየጠረግን ብንበላና ብንጠጣ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ልብ ድካም፣ እሪህ፣ ጉበት ወዘተረፈ. የሚባል ቅጣት ያመጣልና ቢያንስ ለጤናችን ስንል እንኳ ብንጾምስ? አለመታዘዛችን ለሌላም አደጋ ያጋልጠናል፡፡ እግዚአብሔር በነፍስ ብቻ ሳይሆን በሥጋም በቁጣው ይጠፋሉ፣ ለእርኩሰት ለድንቁርና ለጥፋትም አሳልፎ ይሰጣቸዋል፡፡ ሮሜ. 1 ፤ 16 – 25, ኢሳ. 1 ፤ 18 – 20 ይሄንን ታላቅ ጾም በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ የተለያየ ትሩፋት በመፈጸም ስናሳልፍ ለቆየነው መድኃኔዓለም ክርስቶስ እንደበደላችን ሳይሆን እንደቸርነቱ ጾም ጸሎት ስግደት ትሩፋቶቻችንን ተቀብሎልን የሀገር ጠንቆችን አጥፍቶ ሀገሩን ቀየውን ሰላምና ጥጋብ አድርጎ በምሕረቱ ይጎበኘን ዘንድ፣ የስደት የመከራውን ዘመን ያበቃልን ዘንድ ፈቃዱ ይሁንልን! ለምናከፍል ክርስቲያኖች ድካሙን፣ ሕመሙን፣ ስቃዩን ቀላል ወይም የምንችለው አድርጎ አስፈጽሞ ብርሃነ ትንሣኤውን ያሳየን! አክፍሎቱ በሚከብደን ጊዜ ጌታ ለእኛ ሲል የተቀበለውን መራራ መከራ ማሰቡ የጾሙን የአክፍሎቱን ሕመምና ስቃይ ለመቋቋም ይረዳልና ይሄንን እናድርግ!

እንግዲህ የቀራንዮው ንጉሥ የድንግል ልጅ መድኃኔዓለም ክርስቶስ በዚህ በመስቀል መራራ መከራ ላይ በነበረበት ሰዓት የአይሁድን ጥቃት ሳይፈራና ሳይሸሽ እስከ መጨረሻው ጸንቶ ከመስቀሉ ስር ለተገኘው ታማኝ ሐዋርያ ለዘብዴዎስ ልጅ ለዮሐንስ ጌታ እናቱን እናት እንድትሆነው እሱም ልጇ እንዲሆናት እንደሸለመው አደራ እንደሰጠው ሁሉ ዮሐ. 19 ፤ 26 እኛንም እንዲሁ የሚገባን ባንሆንም እንደቸርነቱ ተቀብሎን በጎደለው ሞልቶ የእናቱ ልጆች አድርጎ የመስቀሉን የመከራውን ውድ ሽልማት ለእኛም ይሸልመን ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን! አሜን!!! ጌታ ኢየሱስ ሆይ ና!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር... አሜን!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እሰፋ ማሩ
ዋና ውሃ አጠጪ
ዋና ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1514
Joined: Mon Sep 12, 2016 8:47 pm

Return to Warka General

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 4 guests