ቡርቃና የጋዜጠኛው ማስታወሻ - በፓስወርድ መነጽር ሥር

Topics related to cultures, arts, languages, arts such as humor, music, traditional literary genres of poems, ግጥም ፣ ቅኔ ፣ ተረትና ምሳሌ)

Postby ShyBoy » Sat Apr 04, 2009 6:54 pm

ገና የቡርቃ ዝምታን ሳላነብ እዚሁ ቤት ገጽ 4 መጨረሻ ላይ ይህንን ጽፌ ነበር::

ShyBoy wrote:ሰላም ሰዎች!

እኔ እንኳን አንባቢ ሰው አይደለሁም ሆኖም ግን ይሄ መጽሀፍ ካነበብኋቸው በጣት የሚቆጠሩ መጽሀፍት አልዱ ለመሆን በቅቷል:: መጀመሪያ ላይ ስጀምረው ለመጨረስ አልነበረም:: እዚህ ዋርካ ላይ ብዙ ሲወራለት ሳይ ምን አይነት መጽሀፍ ቢሆን ነው ብዬ ገረፍ ገረፍ ለማድረግ ነበር አጀማምሬ:: ግን መጽሀፉ ማግኔት ሁኖ ነው ያገኘሁት:: በጭራሽ አይለቅም! እጅግ በጣም የሚስብ ሁኖ ነው ያገኘሁት!!! ብራቮ ተስፋዬ ብያለሁ!!!

ወደ ይዘቱ ከተመጣ ብዙ ነገር ሊባልለት የሚችል መጽሀፍ ነው:: እኔ ግን ያን ያህል አንድን መጽሀፍ comprehend አድርጎ ትችት ለመስጠት ልምዱም ሆነ ብቃቱ ስለሌለኝ ዝርዝር ግምገማውን ለሚያውቁት ልተወውና በጥቅሉ ግን መጽሀፉን በማንበቤ ከልቤ ረክቻለሁ!!! ብዙ ትምህር ይሰጣል: ለማመን የሚያጠራጥሩ ነገሮችም አይጠፉትም:: በጣም ያዝናናል: ብሎም ያስተክዛል/ያሳዝናል:: በጣም ከማልረሳቸው እና ከልቤ ካሳቁኝ ሰዎች አንዱ ተክላይ ተክሉ......ነው ወይስ ተክሉ ተክላይ (ጸሀፊው ራሱ ትክክለኛው የቱ እንደሆነ ግራ እንደሚያጋባው ስለገለጸ ነው) ፍርፍር እስክል ነው የሳቅሁት:: የሲያትሉ ገጠመኞቹም በጣም አስቂኝ.......ሲሉም አሳዛኞች ናቸው: የኬንያውም አይረሳም:: የቁንድዶ ፈረሶች ታሪክ ደሞ የሚገርም ነው:: እኔ ስለዚህ ነገር ጭራሽ ሰምቸ አላውቅም ነበር:: ፖለቲካ ነኩ እና የውትድርናው ጊዜማ ምኑ ይወራል?

መጽሀፉን አንብቤ ከጨረስሁ በኋላ ስለ አቶ ተስፋዬ የተሰማኝ ነገር ቢኖር ግልጽነት እና ተንኮል የማያስብ አይነት ሰው ሁኖ ነው የተሰማኝ:: ድሮ ሳይወድ በግድ ያደረገቻውን ስህተቶች ሁሉ የተናዘዘ ሲሆን ላወጣቸው የተሳሳቱ መረጃዎች ሳይቀር እርማት ሰጧል (ለምሳሌ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ስለሚለው መጽሀፍ የተናዘዘው ነገር...እኔ መጽሀፉን አላነበብሁም)::

የቡርቃ ዝምታ የሚል መጽሀፍ መኖሩንም ያወቅሁት አሁን ዋርካ ላይ ሲወራ እና እዚህ መጽሀፍ ውስጥ ነው:: ባላነበብሁት መጽሀፍ ላይ አስተያየት መስጠት ባልችልም እነ ሙዝ እና ሀሪከን መጥፎ መጽሀፍ (ኦሮሞን ከአማራ የሚያቃቅር) እንደሆነ ገልጸዋል:: ዛሬ ወሬ ስቃርም EMF ላይ የሆነ ነገር ተለጥፎ አየሁና ቀልቤን ስቦት ከፍቸ አዳመጥሁት:: ከተስፋዬ ገብረአብ ጋር የተካሄደ ቃለመጠይቅ ነበር:: የቡርቃ ዝምታ ምንም አይነት ተንኮል ከጀርባው እንደሌለ ሰውየው ይገልጻል:: የልቁንም ያለውን እውነታ በማጋለጥ በፍትሄ እንዲፈለግለት ለማድረግ አስቦ እንደጻፈው አይነት ነገር ይገልጻል:: ቃለመጠይቁን እዚህ ጋ በመሄድ በግራ በኩል ካሉት "ቃለ-ምልልስ ከተስፋዬ ገ.አብ ጋር" የሚለውን ተጭናችሁ ማዳመጥ ትችላላችሁ http://www.ethioforum.org/wp/ (የዚህን ቃለ ምልልስ ብቻ ለይታችሁ ሊንክ ማቅረብ የምትችሉ ብትተባበሩ ጥሩ ነው የዌብሳይቱ ይዘት በየጊዜው ሊቀያየር ስለሚችል የቃለምልልሱ ማስታወቂያ ሊጠፋ ይችላልና)::

በሉ ሰላም ሁኑ!


አሁን የቡርቃ ዝምታን አንብቤያለሁ:: የአቶ ተስፋዬ አጻጻፍ ችሎታ በዚህም መጽሀፍ በጣም አስደምሞኛል!!! (ምናልባት ብዙ መጽሀፍ አንብቤ ስለማላውቅ ይሆናል ግን መጥፎ ነገሮቹ እንደተጠበቁ ሁነው አጻጻፉን በጣም ነው ያደነቅሁት........አንባቢን ልብ እየሰቀለ ቁንጥጥ አድርጎ የሚይዝ አይነት ነው-ለኔ)::

መጽሀፉ ልብ ወለድ ቀመስ በመሆኑ እውነትነቱን ማረጋገጥ ባልችልም ሀየሎም አራያ እውነት በዚህ መጽሀፍ እንደተገለጸው አይነት ሰው ከሆነ ከምር እጅግ በጣም ተወዳጅ ሰው ነበር ማለት ነው!!! ግን እውነትነቱን እጠራጠራለሁ:: ምክንያቱም ህወሀት ሰውን አስሮ አያሰቃይም: አይገርፍም እያለ ባንድ በኩል ግን እኔ ባደግሁበት አካባቢ ወያኔዎች እንደገቡ (ከገቡ በኋላ ያለውን እንኳን ሁሉም ያውቀዋል) መሳሪያ አለው የተባለውን ሁሉ ሰው ቤቱ እየገቡ እንዲሁም እስር ቤት እየወሰዱ በጣም ይገርፉ እና ያንገላቱ ነበር::

መጽሀፉ ጥላቻን ለመዝራት የተጻፈ ነው ወደሚለው ስመጣ......... በመሰረቱ እኔ ብዙም የታሪክ አንባቢ እና አዋቂ ስላልሆንሁ "ነፍጠኛ" ስለሚባለው ስርዓት ብዙም የማውቀው ነገር የለም:: ማንም ሰው የመሰለውን እና የተገነዘበውን ነገር በፈለገው መልኩ መጻፍ መብቱ ነው ብዬ ስለማስብ አቶ ተስፋዬ ለምን የቡርቃ ዝምታን እንዲህ አድርጎ ጻፍ ብየ መውቀስ አልፈልግም:: የጻፋቸውን ነገሮች እውነትም ከሚያውቃቸው ኦሮሞዎች ያየው እና የሰማው ከሆነ: መጽሀፉ ላይ ያንጸባረቀው ስሜት በሚያውቃቸው ኦሮሞዎችም ውስጥ ካለ ስለዛ ነገር መጻፍ መብቱ ነው.......ጥፋተኛ ሊያስብለውም አይገባም::

አቶ ተስፋየን የምቃወምበት ግን አንድ ነገር አለ:: ይሄን ያህል ሴንሲቲቭ የሆነ ነገር በሚጽፍበት ጊዜ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች አለመመልከቱ:: በኢትዮጵያ ህዝብ ያለው አመለካከት (በአማራው: በኦሮሞው: በትግሬው ወይም በሌላው) እሱ ባስቀመጠው መልኩ ብቻ ነው ወይ? መጽሀፉ ላይ ያሉት ባህሪያት በትክክል ያሉ (የነበሩ) ሰዎችን ባህሪ ከሆነ ምንም ችግር የለም ይጻፉ:: ግን ትግሬው እና ኤርትራዊው ሁሉ ቆራጥ እና በምግባር የታነጸ ብቻ ነው? ፈሪ እና ምግባረ ብልሹ የለም? ኦሮሞው ሁሉ ቂመኛ እና በኦሮሞው ክልል ሌላ ብሄር እንዳይኖር የሚፈልግ ነው? ተከባብሮ መኖርን የሚያስብ: ኢትዮጵያዊነት የሚሰማው ኦሮሞ የለም? ባለስልጣን የሆነው ሁሉ አማራ (እንዲሁም ተራው አማራ) ሆዳም: ጨካኝ: ለሌላው ብሄር ዴንታ የሌለው ነው? ሩህሩህ: አርቆ አሳቢ: ሰላም ወዳድ: ሌላውን ብሄር የሚያከብር የለም? ፖለቲካ ክፍል ወሮበላው እንዳለው መጽሀፉ ላይ ከአማራው አካል የወጣው አንድ ጥሩ አረፍተነገር ሚካኤል ቤተክርስቲያን ተሰብስበው ሊለያዩ ሲሉ ነው (እኛ አማሮች ከማንም አንበልጥም: ከማንም አናንስም የሚል አይነት):: ከኦሮሞዎች ለአማራው ጥሩ ነገር የሚንጸባረቀው በጣም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ከሀወኒ ብቻ ነው:: የቡርቃ ዝምታ ይሄንን ሚዛናዊነት ባለማሳየቱ በጣም ቅር ብሎኛል:: በተረፈ ግን ጸሀፊው ካንዳንድ ሰዎች ያየውን ጥሩም ሆነ መጥፎ ስሜት በመሰለው መንገድ ማንጸባረቁን አልቃወምም:: መብቱም ነው:: አንድ ሰው ደሞ ይሄንን መጽሀፍ ስላነበበ ብቻ ልቡ በጥላቻ ይሞላል የሚል እምነት የለኝም::

ቸር ያሰማን!!!
ShyBoy
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1118
Joined: Tue Apr 04, 2006 10:36 pm
Location: Gojjam

Postby ShyBoy » Sat Apr 04, 2009 7:00 pm

:arrow:
ShyBoy
ውሃ አጠጪ
ውሃ አጠጪ
 
Posts: 1118
Joined: Tue Apr 04, 2006 10:36 pm
Location: Gojjam

Postby password » Fri Apr 10, 2009 10:20 pm

የቡርቃ ዝምታ
በፓስዎርድ መነጽር ሲታይ


የልቦለድ ድርሰት ዋናው መሰረቱ የታሪኩ መሰምር ነው ይባላል። የታሪክ መስመር ሳይቀየስ ታሪኩን መተረክ አይቻልም። እንደ ንግግር ማለት ነው። ንግግር ስታደርግ ስለምን እንደምታወራ ማወቅ አለብህ። የምታውራውን የማታውቅ ከሆነ እርስ በርሱ የሚምታታ፣ አንዱ ከሌላው ያልተያያዝ፣ የተዘበራረቀ ንግግር ነው የሚሆነው። ልቦለድም ስለምን መተረክ እንደፍለግህ አንጥረህ ካላወጣኸው ዝብርቅርቅ ጽሁፍ ሆኖ ነው የሚቀረው። ገጽባህሪያት፣ መቸት፣ ትልምና ግጭት ወዘተ ንጥር ያለ የታሪክ መስመር ከወጣ በሁዋላ ነው የሚሰናዱት።

ቡርቃ ልቦለድ ድርሰት ነው፣ ተብሎ የቀረበ መጽሀፍ ነው። የታሪኩን መስመር ለማወቅ የዋናዎቹን ገጽባህሪያት ህይወት መመርመር ያስፈልጋል። ገጸ ባህሪያቱ በታሪኩ ውስጥ ምን ለመፈጽም እንደተነሱ የሚጠቁመውን የውስጥና የውጭ ፍላጎታቸውን ማወቅ ያስፈልጋል። ከዚያ ነው የታሪኩን ዋና መስመር ማውጣጣት የሚቻለው። ከዚህ በመነሳት የቡርቃን የታሪክ መስመር ፍለጋ ዳግማይ ገጻት ማገላበጤ አልረዳኝም፣ ምክንያቱም ቡርቃ የተጻፈው የልቦለድ አጻጻፍ ዘይቤን ተከትሎ ይምስል እንጂ ጨርሶ ኪናዊ አጻጻፍን የተከተለ አይደለም።

ቡርቃ እንደ ልቦለድ ገጽባህሪያት አካትቶአል። መቸቱ ይታውቃል። ጭውውት አለው። ግጭትም አለው ግን ኪናዊነት የለውም። ኪናዊነት ስለሌለው የመጽሀፉ ታሪክ አጉዋጊነት የለውም። ልቦለዳዊ ድርስት የሚጠይቀውን የኪንጽሁፍ ስርአትን ስላልተከተል ታሪኩ አይጥምም።

ኪናዊ አይድልም ሲባል ምን ማለት ነው?
ይህን ለማብራራት ገጽባህሪየት አሳሳሉን እንመልከት። ዋናው ገ/ባህሪ አኖሌ ዋቆ ነው።
እኖሌን ደራሲው በሚከተለው መልክ ሊስልልን ሞክሮአል።
አኖሌ፣ ሀያ ዝጠኝ አመት መልሎ ነው። ጀርመን ሀገር፣ ሀምቡር ነው የተማረው። በጣም ብርቱ ነው። ፈጣን ነው። የልቡን ይናገራል። ሶስት ባልሙያዎች የሚሰሩትን ብቻውን መስራት የሚችል ንቁ ልጅ ነው። ለፖለቲካ ጉዳዮች ደንታ ያለው አይመስልም። ቡርቃ ነው የተወለደው። የማደጎ ልጅ ነው። ጨርሶ ጠባብ የሆነ የጎሰኝነት ስሜት አያንጸባርቅም።


ይህ ተራኪው በቀጥታ የነገርንና በሌላ ገ/ባህሪ በኩል ስለ አኖሌ የገለጠልን እውነታ ነው። ይህ አገላለጽ ግን ኪናዊ አይደልም። ደረቅ ራፖርታዥ የምንለው አግላለጽ ነው። ስላዮች፣ ጋዜጠኞችና ፖሊሶች ያጠናቀሩትን መረጃ ለበላይ ሲያቀርቡ የሚጠቀሙበት እጥር ምጥን ያል አግላለጽ ነው። የገጽባህሪውን ቁመና፣ እድሜና ውጨዊ መልክ በቀር ባህሪን በዚህ አይነት መግለጥ ኪናዊ አይደልም።
የልቡን ይናገራል ከማለት የልቡን ሲነገር ማሳየት፣ ፈጣን፣ ብርቱ ከማለት ብርታትና ፍጥነቱ በታሪኩ ውስጥ ማሳየት ነው ኪነዊ አስራር የሚባለው።

አስረጅ
ፓስ የጠፋ ወንድሙን ፍለጋ ሲወጣ ለሶስት ቀን የሚበቃውን ስንቅ ይዞ ነበር። እናቱ በሶውን በአገልግል፣ ውሃውን በኮዳ ሲያደርጉለት ስንት ጉርሻ ለምሳ፣ ስንት ለራት፣ መብላት እንዳለበት አበክረው ነግረውታል። ከዚያ በላይ ከነካ በራብ እንደሚሞት ያውቃል። ግን ይህችን አጥንቶችዋ እንደማገር ገጥጠው የወጡ እናትና ከንፈሮቻቸው እንደ ኩበት የደረቁ ልጆችዋን ሲያይ ያ ኮስታራ አንጀቱ ላላ። አንዴ ወደ ሰማይ ተመለከትና ቅንጣት ሳያመነታ አገልግሉንና ኮዳውን ሰጥቶዋቸው ሁለት ሙሉ ቀኖች የሚቀረው መንገዱን ቀጠለ።


ፓስ ቆራጥ፣ ርህሩህ፣ ቸርና የማያወላውል እምነት ያለው ገ /ባህሪ መሆኑን እንገነዘባለን። ገ /ባህሪ በዚህ መልክ ሲሳል አንረሳውም። ከመንገር አሳይ የሚባልው ለዚህ ነው።

ቡርቃ ውስጥ ያሉ ገጽባህሪያ የልቦለድ አጻጻፍን ዘይቤ በተከተል መልኩ ባለመሳላቸው ምክንያት ገጽበህሪያቱ የሚያደርጉትና የሚናገሩት የደራሲው እንጅ የገጽባህሪያቱ አይመስልም። አንባቢያን ደራሲውን አምረው ሲያወገዙ የምንሰማበት አንዱ ምክንያት ገጸባህሪያት የትናገሩትን ደራሲው እንዳለው ተደርጎ በመወሰዱ ነው።

ለአብነት ያህል ጭውውቱን እንወሰድ።

"ማን ነው የሚያኮርፈው"

"ወንዙ የቡርቃ ወንዝ"

"የወንዝ ማኩረፍ ምን ማለት ነው አኖሌ?"

"ታሪኩ ረጅም ነው ያልኩህ ለዚህ ነው። ገበሬዎቹ ቡርቃ ከመሬት በታች ውሰጥ ውስጡን የሚሄደውኦሮሞዎች በአማራ ወረሪዎች በመገዛታቸው እፍረት ተሰምቶት ነው! ብለው ያምናሉ"
---------------

"ከብዙ አምታት በፊት አልገጆ በምትባል መንደር አመጽ ተቀስቅሶ ነበር። አልገጆች በደል ሲበዛባቸው ተቆጡና አምጹ። የንጉሱ ወታደሮችም የመንደሪቱን ህዝብ በትይት ጨፈጨፉ። ጎጆዎችን በእሳት አጋዩ። የመንደሪትዋ ነወሪ ሁሉ አለቀ። ፈጣሪም በአማሮች ጭካኔ ከልብ በማዘኑ አለቀስ።"


እነዚህ ሁለት አንቀጾች አኖሌ ለጀብሪል የሚያወጋው ናቸው። ገጸባህሪው እንድተማረ ሰው ተስሎልን ስለነበር አማራና ኦሮሞ የሚለውን ስያሜዎች ከጠራ በሁዋላ የራሱን ሚዛናዊ ምሁራዊ አመለካከት ስላላከለ፣ ወይም የንጉሱ ወተደሮች ብሎ እንደጀመርው በዛው አይነት አባባ ባለመጨርሱ እንደ ደረሲው ሀሰብ ሊገምት ይችላ ።ደረሲው እኔ እላልኩም፣ ገጸበህሪዬ ነው ሊለን ይችላል።
እኮ ዋናው ገጸባህሪህ እንዴት እንዲህ ታስብለዋለህ፣ ህዝህብ ማጋጨት አይሆንም ወይ? አማሮች ከማለት የንጉሱ ወታደሮች ለምን አተስብለው? ሲባል
ገጸባህሪዬም ታሪክ ነው ያወራው የራሱ አባባል አይደለም ሊል ይችላል። ተራ ጽሁፍ ከሆነ እቀበለዋለሁ። ኪነጽሁፍ ነው የምጽፈው ሲል ነው የማልስማማው።
ለምን? ኪነጽሁፍ የጋዜጣ ርእስ አንቀጽ አይደለም። የፕሮፖጋንዳ በራሪ ጽሁፍም አይደልም። ኪነጽሁፍ ከተራ ጽሁፍ ይለያል። ኪነጽሁፍ ወገንተኛ አይደለችም። ቂም አታውቅም፣ ውሽት፣ ሽፍጥ፣ አሉባልታና ማስመሰል እስዋጋ የሉም። ኪነጽሁፍ አምጽ አትቀሰቅስም፣ አብዮት አታነሳሳም። ግን እንዲህ ተኖረ ትላለች። እውነቱን ከሀሰት ለይታ፣ መንስኤውን ከባህሪያት፣ ስበቡን ከነባራዊ ሁኔታ ጋር አገናዝባ ታቀርባለች። ፍርዱን ለአንባቢ ትተዋለ ች እንጂ የራስዋን ፍርድ አትሰጥም። የሰውንም አመለካከት እንዲዘባ አታደርግም። የነበረውን እንዳለ፣ የተኖረውን እንደነበረ አድርጋ ታቀርባለች እንጂ።

የቡርቃ ደራሲዎች የነበርውን ነው ያቀረብነው ይሉ ይሆናል። ተስፋዬ ራሱ ከህዝብ የስማሁትን መልሼ ወደ ህዝብ አመጣሁት ሲል ተደምጦአል። እውነትም ሰምቶ ሊሆን ይችላል። ከግን እውን ከህዝብ ነው የሰማው? ከህዝብ ሲባል ስንት ሰዎች? ህዝቡስ እውን ታሪኩን አጣመው የነገሩት ሀይሎች የሉም? ውሽትን እውነት ለማስመሰል አራት ጊዜ ብቻ መደጋገም እኮ ነው የሚበቃው።
አይደለም የመቶ አመቱን በአይናችን ያየነውን የትናንቱን ታሪክ እንኩዋን ፖለቲክኛች እንዴት ህዝብ እንደሳመኑበትና እውነተኛ ታሪክ አስመስለው እንደጻፉት መጥቀስ ይቻላል።

ከብዙ በጥቂቱ

-ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነበርች
-ሻእቢያ የኢትዮጵያ ወታደሮችን የወርቅ ጥርስ በጉጠት አያስወለቀ አባረረ፣
-የኢትዮጵያ ወታድሮች ኤርትራ ውስጥ እርጉዞችን በሳንጃ ይወጉ ነበር፣
-ወያኔ በአንድ ምላጭ ብዙ እስረኛችን ይላጫል፣
-መንግስቱ የአጼ ሀይለስላሴን አስከሬን ከቢሮው ስር ቀበረ፣
-በቀይ ሽብር ከአንድ መቶ ሺ በላይ ወጣት አልቀ፣
-ሀውዜንን ያስደበደበው ወያኔ ራሱ ነው፣

ወዘተ ይባላል። ተብሎም በሰፊው ይታመናል። ማስረጃ ግን የለም። ሁሉም ለተለያየ የፖለቲካ አላማ ተብለው የተናፈሱ ወሬዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በዘመነ ምንሊክ ተፈጸመ ከሚባለውም ምን ያህሉ እውነት ይሆን? ምን ያህሉ ተጋኖአል? እውን የተለየ የፖለቲካ አላማ ያላቸው ሰዎች ይህን ታሪክ አላጣመሙትም? ደራሲያን ብእራቸውን ከማንሳታቸው በፊት ሀስቱን ከእውነት መለየት መቻል አልባቸው። እንዲህ አይነቶችን ከንፋስ ላይ የሚጨለፍ ወሬዎች ለድርስታቸው መሰረት ማድረግ የለባቸውም። ከላይ እንደተቀመተው የገጸባህሪ ቃል እንኩዋ ቢሆን ተራኪው በመሀል ገብቶ የተሰነዘረውን አመለካከት የሚተችበት ኪናዊ አግባብ መጠቀም ይኖርበታል። አለበልዚያ ያ ሀሰብ ደራሲው ሊያስተላልፈው እንደፈለገው ሀሰብ ነው የሚቆጠረው።

ይቀጥላል
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby password » Fri Apr 10, 2009 11:21 pm

የተደገመ

ከላይ የተጀመረው የቡርቃው ግምገማ ይቀጥላል....
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby Janamora » Sat Apr 11, 2009 1:10 am

ሰላምታ ለቤቱ ባለቤት:: ዋርካ ፖሎቲካ ውስጥ ስንጎዳጎድ ያለ ቦታው የገባ የመሰለኝን የ Mር Xን ጽሁፍ አገኘሁ:: ለማነጻጸር እንዲመች እዚህ አምጥቸዋለሁ::
መልካም ውይይት::

እንድናነበው ላስቻላችሁን ወገኖች ሁሉ ምስጋና ይገባችሁዋል :: እንደ ስነጽሁፍ ይህ የሚደነቅ ድንቅ ስራ ነው :: ደራሲው ግሩም ኢትዮጵያዊ ጸሀፊ ነው :: አጻጻፉ የበአሉ ግርማን ኦሮማይ መምሰሉ ብቻ ሳይሆን ሁለቱም በገጽ 16 ና 17 ስለ ፕሮቶኮል ሹም : ስለፕሬዚዳንቱ : እንዲሁም ፕሬዚዳንቱ ላይ ስለነበረው የወቅቱ ውጥረት በየራሳቸው መንገድ ያወሳሉ :: ያም የሚያሳየው ተስፋዬ ገብረአብ በአሉ ግርማን idolize እንዳረገው ነው :: ያም የሚመሰገን መልካም ምርጫ ነው :: በሁዋላ ላይ እንደምናየው (ገጽ 204) ወደ በአሉ ግርማ "ፊያሜታ " ለጨረፍታ ይወስደናል :: ያም ብቻ ሳይሆን ልክ በአሉ ግርማ ፊያሜታን ተጠቅሞ በስልጣን ብልግናና አላማቢስነት የተነከሩትን የደርግ ሹማምንት በብእሩ ያለርህራሔ እንደሚወጋቸው ....ተስፋዬ ገብረአብም ሀውኒ ዋቆ አድርጎ በፈጠራት ገጸባህርይ የኢህአዴግን ባለጌዎች ሲነድፋቸው እናነባለን :: በአሉ ትረካውን ጸጋዬ ገ /ማርያም ብሎ በሰየመው የሚዲያ ሰው ገጸባህርይ ጀምሮ እንደሚጨርሰው ...ተስፋዬም እንዲሁ ስሙ ባልተገለጸ የሚዲያ ሰው ትረካውን ጀምሮ በዚሁ ሰው ይደመድማል :: አንግዲህ ይህ ሁሉ ተስፋዬ ገ /አብ አስቦትም ይሁን ሳያስበው የበአሉ ግርማ የብእር ምርኮኛና ወራሽ (literary captive and heir) መሆኑን ነው ::

በይዘቱ በኩል ደግሞ ጽሁፉ literrary symmetry and balance መጠበቁ ድንቅ ነው :: ለምሳሌ :- በአንድ በኩል የኦሮሞውን ቁጭትና በቡርቃ መንደር በአንዲት ኮረብታ በዋቆ አባዱላ ጎጆ ዙሪያ ለበቀል መዘጋጀትን እያወሳ ...መልሶ በሌላ በኩል ደግሞ የአማራዉን እየተቀጣጠለ ያለዉን መአት ለመመከት መዘጋጀት በሚካኤል ቤተክርስቲያን ዙሪያና በኮረብታ ላይ ያሳየናል :: ያም ማለት ጸሀፊው የአንባቢውን ጭንቀት ከውጥረት ሊያረግበው እንዳሰበ ያሳያል :: ይህ የስነጽሁፍ ሚዛን (balance) በዜኒት ራስ ወዳድነትና በሀውኒ የዋህነት - የባህርይ ልዩነት - እንዲሁም በወጣቱዋ ዮዲት ዘር አልባ ፍቅርና በወላጅ አባቱዋ አሮጌ ዘርኛነት ላይም ይደገማል :: ወደመሀል ስንገባ ውጥረቱ በደብረዘይቱዋ ፍሬወይኒ እሮሮና ጩህት ጀምሮ ...አኖሌን በተጠቀሙበት በሻቢያ ተዋናውያንና በተቀናበረው የእስረኛ ማስመለጫ ዘዴ ዙሪያ እጅግ ሲከር ...መለስ አርጎ በ "ጮማዬ " ሆዳምነትና በወታደር ቤት ጣእም አልባ የብልግና ሞያ ስም የከረረውን ያረግበዋል :: ይህ ደግሞ ለጽሁፉ ውበት ሰጥቶታል ::

ደራሲው በወታደር እስር ቤቶች አካባቢ ያሉትን እውነታዎች ለመግለጽ የሚፈጥራቸው ገጸ ባህርያት ድንቅ ናቸው :: በሞት አፋፍ ላይ ያለው ንኩ ወታደርና ድንቅ ግጥሙ (ወይዘሪት ጨረቃ ...ወይዘሪት ዝምታ ) የአዲስ አለማየሁን ጉዱ ካሳን አስታወሰኝ :: ከላይ ባሉት ገጾች አንባቢው ልቡ ሲቆዝም ...ጸሀፊው በሞት መስመር ላይ ያለውን ሞኙን አያሌውን (መኩዋንንትን ) ያስተዋውቀንና -- ስለ ወደብ ጉዳይ ለካድሬው በሰጠው መልስ ያስቀናል :: እንግዲህ ነገሮች ሁሉ በአኖሌ ዋቆ ዙሪያ ይሽከረከራሉ ::

አኖሌ የህዝብ ቁጣ ነው :: አኖሌ መላ የጠፋውና መላ የጠማው የኦሮሞ ህዝብ ድምጽ ነው :: አኖሌን ለመረዳት የሱ ተቃራኒ ባህርይ ያለዉን በኦሮሞ ድምጽ ስም የሚነግደዉንና ለትርፍ የሚሮጠዉን ኢህአዴግ ያደራጀዉን የኦህዴዱን ሰለሞን ዲሳሳ ማየት ይረዳል :: አኖሌ እንደገጸባህርይ የሚዋጋው የውሸት ስርአትን ነው :: መታለል ይብቃን ይላል :: ነጻነት ተሰፍሮ የሚሰጥ ድርጎ ሳይሆን እስከሰማይ ድረስ ሳይለካ ለህዝብ የተሰጠ መብት ነው ይለናል :: ለዚህ ነው ምክር ሁሉ ቀልድ የሆነበት :: ይሁን እንጂ አኖሌ ተስፋ ቢስ አይደለም :: እነኢብሳን ማድነቁ አልቀረም :: ሀየሎምን በድርጅት ደረጃ ባያምነዉም በግለሰብ ደረጃ ቅንነቱንና ጀግንነቱን ማመኑ አልቀረም ::

የደራሲው መንቲያ ተዋናይ ሀውኒ ዋቆ የአብዛኛው ኦሮሞ ድምጽ ናት :: የኦሮሞን ጥያቄ በመመለስ ደረጃ አማራጭ ናት :: አንባቢው ሳይወድ በግድ ይወዳታል - ሌላው ምርጫ አደገኛ ነውና :: (ምናልባት በምሳሌነት ለመጥቀስ አሜሪካ በሲቪል ራይት ሙቭመንት ወቅት የዶ /ር ኪንግን ሰላማዊ ጥያቄ ባትሰማ ምርጫዋ ከማልከም ኤክስ ጋር መታገል ነበር )

የተስፋዬ ገ /አብ ሀውኒ ኢትዮጵያዊ ከማን ይገነጠላል " ትላለች :: ወደ ድህረ ገጹ ስንዳረስ "እኛ ከኢትዮጵያውያን ጋር የተፈጠርን ኢትዮጵያዊ ነን :: በበቀል የምናተርፈው የለም "...አማሮች ንጹህ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችን ናቸው ትለናለች :: (457) ሀወኒ የዘርኛ ምሳሌ ሳትሆን ዘረኝነት ይብቃንና አብረን ተከባብረን በእኩልነት እንኑር የምትል ድምጽ ናት ::

በአጠቃላይ የቡርቃ ዝምታ በድፍረት የተጻፈ መራራ እውነት ነው :: ለጊዜው ስሜተኞችን ያስከፋል :: ይሁን እንጂ የወደፊት ትውልድ በመጻፉ ይደሰታል :: መጽሀፉን ህወሓት ሊወደው አይችልም :: ኦህዴድ ሊወደው አይችልም :: አስተውሎ ያላነበበው አማራው ሊወደው አይችልም :: ማነው ያልተተቸበት ?

ይቀጥላል ....
The Lion was silent but, The rats were roaring
Janamora
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 97
Joined: Tue Oct 28, 2008 8:45 pm

Postby ዛዙ » Sat Apr 11, 2009 8:16 pm

ጃናሞራ

የፕሮፓጋንዳ ጽሁፍን ከስነ-ጽሁፍ ለይ እንጂ:: ፓስ እየስጠን ያለው ሂስ ምሁራዊ (ባለሙያዊ) ሲሆን MR X ደሞ የጻፈው ንጹህ በፓለቲካ የቀለመ አስተያየት ነው:: ሁለቱ ለውድድር ሊቀርቡ የማይችሉ ስለሆኑ የMR X የመሀይም ትንተና ምናልባት የነበረበት የፓለቲካ ገጽ ላይ ትክክለኛ ቦታው ነበር:: ነገር አትቀላቅል: እና አርፈን ሁላችንም የፓስን ትንተና እንስማ::
ዛዙ
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 199
Joined: Sat Oct 09, 2004 12:46 pm
Location: ethiopia

Postby ሾተል » Sun Apr 12, 2009 12:19 am

ጋዜጠኛና ደራሲ ተስፋዬ ገብረአብ ከረንት አፌርስ የፓልቶክ ሩም ውይይት እያደረገ ነውና ማዳመጥ ወይም መጠየቅ የምትፈልጉ ንኡ::

ሾተል
እሰይ ተመስጌን አምላኬ ለካስ በክብርነቴ እራሴን ሆኜ እኔነቴን ፈልጌ አግኝቼዋለሁ !?
ሾተል
ዋና አለቃ
ዋና አለቃ
 
Posts: 9653
Joined: Thu Jan 13, 2005 9:42 pm
Location: Vienna-Austria

Postby Janamora » Sun Apr 12, 2009 12:48 am

....የመሀይም ትንተና.....


አቶ ዛዙ አቃቢት:: ምነው ሀሳብህን ሳትሳደብና ሰውን ሳትዘልፍ ባግባቡ መግለጽ አትችልም ነበር?? አንተ ያሰብከውን ቅኝት ያልተቀኘ መሀይም መባል አለበት ማለት ነው? ሳትሳድብና ሳትዘልፍ እኮ የ Mር X ን አስተያየት ባስተያየት መምታት ትችል ነበር እኮ:: ልብ ብለህ ከሆነ Mር-x እየተቸ ያለው መጽሀፉ ሊያጨስ የሚፈልገውን የዘረኝነት ጪስ አይደለም;; ይሄ ከሚገባው በላይ ተተችቷል:: Mር - x ያተኮረው በደራሲው የቃላት አሰላለፍ የአረፍተ- ነገር አወቃቀር ትልልቅ ጉዳዮችንና ክስተቶችን በሁለት መስመር አሳጥሮ ማቅረብ መቻልን በጽሁፉ ውስጥ የፈጠራቸውን ግጭቶችና ሚዛናቸውን ለመጠበቅ የሄደባቸውን አካሄዶች ባጻጻፍ ስታይል የበአሉ ግርማን የአተራረክ ስታይል መከተሉ ወ.ዘ.ተ ናቸው:: ይሄ ሁሉ ግን መጽሀፉ ሊያስተአልፋቸው የሞከረውን የዘረኝነት ፖሎቲካ በመጨመር አይደለም:: እና እነዚህን የMር X አስተያየት ሳነብና እዚህ ቤት ደሞ ስነ ጽሁፋዊ ይዘት ያለው ትንተና ስላየሁ ለኮምፓሪዝን አመጣሁት:: ለመወያየት ይጠቅማል እይታን ያሰፋል በሚል ነው:: የመሀይም ትንተና ስለሆነ አይደለም:: ይገርማል.... አንዳንዶቻችን የማናውቀውን ሰው አስተያየቱ ሳላልጣመን ብቻ ስንዘልፍ ደራሽ ጎርፍ ነው..? የገፈርሳ ወንዝ ነው?... ምንድነው እዚህ አምጥቶ የጣለን እያልኩ እገረማለሁ::
The Lion was silent but, The rats were roaring
Janamora
ጀማሪ ኮትኳች
ጀማሪ ኮትኳች
 
Posts: 97
Joined: Tue Oct 28, 2008 8:45 pm

Postby password » Sun Apr 12, 2009 9:08 pm

የቡርቃ ዝምታ
በፓስዎርድ መነጽር ሲታይ


ክፍል ሁለት

ቡርቃ ኪነጽሁፍ ወይም ኪናዊ ድርሰት አይደለም ብያለሁ። ስላልሆነም ገጸባህሪ እሳሳሉ ላይ የነበርው ጉልህ ጉድለት በደራሲው ላይ የተቃውሞ ውርጅብኝ ማስከተሉን ለመግለጽ ሞክሬአለሁ። ደራሲው ገጽባህሪያቱን በኪናዊ ስልት አስተዋውቆ ቢሆን ኖሮ፣ ማለትም ከያንዳንዱ ገጸ ባህሪ የሚወጣውን ቃል አንባቢው የገጸባህሪው አመለካከት እንድሆነ አድርጎ እንዲወስድ የገጽባህሪያቱን ቅድመ-ታሪክ ህይወት በትንሽም ቢሆን ቢያሳይ፣ ቃለ ባህሪያቱ እንደ ራሱ አመለካከት ባልተወሰዱበት ነበር።

አንዳንድ ደራሲዎች ገጸባህሪያትን መሳል ማለት መልክና ቁመናን ብቻ መግለጽ ይመስላቸዋል። በመሰረቱ መልክና ቁመና ተገለጽም አልተገለጸም ለአንባቢው ይህን ያህል ግንዛቤ አይጨምርም። በታሪኩ ሂደት ላይም ያን ያህል ጫና የለውም። ዋናው የባለታሪኩን ባህሪ ሊገልጽ የሚችል ህይወቱን ማሳየት ነው። አኖሌ አሁን ያለውን የህይወት አመለካከትና የፖለቲካ እምነት እንዲይዝ ቀደም ሲል ምን አይነት ታሪክ አሳልፎአል? ህይወቱ አሁን ካለበት ሁኔታ እንዲገኝ በልጅነቱ ያጋጠመው ወሳኝ ነገር ምን ነበር? አሳዳጊዎቹ፣ መምህራን፣ አካባቢው በሱ ላይ የነበራቸው ተራ ምን ይመሰል ነበር? የቡርቃ ተወላጅ ወይም የኦሮሞ ልጅ በመሆኑ ምክንያት በልጅነቱ ይሰደብ ነበር? ይደበደብ ነበር? ይገለል ነበር? ታስሮኣል? ተገርፎኣል? ኦሮምኛ እንዳይናገር ተከልክሎአል? የኦሮሞ ተወላጅ በመሆኑ ለሌላው ኢትዮጵያዊ የተፈቀደን እሱ ተከልክሎ ነበር? እሱ የመጣበት አካባቢ ከሌለው የኢትዮጵያ ክፍለ ሀገሮች ዝቅ ያለበት ልዩ ምክንያት ነበርን?

ያ ሁኔታ በሌላ ቦታ ሳይሆን እዚሁ ድርስት ውስጥ ሳይገለጽ ከአኖሌ አፍ የሚወጡ ቃላት የአኖሌ መስለው ይታያሉ ማለት ዘበት ነው።

እስኪ ከዚህ በታች ያለውን የአሎኔንና የአባቦሩ ንግግር እናዳምጥ። ማንበብ ሳይሆን በጥሞና እናዳምጠው።
-አባቦሩ
-ወዬ ልጄ?
-እስርቤት ውስጥ ደበደቡዋችሁ እንዴ?
-ሰደቡን እንጂ አልነኩንም ልጄ
-ማነው ተሳዳቢው፲
-ቆየ እኮ ልጄ
-ምኑ አባቦሩ?
-ስድቡ ከተጀመረ ነዋ

-ምን ብለው ሰደቡዋችሁ?
-እኔን ጅል ኦሮሞ አሉኝ

አቃሰተ። በጦር ጎኑን የተወጋ ያህል አመመው። በአፍንጫው ትኩስ ትንፋሽ ሰንጥቆ ሲወጣ ተሰማው።

-ይህን ያለውን ደንቆሮ ያስታውሱታል?
-ከምትነዱዋቸው አህዮች አትሻሉም ሲሉም አላገጡብን
-ያው... ውሻ ነው እንዲህ የሚግማማው?
-መቼ ይሆን የምትሰለጥኑት ሲሉም ጠየቁን
-እርሶ ታዲያ ምን መለሱለት አባቦሩይ?
-ማን እየገዛን እንሰልጥን አልኩት?
-ምን መለሰ ይህን ሲሉት?
-ሲሉ ሰምታ ዶሮ ታንቃ ሞተች አሉና ተረቱብን
-ለተረትማ ማን ብሎአቸው? ኑሮአቸው ተረት ነው። አስተሳስባቸው ተረት ነው። እንደ ባልቴት ተረት ከማውራት የተሻለ ምን ያውቃሉ? ደደቦች! እነሱን ብሎ ደሞ ስልጡን! ለዚች አገር ምን ቁምነገር የፈየዱ መሰላቸው? ሶስት ሺህ እያሉ በሚመኩበት ዘመን ጠጅ በመጠልና በመጠጣት ነው ጊዜአቸውን የፈጁት!

-ያንን ሰማይ ታየዋለህ?
-የቱን ብሎ በመስኮት አማተረ።
-እስከ አድማስ የተዘረጋውን
-አዎ! አባቴ
-እንኩዋን መሬቱ ሰማዩም የኦሮሞች ነው። ጊዜ ነው ያዋረደን። ጊዜ ደግሞ ሁሉንም እንደነበረ ያደርገዋል።


ገጸባህሪያት, ብራናና ብእር አገናኝቶ ቀለም እፍ በማለት ብቻ አይፈጠሩም። ወይም ስም ብቻ የሰጠነው ምናባዊ አካል ገጸባህሪ አይሆንም። ገጽባህሪያት ልክ በውኑ አለም እንዳለነው ሰዎች የህይወት ታሪክ አላቸው። ያሳለፉት ታሪክ ይገዛቸዋል። በልብወለድ ታሪከ ውስጥ ገጽባህሪያት ከገጻት ውስጥ ወጥተው እንዲታዬ ማንነታቸውን በሚገባ መግለጽ ያስፈልጋል። ገጸባህሪያት የሚናገሩትን የምናምነው ወይም ቃሉ ከራሳቸው አፍ የወጣ መሆኑን የምንቀበለው ያ ያሳለፉት ታሪክ፣ ያ አሁን ለሚናገሩት ምክንያት የሆነው ጉዳይ በዚያው በልቦለዱ አለም ትረካ ውስጥ ሲገለጽ ብቻ ነው።

ስለ አኖሌ የምናውቀው በቂ ባለመሆኑ፣ ስለ አባቦሩ የምናውቀው ምንም ነገር ስለሌለ ከላይ የሰፈረው ጭውውት፣ ከአኖሌና ከአባቦሩ አፍ የወጡ ሳይሆን አንድ የተለየ አላማ ያለው ቡድን ለሚፈልገው ግብ ሲል ያስቀመጣቸው ቃላት ናቸው የሚመስሉት። ሁለቱን ገጸባህሪያት በደንብ ብናውቃቸው ኖሮ አዎ፣ እነሱማ እንዲህ እንዲህ አይነት ህይወት ያሳለፉ አይደሉ እንዴ፣ አዎ ከነሱ አፍ ከዚህ የባሰም ሊወጣ ይችላል እንል ነበር። አኖሌ ውጭ ሄዶ የተማረ ሰው መሆኑን እናውቃለን፣ ከአፉ የወጣው ግን ከዚያ ፊደል ካልቆጠረው ገበሬ የባሰ ነው።

አኖሌ ሀምቡርግ በነበረበት ወቅት ከአክራሬ ኦሮምኛ ተናጋሪ ቡድኖች ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው፣ ጠባብ ጎጠኛ መሆኑ ተገልጾልን ቢሆን፣
-ለተረትማ ማን ብሎአቸው? ኑሮአቸው ተረት ነው። አስተሳስባቸው ተረት ነው። እንደ ባልቴት ተረት ከማውራት የተሻለ ምን ያውቃሉ? ደደቦች! እነሱን ብሎ ደሞ ስልጡን! ለዚች አገር ምን ቁምነገር የፈየዱ መሰላቸው? ሶስት ሺህ እያሉ በሚመኩበት ዘመን ጠጅ በመጠልና በመጠጣት ነው ጊዜአቸውን የፈጁት!


ሲል አይገርመኝም ነበር። የደራሲው ድምጽ ነው ብዬም አልልም፣ ምክንያቱም አኖሌ ካሳለፈው ህይወት አንፃር ያን ሊል እንዲችል አስቀድሜ እጠብቃለሁና።

ቡርቃ ኪነጽሁፍ አይደለም፣ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው ያልኩበትን ሌላው ምክንያት ከእዚሁ ጭውውት ሳንወጣ እንመልከት።

-እስርቤት ውስጥ ደበደቡዋችሁ እንዴ?
-ሰደቡን እንጂ አልነኩንም... ልጄ
-ማነው ተሳዳቢው!

ይህ ወሳኝ ጥያቄ ነበር። የደራሲው ስራ ኪነጽሁፍ ቢሆን ኖሮ ለዚህ ጥያቄ አግባብ ያለው መለስ ስጥቶ ያልፍ ነበር እንጂ እንደ ተራ ነጥብ አይዘለውም ነበር። መቸቱ ደርግ ስልጣን ላይ የወጣበት አስራ አምስተኛው ዐመት ነው። ዘመነ ምንሊክ አይደለም። ይህ ማለት አባቦሩ የታሰረበትን እስር ቤት የሚያስተዳድረው ክፍል ሆነ አገሪቱን የሚመራው አካል የሁሉም የኢትዮጽያ ብሄረስቦች ተዋጽኦ ያለው እንጂ የአንድ ብሄረስብ ሰዎች አይደለም። ተሳዳቢው አንድ ባለጌ ትግርኛ ተናጋሪ ወይም አዲስ አበባ ተውልዶ ያደገ ከኦሮምኛ ተናጋሪዎች የተወለደ ዋልጌ ሊሆን ይችላል። ... ማንም ሊሆን ይችላል። ይህ የሚያጠያይቅ ጉዳይ አይደለም። ተስፋዬ (ትግሬው) ራሱ የደርግ ወታደር ነበር አይደል? ግን ድርስቱ ማስተላለፍ የፈለገው ባለፉት ገጾች በተደጋጋሚ የተጠራ ብሄሬስብን ማጉድፍ ስለሆነ ደረሲው ያንን ጥያቄ ሳይመልስ ማለፍን መረጠ።

እንቀጥል።

-ምን ብለው ሰደቡዋችሁ?
-እኔን ጅል ኦሮሞ አሉኝ
አኖሌ አቃሰተ። በጦር ጎኑን የተወጋ ያህል አመመው። በአፍንጫው ትኩስ ትንፋሽ ሰንጥቆ ሲወጣ ተሰማው።


እዚህ ላይ አንባቢ ማስተዋል ያለበት የተሳዳቢዎቹን ቁጥር ብዛት ነው። ብዙ ሰዎች በአንድ ላይ፣ በአንድ ጊዜ አባቦራን "ጅል ኦሮሞ" አሉዋቸው። ሊሆን አይችልም። በኪነ ጽሁፍ አይቻልም። ፕሮፖጋንዳ ነው። ለመሆኑም በሚቀጥለው የአኖሌ በጣም የተጋነነ ስሜት መገንዝብ ይቻላል።

-ይህን ያለውን ደንቆሮ ያስታውሱታል?
ይህም ጥሩ ጥያቄ ነበር። አንባቢ መልሱን ለማወቅ የሚጉዋጉዋለት ጥያቄ። ኪነጽሁፍ ቢሆን ደራሲው የዚህን ነጥብ ክብደት አይሰተውም ነበር። ፕሮፖጋንዳ ስለሆነ ግን ዘሎታል። የሚፈለገው እሳት መለኮስ ስለሆነ ደራሲው የሚቀጥለን ክብሪት ቃል መረጠ።

-ከምትነዱዋቸው አህዮች አትሻሉም፣ ሲሉም አላገጡብን

-ያው ውሻ ነው እንዲህ የሚግማማው?
ይህን የሚለው ሀምቡርግ የተማረው ሳይኮሎጂስት ነው። የሰነዘረው ስድብ ለአንድ ሰው አይመስልም።

-መቼ ይሆን የምትሰለጥኑት ሲሉም ጠየቁን

ቡርቃ የቡድን ድርሰት የሚመስልበት አንዱ ባህሪው ደግሞ የተራኪው ድምጽ ከምእራፍ ምእራፍ ብቻ ሳይሆን ከመስመር መስመርም በመለያየቱ ነው። እዚህ መስመር ላይ ጥያቂዎቹ ብዙ ናቸው። የሚቀጥለውን መስመር ያስተውሉ።
-እርሶ ታዲያ ምን መለሱለት አባቦሩ?
እዚህ መስመር ላይ ደራሲው የአባቦሩ ጠያቄ አንድ ሰው ብቻ አድርጎታል።

-ማን እየገዛን እንሰልጥን አልኩት?

ደረሲዎቹ ደራርሰው ሞተዋል። አባቦሩ ይጠቅሱአቸው የነበሩት በዳዮቻቸው ብዙ መሆናቸው ተረሳ። ጠያቂያቸው አንድ ሰው ሆነ። አንድ ሰው። አንድ ባለጌ... አዎ ሊስድባቸው፣ ሊያዋርዳቸው፣ በብሄረስብ ማንነታቸው ሊንቃቸው ይችላል። አንድ ድፍን ብሄሬስብ ግን ያን ማድረግ አይችልም። ያደርጋል ከተባለም በዚሁ በልቦለድ አለሙ ታሪክ ውስጥ፣ ከውጭ አይደለም፣ በትረካው ማሳየት አለበት። አለበለዚየ ድርሰቱ ኪናዊ አይባልም። ኪነጽሁፍ አይባልም። አንጋፋው ጋዜተኛና ደራሲ ሙሉጌታ ጉደታ ቡርቃ "አራት መቶ ገጽ አዲስ ዘመን ነው፣" እንዳለው ነው የሚሆነው።

የቡርቃ ደራሲዎች፣ ከላይ ያነበብነውን የጭውውት መቸት ወደሁዋላ ሰባ አመት ቢመልሱት ጭውውቱ ምናልባት ተኣማኒነት ይኖረው ነበር። ይህ ግን ዘመነ ደርግ ወደ 1982 ገደማ ነው። በዚህ ዘመን ኢትዮጵያን አንድ ብሄሬሰብ ነበር የሚገዛት የሚል ከመጣ እሱ ወይ እኔ፣ ብቻ ከሁለት አንዳችን... እዚች ፕላኔት ላይ አልነበርም።


በኔ እምነት ቡርቃው የእንድ ደራሲ ስራ አይደለም። ቡርቃን በተመስጦ ያዳመጠ አንባቢ የተራኪው ድምጽ ከምእራፍ ምእራፍ ሲለዋወጥ ያስተውላል ብዬ እገምታለሁ። በተለይ የመጀመሪያው ክፍል ላይ ያለው ቁዋንቁዋና ሀሳብ እንደ ተስፋዬ በእማርኛ ተናጋሪዎች መሀል ያደገ ሰው ሊጠቀምበትና ሊታስበውም የማይቻለው ሆኖ ነው ያገኘሁት። ምናልባት በሌላ ሰው የተጀመረና ማጣፊያው ሲያጥር ወደ ተስፋዬ የተወረወረ ስራ ይሆናል ብዬም እገምታልሁ። ደራሲ ተስፋዬ በብሄረሰቦች መሃል የሚያስከትለውን ውዝግብና በራሱም ላይ የሚያመጣውን ጣጣ ሳይገነዘብ ችሎታውን ለማስመስከር፣ ትኩርት ለመሳብ፣ ዝናን ለማግኘት ሲል ወይም በድርጅታዊ ስራ ታዝዞ የተፈናጠጠበት የሌላ ሰው ወይም ቡድን ጅምር ስራ ሳይሆን አይቀርም የሚል ግምትም አለኝ።

ይህን የምለው ዝም ብዬ አይደለም። በሚቀጥለው ክፍል የገጽባህሪያትን ቃል ወይም ጭውውት ስዳስስ እንቃኛዋለን።

እስከዚያው
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby password » Tue Apr 14, 2009 11:21 pm

የቡርቃ ዝምታ
በፓስዎርድ መነጽር ሲታይ


ክፍል ሶስት - ሀ

በቀጣዩ ገጽ ቀርቧል........
Last edited by password on Wed Apr 15, 2009 11:46 am, edited 2 times in total.
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby password » Tue Apr 14, 2009 11:24 pm

የቡርቃ ዝምታ
በፓስዎርድ መነጽር ሲታይ


ክፍል ሶስት - ሀ/

ቡርቃ ኪነጽሁፍ አይደልም ስል ዝም ብዬ አይደለም። ከላይ የገጸባህሪ አሳሳሉ ላይ የነበረውን ጉድለት በመጥቀስ ለማሳየት እንደሞከርኩ ሁሉ እዚህ ሶስተኛውና የመጨረሻው ክፍል ውስጥ ደግሞ ቃለ ባህሪያት ላይ የሚነበበውን ኢኪኒያዊ አባባል ለማሳየት እሞክራለሁ። በማያያዝም አማርኛው ላይ የሚታየውን ግድፈት በመጠቆም ድርሰቱ በከፊል የሌላ ሰው ብእር እንዳረፈበት ለማሳየት እሞክራለሁ።

እንጀምር።
በርድ፣ የቡርቃ ዝምታ ገጽ 17 & 18ን ግለጭ።

"ሶስት አስደናቂ ጉዳዮች ባንድ ጊዜ ተፈጽመዋል" ሲል ጀመረ ሚንስትሩ።


(አስደናቂ፣)
ደራሲው ያልሆነ ቃል በማይሆን ቦታ የሞጀረ መሰለኝ። ኢትዮጵያ ውስጥ በወቅቱ በነብረው የሶሽዎ ፖለትካና የሀገር ጸጥታ ሁኔታ ሶስት ጉዳዮች ባንድ ጊዜ የመፈጽማቸውን አጋጣሚ ፕሬዚዳንቱይም ሆኑ ሚንስትሩ ከቁብ የሚቆጥሩት አይሆንም። ወረድ ብለን ስናነብ አስደናቂ የተባሉት ጉዳዮች በኮሎኔል መንግስቱ ቢሮ ውስጥ ድራቸውን ከሰሩ የቆይዩና፣ ለጆሮአቸውም የሰለቹ ናቸው። ደራሲው ምናልባት የአንባቢን ቀልብ ከመጀመሪያው ለመሳብ አስቦ ይሆናል፣ ግን ዘዴው ይህ አይመስለኝም። ርእሰ ጉዳዩ ካዘልው ስሜት በላይ ገጸባህሪን ማስጮህ ወይም ያልሆነ ቃል ማስባል ድርሰትን ያጎምዝዛል እንጂ አያጣፍጥም።

"ምንድንናቸው ፣" ትእግስት ባጣ ድምጽ

"የመጀምሪያው፣" አለ የደህንነት ሚንስትሩ "የወያኔ ቀንደኛ መሪዎች በእጃቸን መዳፍ ወስጥእንደገቡ የሚያስቆጥር ሙሉ እድል ተገኝቶአል።"


በመጀመሪያ አማርኛው የተስፋዬ አማርኛ አይመስልም። ቀጥሎ አስደናቂ የተባለው ጉዳይ ራሱ እድል ነው። እድል እስከሆነ ድረስ ሊያመልጥ ይችላል። ለምሳሌ፣ በረኛን ጨምሮ ሁሉንም ተከላካዮች ያለፈ የእግር ኩዋስ ጨዋታ አጥቂ ከሁለት ሜትር ርቅት ጎል የማግባት እድሉ ሙሉ ነው ማለት ይቻላል፣ ይሁን እንጂ ሊስትም ይችላል። መዳፍ ውስጥ እንደገቡ የሚያስቆጥር ሙሉ እድልም ያው ነው። ሊያመልጥ ይችላል ስለዚህ አስደናቂነቱ አልታየኝም። የደህንነት ሚንስትሩ በረጅም የስራ ዘመኑ ስንት በመዳፉ የገቡ እድሎች እንዳመለጡት መታሰብ አለብት።


ሌለው፣ ሙሉ እድል ተገኝቶአል፣ የሚለው ሀረግ ደራሲው ሊያስተላልፍ የፈለገውን ሃሳብ አደብዝዞታል። ገድሎታልም ማለት ይቻላል። ምናልባት ሙሉ ድል ለማለት ታስቦ እንድሆን ብዬም አውጠንጥኜ ነበር። ሆኖም በዚያም በኩል ቤት አላንኩዋኩዋም።

"የወያኔ ቀንደኛ መሪዎች በእጃቸን መዳፍ ወስጥ እንደገቡ የምንቆጥርበት ሁኔታ ተመቻችቶልናል።" የሚል ሀሳብ መሰንዝር ነበር የተፈለገው። ደራሲው፣ የጋዜጠኛው ማስታወሻን የጻፈው ተስፋዬ ቢሆን ኖሮ አረፍተ ነገሩን ከዚህ በተሻለ ሊያስቀምጠው ይችል ነበር ብዬ አገምታለሁ።

የፕሬዚዳንት መንግስቱ ዓይኖች ላይ የብርሃን ጮራ ታየ።
በዚህ ክፍል የምዳስሰው ቃለ ባህሪያትን ነው ብዬ ነበር። ስለሆነም ከላይ የሰፈረውን አይነት ገለጣ ላይ ሳልተች አልፋለሁ።

"እኮ እንዴት?" በሚል ስሜትም በደህንነት ሚንስትሩ ላይ አፈጠጡ።

"አዎ፣ ቀዩ ጆፌ ተሳክቶለታል፣ ታውቀዋለህ ቀዩ ጆፌንከስድስት ወር በፊት ስራዊታችንን ከድቶ ወያኔን እንዲቀላቀል ያደረግነው መስመራዊ መኮንን..."

ጀማሪ ደራሲያን ደጋግመው የሚስቱት አንድ ነጥብ አለ። ይኽውም ገጸባህሪያት ታሪካቸውን የሚያነብ ሰው ስለመኖሩ ምንም ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑን መዘንጋታቸው ነው። ገጸባህሪያት ሲነጋገሩ ልክ በውኑ አለም እንዳለንው ሰዎች ነው ሃሰብ የሚለዋወጡት እንጂ አንባቢ መኖሩን አውቀው፣ ያ አንባቢ በደንብ እንዲገባው ነገሮችን አፍረጥርጠው አይነጋገሩባቸውም። ስለሆነም አንዱ ገጸባህሪ ሊያውቀው የሚችለውን ነገር ይዘሉታል እንጂ አይናገሩትም። ከስድስት ወር በፊት ወያኔን እንዲቀላቀል ስለተደረገው መስመራዊ መኮንን ፕሬዝዳንቱ በሚገባ ስለሚያውቁ ያን ትንትን አድርጎ መናገር አስፈላጊ አይደለም።

ግን ፕሬዝዳንቱ ከስድስት ወር በፊት ስለተላከው ሰላይ ዘንግተው ከሆነስ? እንግዲያው የጭውውቱ ሂደቱ እንደሚከተለው ቢሆን ይሻል ይመስለኛል።

"አዎ፣ ቀዩ ጆፌ ተሳክቶለታል፣

'ማን ነበር እሱ?'

'ዘነጋኸው? ያ ወያኔን እንዲቀላቀል ያደረግነው መኮንን ነዋ."

በርድ ልብ በይ፣ መስመራዊ የሚለው ቃል ራሱ ወጥቶአል፣ እሱም እዚህ ውስጥ አይመችም።

"መቼ ነበር?"

"ስድስት ወር ገድማ ሆነው"


ከስድስት ወር በፊት ስራዊታችንን ከድቶ ወያኔን እንዲቀላቀል ያደረግነው መስመራዊ መኮንን..." ይህን አረፍተ ነገር የያዘውን ሃሳብ አንባቢው እንዲያውቀው ተፈልጎ ከሆነ ተራኪው ራሱ በጭውውት መሀል በሚገቡ ማብራሪያዎች መግለጽ ነበረበት እንጂ ገ/ባህሪውን ማስባል የለብትም።

አስረጅ
"አዎ፣ ቀዩ ጆፌ ተሳክቶለታል፣"
ከስድስት ወር በፊት፣ ስራዊቱን የከዳ በማስመሰል ወያኔን እንዲቀላቀል የተደረገ እንድ መስመራዊ መኮንን ነበር። ፕሬዝዳንቱ ግን የዘነጉት ይመስላሉ።

[color=red]"ነግረኽኛል" አሉ ፕሬዚዳንቱ ለማስታወስ እየጣሩ


ተራኪው የፕሬዚዳንቱ ጭንቅላት ውስጥ ዘው ብሎ ገብቶአል። ፕሬዝዳንቱ ለማስታወስ እየጣሩ መሆናቸውን ከፊታቸው ላይ በማንበብ ሳይሆን ውስጣቸው በመግባት ነው የነገረን። እንዲህ አይነት ተራኪ አዋቂ ኩሉ ይባላል። የማይገባበት ቦታ፣ የማያውቀው ነገር የለም። ከቦታ ቦታ፣ ከሰው ሰው እየዘለለ መተረክ ይችላል። ለዚህ አይነት ተራኪ ምንም ድብቅ ነገር የለም። ደራሲው እንዲህ አይነት ተራኪ መምረጡን ዘንግቶ ሌላ ቦታ ላይ...
'ፕሬዝዳንቱ በዚህ አመት ይህን መሰል አስደሳች ሪፖርት ሲሰሙ ይህ የመጀመሪያ ሳይሆን አይቀርም፣' ቢል ወይም
'አኖሌ ምን ትዝ እንዳለው... ብቻ አይኖቹ በአንዴ በእንባ ተሞሉ። ቢል አንባቢን ግር ይለዋል፣ ምክንያቱም ተራኪው ሁሉንም ነገርና ሀሳብ፣ ከገጸባህሪያት ውጭና ውስጥ እያመጣ ሲተርክ ነበርና። አንባቢው ሳያውቅ ተራኪን ከአዋኪ ኩሉነት ወደ ውሱን ተራኪ ዝም ብሎ መቀየር ኪነጽሁፋዊ ስርዐት ማፋለስ ነው።

ክፍል ሶስት - ለ/ ይቀጥላል
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby password » Wed Apr 15, 2009 9:18 am

:arrow: 3 -ለ-
ይቀጥላል..............
Last edited by password on Wed Apr 15, 2009 11:49 pm, edited 1 time in total.
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby password » Wed Apr 15, 2009 9:21 am

ክፍል 3 (ለ)


"መልእክት ለመላክ ችሎአል፣ እጅግ አንገብጋቢ መልእክት. ...."

እጅግ አንገብጋቢ መልእክት? ይህም ተስፋዬ ተስፋዬ አይልም።
አንገብጋቢ ጥያቄ፣ እንገብጋቢ ጉዳይ ይባላል፣ መዋል ማደር የሌለበት አስቸኩዋይ ምላሽ የሚሻ ጉዳይ ሲያጋጥም። ጆፌው የላከው የወያኔ መሪዎችን በመዳፍ እንደገቡ የሚያስቆጠርው እድል ግን አስቸኩዋይ ሳይሆን በጣም ጠቃሚ ነው። አደረ ዋለ እርምጃ የሚወሰደው ወያኔዎቹ በሚሰበሰቡበት እለት ነው። ያ ቀን ደሞ ገና መሆኑ በቀጣዩቹ መስመሮች እናንባልን። ስለዚህ አንገብጋቢነቱ ምን ላይ ነው?

"ጆፌው የስብሰባውን ቦታና ቀን፣ ሰዓት ጭምር የሚገልጽ መረጃና፣ ጨርሶ የማያምታታ ካርታ ልኮልናል። .... የሚያስደንቀው ጉዳይ ቀዩ ጆፌ የአየር ሃይላችንን ሚስጥሮች እንደሚያውቅ ሆኖ በመቅረቡ መረጃዎችን በጽሁፍ እንዲያቀርብ ወደ ዋሻቸው አስጠግተውታል። እጅግ ወሳኝ ወታደራዊ መረጃ ነው ያገኘው።"


ወሳኝ መረጃ የሚባለው አንድ ወታደራዊ ተልእኮ በአሽናፊነት እንዲጠናቀቅ መረጃው የሚያስፈልግ ሲሆን እንጂ እንዲሁ ጠቀሜታ ብቻ ያለው ከሆነ ወሳኝ የሚለው ቃል ቦታው አይደለም።
ጆፌውን ወደ ዋሻቸው ማስጠጋታቸው የሚያስደንቅ እንድሆነ ተመልክቶአል... የሚያስደንቀው የተባለው የሚያስደንቅ ነገር ኖሮ ሳይሆን ደራሲው የአባቢን ቀልብ ለመያዝ ሲል ብቻ የወተፈው ቃል ነው። በአጠቃላይ ጆፌው ወደ ዋሻቸው መጠጋቱን አንባቢ እንዲያውቅ ስለተፈለገ የገባ ድረታ ስለሆነ ቃለ ባህሪው አያሰማም። ጆፌው ዋሻቻውን መጠጋቱ እንዲታወቅ የተፈለገው፣ ሁዋላ አየር ድብደባ ሲደረግ ኢላማ እንዲመቱ ካምድር ምልክት በመስጠት እንድያግዝ ታስቦ ይሆናል ግን ያን ለመተረክ ገጸባህሪን እንዲህ በማናለብኝነት ማስለፍለፍ ኪነጽሁፋዊ ግፍ ነው።


"ለመሆኑ በስብሰባው የሚካፈሉት እነማን ናቸው?"

ሚንስትሩ የማስታወሻ ደብተሩን ገላልጦ ማንበብ ጀምረ።

"መለስ ዜናዊ ...ስ አ ፣ መ ስ፣...ገ አ ... እናለዘመናት እንደ አሳ እየተሙለጨለጨ ሲያመልጠን የኖረው የወያኔ ቁልፍ ሰው / ሃየሎም አርዓያ። እነዚህ ናቸው ፊትአውራሪዎቹ። እነዚህ ተወገዱ ማለት ወያኔ አከተመለት ማለት ነው። በጣም ቁልፍ ሰዎች ናቸው። በጣም ... በጣም ባለን አቅም ሁሉ መስዋእትነት ከፍለን እነዚህን መርዘኞች ካጠፋን ሁሉም ነገር ይዘጋል። ሁሉም ነገር ይዳፈናል። የኢትዮጵያ ህዝብም የእፎይታ ባለቤት ይሆናል። ይከው ነው።"


ይህ የተስፋዬ አማርኛ ነው ብዬ ለመቀበል ያስቸግረኛል። ደርሰቱ ቢያንስ በተስፈዬ አልተጀመረም የምለውም እንዲህ አይነት አማርኛ ስላነበብኩ ነው። በጦርነት ውስጥ አደጋ ሳይደርበት የሚያመልጥ ሰው "እንደ አሳ እየተሙለጨለጨ" ይባላል እንዴ፣ በርድ። ብሂሉ የሚከስተው ምስል ጽናተ ቢስነትን፣ ወላዋይነትን እንጂ ከአደጋ፣ ከጥይት፣ ከእሳት የሚወጣን ወይም የሚያመልጥን አይደለም። ተስፈዬ ይህን ይስተዋል ብዬ መቀበል በውነት ያዳግተኛል።

በተረፈ ቃለባህሪው ራሱ ከመጠን በላይ ተደርቶአል። ሀቅነት አይነብብበትም። ለረጅም ጊዜ የአገሪቱን የደህንንት መስሪያ ቤት የመራ ሰው ገና ውጤቱ ያልታወቀ መረጃን መሰረት አድርጎ እንዲህ አይነት ማጠቃላያ ሃሳባት ይሰነዝራል ማለት ተአማኒነት የለውም። ሚንስትሩ እንዲያ አይነት ሰው ከሆነም ተራኪው ከጭውውቱ ወጣ ብሎ የደህንነት ሚንስትሩ በዚህ ችኩል ባህሪው የታወቀ መሆኑን መግለጽ ይኖርበታል። አለበለዚያ አንባቢ የደህንነት ሚንስትሩ ነው ብሎ የሚወስደው በወቅቱ የድህንነት ሚንስትር የነበረውን ኮሎኔለ ተስፋዬ ወልድሥላሴን ስለሚሆን ግንዛቤው ይዛባል።

"የቀዩ ጆፌ መረጃ ምን ያህል ይታመናል?"


መረጃ አቅራቢው ሰላይ ቀዩ ጆፌ እንደሆነ ታውቆአል፣ አስሬ ቀዩ ጆፌ ቀዩ ጆፌ ማለት ምን ያስፈልጋል!

".መረጃው ምን ያህል አስተማማኝ ነው?"
ማለት ይበቃል።

"ይታመናል! መቶ በመቶ ይታመናል። ልጁ ጭራቅ ነው! አውሬ ነው!

እንዴት አይነት ጉድ ነው? የታማኝነት ጥያቄ ሲንሳ፣ "ጭራቅ"ና "አውሬ" በማለት ነው እንዴ፣ ታማኝነትን የምንመሰክረው? አረ በርድ፣ እነዚህን ሰዎች አንድ በይልኝ። ለመሆኑ አለሽ ወይስ በረሻል?

.....ዞሮ ዞሮ ዛሬውኑ የህዝብ ልጅ የሆኑ ታማኝ ፓይለቶች እንዲመደቡልኝ እፈልጋለሁ። ስልጠናው ላይ ራሴ መገኘት እሻለሁ። የስብሰባውን ዋሻ ለይተው ዶጋመድ የሚያደርጉ ቆራጥ አብራሪዎች ያስፈልጉናል።"


እዚህም ላይ ተስፋዬ አለበት ማለት ያስቸግረኛል። ተስፋዬ "ስልጠና"ና "ልምምድ" ለየቅል መሆናቸውን አሳምሮ ያውቃል ባይ ነኝ።
.የህዝብ ልጅ የሆኑ ታማኝ ፓይለቶች ክራይቴሪያው አልበዛም። ለመሆኑ የህዝብ ልጅ የሆነው ካልሆነው በምንድን ነው የሚለይለት? በኔ እምነት ሚንስትሩ ግፋ ቢል ጎበዝ አብራሪ እንዲመደብለት ይተይቅ እንደሆ እንጂ እንዲህ የጉዋነ የሞኝ ጭያቄ ..... እ እ።
"ዶጋመድ" ይሄ የደብተራ ቃል ነው፣ የወታደር አይደለም። መንግስቱ ቢሮ ዶጋመድ የሚል ቃል ተስምቶ የሚታወቅ አይመስለኝም።

ጭውውት ወይም የቃለ ባህሪ ድምጽ እውነት የሚመስለው ገጸባህሪያቱ እውን ሲመስሉ ነው። በድንብ ያልተቀረጹና ያላደጉ ገጽባህሪያት የሚናገሩት ቃላት እንጨት እንጨት ይላል። የሁሉም ድምጽ አይለያይም፣ ምክንያቱም ሁሉንም ሆኖ የሚናገረው ደራሲው ሰለሆነ።

"መልካም ቀጥለበት."
ቀጥልበት? ያን "አንገብጋቢ፣" "ወሳኝ" "መዳፍ የገባ ሙሉ እድል" ሲባል የነበረውን ጉደይ ፕረዝዳንቱ ትንሽ መመሪያ እንኩዋን ሳያክሉበት ነው በእንድ ቁንጽል ትእዘዝ የሚተውት? ለነገሩ ጉዳዩ በደራሲው ተጋነነ እንጂ ለነመንግሰቱ የእለት ተለት ህይወት ስለሆነ ከዚህ በላይ የሚያተኩሩበት አይደለም። መንግስቱም ጋ መቅረብ ያለበት መረጃ አልነበረም።

ፕሬዚዳንቱ ሌላ ሲጋራ ለኮሱ።

"ሁለተኛው ጉዳይ" አለ የድህንነት ሚንስትሩ

"ዛሬ ማለዳ የሻእቢያ ቁልፍ ሰው እጃቸን ገብቶአል። በማይታመን ትንሽ ፍንጭ፣ ጨርሶ ተስፋ በሌለው ግምታዊ ሁኔታ፣ አብርሃ ጸሎት የተባለ የአስመራ ከተማ የሻእቢያ የስለላ ሀላፊ በቁጥጥራቸን ስር ውሎአል። እስካሁን አንድም መረጃ አልሰጠም። ቢሆንም የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግ ልናናዝዘው እንችላለን። በተለይ በቅርቡ ለምናደርገው የሳይኮሎጂካል ዎር ፌር ጥናት ሊጠቅመን ይችላል የሚል እምነት አለኝ።"


ኪናዊነት ያልተላበሰ፣ እውነት የማይመስል ጭውውት።
እንዴት?
ከአስራ አምስት አመት በላይ በስልጣን ላይ የነበሩ አንድ ፕሬዚደንትና አንድ ሚንስትር መረጃውን ሳይሆን መረጃው እንዴት እንደተገኘ የሚወያዩበት ጊዜ አላቸው? ያውም ሶስት ወሳኝ፣ አንገብጋቢ፣ ሙሉ እድል ምናምን የተባሉ ጉዳዮች በተገኙበት በዚህ ቀን?

ቀይ የተቀቡት ሀሳባት ከላይ እንዳብራራሁት፣ ደራሲው በገጽባህሪያት በኩል መተረክ ስለፈለገ ይተዘፈቀባቸው ስህተቶች ናቸው።

ፕሬዚዳንት መንግስቱ ራሳቸውን ላይ ታች ሲወዘውዙ ቆይተው፣
"ወደ ሶስተኛው ጉዳይ ዝለቅ" ሲሉ አዘዙት።

ይህም ከአማርኛ ይልቅ ትግርኛ ትግርኛ ይላል። የተስፋዬ ቁዋንቁዋ አይመስልም።

"ሶስተኛው መጥፎ ወሬ ነው። አንድ ሺህ ኦሮሞ ገበሬዎች ቡርቃ በተባለች መንደር ላይ አምጸዋል። አስቸኩዋይ መፍትሄ የሚያሰፈልገው ጉዳይ ነው።"


አረፍተ ነገሩ በተስፋዬ አማርኛ ሲስተካከል

"ሶስተኛው ደስ የሚል አይደለም። ቁጥራቸው በዛ ያለ ገበሬዎች ቡርቃ በተባለች መንደር ውስጥ አምጸዋል። እና አስቸኩዋይ መፍትሄ"

"የት ነው ቡርቃ ደግሞ?" ሲሉ ጠየቁ ፕሬዚዳንቱ.

አመጹ ስሜት አልሰጣቸውም፣ ቦታው እንጂ ...አይገርምም?

እውነት ቡርቃ የት ነው፣ በርድ?

///////////////
በርድዬ አበባዬ፣ እዚህ እኛጋ ስንብተሽ ነበራ የጠፋሽው። እኔ ዲየሞ አፌ አያርፍም ማይዶል አስቀይሜአት ይሆን ብዬ መጨነቄ።
ታዲያ ፋሲካ እንዴት ነው፣ እናንተጋ። ለመሆኑ ትጦሚያለሽ ወይስ ዝም ብለሽ ያገኘሽውን ነው?
/////////////////
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

Postby አዋሽ98 » Fri Apr 17, 2009 3:13 pm

password wrote:ክፍል 3 (ለ)ይህ የተስፋዬ አማርኛ ነው ብዬ ለመቀበል ያስቸግረኛል። ደርሰቱ ቢያንስ በተስፈዬ አልተጀመረም የምለውም እንዲህ አይነት አማርኛ ስላነበብኩ ነው። በጦርነት ውስጥ አደጋ ሳይደርበት የሚያመልጥ ሰው "እንደ አሳ እየተሙለጨለጨ" ይባላል እንዴ፣ በርድ። ብሂሉ የሚከስተው ምስል ጽናተ ቢስነትን፣ ወላዋይነትን እንጂ ከአደጋ፣ ከጥይት፣ ከእሳት የሚወጣን ወይም የሚያመልጥን አይደለም። ተስፈዬ ይህን ይስተዋል ብዬ መቀበል በውነት ያዳግተኛል።

ፓስወርድ
በቅድሚያ በኢትዮጵያውያን በተዘጋጁ ስነ-ጽሑፎች አና ፊልሞች ላይ የምታቀርባቸውን ሙያዊ እና በሳል ሂሶች በቅርብ ከሚከታተሉት አንዱ ነኝ:: ብዙዎቻችን ካንተ የማይናቅ ትምህርት እንዳገኘን አምናለሁ::
ከዛ በመቀጠል ግን የተስፋዬ ገ.አብን ስራዎች በተመለከተ በሰጠሀቸው አስተያየቶች ግን I have some reservations. በተለይም የቡርቃ ዝምታ በተስፋዬ እንዳልተጻፈ ለማሳመን እየሞከርክ ነው:: እንደምገምተው የቡርቃ ዝምታን ከማንበብህ በፊት የጋዜጠኛው ማስታወሻን ስላነበብክ የአጻጻፍ ዘይቤውን በጣም ስለወደድከው ይመስለኛል:: የብርሀኑ ዘርይሁንን ቀደምት ስራዎች ብታነብ እውን እሱ ነው እንዲህ ደርቶ ደርቶ የጻፈው ብለህ ትገረማለህ:: በኔ ግምት ተስፋዬን ምልኡ በኩልሄ ያደረግከው ይመስለኛል:: ተስፋዬ ያንን መጽሀፍ በመጻፉ ምን ያህል እንደሚኮራና ለስደት ካበቁትም ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ በጋዜጠኛው ማስታወሻ ላይ በግልጽ አስቀምጦታል ገጽ 225
ክንፈ ሰበብ ፈጥሮ እኔን ከሀገር እንዲያባርር መታዘዙን ጠረጠርኩ:: የቡርቃ ዝምታም አልተመቻቸውም::
አንተ ደሞ ሽንጥህን ገተረህ የምትከራከረው ይሄ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ በሌሎች ሰዎች ተስፋዬ ላይ እንደተጫነ እንጂ የተስፋዬ አማርኛ እንዳልሆነ ነው:: ይህ የተስፋዬን ማንነት በደንብ ካለመረዳት ወይም you are overwhelmengily charmed by his recent book.
አንተ ስታስበው እንዲህ አይነት ተራ ፕሮፓጋንዳ መጻፍ ባይችል ኖሮ, ከትምህርት ትምህርት ሳይኖረው, ከልምድ የታጋይነት ልምድ ሳይኖረው (ወያኔን የተቀላቀለው በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ እንደሆነ ተናግሩዋል) ባንዴ የኢትዮ ፕሬስ ዋና ስ/አስኪያጅ ሊሆን እንዴት ይችላል ብለህ ታስባለህ? so, I'm afraid you are misleading your readers when it comes to who was behind this 'crap'. It was written by Tesfaye and only by Tesfaye with his consent to fullfill Afeworki's 100years homework for Ethiopia.
መልካም ቀን
አዋሽ98
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 172
Joined: Mon Sep 26, 2005 3:22 pm
Location: Lay Sefer

Postby password » Sun Apr 19, 2009 5:12 pm

ሰላም አዋሽ

የሰንዘርከውን ሀሳብ በጥሞና አንብቤዋለሁ። ከጽሁፍ ውስጥ ምላሽ ልሰጥባቸው የፈለግሁዋቸውን አውጥቼ በጥቅስ ውስጥ ቀንፌአቸዋለሁ።

እነሆ

በተለይም የቡርቃ ዝምታ በተስፋዬ እንዳልተጻፈ ለማሳመን እየሞከርክ ነው ::


ለማሳመን ሳይሆን ለጥርጣሬዬ መሰረት የሆኑትን ነጥቦች ለማሳየት፣ አዎ ሞክሬአልሁ። አንባቢ የቀረቡትን መረጃዎች አይቶ የራሱን ግምት ይሰጣል ብዬ አምናልሁ። የማሳመን አልማሳመን ጉዳይ ሳይሆን እንደ አንድ የመወያያ ርእስ መነሳት የሚችል ይመስለኛል።


እንደምገምተው የቡርቃ ዝምታን ከማንበብህ በፊት የጋዜጠኛው ማስታወሻን ስላነበብክ የአጻጻፍ ዘይቤውን በጣም ስለወደድከው ይመስለኛል ::


የሰጠሁት አስተያይት በመውደድና በመጥላት ላይ እንዳልተመሰረተ ቁልጭ ብሎ የሚታይ ይመስለኛል። ከመጽሀፉ የጠቀስኩዋቸው አረፍተ ነገሮች ውስጥ ሰዋስዋዊ ቅርጻቸው፣ የቃላት አጥቃቀምና ማንም አማርኛ ተናጋሪ የማይስታቸውን ብሂሎች ተዛብተው ይገኛሉ። ከዚህ በመነሳት ነው፣ ድርሰቱ የሌላ ሰው ብእር ነክቶታል የምለው፣ እንጂ የጋዜጠኛው ማስታወሻን ስለወደድኩልት ብቻ አይደለም።

የብርሀኑ ዘርይሁንን ቀደምት ስራዎች ብታነብ እውን እሱ ነው እንዲህ ደርቶ ደርቶ የጻፈው ብለህ ትገረማለህ ::


ሁለቱን መድብሎች አንብቤአቸዋለሁ።


በኔ ግምት ተስፋዬን ምልኡ በኩልሄ ያደረግከው ይመስለኛል ::
v

ግምትህ የተሳሳተ ነው። የጋዜጠኛው ማስታዋሻ እንደ ቡርቃ በፓስወርድ መነጽር ስር ቢውል ብዙ እንከን ይገኝበት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ። የማስታወሻ ጽሁፍ ውስጥ ንግግሮች፣ በመቀርጸ ድምጽ ካልተቀዱ በቀር፣ እንዲህ ቃል በቃል የመጻፋቸው ጉዳይ የሚያሰነሳው ጥያቄ አለ ብዬ ከሚያምኑት ወገን ነኝ።


ተስፋዬ ያንን መጽሀፍ በመጻፉ ምን ያህል እንደሚኮራና ለስደት ካበቁትም ጉዳዮች አንዱ እንደሆነ በጋዜጠኛው ማስታወሻ ላይ በግልጽ አስቀምጦታል ገጽ 225


ተስፋዬ በቡርቃ ስራ ላይ የፈጽመውን ስህተት አሁንም የተረዳው አይመስልም፣ ስለዚህ መኩራራቱን ሊቀጥል ይችላል። ራስህን ማየት በጣም ከባድ ነው። ፊትህን የምታይበት አንድ ጥሩ መስታወትና መስታወት የሚይዝልህ ደህና ወዳጅ ያስፈልግሀል። በዚህ መጽሀፍ ማን ምን እንደሚጠቀም ሊያስረዳ የሚችል አይመስለኝም። የባድሜው ግጭት የተፈጠረ ሰሞን ወያኔ ብአጠቃላይ የኢትዮፕያን በተለይ ደግሞ የትግራይን ህዝብ ለማነሳሳት የተጠቀመበት የቅስቀሳ ስልት ሁላችንንም ያስደመመ ነበር። የአቶ ገብሩን ንግግር ያስታውሱዋል። "ኤርትራዊያን ለአንድ ሺ ዝንብ አንድ ፍሊት ይበቃዋል።" በሚሊዮን የሚቆጠር ኤርትራዊያንና በትውልደ ኤርትራዊ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚደርስባቸው የበቀል እርምጃ ግድ ያልነበርው ስድ ንግግር ነበር።
ይህን ሲስማ ተስፋዬ ምን ተሰምቶት ይሆን? በዚያን ስሞን በመንግስት መገናኛ ሚዲያ ይተላለፍ የነበርው ለጆሮ የሚቀፍ ነበር።
ኤርትረዊያን የአማራ፣ የኦሮሞ ለተለይም የትግረይ ህዝብ ላይ ያላቸውን ንቀት ሀላፊነት በጎደለው መልኩ ይዘከዘክ ነበር። አላመው በወቅቱ የህዝብን የጥላቻና የበቀል ስሜት ለመቀስቀስ ነበር። ያንን ተስፋዬ እንዴት ያየው ይሆን? የሱስ ቡርቃ ከዚያ በምን ይለያል? ቡርቃ ሰዎችን ለበቀል የሚያነሳሳ ይዘት የለውም? አንዳንዴ እንኩዋን ህዝባችን ፊደል አልቆጠረ ያሰኛል። ፊደል ቆጥሮ የትኛውን የረባ ነገር ሊያነብ!

ክንፈ ሰበብ ፈጥሮ እኔን ከሀገር እንዲያባርር መታዘዙን ጠረጠርኩ :: የቡርቃ ዝምታም አልተመቻቸውም ::


አቶም ቦንብን የፈጠሩ ሳይንቲስቶች ቦንቡ የሚያስከትለውን ጥፋት ካስተዋሉ በሁዋላ መልሰው ሊያጠፉት መጣራቸውን ታውቃለህ ብዬ እገምታለሁ። አነ ክንፈ የብሄርስቦችን መቃቃር የሚፈልጉት በተወሰነ መጠን ይመስለኛል። ለአገዛዛቸው በሚመች መጠ። አንሱ በሚገዝዋት ኢትዮጵያ ሁዋላ ሊያቆሙት የማይቻላቸው የጎሳ ጦርነት እንዲቀጣጠል አይፈልጉም። የሚፈልጉት በልክ ነው። የተስፋዬ "ዶስ" የበዛባቸው ይመስለኛል እና አልወደዱትም።

አንተ ደሞ ሽንጥህን ገትረህ የምትከራከረው ይሄ ርካሽ ፕሮፓጋንዳ በሌሎች ሰዎች ተስፋዬ ላይ እንደተጫነ እንጂ የተስፋዬ አማርኛ እንዳልሆነ ነው ::


በእንድ አማርኛ ተናጋሪ ሊባል የማይችል ሀረግ ሳነብ ምን ልበል? እስኪ ይሄን እይ።
ጂብሪል፣ ምንም እንኩዋ የስራተኛው ፓርቲ አባል ቢሆንም ብዙውን ጊዜ የታዘዘውን እንደ ጥሩንባ ከማስተጋባት የተቆጠበ ....


እግዜር ያሳይህ አንተስ ብትሆን እንዲህ አይንት አረፍተ ነገር ስታነብ አማርኛ ተናጋሪ አልጻፈውም ብለህ አትጠራጠርም። አንድ ቦታ አንቱ ያለውን ገጸባህሪ ሌላ ቦታ አንተ የሚለው ከሆነ ምናልባት ደራሲያኑ ከሁለት በላይ ይሆናሉ አትልም? ለምሳሌ፣ አንቱ ሲባል የነበረውን ፕ/ መንግስቱ ገጽ 252 ላይ አንተ ብሎታል።

ይህ የተስፋዬን ማንነት በደንብ ካለመረዳት ወይም you are overwhelmingly charmed by his recent book.


ከማንነቱ ጉዳይ የለኝም። And I have enormous respect for his resent book both as a literary work and source of vital information.

አንተ ስታስበው እንዲህ አይነት ተራ ፕሮፓጋንዳ መጻፍ ባይችል ኖሮ , ከትምህርት ትምህርት ሳይኖረው , ከልምድ የታጋይነት ልምድ ሳይኖረው (ወያኔን የተቀላቀለው በሰማኒያዎቹ መጀመሪያ እንደሆነ ተናግሩዋል ) ባንዴ የኢትዮ ፕሬስ ዋና ስ /አስኪያጅ ሊሆን እንዴት ይችላል ብለህ ታስባለህ ?


የኢህአዴግ ሹመት አስጣጥ መስፈርት ቅድሚያ የሚሰጠው ታማኝነትን እንደሆነ አባላቱ አይደብቁም። የፕሬስ መምሪያን ለመቆጣጠር ተራ ፕሮፓጋንዳ መጻፍ የሚችል ሰው ሳይሆን አንድ እሺ ባይ ነው የሚያስፈልግህ። አቶ ታምራት ተስፋዬን ሲሾሙት እሺ ባይነቱን እንጂ ለትምህርቱ ግድ አልነበራቸውም። እሳቸውም ቢሆኑ እንኩዋን አገር አንድ አውራጃ ለማስተዳደር የሚያበቃ ትምህርት የነበራቸው አይመስለኝም።


so, I'm afraid you are misleading your readers when it comes to who was behind this 'crap'.


I was simply entertaining my right to share my opinion with warka mates. Readers are entitled to freely form theirs opinion as well. "Misleading" is not the right word here.

It was written by Tesfaye and only by Tesfaye with his consent to fulfill Afeworki's 100-years homework for Ethiopia.


This is a serious allegation. If you really meant you words, you will be required to come up with a convincing evidence. I 'm sure your allegation is not based on the simple fact that Tesfaye is born to Eritrean parents.


ብርሀነ ትንሳኤው ለሁላችንም ።
password
ኮትኳች
ኮትኳች
 
Posts: 324
Joined: Fri Apr 04, 2008 2:02 am
Location: Europe

PreviousNext

Return to Warka Culture and Literature - ዋርካ ባህልና ሥነ ጽሑፍ

Who is online

Users browsing this forum: No registered users and 3 guests